ሰው ጉልበቱ የሚደክመው ልቡ ያየውን ያህል ነው፡፡ ወይም በሌላ አነጋገር መኪናችን የሚጓዘው እስከሞላነው ነዳጅ መጠን ነው፡፡ ረጅም ርቀት የሚወስደንን ያህል ከሞላን ረጅም ርቀት እንጓዛለን፤ አሳንሰን ሞልተንም እንደሆነ ያው አጭር ርቀት ያህል እንሄድበታለን፡፡
እንግዲያው በእውነት ከልባችን የምንፈልገው አንድ ወይም ብዙ ጉዳይ ምንድነው ይሁን? በእኔ በኩል ለሁለተኛ ጊዜ የመምህርን ጉባዔዎች የተመለከትኩት በልቤ ከነበረው ፍላጎት ጋር ነውና ዛሬ የመጣሁበትን ርቀት ያህል ወስዶኛል፡፡ መግቦኛል፡፡ መርቶኛል፡፡ ከልጅነቴ አንስቶ ወደ ሰዎች የሚከፈል አንዳችን ነገርን ማግኘት የውስጥ መሻቴ ነበር፤ እንዲሁ ከእኔ ዘንድ የነበረ ፍላጎቴ ነበር፡፡ ይህንንም አበርክቶ ባሉኝ የኪነ ጥበብ ዝንባሌዎች በኩል መግለጽ እፈልግ ነበር፡፡ ጽሑፍ፣ ሥዕል፣ ዜማ ወዳጆቼ ነበሩ፡፡ በተለይም ጽሑፍ የማዘነብልበት ነበር፡፡
ይህ ቅድሚያ በእኔ ዘንድ በመሆኑ ምክንያት የመምህርን ቪሲዲዎች ሳይ ከዚህ ፍላጎቴ ጋራ ነበር ማየው፡፡ ከልቤ መሻት ጋራ ነበር የምከታተለው፡፡ ከመክሊቴ ጋራ ነበር የማዳምጠው፡፡
ብዙ ሰዎች በበኩላቸው ዛሬም ድረስ የመምህርን ፕሮግራሞች የሚከታተሉበት ፍላጎት ለገጠማቸው ችግር መፍትሔ በመስጠት ላይ ተይዞ ይገኛል፡፡ #ፈውስን ማዕከል በማድረግ ሀሳብ ነው ብዙ ወንድም እህቶች የተዓሞረ ጽዮንን ፕሮግራሞች አሁንም ድረስ የሚከታተሉት፡፡ በመሆኑ ለመንፈሳዊ መንገዳቸው የሞሉት ነዳጅ እስከ ፈውስ ድረስ የሚወስድ ርቀት ነውና፣ እስከ ፈውሱ ድረስ ተጉዘው ከውስጣቸው ይቆማሉ፡፡ እስከጠየቁት ድረስ ነውና የፈለጉት እስከጠየቁት ድረስ አግኘተው በሥነ ልቦናቸው ያበቃሉ፡፡
ጉባዔው ዙሪያ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ ማንኛውም ሰው ለመታዘብ እንደሚችለው፣ አብዛኛው ሰው መፍትሔን ፍለጋ በመዳከር ሳለ ነው ሊሰባሰብ የቻለው፡፡ ምእመኑ ከመነሻው በልቡ ይዞት የመጣው ጥብቅ መሻት፦ የቸገረውን ቦታ ከመናፍስቱ ክፉነት አንጻር ገምቶ፣ ከችግሩ ቶሎ የመገላገልን ውጥን የያዘ ነው፡፡
ሕዝባችን ጤናውን አሞታል፤ ስለዚህ የሕመሙ ምንጭ እንደሆነ ካሰበው የመንፈሶች ተጽዕኖ ነጻ መውጣትን ይፈልጋል፡፡ ተጨባጭ የኑሮ በረከትን አጥቷል፤ ስለዚህ የተዘጋበት የበረከት በር እንዲከፈትለት ይፈልጋል፡፡ ቤተሰቡ ሰላም አጥቶበታል፤ ስለዚህ ሰላም ወደቤቱ እንዲመጣለት ይፈልጋል፡፡ ወዘተ...
ይህ የአብዛኛው ሰው እዚህ ትምህርት ዙሪያ የመጣበትና ያለበት መሰረታዊ ፍላጎት ነው፡፡
ለመሆኑ ይሄ ለምን ሆነ? የሰዉ ፍላጎት መፍትሔ ላይ ማተኮሩ ትክክል ነው? ወይንስ ጥፋት ነው? ወደሚሉ ጥያቄዎች ደግሞ እስቲ ከእኔው ታሪክ ጋራ እንሂድ፡፡ በርቱ!
፡፡ አይ ጎስቋላው ሥጋ!
በደንብ ካየነው እንደ ሥጋችን ያለ ቀንደኛ ጠላት ያለብን አይመስለኝም፡፡ የሚራበው እርሱ፤ የሚጠማው እርሱ፤ የሚታረዘው እርሱ፤ የሚታመመው እርሱ፤ ቶሎ የሚደክመው እርሱ፤ እረፍት የማይጠግበው እርሱ፤ ስለ መክሳት መወፈር የሚያስተክዘው እርሱ፤ ስለ መድረቅ መውዛቱ የሚያስጨንቀው እርሱ፤ ለሌሎች ሰዎች ተገልጾ የሚታየው እርሱ፤ የፍትወት ጥያቄ የሚወተውተው እርሱ፤ የገዛ ጀርባውን እንኳ ማየት የማይችለው እርሱ፤ እርጅና ከጉስቅልና ጋር የሚያገኘው እርሱ፤ .. ከሁሉ በላይ ግን ሞትን የሚሞተውም እርሱ! አይ ጎስቋላው ሥጋ!
መጽሐፍ እንደሚለው እርግጥም ሥጋ ደካማ ነው፡፡ (ማቴ. 26፥41) በዚያውስ ላይ በዚህ ጎስቋላ ሥጋችን ውስጥ በጎ ነገር እንዳይኖር እናውቃለን፡፡ (ሮሜ. 17)
ቁጭ ብለን ካስተዋልነው ብዙ ችግሮቻችን ከዚህ ከሥጋችን ድክመት የሚመነጩ ናቸው፡፡ እንደው ሌላ ሌላውን እንኳ ብንተወው፣ በሥጋችን ያለው የጤና ሁኔታና ሥጋችን የተሸከመው የሆድ ነገር የኑሮአችንን ግማሽ አይፈትነውም ብላችሁ ነው?
ሆዳችን እኮ የኑሮአችንን ግማሽ ይወስዳል፡፡ አንዳንዴ እንደውም ከዚያ በላይ ይወስዳል፡፡ ያው መቼም ወጥተን ወርደን የቀኑ መጨረሻ ላይ ዋናው ነገር መብል መጠጡ ነው፡፡ ነፍስ ያለ ሥጋ አትቆምምና ሕይወታችንን በሥጋ ለማቆየት ሥጋችንን ጠዋት ማታ እንመግበዋለን፡፡ ከዚህ ነገር የተነሳ አበው 'የሥጋ ሕይወቱ መብል መጠጥ ነው' ይላሉ፡፡ ያው ስለምንበላ ስለምንጠጣ ነው ሰውነታችን የሚኖረውና የሚቆየው፡፡ በመሆኑ ጠዋት ማታ ተከታትለን እንቀልበዋለን፡፡
ዝም ብላችሁ ካያችሁት እኮ ኑሮአችን የሆዳችን ጉድጓድ ውስጥ ተጥሎ ታያላችሁ፡፡ የዓለማችን ብዙዉ ትርምስና ምልልስ ይኸው የፈረደበት እንጀራ ዙሪያ አይደለምን? ሆዳችን የገዛ እስር ቤታችን ይመስላል፡፡
አስቡት እስቲ ሰው የማይራብና የማይጠማ ለሰውነቱም እንጀራ የማያስፈልገው ቢሆን ኖሮ፡፡ ሙሉ ለሙሉ የሚባል የአኗኗር ለውጥ ይኖረው ነበር፡፡ ከእንጀራና ተያያዥ ጉዳዮቹ ተጽዕኖ ሁሉ ነጻ ይሆን ነበር፡፡ ስለ እንጀራ አብዝቶ የሚደክምበትን ጉልበትና ጊዜ ለሌላ ብዙ ነገር ያውለው ነበር፡፡
ይህን የምልበት ዋና ምክንያት ምን ያህል በሥጋችን ውስጥ ታሽገን እንደምንኖር መረዳቱ እንዲኖረን ስል ነው፡፡ ሰዎች መላ ዘመናችንን የማይጠረቃውን የሥጋ ጥያቄዎች ስለመመለስ መዳከራችንን እንድናስተውል ነው፡፡ ነገርየውን ቁጭ ብሎ ለሚያውጠነጥን ሰው፥ ሥጋ ላይ ወድቀን እንደምንኖር የሚሰወረው አይደለም፡፡
በተለይ ደግሞ እንደኛ ባሉ ደሃ ሀገራት ላይ እነዚህ የሥጋ ጥያቄዎች ከጥያቄነት አልፈው የመኖርና ያለመኖር ግብግቦችም ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ዋና ዋና ፍላጎቶች የሚባሉት የሥጋ ውትወታዎች፣ እንደ እኛ ባሉ ሀገራት ውስጥ በበቂ ሁኔታ የተመለሱ አይደሉምና ታላቅ ትንንቅ ውስጥ ስለመሆናችን ብዙዎቻችን የምናውቀው ነን፡፡ አፍሪካ ውስጥ ትምህርትና ሥራ ማለት፣ የእንጀራን የተፈጥሮ ጥያቄ ስለመመለስ የሚደረጉ አድካሚ ትግሎች ናቸው፡፡ በሌላ አባባል በእዚህች አህጉር ውስጥ ያለን ሕዝቦች የምንማረውና የምንሠራው መሠረታዊ የኑሮ ፍላጎቶችን ስለመመለስ ተጨንቀን ብቻ ነው፡፡
እርግጥ ነው ያደጉ በሚባሉ ሐብታም ሀገራትም ውስጥ የሥጋ ጥያቄዎች አሁንም የሰውን ልጅ ከመወትወት ያቋረጡ አይደሉም፡፡ መሠረታዊ የሚሰኙትን የእንጀራና የመኖሪያ ቤት ጉዳዮችን እንኳ በተሻለ ደረጃ ለዜጎቻቸው መልሰዋል በሚባሉ "ባለጸጋ" ሀገራትም ውስጥ፣ ሥጋ በሌሎች ጥያቄዎቹና መሻቶቹ በኩል መጨቅጨቁን እንደቀጠለ ይገኛል፡፡
እንግዲህ በጥቅሉ ዋናው ሀሳብ የሰው ልጆች ሥጋችን ላይ ወድቀናል ከሚለው እውነት ጋር የሚገኝ ነው፡፡ የሰው ልጆች ሥጋችን ውስጥ ታጥረናል፤ ወይም ደግሞ ሥጋችን ውስጥ እንደታጠርን ሆኖ ይሰማናል፡፡ ይሄ ሁነት ያበሳጫቸው የሚመስሉ አንዳንድ ተናጋሪዎች፥ 'የሰው ልጆች እኮ ሥጋ ላይ ተውርወረናል' ይላሉ፡፡ እውነትም የዚህ ዓለም ኑሮአችን በጠቅላላ ሥጋችንን የሚመለከት ሆኖ እናየዋለን፡፡ ሥጋን በማብላት፣ ሥጋን በማጠጣት፣ ሥጋን በማልበስ፣ ሥጋን በማጠብ፣ ሥጋን በማስዋብ፣ ሥጋን በማሳረፍ፣ ሥጋን በማስደሰት፣ ... ተግባራት መላው ዘመናችንን ተጠምደን እንመላለሳለን፡፡
የሚያሳዝነው ደግሞ እንደዚህ መላ ዘመናችንን የሚያባትለን የሥጋ ነገር ሞልቶ የሚጠናቀቅ ጉዳይ አለመሆኑ፡፡ ሥጋ ሁሌ ጎዶሎ ነገር አለው፡፡ ሁሌ ጠያቂ ነው፡፡ አሁን እንበላለን፤ ሳይቆይ እንራባለን፤ አሁን እንጠጣለን፤ ወዲያው እንጠማለን፤ አሁን እናርፋለን፤ ሳይዘልቅ እንደክማለን፤ በተደጋጋሚ እንታመማለን፤ በተደጋጋሚ እንጎሰቁላለን፤ በተደጋጋሚ የሥጋ ችግር ውስጥ እንገባለን፡፡ ማሕበረሰባዊ ብሂላችንን 'ዓለም ዘጠኝ ናት፤ ከቶውን ዐሥር አትሞላም' ያሰኘው፥ ይሄው የሥጋ ነገር አይደለም ብላችሁ ነው?
ይቀጥላል ...