የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ማስጀመር ለትምህርት ጥራትና ንቁ ትልድ ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና እንዳለው የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ገለጸ።
በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ለቅድመ መደበኛ ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም በሰላም በር 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በዛሬው እለት በይፋ ተጀምሯል።
የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደ ማርያም ምገባው ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት በዞኑ በ42 ቅድመ አንደኛ ጣቢያዎች በማህበረሰብና በአጋር ድርጅቶች ድጋፍ ምገባ በሙከራ ደረጃ ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ተግባር መገባቱ አስታውቀዋል።
በዛሬው እለትም እንደ ዞን ወልቂጤ ከተማ ጨምሮ በምሁር አክሊል እና በገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ ምገባ ተጀምሯል።
አቶ መብራቴ እንደገለጹት አንድ አንድ ህጻናት ምግብ ሳይበሉ ወደ ትምህርት ቤት የሚገቡና ሲመልሱም ምግብ የማያገኙ እንዳሉ አመላክተው በዚህ ችግራቸው ትምህርት መማር አስቸጋሪ ነበር።
ስለሆነም ምገባው መጀመሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ፣ የትምህርት ጉጉት እንዲኖራቸው ከማድረጉም ባለፈ በትምህርት ውጤታቸው ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አንስተዋል አቶ መብራቴ።
ምገባው መጀመሩ ተማሪዎች ረጅም ሰዓት ሳይራቡ በትምህርት ቤት እንዲቆዩ ከማድረገም ባሻገር የትምህርት ፍላጎታቸው እንዲጨምር እና ቀጣይ ንቁ ትውልድ ለማፍራት ሚናው የላቀ ነው ብለዋል።
በመሆኑም በዛሬው እለት በወልቂጤ ከተማ የተጀመረው የምገባ ፕሮግራም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ተግባሩ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አቶ መብራቴ አሳስበዋል።
የወልቂጤ ከተማ ምክትል ከንቲባና የጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙባረክ ዘይኑ በበኩላቸው ለተማሪዎች ምገባ መጀመሩ የትምህርት ፍላጎታቸው እንዲጨምር፣ መጠነ መቅረት ከመቀነሱም ባለፈ መቀንጨርን በመቀነስ ጤናማ ትውልድ እንዲፈጠር ያደርጋል ነው ያሉት።
አክለውም በህጻናት ላይ የሚከሰቱ ተያያዥ በሽታዎች የመከላከል አቅም ይፈጥርላቸዋል ያሉት አቶ ሙባረክ ትምህርት ቤቱ ወቅቱን ታሪኩን የሚመጥን ተቋም ለማድረግ በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የወልቂጤ ከተማ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ስሜነሽ ግርማ የትምህርት መሰረት የሚጣለው ከቅድመ አንደኛ ጀምሮ ነው።ስለሆነም ለቅድመ አንደኛ ተማሪዎች ትኩረት መስጠት የትምህርት ውጤት እንዲሻሻል የማይተካ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም፦ለህጻናት ብሩህ አእምሮ ፣ለተሻለ የትምህርት አቀባበል እና ያለ እረሀብ ሰፊ ጊዜ እንዲማሩ ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል።
በከተማው በ3 ቱም ክፍለ ከተሞች ከ9 መቶ በላይ የቅድመ አንደኛ ተማሪዎች በዛሬው እለት ምገባ መጀመሩ አስገንዝበዋል።
ኃላፊዋ አክለውም ይህ የምገባ ፕሮግራም ደግሞ የተማሪ የምግብ እጥረት ችግሮችን በመቅረፍ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ቀጣይነት እንዲኖረው ከአጋር ድርጅቶች እና ከወላጆች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ገለጸው እገዛቸው እንዲያጠናከሩም ወ/ሮ ስሜነሽ አሳስበዋል።