🔵 " ያለ ፍላጎት እና ያለ አግባብ 'በልማት ሰበብ' ደሞዝ ተቆርጦብናል " - የጎባ ወረዳ መምህራን
🔴 " ከነሱ ጋር ተነጋግረን የምንግባባ ከሆነ እንግባባለን፤ ካልሆነም ብራቸው ይመለሳል " - የጎባ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጽያ ክልል ጎባ ወረዳ ያሉ መምህራን ለልማት በሚል ሳቢያ " ያለ ፍላጎታችን እና አላግባብ " ደሞዝ ተቆርጦብናል በማለት ቅሬታቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አሰምተዋል።
34 ገደማ ይሆናሉ የተባሉት መምህራን በዚህ ምክንያት ስራቸውን አቁመው ከትላንት በስቲያ ተቃውሞአቸውን ለማሰማት ወደ ሚመለከተው አካል በሰልፍ እንደሄዱ የጎባ ወረዳ መምህራን ተወካይ የሆኑት መ/ር ሀብታሙ ታደሴ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
የመምህራኑ ቅሬታ ምንድነው ?
- መምህራኑ እንዲቆረጥ የተወሰነባቸው ደሞዝ በአንድ አመት ውስጥ የአንድ ወር ደሞዝ ሲሆን ደሞዛቸው ያለፍቃድ በጥቅምት መቆረጥ ተጀምሯል።
- የወረዳውን መምህራን ከአንድም ሁለቴ በዚህ ጉዳይ ተወያይተዋል ነገር ግን " በወቅቱ የኑሮ ሁኔታ ምክንያት በየወሩ ከብድር ወደ ብድር እየተሻገርን ባለንበት ወቅት ደሞዝ እንዲቆረጥ አንፈልግም " ብለው ነበር።
- " እኛ ልማት ጠል አይደለንም " ያሉት መምህራኑ " በራሳችን ፍላጎት ልማቱን እንደግፍ እንጂ በግዴታ አይደለም " ሲሉ ነው የገለጹት።
- ከዚህ ቀደም ወረዳው በዚህ ጉዳይ መምህራንን ባወያየበት ወቅት እንደ ወረዳ መምህራን የራሳችን የአቋም መግለጫ አውጥተናል ሲሉ የመምህራኑ ተወካይ መ/ር ሀብታሙ ተናግረዋል።
ተወካዩ አክለው " ወደው፣ ፈቅደው፣ ፈርመው የሰጡት መምህራን እንዲቆረጥባቸው፤ ያልተስማሙት ደግሞ መብታቸው ተከብሮ እንደፍላጎታቸው እንዲደረግ አሳውቀናል" ሲሉም አስረግጠዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ ለመምህራኑ ቅሬታ ምላሽ እንዲሰጡ የጎባ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑትን አቶ አስፋቸዉ አቱሞን አነጋግሯል።
አቶ አስፋቸው ምን አሉ ?
በወረዳው ከ400 በላይ መምህራን እንዳሉ የገለፁት አቶ አስፋቸው ወደ ሰባ ደገማ የሚሆኑት በደሞዝ ቆረጣው እንዳልተስማዉ ገልፀዋል።
" የወረዳ ልማት ተብሎ ሁሉም መንግስት ሰራተኛ ተስማምቶ እየተቆረጠባቸው ነበር " ያሉት አቶ አስፋቸው " የተወሰኑ መምህራኖች ናቸው ችግር እየፈጠሩ ያሉት " ብለዋል።
መምህራኑ የተቆረጠባቸውን ደሞዝ በተመለከተ ከሚመለከተው ክፍል ጋር መነጋገራቸውንም ያስረዱት ኃላፊው " ከነሱ ጋር ተነጋግረን የምንግባባ ከሆነ እንግባባለን፤ ካልሆነም ብራቸው ይመለሳል እንጂ ልማቱ ምንም የሚሆንበት የለም " ሲሉ ተናግረዋል።
ውሳኔውን ብቻቸውን መወሰን እንደማይችሉ የገለፁት ኃላፊው ከሌሎች የወረዳው ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚነጋገሩ አስረድተዋል።
" ከወረዳ ጋር ተነጋግረን መምህራኑ ሊስማሙ ይችላሉ። ካልተስማሙም መመለስ ይችላል " ያሉት አቶ አስፋቸው " ያን ያህል የተጨቆኑበት እኛ ያረግነው የሚካበድ አይደለም። ቀላል ነው። ትንሽም ስለሆኑም የነሱን ባንቆርጥም ልማቱን ወደ ኃላ ሊጎትት አይችልም " ሲሉ ገልፀዋል።
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia