የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የ2017 በጀት ዓመት ያለፉት ስድስት ወራት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ በዘርፍ፣ በዳይሬክቶሬትና በዋና ክፍል ደረጃ ተገመገመ፡፡
ግምገማውን የመሩት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ በኃይሉ ንጉሴ አፈጻጸሙ ከተያዘው እቅድ አንጻርና በትርፍ ደረጃ ጥሩ አፈጻጸም መሆኑን ገልጸው፤ ኮርፖሬሽኑ ካለው አቅም አኳያ ግን አፈጻጸሙ መታየት እንዳለበትና ጉድለቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መወያየት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ አያይዘውም ሂደት ላይ ሳይሆን ውጤት ላይ ያተኮረ ሃሳብ ከቤቱ እንዲነሳ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
የኮርፖሬሽኑን የግማሽ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ያቀረቡት በኮርፖሬት እቅድ ዝግጅትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ እንደገለጹት በመሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች ግዢ 659, 147 ኩንታል ምርት ግዢ ለማከናወን ታቅዶ 316, 070 ኩንታል ምርት በመግዛት እቅዱን በመጠን 48 በመቶ እና በዋጋ 68 በመቶ ማከናወን ተችሏል፡፡
የፍጆታ ምርት ስርጭትን በተመለከተ 696,310 ኩንታል ምርት ለገበያ ለማቅረብ ታቅዶ 382, 466 ኩንታል ምርት ለሽያጭ ቀርቧል፡፡ አፈጻጸሙም በመጠን 72 በመቶ እና በዋጋ 86 በመቶ ሆኗል፡፡
የውጭ ሃገር ሽያጭ/ ኤክስፖርትን በተመለከተ ደግሞ በግማሽ ዓመቱ ከ400 ሺ ኩንታል በላይ የተለያዩ የብርዕ፣ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ ከ 400 ሺ ኩንታል በላይ ምርት በመላክ እቅዱን በመጠን 100 በመቶ እና በዋጋ 131 በመቶ ማሳካት ተችሏል። በዚህም ከ 27 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ተችሏል።
ገበያ ማረጋጋትን በተመለከተ በግማሽ ዓመቱ ለአምራቹ ምርትና ለፋብሪካዎች የገበያ እድል ከመፍጠር አኳያ ከ 270 ሺ ኩንታል ምርት በላይ ግዢ ተፈጽሟል፡፡ ሸማቹን ህብረተሰብ በዋጋ ንረት ተጎጂ እንዳይሆን ከገበያ ዋጋ ከ713 ሺ ብር በላይ ቅናሽ ያለው ምርት በማቅረብ ገበያውን ለማረጋገት ጥረት ተደርጓል፡፡
የቀረበውን የእቅድ አፈጻጸም ተከትሎ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡