አዋጅ አይሻርም፤ ይሻሻላል እንጂ። በርግጥ ሊደረግ የታሰበው ግን ከመሻር ተለይቶ የሚታይ አይደለም። ረቂቁ የባለሞያውን ማለትም የአርኪቴክቱን ፡ የኢንጂነሩን ድርሻና ኃላፊነት እንዲቀርፅ ተደርጎ የተዘጋጀን አዋጅ ለድርጅት አሳልፎ ለመስጠት የተቀረፀ ረቂቅ ነው።
አንድ ቀላል ማሳያ እንመልከት። አሁን በስራ ላይ ያለው አዋጅ (ቁጥር 624 /2001) አንቀፅ 26 ምን ይላል?
26 የተመዘገቡ ባለሞያዎችን ስለመቅጠር
ለማንኛዉም ህንፃ ህንፃው ለሚገኝበት ምድብ የሚጠየቁ የዲዛይን አይነቶች ለየስራው በሚመጥኑ የተመዘገቡ ባለሞያዎች መሰራት አለባቸው፡፡ ዝርዝሩ ይህን አዋጅ ለማስፈጸም በሚወጣው ደንብ ይወሰናል፡፡ የሕንፃዉ ግ ንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስም የባለሞያዎቹ ቁጥጥር ሊኖር ይገባል፡፡ የሕንፃ ዲዛይኑን ቴክኒካል ስራ የሚያስተባብረው አርኪቴክቱ ይሆናል፡፡
ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ አዲሱ ማሻሻያ ረቂቅ በለሞያ የሚለውን በቀጥታ በድርጅት በመተካት አንዴት እንደተለወጠ እንመልከት:
19. የተመዘገበ አማካሪ ድርጅት ስለመቅጠር፡
ለማንኛውም ህንፃ ህንፃው በሚገኝበት ምድብ የሚጠየቁ የዲዛይን ዓይነቶች ለግንባታው በሚመጥን በተመዘገበ አማካሪ ድርጅት መሠራት አለበት፡፡ የህንፃ ዲዛይኑን ቴክኒካል ሥራ የሚያስተባብረው የዲዛይን ባለሙያ የምስክር ወረቀት ያለው ወይም አርክቴክቱ ነው፡፡ ዝርዝሩ ይህን አዋጅ ለማስፈፀም በሚወጣው ደንብ ይወሰናል፡፡ የህንፃው ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ የቁጥጥር ስራውን የሚያከናውነው አማካሪ ድርጅት የሥራ ተቋራጩን የግንባታ ባለሙያዎችንም ይቆጣጠራል፡፡ የግንባታ ሥራው ሲጠናቀቅ አማካሪ ድርጅት የፈረመበትና መጠናቀቁን የሚያረጋግጥ ምስክር ወረቀት ለተቋሙ መቅረብ ይኖርበታል፡፡
አማካሪ ድርጅት በባህሪው ተለዋዋጭ የሆነ ፤ ንግድን ማእከል አድርጎ የሚቋቋም ተቋም በመሆኑ ቋሚ በሆነ ህንጻ አዋጅ ውስጥ የሚታቀፍ አይደለም፡፡
ይህ ከባለሞያ ወደ ድርጅት እንዲዞር ተደርጎ የተቀረፀ የሕንፃ አዋጅ አደጋ ምንድን ነዉ? የሕንፃ ሙያ ልክ እንደ ህክምና ፡ እንደ ህግ ባለሞያ በህግ ሊጠበቅ የሚገባ የሙያ ዘርፍ ነው። ይሄ የሚደረገው ደግሞ ባለሞያውን ለመጥቀም አይደለም። በዋነኛነት ማህበረሰቡ ተገቢውን የሙያ አገልግሎት በትክክለኛው ባለሞያ እንዲያገኝ ለማድረግ ነው።
ከተሞቻችን የተሻሉ ከተሞችና ተወዳዳሪ፣ ጤናማና ደህነነታቸው የተጠበቁ ከተሞች እንዲሆኑ ለማድረግ አዋጁ ስራው በቀጥታ ባለሞያው እንዲሰራው መደረጉን ማረጋገጥ አለበት። ዛሬ የህንፃ ፡ የከተማ ጥራት ወድቋል ብለን የምናስብ ከሆነ ይህ አዋጅ ቢፀድቅ ደግሞ ጨርሶ ይሞታል።
አለም አንድ እየሆነች ባለችበት ፤ በስራ እና በንግድ የአለም ትስስር እየጨመረ በመጣበት በዚህ ዘመን ህጎቻችን ከአለማቀፍ ህግጋት ጋር መተሰሳር አለባቸው፡፡ የአለማቀፍ የህንጻ ኮድ ክፍል 107 እንዲሚያሳየው ሃላፊነቱን የሚሰጠው ለተመዘገበ ባለሞያ ነው፡፡በሁሉም የአለም ዙሪያ ብንሄድ የምናገኘው ይህንኑ ነው፡፡
በመሠረቱ በስራ ላይ ያለውን አዋጅ ለመቀየር የሚያስፈልግ ምንም ምክንያት የለም። አዋጅ እንደ መዋቅር ነው። ቋሚ የሆነ መርህን ተከትሎ የሚዘጋጅ ነው። መነካት አያስፈልገውም። መሻሻል የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ካሉ በደንቡ ላይ ወይም በመመሪየዎች ላይ መካተት ይችላሉ።
ረቂቁ በቅርቡ ለፓርላማ ቀርቦ ለከተማ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ቋሚ ኮሚቴ መመራቱ ይታወሳል፡፡ ቋሚ ኮሚቴውም ከዚያ በኋላ የዘርፉን ባለሞያዎች ጠርቶ ውይይት የተደረገበት ሲሆን የቀረቡትን ግብአቶች ለማካተት ከፍተኛ ፈቃደኝነት አሳይቷል፡፡
ይህ ማሻሻያ መሠረታዊ የመርህ መዛባት የታየበት በመሆኑ መስተካከል ይኖርበታል፡፡
https://t.me/engineer03