የስነልቦና ምክሮች psychology @ethteksimyo Channel on Telegram

የስነልቦና ምክሮች psychology

@ethteksimyo


ጠቃሚ ለሂወት ወሳኝ የሆኑ ነገሮች የሚለቀቁበት ቻናል

የስነልቦና ምክሮች psychology (Amharic)

የስነልቦና ምክሮች psychology የማክሰኞ አምስት ሰአት በቀላሉ እየበላሁን ባላየዋለው መንፈሱ በላታ የአሻሻሎ ደረጃ አካሄደ ምንድን ነው? ምክሮችን ለማስመዝገብ የሚከተለው ነገር ምንድን ነው? እመስለኝ ወይም ተጨማሪ ነገር እንደሆነ የመረጡ እንደሆና - ethteksimyo ታሪካዊ ቻናሎችን እና የስለስል ልብ ወንበዴዎችን በማስከተለያየት የስነልቦና ምክሮችን ቁልፍ ባለንብቶቹ ፣ ምስል እና እንደማስነሳስ አገልግሎቶች አሉ። ከእኛ ጋር በሚያሳይ እጅ ሰጥተናል።

የስነልቦና ምክሮች psychology

13 Nov, 03:17


⬇️
ከሰዎች ጋር ባላችሁ ግንኙነት . . .

1.  ያልሆናችሁት ላይ ሳይሆን የሆናችሁት ላይ አተኩሩ፡፡

ያልሆናችሁት ላይ ስታተኩሩ የሆናችሁትን እውነተኛ ማንነት መኖር ያስቸግራችኋል፡፡ የዚህ ሁኔታ ውጤት እንዳገኛችሁት ሰው ሁኔታ ያልሆናችሁትን ማንነት እየለዋወጡ መኖር ነው፡፡

2.  የሌላችሁ ላይ ሳይሆን ያላችሁ ላይ አተኩሩ፡፡
የሌላችሁ ነገር ላይ ስታተኩሩ ያላችሁን ነገር በትክክለኛው መንገድ መጠቀም ያስቸግራችኋል፡፡ የዚህ ሁኔታ ውጤት ከሌላችሁ ነገር በመነሳት በዝቅተኝነት ስሜት የመመታት ሁኔታ ነው፡፡

3.የማታውቁት ላይ ሳይሆን የምታውቁት ላይ አተኩሩ፡፡
የማታውቁት ላይ ስታተኩሩ የምታውቁትን እውቀት ተግባራዊ ማድረግ ያስቸግራችኋል፡፡ የዚህ ሁኔታ ውጤት እውቀታችሁን ተጠቅማችሁ ከማደግ ይልቅ ስለማታውቁት ነገር በማሰብ ጊዜን መፍጀት ነው፡፡

ወሳኙና ጨዋታውን የሚለውጠው ነገር ትኩረታችሁ ነው፡፡ የሆናችሁት፣ ያላችሁና የምታውቁት ነገር ላይ ስታተኩሩና ቀና ብላችሁ በድፍረት ስትኖሩ፣ ያልሆናችሁት፣ የሌላችሁና የማታውቁት ነገር ላይ የመስራትና የማደግም እድላችሁ የሰፋ ነው፡፡

የስነልቦና ምክሮች psychology

11 Nov, 18:06


የአታላይ_ሰዎች_ምልክቶች

👉እንደ ተበዳይ ይሆናሉ
👉በዝምታ ይቀጡሃል
👉ድክመትህን አንተን ለማጥቃት ይጠቀሙበታል
👉ቀልደኞችና ሁልጊዜ ለክርክር የተዘጋጁ ናቸው
👉ተበዳዮቻቸው ላይ ይፈርዳሉ፣ ይተቻሉ
👉ስሜቶቻቸውን ወደ አንተ ያስተላልፋሉ
👉ከአንተ የሚፈልጉትን እስኪያገኙ ድረስ አያርፉም
👉ራስህን እንድትጠራጠር ያበረታቱታሃል

የስነልቦና ምክሮች psychology

18 Oct, 16:45


በአንድ ወቅት የአንድ ከተማ ገዢ ለሕዝቡ

"የሁላችሁም ጠላት የሆነ ሰው ሞቷል፤ ስለዚህ ለትምህርት እንዲሆናችሁ በሬሳ ሳጥን ውስጥ ተቀምጦላችኋል። ሁላችሁም መጥታችሁ እንድትመለከቱ።” የሚል አዋጅ አስነገረ።

‘የሁላችንም ጠላት ሊሆን የቻለው ሰው ማነው?’ በሚል ብዙ የከተማው ነዋሪ በሬሳ ሳጥን ውስጥ ያለውን ለማየት በመጓጓትና በመገረም ስሜት ወደ ቦታው ሄደ።

"የሁላችሁም ጠላት የሆነ ሰው...” የተባለውን እያዩ ከተመለሱ በኋላ ብዙዎች ባዩት ነገር የተገረሙ ሲሆን፤ አንዳንዶች ደግሞ ግራ የመጋባት ስሜት ተስተውሎባቸዋል።

ለመሆኑ ህዝቡ በሳጥን ውስጥ ያየው ምን ይመስላችኋል?

በሬሳ ሳጥን ውስጥ የተቀመጠው ሰይጣን፣ አሸባሪ፣ አደገኛ ነፍሰ ገዳይ ወይም ክፋ ሰው ሳይሆን የራስን መልክ መመልከቻ መስታወት ነበር።

ስለዚህ ሁሉም ሰው ጎንበስ ብሎ ጠላቱን ሲፈልግ የሚያየው የራሱን መልክ ነበር::

የከተማዋ ገዥ ይህን ያደረገበት ምክንያት፤ ሁሉም ሰው የራሱ ጠላት ራሱ መሆኑን ለማስተማር ነበር።

ደሴ አዳም ‘ውብ’ በሚል መጽሐፉ እንዳለው:-

"በህይወትህ ትልቁ ጠላትህ ውስጥህ ያለው መጥፎ ሀሳብ ነው ስለዚህ መጀመሪያ እሱን ታግለህ አሸንፍ ከዛ ሌላው ቀላል ነው!"

እውነት ነው! በህይወትህ ብዙ ነገሮችን ማሳካት ትችላለህ፤ እንዳይሳካልህ የሚያደርገው ነገር በውስጥህ የሚወራው አሉታዊ ወሬ ነው። ከዚህ ውጭ ሌላ የሚያግድህ ነገር የለም።

ጆሮ አትስጠው፣ ስኬትህን ይነጥቅሃል፣ ህልምህን ያዳፍነዋል። ከሰራህ፣ ከተለማመድክ፣ ከተማርክ፣ በህይወት እስካለህ ድረስ ያሰብከው ይሳካልሃል!

የውሸት ወሬ እየፈጠረ ሽባ የሚያደርግህ ይህ የውስጥ ጠላትህ ነው። ንቃበትና ታገለው። ይሸነፋል!!

ለቀልድ እንኳን ቢሆን ስለራስህ አሉታዊ ነገር አትናገር። የምትናገረው ነገር የምር ይሁን የቀልድ ድብቁ አእምሮህ አይገነዘበውም፣ እንዳለ ተቀብሎ ያምነዋል። ቃላት ደግሞ ሀይል አላቸው። በውስጥህ የተሳሳተ እምነትን ይፈጥራሉ። ራስህን የምትገልፅበትን መንገድ ስትቀይረው ደግሞ ህይወትህም ይቀየራል።

አንድ ሰው አመለካከቱ የተዛባ ከሆነ የራሱ ጠላት ነው።

“የራስህ ተጠቂ አትሁን!” ይላል ጂም ሮህን። የወረኞች፣ የወሮ በሎች፣ የምቀኞች፣ የአደጋዎች፣ እና የሌሎችም ውጫዊ ሁኔታዎች ተጠቂ ልትሆን ትችላለህ፤ የራስህ ተጠቂ ግን አትሁን። ውጫዊ አካል ሊበድልህ ይችላል። ተፅዕኖ ሊያደርስብህ ይችላል። አንተ ግን ራስህን አትበድለው።

ከኪስህ ገንዘብ የሚሰርቅህን ሌባ ትተህ ውስጥህ ላይ ተቀምጦ ህልምህን የሚያጨናግፈውንና ምኞትህን የሚያቀጭጭብህን ውስጣዊ ሌባ ታገለው።

በውስጥህ ያለው ጠላትህ፣ “ አንተኮ አቅም የለህም፣ እውቀት የለህም፣ አጭር ነህ፣ አንተኮ አታምርም፣ አንተኮ አካል ጉዳተኛ ነህ፣ አንተኮ አትችልም፣ አንተኮ እንዲያ ነህ አንተኮ እንዲህ ነህ......” እያለ ሊያንኳስስህና ዝቅ ሊያደርግህ ይታገላል።

ወይም “ይሄ ያሰብከው እቅድህ እኮ በሌላው አገር ላይ ነው እንጅ እዚህ አንተ ያለህበት አገር ላይ አይሳካም።....ወዘተ” ሊልህ ይችላል።

ይህን ጠላትህ የሆነ መጥፎ ድምፅ አትስማው። አእምሮህ ውስጥ ያለውን ጠላት ታግለህ አሸንፈው።

በሚቀጥለው የገጣሚ ሰለሞን ሞገስ ግጥም እናጠቃለው!

ጠላቴን ስፈልግ ከጎረቤቶቼ
ጠላቴን ስፈልግ ከባልደረቦቼ
ጠላቴን ስፈልግ ከሩቅ ከቅርቦቼ
ለካስ ክፉ ጠላት ደመኛዬ ያለው
ከገዛ እኔነቴ ከራሴ ውስጥ ነው !!!

የስነልቦና ምክሮች psychology

13 Oct, 14:52


ጥሩ የሚባል ሬስቶራንት ነው በአንዱ ቀን ታድያ
አንድ ሃብታም ሰው ወደዚህ ሬስቶራንት መጣ። ደምበኞችን ጠብ እርግፍ እያለ ሚያስተናግደው ወጣት አስተናጋጅ ወደ ሃብታሙ ሰው ጠጋ ብሎ ምን ልታዘዝ በማለት በሬስቶራንቱ ውስጥ የሚገኙትን ምርጥ የምግብና የመጠጥ አይነቶች በዝርዝር ይነግረዋል።

ሆኖም ግን ባለጠጸጋው ሰው ከማስታወቂያ የፈጠነውን የአስተናጋጁን ሀተታ ከቁብም ሳይቆጠረው ሳንድውች እና ሻይ ብቻ አዘዘ።

አስተናጋጁ በተወሰነ መልኩ ቅር ቢሰኝም የታዘዘውን ወዲያው ያቀርብለታል።
ሰውየውም ከጨረሰ በኋላ ሒሳቡን ጠየቀ።
አስተናጋጁም አሰርቶ ሒሳቡን አሰርቶ ሲመጣ ሃብታሙ ሰው በዓይኑ ውስጥ ሀዘን እንዳለ አስተዋለ።
ጠየቀውም “ሁሉም ነገር ደህና ? ቢለው
"ከባድ ህይወት እያሳለፍኩ ነው" አገልጋዩ መለሰ።

ከዚያም ምንም ሳያስብ ሥራውን ቀጠለ። ወደ ሃብታሙ ሰው ጠረጴዛ ሲመለስ ግን 10,000 ዶላር ከስኒው መቀመጫ ስር አገኘ።
አስተናጋጁ ልጅ ባለጸጋውን ሊደርስበት ሮጠ። ወደ መኪናው እየገባ ነበር።
እሱም “ለምን ይህን አደረግክ ? ” ሲለው
ሰውየው እንዲህ ሲል መለሰ፡- እኔም በአንተ እድሜ ሆኜ “እንደዚህ ባሉ ሬስቶራንቶች ውስጥ እሰራ ነበር። ህይወትን ለማሸነፍ ከባድ ውጣ ውረዶችን አሳልፌአለሁ ሁሉ ነገር ይገባኛል አንድ ሰው በአንድ ወቅት የኮሌጅ ክፍያዬን ሲሸፍንልኝ ለሱ ምንም ማለት ባይሆንም ለእኔ ግን ያቺ ቅፅበት ህይወቴን ለውጠዋለች። ትንሽ ቢሆንም ገንዘቡ እንደሚረዳህ ተስፋ አደርጋለሁ” ከማለቱ
ወጣቱ አስተናጋጅ ሚለውን አጥቶ ፊቱ በእንባ ራሰ

በመጨረሻም “ጌታዬ ለበሽተኛዋ እናቴ አሁን ደረስክላት። ” ብሎት ተለየው።

በማግስቱም ይህ ምስኪን ልጅ ባገኘው ገንዘብ አሳክሞበት እናቱ ከበሽታዋ ተፈወሰችለት።

ለናንተ ትንሽ የሚመስላችሁ ማንኛውም ነገር የብዙሃንን መንገድ ታቃናለችና ከልባችሁ በመስጠት ብቻ ካላችሁ በላይ ፀጋ እና በረከቱን መቀበል ትችላላችሁ።

የስነልቦና ምክሮች psychology

02 Sep, 20:05


ሶስቱ የእውቀት ደረጃዎች
• በመጀመሪያው የእውቀት ደረጃ ላይ የደረሰ ሰው ሁሉንም ነገር ያወቀ ይመስለዋል፡፡

• በሁለተኛው ደረጃ ላይ የደረሰ ሰው የማወቅ ጉጉቱ በጣም ይጨምራል፡፡

• ሶስተኛው ደረጃ ላይ የደረሰ ሰው ግን ምንም ነገር እንደማያውቅ ይረዳል፡፡

የስነልቦና ምክሮች psychology

17 Aug, 16:48


የታላላቅ ሰዎች ምርጥ አባባሎች

❖“ሰው የሚማረው አንድም በፊደል፣ አንድም በመከራ ነው፣ አንድም በሳር “ሀ” ብሎ፣ አንድም በኣሳር “ዋ” ብሎ።”
ፀጋዬ ገ/መድህን

❖ ‹‹ እውነት እርቃኑን በባዶው መራመድ ይችላል፡፡ ውሸት ግን ሁልጊዜ
አምሮና ደምቆ መልበስን ይፈልጋል፡፡ ››
ካህሊል ጂብራን

❖ "የውሸት ጓደኛና ጥላ ሁለቱም አንድ ናቸዉ። ሁለቱም የሚቆዩት ፀሐይ እስካለች ድረስ ነው።"
-ዊሊያም ሼክስፒር

❖ እምነት ባለዩት ነገር ማመን ሲሆን ሽልማቱም ያመንቱን ነገር ማየት ነው።"
-ጳጳስ ኦገስቲን

❖"ማለም የፈጠራ መነሻ ነው ፤ የምትፈልገውን ታልማለህ ፣ ያለምከውን ትመኛለህ ፤ በመጨረሻም የተመኘኸውን ትፈጥራለህ።"
-ጆርጅ በርናንድ ሾው

❖ ለመጀመር ስኬታማ መሆን አይጠበቅብህም ነገር ግን ስኬታማ ለመሆን መጀመር አለብህ ፡፡
-ዚግ ዚግላር

❖"በብርሃን ስትሆን ሁሉ ነገር ይከተልሃል:: ጨለማ ውስጥ ከሆንክ ግን ጥላህ እንኳን አይከተልህም።"
   - ሂትለር

❖"ሳንቲም ብዙ ድምፅ ያሰማል:: ገንዘብ ግን ምንም አያሰማም:: ስለዚህ ዋጋህ ሲጨምር ወሬህን እየቀነስክ ና!"
  - ዊሊያም ሼክስፒር

❖"ደሀ ሆነህ ብትወለድ ጥፋቱ ያንተ አይደለም ደሀ ሆነህ ብትሞት ግን ጥፋቱ ያንተ ነው።"
   - ቢል ጌትስ

❖“ደካሞች ይቅር ማለት አይቻላቸውም። ይቅር ባይነት የጠንካሮች ብቻ ባህርይ ነው።”
-መሀተመ ጋንዲ

❖"በምድር ላይ የማያለወጠው ነገር ቢኖር ራሱ ለውጥ ነው።"
-መሀተመ ጋንዲ

❖‹‹ ቁንጅና ያለው ፊት ላይ አይደለም፡፡ ቁንጅና በውስጣችን የሚገኝ የልብ
ብርሃን ነው፡፡ ››
ካህሊል ጂብራን

❖"በዓለም አንተ ልታየው የምትፈልገውን ለውጥ ራስህ ኹነው።አለም ላይ ሰላም ፍቅር እንዲኖር ከፈለክ አፍቃሪ እና ሰላማዊ በመሆን ከራስህ ጀምር"
-መሀተመ ጋንዲ

ሼር##

የስነልቦና ምክሮች psychology

01 Aug, 22:14


በዋናው ነገር ላይ ማተኮር!
(“ትኩረት” ከተሰኘው የዶ/ር ኢዮብ ማሞ መጽሐፍ የተወሰደ)

አንድን እጅግ በጥበብ የላቀን ሰው አገኘሁትና ባለችኝ የጋዜጠኝነት ሙያ ተጠቅሜ መጠየቅ የምችለውን ያህል ለመጠየቅ ሞከርኩ፡፡

ጠቢቡ - “ና ጠጋ በል … ጥያቄ ልትጠይቀኝ እንደፈለግህ ታስታውቃለህ” አለኝ፣ የልቤን ፍላጎት ገምቶ፡፡

እኔ - “ጊዜ ካለህ” አልኩት፡፡

ጠቢቡ (ልብን በሚሰርቅ ፈገግታ) - “ለማወቅ ለሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ጊዜ አለኝ” ብሎ መለሰልኝ፡፡

ይህ ጥበበኛ እንዴት ለሰው ሁሉ ጊዜ ሊኖረው ቻለ? እያልኩ ሳወጣና ሳወርድ በፈገግታና በትእግስት ይጠብቀኝ ነበር፡፡

እኔ፡- “ስለ ሰው ፍጥረት ከሚያስገርሙህ ነገሮች መካከል ጥቂቱን ንገረኝ” አልኩት፡፡

ጠቢቡ -

•  “ልጆች ሳሉ መሰልቸታቸውና ትልቅ ለመሆን መሮጣቸው … ካደጉ በኋላ ደግሞ ልጅ መስሎ ለመታየት መሯሯጣቸው ያስገርመኛል …

•  ገንዘብ ለማካበት ጤንነታቸውን ማጣታቸው … ጤናቸውን ለመመለስ ደግሞ እንደገና ያንኑ ገንዘብ ማፍሰሳቸው ያስደንቀኛል …

•  ስለ ነገ በመጨነቅ ዛሬን ለመኖር አለመቻላቸውና ከዛሬም ሆነ ከነገ ሳይሆኑ መንከራተታቸው ያስገርመኛል …

•  ልክ እንደማይሞት ሰው መኖራቸውና ልክ እንዳልኖረ ሰው ተጽእኖ ቢስ ሆነው መሞታቸው ያስገርመኛል፡፡

ይህን ጠቢብ ዝም ብለው ሌሎች ሃሳቦች እንደሚጨምር እየተሰማኝ በማቋረጥ፣ “ሌላ ጥያቄ ልጠይቅህ?” አልኩት፡፡

ጠቢቡ፡-
ደስ በሚያሰኝ ፈገግታ ፈቃደኝነቱን ገለጠልኝ፡፡

እኔ፡- “የሰው ልጅ ሁሉ አባት ብትሆን ለሰው ልጆች እንዲያደርጉ ከምትመክራቸው ነገሮች መካከል ጥቂቶቹን ንገረኝ” አልኩት፡፡ 

ጠቢቡ (ረዥም ጺሙን ዳበስ ዳበስ በማድረግ ካሰበ በኋላ)፡-

•  ማንም ሰው እንዲወዳቸው ማስገደድ እንደማይችሉ፣ ነገር ግን ማድረግ የሚችሉት የሚወደድ ማንነትን ማሳደግ ብቻ እንደሆነ እንዲያወቁ እመክራቸው ነበር፡፡

•  መልካም ማንነትንና የተመሰከረለት ማህበራዊ ሕይወት ለመገንባት አመታት እንደሚፈጅ፣ ለማፍረስ ግን አንድ ደቂቃ እንደሚፈጅ እንዲያውቁ አስተምራቸው ነበር፡፡

•  የሕይወታችቸውን አቅጣጫ የሚወስነው ያላቸው ንብረትና ሃብት ሳይሆን በሕይወታቸው ያስጠጓቸው የወዳጆች አይነት እንደሆነ እንዲገነዘቡ አሳስባቸው ነበር፡፡

•  ታላላቅ ሕልሞችን ለማለምና ከግባቸው ለማድረስ የሚያስፈልገው ታላቅ ሰው መሆን ሳይሆን ከግብ ለመድረስ የቆረጠ ማንነት እንደሆነ እንዲያውቁ የተቻለኝን አደርግ ነበር፡፡

•  ሃብታም ሰው ብዙ ገንዘብና ቁሳቁስ ያለው ሰው ሳይሆን የሚያስፈልገውን ነገር ያወቀ ሰው እንደሆነ እንዲያውቁልኝ እጥር ነበር፡፡

•  ራሳቸውን ከሌላው ጋር ማነጻጸርና ማወዳደር እንደማይገባቸውና ከእነርሱ የሚያንስ ሰው እንዳለ ሁሉ የሚበልጥም ሰው የመኖሩን እውነታ እንዲቀበሉት አስረዳቸው ነበር፡፡

•  አመለካከታቸውን መቆጣጠር እንዳለባቸው አለዚያ አመለካከታቸው እነሱን እንደሚቆጣጠራቸው እንዲማሩ እሞክር ነበር፡፡

•  እጅግ በጣም የሚወዷቸውና የሚያከብሯቸው ነገር ግን ያንን በቅጡ ለመግለጽ የማይሆንላቸው ብዙ ወዳጆች እንዳሏቸው አስረዳቸው ነበር፡፡ 

•  እውነተኛ ጓደኛ ማግኘት እጅግ ከባድ እንደሆነ፣ ያንን ያገኘ ግን የሕይወቱን አብዛኛውን ችግሩን እንዳቃለለ እንዲያውቁ እመክራቸው ነበር፡፡

•  የቅርብ ወዳጆቻቸውን ለማቁሰል ሰከንድ እንደሚበቃ ለመፈወስ ግን አመታት እንደሚፈጅ እንዲገባቸው እጣጣር ነበር፡፡

•  ሰዎችን ለመቆጣጠር በመሞከር እንደሚያጧቸው፣ ምርጫቸውን በማክበር ነጻነታቸውን በመስጠት ግን ለዘለቄታው ወዳጆች እንደሚያደርጓቸው እንዲገነዘቡ ለማድረግ እሞክር ነበር፡፡

•  የውስጥ ሰላም ለማግኘት ከሰዎች ይቅርታን ማግኘት ብቻ ሳይሆን ራሳቸውንም ይቅር ማለት እንደሚገባቸው እንዲያስታውሱ አሳስባቸው ነበር፡፡

•  ከመናገር በሚቆጠቡበት ነገር ላይ ጌታ፣ በልቅነት ለሚናገሩት ንግግር ደግሞ ባሪያ ሆነው እንደሚኖሩ አሳውቃቸው ነበር፡፡

•  እውነተኛ ደስታ የውሳኔ ጉዳይ እንደሆነ፣ በማንነታቸውና ባላቸው ነገር ደስተኛ መሆን፣ አለዚያ በቅንአትና በፉክክር ወጥመድ ውስጥ እንደሚገቡ አስገነዝባቸው ነበር፡፡

•  በአጭሩ በዋናው የሕይወት ነገር ላይ ያተኮረ ዝንባሌ ቢኖራቸው እመክራቸዋለሁ፡፡

https://t.me/ethteksimyo

የስነልቦና ምክሮች psychology

15 Jul, 00:33


አትልፋ የተጻፈልህን ነው የምትኖረው🍒🍒🍒
አፍራ ያለው ማሽላ ተኝቶም ያፈራል!🍒🍒🍒

ማነክ ኧረ እንደዚህ አባባል የመጨረሻ ስህተት የለም።
አፍራ ያላለው ማሽላ ተኝቶ ምስጥ ይወጣበታል ቢሆን ይሻላል።
🎤አንዳንድ ሰዎች የተጻፈልህን ነው የምትኖረው አትድከም ብለው ሲመክሩ ይታያሉ።እመነኝ እንደዚህ አድካሚ እና የተዛባ ሀስተሳሰብ የለም።
🎤አትናደድ እስከ መጨረሻው አድምጠኝ!!
ፈጣሪ አንተ ለክብር አንተ ለውርደት ብሎ ከሆነ
አንተ ለሀብት አንተ ለድህነት ብሎ ከሆነ
አንተ ለጤንነት አንተ ለህመም ብሎ ከሆነ
አንተ ለስደት አንተ ለሰላም ብሎ ከሆነ
ባጠቃላይ አንተ ለሀጺያት አንተ ለቅድስና
አንተ ለሲዖል አንተ ለገነት ብሎ ከሆነ....
አንተ ለአለም አነተ ለዘላለም ለሕይወት
🎤ለምን ፈልጉ ታገኛላች ጠይቁ ይሰጣችኋል ይለናል።???ምናልባት ሀጺያት ሰርተን ሲዖል ብንገባ ለመግባታችን እግዚአብሔር ለሲዖል ብሎን ነው ካልን ።ለመግባታችን እሱ ነው ምክንያቱ ማለት ነው????[ሎቱ ስብሀት] አይደለም።
🎤 ለዛማ ለምን ጹሙ ሰውነታችሁን አስገዙ
ወደፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ ይለናል? አንዴ ለገነት ለሲዖል ከተባልን ለምን ቃሌን የጠበቀ የዘላለም ሂወት አለው ለምን ይለናል??? ስለዚህ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ነጻ ፍቃድን ሰጥቷል እኛ አስበን የሚጠቅመንን መምረጥ የኛ ፋንታ ነው ። እንጂ እሱ በሁሉም ላይ ሾሞናል።እሳትና ውሀ አስቀምጬልሀለሑ እጅህን ወደወደድከው ጨምር ነው ያለን።እንጂ ላንተ የሆነ ነገር ለኔ የህነ ነገር አልተጻፈም። ጽድቅ ብንሰራ እስከ መልአክነት ድርስ እንዲያም ከኔ በላይም መስራት ትችላላችሁ ብሎን የለምን።አሳማነት ዘላይነት ደንቆሮነት አለምን ብቻ የምናይ እንስሶች ከሆንን እንደምርጫችን አንተን አንፈልግም ስላልን ሲዖልን ያስረክበናል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን ቸርነቱን አድንቅ ። አለምን ንቀው እሱን ለተከተሉ የዘላለም ብርሀንን ይሰጣቸዋል ። ደግሞም አያስጨንቀንም አመስግኑኝ እንጂ ምንም አላለን ማረን በሉኝ አለቀ ። የሚያስብ አይምሮ ስላለን የሚረባንን መመርመር የኛ ፋንታ ነው።እንስሳት እንኳን ተላምደው ቁም ነገር ይሰሩ የለምን እኛ ግን ከሰውነት ወደእንስሳነት ወረድን!
ፈጣሪ ከፍ ያለ አይምሮን ያድለን 🎤
ሁሌም ፈልገው። አሳ ነባሪ ሆድ ውስጥም ሆነህ ተስፋ አትቁረጥ አውጣኝ በለው ሰንጥቆም ያወጣሀል።
በሀዘን ውስጥ እግዚአብሔር አመስግን ።

ስለዚህ ተጽፎልኛል ብለህ አትተኛ ስራ ልፋ ጣር እርዳታውን ጠይቅ ተኝተህ ብትለምን ፈጣሪ የሚያውቀው መተኛትህን ነውና ተነስተህ ባርክልኝ በለው አምነህ ተሰማራ ብታሳዝነውም አትርሳው አውጣኝ በለው ቀን ውሎህ ቢያስቀይመው አንተ በሌሊት ተገናኘው።
በቃ አለቀ...

📘➤3

የስነልቦና ምክሮች psychology

06 Jul, 03:26


ከዘመዶችህ ጋር በሚኖርህ ውብ ጊዜኣት ብቻ ነው፡፡ ከእነርሱ ጋር በምታሳልፈው ጊዜ ፣በምትጫወተው ጨዋታ፣ በምትዘምረው መዝሙር፣ በምትስቀው ሳቅ እውነተኛ ደስታን ታገኛለህ ።
እምስቱ ሊካዱ የማይችሉ የህይወት እውነታዎች
1. ልጆችህ ሀብታም እንዲሆኑ አታስተምራቸው፥፥ ይልቅ እንዴት ደስተኛ መሆን እንደሚችሉ አስተምራቸው፥፥ ሲያድጉ የነገሮች ዋጋ ሳይሆን ጥቅማቸው ይገባቸዋል፡፡
2. ምግብህን እንደ መድሃኒት ውሰድ ካልሆነ መድሃኒት እንደምግብ ትወስዳልህ።
3. የሚወድህ ሰው በቀላሉ አይለይህም፣ ከአንተ ለመለየት 99 ምክንያት ቢኖረው እንኳ መለየት በማይችልባት አንዲት ነገር ላይ ፀንቶ ይቆማል።
4. ሰው ሆኖ በመፈጠር'ና ''ሰው በመሆን'' መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። ይህ የሚገባቸው ጥቂት ሰዎች ናቸው፡፡
5. ስትወለድ ውድ ነበርክ፣ ስትሞትም ውድ ትሆናለህ፣ በመካከል ያለውን ማስተካከል ያንተ ፋንታ ነው፡፡

የስነልቦና ምክሮች psychology

06 Jul, 03:26


★ ራስህን ተንከባከብ ፣ ከሌሎች ጋር መልካም ግንኙነት
ይኑርህ።
★ ለቤተሰብህ፣ለትዳር አጋርህ እና ለጏደኞችህ የፍቅርን ውርስ አስቀምጥላቸው፡፡
★ ራስህን ተንከባከብ ፣ ከሌሎች ጋር መልካም ግንኙነት ይኑርህ።
★ እያደግን ስንሄድና የህይወት ትርጉሙ ሲገባን ውድ ሰዓትም አሰርን ርካሽ ሰዓት ፣ ሁለቱም የሚነግሩን ጊዜ እኩል መሆኑ ይገባናል።
★ በኪሳችን ውድ ቦርሳም ያዝን ርካሽ ቦርሳ ፣በውስጡ የሚኖረውን የገንዘብ መጠን አይቀይረውም ።
★ የአንድ ሚሊዮን ብር መኪናም ነዳን የሶስት መቶ ሺህ ብር መኪና ፣የመንገዱ ርዝመት አይቀየርም፣ አቅጣጫውም ያው አንድ ነው፥፥የምንደርሰውም ያው እዚያው ቦታ ነው ።
★ ውድ መጠጥም ጠጣን ርካሽ መጠጥ፣ ስካሩና አድሮ የሚያመጣው ራስ ምታት ለውጥ የለውም፡፡
★ የውስጥ ደስታ በቁሳቁስ እንደማይገኝ ያን ጊዜ ይገባሃል። ★ አውሮፕላን ላይ የክብር ቦታም ተቀመጥክ ወይም ተራ ቦታ ፣አውሮፕላኑ ከተከሰከሰ እኩል ቁልቁል ትወርዳለህ። እውነተኛው ደስታ የሚገኘው ከቤተሰብህ፣ከጓደኞችህ፣ ከዘመዶችህ ጋር በሚኖርህ ውብ ጊዜኣት ብቻ ነው፡፡
ከእነርሱ ጋር በምታሳልፈው ጊዜ ፣በምትጫወተው ጨዋታ፣ በምትዘምረው መዝሙር፣ በምትስቀው ሳቅ እውነተኛ ደስታን ታገኛለህ ።

የስነልቦና ምክሮች psychology

06 Jul, 03:25


የአፕል ካምፓኒ ባለቤት የነበረው ቢሊዬነሩ ስቲቭ ጆብስ ህይወቱ ያለፈው በ 56 ዓመቱ በካንሰር በሽታ ነው፡፡
በንግዱ ዓለም ውስጥ የመጨረሻ ከፍታ ጫፍ የሚባለው
ቦታ ደርሻለሁ፣ ይሁን እንጂ ከዚህ ሁሉ ሀብት ደስታን ማግኘት አልቻልኩም። በልፋቴ ካከማቸሁት ሃብት ያገኘሁት ደስታ እዚህ ግባ የማይባል ነው፡፡
አሁን፣በህይወቴ የመጨረሻው ሰዓት አካባቢ፣አልጋ ላይ ሆኜ ያሳለፍኩትን ነገር ሁሉ ወደሗላ ሳስበው ፣ እኮራበት የነበረው ሀብቴና ዝናዬ ከንቱ እና ትርጉም አልባ እንደሆነ ተረድቻለሁ ይላል ጆብስ።
✓ አንድን ሰው መኪና እንዲነዳልህ ወይም ሰርቶ ገንዘብ እንዲያስገባልህ ልትቀጥረው ትችላለህ፣ እየተሰቃየህበት ያለውን ህመም እንዲሸከምልህ ግን ልትቀጥረው አትችልም፡፡
✓ ምድራዊ የሆኑ ቁሳቁሶች ሁሉ ሊጠፉ ፣ዳግም ሊገኙም ይችላሉ፥ አንድ ጊዜ ካመለጠ ደግመህ ልታገኘው የማትችለው አንድ ነገር ግን አለ... እርሱም ህይወትህ ነው፡፡
✓ አንድ ሰው የቀዶ ጥገና ወደሚደረግለት ክፍል ሲገባ አንብቦ ያልጨረሰው አንድ መጽሃፍ ትዝ ቢለው የመጽሐፉ ርዕስ 'ጤናማ ህይወት የመኖር ሚስጥር'' የሚል ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡
✓ በየትኛውም የህይወት ከፍታ ላይ ብንሆን የህይወታችን መጋረጃ የሚዘጋበትን ቅጽበት ፊት ለፊት የምንጋፈጥበት አንድ ቀን መምጣቱ አይቀርም።
★ ለቤተሰብህ፣ለትዳር አጋርህ እና ለጏደኞችህ የፍቅርን ውርስ አስቀምጥላቸው።

የስነልቦና ምክሮች psychology

03 Jul, 11:59


ሊሆንም ላይሆንም ይችላል!
==================
በአንድ መንደር ውስጥ የሚኖሩ ጠቢብ ሽማግሌ ነገሩ ፡፡ በመንደሩ ውስጥ የነበሩት ነዋሪዎች ጥያቄዎቻቸውን ይዘው እርሳቸው ጋር ይሄዱ ነበር ፡፡

አንድ ቀን በመንደሩ የሚኖር ገበሬ ወደ ጠቢቡ ሽማግሌ መጥቶ ግራ በተጋባ ድምፀት ”እባክዎ ይርዱኝ ፡፡ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነኝ፡፡ በሬዬ ሞተ ስለዚህም የማርስበት እንሰሳ የለኝም ፡፡ ከዚህ የከፋ ምን ሊሆን ይችላል?" አላቸው ፡፡ ጠቢቡ ሽማግሌ በእርጋታ “ከዚህ የከፋ ነገር ሊሆርም ላይኖርም ይችላል።” ብለው ሲመለሱለት ገበሬውም በጥድፊያ ወደ ሰፈሩ ተመልሶ ለጎረቤቶቹ "ሽማግሌው አብዷል፡፡ ከዚህ የባሰ ነገር ምን ሊኖር ይችላል? እንዴት ይህንን ማወቅ ይሳናቸዋል?" አላቸው ፡፡

በነጋታው ገበሬው እርሻ ውስጥ አንድ ፈረስ ይመለከታል፡፡ ምንም በሬ ስላልነበረው “በፈረሱ ባርስስ?” የሚል ሀሳብ ይመጣለታል፡፡ ከዚያ ፈረሱን ይዞ ማረስ ይጀምራል፡፡ ማረስ እንደዛ ቀሎት አያውቅም፡፡ ጠቢቡ ሽማግሌን ይቅርታ ለመጠየቅ ሄደ፡፡ "ልክ ብለው ነበር ፡፡ በሬን ማጣት የመጨረሻው አስከፊ ነገር አይደለም፡፡ እንደውም በረከት ነው፡፡ በሬዬ ባይጠፋ ኖሮ ፈረስ አላገኝም ነበር፡፡ እንደውም በሬዬ መሞቱ በጣም ጥሩ ነገር ነው አይደል?" ሲላቸው። ሽማግሌው በተረጋጋ ድምፀት አሁንም “ምናልባት ሊሆን ይችላል፤ ምናልባት ላይሆንም ይችላል፡፡" ብለው መለሱለት፡፡ ገበሬው እኝህ ሰው አእምሯቸውን ስተዋል ብሎ አሰበ ፡፡

ነገር ግን ገበሬው ቀጣይ የሚፈጠረውን አላወቀም ነበር፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ የገበሬው ልጅ ፈረሱን እየጋለበ ይወድቅና እግሩ ይሰበራል ፡፡ “እርሻ ላይ ማን ያግዘኛል?” ብሎ ይጨነቅና ሽማግሌው ጋር ይሄዳል ፡፡ “ፈረስ ማግኘቴ ምርጥ ነገር እንዳልነበረ እንዴት አወቁ? ልጄ እግሩ ተሰብሯል፡፡ እርሻ ላይም አያግዘኝም፡፡ ይሄ በርግጠኝነት እጅግ አስከፊ ነገር ነው፡፡ በዚህ መቼም ይስማማሉ፡፡" ይላቸዋል ፡፡ ሽማግሌው ግን ከዚህ በፊት እንዳደረጉት በእርጋታ “ሊሆንም ላይሆንም ይችላል” ብለው ይመልሳሉ፡፡ "አሁንስ መሳሳታቸው እርግጥ ነው!" ብሎ በንዴት ጥሏቸው ይሄዳል፡፡ በነጋታው በመንደራቸው ጦርነት  ታውጆ ወታደሮች አቋማቸው ብቁ የሚመስሉ ወጣቶችን በግዳጅ ሰብስበው ይዘው ይሄዳሉ፡፡ ከመንደራቸው የቀረው የሱ ልጅ ብቻ ነበር፡፡ ሌሎቹ ወደ ሞት ቦታ ሲወሰዱ የእርሱ  ልጅ በሕህይወት ቤት ቀረ፡፡

ከዚህ ታሪክ ትልቅ ትምህርት እናገኛለን ፡፡ በእውነታው ዓለም ቀጣይ የሚከሰተውን ነገር ማወቅ አንችልም ፡፡ የምናውቅ ይመስለናል እንጂ አናውቅም ፡፡ ቀጣይ ይፈጠራሉ ብለን የምንሰጋቸውን ነገሮች በአእምሯችን ውስጥ እናሰላስላቸዋለን፣ እንጨናነቅባቸዋለን፡፡ ብዙ ጊዜ እንሳሳታለን፡፡ ተረጋግተን ነገሮችን ለመቀበል ከተዘጋጀን ግን ሁሉ ለመልካም ይሆናል ፡፡ አስታውስ አሁን አስቸጋሪ የሚመስልህ ሁኔታ ጥሩ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል።

ከ"ቀላሉን ነገር አታካብድ"  መፅሀፍ የተቀነጨበ በዶ/ር ሪቻርድ ካርሰን
ትርጉም ዶ/ር ዮናስ ላቀው

የስነልቦና ምክሮች psychology

23 Jun, 15:20


" ያ ደግ ሰው በመንገዱ እየኼደ ሳለ ሽፍታ አገኘ፡፡ ያ ደግ ሰው፤ “ሰላም ለአንተ ይኹን! በዚህ ስፍራ ለምን ብቻህን ትዘዋወራለህ?” አለው። ያ ሽፍታም፡ “እኔ ሽፍታ ነኝ! ለዚህም ነው በዚህ ሰዋራ ስፍራ የምዘዋወረው::

ይልቅ ምን ይዘሃል? ወዲህ በል የያዝኸውን ኹላ! አምጣው!” አለው። ያ ደግ ሰው፡ “ለምን ግን ሠርተህ አትበላም? ሰው የደከመበት ገንዘብ ላንተ ምን ያደርግልሃል?" አለው፡፡

ያ ሽፍታ እየሣቀ፡ “ስማ! ማር በልተህ ታውቃለህ?" አለው:: ያ ደግ ሰው፡ “እንዴታ! በደንብ አድርጌ ነዋ የምበላው!" አለው::

ያ ሽፍታ፡ “ሠርተህ ነው ወይስ ከንብ ቀምተህ ነው? በጭስ እያስፈራራህ፣ እንዳትታይ በጭንብል እየተከለልህ ነው ንብ ለፍታ የሠራችውን የምትቀማት” አለው፡፡

ያ ደግ ሰው፤ ኹሉም ሰው “ለፋኹበት” በሚለው ጕዳይ ወስጥ መዝረፍ እንዳለበት ዐወቀ። ከዚያም፣ ለሽፍታው “ብዙ ገንዘብ የለኝም:: ምናልባት ይህቺ ኹለት ፈረንካ ከበቃችህ እንካ” አለው፡፡

ያ ሽፍታ፡ “ለዛሬው ምሬሃለኹ፣ ከዚህ በኋላ ግን በማያገባህ ጕዳይ አትግባ" አለው፡፡

ያ ደግ ሰው፡ “እንኳን ማርኸኝ እንጂ በል ደኅና ሰንብት" ብሎት ፈጠን ፈጠን እያለ ተራመደ፡፡ በመንገዱም ላይ ሳለ እንዲህ እያለ እያሰበ ነበር፡፡

“አኹን ግን የእውነት እንቁላልን ዶሮ የምትሸጠው ቢኾን ዋጋው ስንት ይኾን ነበር? ሰው ከዕቅፏ ፈልቅቆ ይወስድባታል እንጂ መቼ ይጠይቃታል። እና፣ ከደምና ከዐጥንቴ ያልሠራኹትን ገንዘብ ሽፍታ ወስዶብኝ እንዲህ ከተንገበገብኹ ልጅ ይኾነኛል ያልኹትን፣ ከብቤ ያኖርኹትን ቢያነሡብኝ ቀድሜ አበድኹኝ” እያለ ኑሮውን እየታዘበ ኼደ፡፡ "

የስነልቦና ምክሮች psychology

09 Jun, 10:42


እድሜ መሄዱ ካልቀረ!
___
አንድ የ30 አመት ጎልማሳ ብዙ ከወላወለ በኋላ እድሜ ልኩን ሲመኘው የነበረን የምህንድስና ትምህርት ለመማር ለምዝገባ ወደ አንድ ኮሌጅ ሄደ፡፡ ቢሮ እንደገባ የተማሪዎች አማካሪ አገኘውና ሲያማክረው፣ “በመማርና ባለመማር መካከል ብዙ ወላውያለው” አለው፡፡

አማካሪው ምክንያቱን ሲጠይቀው፣ “አሁን 30 አመቴ ነው፡፡ ስመረቅ እኮ 35 ሊሆነኝ ነው” በማለት የመወላወሉን መነሻ ምክንያት ነገረው፡፡

አማካሪው የመለሰለት መልስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ትምህርት ገፋው፡፡ “የዛሬ አምስት አመት እኮ ብትማርም ሆነ ባትማር 35 አመት መሙላትህ አይቀርም፡፡ ሳትማር 35 አመት ከሚሞላህ፣ ተምረህ ቢሞላህ አይሻልም?”

እስቲ አንድ ጊዜ ጸጥ በሉና ስንት እድሜ ላይ እናዳላችሁ አስቡት፡፡ ከዚያም በአሁኑ እድሜያች ላይ አምስት አመት ደምሩበት፡፡ ድምሩ ስንት መጣ?

በሉ እንግዲህ . . .

• ብትማሩም ሆነ ባትማሩም የዛሬ አምስት አመት እድሜያችሁ በአምስት አመት መጨመሩ አይቀርም! ሳትማሩ ከሚጨምር፣ እየተማራችሁ ቢጨምር አይሻልም?

• ብትነግዱም ሆነ ባትነግዱም የዛሬ አምስት አመት እድሜያችሁ በአምስት አመት መጨመሩ አይቀርም! ሳትነግዱ ከሚጨምር፣ እየነገዳችሁ ቢጨምር አይሻልም?

• ብታቅዱም ሆነ ባታቅዱም የዛሬ አምስት አመት እድሜያችሁ በአምስት አመት መጨመሩ አይቀርም! ሳተቅዱ ከሚጨምር፣ አቅዳችሁና ተንቀሳቅሳችሁ ቢጨምር አይሻልም?

በእድሜ ምክንያት ከመንቀሳቀስ ራስን ማገድ ማለት፣ ነገ መሞቴ ካልቀረ ዛሬውኑ መኖርን ላቁምና እንደሞተ ሰው ልኑር እንደማለት ነው፡፡

በሉ ተንቀሳቀሱ !!!
___
✍️ Dr Eyob Mamo 🥰

የስነልቦና ምክሮች psychology

06 Jun, 13:46


ተረጋጋ (calm down)
መረጋጋት ሁሉንም ነገር ይፈታል። ስለዚህ ረጋ እንበል። ሰላምታችን አይፍጠን፣ስንበላ ምግቡን እናጣጥመው፣ስንጠጣ ተረጋግተን ቦታ ይዘን እንጠጣ፣ስናወራ እያዳመጥን መልስ ለመስጠት ሳይሆን ለመስማት ጊዜ እንስጥ፣ስናወራ ከልባችን በግልፅ እናውራ፣ትኩረት የለለበት ጥድፊያ ብዙ ችግር ውስጥ ያስገባናል። በአንፃሩ ከመረጋጋት ብዙ ጥሞችን እናገኛለን። ከብዙ በጥቂጡ ላካፍላችሁ።
.........#አንድ
የጥበብ እና የማስተዋል ምንጩ ትዕግስት ነው።ትዕግስት
በጽናቷና እርጋታዋ ምክንያት የጥበብ እውነተኛ ወዳጅ ናት! #ሁለት
እሳትን በእሳት እንደማናጠፋው ትዕግስት እና መረጋጋትም የቁጣና የፀብ ማብረጃ ነው፤ ልክ እሳትን ለማጥፋት ውኃ እንደሚያስፈልግ መረጋጋትም የብዙ ጥፋቶች ማጥፊያችን ነው ።
.........#ሶስት
ሰው በንግግሩ ሳደማህ እግዚአብሔር በዝምታ እንደሚያክምህ ሁሉ እምነትህ በልብህ ይሁን።ለታይታ ያልሆነ እምነት
እርጋታን እና ሞገስን ያስገኛል።ስለ ኃይማኖት መከራከር እንደለለብህ እወቅ።ስለ እምነት መከራከር ፍጹም ቀይ መስመር ነው።ምክንያቱም እምነት በልብ ስለሆነ ሰዎች በገባቸው ልክ
ያምልኩ ዘንድ ካወክ ትረጋጋለህ የራስህን አብልጠህ የሌሎችን አታሳንስም። ..#አራት
ገረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል። መረጋጋት ሁሉንም ነገር ይፈታል!
ረጋ እንበል።ረጋ ስንል የደፈረሰው ይጠራል። መረጋጋት የእውነት ማረጋገጫው ነው።
.....#አምስት
ዓለም የእግዚአብሔር ልጅ መሆንና አለመሆን የምትለየው ምግባርህንና ባህሪህን አይታ ነው።ምግባርህ የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን ያሳይ እንጅ ምግባርህን ለማስረዳት አትድከም።
#ስድስት
መንፈሳዊ እድገት የምትወጣጣበት መሰላል አይደለም፤
መንፈሳዊ እድገት ያለማቋረጥ የምትከተለው ጉዞ ነው!ለዛ ደግሞ መረጋጋት እና ፅናት ይፈልጋል እና ረጋ እንበል።
.......#ሰባት
የመንፈስ ቅዱስ ማረፊያ እንደመሆናችን ከቅዱሱ መንፈስ ጋር መተሳሰር አለብን። የእያንዳንዱ አማኝ ሰው ስራ የአንድ ተራ ሰው ስራ ብቻ አይደለም፤ የመንፈስ ቅዱስም ጭምር እንጂ!መንፈስ ቅዱስ የቀረበው ሰው ረጋታው ብዙ ያወራል። ሲናገርም አንደበቱ አታውቅምና ፈጽሞ ፈራጅ አትሁን። ለመርዳት የፈጠንክ ለመፍረድ የዘገየህ ሁሉ። ........#ዘጠኝ
እግዚአብሔር የማትችለውን ግዴታ አይሰጥህም! ሸክምህ
ከአቅምህ በላይ ሆኖ በተሰማህ ቁጥር፤ አንተ ያላየኸው እግዚአብሔር ግን ያየብህ ትልቅ አቅም ውስጥህ እንዳለ እወቅና ረጋ በል ለውሳኔ አትቸኩል።ከውሳኔህ በፊት ፈጣሪህ ጋር ለመነጋገር ሞክር ያኔ ሚዛናዊ ውሳኔ ትወስናለህ።
..........#አስር
አንተ ለሕይወትህ ካቀድከው የተሻለ እግዚአብሔር እንደሚያቅድልህ ታውቃለህ እና ረጋ በል።አንተ ስለአንተ ልትሳሳት ትችላለህ፤ እግዚአብሔር ግን አይሳሳትም። አንተ ስለሕይወትህ ስታቅድ ልትሳሳት ወይም ያነሰውን ልታስብ ትችላለህ፤ እግዚአብሔር ግን ላንተ የሚገባውንና የተሻለውን በፍጹም ትክክለኛነት ያዘጋጅልሃልና ረጋ በል።

የስነልቦና ምክሮች psychology

22 May, 21:43


አንድ ሰው አንዲት የከሳች በቅሎ ነበረችው።አወጣና ሸጣት።ከዓመታት በኋላ ገበያ ሲወጣ አንድ ሰው እጅግ ያማረች የኮርቻ በቅሎ ይዞ ተመለከተ።ሰውዬው ጠጋ ብሎ "ጌታው ይህችን የመሰለች በቅሎ ከየት ትገኛለች እባክዎ ? እኔም ለመግዛት እፈልግ ነበር" አላቸው።ሰውዬውም "እኔም በአጋጣሚ ከሰው ነው የገዛኋት።ስትገዛ ከስታ ልትሞት
ደርሳ ነበር።የሸጠልኝ ሰው እንደነገረኝ ባለቤቷ ለበቅሎ ግድ አልነበረውም።እኔ የበቅሎ ጠባይ ስለማውቅ ነው ከሰውዬው የገዛኋት።በአንድ አመት ውስጥ በደንብ ስይዛት ጊዜ እንዲህ ያማረች በቅሎ ሆነች" አሉት።"መቼ ነበር የገዙት ?"አላቸው "የዛሬ አራት ዓመት ከዚሁ መንደር ገዝቷት ሲሔድ ነው ለምኜ የገዛሁት" አሉት።እራሱን እየነቀነቀ ተመለሰ ። በቅሎዋ የእርሱ ነበረች።የሰውዬውን ያህል ግን የበቅሎዋን ዋጋ አላወቀውም ነበር።ተፈላጊዋን ምርጥ በቅሎ ይፈልጋል።እኛም ያሉንን ምርጥ ነገሮች እየሸጥን የሌሉንን ምርጥ ነገሮችን እንፈልግ ይሆናል።
በእጃችን ያለው ነገር የእኛ ነው።በእጃችን የሌለው ግን ገና የእኛ አይደለም።የእኛ የሆነው የእኛ ካልሆነው ነገር ይበልጣል።ምክንያቱም የእኛ በሆነው ነገር መጠቀም እንችላለን የእኛ ባልሆነው ነገር ግን ልንጠቀም አንችልም።የእኛ በሆነው ነገር ልናዝ እንችላለን የእኛ ባልሆነው ነገር ግን ልናዝ አንችልም።የእኛ የሆነው ነገር ማግኘታችንን እርግጠኛ ሆነናል።የእኛ ያልሆነውን ማግኘት ግን እርግጠኛ መሆን አንችልም፤የእኛ በሆነው ነገር ልንወስንበት እንችላለን፤የእኛ ባልሆነው ነገር ግን ልንወስን አንችልም።የእኛ የሆነውንነገር ለሌላው መስጠት እንችላለን የእኛ ያልሆነውን ግን መስጠት አንችልም።ካለን ነገር ላይ ቆመን የሌለንን ማየት እንችላለን፤ከሌለን ነገር ላይ ቆመን ግን ያለንን ነገር ማየት አንችልም።
አንዳንድ ጊዜ የምናማርረው ችግር ስለደረሰብን ብቻ ሳይሆን ያለንን ስለማናውቀው ጭምር ነው።ችግር በራሱ ችግር አይደለም።ችግር ችግር የሚሆነው መፍትሔ መስጠት ለማይችል ሰው ብቻ ነው።መፍትሔ መስጠት ለለመደ ችግር ትምህርት ቤት ነው።ችግር የፍች፣የመለያየት፣የጠብ፣የኩርፊያ፣የክስ፣የመለቀቂያ መንገድ የሚሆነው ለዐቅመ ቢስ ሰው ነው።ለብርቱ ሰው ግን ሞት የትንሳኤ መቅድም ነው ። የሌለንን ነገር ብቻ ካሰብን ያለንንም እናጣለን።ያለንን ነገር ካሰብን ግን የሌለንንም እናገኛለን።እስኪ ያለንን እንወቀው፣እናክብረው፣አሟጠን በሚገባ እንጠቀምበት፣እንኑርበት እናጊጥበት።ከዚያ ሌላውን ያጣነውን ለመያዝ እንፈልግ።ባለን የማንረካ ከሆን ግን ሩጫችን የተሻለ ነገር ፍለጋ ሳይሆን ሌላ ነገር ፍለጋ ድካም ብቻ ይሆናል።ባለው ያለረካ ቢሰጠውም አይረካ፣ባለው ያልተደሰተ ቢጨመርለትም አይደሰት፣ባለው ያላመሰገነ ቢጨመርለትም አያመሰግንም፣ባለው መጠቀም ያልቻለ ቢጨመርለትም መጠቀም አይችልም፣ያለውን ባግባቡ ያልያዘ ቢጨመርለትም መያዝ አይችልም።

የስነልቦና ምክሮች psychology

18 May, 21:21


👉🏿በሕይወት ዘመንህ!፦

👉🏿ስኬትህን በራስህ ሚዛን መዝነው፤ በሰው ሚዛን ከመዘንከው ሚዛን አይደፋልህምና።

👉🏿ደስታህን በራስህ መስፈሪያ ስፈረው፤
በሰው ሚዛን ስትሰፍረው አይሞላልህምና።

👉🏿ውድቀትህን በራስህ አይን እየው፤ በሰው አይን ከተመለከትከው ጉድጓዱ ይበልጥ
ይርቅሃልና።

👉የራስህን ህይወት በሌላ ሰው እይታ
ከተመለከትከው ፈጽሞ እርካታ አይኖርህም::

👉ህይወትሀን ከሰው ጋር እያነጻጸርክ የምትኖር ከሆነ እርካታ የሌለው ኑሮ እየኖርክ ነው፤

ምክንያቱም በንጽጽር ህይወት ውስጥ  ሁሌም የሚበልጥህ አታጣምና።

የስነልቦና ምክሮች psychology

18 May, 12:42


MOVIE SUGGESTION

ውሸት በጣም ጠቃሚም፣ አስፈላጊም ነገር ነው። እውነት ሁሌ አይነገርም ሙድ፣ አገባብ፣ መቼት ተጠብቆ ነው። እውነት ሁሌ ሲነገር ይሰለቻል፣ ይቸካል፣ ይረክሳል። እውነት የክት ነው። አንዳንዴ እውነት መናገር ስሜት ሊጎዳ ይችላል። ያኔ እንዋሻለን። ውሸት ባይኖር በድብርት እንሞት ነበር።

የፊልሙ ርእስ The Invention of Lying ይሰኛል። ሰዎች መዋሸት የማይችሉበት አለም ነው። ዋና ገፀባህሪው ማርክ ይባላል። ከአንዲት ውብ ኮረዳ ጋር የፍቅር ቀጠሮ አለው። ታዲያ ልጅት እንዲህ ትለዋለች፦

"መልክህ ብዙ አያምርም። በዚያ ላይ ሃብታም አይደለህም። የሁለታችን ነገር የሚሆን አይደለም"

ቆይ! ላስብበት የለ! ሌላ ሰው አለኝ የለ! እውነቱን ቁርጥ፣ ፍርጥ አድርጎ መናገር። እና ይሄ አለም አያስቀይምም?!

ለማንኛውም ጥናት እንደሚለው እያንዳንዱ ሰው በቀን 4 ግዜ ይዋሻል። በአመት 1460።

የስነልቦና ምክሮች psychology

10 May, 20:03


በአንድ ወቅት አንድ ገበሬ አህያው ጉድጉድ ውስጥ ትገባበታለች፡፡ ጉድጓዱ ሩቅ ከመሆኑ የተነሳ አህያዋ ለመውጣት በእጅጉ ተቸገረች፡፡ በጣም መጮህ ጀመረች፡፡

ባለቤቱም እሷን ለማውጣት ብርቱ ሙከራ አደረገ አልተሳካለትም ፤ አህያዋ አርጅታለችና እዚያው ጉድጓድ ውስጥ ሊቀብራት አሰበ።

ጎረቤቶቹንም ጠራና ጉድጓዱን በአፈር መሙላት ጀመሩ፡፡ አህያዋ ይህንን ስተመለከት እየቀበራት መሆኑን ተረዳችና እጅጉን አዘነች፡፡

ይሁን እንጂ አፈር በተደፋባት ቁጥር አህያዋ አንድ ነገር ታደርግ ነበር። አፈሩን እያራገፈች ከአፈሩ ውስጥ ብቅ ትል ነበር። በተደጋጋሚ በተደፋው አፈር ላይ መቆም ትጀምራለች።

በሂደት በአፈሩ ላይ በቆመች ቁጥር ከነበረችበት ጉድጓድ ከፍ እያለች በመጨረሻም ከጉድጓዱ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መውጣት ቻለች፡፡

በሚገርም ሁኔታ አህያዋን ሊቀብሯት የሞከሩት ስዎች ሁሉ በአህያዋ አወጣጥ በእጅጉ ተደነቁ፡
የአህያዋ ታሪክ ሁላችንንም ይመለከተናል። የሚጫንብን አፈር  በየጊዜው የሚያጋጥሙንና ዝም ብንላቸው በመጨረሻ ሊቀብሩን የሚችሉ ችግሮች ወይም መሠናክሎች ናቸው፡፡

አፈሩን የሚጭኑት ሰዎች በዙሪያችን ያሉ ሰዎች፣ ነገሮች፣ በህይወታችን ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩብን አዳዲስ ለውጦች እንዲሁም የራሳችን አፍራሽ ስሜቶች ሊሆኑ ይችላሉ። 

ጉድጓዱ ደግሞ አሁን ያለንበት ግራ የተጋባንበት! ተስፋ ቢስ የሆንበት፡ መላ ያጣንበት ህይወት ወይም ገጠመኝ ሊሆን ይችላል፡፡
በእርግጥም እኛ ሰዎች በጤናችን! በኢኮኖሚ ህይወታችን፤ በትዳርና ፍቅር ህይወታችን በተለያየ አጋጣሚ ልክ እንደ አህያዋ ጉድጓድ ውስጥ የመግባት ዕድላችን ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ጠንካሮች እንደ ጠንካራዋ አህያ ከገቡበት ጉድጓድ ውስጥ መውጣት ሲችሉ አንዳንዶቹ በዚያው ተቀብረው ቀርተዋል፡፡
በህይወታችን ውስጥ ያለው አማራጭ! ወደ ላይ መውጣት አልያም ደግሞ ወደ ታች ወርዶ ከጥልቅ ጉዳጓድ ውስጥ ተቀብሮ መቅረት ብቻ ነው!

ልክ እንደ አህያዋ (የሚጫንባትን አፈር እየረገጠች ወደ ላይ ከፍ እንዳለችው) ሁሉ እኛም በየጊዜው የሚያጋጥሙንን ችግሮች እንደ ድጋፍ እየተጠቀምን በጥንካሬ ወደ ላይ መነሳት ያስፈልገናል።
ከጥልቁ ጉድጓድ ውስጥ ለመውጣት የምንችለው ለመውጣት የምናደርገውን ጥረት ባለማቆም ብቻ ነው!

ምንጊዜም በጠንካራ ውስጣዊ ቁርጠኝነትና እምነት ችግሮችን እንደ መወጣጫ ደረጃ በመጠቀም ከታች ወደ ላይ እንጓዝ!!
እያንዳንዱን ችግር እንደ መሰላል ከተጠቀምክበት ከስኬት ጫፍ ትደርሳለህ!

የስነልቦና ምክሮች psychology

09 May, 18:02


ወዳጄ ሆይ.... ንጉስ ሰለሞን ‹‹ልጄ ሆይ...... ከሕዝብ ጋር አትሂድ!›› የሚልህ ከህዝብህ ተለይተህ ጥፋ ለማለት ሳይሆን ለሕዝብህ የሚሆን መፍትሄ ታበጅ ዘንድ ከመንጋው ተለይተህ አስብ እያለህ ነው፡፡ ከህዝብ ጋር ሙሉ ጊዜህን የምታጠፋ ከሆነ የምታስብበት ጊዜ አይኖርህም፡፡ ህዝብ በተፈጥሮው በወል ነው የሚያስበው፡፡ አይመረምርም፣ አይፈትንም፣ የተቀበለውን መስጠት እንጂ አዲስ የሕይወት መንገድ አይቀርፅም፡፡ ህዝብን የምትከተል ከሆነ ለራስህም፣ ለሐገርህም አትሆንም፡፡ ማሰላሰያ፣ ማገናዘቢያ፣ ራስህንም ዓለሙንም ማንበቢያ ጊዜ ከሌለህ ራስህን ዘንግተህ ያንተ ባልሆነው የሌሎች ዓለም ስደተኛ ነው የምትሆነው፡፡ መንጋው ያንጋጋሃል!

ወዳጄ ሆይ.. ወዳጅነት መልካም ነው፤ ዝምድና አይከፋም፣ አብሮአደግነት ደግ ነገር ነው፤ ባልንጀርነት ደስ ይላል፡፡ ነገር ግን የማሰቢያህን ጊዜ የሚሻማ ማንኛውም የማህበራዊ ግንኙነት ሁሉ ዘለቄታዊ ጥቅም አይሰጥህም፡፡
ሰዎች በዘልማድ ባሰመሩት የአኗኗር መስመር ብቻ መሄድ የሚያስገኘው አንዳች ነገር የለም፡፡ የብዙዎቻችን ሕይወት አሰልቺ እየሆነ የመጣው በድግግሞሽ ህይወት ውስጥ ስለምንመላለስ ነው፡፡ ኑሯችን አዙሪት የሆነው በሰጡን ርዕዮት ዓለም፣ ባቀበሉን የአኗኗር ዘይቤ ስለምንጓዝ ነው፡፡ የራሳችን መንገድ የሌለን የማሰቢያ ጊዜ ስላጣን ነው፡፡ የተወጠርንበትና የተጠመድንበት ነገር ሁሉ የሚያለማን ሳይሆን የሚያጠፋን ነው፡፡ በራሳችን መንገድ ካላሰብን የትም አንደርስም፡፡ እንዲሁ የኋሊት እንምዘገዘጋለን፡፡ ህዝብነት አያተርፍም፤ መንጋነት በራስህ እንዳትተማመን ያደርግሃል፡፡ ለህዝብ መቆም እንጂ ከህዝብ ጋር መሄድ የተለየ ውጤት አያስገኝም፡፡ ለህዝብህ ጠብ የሚል መፍትሄ አምጠህ የምትወልደው ከመንጋው ተነጥለህ ማሰብ ስትችል ብቻ ነው፡፡ መነጠልህ እስመጨረሻው የሚለይህ ሳይሆን ህዝብህን መልሶ እንዲጠቅም የሚያደርግ ነው፡፡

ወዳጄ ሆይ.... ምርጫዎችህን ለመምረጥ፣ የሕይወት መንገድህን ለመቀየስ፣ መነሻህን አሳምረህ ፍጻሜህን ለማስዋብ አንተ አንተን ሆነህ መገኘት አለብህ፡፡ ለራስህ የማታውቅ ከሆነ ሌሎች ባወቁትና በቀረፁት መንገድ ትከተላለህ እንጂ ራስህን አትመራም፡፡ ስታስብ፣ ስትመረምር፣ ስታሰላስል፣ ስታስተውል፣ አዲስ ሃሳብ ስትፈጥር ግን ችግሮችህን ትቀርፋለህ፣ መሰናክሎችህን ትሻገራለህ፣ ስልጣኔን ታመጣለህ፡፡ ራስህን ከሌሎች ባርነት ነፃ ታወጣለህ፡፡ አልያ ግን በመንጋው ተጠልፈህ በራስህ መንገድ ትመላለስ ዘንድ እንዳትችል አቅም ታጣለህ፡፡ ተከታይነት በራስህ ፀንተህ ለመቆም ሃይል እንዳይኖርህ ያደርግሃል፡፡ ተጎታች እንጂ መሪ አትሆንም፤ ጠባቂ እንጂ ሰጪ ትሆን ዘንድ አትችልም፡፡ የሰው ዓለም መፃተኛ እንጂ የራስህ ዓለም ሰሪ ለመሆን አይቻልህም፡፡ በተኮረጀ ሕይወት ዘመንንህን ትጨርሳለህ፡፡


እስኪ ሃሳብ ስጡበት👆
             

የስነልቦና ምክሮች psychology

08 May, 06:25


የትኩረት ለውጥ!

ከሰዎች ጋር ባላችሁ ግንኙነት . . .

1.  ያልሆናችሁት ላይ ሳይሆን የሆናችሁት ላይ አተኩሩ፡፡


ያልሆናችሁት ላይ ስታተኩሩ የሆናችሁትን እውነተኛ ማንነት መኖር ያስቸግራችኋል፡፡ የዚህ ሁኔታ ውጤት እንዳገኛችሁት ሰው ሁኔታ ያልሆናችሁትን ማንነት እየለዋወጡ መኖር ነው፡፡

2.  የሌላችሁ ላይ ሳይሆን ያላችሁ ላይ አተኩሩ፡፡

የሌላችሁ ነገር ላይ ስታተኩሩ ያላችሁን ነገር በትክክለኛው መንገድ መጠቀም ያስቸግራችኋል፡፡ የዚህ ሁኔታ ውጤት ከሌላችሁ ነገር በመነሳት በዝቅተኝነት ስሜት የመመታት ሁኔታ ነው፡፡

3.  የማታውቁት ላይ ሳይሆን የምታውቁት ላይ አተኩሩ፡፡

የማታውቁት ላይ ስታተኩሩ የምታውቁትን እውቀት ተግባራዊ ማድረግ ያስቸግራችኋል፡፡ የዚህ ሁኔታ ውጤት እውቀታችሁን ተጠቅማችሁ ከማደግ ይልቅ ስለማታውቁት ነገር በማሰብ ጊዜን መፍጀት ነው፡፡

ወሳኙና ጨዋታውን የሚለውጠው ነገር ትኩረታችሁ ነው፡፡ የሆናችሁት፣ ያላችሁና የምታውቁት ነገር ላይ ስታተኩሩና ቀና ብላችሁ በድፍረት ስትኖሩ፣ ያልሆናችሁት፣ የሌላችሁና የማታውቁት ነገር ላይ የመስራትና የማደግም እድላችሁ የሰፋ ነው፡፡
Dr እዮብ ማሞ