የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች ከዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ጋር ዛሬ ታኅሣሥ 29/2017 ዓ/ም የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓልን አክብረዋል፡፡
ከፍተኛ አመራሮቹ ተማሪዎች ከወላጆቻቸው ርቀው በትምህርት ላይ ስለሚገኙ ብቸኝነት እንዳይሰማቸው እና ከተማሪው ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ስኬታማ የመማር ማስተማር ሒደትን ለማስፈን በዓሉን በጋራ ማሳለፋቸውን ገልጸው ለተማሪዎች፣ ለወላጆቻቸው፣ ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ የመልካም ምኞት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንት ተማሪ ሶፎኒያስ ፈንቴ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች በዓሉን ከተማሪው ጋር ማሳለፋቸው ቤተሰባዊ መንፈስ እንዲዳብር የሚያስችልና በተማሪዎች በኩል መነቃቃትና የተሻለ ስሜትን የሚፈጥር መሆኑን ገልጿል፡፡ ተማሪ ሶፎኒያስ በቀጣይም በመማር ማስተማርና በሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ተማሪዎችን በመጎብኘትና የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን በመፍታት ለተማሪዎቹ ስኬታማነት የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ አጽንኦት የሰጠ ሲሆን ተማሪዎችም የዩኒቨርሲቲውን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሒደት ከማስጠበቅ ባሻገር ዩኒቨርሲቲው በሚያደርገው ራስ ገዝ የመሆን ጉዞ የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡
ተማሪዎቹ በዓሉን በድምቀት እንዲያከብሩ ከዝግጅት ጀምሮ ሥራዎች መሠራታቸውን የገለጹት በዋናው ግቢ ተማሪዎች አገልግሎት ምግብ ዝግጅትና መስተንግዶ አስተባባሪ አቶ ሸዋንግዛው ታደሰ ለተማሪዎችና ለወላጆች መልካም የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል እንዲሆንላቸው መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተማሪዎች አገልግሎት ምግብ ዝግጅትና መስተንግዶ ክፍል ሼፍ ወ/ሮ ውድነሽ ተረፈ በበኩላቸው ከዋዜማው ጀምሮ በቂ ዝግጅት በማድረግ ከተማሪዎች ጋር በዓሉን ማሳለፍ መቻሌ ደስታን ፈጥሮልኛል ብለዋል፡፡ ‹‹እኛም በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ልጆች አሉን›› ያሉት ወ/ሮ ውድነሽ ተማሪዎች በመልካም ስሜት በዓሉን እንዲያሳልፉ ተመኝተው የእንኳን አደረሳችሁ ልባዊ ምኞታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የ5ኛ ዓመት የኤሌክትሪካል ምኅንድስና ፋከልቲ ተማሪ ማሺን ዊዩዓል የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ከእኛ ጋር በመሆን የቀመስነውን ቀምሰው ማየት መቻሌ በእኔና በዩኒቨርሲቲው መካከል የተሻለ ግንኙትን መኖሩን ማሳያ ምልክት ሆኖ አግንቼዋለሁ ብሏል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት