የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ቁጥራቸው 20 የሚሆኑ መምህራንን ለአንድ አመት አሰልጥኖ በከፍተኛ ዲፕሎማ ጥር 29 ቀን 2017 ዓ.ም አስመረቀ፡፡
በምረቃ መርሃ-ግብሩ ላይ ተገኝተው የከፍተኛ ዲፕሎማውን ሰርቲፍኬት የሰጡት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ፣ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ካስተላለፉ በኋላ፣ ስኬት ማብቂያ የሌለው የህይወት ጉዞ መሆኑን ገልጸው፣ "ይህንን ስልጠና በመውሰዳችሁ እንደ አንድ ምሁር ዋጋችሁን ከፍ አድርጋችኋል፤ አቅማችሁን ከፍ አድርጋችኋል፤ አቅማችሁ ከፍ ሲል ዋጋችሁም ከፍ ይላል፡፡" በማለት ተናግረዋል፡፡ አስከትለውም ስልጠናው ለዩኒቨርሲቲያችን መምህራን የማስተማር እና የምዘና ስነዘዴዎችን ዘመናዊ በሆነ ጥበብ እና ሳይንስን መሰረት በማድረግ መተግበር እንዲችሉ አቅም የሚፈጥርላቸው መሆኑን፣ በመማር ማስተማር ስራ ላይ ችግር ሲያጋጥም ችግሩን በምርምር ለመፍታት የሚያስችላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፕ/ር ፍቅሬ የትምህርት ሚኒስቴር በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የከፍተኛ ዲፕሎማ ስልጠና እንዲሰጥ ማድረጉን አስታውሰው፣ ስልጠናው እንዲሰጥ የተደረገበትን ምክንያት ሲያብራሩ "የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ እና ለማረጋገጥ ቁልፉ መምህር መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡" በማለት ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ተመስገን ቢረጋ የአካዳሚክ ጉዳዮች ዳይክቶሬት ዳይሬክተር በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በውስጥ አቅም የዛሬውን ጨምሮ በስድስት ዙር 156 መምህራንን አሰልጥኖ ያስመረቀ መሆኑን ገልጸው ይህ አሃዝ ከአጠቃላይ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ቁጥር 66% ያህሉ መሰልጠናቸውን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡ መርሃ-ግብሩም 290 ሰዓት የወሰደ እና አምስት ሞጁሎችን ያካተተ እንደነበርም አመላክተዋል፡፡ ዶ/ር ተመስገን አክለውም ዩኒቨርሲቲው ከኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር ጋር ከተፈራረማቸው የቁልፍ ተግባራት አመላካቾች መካከል አንዱ የከፍተኛ ዲፕሎማ ስልጠና በመሆኑ በተያዘው የትምህርት ዘመንም ለሰባተኛ ዙር 25 መምህራንን በመቀበልና በማሰልጠን ላይ መሆኑን ጠቅሰው ሰልጣኞቹም ስልጠናቸውን ሲያጠናቅቁ በተቋሙ ያሉ የከፍተኛ ዲፕሎማ ስልጠናው የወሰዱ መምህራንን ቁጥር ወደ 75 በመቶ እንደሚያደርሰው ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም የከፍተኛ ዲፕሎማ ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ወ/ሮ አበባ ስዩም ለፕሮግራሙ መሳካት ድጋፍ ያደረጉ አካላትን አመስግነው፣ የተመራቂዎቹን ዝርዝር በማቅረብ ሰርተፍኬት እንዲቀበሉ አድርገዋል፡፡