ለጎጆዬ @legojoye_minbertv Channel on Telegram

ለጎጆዬ

@legojoye_minbertv


በትዳር እና በልጅ አስተዳደግ ዙሪያ የሚያጠነጥነውና በሚንበር ቲቪ ተዘጋጅቶ ስለ ሚቀርበው ለጎጆዬ ዝግጅት መረጃ እዚህ ያገኛሉ።

ለጎጆዬ (Amharic)

ለጎጆዬ የቴሌግራም ቻናል ነው ። ይህ ትዳር እና ልጅ አስተዳደግ ዙሪያ ነው። ይህበን የሚያጠነጥንበት በሚንበር ቲቪ ተዘጋጅቶ ስለ ሚቀርበው ለጎጆዬ ዝግጅት መረጃ እዚህ ያገኛሉ። በዚህ ታሪኩ የጎጆዬ ቻናል እና በሉ መንበረሽ መረጃዎችን ስለ ሚቀረበው ስፍራ ይመልከቱ። የቴሌግራም ቻናል የተነሳ በለጎጆዬ ይመልከቱ።

ለጎጆዬ

14 Nov, 11:58


የእራት ሰዓት ደርሷልና ሱፍራው ቀርቧል! በተለምዶ ብዙ ቤት እንደሚደረገው አባወራው መጥቶ ሰብሰብ ብለው መመገብ እንዲጀምሩ እየተጠበቀ ነው።
እርሱ ግን ካለበት ንቅንቅ አላለም። በዚህ መሃል ባለቤቱ በተደጋጋሚ ወደ ገበታው እንዲቀርብ ተጣርታ ምላሽ ታጣለች!! ሁኔታውን መቋቋም ሲያቅታት ድንገት ወዳለበት ጠጋ ብላ የያዘውን መፅሃፍ/ ሞባይል ነጥቃ ትወረውረውና ትታው ትሄዳለች!!
ጥያቄው አንተ በዚህ አባወራ ቦታ ብትሆን ምላሽህ ምን ሊሆን ይችላል? የሚል ሲሆን ለእህቶች ደግሞ በርሷ ቦታ ላይ ብትሆኑ ልትወስዱት የምትችሉት እርምጃ ምን ሊሆን ይችል ነበር? የሚል ነው።
ይህን ጥያቄ ለጎጆዬ ፕሮግራምን ለመከታተል ስቱዲዮ ለተገኙ ታዳሚዎቻችን አቅርበነው የሰጡንን አስገራሚ ምላሽና የትዳር ህይወት ቁልፍ ሚስጥር እንደሆነ ስለሚታመነው ተግባቦት የተዋያየንበት ለጎጆዬ ቤተሰብ ተኮር ፕሮግራማችን "ውጤታማ ተግባቦት በትዳር ውስጥ ስላለው ቁልፍ ሚና" እያነሳሳንበት እንቆያለን።
የትዳርን ቅዱስ ምዕራፍነት፣ ኢስላማዊ የቤተሰብ አመራር ጥበብንና ጤናማ የልጆች አስተዳደግን ከመሠረቱ እየተመለከትንበት በምንገኘው ለጎጆዬ የቤተሰብ ፕሮግራማችን ላይ በአካል ተገኝታችሁ ልምድና ተሞክሯችሁን እንደዚሁም ንባብና ምልከታዎቻችሁን በማካፈል መሳተፍ ለምትፈልጉ ታዳሚያን ዘወትር በሥራ ሰዓት ብቻ በ0947700070 አጭር መልዕክት ልታኖሩልን ትችላላችሁ!
እንደዚሁም የጎጆዬን የቴሌግራም ቻናል ዛሬውኑ ጆይን በማለት በየወቅቱ የሚነሱ ሃሳቦችን በተሟላ መልኩ በፅሁፍ ማግኘት እንደምትችሉ እናስታውሳለን።

ዕለተ ማክሰኞ ህዳር 4 | 2016

★★★★★

ሚንበር ቲቪን በኢትዮሳት በተሻለ የምስል
ጥራት ለመከታተል👇
ፍሪኩዌንሲ:- 11545
ፖላራይዜሽን:- ሆሪዞንታል
ሲምቦል ሬት:– 45000

★★★★★

#ሚንበር_ቲቪ
#ሁለንተናዊ_ከፍታ!

ለጎጆዬ

03 Nov, 18:30


በአላህ ስም እጅግ አዛኝ ሩህሩህ በሆነው
ተጣማሪን መምረጫ መስፈርቶች
ክፍል (6)
6ኛ፤ ውበት
☪️እስልምና ውበትን እንደ አንድ ለጋብቻ ቀስቃሽ አጋጣሚ ያደርገዋል፡፡ 🔸መልክተኛው (ሰዐወ) ቡካሪና ሙስሊም በዘገቡት ሀዲሳቸው እንዲህ ማለታቸው ተወርቷል፡፡
🧕🏼አንዲት ሴት ለአራት ምክንያት ትገባለች፡ ለገንዘቧ፤ ለቤተሰቧ ክብር፤ ለቁንጅናዋና ለዲኗ፤እጅህ አፈር ይዘገንና ዲን ያላትን ምረጥ)፡፡
🔸ውበት ወይም ቁንጅና አንጻራዊ ነገር እንጂ ቋሚ መለኪያ የለውም፡፡ አንድ ሰው ከሚስቱ ላይ የሚያየውን ውበት ሌላን ሰው በፍጹም አይዋጥለት ይሆናል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰው የራሱን የውበት መስፈሪያ እንዲጠቀም ቢፈቀድለት መልካም ነው፡፡ መልክተኛውም ከላይ ያነሱት ሲያያት የምታምረው ነው ያሉት፡
•እይታው የሚፈጥረው ስሜት ለግለሰቡ ነው የተተወው፡፡
🫵🏼እዚህም ጋር ማስታወሻ ለእናቶችና እህቶች ባስቀምጥ ደስ ይለኛል፡፡ እሱም ለልጃችሁ ቆንጆ ሚስት መረጥንልህ አግባት ስትሉ ካልታየው ባትጫኑና ባታስገድዱ መልካም ነው፡፡ የሚያገባት እሱ ነውና ውበቷን ካደነቀና ስሜት ከሰጠው መልካም፡ ካልሆነ ግን እሱ ስለሆነ የሚያገባት በእናንተ መስፈርት ቆንጆም ብትሆን ገፋፍቶ ማስገባቱን ብትተውት ትመከራላችሁ፡፡
👱🏼‍♂️ወጣት ወንዶችም ውበት ላይ ከፍተኛውን ትኩረት ስታደርጉ የሚከተሉትን ሀሳቦች ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል፡
🫵🏼አንደኛ፡ ውበቷ ለአንተና ለቤቷ መሆኑን ብታረጋግጥ ፡ የሴት ልጅ ውበት ለአደባባይ፡ ለጎዳናና ለሰርግ ቤት ወይም በተለያዩ መድረኮች ላይ መፎካከሪያ ተደርጎ መቅረብ የለበትም፡፡ ይህ በፍጹም ተቀባይት ያለው ስነምግባር አይደለም፡ ኢስላማዊ ሸሪዓንም ይጋፋል፡፡ ለሚስትህ ቁንጅና የጓደኞችህን ምስክርነት አትፈልግ፡ ይህ አካሄድህ ኋላ ላይ ዋጋ ሊያስከፍልህ ይችላል፡፡
🫵🏼ሁለተኛ፡ በቁንጅናዋ የተፈተነች መሆን የለባትም፡ እራሷን ከፍጥረት ሁሉ በላጭ አድርጋ በመመልከት የምትኩራራ እንዳትሆን ያስፈልጋል፡ ባሎችን በጣም ከሚደብራቸው (ከሚያስቆጣቸው) የሚስት ባህሪ አንዱ ደግሞ ኩራት ነው፡
🔸ይህ ስሜት ሌሎችን ዝቅ አድርጎ መመልከትና መሬት አይንካኝ ካስባላት ይህ ውበት ለሚስትነት አያገለግልም፡ ሲጀምር ባልለፉበት ነገር የሚኩራሩ ሰዎች ግብዞች ናቸው፡፡
🫵🏼በነገራችን ላይ ወንዶችም በውበታቸው የሚኩራሩ ከሆነ ዋጋቸው ይወርዳል፡፡
🔸አላህ ሰርቶ በሰጠን ነገር ላይ አመስጋኝ እንጂ ትእቢተኛ መሆን አይገባም፡ በእርግጥ እራሳችንም ለፍተን አግኝተነዋል ብለን በምናስበውም ነገር መኩራራት ተገቢ አይደለም፡ ጸጋዎች ሁሉ ባለቤትነታቸው ለአላህ ነው የሚመለሰው፡፡
🔸እንደ ተረት አንድ አይነስውር ሰው አንዲት አይናማ ሴትን አግብቶ ይኖር ነበር፡፡ ሚስቱም የአይነስውርነቱን አጋጣሚ እንደ እድል በመጠቀም ዘወትር ልትኩራራ ትሞክራለች፡፡ አይኔን፤ ቅንድቤ፡ ሽፋሽፍቴ፡ ማማር የጥርሴን አደራደር፡ የጉንጬን አወራረድ ወዘተ ብታይ ውበቱ ለጉድ እኮ ነው፡ እያለች ጉራዋን እየነዛች አስቸገሪቺውና አንድ ቀን አንቺ ሴትዮ እስኪ ተይኝ ባክሽ እንደምትይው ወደር የለሽ ቆንጆ ብትሆኝ እኮ አይናማዎቹ ለኔ አይነቱ አይተውሽም ነበር አላት ይባላል፡፡
🫵🏼ሶስተኛው፡ ዉበቷ በዲን መርሆዎች የተጠበቀ መሆን አለበት፡፡ ውበት በሴቶች ላይ በጣም ያምርባቸዋል፡ የበለጠ የሚያምረውና የሚደምቀው ደግሞ በኢስላማዊ ስረአት ሲሸፈን፡ በጥብቅነት ሲሞሸር ነው፡ ለአደባባይ የማይቀርብ ውድና ብርቅ ጌጥ መሆኑ ታውቆ ጥበቃና ከለላ ሲደረግለት፡ በጨዋነት ሲከሸን፤ በእርግጥ ጸጋ ይሆናል፡፡ ተቃራኒው ገዳይ መርዝ ስለሆነ መራቁን እንመክራለን፡፡
👱🏼‍♂️ወንዱንም በተመለከተ ሰይዲና ዑመር ረአ ሴት ልጃችሁን ፉንጋና ወራዳ ለሆነ ሰው አትዳሩ፡ እናንተ የምትወዱትን ውበት እነሱም ይወዳሉና ብለዋል፡፡ (ሀዲሱ ደኢፍ ነው ተብሎዋል) ወንዶች ለራሳችን የምንወደውን ለሴት ልጆቻችንና እህቶቻችን መውደዱ ፍትሃዊ የመሆን ምልክትም ነው፡፡
7ኛ፡ የቤተሰብ ክብር
🔸ይህ የቤተሰብና የአያት ቅድመ አያቶች ክብር ነው፡፡ በቤተሰቡ መካከል ቤተሰባዊ ትስስር፡ የተቅዋና ኢማን ቤተሰብ የመሆን ታሪክ ማለቴ ነው፡ ማግባት የሚፈልግ ሰው የተከበረ ቤተሰብን፡ በታላላቅ እሴቶች (እንደ ኢማን ተቅዋ፡ ዒልም፡ ጥብቅነት፡ መተባበር እና ቤተሰባዊ ትስስራቸው፡) የታወቁ ቤተሰብ ልጅ ካገኘህ አትልቀቅ፡፡
🔸የሰው ልጅ የሚኖርበት ከባቢ ልጅ ነው ይላሉ አረቦች፡ ከላይ ያነሳናቸው እሴቶች መሀል ያደገ ሰው ምንም ቢሆን የተወሰነውን ያህል መውረሱ አይቀርም፡ መልክተኛውም ለዘር ፍሬያችሁ ማረፊያውን ቦታ በጥንቃቄ ምረጡ ብለዋል፡ (ዘር ከልጉዋም ይስባልና) ሴቶች እህቶቻቸውንና ወንድሞቻቸውን አምሳያ ይወልዳሉና፡
🔸በታወቀው ሀዲሳቸውም፡ አንዲት ሴት ሚስት ተደርጋ ከምትወሰድበት ምክንያት አንዱም ከተከበረ ቤተሰብ መምጣቷን አድርገውታል፡፡ በጋብቻ የምንጣመረውን ሰው ምንጩን በደንብ ማጣራት ጥሩ ነው፡ ክብር አደብ፤ እውቀት፡ ጠንካራ የዝምድና ትስስርና የመተባበር ባህል ያለበት፡ ወዘተ ጉዳዮች በአግባቡ ቢታዩ አይከፋም፡
🔥ብልግና፡ ዝርክርክነት፡ መቆራረጥና መበጣበጥ፡ ፍችና መለያየት ባህላቸው የሆኑ ቤተሰቦች ውስጥ ያደጉ ሰዎች አዙሪቱ ውስጥ የመግባት እድላቸው ሰፊ ነው፡፡ ሰው ከቤተሰቦቹ ብዙ ነገር የሚማር ፍጡር ነው፡ ሳያውቀው ጭምር፡ (አንዳንዴ ልክ መስሎት ሊያድግ ይችላል)፡ መቼም ከዚህ አይነት ቤተሰብም አላህ መልካሞችን ሊፈጥር እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡ እኔ ግን የማወራው እንደአጠቃላይ መርህ ነው፡ ዩክሪጁል ሀየ ሚነል መይት ነውና፡፡
🔸አናሱ ከማዓዲኒ ዘሃቢ ወልፊደቲ፡ ሰዎች እንደ ማእድናት ናቸው፡ ወርቅና ብር እንዳለበት፡፡ ከማእድናት ውስጥ እጅግ በጣም ውድና ብርቅ የሆኑ አሉ፡ መካከለኛም አሉ ዝቅተኛም አሉ፡ (ወርቅ እንኳ ባለ 14፤18፤24 ካራት አለው እኮ) ከቻልክ ውድና ብርቅ የሆነውን አይነት ሰው ካገኘህ እንዳትለቅ፡ ህይወትህን በሙሉ የምታጌጥበት ነውና፡፡
🫵🏼የትዳር አጋርህን ስትመርጥ ከምርጥ ቤተሰቦች የተቀዳች መሆኗን ከግምት አስገባ፡፡ ከተከበረ ቤተሰብ የመጣች ልጅ ከቤተሰቧ የወረሰችው መልካም ነገር ይከተላታል፡ አንድ አባት ለልጁ እንዲህ አላት፡ ልጄ ሆይ ባልሽን በክብርና ፍቅር ያዢ፡ ከቤተሰባችን መዝገበ ቃላት ውስጥ ፍቺ የሚል ቃል የለም፡፡
🔸ሌላኛዋ እናት ደግሞ ልጄ ሆይ ለባልሽ ባሪያ ሁኚለት፤ ሎሌ ይሆንልሻልና፡፡
🔥በተቃራኒው ሲሆንም አይተናል፡ የልጃቸውን ባል የሚንቁ ደፍረው የሚያስደፍሩ ቤተሰቦች አሉ፡ ከማህበረሰቡም ጋር ያላቸው የሻከረ ግንኙነት ቤተሰቡ ውስጥ ያለውን የስነምግባር ልኬት ያሳብቅባቸዋል፡፡
🫵🏼ይህ ሁሉ ነገር ልጅቱን በቀጥታ ሊወክላትም ላይወክላትም ይችላል፡ ግና ማንኛውም ሰው ከቤተሰቡና ከኖረበት ማህበረሰብ የሚወርሰው ባህሪ መኖሩ አይቀርምና በአንክሮ መመልከት መልካም ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ቀጥታ ለወንዱም እኩል በኩል የሚገለበጥ መሆኑ እንዳይረሳ፡ ሁሉም የተቀዳበትን ምንጭ መምሰሉ አይቀርምና፡
🫵🏼ወንድሞችና አባቶች ለሴት ልጃችሁና እህታችሁ መጥቶ የሚጠይቀውን ሰው ከዚህ አንጻር መገምገም ጥሩ ነው፡፡ ምንጩ ጥርት ያለ ክብርና ማእረግ፡ እምነትና ተቅዋ፡ አደብና አኽላቅ፡ ካለበት ቤት የመጣውን ጎረምሳ ቅድሚያ መስጠት ብልህነት ነው፡
8ኛ ባህል
🔸እኛ ያደግንበት የሥልጣኔ ውጤቶች ነን፣ እናም በተለያዩ ባህሎች ባህሪያት ተጽዕኖ ይደረግብናል።

ለጎጆዬ

03 Nov, 18:30


🧕🏼👱🏼‍♂️ሁለቱም ወገኖች ልዩነትን ሲቀበሉ እና የባህል ልዩነቶችን ለመፈተሽ ጥረት ሲያደርጉ፣ የባህል ልዩነቶች ግንኙነቱን ለማበልጸግ እና ለማሳደግ  ያገለግላሉ።
🧕🏼👱🏼‍♂️ሁለቱም ሰዎች ከአንድ ሀገር የመጡ ቢሆኑም፣ በግንኙነት ሂደት ውስጥ የባህል ልዩነቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ንዑስ ባህሎች በከፍተኛ ሁኔታ ሊለያዩ ይችላሉ፣ ለምሳሌ፣ በተለያዩ የዘር ቡድኖች፣ በገጠር እና በከተማ አካባቢዎች፣ በማህበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ደረጃዎች እና በሀገሪቱ አካባቢዎች።
🔸እያንዳንዱ ቤተሰብ ድርጊቶችን፣ ስሜቶችን፣ የንግግር እና የአለባበስ ዘይቤን፣ የቤተሰብ ትስስርን እና ሌሎች ገጽታዎችን በተመለከተ የራሱ የሆነ ባህላዊ ደንቦች አሉት።
🔸በባህሎች መካከል የተለያዩ የልዩነት ደረጃዎች አሉ፡ ጎሳ + ደረጃ + የጠባቂነት  ደረጃ።
🔸በባህል ልዩነት ምክንያት ግጭቶች ወይም መሰናክሎች በትዳር ህይወት ዑደት ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ።
🤔አንድ ሰው ባህሉን እንዲተው ከመጠበቅ፣ እርስ በርስ ለመማማር እና ባህሎችን ለመጋራት መልካም አስተሳሰብን መቀጠል አስፈላጊ ነው። የሌላውን ሰው ባህል ካልተቀበልክ ወይም ከራስህ ባህል የሆነን ሰው እንደምትመርጥ በልብህ ሀሳቡ ካለብህ ከራስህ ባህል የሆነን ሰው ማግባት ተገቢ ነው።
🫵🏼የትዳር ጓደኛዎ የሚስማማቸውን እና መቀበል የሚፈልጉትን የባህልዎን ክፍሎች እንዲመርጥ ይፍቀዱለት።
 ይቀጥላል…
በኡስታዝ አብዱልገፋር ሸሪፍ
ሚንበር ቲቪ ዘወትር ማክሰኞ
ምሽት 2:30-3:30

ለጎጆዬ

18 Oct, 17:43


በአላህ ስም እጅግ አዛኝ ሩህሩህ በሆነው
ተጣማሪን መምረጫ መስፈርቶች
ክፍል (5)
4ኛ:ሀያዕ (ጨዋነት)
🔸ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) “ለሁሉም ሀይማኖቶች የራሳቸው መገለጫ የሆነ ስነ-ምግባር አላቸው የኢስላም ባህሪ (የተለየ) ሃያዕ ነው” ብለዋል፡፡ በሌላም ዘገባ “የማታፍር ከሆነ የፈለከውን ስራ” ብለዋል፡፡
🧕🏼ሃያዕ ከሴት ልጅ በእጅጉ የሚፈለግ element ነው፡፡ ሃያዕ በወንዶችም ላይ የሚያምር ቢሆንም በሴቶች ላይ ደግሞ እጅግ በጣም የሚያምር ምግባር ነው፡፡
🧕🏼በእውነት ለሴት ልጅ በተለይ እጅግ ድንቅና ውብ ነገር ነው፡፡ የሴት ውበትዋ በሃያዕዋ ውስጥ ነው ይባላል፡፡ ወንዳወንዷን ሴት፣ እንደ ወንዶች ጮኻ የምትስቅ አካሔዷም አወጣጥ አገባብዋም ከወንዶች ጋር የተመሳሰለች ከሆነ ልክ አይመጣም፡፡
🫵🏼በአላህ መልዕክተኛም አንደበትም ተረግማለች፡፡ አብደላህ ኢብኑ ኡበይዱላህ ኢብኑ አቢ መሊከተ እንዳወሩት “ለአይሻ እንዲህ ብለው ተጠየቁ ሴት ልጅ የወንድን ጫማ ትጫማለች? ሲመልሱም በርግጥ ወንዳ ወንዷን ሴት መልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ረግመዋል” አለች፡፡
🔥ከቂያማ ምልክቶችም አንዱ ወንዶች ሴቶችን፤ እና ሴቶችም ወንዶችን መመሳሰላቸው ነው፡
🤔በጨዋነትና በእራስ አለመተማመን (ለራስ ዝቅተኛ ግምት በመስጠት) መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ፡፡ የደካማ ስብእና ባለቤት በመሆን የሚመጣው ልፍስፍስነት ሃያዕ አይባልም የዚህ ባህሪ ምንጩም ፍርሃትና ድክመት በመሆኑ ነው፡፡
🫵🏼ፈሪና ልፍስፍስ ሰው መብቱን ከመጠየቅ ይቆጠባል ይህ ደግሞ ተፈላጊ ምግባር አይደለም፡፡
🔸ሃያዕ (ጨዋነት) ምስጉን ባህሪ ሲሆን የጥንካሬ ምልክትም ነው፡፡ ፈሪ እና ልፍስፍስ መሆን የማይፈለግ ምግባር እና የደካማነት ምልክት ነው፡፡
🤔የአንዲት ሴት ሃያዕ እንዴት ሊታወቅ ይችላል? የሚታወቀውማ በአኗኗር ዘይቤዋ ነው፡፡ ከሌሎች ጋር ባላት ግንኙነት፤ በተለይም ከቤተሰቦቿ (አባቷ፤ወንድሟ በተለይ በአንተ ፊት የምታሳየቸው ተግባራትና የምትጠቀማቸው ቃላት ስለ ሀያእዋ ሊያሳብቁባት ይችላል፡
🤔የሰው ልጅ  ሲናገር እና ሲናደድ አስተሳሰቡና ስነምግባሩ ይጋለጣል፡ ይባላል፡ ስለዚህ በተለያዩ አጋጣሚዎች ይህን ወሳኝ ባህሪ ማረጋገጡ መልካም ነው፡
🧕🏼ለአንዲት ሴት ሀያእ እጅግ በጣም አስፈላጊ መገለጫዋ ነው፡ ይህን ማጣት አጉል ነው፡ ከቤት ስትወጣ፡ ከወንዶች ጋር ያላት ቅርበት፡ የአነጋገር ስታይሏ፡ ባእድ ከሆኑ ሰዎችም ጭምር ያላት የመግባባትና ድንበርን ያለመጠበቅ፡ ቅጥ ያጣ ድፍረት ከሰው መሀል (በተለይ በወንዶች) ማሳየት፤ ለሴት ልጅ፡ ከአለባበስ ከአረማመድና ከአጠቃላይ የላይፍ ስታይሏ፡ ይህን እሴት መገመት ይቻላል፡፡
🔸እሴቱ ለሌሎች የስነምግባር መርሆዎችም መገለጫና ማሳያ በመሆኑ ቸል መባል የለበትም፡፡ አብደላ ኢብኑ ኡመር እንደዘገቡት አንድ ቀን ረሱሉ (ሰዐወ) ከሰዎች አጠገብ ሲያልፉ አንደኛው ወንድሙን ስለሀያእ (አታብዛ) በሚል ሲመክረው ሰሙና ተወው ሀያእ ከኢማን ነው፡ አሉት፡ ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል፡፡

5ኛ፡ መታዘዝ
🧕🏼ከላይ እንዳነሳነው ረሱሉ (ሰዐወ) የመልካም ሴትን መገለጫዎች ሲጠቅሱ፡ ለባሏ ታዛዥ መሆኗን አንዱ አድርገው ገልጸዋል፡፡ ሚስት በሏን የምትታዘዘው የቤቱ አስተዳዳሪ (መሪ) በመሆኑ ነው፡፡መሪ ደግሞ ይታዘዙታል፡ የትኛውም ስብስብ መሪውን ካልታዘዙት ስረአት አልበኝነት መንገሱ አይቀርም፡ ስብስቡም አይቀጥልም፡፡
🤔የሚገርመው ሚስቶች ባሎቻቸውን እንዲታዘዙ ስናስተምር ቅር የሚላቸውና ሴቶችን እንደመጫን የሚቆጥሩ ሰዎች መከሰታቸው፤ ነው፡ እነዚህ ሰዎች የትኛውም ተቋም ሄደው አብሮ ለመስራት ታዛዥና አዛዥ መኖሩን መቀበላቸው አይቀርም፡ ቤትም ተቋም ነው እስካልን ድረስ የእዝ ሰንሰለት ያስፈልገዋልና እንግዳ የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለም።
🔸ባይሆን ቤቱ የተመሰረተበትን አላማ ለማሳካትና በቤተሰቡ መካከል ያለውን የስራ ክፍፍል አሳልጦ ውጤታማ ለመሆን መልካሞቹ ሴቶች ባሎቻቸውን በመልካም ነገር እስካዘዙዋቸው ድረስ መታዘዝ ይኖርባቸዋል፡፡ እዚህም ጋ ጥያቄው የአንዲት ወጣት ሴት ለባሏ ታዛዥነት እንዴት ይታወቃል የሚለው ነው፡፡
🧕🏼ከልምድና ተሞክሮ የተወሰደው ቤተሰቦቿን በመመልከት መሆኑ ነው፡፡ በእርግጥ ሰዎች አንድ አይነት አይደለንም፡ ነገር ግን ሴቶች በእናቶቻቸው ተጽእኖ  ስር መኖራቸውና አርአያ አድርገው እንደሚከተሏቸው ልንክደው አንችልም።
ይቀጥላል…
በኡስታዝ አብዱልገፋር ሸሪፍ
ሚንበር ቲቪ ዘወትር ማክሰኞ
ምሽት 2:30-3:30

ለጎጆዬ

08 Oct, 00:16


በአላህ ስም እጅግ አዛኝ ሩህሩህ በሆነው
ተጣማሪን መምረጫ መስፈርቶች
ክፍል (4)
3ኛ፡ ንቃተ ህሊና
👱🏼‍♂️ንቃተ ህሊናዋ ከፍ ያለችዋን ብትመርጥ በትዳርህ ዕረፍት ለማግኘት ይረዳሃል፡፡
🧕🏼ይህቺ አይነት ሴት (ንቃተ ህሊናዋ ከፍ ያለችዋ) ማለት ስለ ቤት አያያዝ፣ ስለ ገንዘብ አወጣጥና አገባብ፣ ስለ ልጆች ተርቢያ ስለ ባል እንክብካቤ ስለ ጠቅላላ ዕውቀት የተወሰነ ግንዛቤ ያላት ማለት ነው፡፡ ይህቺ ሴት አዕምሮዋን የምታሰራ እና የምትሰጣቸውን ውሳኔዎችም ተቀባይነት የሚኖራቸው አይነት ናት፡፡ እንደዚህ አይነት አቅለኛ ሴት ካልሆነች ግን እራሷንም ባሏንም ብዙ ችግር ውስጥ ልትከት ትችላለች፡፡በርካቶችን ልታስቀይም ትችላለች፡፡ ይህ የሚሆነው አውቃም ሳታውቅም ሊሆን ይችላል፡፡ 👱🏼‍♂️በተመሳሳይ የወንዱም ያው ነው፡ ብስለት የማይታይባቸውን ሰዎች ለትዳር መገፋፋት ተገቢ አይደለም፡ ቀድሞ እንዲበስሉና፡ ሃላፊነት ለመሸከም እንዲችሉ ማብቃት ያስፈልጋል፡፡እንዴት ታውቃለህ የግንዛቤዋን መጠን (አቂል መሆኗን) ይህ የሚታወቀው በተወሰነ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ የተወሰኑ ጥያቄዎችን በማንሳት ስለ ሕይወት እና ተያያዥ ጉዳዮች ያላትን ምልከታ መረዳት ይቻላል፡፡ ስለ ትዳር፣ ስለ ዕውቀት፡ ከሰዎች ጋር ስላላት ግንኙነት፡ ስለሀገርና፡ አካባቢዋ ወዘተ… ጉዳይ በማንሳት መጠያየቅ አቅማችንን መተዋወቅ እንችላለን፡፡
🤔ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ እና አስተያየትዋን በጥንቃቄ አዳምጥ፡፡
🔸ስለ ት/ቷ፣ ስለ ምትወዳቸው ጉዳዮች ስለ ዲንና ስለ ጓደኞቿ ወዘተ… በማንሳት የአዕምሮዋን የብስለት ደረጃ መገመት ትችላለህ፡፡
🤚🏼ሞኛ ሞኝ ሰው ጋር መጋባት በጣም አድካሚ የቤት ስራ የመውሰድ ያህል ነው፡፡ በአባባል ከሞኝ ጋር አትወዳጅ ሊጠቅምህ ፈልጎ ይጎዳሃልና ይባላል፡፡🔸ይህንን ስንል ራሳችንን በማጥራራትና ለሌሎች ዝቅ ያለ አመለካከት በማሳየት መሆን መሆን የለበትም እራሳችንም መለስ ብለን መፈተሸ ተገቢ ነው፡፡
🔸ረሱሉ (ሰ.ዐ.ወ) አላህ የሰጣቸውን እልቅናና ደረጃ በሌሎች ላይ የበላይ ለመሆን ወይም ሌሎችን ለማግለል አልተጠቀሙበትም። ብዙ ጊዜ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ባልደረቦቻቸውን እና ሚስቶቻቸውን ያማክሩ ነበር። ቤታቸው ሲገቡ እንደ ባል (መሐመድ )ነበር የሚሆኑት።የእሳቸው አስተያየት በወህይ ባልተነሳባቸው ሁኔታዎች ውስጥ፣ ሚስቶቻቸውን በክርክር ውስጥ ያሳትፉ ነበር። በተለይ ሀፍሳ በጠንካራ አስተያየት እና ሀሳቧን ለመግለጽ ፈቃደኛ በመሆን ትታወቅ ነበር።
👱🏼‍♂️🧕🏼በተመሳሳይ፣ አጋሮች ሌላውን ለመቆጣጠር ዲግሪ፣ እድሜ ወይም ሌላ ሁኔታዎችን መጠቀም የለባቸውም።
😡"እኔ የበለጠ አውቃለሁ" የሚለው አመለካከት ወደ ኃይልና ግጭት ሊያመራ ይችላል፡ የስልጣን የበላይነትን ለማሳየት አላስፈላጊ ፉክክር ውስጥ ሊከት ይችላል፡🧑🏼‍🎓ብዙ የተማሩ ሴቶች ባለሙያ የመሆን ፍላጎት አላቸው፤ አንዳንዶች ደግሞ ፍላጎት የላቸውም፡፡ አንዳንድ ሴቶች እቤት ውስጥ መቆየታቸው ስራቸውን/ትምህርታቸውን እንደሚያባክን ያምናሉ እናም እርካታ እንዲሰማቸው ለማድረግ መስራት ይፈልጉ ይሆናል፡፡ ሌሎች የተማሩ ሴቶች ከቤት ውጭ ለመስራት ፍላጎት ላይኖራቸው ይችላል።
👱🏼‍♂️ብዙ ወንዶች የተማረች ሴት ቢፈልጉም፣ እሷ ግን ባለሙያ (ፕሮፌሽናል) እንድትሆን ላይፈልጉ ይችላሉ። ሌሎች ወንዶች ሚስታቸው ከመጀመሪያው ጀምሮ ባለሙያ ትሆናለች የሚል ጠንካራ ተስፋ ሊኖራቸው ይችላል። ሁሉም የበላይነት ስሜትን ሳያንፀባርቁ ማስኬድ ይቻላል። 🫵🏼ለዚህም ነው የትዳር አጋርን ለመምረጥ ስናስብ በዚህ ጉዳይ ላይ ልናተኩር የሚገባው።
ይቀጥላል…
በኡስታዝ አብዱልገፋር ሸሪፍ
ሚንበር ቲቪ ዘወትር ማክሰኞ
ምሽት 2:30-3:30

ለጎጆዬ

01 Oct, 04:49


🔸ሌላው የምንኖርበት ማህበረሰብም መረሳት የለበትም፡ አንድ ከመቶ ሙስሊም በሆነበት ሀገር የሚኖሩ ሙስሊም ወንድሞችና እህቶች 99 ከመቶ ሙስሊም ማህበረሰብ እንዳለበት አካባቢ እኩል የኢማን ደረጃ (እኛ ደረጃ መዳቢ ባንሆንም) ልንጠብቅባቸው አንችልም፡ መሰረታዊ የኢስላም መርሆዎች ግን ለምሳሌ ፈርድን (ግዴታዎችን) መስራትና ከባኢረዙኑብን (ታላላቅና አጥፊ ወንጀሎችን) መቆጠብ፡ ትንሹ ስታንዳርድ ተደርጎ ሊወስድ ይችላል፡፡
🔸ሌላው ሙስሊሞች በጣም አናሳ ቁጥር ባላቸው አካባቢ የሚኖሩና ሊጋቡ የሚያስቡ ወንድምና እህቶች በዚህ የዲን ግንዛቤ ላይ በአግባቡ ቢነጋገሩና ቢግባቡ መልካም ነው፡፡ እኔ ይህን ያህል አጥባቂ አልመሰለቺኝም፤ አልመሰለኝም በማለት የሚያማርሩ ሰዎችን ማግኘት ሊያስደነግጥ ይችላል፡፡ እኔ የምፈልገው ለዘብተኛ ሙስሊም እንጂ ሁሉንም ነገር የሚያጠባብቅ መሆኑን ብረዳ አልገባበትም ነበር የሚሉ ባለትደሮች ተገኝተዋል፡ ስለሆነም መርሆዎቹን በግልጽ ማስቀመጥና የት ድረስ እንደምንጠብቅ ማሳወቅ ቀድሞ ነው፡
🫵🏼ከላይ የተዘረዘሩት ጉዳዮች ወንዱንም ሴቱንም መመልከታቻቸው እንዳለ ሆኖ የሴት ልጅ ቤተሰቦች በተለይ ወንዱን ለማወቅና ስለ ባህሪው ለመረዳት ልጃቸውን ሊያግዙ ይገባል፡ ኢማም ሻእፊይ ፡ ፋሲቅ ሰውን ልጁን የዳረለት ከሆን በእርግጥ ዝምድናዋን ቆርጦዋል ብለዋል፡፡ ፋሲቅ (አመጸኛ) ሰው ደግሞ ባል መሆን አይችልም፡ ፊስቁ መከራዋን ነው የሚያበላትና የወልዮች ሚና በተለይ በዚህ ቦታ ይፈለጋል፡፡
ይቀጥላል…
በኡስታዝ አብዱልገፋር ሸሪፍ
ሚንበር ቲቪ ዘወትር ማክሰኞ
  ምሽት 2:30-3:30


 

ለጎጆዬ

01 Oct, 04:49


በአላህ ስም እጅግ አዛኝ ሩህሩህ በሆነው
ተጣማሪን መምረጫ መስፈርቶቸ
ክፍል(3)
2ኛ፡- ሳሊህ መሆን
👱🏼‍♂️🧕🏼ሙስሊሞች የትዳር ጓደኛ ከማግኘታቸው በፊት ሃይማኖታዊ ማንነትን ቅድሚያ እንዲሰጡ መልክተኛው (ሶ.ዐ.ወ) በአበክሮ ተናግረዋል።
🫵🏼አንድ ወንድ ሴት ልጅዎን ለማግባት ቢፈልግ እና ስነምግባሩ ጥሩ ከሆነ እና ለሃይማኖቱ ያለውን ታማኝነት ካረጋገጣችሁ ዳሩለት  ያለበለዚያ ፈተናዎች  እና ጉልህ የሆነ ብክለት በአለም ላይ ይሰራጫል ብለዋል።
🔸ይህ ሐዲሥ አላህን የመፍራት እና የመልካም ባህሪ አስፈላጊነትን አጉልቶ የሚያሳይና አንድ ሰው  ሙሉ በሙሉ ህይወቱን ወደ ወዲያኛው ዓለም በትኩረት መምራት እንዳለበት ያሳያል።
🤔ብዙ ሙስሊሞች ሃይማኖትን ከአምልኮ ጋር በተያያዙ ውጫዊ ድርጊቶች ለምሳሌ እንደ ሰላት ወይም ልብስ ስለመልበስ ብቻ አድርገው አቅልለው ያዩታል።
👱🏼‍♂️🧕🏼ጥሩ ሙስሊም መሆን የእስልምናን ህግ ከመከተል ያለፈ ነገርን ይጨምራል።
🔸ጠንካራ መንፈሳዊ መሠረት መያዝንም ይጨምራል። ከአላህ (ሱ.ወ) ጋር ያለን ግንኙነት እና “መንፈሳዊነት” የሚለው ቃል ሁለቱም የሚያመለክተው የአምልኮን ውስጣዊ ገጽታ ነው። እርስ በርስ መተሳሰርን የሚገነዘቡ እና አላህን (ሱ.ወ) ለማስደሰት የሚጥሩ ሰዎች ደግ፣ አሳቢ እና አፍቃሪ በመሆን ግንኙነቶችን ለመፍጠር እና ለማጠናከር ይረዳሉ።
🔸ጋብቻን በተመለከተ ሰዎች ለሃይማኖታዊ እሴቶቻቸው ምን ያህል ትልቅ ቦታ እንደሚሰጡ እና ሃይማኖትን የሚገልፁበት መንገድ ይለያያል፡፡. 🤔አንዳንድ ሰዎች ማንኛውም ሁለት "ጥሩ" ሙስሊሞች መጋባት ደስተኛ ትዳር ሊኖራቸው ይችላል ብለው ያስባሉ፡፡ እውን ነገሩ ሁሉ እንደዚያ ነው ወይ የሚል ጥያቄ ማንሳታችን ግን አይቀርም።
⚖️የአንድን ሰው የመንፈሳዊነት (የኢማን) ደረጃ ለመለካት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል ምክንያቱም የልብ ጉዳይ ስለሆነ፡፡
🤔አብረው ጊዜ ማሳለፍ፣ የአንድን ሰው አመለካከት እና እምነት ለመወሰን የሚረዱ ጥያቄዎችን መጠየቅ እና ስለዚህ ሰው የሚያውቁትን ሌሎችን መጠየቅ የአንድን ሰው ባህሪ እና የሞራል ሁኔታ ለመገምገም ብቸኛው መንገዶች ናቸው።  
🧐ውጫዊ ገጽታ ባህሪያትን እና አመለካከቶችን ከሚቀርፀው ውስጣዊ ኮምፓስ ጋር መመሳሰል አለበት።
🫵🏼አንድ ሰው ከእስልምና ስርዓቶች (ኢባዳዎች ) አንፃር ሲታይ ሀይማኖተኛ ሆኖ ከስነምግባር አንፃር ግን  ተሳዳቢ፣ ግትር፣ ስስታም ወይም ትምክህተኛ ሊሆን ይችላል።
🤔እንደ አለመታደል ሆኖ፣ በጣም ብዙ ሰዎች የኢስላም ውጫዊ ገጽታዎች ከእውነተኛው እስላማዊ ባህሪ ጋር ሲምታታባቸው እናያለን። ሙስበሀን መያዝ፣ ጀለቢያና ኮፊያ ማድረግ፡ ሂጃብ መልበስ ወይም ረጅም ፂም መያዝ አንድ ሰው ጥሩ ባህሪ እንዲኖረው ዋስትና አይሆንም።
🤔አንዳንድ ሰዎች ከእውነተኛው ኢስላማዊ ባህሪ ይልቅ እነዚህን ውጫዊ የእስልምና ገጽታዎች መተግበር በጣም ቀላል ሆኖ አግኝተውታል።
🔸እስልምና እንደማንኛውም ሀይማኖት በተለያየ ዲግሪ እና በተለያዩ ትርጓሜዎች ሊተገበር ይችላል። በሙስሊሞች መካከል እንኳን ልዩነቶች ሊኖሩ ይችላሉ።ትዳር ቀጥተኛ አመለካከት ባለው ሰው እና የበለጠ ሚስጥራዊ አመለካከት ባለው ሰው መካከል በአኗኗር ምርጫዎች ልዩነት የተነሳ እንዲሁም እርስ በርስ ሊጋጩ በሚችሉ አመለካከቶች እና እምነቶች የተነሳ አንዱ ለአንዱ ጥሩ ምርጫ ላይሆን ይችላል።
🤔ከኛ ጋር ተስማሚ ሊሆኑ ስለሚችሉ የትዳር ጓደኞች ሁሉንም ነገር ማወቅ  ከጋብቻ በኋላ ምንም አይነት አስደንጋጭ ነገር እንደማይኖር ዋስትና አይሆንም። ምክንያቱም ስለ አንድ ሰው አንዳንድ ነገሮችን የሚማሩት ከእነሱ ጋር ሲኖሩ ብቻ ነው። ነገር ግን ከቅርብ ቤተሰብ እና ጓደኞች ዘንድ ስለነሱ መጠየቅ ትልቅና ድንገተኛ የብስጭት እድልን ለመቀነስ ይረዳል።
🔸በመሰረቱ በሙስሊም ህይወት ውስጥ ከሀይማኖት አንፃር ጥሩ ሙስሊም እንደሆኑ ለማወቅ በጣም አስፈላጊው ነገር ሁለት ነገሮች ናቸው።
🔸ኢስላማዊ መስፈርቶችን (እንደ ሰላት እና ፆም) ማሟላት እና ከባድ የሆኑ ወንጀሎችን ማስወገድ (እንደ ሽርክ፣ ግድያ፣ ዝሙት፣ ወዘተ)
🧕🏼መልካም ሴት ለባሏ ጌጥ ናት ጀርባው ጥብቅ ነው መልእክተኛው ሰ.አ.ወ እጅህ አፈር ይንካና ዲን ያላትን ምረጥ ማለታቸው ለዚህ ነው “ዱኒያ በሙሉ መጠቀሚያ ናት ከነዚህ መልካሙ ወይም በላጩ ደግሞ መልካም ሴት ወይም ሚስት ናት ብለዋል
🫵🏼ከዱንያ ምርጡ ወይም በላጩ መጠቀሚያ ሲባል ከስራህም ከዩኒቨርስቲ ዲግሪዎችህ ወይም ሰርተኪፌቶችህ፡ ከድርጅትህ፣ ከካምፓኒህ ከገንዘብህ ሁሉ መልካም ሚስት ትበልጣለች ማለት ነው፡፡
🧕🏼አንድ የአላህ ባሪያ ከተቅዋ ቀጥሎ የሚጠቅመው ነገር ካለ ካዘዛት መርሀባ የምትለው፣ ሲያያት የምታስደስተው ቢምልባት የምታጠራው፣ርቆ ቢሄድ ነብሷንም ገንዘቡንም በታማኝነት የምትጠብቅ ሴት ብትሆን እንጂ፡፡
👱🏼‍♂️አንድ ወጣት አንዲት እኩያው ጋር ተዋደዱ እና አገባት እየዘረዘርን ያለውን ጉዳይ ባብዛኛው ከግምት አልከተተም ነበርና ከጥቂት ጊዜ ቆይታ በኋላ ከጎረቤቱ  ሰውዬ ጋር ትስስር እንዳላት አወቀና በድንጋጤም ተዋጠ፡ እናም የታለ ታዲያ ፍቅራቸው የጠቀማቸው?  🔸ለሚስትነት አፍቃሪ መሆን ብቻ አይበቃም የራሷንም የባሏንም ክብር የምትጠብቅበት የበጎነት ባህሪ ሊኖራት ይገባል፡፡
🤔ከላይ ያለውን መስፈርት (መልካም ሴት) ብዙዎቻችን ጋር ፈጥኖ የሚመጣው ሀሳብ ሂጃቧን በደንብ የምትለብስ ሰላት እና ፆም ላይ ጎበዝ፣ቁርአን እና አዝካር የምትለዋን ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ በመልክተኛው ሀዲስ ላይ በዝርዝር የተቀመጡ አራት መስፈሪያዎች ናቸው፡፡
🔸ሲያዛት የምትታዘዝ
🔸ሲያያት የምታስደስተው
🔸ሲምልባት የምታጠራው
🔸ርቆ ሲሄድ በነብሷም በገንዘቡም ታማኙ ናት (እምነት የማታጓድለው፡)፡ ስለሆነም ሁሉም ሙስሊም ሴት መረዳት ያለባት እውነታ የሷ መልካምነት መገለጫዎች ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች ናቸው፡፡ ማለትም ለባሏ ታዛዥ የምትሳመር፡ መሃላውን የምትሞላለትና ነፍሷና ገንዘቡን ባለበትም በሌለበትም የምትጠብቅ ታማኝ መሆኗ ነው፡፡ በእርግጥ ሒጃብ ሰላት ፆምና ባጠቃላይ የግዴታ ኢባዳዋን የምትተገብር መሆኗ ሳይረሳ ማለት ነው፡፡
🫵🏼እዚህ ጋር ትኩረት የሚያሻው ነጥብ አለ፡ ማናችንም ብንሆን የመልካም ሰውነት ጥጉን አንደርስም፡ ኢማን የምንለው ነገርም ፕሮሰስ (ሂደት እንጂ፡ ሙስሊም ስለሆንን ሙእሚን አውቶማቲካሊ አንሆንም፡
•قَالَتِ الْاَعْرَابُ اٰمَنَّا ۗ قُلْ لَّمْ تُؤْمِنُوْا وَلٰكِنْ قُوْلُوْٓا اَسْلَمْنَا وَلَمَّا يَدْخُلِ الْاِيْمَانُ فِيْ قُلُوْبِكُمْ ۗوَاِنْ تُطِيْعُوا اللّٰهَ وَرَسُوْلَهٗ لَا يَلِتْكُمْ مِّنْ اَعْمَالِكُمْ شَيْـًٔا ۗاِنَّ اللّٰهَ غَفُوْرٌ رَّحِيْمٌ  ا:
•የዐረብ ዘላኖች «አምነናል» አሉ፡፡ «አላመናችሁም፤ ግን ሰልመናል በሉ፡፡ «እምነቱም በልቦቻችሁ ውስጥ ገና (ጠልቆ) አልገባም፡፡ አላህንና መልክተኛውንም ብትታዘዙ ከሥራዎቻችሁ ምንንም አያጎድልባችሁም፡፡ አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና» በላቸው፡፡[ሱረቱል ሁጁራት ፡ 14]
 👱🏼‍♂️🧕🏼ወደ ኢማንናኢህሳን ደረጃ መድረስ ገና ወጣት ለሆኑ ወንዶችና ሴቶች እንዲሁ ቀላል አይመስለኝም፤ የኢስላም የመነከር ጉዳይ እድሜ ልክ የሚሰራ፤ ልፋትና ጥረት ከፍላጎት ጋር የሚፈልግ ነገር ነው፡፡

ለጎጆዬ

24 Sep, 03:34


በአላህ ስም እጅግ አዛኝ ሩህሩህ በሆነው
ተጣማሪን መምረጫ መስፈርቶች
ክፍል(2)
1. ኢስላም  
•ሙስሊም የሆነ ግለሰብ ሙሽሪክ (ጣኦት አምላኪ) ሴትንም ሆነ ወንድን ማግባት ፈፅሞ አይፈቀድለትም፤ የፈለገውን ያህል ውብና ድንቅ ብትሆንም ንግግሯ ጣፋጭ ፈገግታዋም ማራኪ ቢሆንም፡
•وَلَا تَنكِحُوا۟ ٱلْمُشْرِكَـٰتِ حَتَّىٰ يُؤْمِنَّ ۚ وَلَأَمَةٌۭ مُّؤْمِنَةٌ خَيْرٌۭ مِّن مُّشْرِكَةٍۢ وَلَوْ أَعْجَبَتْكُمْ ۗ وَلَا تُنكِحُوا۟ ٱلْمُشْرِكِينَ حَتَّىٰ يُؤْمِنُوا۟ ۚ وَلَعَبْدٌۭ مُّؤْمِنٌ خَيْرٌۭ مِّن مُّشْرِكٍۢ وَلَوْ أَعْجَبَكُمْ ۗ أُو۟لَـٰٓئِكَ يَدْعُونَ إِلَى ٱلنَّارِ ۖ وَٱللَّهُ يَدْعُوٓا۟ إِلَى ٱلْجَنَّةِ وَٱلْمَغْفِرَةِ بِإِذْنِهِۦ ۖ وَيُبَيِّنُ ءَايَـٰتِهِۦ لِلنَّاسِ لَعَلَّهُمْ يَتَذَكَّرُونَ
•(በአላህ) አጋሪ የሆኑ ሴቶች እስከሚያምኑ ድረስ አታግቡዋቸው፡፡ ከአጋሪይቱ ምንም ብትደንቃችሁም እንኳ ያመነችው ባሪያ በእርግጥ በላጭ ናት፡፡ ለአጋሪዎቹም እስከሚያምኑ ድረስ አትዳሩላቸው፡፡ ከአጋሪው (ጌታ) ምንም ቢደንቃችሁ ምእምኑ ባሪያ በላጭ ነው፡፡ እነዚያ (አጋሪዎች) ወደ እሳት ይጣራሉ፡፡ አላህም በፈቃዱ ወደ ገነትና ወደ ምሕረት ይጠራል፡፡ ሕግጋቱንም ለሰዎች ይገልጻል እነርሱ ሊገሰጹ ይከጀላልና፡፡ በቀራ ፡- 221
•እናም አንድ ሙስሊም ወጣት ከጣኦት አምላኪ ወይም እምነት አልባ ከሆነች ሴት ጋር የትም ቢሆን መጋባት አይሆንም፡፡
•ለምሳሌ ለት/ትም ይሁን ለስራ ወደ ተለያየ ዓለም የሚጓዙ ወንድሞች ይህ ጉዳይ ሊገጥማቸው ይችላል በስራ/ በት/ት ምክንያት መቀራረቡ ቢከሰትና ላግባት/ላግባው ብሎ ማሰብ ይፈጠራል፡፡ ምንም ያህል ብትስብህና ብትማርክህ (ለሴትም ቢሆን) ከኢስላም አንጻር ከባድና ስህተት የሞላበት ውሳኔ ነው የሚሆነው፡፡
•መርሰደል ገነዊ ደስ የሚል ታሪክ አለው እዚህ ጋር ጠቀስ ብናደርገው ያስተምራል፡፡ ትልቁ ሰው መርሰድ ከመስለሙ በፊት አናቅ ከምትባል የመካ ሴት ጋር ትስስር (ግንኙነት) ነበረው፡፡)፡፡
•ቲርሚዝ አብደላ ኢብኑ አምር ኢብኑል አስን ጠቅሰው ታሪኩን እንዲህ ዘግበውታል፡፡ መርሰድ ኢብኑ አቢ መርሰድ የሚባል ሰው ነበር የመካ ምርኮኞችን በለሊት እየገባ በማስመልጥ መዲና ድረስ ይዟቸው ይመጣ ነበር፡ በመካ ሲኖር አንዲት አናቅ የምትባል ሴተኛ አዳሪ ሴት ጓደኛው ነበረች፡፡ አንድ ቀን አንድ ምርኮኛ ሰውን ሊያስመልጠው ቀጥሮት ነበርና ወደዚያው ሰፈር አቅንቶ ሳለ የገጠመውን ሁኔታ እራሱ ይተርካል፡-
•በአንድ ጨረቃማ ሌሊት ከመካ ቤቶች (ግድግዳ) በአንዱ ተጠልዬ ሰውዬዬን እየጠበኩት ሳለ በድንገት ወደ ቆምኩበት አናቅ መጣችና በጥላዬ አወቀቺኝና
🧝🏻‍♀️መርሰድ
ብላ ተጠራች
🥷🏼አቤት መርሰድ ነኝ
አልኳት
🧝🏻‍♀️እንኳን ደህና መጣህ (አህለን ወመርሀበን) እኛ ቤት እንሂድና ማደር አለብህ
አለችኝ እኔም
🥷🏼አናቅ ሆይ አላህ ዚናን እርም አድርጎታል አልኳት፡፡
ከዚያም
🧝🏻‍♀️እናንተ ሰዎች ሆይ ይሄ ሰውዬ ምርኮኞቻችሁን ይዞ ሊጠፋ ነው
ብላ ጮኸች
ስምንት ሰዎች ይከታተሉኝ ጀመር ኸንዳማ ከሚባለው ተራራማ መንገድ ሮጬ አንድ ዋሻማ ጉድጓድ ውስጥ ገባሁ እየተሯሯጡ መጡና ከጉድጓዱ ጫፍ ላይ ቆመው ሽንታቸውን በአናቴ ላይ ለቀቁት እኔን ከማየት ግን አላህ ጋረዳቸውና አመለጥኩኝ፡ ከዚያም ወደ ቄያቸው ተመለሱ እኔም ወደ ቀጠርኩት ወፍራም ሰውዬ ተመልሼ እያደከመኝም ቢሆን መዲና አደረስኩት።
•ከዚያም ወደ ረሱል ሰ.ዐ.ወ ሄድኩና
🥷🏼አናቅን ላግባት  አልኳቸው
መልስ ሳይሰጡኝ ቀሩ ወድያው መጡና ያመርሰድ
•اَلزَّانِيْ لَا يَنْكِحُ اِلَّا زَانِيَةً اَوْ مُشْرِكَةً ۖوَّالزَّانِيَةُ لَا يَنْكِحُهَآ اِلَّا زَانٍ اَوْ مُشْرِكٌۚ وَحُرِّمَ ذٰلِكَ عَلَى الْمُؤْمِنِيْنَ
•ዝሙተኛው ዝሙተኛይቱን ወይም አጋሪይቱን እንጂ አያገባም፡፡ ዝሙተኛይቱንም ዝሙተኛ ወይም አጋሪ እንጂ አያገባትም፡፡ ይህም በምእምናን ላይ ተከልክሏል፡፡[ሱረቱል ኑር  ፡ 14]
    የሚለውን ቀሩና እንዳታገባት አሉኝ፡፡
•ስለዚህ ለአንድ ሙስሊም ሙሽሪክ ወይም እምነት የለሽ ሰውን ማግባት እርም ሆኖበታል፡፡
•እዚህ ጋር የአህለል ኪታብ (የአይሁዳና የክርስታኖች ጉዳይ መነሳቱ አይቀርም እንደተጠቀሰው ፍቃድ ስላለበት ማለት ነው፡፡
•يٰٓاَيُّهَا الَّذِيْنَ اٰمَنُوْٓا اَوْفُوْا بِالْعُقُوْدِۗ اُحِلَّتْ لَكُمْ بَهِيْمَةُ الْاَنْعَامِ اِلَّا مَا يُتْلٰى عَلَيْكُمْ غَيْرَ مُحِلِّى الصَّيْدِ وَاَنْتُمْ حُرُمٌۗ اِنَّ اللّٰهَ يَحْكُمُ مَا يُرِيْدُ
•ዛሬ መልካሞች ሁሉ ለናንተ ተፈቀዱ፡፡ የእነዚያም መጽሐፍን የተሰጡት ሰዎች ምግብ (ያረዱት) ለእናንተ የተፈቀደ ነው፡፡ ምግባችሁም ለነሱ የተፈቀደ ነው፡፡ ከምእመናት ጥብቆቹም ከእነዚያ ከእናንተ በፊት መጽሐፍን ከተሰጡት ሴቶች ጥብቆቹም፤ ዘማዊዎችና (ዝሙተኞች) የምስጢር ወዳጅ ያዢዎች ሳትኾኑ ጥብቆች ኾናችሁ መህሮቻቸውን በሰጣችኋቸው ጊዜ (ልታገቡዋቸው የተፈቀዱ ናቸው)፡፡ ከእምነትም የሚመለስ ሰው በእርግጥ ሥራው ተበላሸ፡፡ በመጨረሻም ቀን እርሱ ከከሳሪዎቹ ነው፡፡[ሱረቱል ማኢዳህ 5]
ይቀጥላል…
በኡስታዝ አብዱልገፋር ሸሪፍ
ሚንበር ቲቪ ዘወትር ማክሰኞ
ምሽት 2:30-3:30

ለጎጆዬ

15 Sep, 18:17


በአላህ ስም እጅግ አዛኝ ሩህሩህ በሆነው
ተጣማሪን መምረጫ መስፈርቶች

መግቢያ
ክፍል(1)
ለራስህ ጥሩ አጋር የማግኘት ሂደቱን ለመጀመር በአንተ/ቺ መርሆች እና ቅድሚያ በምትሰጣቸው ነገሮች ላይ ለማሰብ ብቻ ጊዜ ማሳለፍ አስፈላጊ ነው።
🤔ከአንተ/ቺ ጋር በጣም ሊስማሙ የሚችሉ የሰው ዓይነቶች እና በጣም ምቹ የሆኑትን የስብዕና ዓይነቶችን ግምት ውስጥ አስገባ/ቢ።
📝የአንተን/ቺን እሴቶች እያሰብክ ከትልቁ ጀምራችሁ በቅደም ተከተል ጻፉት፤የማትደራደሩበትን ወይም ያለሱ መኖር የማትችሉትን እሴቶች (ኮር ቫልዩስ) ያድምቁ።
📝በመቀጠል በትዳር ጓደኛህ ውስጥ የምትፈልጓቸውን ባህሪያት ዝርዝር አዘጋጁ  ደረጃም አውጡላቸው እና አስፈላጊ የሆኑትን ጎላጎላ ባለ መስመር ጻፉት.
🤔ከዚያም፣ በደንብ ከሚያውቃችሁ የቤተሰብ አባላት እና ጓደኞች ጋር ተነጋገሩ፡ ስለአንተ/ቺ ያላቸውን ስሜት እንዲገልጹ ጠይቋቸው፣ በተለይም አንተ ከፍተኛ ዋጋ ስለሰጠሃቸው ገዳዮች ያላቸውን አስተያየት ጠይቅና ግብረመልሳቸውን ውሰድ፡ በእርግጥስ ለአቅመትዳር የደረስክ/የደረሽ ይመስላቸዋል፡ ትዳርን ለመመስረት በሚያስፈልገው ቁመና ላይ እንደሆንክ/ሽ ይሰማቸው እንደሆነ በግልጽ ጠይቃቸውና ስሜታቸውን በነጻነት እንዲያጸባርቁ ጠይቋቸው፡፡
🤔የራስህንም ጥንካሬና ድክመት ከግምት ውስጥ አስገባ፡
👱🏼‍♂️ባል ብሆን ለሚስቴ ምን ልሰጣት እችላለሁ፡ በምን ምክንያትስ ላስከፋትና ላልመቻት እችላለሁ፡ ብሎ ከራስ ጋር ማውራት ደግ ነው፡
🧕🏼እህትም እንዲሁ እውን ሚስት ለመሆን ዝግጅቱ (ውጫዊውም ውስጣዊውም) ዝግጅት አለኝ ብለሽ እራስሽን በታማኝ ሚዛን ላይ አስቀምጠሸ እይው፡
🔸ይህን ሁሉ ውጣውረድ ለምን አመጣህ ልባል እንደምችል እገምታለሁ፡ መልሴ
🫵🏼የሰው ልጅ በሕይወቱ ከሚወስናቸው ትላልቅ ውሳኔዎች መካከል የትዳር አጋሩን መምረጥ ነው፡፡ የህይወቱ አጋር፣ የልጆቹ እናት/አባት የሚመርጥበት ሂደት ከባዱ እና ትልቁ የውሳኔ አጋጣሚ ነው፡፡ ምክንያቱም ረጅሙ የህይወት ክፍል በዚህ ውሳኔ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የዚህን ውሳኔ ውጤት ተከትሎ መደሰት ወይ ተቃራኒ ሊገጥመው ይችላል፡፡ ስለሆነም ተቻኩሎ ከመወሰኑ በፊት ከራሱ ጋር ጊዜ ወስዶ ማሰብ፣ ከአዋቂዎች ጋር መምከር አለበት ጌታውንም ጠለቅ ብሎ መለመን አለበት (ኢስቲኻራ ማድረግ አለበት)
አንዳንዴ የፊልምና የድራማው ዓለም ምርጫውን ቀለል አድርጎ የሚያቀርብበት አጋጣሚ አለ አንዴ በጓደኝነት ሌላ ጊዜ በድንገት፣ የአይን ፍቅር፣ በአድናቆትና ተያያዥ አጋጣሚዎች ወጣቶች ፍቅር ይዟቸው በዚያው እንደተጋቡ ለማሳየት ይሞክራሉ፡፡ በዚህም ወጣቶችን ሳያውቁም ሆነ አውቀው በዚሁ አቅጣጫ እንዲፈሱ ለማድረግ ስራን ይሰራሉ፡፡
አድናቆት ብቻውን አይበቃም ጣፋጭ የፍቅር ቃላትን መለዋወጥ ብቻውን ለዚህ ከባድ ውሳኔ በቂ ግብአት አይደለም ምክንያቱም ሕይወት በስሜት ትስስር ብቻ የምትፈስ ወንዝ አይደለችምና፡፡ አላህም እንዲህ ይላል “ጌታችን ሆይ በዚህ ዓለም በቀጣይም ዓለም በጎ ነገርን ለግሰን……” ሰይዲና አሊይ “ፊዱኒያ ሀሰነተን” ማለት መልካም ሚስት ማለት ነው ብለው ተርጉመውታል በአኼራ ደግሞ ሁረልአይን ነው ብለዋል “ወቂና አዛበናር” ከመጥፎ ሚስት ነው ብለዋል፡፡
መልካም ተጣማሪ ማግኘት በዱንያ ላይ ሰላምና ደስታ ሲያጎናፅፍ መጥፎ ምርጫ ደግሞ ውጥንቅጥ መከራና ድካምን ይዞብህ መምጣቱ አይቀርም፡፡ አላህ ይጠብቀንና
መልካም ሚስትና ሙዕሚን የሆኑ ልጆች ቀጣዩ ዓለምም ከእትና አባት ጋር የሚሰበሰቡ መሆኑን አላህ ነግሮናል፡፡
ادْخُلُوا الْجَنَّةَ أَنتُمْ وَأَزْوَاجُكُمْ تُحْبَرُونَ 
«ገነትን ግቡ እናንተም ሚስቶቻችሁም ትደሰታላችሁ ትከበሩም አላችሁ» (ይባላሉ)፡፡[ሱረቱል ዙህረፍ ፡70]
 
وَٱلَّذِينَ ءَامَنُواْ وَٱتَّبَعَتۡهُمۡ ذُرِّيَّتُهُم بِإِيمَٰنٍ أَلۡحَقۡنَا بِهِمۡ ذُرِّيَّتَهُمۡ وَمَآ أَلَتۡنَٰهُم
مِّنۡ عَمَلِهِم مِّن شَيۡءٖۚ كُلُّ ٱمۡرِيِٕۭ بِمَا كَسَبَ رَهِينٞ
እነዚያም ያመኑትና ዝርያቸውም በእምነት የተከተለቻቸው ዝርያቸውን በእነርሱ እናስጠጋለን፡፡ ከሥራቸውም ምንም አናጎድልባቸውም፡፡ ሰው ሁሉ በሠራው ሥራ ተያዢ ነው፡፡[ሱረቱል ጡር ፡ 21]
 
🤔ስለሆነም ተጣማሪን ለመምረጥ መረጋጋት፣ ማስተዋል መመካከርና ኢስቲኻራ የሚያስፈልገው ትልቅ አጀንዳ ነው፡፡ የስሜት ግፊት በዚህ ውሳኔ ላይ ተቀባይነት የለውም ወይም ከዚህ በታች የምንዘረዝራቸውን መስፈርቶች ከግምት ሳይከቱ ልቤ ወዷታል ማለት ዋጋ የለውም፡፡ የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ማለታቸው ተዘግቧል፡፡ “ለዚህ ፍሬያችሁ የምታኖሩበትን ስፍራ በጥንቃቄ ምረጡ እኩዮችን አጋቡ ለሴቶቹም እኩዮቻቸውን አጋቡዋቸው“ ኡስማን ኢቢልአስ የሚባል ሰሃባ ልጆቹን፣እንዲህ ይላቸው ነበር፡፡ ጋብቻ አድራጊ ሰው እንደ ገበሬ ነው ገበሬ ደግሞ ቡቃያውን የት እንደሚተክለው ያስተውላል፡ መጥፎ ዝርያ ጥሩ ፍሬ የሚሰጥበት እድል በጣም ጠባብ ነው፡፡”
🫵🏼ወደ ዝርዝር መስፈርቶች ከመግባታችን በፊት የሚከተሉት ጥቂት ነጥች ማስታወሻ ተደርገው ይወሰዱልኝ፡እየተዘረዘሩ ካሉት ነጥቦች መካከል የኔ ሚስት ወይም ባል የትኛውን ነው አሟልታ/አሟልቶ ያገባሁት እያልን መብሰልሰል ዋጋ የለውም፡ ባይሆን፡-
1ኛ. አላህ የሰጠንን ወደን መቀበል፡- አንተ ገይብን (የሩቅ) ማወቅ ቢሰጥህ ኑሮ አሁን ያለውን ነበር የምትመርጠው፡፡
2ኛ. ለባለቤትህ/ሽ በርህራሔና በመልካም ዘዴ አስተምራት/ሪው፣ ስታነብ ለምሳሌ አንዱን ጉዳይ ግልፅ ድክመት ሆኖ ሊታይህ ይችላል ያንኑ ጉዳይ (ምሳሌ ንፅሕና ቢሆን) ከዱዓው ጎን ለጎን ብታስተምራት በዘዴ ልትቀየር/ ሊቀየር ትችላለች/ይችላል፡፡
3ኛ. እውቀትና ተሞክሮ የሚገኝባቸው የእውቀት መድረኮች ላይ ለመገኘት ሞክሩ፡ ይህ ስፍራ የአላህ ራህመት የሚወርድበት ቦታ ነው፡፡ ከሰማዩ ጀነት በፊት የምድር ላይ የጀነት ጨፌም ነው፡፡
ከዚህ ቀጥሎ ተጣማሪዎቻችንን ከመምረጣችን በፊት ከግምት ከተን ማሳብ ያሉብንን ነጥቦች በዝርዝር እናያለን፡ ሀሳቦቹ የመጨረሻና ያለቀላቸው ናቸው ብዬ አላስብም፡ ሰው የራሱ ብዙ  ፍላጎቶች ሊኖሩት ይችላል፡ በተጨማሪም የተወሳሰበ መስፈርት በመደርደርም ጋብቻን ማወሳሰብም ተገቢ አይደለም፡ ግና የህይወት አጋርንም መምረጥ ትልቅ ቁም ነገር መሆኑን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለበትም፡፡
ይቀጥላል…
በኡስታዝ አብዱልገፋር ሸሪፍ
ሚንበር ቲቪ ዘወትር ማክሰኞ
ምሽት 2:30-3፡30

ለጎጆዬ

01 Sep, 13:03


በአላህ ስም እጅግ አዛኝ ሩህሩህ በሆነው
ለትዳር መመስረት ሊኖር የሚገቡ
ስነልቦናዊ ዝግጅቶች
ክፍል (2)
🤚🏼መስዋዕትነት
🏠ቤት (ትዳር) ያለመስዋዕትነት አይቆምም አይዘልቅምም ወንዶች አባቶቻቸውን ሴቶችም እናቶቻቸውን እንደምን ቤቱ እንደቆመና እስከ ዛሬ እንደቀጠለ ይጠይቁ ያለልዩነት ሊነግሯቸው የሚችሉት ዋጋ የተከፈለበት መሆኑን ነው፡፡
🤔በተደጋጋሚ የነካቸውን የህይወት ውጣውረድ ታግሰው አሣልፈውታል፡፡ በእጃቸው ያለን ውድ ነገር ገብረውለታል ለቤቱ መቀጠል፤ ትዳሩ እንዳይፈርሰ ስለሆነም በብዙ ደክመውለታል፡ ለሰነበተ ትዳር በእርግጠኝነት የተከፈለ መስዋዕትነት አለ፡፡ ምክንያቱም ትዳር ባጠቃላይ ያለመስዋዕትነት የሚቆምና የሚዘወትር ነገር አይደለምና፣በነገራችን ላይ ይህን መስዋእትነት የሚከፍሉት ባልና ሚስቶች ብቻ አይደሉም።አንዳንዴ ልጆችና ሌሎችም ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
🔸ኡሙ ሀኒዕ የአልይ ኢብኑ አቡጣሊብ እህት (ለረሱሉ የአጎት ልጅ ናት) ህፃናት ጥሎባት ሞተ እናም ረሱሉ ለጋብቻ አጭተው ጠየቋት እሷም ይቅርታ ጠይቃ ይቅርብኝ አለች፡፡ የቲም ልጆቿን እንደምክንያትም አቀረበች ማለትም እነሱን ተንከባክቦ ለማሳደግ እየታተረች መሆኑን ገለጸች ምክንያቱም ልጆቿን ስትንከባከብ ቢዚ ስትሆን የባሏን መብት ልታጓድል ነው፡፡
የባሏን መብት አሟላለሁ ስትል ደግሞ ልጆቿን ጣልጣል ልታደርጋቸው ነው ስለዚህ ረሱሉን (ሰ.ዐ.ወ) የመሰለ ባል ይቅርብኝ ይቅርታ አለች፡፡ በእርግጥ በዱንያም በአኼራም የምዕመናን እናት የሚባለውን ማዕረግ ነው ይቅርብኝ ያለችው በዘመናዊው ቋንቋ (ክብርት እመቤት) ይህን ማን ያደርጋል?ከባድ ዋጋ ነው የከፈለችው ባሏ ትቶት የሞተው ቤት ችግር እንዳይደርስበት በመፍራት
🤚🏼መስዋዕትነት
🔸ረሱሉም (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፡- ግመልን ከተሣፈሩ ሴቶች ምርጦቹ የቁረይሽ ሴቶች ናቸው፡፡ ለህፃናት ልጆቻቸው እጅግ አዛኝ በተመሣሣይም ለባሎቻቸው ታማኝ ጠባቂዎች በማለት አወደሱ፡፡
🔸ጃቢርም አንድ ቀን ረሱሉ የሙሽርነት ምልክት አይተውበት አገባህ እንዴ ሲሉ ጠየቁኝ ይላል፡፡ አዎ አልኳቸው ድንግሏን ወይስ አግብታ የምታወቀውን አይ አግብታ የምታውቀውን አልኳቸው ስለምን ወጣት ሴት አላገባህም እርስ በርስ ትጨዋወቱ ነበር አሉኝ፡፡ እኔም አብደላ(አባቱን) ሰባት ሴት ልጆችን ነው ትቶብኝ የሞተው ስለዚህ ያመጣኋት ሴት እነሱንም የምትንከባከብልኝ እንድትሆን ብዬ ነው (በሰል ማለቷን ፈልጎ) ዱአም አደረጉልኝ፡፡ ይላል፡፡
🔸ጃቢር ሁሉም ወጣት በትዳር ማግስት የሚፈልጋት ጣዕም (ከወጣትና ቆንጆ ሴት ጋር መደሰትን) መስዋዕት አድርጎ የአባቱን ጎጆ ከመበተን ታደገው፡፡ ወጣት (ድንግሏን) አምጥቶ እራሱን ቢያዝናና የማይወድ ወንድ የለም ግና ከራስ አልፎ ማሠብ የሚያስፈልግበት አጋጣሚ ነበርና ጃቢር ከወነው፡፡
🤚🏼መስዋዕትነት
🤔መቼም ከግለስብ ጥቅም የግሩፕ ጥቅም ይቀድማል ቤተሰቡን ከራሱ ያስቀደመ በዚህ ስራውም የአላህን ውዴታ የሻበት ሰው ምንዳውን ሣያገኝ አይቀርም፡፡
🔸አውፍ ቢን ማሊክ እንደዘገቡት መልዕክተኛው እንዲህ ብለዋል፡ “እኔና ጉንጯ የደረቀ ሴት እንዲህ ነን በቂያማ ቀን (መሀልና ሌባ ጣታቸውን) አጣመሩ ሴቶዮዋ ባሏ ሞቶባት የጥሩ ቤተሰብና ቆንጅና ባለቤት ሆና ሳለ ነፍሷን ልጆቿ እስኪያድጉ ወይም እስኪሞቱ የተቆጣጠረች (ምንዳዋ ይህ ነው አሉ)፡፡
🫵🏼ወደ ትዳር ለተነሳ ሰው ይወቀው ለመስዋዕትነት ዝግጅቱ ሊኖረው እንደሚገባ፡፡ ወደ ጋብቻ መጓዝም ወደ መስዋዕትነት መጓዝ እንዳለበትም መረዳት አለበት በዚህም ምንዳ የሚያገኝበት መሆኑ እንዳይረሳ “አላህ የበጎ ሰሪዎችን ምንዳ አያጠፋም”9፥120
🤔እንደጥያቄ  ምናችንን ነው መስዋእት አድርገን የምንከፍለው፡ ማለታችን አይቀርም ፡፡ ከላይ ያነሳነው የሃላፊነት ስሜት ከፍተኛ ደረጃው መስዋእትነት ነው፡፡
👱🏼‍♂️🧕🏼ትዳራችን እንዲጎለብት፡ አምሮና ደምቆ እንዲቀጥል የሚጠይቃቸው ዋጋዎች በተለያየ ጊዜ የተለያየ ነው፡ ሳንሰለች ከከፈልንለት አምሮና ደምቆ ይዘልቃል።ካልሆነም በተቃራኒው ይሆናል።
👱🏼‍♂️🧕🏼ለትዳር ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ጉዳዮች መስዋእትነት የሚጠይቁን ነገሮች ገንዘባችንን፣ጊዚያችንን፣ ምቾታችንን፣ደስታችንን፣እረፍታችንን፤ ክብራችንን፡ ህይወታችንን ጭምር ልንጠየቅ እንችላለን።
  🤚🏼መስዋዕትነት
👱🏼‍♂️🧕🏼ይህ ቤት ደግሞ ልጆች ተመርተው ለአላማ የሚሰናዱበት ማሰልጠኛ በመሆኑ ብዙ ነገር ነው የሚጠይቀው፡የግል ጥቅምና ፍላጎትን ብቻ በማሳደድ ሊቆም አይችልም።
👱🏼‍♂️🧕🏼በተለይ ባለንበት ተጨባጭ  ከበርካታ አድካሚና አስቸጋሪ እውነታዎች ጋር ተጋፍጦ ቤተሰብን ሰብስቦ፤ ምቾቱተን ጠብቆ ማቆየት ቀላል አይደለም።
👱🏼‍♂️🧕🏼ስለዚህ  የምንገባበት የትዳር ስምምነት በውስጡ የሚገኙ በርካታ ጸጋዎችን ለማግኘት ስንል የሚጠይቀንን ዋጋ ለመክፈል እራሳችንን ማሰናዳት አለብን።
👱🏼‍♂️🧕🏼ወጣት ወንዶችና ሴቶች የምታውቁት የሚመስላቹ የወላጆቻቹ ቤት የማታውቁት መሆኑን ትዳር ይዛችሁ ስትወጡና የምትከፍሉት ነገር ሲበዛ ነው የምትገረሙት።
👱🏼‍♂️🧕🏼ህይወት በተለያየ አጋጣጠሚ ብዙ ዜናዎች ይዛለች ባል ይታሰራል፣ሚስት ትታመማለች፣ልጆች ባልተለመደ ሁኔታ ሊፈጠሩ ይችላሉ፣ ገንዘብ በጣም ሊቸግር ይችላል፣ ከባል/ሚስት ቤተሰቦች መጣላትና መሻከር ይከሰታል፡ እነዚህና መሰል  አጋጣሚዎች ሲከሰቱ የሚጠይቁት ዋጋ ከፍ ሊል ይችላል፡ አልፈልግምና አልችልም ብሎ መሄድ  ተገቢ አይደለም።ዘላቂ ጥቅማችንንም አያስከብርም፡ የሚቻለውን ያህልለ ዋጋ ከፍሎ ቤቱን ማስቀጠልና የአላህን እገዛ መጠየቅ ነው የሚሻለው፡፡
🤚🏼ልዮነትን መቀበል
🔸አላህ እንዲህ ብሏል፡፡ “ጌታህም ቢሻ ኖሮ ሰዎችን ሁሉ አንድ ህዝብ ባደረጋቸው ነበር፡፡ የተለያዩም ከመሆን አይወገዱም፤ ጌታ ያዘነለት ብቻ ሲቀር፤ (ከመለያየት አይወገዱም) 11፤-118-119
🔸ልዩነት አላህ በፍጥረተ አለሙ ላይ ያኖረው ህጉ ነው፡፡ ህይወትም ያለ ልዩነት መሣል ፈፅሞ የማይሆን ነገር ነው፡፡ “ልዩነት የሚባል ነገር ከጠፋ ሁለትነትም አብሮ ይጠፋል”
•ባልና ሚስት የሚለያዩበት ጉዳይ ቁጥር ስፍር የለውም ነገር ግን አብረው እንዲኖሩ ነው የተሰሩት በጣም የሚፈላለጉ ግና በጣም የሚለያዩ ፍጡሮችን
🔸ከአካላዊ እስከ ስነልቦናዊ አወቃቀር ከፍተኛ ልዩነት አላቸው፡፡ ለተለያዩ የእለተለት ጉዳዮቻችን እንኳ ያለን ምልከታ ከፍተኛ ልዩነት አለው፡ በቋንቋችን ውስጥ የምንፈጥረው ትርጉም በጣም ይለያያል፡ እናም ወንድ ወንድ ነው ሴትም ሴት ናት፡ ይህ ታውቆ ነው ጥምረቱ መፈቀድ ያለበት።
👱🏼‍♂️🧕🏼ስለሆነም ተጋቢዎች ማድረግ ካለባቸው ስነልቦናዊ ዝግጅት አንዱ ተጣማሪን ወገን ባለበት ሁኔታ መቀበል ነው፡፡ ከዚያም በጊዜ ሒደት ለመቀራረብና ለመረዳዳት በጋራ መጣር ይኖርባቸዋል፡፡
🤚🏼ልዩነትን መቀበል
👱🏼‍♂️🧕🏼በሁሉም ነገር (100%) የሚስማሙ ባልና ሚስት በአለም ላይ አይገኙም 60% የሚስማሙ ከሆነ ጥሩ ተቀባይነት ያለው ደረጃ ነው፡፡ 50% ከሆነ የስምምነት መጠኑ ይህም ጥሩ ነው፡፡ 70% የሚደርሰው አልፎ አልፎ ነው፡፡ ስለሆነም መረዳዳት እንጂ አንዱ ሌላውን መምሰል ፈጽሞ የማይቻል ነገር ነው።

ለጎጆዬ

01 Sep, 13:03


👱🏼‍♂️🧕🏼በእርግጥ አብሮ በመቆየትና በሒደት ግን የመቀራረብ እድላቸው እየጨመረ ይመጣል አንዱ ሌላውን መረዳትና መግባባቱ እያደገ ሲሄድ የልዩነት ነጥቦች ደግሞ እየጠበቡና እያነሱ ይሔዳሉ፡፡ የትዳር ተጣማሪን ባለበት ሁኔታ ተቀብሎ ለመኖር እራስን ማዘጋጀት ብልህነት ነው፡፡ የሚመሰረተው ቤት ከአደጋ ለመከላከል እጅግ ስለሚረዳው::
👱🏼‍♂️🧕🏼አንዳንድ ጥናቶች ባልና ሚስት ረዘም ላለ ጊዜ አብረው ከመኖራቸው የተነሳ ብዙ ነገራቸው እየተመሣሠለ ሄዶ በመጨረሻም አካሔዳቸውና ቁመናቸው ጭምር እንደሚመሣሰል ይገልፃሉ፡፡
•“ባልና ሚስት ከአንድ ወንዝ ይቀዳሉ” ማለትም ይኸው ነው፡፡
👱🏼‍♂️🧕🏼ስለባልና ሚስት ልዩነት ወደፊት በተለያዩ ርእሰጉዳዮቻችን እየተመላለስን ግንዛቤ ለመፍጠር የቻልነውን ያህል ስለምንሞክር ለጊዜው እዚህ ላይ እናቁም።
በኡስታዝ አብዱልገፋር ሸሪፍ
ሚንበር ቲቪ ዘወትር ማክሰኞ
ምሽት 2:30-3:30
 

ለጎጆዬ

30 Aug, 06:11


በኡስታዝ አብዱልገፋር ሸሪፍ
ሚንበር ቲቪ ዘወትር ማክሰኞ
ምሽት 2:30-3:30

ለጎጆዬ

30 Aug, 06:10


በአላህ ስም እጅግ አዛኝ ሩህሩህ በሆነው
ለትዳር መመስረት ሊኖር የሚገቡ
ስነልቦናዊ ዝግጅቶች
ክፍል (1)
መግቢያ
 🧕🏼👱🏼‍♂️አንድ ግለሠብ ደስተኛ፣ ሠላማዊ፣ ፍቅር የሠፈነበት፣ እርስ በርስ መከባበርና መተዛዘን የሰፈነበት ቤት ለመመስረት ጉዞ ሲጀምር የሚያስፈልጉት በርካታ ዝግጅቶች ያሉት መሆኑን መረዳት አለበት፡፡
🚶🏻‍♂️ማንም ሰው እንደሚጉዋዝበት ጉዳይ የመንገዱ ርቀትና መሰል ጉዳዮች ልክ ቅድመ ዝግጅት ያደርጋል።
•ይህም የሰዎች ልምድ ሆኖ የትኛውም አይነት ጉዞ በተለይ አካላዊና መንፈሣዊ ዝግጅቶች ይደረጉበታል፣ጉዞው ለጉብኝት፣ ለስራ፣ ለዳዕዋ፣ ለጦርነት ወይም ትግል ለትምህርት (ለመማር/ለማስተማር/ ሊሆን ይችላል፡፡
•ለዚህም ጉዞው ይረዳው ዘንድ ቁሣዊና ስነልቦናዊ ዝግጅት ማድረጉ አይቀርም ሁሉም የህይወት ዘርፎችም እንዲሁ ናቸው፡፡
•በዚሁ አግባብ ወደ ትዳር የሚጓዝ ማንኛውም ግለሰብ ቁሣዊ፣ አካላዊና፣ ስነልቦናዊ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አለበት፡፡ ይህ የጥምረት ህይወት ረጅምና ውስጡ በርካታ ውጣውረዶች ሊገጥሙት እንደሚችል ከግንዛቤ መግባት አለበት፡፡
•ለዛሬ ሥነልቦናዊውን ዝግጅት ትኩረት አድርገን ብንመካከር ጥሩ ነው፡፡
🤔በዚህ ርእሰ ጉዳይ ስንመካከር አላማው ማስፈራራት ወይም ትዳርን ማወሳሰብ አይደለም።ተቁዋሙ ሊደረግለት የሚገባውን ዝግጅት በማስታወስ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ወደ ትዳር ሲያቀኑ ሊያደርጉት የሚገባን ቅድመ ጥንቃቄና ከአሁኑ ለትዳራቸው መሳካት ማድረግ ያለባቸውን ጥረትና ኢንቨስተመንት ለማስታወስ ነው፡፡
👏🏼ስኬታማ ቤተሰባዊ ህይወት እንዲሁ ዝም ብሎ የሚከሰት ወይም በእድል የሚገኝ ሳይሆን  በቂ ቅድመ ዝገጅት የሚፈልግ፣በእውቀት፣በእቅድና ፕሮግራም ተመርቶ የሚጉዋዝ ጠንካራ ስራ የሚፈልግ መሆኑን በጊዜ ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡
👇🏼ስለሆነም ከዚህ በታች ለትዳር በመንደርደር ላይ ለሆኑ እህት ወንድሞች ትኩረት አድርገው ሊዘጋጁባቸው የሚገቡ ወሳኝ ነጥቦችን እናነሳለን፡፡ ቀድሞውኑ በትዳር ውስጥ ያለን ሰዎች ደግሞ አሁንም የቀረንን ጊዜ ደስ ብሎን እንድናሳልፈው ከሚጠቀሱት ባህሪያት አንጻር እራሳችንን ገምግመን ማስተካከል ያለብን ነገር ካለ ብንሞክር ለውጥ ማግኘት እንችላለን በአላህ ፍቃድ፡፡ 🤚🏼1. ትዳር ሀላፊነትን መውሰድ ነው
•ማንኛውም ለትዳር የሚንደረደር ግለሰብ መረዳት ካለበት እውነታዎች አንዱና ዋነኛው ጫንቃው ላይ አዲስ ሃላፊነት የሚጫንበት መሆኑን ነው፡፡
👱🏼‍♂️ወንድሜ ባል በሆንክ ማግስት ስለራስህ ብቻ ሳይሆን ስለሌሎችም ህይወት ሃላፊና ተጠያቂ መሆንክን መርሳት የለብህም፡፡ የሚስትህ (ቀለቡዋ  ጤናዋ ደህንነቱዋ ስነምግባሩዋ ወዘተ)፣ የልጆችህ (ቀለባቸው፣ ጤናቸው፤ ትምህርታቸው፡ የዲናቸውና የስነምግባራቸው)  የቤት ጉዳይ (ኪራዩ፡ ደህንነቱ አመቺነቱ ወዘተ) ወዘተ ጉዳይ ቀጥታ ይመለከትሃል፡፡ ዝም ብሎ ማር እየላሱ መኖር ትዳር ውስጥ የለም
🧕🏼ሚስትም፤ በርከት ያሉ ሃላፊነቶች እንደሚጠብቅሽ ልታውቂ ግድ ነው፡ የቤቱ አስተዳደር፡ የልጆችሽ ጉዳይ፣የባልን ምቾት መጠበቅ፡ የቤቱ ሰላም ወዘተ ያልለመድሺያቸው ሃላፊነቶች ግር ብለው ይመጡብሻል፡
•ከእንግዲህ የታጠበ መልበስ፤ የበሰለ መብላት፤ በተነጠፈ መተኛት አሁን ላይኖር ነው፡ አንቺው ልትሰሪው ነው፡ ለራስሽ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም፡፡

🤚🏼ሀላፊነት
 
•በዚህ ህይወት ውስጥ ስሜታዊ ትስስር ብቻውን አይበቃም፡፡ ባይሆን የወሰድከውን ሃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት በምትችልበት ቁመና ላይ መገኘት የግድ ነው፡፡ መልዕክተኛው እንዲህ ማለታቸው ይታወቃል
•“አዋጅ ሁላችሁም ጠባቂዎች ናችሁ፤ ሃላፊነት በወሰዳችሁበትም ጉዳይ ተጠያቂዎች ናችሁ፡፡”
🤔ይህ ጉዳይ ወንዶችን ብቻ የሚመለከት አይደለም ሴቶችንም የትዳር ሃላፊነት መሸከም እንዲችሉ ማሰናዳት ያስፈልጋል፡፡
•ማፍቀርና መፈቀር ታላቅ ፀጋ ቢሆንም ትዳር የሚፈልጋቸው ሌሎች ግብዓቶች እንዳሉት መረዳት አለብን፡፡ አንድ ቤት የሚገነባው በስሜታዊው ትስስር (ፍቅር) ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ጉዳዮች አሉት በተለይ ከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት ይፈልጋል።
🤫ፍቅር ያሸንፋል እያሉ በመፎከር ብቻ ትዳር አይሰምርም፡፡ ይህ አባባል ጥልቀት የሚጎድለው ይመስለኛል፡ ምሳሌ ፡
🧕🏼ሚስት ባሏ ችግር ቢነካውና ስራ ቢበላሽበት ወይም ግራ መጋባት ቢያዋክበው ቤቷን ሳታፈርስ እንዴት ነው ይህን ፈተና የምታልፈው?
👱🏼‍♂️ባልም ሚስቱ አያርገውና በከባድ ህመም ብትያዝ ወይም ስነምግባሩዋ ቢጎረብጠው ምንድነው የሚያደርገው?  ቤተሰቦቹዋ ጋር መመለስ ነው የሚያስበው ወይስ ወድቆ ተነስቶ እንድትድንና እንድደትሻሻል በመጣር ወደ ድሮ ፍቅራቸው ለመመለስ ነው የሚያስበው???

🤚🏼ሀላፊነት
👱🏼‍♂️🧕🏼ሁለቱም ሃላፊነት ለመውሰድ ቅድመ ዝግጅት የነበራቸው (የሰለጠኑ) ከሆነ አንዱ ሌላውን ተንከባክቦ የመጣውን አስቸጋሪ አጋጣሚ ለመጋፈጥ ታጥቆ ይነሣል፡፡
❤️ይህም እንክብካቤና የአይዞህ ባይነት መንፈስ እውነተኛውንና ቤታችንን ቀጥ አርጎ የሚያቆመውን ጥልቅ ፍቅር በሌላኛው ወገን ላይ ይፈጥራል፡፡
•በኖርማል (መደበኛ) ጊዜማ ሁሉም አፍቃሪ መምሰሉን ሊያውጅ ይችላል፡፡ በጣፋጭ ቃላት ከተከሸኑ አንድ ሺ የፍቅር ቃላት በዚህ አይነት አጋጣሚዎች የሚንፀባረቁ የሃላፊነት ስሜቶች ቀልብን ይገዛሉ፡፡ በጥምረታችን ላይ ተጨማሪ ማጠናከሪያ ማህተሞች ሆነው ያገለግላሉ፡፡
 
🤚🏼ሀላፊነት
•ቀጥሎ ባለው የአላህ ቃል የሁለቱም ወገኖች ሁለት ሁለት ሃላፊነቶች እንዳለባቸው ተንፀባርቋል፡፡
👱🏼‍♂️“ወንዶች በሴቶች ላይ ቋሚዎች (አሣዳሪዎች) ናቸው፡፡ አላህ ከፊላቸውን በከፊሉ ላይ በማበላለጡና (ወንዶች) ከገንዘቦቻቸው ላይ (ለሴቶች) በመስጠታቸው ነው፡፡
🧕🏼መልካሞቹም ሴቶች (ለባሎቻቸው) ታዛዦች አላህ ባስጠበቀው ነገር ሩቅን ጠባቂዎች ናቸው፡፡”
👱🏼‍♂️በአንቀፁ እንደተጠቀሰው ወንዶቹ የበጀትና አስተዳደር ጉዳይ ሃላፊነታቸው ሲሆን
🧕🏼ሴቶች ደግሞ ቤትን ልጅንና ባልን (ባለበትም በሌለበትም) መንከባከብና መጠበቅ ሌላኛው ደግሞ ባልን በመልካም ሲያዝ መታዘዝ ሃላፊነቷ ነው፡፡
🤚🏼ሀላፊነት
👱🏼‍♂️ሚስትህን ማብቃት፡ ማሳደግ (ማስተማር ማሰልጠን)፤ በአካልም፤ በአእምሮም፡ በመንፈሳዊ ህይወቷ፤ ላይ በሙሉ ማገዝና መደገፍ አለብህ ለልጅህ ምን አይነት እናት ነው የምትመርጠው?ስገምት ንቃተ ህሊናዋ ከፍ ያለ፣በእምነቷ ላይ በቂ ግንዛቤ ያላት፣በራሷ የምትተማመን፤ ብስለት ያላት እንድትሆን የምትፈልግ ይመስለኛል ስለዚህ በነዚህ ጉዳዮች ላይ እድገት እንዲኖራት ለማገዝ ተዘጋጅ።
🧕🏼ሴቶችም እሱ አስተምሮ አግዞ  ሲያበቃሽ ለቤቱ ብርታት እንድትሆኚ እንጂ ትከሻ ለመለካካት እና አላስፈላጊ ፉክክር ውስጥ ለመግባት እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡
•የወደፊቷ ሚስትም (አሁን በትዳር ላያ ያላቹም ብትሆኑ) ባልን አግዞ ለስኬታማነቱ መትጋት፣ለልጆችሽ የተሻለ አባት እንዲሆን ነውና ጥቅሙ የጋራ ስለሆነ አስቢበት፤ በምን መንገድ ነው ላግዘውና ብቃቱ እንዲጎለብት የምረዳው ብለሽ  ብትለፊ መልካም ነው፤ ውጤቱን ታይዋለሽ፡፡
•መደጋገፍ እውነተኛ የፍቅር ስሜትን ያመጣል፡ ሃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች ደግሞ ለመፈቀር (ለመወደድ) ከፍተኛ እድል አላቸው፡
 ይቀጥላል…

ለጎጆዬ

21 Aug, 17:04


በአላህ ስም እጅግ አዛኝ ሩህሩህ በሆነው
ኢስላም ወደ ጋብቻ ያደረገው ጥሪ
ክፍል(5)
(ሁክሙ) አዝዋጅ
🔸ጋብቻን አስመልክቶ የሚኖረው ህግ (ፍርድ) እንደየግለሰቡ ነባራዊ ሁኔታ የሚለያይ ሆኗል አራት አይነት ፍርድ (ስርዓት) የሚያርፍበት ይሆናል፡፡ እነሱም ግዴታ፣ ሱና (የተወደደ)፣ የተጠላ (ከረሃ)፣ ሐራም ናቸው።
🤔 ግዴታ
ነፍሱ ጋብቻን የምትፈልግ፣ ችሎታው (አቅሙ ያለው) እና ካላገባ ሐራም እሠራለሁ ብሎ ለሚፈራ ሰው ጋብቻ ግዴታ ተደርጎበታል፡፡ ችሎታ (አቅሙ) ያለው በማለት ውስጥ የተፈለገው አካላዊ፣ ስነልቦናዊና የገንዘብ አቅምን ያካትታል “እናንተ ወጣቶች የትዳርን ጣጣ ከቻላችሁ አግቡ” ብለዋል ሩሱሉ(ሰ.ዐ.ወ) ጥሪው ሁሉንም አቅም ያለው አካል ወንድም ሆነ ሴት የሚመለከት ነው።
🤔ዋጂብ
(ፈርድ) ነገር በኢስላም የህግ ሊቃውንት (ፉቀሃዕ) ዘንድ ለሰራው ሰው ሽልማት (አጅር) የሚያስገኝ ለተወው ሰው ቅጣትን የሚያስከትል ድንጋጌ ነው፡፡ ልክ እንደ ፆም (ረመዳን) ለፆመኛው አጅር አለው፡፡ ያለበቂ ምክንያት ለሚያፈጥረው ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡ ሰላትም እንዲሁ ነው ለሰገደው ያሸልማል ለተወው ያስቀጣዋል፡፡
እናም ነፍሱ ለፈለገች (ለጓጓች) ፀያፍን ለፈራ (ካላገባሁ መንዳለጤ አይቀርም ብሎ ለፈራ ማለት) ነው አቅም ያለው ሆኖ ከተገኘ በሱ ላይ ጋብቻ ዋጅብ ወይም ግዴታ ይሆንበታል፡፡ ከተወው ወንጀል ይሆንበታል “ያላገቡትን ከናንተ መካከል አጋቡዋቸው፡… አንኪሁ (አጋቡ) የሚለው ትዕዛዛዊ ዓረፍተ ነገር ነው፡፡ የሚያናግረውም በተለይ ወላጆችን ሲሆን የሚመለከታቸው ባለስልጣናትም (ቢኖሩን) ይካተታሉ ባገሩ የሚኖሩ ተደማጭነት ያላቸው ሰዎች ሃብታሞች፣ ታላላቆች ሁሉም በቻለው ልክ ወጣት ወንዶችንና ሴቶችን አቅማቸው የፈቀደውን እንዲያጋቡ ታዘዋል፡፡ በሌላ በኩል ወጣቱ በራሱ ላይ ፊትናን ይፈራል የአቅም ውስንነት አለበት የሚረዳው አካል አላገኘም እራሱን መጠበቅ ብቻ ነው፡፡ የሚችለው ይታገስ “የኒካህን ጣጣ መሸፈን የማይችሉ ይጠበቁ…
አላህ ከችሮታው እስኪያብቃቃቸው ድረስ እስከዚያም በፆም ላይ ይበርታ (ያዘውትር) አብደላ ኢብኑ መስዑድ እንዳወሩት ከረሱሉ ዙሪያ እንኖር ነበር ለጋብቻ የሚሆንም ምንም ገንዘብ አልነበረንም እንዲህ አሉን “እናንተ ወጣቶች ከናንተ መሀል የትዳርን ጣጣ የሚችል ያግባ አይንን ለመስበርና ብልትን ለመጠበቅ ይረዳናልና የሚልችል ሰው ፆምን ያዘውትር እርሱ የፍትህወት ፍላጎትን ይቀንሳልና አላህም እንዲ ብሏል፡ “ሴቶች ባሮቻችሁን መጠበቅን ቢፈልጉ የቅርቢቱን ህይወት ጥቅም ለመፈለግ ብላችሁ በዝሙት ላይ አታስገድዷቸው፡፡ የሚያስገድዳቸውም ሰው አላህ ከመገደዳቸው በኋላ (ለተገደዱት) መሀሪ አዛኝ ነው፡፡” ኑር 33 እዚህ ጋር መልዕክቴ ማንኛውም አባት ወይም እናት ለሴት ልጃቸው የሚመጥናት ሰው መጥቶ ሲጠይቃቸው የግል ጥቅማቸውን (ገንዘብን) ምክንያት አድርገው የሚመልሱ ከሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ልጆቹን ለዝሙት እያበረታቱ መሆኑን ይገንዘቡ፡፡ በእርግጥ ዛሬ ላይ ስንት የዚህ አይነት ቤተሰብ እንዳለ ባላውቅም አልፎ አልፎ ቢሆንም አይጠፋምና መጠንቀቅ መልካም ነው፡፡ሐርም በጣም ቀሎና ተመቻችቶ ባለበት ሁኔታ ሀላልን ማወሳሰብ ለሀራም በር እንደመክፈት ስለሆነ ቢታሰብበት ለማለት እወዳለሁ፡፡ በቲርሚዚ ዘገባም ረሱሉ(ሰ.ዐ.ወ) “አሊይ ሆይ 3 ነገሮችን አታዘግይ ሰላት ወቅቷ ከደረሰ፣ ጀናዛም ከቀረበ(ከተሰናዳ) እና ለላጤዋ እኩያዋ ከመጣላት” ፈጥኖ መፈፀም ከሚገቡ ተግባራት ናቸው፡፡
😀 ሱና (ተወዳጅ)
ነፍሱ ለምትፈልግና አቅሙ ለቻለ ሆኖም ዚና ላይ እወድቃለሁ ብሎ ለማይሰጋ ሰው ጋብቻ ተወዳጅ (ሱና) ይሆንለታል፡፡ ሱና (ተወዳጅ ስራ) በአሊሞቹ ዘንድ ለሰራው ሰው ምንዳ (አጅር) የሚያስገኝ ሲሆን የተወውን ሰው አያስቀጣም፡፡ ልክ እንደ ሱና ሰላትና ፆሞች ነው፡፡ ለሰገዳቸውና ለፆማቸው ሰው ከአላህ ዘንድ ትሩፋትን ያስገኛሉ ላልሰራ ሰው ኸይር አመለጠው እንጂ ወቀሳ አይኖርበትም ነፍሱ ፈላጊ ሆና አቅሙም እያለው ዚና ላይ እወድቃለሁ ብሎ ስላልፈራ ብቻ ጋብቻን ሱና ነው ብንልም መተውን ለማበረታታት አይደለም፡፡ በእርግጠኝነት ማግባቱ ካለማግባቱ ይበልጣል፡፡ ጥንድነት የፍጥረተ አለሙ ሱና መሆኑን ከዚህ ቀደም አንስተናል ለብቻ መሆንም ነገሮች ካላመቹና ከአቅም በላይ ከሆነ ነው እንጂ የሚደገፍና የሚበረታታ ተግባር ሆኖም አይደለም፡፡ ጋብቻ የሚመሰረተውም ዚና ፍራቻ ብቻ አይደለም፡፡
ከዚህ ቀደም ረሱሉ ቤት መጥተው ጠይቀው ስለሔዱ ሦስት ሰዎች ባነሳነው ሀዲስ ጋብቻ ሱናቸው እንዲሆንና ይህን ሱና (መንገድ) የሚተው ሰው ከእሳቸው መንገድ ውጭ መሆኑን ማንሣታችን አይዘነጋም፡፡ ስለሆነም የረሱል መንገድ ተከታይና የረሱሉ ወዳጆች የሆናችሁ ወጣቶች አቅማችሁን አሰባስባችሁ ብታገቡ፣ ቤተሰብ ብትመሠርቱ ይበልጥባችኋል፡፡ ከረሱሉ (ሰ.ዐ.ወ) የህይወት መንገድ ማፈንገጥም አይገባም።
🤔ከረሃ (የሚጠላበት) ሁኔታ
ጋብቻ በሚከተሉት ሁኔታዎች የማይደገፍ የማይበረታታ ወይም የተጠላ ተግባር ይሆናል፡፡ የተጣማሪውን መብት በገንዘብ፣ በጤና ወይም በስነ ልቦና ችግሩ ምክንያት ማሟላት የማይችል ሰው ጋብቻ አይወደድለትም፡፡(ወል የስታእፊፊለዚነ ላየጂዱና ኒካሃን ሀታ ዩግኒየሁሙላህ)ሌላ ሰው ያጫትን ሴት ለማጨት መሔድም የተጠላ ነው “ከእናንተ አንዳችሁ ወንድሙ ያጫትን ሴት እንዳጫት (ተደርቦ)” ብለዋል መልዕክተኛው፡፡ በዚህ ሁኔታ ያገባ ሰው ጋብቻው መክሩህ (የተጠላ) ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ጉዳይ የኪላፍ አጅንዳ ነው ሀራም ነው ከራሃ በሚለው፡፡ ይህ በወንድማማቾች መካከል ቅራኔ አልፎም ብጥብጥ ሊከስት የሚችልና ማህበራዊ ትስስርን የሚበጣጥስ ተግባር በመሆኑ ተገቢ አይደለም፡፡አንዲት ሴት ታሪክ ጓደኛዋን ይህ ሰው በዲኑ ጥሩ አይደለም አታግቢው ብላት ለራሷ አገባቺው ምነው እንዴት እንዲህ ታደርጊያለሽ ስትላት የወላጅ ትእዛዝ ሆኖብኝ ነው ብላት እርፍ።
ሌላም እገሊትን ለምንልኝ ብሎት ሽምግልና ይልከዋል እሱም ሄዶ ለራሱ ለምኖና ኒካህ አስሮ ምልስ ምን አሉህ እገልዬ ልጅቷ አንተን ከሆነ እሺ ስትል እኔም በቃ ይሁን ብዩ ኒካህ ለራሴ አስሬ መጣሁ፤ አለው፡፡ ሙጊራ ኢብኑ ሹዕባ (ከአረብ ስማርቶች አንዱ ነበር) እንዲህ ሆንኩ ብሎ የራሱን አጋጣሚ ይተርካል “ሰዎች በሃሳብ በልጠውኝ አያውቁም ነበር አንድ ከቁረይሽ የሆነ ወጣት ሲቀር አንዲት ቆንጆ ልጅን ላገባት ፈልጌ አማከርኩት፤ ኧረ አትሆንህም እኔ አንድ ወንድ ሲስማት አይቻለሁ አለኝ፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እዚያው ወጣት ቤት ለሰርግ ተጠራና ያቺን ልጅ አግብቷት ያያል፡፡ ሙጊራም እንዴት እንዲህ ታደርጋለህ ለኔ ያልከኝ ብለህ ይለዋል አዎ አባቷ ሲስማት አይቻለሁ አለና አረፈው።ብዙ ታሪኮች ብናወራ እህቷን ለመጉዳት ማግባት፣ ጓደኛዋና አግብቼ ላበሳጫት ተብሎ ማግባትም የሚጠላ ነው።
🔸 አታሎ (ሸውዶ) ማግባት

ለጎጆዬ

21 Aug, 17:04


ከሁለት አንዱን አታሎ ኒካህ እንዲታሰር ማድረግ ለምሳሌ ቤቱ የኔ ነው ይላል ኋላ ተከራይ ሆኖ ይገኛል፡፡ ከዚህ ዩኒቨርሲቲ ተመርቂያለሁ ትላለች ከዚያም ውሸት መሆኑ ሲታወቅ ይህ አይነቱ ስታይል ተገቢ አይደለም፡፡እራስን ክቦ አጋኖ ማቅረብና ኋላ ሲታወቅ ከማፈር እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር ይሻላል፡፡
😲ሀራም (እርም) የሚሆነው
ሚስቱን (ባሏን እንደሚበድል እርግጠኛ ለሆነ ሰው ጋብቻ ሀራም ነው፡፡ ሀራም እንደሚታወቀው የሰራ ሰው የሚቀጣበት የተወው ሰው የሚሸለምበት አግባብ ነው፡፡ ተጣማሪውን በተለያየ ሁኔታ እንደሚበድል ያረጋገጠ ሰው ለምሳሌ ቀለብ ባለመስፈር አዛ እንደሚያደርግ እያወቀ፣ ባለበት አካላዊም ሆነ ስነልቦናዊ ችግር ተራክቦ መፈፀም እንዳለበት እያወቀ(ቀች) ጋብቻን መፈፀም ክልክል ነው፡፡ ከስግብግብነቱ ብዛት ሚስቱን ቀለብና አስፈላጊ ነገሮችን ባለማሟላት የሚቀጣ መሆኑ ለታወቀ ሰው ልጁን መስጠት ክልክል ነው።
ይህ ኢስላማዊው የሸርዓ ህግ ያስቀመጠው ስርዓት ነው፡፡ ተጨማሪ ማብራሪያ የፈለገ ሰው ዝርዝር ከሚያቀርቡ የፊቅህ ኪታቦች ወይም አሊሞች ዘንድ መሔድና ማግኘት ይችላል፡፡ በግሌ ግን ጋብቻን የሚስትን ያልወደድነውን ባህሪ ለመግራት፣ ለመበቀል (የልጅቷን ህይወት) ለማበላሸት፣ ሆነ ዱንያዊ ጥቅም ተጠቅሞ ለመውጣት (የተወሰነ ገንዘብ ቦጭቆ ለመፍታት) ወዘተ… በሆኑ መጥፎ ኒያዎች ጋብቻን መመስረት ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ውጭ ለመድረስ ብቻ ዲያስፖራ ስለሆነ ተስማምቶ እዚያ ስደርስ ወይም ከትንሽ ጊዜ በኋላ ፈትቼው የራሴን ኑሮ እኖራለሁ ብሎ ማግባትም ነውር ነው፤ ይህ ለሙተዓ የቀረበ በመሆኑም ተቀባይነት የለውም፡፡ ነግ በኔን ማሰብ ጥሩ ነው በራስህ ላይ እንዲሰራ የማትፈልገውን ክፋት በሌሎች ላይ አትሰራ ሲደርስብህ መፅናኛ አታገኝም፡፡
🔸 ከላይ ባሳለፍነውም ይህን በሌላ ምክንያት ፆታዊ ግንኙነት ማድረግ የማይችል ሆና ሳለ ኒካህ ታስሮ ወደቤት ከተገባ በኋላ ከታወቀ (አንዱ ሌላውን ቀድሞ ሳያሳውቅ የገባበት ከሆነ ኒካሁን ያለ ሌላኛው ሰው ፍቃድ ለሴቷ በቃዲው ውድቅ ሊደረግላት መብት አላት። ለወንዱም መፍታት መብቱ ነው፡፡በእድሜ ልክ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ነግረው ቢገቡበት መልካም ነው ከገቡ በኋላ ከመነታረክና ከመራበሽ ቀድሞ አሳውቆ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ከሆነ ችግር የለም፡፡ ነገር ግን ተደብቆ (ከሁለት አንዱ) ከኒካሁ በኋላ ከታወቀ በፍርድ ቤት ኒካሁ ይቀደዳል ቅጣት ሊጣልበት ይችላል ማለት ነው፡፡ይህ ክፍል ተጠናቀቀ🙏
በኡስታዝ አብዱልገፋር ሸሪፍ
ሚንበር ቲቪ ዘወትር ማክሰኞ
ምሽት 2:30–3:30

ለጎጆዬ

16 Aug, 07:35


በአላህ ስም እጅግ አዛኝ ሩህሩህ በሆነው
ኢስላም ወደ ጋብቻ ያደረገው ጥሪ
ክፍል(4)
🔸እስልምና ተፈጥሯዊውን የፍትወት ፍላጎት ከሥጋዊው መንገድ ውጭ ላረከ ሰው ከባድ ቅጣትን (ግርፋት/ግድያ) በዱንያ ላይ ደንግጓል፡፡ ውሸታሞችን መቅጣት ለእውነተኞች ማበረታቻ ነው ሰነፎችን መቅጣት ለስራ ለማበረታታት ነው ከትዳር ውጭ የሚማግጡ ሰዎችን ከባድ ቅጣት ሲቀጣ ጨዋዎችን ወደ ትዳር ለመጣራትና በማበረታታት ነው፡፡
🔸የትዳርን ጣጣ (መህርን) ቀለል በማድረግ ኢስላም ጋብቻን አበረታቷል አቅም ያላቸውን ሰዎችም ማግባት የሚፈልጉ እህት ወንድሞችን እንዲረዱ ጥሪ አድርጓል፡፡ እንግዲህ ወጣቶቻችን ከጋብቻ መራቅ ምን ያመጣል ማንስ ነው ተጠያቂው?በአንድ በፓሪስ (የሚገኝ የጥናት ተቋም) በተደረገ ጥናት የወጣቶች ከህጋዊ የጋብቻ ማዕቀፍ መራቅ በተለይ በአውሮፓ ብልግና እንዲስፋፋ፣ እራስን ማጥፋት፣ የስነ ልቦና ቀውሶች እንዲበራከቱ፤ስርዓት የለቀቀ የፆታ ልቅነት (ሹዙዝ) እንዲበራከት የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ማነስ፣ ወዘተ.. ጣጣ በማምጣት አውሮፓን አሮጌው (አሮጊቷ) አህጉር አስብሏል፡፡ይህን ካስተዋሉ በኋላ አሁን አሁን ድምፆች መሰማት ጀምረዋል አግቡ ተጋቡ የሚሉ አንዳንድ ቆጠራዎች የተወሰኑ ሀገራት በዚሁ ሂደት ከቀጠሉ ከህዝብ ማነስ ምክንያት ሊጠፉ (ሊወድቁ) እንደሚችሉ ተፈርቷል።
🤔ዛሬ ላይ የሚኖረው ህዝባቸው እየሞተ ስለማይተካ መሬት፣ ህንፃ፣ ፋብሪካ፤ መኪና አውሮፕላን ገንዘብ ወዘተ ያለበት ግና ሰው የሌለበት ምድር እንዳይሆኑ ያስፈራቸዋል ወጣቶች ከትዳር የሸሹበትና ቤተሰብ የፈረሰበት ማህበረሰብ መሆናቸውን አምነው አንዳንዶቹ ስለቤተሰበ ጠቀሜታ የሚያስተምር ኮሌጅ ከፍተዋል።በተጨማሪም ቤተሰብን ለማበረታታትና ለመደገፍ የሚሰራ የሚያስተምር እና ቤተሰቦችን እንዲያጠናክር ሚኒስቴር መስሪያ ቤትም አቋቁመዋል፡፡ (የቤተሰብ ሚኒስቴር) እንደ ጀርመን ባለ ሀገር “በአንድ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የቤተሰብ ታሪክ መምህር የሆነች አንዲት ምሁር “ወጣቶቻችን ለትዳር ማበረታታትና ቤተሰብ እንዲመሰርቱ ማስገደድ አለብን አሁን ቤተሰብ መመስረታቸው ግድ ሆኗልና” ብላለች፡፡ እንግዲህ ትዳርን በግዳጅ የሚል ማህበረሰብ መፍጠሩ አግራሞትን ይጭራል፡፡ እንዲፈርስ ሲሰሩ ከከረሙ በኋላ🤔ይቀጥላል…
በኡስታዝ አብዱልገፋር ሸሪፍ
ሚንበር ቲቪ ዘወትር ማክሰኞ
ምሽት 2:30–3:30

ለጎጆዬ

12 Aug, 18:46


በአላህ ስም እጅግ አዛኝ ሩህሩህ በሆነው
ኢስላም ወደ ጋብቻ ያደረገው ጥሪ
ክፍል(3)
🔸 የረሱሉን ሱና ተግባራዊ በማድረግ
የሚገኝ አጅር
አነስ በዘገቡት ሀዲስ “ሦስት ሰዎች ወደ ነቢዩ ሚስቶች (ቤት) በመምጣት ስለ ኢባዳቸው ጠየቁ ሲነገራቸው ጊዜ እንደማሳነስ አሉና ከዚያም የት ነን እሳቸውን እንደሆነ ያለፈውንም የወደፊቱንም ስህተት አላህ ምሯቸዋል፡፡ ስለዚህ ተባባሉ አንዱ እኔ የለይል ሰላት ለሁሌውም እሰግዳለሁ፤ ሌላኛው እድሜ ልኬን እፆማለሁ አላፈጥርም ሦስተኛው ደግሞ ሴቶችን እርቃለሁ፡፡ ለዘላለሜ አላገባም አለ፡፡ ረሱሉም(ሰ.ዐ.ወ) መጡና እናንተ ናችሁ እንዲህ እንዲህ ያላችሁት እኔ ግን በአላህ ይሁንብኝ ከሁላችሁም በላይ አላህን የምፈራውና የምጠነቀቅ ነኝ ነገር ግን እፆማለሁ አፈጥራለሁ፤ እሰግዳለሁ እተኛለሁ ሴትም (ሚስትም) አገባለሁ፤ (ይህ መንገዴ ነው) ከኔ መንገድ ያፈነገጠ ከኔ አይደለም፡፡ አሉ፡፡ ስለዚህ ያለ በቂ ምክንያት ከጋብቻ እራሱን ያገለለ ሰው ከነቢ መንገድ አግልሏል፡፡ የመልክተኛውን መንገድ ተቃርኗል፡፡ በተቃራኒው ለፍቶ ጥሮ ግሮ ቤተሰብ ለመመስረት የሚታገለው ሰው ግን የእሳቸውን ተከትሏል ፈለጋቸውን በህይወቱ በሙሉ ፈፅሟል።
🔸አላህን በመታዘዝ መረዳዳት ያስገኛል
ላጤ ጎረቤቱን ጓደኛውን ወይም ወንድሙን በኢባዳ ላይ ላያግዘው ይችላል፡፡ ነገር ግን የሚያግዛት ወይም የምታግዘው ሲያገባ (ስታገባ) ይህን ደረጃ ያገኛሉ፡፡ ካልሆነ አያገኘውም ሚስትም እንደዛው አባሁረይራ በዘገቡት ሀዲስ ረሱሉ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል “ሰውዬው (ባል) ከሌሊቱ ክፍለ ጊዜ ተነስቶ ለራሱ ሰግዶ ሚስቱንም የቀሰቀሰ እንደሆነ እምቢም ካለች ውሃ ረጭቶ ከቀሰቀሳት አላህ ይዘንለት፡፡ ሚስትም ለራሷ ተነስታ ሰግዳ እሱንም የቀሰቀሰች እምቢም ካለ ውሃ ረጭታ የቀሰቀሰችው ከሆነ አላህ ይዘንላት” ይህ እንግዲህ የትዳር አጋሩን አላህን በመታዘዝ ላይ ለሚረዳ ሰው ከመልዕክተኛው የተደረገለት ዱዓ ነው፡፡ ከኛ መሀል ከወንድሞቻችን በሌለበት ዱዓ አርግልኝ የሚል ሰው ብዙ ነው ከአላህ መልዕክተኛ ሲሆን ግሩም ነው በእርግጥ ከሳቸው በላይ ዱዓ ሊያደርግልን የምንፈልገው ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡
🔸ልጆችን ገርቶ የማሣደግ አጅር
ይህ አጅር አግብቶ ላልወለደ ሰው አይገኝም “የረሱሉን አዝወትሮ በመጠባበቅ የሚታወቅ አለም ነበር፡፡ እንዲህ ይል ነበር ከረሱሉ ሱና አንዱ አምልጦኛል እሳቸው ከሀሰንና ሁሴን ጋር ይጫወቱ ነበር በጀርባቸውም ያስጋልቧቸዋል እኔ ልጅ አልተሰጠኝምና ይህን ሱና መተግበር ሳልችል ቀረሁ ይል ነበር፡፡ አቢ ሰዒዲኒልኹድሪ እንዳወሩት ረሱሉ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲ ብለዋል “ሶስት ሴት ልጆችን በስርዓት አሳድጎ የዳረና ለነርሱ መልካምን የዋለ ሰው (አባትና እናትን የሚመለከት ነው) ለርሱ ጀነት ተገባው (አለለት) “እነዚህን ሴት ልጆች በመልካም ያሳደገና በጎ የዋለላቸው ለሱ ከእሳት ግርዶ ይሆኑለታል የአንድ ሙስሊም የትግሉ ጥግ ከእሳት አምልጦ ጀነት መግባት መሆኑ አይዘነጋም፡፡ እናም አግብቶ የወለዳቸውን በአላህ ህግና ስርዓት አሣድጎ ለቁም ነገር ሲያበቃ ከጀሀነም ግርዶውን አሰናዳ ማለት ነው፡፡
🧕 ሴቶች በተለይ ባልን በመታዘዝ
የምታገኙት አጅር
አንዲት ሴት ከወንጀል በመለስ ያለን የባሏን ትዕዛዝ ስትፈፅም የአላህን ውዴታ ትሸምታለች፡፡ ረሰሉ (ሰ.ዐ.ወ) “የትኛዋም ሴት ባሏ በሷ ረክቶባት (እየተደሰተባት) ከሞተች ጀነት ገባች” አሉ፡፡ በሌላ ዘገባም “አንዲት ሴት አምስት ወቅት ሰላቷን ከሰገደች፣ ወሯን (ረመዳንን) ከፆመች፣ ብልቷን (ከሃራም) ከጠበቀች፣ ባሏን ከታዘዘች የጌታዋን ጀነት ገባች” ብለዋል፡፡ ይቀጥላል…
በኡስታዝ አብዱልገፋር ሸሪፍ
ሚንበር ቲቪ ዘወትር ማክሰኞ
ምሽት 2:30–3:30

ለጎጆዬ

10 Aug, 10:56


በአላህ ስም እጅግ አዛኝ ሩህሩህ በሆነው
ኢስላም ወደ ጋብቻ ያደረገው ጥሪ
ክፍል(2)
ጋብቻ በቁርአንና በሱና
1. ቁርዓን ስለ ቤተሰብ ህግና ስርዓትን አስመልክቶ በልዩ ትኩረት አስተናግዶታል፡፡ ባጠቃላይ 146 አንቀፆችን ስለቤተሰብ፣ ጋብቻ(ትዳር)፣ ስለ አባት፣ እናት፣ ልጆች፣ አስቤዛ፣ ጡት ማጥባት ወዘተ… ሰፋ ያለ መመሪያ ሰጥቷል፡፡
🔸የአላህ መልዕክተኛ በበርካታ ዘገባዎች ስለዚሁ ጉዳይ በዝርዝር ስለመናገራቸው ተዘግቧል፡፡
🔸የኢስላም የህግ (ፊቅህ) ትምህርት ክፍልም ከጠቅላላው የፊቅህ ዝርዝር ትምህርት 1/5ኛውን በዚህ ርዕሰ-ጉዳይ በማድረግ ጥልቅና ዝርዝር ትንታኔ ተሰጥቶበታል በተለይም ስለ ማጨት፣ ኒካህ፣ የባልና ሚስት መብትና ግዴታዎች የልጆች መብትና ግዴታዎች የፍች ህግና ተያያዥ ስነ ስርዓቶች፣ የገንዘብ አያያዝና የአስቤዛ ጉዳይ የውርስ ክፍፍል ጉዳይ በዝርዝርና በተደራጀ መልኩ ተሰርቷል፡፡
🔸የዚህ ሁሉ የእውቀት ክምችት በዚህ ጉዳይ ላይ መኖሩ ባጠቃላይ ኢስላም ለቤተሰብ የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት ሚያሣይ ነው፡፡
🔸ጋብቻ ምን ያህል ክቡርና ቅዱስ መሆኑን ከማስገንዘቡም በላይ እንዴት የተበረታታ መልካም ባህል (ነገር) መሆኑንም ያስረዳናል፡፡
2. ሌላው ኢስላም ለተጋቢዎች በርካታ ሽልማቶችን (አጅር) ያዘጋጀበት ስረአትም ሳቢ ነው፡፡
🔸በሸሪዓችን የሚፈፀሙ በርካታ ተግባራት በጥንዶች (ባለትዳሮች) እንጂ አይፈፀሙም፡፡አጅራቸውም ለነሱ እንጂ ለላጤዎች አይገኝም ስለሆነም ላጤዎቻችን (ወጣቶቻችን) ቀጥሎ የተዘረዘሩትን አጅሮች ባያገኙም ኢንሻአላህ ሌሎች የኸይር ደጃፎችን እንደማያጡ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ባለትዳሮችን የሚጠብቃቸውን አጅር በከፊልም ቢሆን እንመልከት
🤔 ሚስትንና ልጆችን መቀለብ
ይህ ለባለትዳሮች ብቻ የተገራ ኸይር ነው፡፡ “አንድ ብር በአላህ መንገድ ላይ ብታመጣ፣አንድ ብር ባሪያ ነፃ ለማውጣት ብታወጣ፣አንድ ዲናር ለሚስኪን ሰደቃ ብትሰጠው፣አንድ ብር ለቤተሶበችህ ብትሰጥ፡- በአጅር በላጩ በቤተሰብህ ላይ ያወጣኸው ብር ነው፡፡
🤔ለሚስትህና ልጆችህ ወጭ የምታደርገው ገንዘብ ግዴታና አጅሩም ከሁሉም በላይ እንደሆነ እንረዳለን ነገሩ ጂሃድ ላይ የሚወጣ ቢሆን እንኳ ጂሃዱን በገንዘብ መደገፍ በግለሰብ ላይ ሱና በመሆኑ ረሱሉ(ሰ.ዐ.ወ) “አንድ ሰው ለቤተሰቦቹ ወጪ ሲያደርግ ከአላህ ምንዳን አገኝበታለሁ ብሎ እያሰበ ከሆነ አላህ ዘንድ ወጪው ሰደቃ ተብሎ ይመዘገብለታል! ብለዋል፡፡
🤔ለልጆችህ ባለቤትህ ወጭ በምታደርግበት ጊዜ ይህንን ኒያ (ስሜት) በውስጥ ካኖርክ በአላህ ፈቃድ አጅርህ ተመዝግቦ መቀመጡ አይቀርም፡፡
🤔ትንሽ ቅሬታ በገባህ ቁጥርም ሃላፊነትህን ባለመወጣት (ወጭ በመቁረጥ) ቤተሰቦችህን አታንገላታም፡፡
🤔አጅሩን ካአላህ በመጠበቅ ባለቤትህ ምንም ያህል የሚያስከፋ ነገር ብታደርግም የጋብቻው ሰንሰለት እስካለ ድረስ በርሃብና ችግር አትቀጣም። 🤔ሚስትም የቤቷን ጉዳይ በመጠበቋና በስርዓት በማስተዳደሯ ምንዳን ከአላህ ትከጅላለች፡፡ይቀጥላል…
በኡሰታዝ አብዱልገፋር ሸሪፍ
ሚንበር ቲቪ ዘወትር ማክሰኞ
ምሽት 2:30–3:30

ለጎጆዬ

08 Aug, 15:42


ሊንኩን ሼር በማድረግ ተደራሽ ያድርጉ!

ለጎጆዬ ፕሮግራም ላይ የቀረቡ ሃሳቦችን እዚህ ይከታተሉ!

https://t.me/legojoye_minbertv

ለጎጆዬ

08 Aug, 14:35


በአላህ ስም እጅግ አዛኝ ሩህሩህ በሆነው
ኢስላም ወደ ጋብቻ ያደረገው ጥሪ
ክፍል(1)
መግቢያ
🔸ጋብቻ በኢስላም መለኮታዊ ስረአት ነቢያዊ ፈለግና ሰዋዊ ባህሪ ነው። ህይወት በሙስሊሞች ቤት ምሉእ የሆነ ኢባዳ (አምልኮ)፤ የነቢያትን ሱና (ፈለግ) ህያው ማድረጊያ ስፍራና የማያቋርጥ የስልጠና ማእከል ነው፡፡
🔸የአላህ ፍላጎቱና ውሳኔው ሆኖ ሰዎች በምድር ላይ ስንኖር በሴትና ወንድ የጋብቻ ጥምረት ውስጥ እንዲሆን ተደረገ፡፡ የመጀመሪያው የሰው ዘር መቀጠያ ምክንያትም የአባታችን አደምና የእናታችን ሀዋ ቤተሰብ ምስረታ ሆነ። በውስጡ በርካታ ታአምራትን የያዘው ይህ ቤተሰብ በአላህ ምስክርነት ሶስት ትላልቅ መገለጫዎችን ይዞ ይገኛል፡፡
ሰኪና መወዳና ራህማ
🔸የአላህን መኖርም ለሚጠራጠርም ሰው አይነተኛ ምልክትና ታአምር ሆኗል፡፡ ወሚን አያቲሂ፣ ለእናንተም ከነፍሶቻችሁ (ከጎሶቻችሁ) ሚስቶችን ወደ እነሱ ትረኩ ዘንድ መፍጠሩ፤ በመካከላችሁም ፍቅርንና እዝነትን ማድረጉ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው።
🔸በዚህ ውስጥ ለሚያስተውሉ ህዝቦች ወሁለዚ…እርሱም ያ ከውሃ ሰውን የፈጠረ የዝምድናና አማችም ባለቤት ያደረገው ነው።ጌታህም ቻይ ነው፡፡
🔸ህጋዊው ጋብቻ ወንድና ሴት ለብቻቸው የሚኖሩበትና ተፈጥሯዊ ስሜትን ለማርካት ብቸኛው አማራጭ ነው። በኢስላም ከዚህ ውጭ ሁሉም መንገዶች ጥፋትና ርክሰትን የሚያስከትሉ አመጾች ናቸው።ከአላህ ጋርም ያራርቃሉ። ስለሆነም ቤተሰብ መመስረት የዲን አካል ነው።
🔸ለቤተሰብ ጥበቃና ከለላ ማድረግ ከኢማን ነው።ቤተሰብን ለማፍረስና ከነጭራሹ ለማጥፋት ከዘመቱ በርካታ ፈተናዎችና መከራዎች ጋር መታገል ጂሃድ ነው።የጋብቻ ፍሬ የሆኑ ልጆችን መንከባከብና መጠበቅ የአላህን የሀይማኖት ምልክቶችን (ታእዚም ሸዓኢረላህ) ከማክበርነው።
ያ አዩሀለዚነ…እናንተ የመናችሁ ሆይ፤ ነፍሶቻችሁንና ቤተሰቦቻችሁን መቀጣጠያዋ ሰዎችና ደንጋዮች ከሆነች እሳት ጠብቁ…አንድ ሙስሊም ቤተሰብ ከዝግጅት እስከ ምሰረታው ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጠው ከዚያም አላህ ያኖረውን ኢስላማዊ ስርዓት ለመተግበር ከተቻለ እንደ አላማ ያስቀመጥነው አርአያ የሆነ ሙስሊም ማህበረሰብ ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ውጤቱም ፍቅር ፤ሰላም፤ ህብረት፤ መተሳሰብና መደጋገፍ፤ ጨዋነትና (ንጽህና) ባጠቃላይ መልካም ስነምግባር የጎላበት ስረአት ይፈጠራል፡፡
🔸ለዚህ ነው አላህ የቤተሰብን ስርዓት የዘረጋበትን መንገድ በአንክሮ እንናስተውል ዘንድ ይህ ርእስ የተዘጋጀው፡፡
🔸ከዚህ ቀጥሎ እንደመግቢያ ካነሳነው ሀሳብ በላይ ገባ ብለን ኢስላም ለቤተሰብ ምስረታ (ጋብቻ) የሰጠውን ቦታ (ትኩረት) እንመልከት።ይቀጥላል…
በኡስታዝ አብዱልገፋር ሸሪፍ
ሚንበር ቲቪ ዘወትር ማክሰኞ
ምሽት 2:30–3:30

5,100

subscribers

1

photos

8

videos