Tesfaye Gabbiso @tesfayegabbiso Channel on Telegram

Tesfaye Gabbiso

@tesfayegabbiso


A pastor at Hawassa Mulu Wongel Church and a gospel singer (Ethiopia)

ተስፋዬ ጋቢሶ (Amharic)

ተስፋዬ ጋቢሶ ከሀዋሳ ሙሉ ወንጌል በተለምከተ ሀገር አሰራር ስሜት ውስጥ ጥሩ ታዝዝዝ ሁን እና ትራንስ፡፡ ይህ ተስፋዬ በተናገር ከዚህ ህዝብ ጋር ለወጣቶች አደጋ ያለው የደረሱ ነገሮች እና አስመዝግቡት ሰይጣን ነው። ትምህርት፣ የግል መሻሻል እና ምክር ጥያቄዎች እንዲሆኑ እና መዝገቡ እንዲጠበቅልል ሲሆን፣ ሌሎች የደብዳቤዎችም እንዲጠበቁ መሆኑን አስቀድሞ ስለነፃፀሙ የተባለውን ታገዱ። ተስፋዬ ጋቢሶ አስተያየቷ ስለ የሀዋሳ ሙሉ አምላክ ቤተሰብን እና የሰማ ታማኝ ድምፅ እንዲደርሰው ውደቁ።

Tesfaye Gabbiso

20 Nov, 14:01


https://youtu.be/lUBRCLYm-8g?si=XZhuaQ-wStmkyVJp

Tesfaye Gabbiso

04 May, 07:48


https://www.youtube.com/watch?v=oVICuYZSi1M

Tesfaye Gabbiso

15 Apr, 19:53


«ሁል ጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ» (ፊል 4፡4)

ይህ ዛሬ ማታ በቤታችን የጸሎት ጊዜ የተካፈልነው ቃል ነው። ይህን መልዕክት የጻፈው ሐዋርያው ጳውሎስ ሲሆን፥ የተጻፈላቸው የፊልጵስዩስ ምእመናን ነበሩ። ጳውሎስ ደስታ ከማይሰጥ እስር ቤት ሆኖ፥ በመከራ ውስጥ እያለፉ ጌታን በማገልገል ላይ ለነበሩት፥ በጌታ ደስ ይበላችሁ በማለት ጻፈላቸው። ይህን ዓይነት ደስታ ለራሱም እየተለማመደ ነበር ። (ፊል 1፡18፥2፡17) በሁኔታ ሳይሆን በጌታ ደስ መሰኘት ይቻላል ማለት ነው። ጌታ ኢየሱስ የደስታችን ምንጭ ነው።

ከዚህ ምንጭ ለመቅዳት የጸሎት ልምምድ አስፈላጊ ይሆናል።(4፡6)ምልጃና ምስጋና የተካተተበት ጸሎት መጨነቅን በማስወገድ በጌታ ደስ ለመሰኘት ያግዛል። ደስታው ወደ ዝማሬም ይመራናል።(ያዕ 5፡13)

እውነተኛ፥ ዘላቂና ንጹሕ የሆነ ደስታን ከሌላ ቦታ በመፈለግ አንባክን። ከኢየሱስ ጋር እንጣበቅ። ሁል ጊዜ በጌታ ደስ ይበለን። ደስታው መቋቋሚያ ሃይላችን ይሆናል።

በጸሎታችን ማብቂያ ደግሞ ወንድማችን ገዛኀኝ ሙሴ የዘመረውን መዝሙር አብረን አዜምን። መዝሙሩ ከዚህ በታች ያለው ነው፦

ልቤ ሲያስብህ፥ ልቤ ሲያስብህ፥
ልቤ ሲያስብህ ረካ
የደስታዬ ምንጩ ኢየሱስ፥ ሰላሜ አንተ ነህ ለካ!

Tesfaye Gabbiso

31 Mar, 07:00


ውድ አንባብያን፦ የጌታ ሰላም ይብዛላችሁ።

አምልኮና ዝማሬን በሚመለከት፣ የጌታን ቃል መሠረት በማድረግ፣ ከተሞክሯችንም በማያያዝ፣ አንዳንድ አሳቦችን በመካፈል እስከ አሁን አዘገምን። ዓላማው ለእግዚአብሔር ክብርን፣ ለምዕመናን መታነጽን፣ በክርስቶስ ላላመኑት የመዳንን ዕውቀት ለማምጣት የሚያግዝ አገልግሎት በተሻለ መንገድ እንዴት ማበርከት እንደምንችል መመካከር ነው። አሳቦቹን በግል በማሰላሰል፣ በዝማሬ ከሚያገለግሉ ባልንጀሮችም ጋር በመወያየት፣ ዕውቀታችሁን እንዳዳበራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። ከዚህም በኋላ፣ በማከታተል ባይሆንም፣ በአምልኮ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ከተማርኩት ማካፈሌ፣ ጌታ በረዳኝ መጠን የሚቀጥል ይሆናል። ለዛሬ ያለኝ ከዚህ በታች የቀረበው ነው። ርዕሱም እነሆ፦

የምናመልከውን እንወቀው

(ዮሐ 4:22)

"እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን።" ይህ ጌታ ኢየሱስ በአምልኮ ውይይት መካከል ለሳምራዊት ሴት የነገራት እውነት ነው። ማወቅ ማምለክን መቅደም እንደሚገባው ከዚህ ንግግሩ እንረዳለን።

ማወቅ መለየት ነው። መገንዘብና ማረጋገጥም ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ፣  በዕውቀት ስለ ማምለክ፣ ሶስት እስፈላጊ ጉዳዮችን ቀጥለን እንመለከታለን።
           
1. ልናውቀው የሚገባን አምላክ

- አባቶች፣ እነ አብርሐም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ፣ አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች፣ የቀድሞ ነቢያትና ሐዋርያት ያመለኩት  እውነተኛ፣ ሕያውና ዘላለማዊ ነው። እርሱም የፍጥረተ -  ዓለም  ሁሉ ባለቤት፣  የምድር ሁሉ ፈራጅ (ገዥ)፣ (ዘፍጥ 19፡25) ይህ አምላክ አባቶች ባመለኩበት መንገድ ሊመለክ የሚገባው፣ በሕያውነቱ ለሙታን ሕይወትን የሚሰጥ፣ የሕይወት ውኻ ምንጭም የሆነ  አምላክ ነው።  (ዮሐ 4: 14 ።  ኤር 2:13 )

- መንፈስ ነው - ሰማይና ምድርን የሞላ፣(ኤር 23:24)  "ሰማይ ከሰማያትም በላይ ያለ ሰማይ ይይዘው ዘንድ" የማይችል (2 ዜና 6:18) እጅግ ትልቅ አምላክ፣ አንድ ሥፍራ፣ ተራራም ሆነ ከተማ የማይወስነው፣ በአንድ ጊዜ በሁሉ ሥፍራ ሊገኝ የሚችል፣ በመንፈስም የሚመለክ ነው።(ዮሐ 4:24)

- ነጻ የሚያወጣ እውነተኛና የእውነት አምላክ ነው። እንደ ቃሉ፣ ያለ ማስመሰል- ከልብ፣  በእውነትም መመለክ የሚገባው።

- በፈቃዱ ራሱን ለፍጥረቱ  የገለጠና የሚገልጥ የፍቅር  አምላክ ነው።  ለአባቶች፣ ለእስራኤል ሕዝብ፣ ለነቢያት፣ ለሐዋርያት ለቤተ ክርስቲያን ራሱን ገልጧል።

ልናመልከው የሚገባን ለእነዚያ አባቶች ራሱን የገለጠውን አምላክ እንጂ ከዚህኛው የተለየ እንግዳ አምላክ አይደለም።

2. የማወቅ አስፈላጊነት
ወደ ስሕተትና ወደ ጥፋት ከሚመራ አለማወቅና ከተሳሳተ አምልኮ ለማምለጥ - እግዚአብሔር  "ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቷል"  ብሏል። (ሆሴዕ 4:1-6) እውቀቱ የእግዚአብሔር ነበረ። ከእውነት ዕውቀት ተነሥቶ ለማምለክ ማወቅ አስፈላጊ ነው። የምናመልከውንና የምናገለግለውን፣ የምንገዛለትን ጌታ ለይተን ማወቅ ያስፈልገናል።  ጌታ ኢየሱስ፦ "እኛ ለምናውቀው እንሰግዳን" አለ፣ የሰማርያ ሰዎች፦ "እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት  ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን" በማለት መስክረዋል። (ዮሐ 4:42) የእኛስ አምልኮ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ይሆን?

3.  የማወቂያ መንገዶች -  እግዚአብሔርን ልናውቀው እንችላለን። ከላይ እንደተመለከትነው፣  እግዚአብሔር ራሱን የገለጠና የሚገልጥም አምላክ ነው።

- በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል(1:14-18) እግዚአብሔርን "አንድ ልጁ እርሱ ተረከው።"
      
- መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠን የዕውቀት ብርሃን (ኤፌ 2:18-19) "የመገለጥ መንፈስ" የሆነው መንፈስ ቅዱስ አንዱ ሥራው የልባችንን ዓይኖች እያበራ የከበረውን ክርስቶስ ማሳየት ነው። ጌታ ኢየሱስ፦ "እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል" ስላለ። (ዮሐ 15፡26)

- በቅዱስ ቃሉም በኩል እግዚአብሔርን ማወቅ ይቻላል።  ተጽፎ የተሰጠን የእግዚአብሔር እስትንፋሳዊ ቃል ከእግዚአብሔር ማንነትና ሥራ ጋር ያስተዋውቀናል።

- የእጁን ሥራ በመመልከት - "ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል" (መዝ 19:1-2 ) ኒቆዲሞስን ጌታን ወደ ማወቅ የመራው የጌታን ሥራ ማየቱ ነበረ።(ዮሐ 3:2)
 
አንድ ዕድሜ-ጠገብ የሆነ ዝማሬ የሚከተለውን ይላል፦

          "ጌታ አምላኬ እንዴት እገረማለሁ፣
            ሳስብ ሳለሁ የእጆችህን ፍጥረት፣
             ከዋክብትን ሳይ ነጎድጓድን ስሰማ፣
            የአንተ ሥልጣን በሕዋ ውስጥ ታየኝ"

- በጸሎት አማካይነት - መጸለይ ከጌታ ጋር መነጋገር ነው።  የሳምራዊቱ ሴት ዕውቀት የተገኘው በዚህ ንግግር ውስጥ ነው። በመነጋገር ውስጥ መጠየቅ፣ በመጠየቅም ማወቅ አለ። በመጸለይ፣ ጌታን በመጠየቅ፣ ጌታን ወደ ማወቅ የደረሱ አሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ሌላው ምሳሌ ነው። "ጌታ ሆይ፥ ማን ነህ?" በማለት ጠየቀው። ጌታም ራሱን በሚገባ ገለጠለት(የሐዋ 9:5)

በሰው ሁሉ ውስጥ የማምለክ ረሃብ አለ። ይህን ረሃብ ለማስታገስ ሲል አምላክ መስሎ የታየውን ሁሉ ያመልካል። ፈጣሪውን ሳያውቅ ሲቀር  የተፈጠረውን ያመልካል። (ሮሜ 1:25) ብዙ ጊዜም በራሱ አእምሮ ወይም እጅ አማልክቱን ይቀርጻል።  ሳምራዊያን ለማያውቁት ይሰግዱ እንደነበረ ጌታ ኢየሱስ ተነገረ።  የአቴና ሰዎች በአንድ መሠዊያቸው ላይ "ለማይታወቅ አምላክ" የሚል ጽሑፍ አኑረው ነበረ። (የሐዋ 17:22-30)

ሰው የእግዚአብሔርን ዕውቀት ከማጣት የተነሣ ስቶ ሊጠፋ ይችላል።(ሆሴዕ 4:6) እየተጎዱም ቢሆን፣ ሳያውቁ፣ አጋንንትን የሚያመልኩ ነበሩ፤ ይኖራሉም። መጽሐፍ ቅዱስ "የአሕዛብ አማልክት አጋንንት ናቸው" ይላል። (1ቆሮ 10:20) ይህ አሳሳቢ የሆነ እውነት ነው። በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ ከአጋንንት እስራት የተፈቱ አጅግ ብዙ ምስክሮችም በዓለም ላይ አሉ። አንዳንዶቹ ምስክሮች  ወላጆቻችንና የቅርብ ቤተ ዘመዶቻችን ናቸው።

ከእውነተኛው አምላክ ጋር መተዋወቅ ነጻ ያወጣል። እኛም ከኃጢአትና ከዘላለም ሞት፣ ከጨለማውም ሥልጣን - ከዲያብሎስ አገዛዝ ባዳነን፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ተገልጦልን የወቅነውን እውነተኛ አምላክ ለማምለክ በቅተናል። ስሙ የተመሰገነ ይሁን። (ዮሐ 14:6።ዕብ 10: 19-20 )

እንግዲህ፣ በእግዚአብሔር እውቀት እያደግን፣ በዕውቀትም ላይ ዕውቀትን እየጨመርን በታላቅ አክብሮትና በፍቅር፣ በታማኝነትም እናምልከው። "ለምናውቀው እንሰግዳለን" ለማለት እንድንችል።

ከብርና ውዳሴ፣ ስግደትና ዝማሬ ራሱን በፍቅር ለገለጠልን፣  በአንድያ ልጁ በክርስቶስ ደም ለዋጀን፣ በመንፈሱም ላተመን፣ ለታመነው የቃል ኪዳን አምላክ፣ ለእግዚአብሔር ይሁን።
     

Tesfaye Gabbiso

24 Mar, 04:29


ለግልና ለሕብረት መዘምራን የሚጠቅሙ ጥቂት ምክሮች፡-     
(ካለፈው የቀጠለ)

9. ከጠፊ ገንዘብ ይልቅ የተገልጋይን ነፍስ ለክርስቶስ ገንዘብ ለማድረግ መትጋት - ገንዘብ መገልገያ ብቻ ነው፤ በፍቅሩ ከተያዙና ከተሸነፉለት ግን ገዢና ተቆጣጣሪ ጌታ ይሆናል። ገንዘብ ራሱ ባይሆንም፣  የገንዘብ ፍቅሩ የክፋት ሁሉ ሥር እንደሆነ በቅዱስ ቃሉ ተነግሮናል። ምኞቱና ፍቅሩ ብዙዎችን ከእምነት አሳስቶ  በብዙ ስቃይ  ራሳቸውን እንዲወጉ ማድረጉንም ነግሮ ያስጠነቅቀናል። (2 ጢሞ 6:10) ሣር ሣሩን እያየ ገደል እንደሚገባ በሬ መሆንም አለ። "የለመኑትንም ሰጣቸው፣ ለነፍሳቸው ግን ክሳትን ላከ።" የሚለውንም እንዘንጋ። (መዝ 106:15) በአገልግሎታችን ነፍስን ለማትረፍ የምናልም፣ የምንጸልይና የምንተጋ እንሁን። እኛ የክርስቶስ ኢየሱስን ስፈልግ እርሱ፣ የምንፈልገውን ሁሉ ባይሆንም፣ የሚያስፈልገንን ሁሉ ይሞላብናል። (ፊል 4:19) ምስጢሩ  ያለው በእርሱ ላይ ሙሉ በሙሉ ተደግፎ በመኖር ውስጥ ነው። ከገንዘብ ፍቅር ወጥመድና ጠንቅ እየተጠበቅን እናገልግል።

10. የአገልግሎትን ተደጋጋፊነት መገንዘብ - የዝማሬ አገልግሎት ብቸኛ አይደለም። ዝማሬ፣ በቤተ ክርስቲያን አመራር፣ በቃሉ አገልግሎት፣ በምልጃ ጸሎትና በመሳሰሉት መካከል የቆመ አገልግሎት ነው። አንዱ ሌላውን ይደግፋል።

ለሁሉም  ያለኝ አጠቃላይ ምክር፣ መሪዎች በማስተማርና በመምከር፣ በማረምና በተለያየ መንገድ በማበረታታት፣ ማላጆችም በጸሎታቸው በመደገፍ፣ ዘማርያንም በመማር፣ በመመከር፣ መልካም ምክርን ተግባራዊ በማድረግ፣ በመጸለይና ተጠያቂነትን በመለማመድ ቢተጉ የአገልግሎት ፍሬያማነት ይጨምራል የሚል ነው። የአምላካችን የእግዚአብሔር ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን።

Tesfaye Gabbiso

17 Mar, 04:50


ለግልና ለሕብረት መዘምራን የሚጠቅሙ ጥቂት ምክሮች፡-     
(ካለፈው የቀጠለ)

5. ጠንካራ ዝማሬዎችን ስለ መጻፍ - ጠንካራ ዝማሬ ቅዱስ ቃሉን መሠረት የሚያደርግ፣ ክርስቶስን በማዕከላዊነት የሚያሳይ፣ በመንፈስ ቅዱስ ሙላትና በእምነት የሚዘመር፣  ሕይወትን የሚሞግትና የሚለውጥ፣ ዘመንና የቦታ ርቀትን አቋርጦ የሚሔድ ነው። ለዚህ ደግሞ  መሠረቱ በቂ የሆነ ጸሎትና የቅዱስ ቃሉ ምግብ  ነው። ቃሉን ተመግቦ መጠንከር ጠንካራ መልዕክትን ለመጻፍና ለመዘመር ያዘጋጃል።  "የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና  ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምሕርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።" (2 ጢሞ 3:16-17)

6. የቋንቋ ዕውቀትና የጽሑፍ ክህሎትን ለማሳደግ በጥራት የሚጽፉ ሰዎችን ሥራ በስፋትና በእርጋታ ማንበብ፣

7. አስቀድሞ በሌሎች የተዘመሩ ዝማሬዎችን ሲዘምሩ - ይዘት፣ ቅርጽና ዓላማቸውን መጠበቅ - በተቻለ መጠን፣ ቃላትና ዜማ ሳይዛቡ ቢዘመር ይመረጣል። ከጉባዔ ላይ አጠቃቀም ባለፈ፣ ታስቦበት ሲታተምና ወደ ሚዲያ ሲወሰድም በዓላማውና በአስፈላጊው ሒደት ላይ ከሚመለከታቸው ጋር መማከር ቢኖር መልካም ይሆናል።

8. ከእግዚአብሔር ክብር በስተቀር ለራስ ስምና ዝና አለመጨነቅ

(ይቀጥላል)

Tesfaye Gabbiso

09 Mar, 18:27


ለግልና ለሕብረት መዘምራን የሚጠቅሙ ጥቂት ምክሮች፡-    
 
(ካለፈው የቀጠለ)

3. በመሰጠት ማገልገል (ሮሜ 12:1-2)
በመሥዋዕትነት ማገልገል ለማለት ነው። መሰጠት የሚጀምረው ከእግዚአብሔር ፊት ነው። ለእግዚአብሔር የተሰጠ ለሰው መሰጠት አይቸግረውም። መሰጠት ለሰው የገቡትን ቃልና ቀጠሮ በማክበር ይገለጣል። ከሚጠበቁበት ቦታ አለመታጣት፣ አርፍዶ ሳይሆን ቀድሞ ለመድረስ መትጋትም ነው።

ለእኛ ለአገልጋዮች ከገጠሙን ከዘመኑ ከባድ ፈተናዎች መካከል አለመሰጠት ይገኛል። የፈተናው መነሻ (ሰበብ) ይለያያል። ለተፈለግንለት ጉዳይ የምንሰጠው የክብደት መጠን፣ የሥራ ብዛት፣ የድንገተኛ እክሎች ማጋጠምና መደራረብ፣  የታወቀና  ያልታወቀ ቅሬታ ወዘተ. ሊሆኑ ይችላሉ። ከአቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ እውነተኛና አሳማኝ ምክንያት በማቅረብ ይቅርታ መጠየቅ ተአማኒነትን ያስጠብቃል። ከሁሉ በላይ፣ የልብ ታማኝነት፣ መሰጠትን ለመለማመድ መሠረታዊ ነው።

ሙሉ የሆነ መሰጠት መሥዋዕትነትንና ሞትን ይጠቁማል። ጌታ ኢየሱስ ቀዳሚው ምሳሌያችን ነው። "የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች።" ያለም እርሱ ነው። (ዮሐ 12: 24) ሐዋርያው ጳውሎስ ሞታችኋልና.... ይላል። (ቆላስ 3:3) ይህ  በሌለበት የግልም ሆነ የጋራ አገልግሎት በእጅጉ ይጎዳል። ፍሬውም እየቀነሰ ይሔዳል። ሙሉ የሆነ መሰጠት ለፍሬያማነት ይጠቅማል። በአገልግሎታችን የምንደክመውስ ፍሬ ለማየት አይደል? በመሰጠት እናገልግል።

4.  የዝማሬ መልእክቶች ሲኖሩ ያለ ጥድፊያ በሥርዓቱ ማዘጋጀት- የእግዚአብሔር ሥራ ክቡር ነው። በ"ይድረስ ይድረስ" ሊሠራ አይገባውም። በመሆኑም ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄን ይጠይቃል።

በዝማሬ ዝግጅት ወቅት ለይዘትና ቅርጽ ተገቢ ትኩረት  መስጠት  ያስፈልጋል-  ይዘት የምንለው መልዕክቱን ነው። በዜማ ለምናቀርበው መልዕክት መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ መሆን አለበት። ቤተ ክርስቲያን በምድር ያለችው ቃሉን ለማገልገል ነው። ሐዋርያቱ እነ ጴጥሮስና ጳውሎስ ቃሉን ነበር ያገለገሉት።(የሐዋ 6፡4) ለተተኪ አገልጋዮች የሰጡት አደራም "ቃሉን ስበክ" በሚል የተገለጠ ነው።(2 ጢሞ 4፡2)

የመጀመሪያዎቹ የቃሉ አገልጋዮች በዋናነት ክርስቶስን ሲሰብኩ ቀድሞ በእጃቸው የገባውን ቅዱስ ቃሉን እየጠቀሱ በማብራራት ነበረ።(የሐዋ 2: 16-35) እኛም በዜማ የምናስተላልፈው መልዕክት በቃሉ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ለማረጋገጥ በተረጋጋ ሁኔታ መዘጋጀትን መልመድ ይኖርብናል። የቃሉ (የወንጌሉ) መልዕክት ዋና ይዘቱ - ክርስቶስ ነው።

የአስተምህሮን ቅንነት ለመጠበቅ፣ ለጽሑፍ ውበትና ለዜማ አዲስነትም መጠንቀቅ ያስፈልጋል። እዚህ ላይ፣ ውበትና አዲስነትን ቅርጽ ልንላቸው እንችላለን። ይህ ሁሉ ከጥድፊያ ነጻ መሆንና መታገሥን ይጠይቃል።

     (ይቀጥላል)

Tesfaye Gabbiso

03 Mar, 07:03


ለግልና ለሕብረት መዘምራን የሚጠቅሙ ጥቂት ምክሮች፡-
1.  ሕይወትን የሚያዳብሩ በቂ የሆኑ የግል
ጊዜያትን መውሰድ - ለግላዊ ጸሎትና አምልኮ
- በግል የማንለማመደውን አምልኮ በጉባኤ
ለማሳየት መምጣት የለብንም። ይህ ጌታ ኢየሱስ
        የነቀፈው ታይታዊነት (ፈሪሣዊነት) ስለሚሆን ነው።
(ማቴ 6: 1-7)
      - ለግላዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብና ጥናት ጊዜ
መመደብ ያስፈልጋል።
       - ዝማሬያችንም ሆነ በሌላ መልክ የምንገልጠው
አምልኮ መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ (የእግዚአብሔር
ቃል መሆኑ እየተረገጠ መቀጠል አለበት።
      - በዚህ ሕይወታችን ይገነባል። የምንጽፈውም
ሆነ የምንዘምረው መጽሐፍ ቅዱሳዊነትን የተከተለ
እንዲሆን ለማድረግ ይረዳል።

2. ራስን  በእረኝነት ጥላ ሥር ማኖር - ይህ የጥበቃን አገልግሎት የማግኘት ና
         ተጠያቂነትን የመለማመድ ጉዳይ ነው።
       - በመማር፣ በመመከር፣ በመታረም፣ በተጠያቂነት
ልምምድ፣ የሕይወት ክብካቤን መቀበል
በመንፈሳዊ ጤንነት ለመዝለቅ
ይጠቅማል።
       - የአገልጋይነት ዝንባሌን ለማሳደግ
(ዝንባሌው የትሕትና ነው።)
       - የቡድን መዘምራን የተጠያቂነት ችግር
ላይኖርባቸው ይችላል፤ ቡድኑ የአባሉ ጠባቂ
ስለሚሆን።
       - የተጠያቂነት ፈተና የሚጠነክረው በግላዊ
የአገልግሎት እንቅስቃሴ ውስጥ ነው።
       - ያለ ተጠያቂነት መመላለስ፣ ነጻነትን ከልክ
በላይ እያስወደደ ወዳልታሰቡ የኃጢአት
ወጥመዶችና ባርነቶች ውስጥ ያስገባል።
በወንጌል ነጻ የወጣነው ከአመጽ ነው።
ለማመጽ አይደለም።
ለአገልጋዩ ለጢሞቴዎስ የተሰጠው ምክር
ለሁላችንም የሚጠቅም ነው። "የጌታን ስም
የሚጠራ ሁሉ ከአመጽ ይራቅ...." (2 ጢሞ 2:19)
       - ተጠያቂነትን መለማመድ እንደ ልጓምና
በተሽከርካሪ ውስጥ ስንሆን እንደምንጠቀምበት የደኅንነት ቀበቶ ያገለግላል።
         ሁለቱም የተሠሩት እንቅስቃሴን ለማስቀረት
አይደለም። ከአደጋ እየተጠበቁ በደኅና ለመጓዝ
ነው እንጂ።
       - ልጓም በአስፈላጊ ቦታ ላይ ከእንቅስቃሴ
ለመገታትም ያገለግላል።
         በአስፈላጊው ጊዜ ያዝ እያደረጉ የሚያስቆሙን
እረኞች ያስፈልጉናል።
       - ይህ የእረኝነት አገልግሎት በመፈለግና በመቀበል
ውስጥ ይገኛል።
       - ጌታ የሁላችንም እረኛና ጠባቂ ነው። የእረኞች
አለቃ የሆነው እርሱ ራሱ ለቤተ ክርስቲያን
እረኞችን እንደሰጠም ልብ ልንል ይገባል።
(ኤፌ 4:11)
         አገልጋዮች፣ በራሳችሁ ላይ የሰው ጠባቂም
አስቀምጡ። ጥቅሙን በኋላ ታዩታላችሁ። ይህ
አስተዋይነት ነው።    
  
(ይቀጥላል)       

Tesfaye Gabbiso

25 Feb, 15:56


ምቹ  የሆነ አዘማመር
(ካለፈው የቀጠለ)

ቀጥሎ በተዘረዘረው የአዘማመር አመቺነት ብዙዎች እንደሚስማሙበት ይታመናል።

1. አመቺ የሆነ የድምጽ ቁልፍና ቅኝት መጠቀም - ለተመረጠው ዝማሬ የሚስማማ የድምጽ ቁልፍ መርጦ መጠቀም አስፈላጊ ነው። የማረፊያ ቁልፉ በጣም ሲወርድም ሆነ ሲያሻቅብ ለአዘማመር አይመችም። ለብዙኃኑ ዘማሪ ጉባዔ፣ አመቺው ቁልፍ የፈረንጂኛው "ሲ" ሆኖ እያለ አንድን መዝሙር በ "ጂ" መጀመር ጭንቅ ውስጥ ይከትታል። እዚህም ላይ ማስተዋል ጠቃሚ ይሆናል።

2. አመቺ - ጤናማ የሆነ የድምጽ መጠን - ለጆሮ ሕመም የማይዳርግ

3. አመቺ የሆነ የአዘማመር ፍጥነት -  በእርጋታ ሲዘመር የሚመቸውን ትንፋሽን ወደሚያሳጣ ፍጥነት ስንወስደው የመዝሙሩን ጣዕም ያጠፋዋል። ሲጎተተም እንዲሁ ነው። አመቺውን አማካይ ፍጥነት አመዛዝኖ መምረጥ ይመከራል።

4. አመቺ የሆነ የሙዚቃ ስልት - (Beat & rhythm)

5. አመቺ የሆነ የልብ ዝንባሌ - ለእግዚአብሔርና ለተገልጋይ በሚሆን ተገቢ አክብሮትና ፍቅር መዘመርም መልካም ይሆናል።

(ይቀጥላል)

Tesfaye Gabbiso

18 Feb, 05:54


ክፍል ዐራት

የአምልኮ አመራር በመዝሙር

1. ተመጣጣኝነት ያለው የጸሎትና የጥናት
ዝግጅት የተደረገበት፣ ዝግጅቱ
የዕውቀትና የዕቅድም ነው።
2.  ከቤተ ክርስቲያኒቱ መጋቢ (መሪ) ጋር
የቅርብ ምክክር የሚደረግበት፣
3.  የሚዘመሩ ዝማሬዎች በሚገባ
የታሰበባቸው፣ የዕለቱንና የወቅቱን
ልዩ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገቡ
መሆን አለባቸው። ለምሳሌ የጌታ ልደት፣
ስቅለት ወይም ትንሣዔ፣ ጥምቀት፣ የጌታ
ዕራት፣ ሠርግ፣ ምረቃ፣ ቀብር፣ ሸኝትና
የመሳሰሉት ሁነቶች።
4.  በማስተዋልና በጥበብ የሚመራ፣-
የዜማ ጉዳይና የሰው አያያዝ፣
ማስተዋልና ጥበብን ይጠይቃል።
     ማስተዋል ተግባቦትን ያግዛል።
አለማስተዋል ያደናቅፋል።
5.  መልእክታቸው የማይገናኝ መዝሙሮችና
አዝማቾችን መቀጣጠል ያልበዛበት፣
6 . የጊዜ አጠቃቀም ዲሲኘሊን (ጥብቅነት)
የሚታይበት፣ ለሌሎች የተመደበውን ጊዜ
ከመሻማት መ'ቆጠብ ያስፈልጋል።
7.  አላስፈላጊ ማብራሪያና ስብከት
የማይሰጥበት፣
8.  በአክብሮትና በትሕትና የተሞላ -
ጉባኤውን መዝለፍ የሌለበት፣
9.  ጉባዔን ያለፈቃዱ ለረዥም ጊዜ
በማስቆም ማድከም የማይታይበት፣
10. ራስ ተኮርነት፣ ከላይ እንዳወሳነው፣
በአካላዊ ከፍ ያለ እንቅስቃሴ ራስን ብቻ
ማስደሰት "ያልተቆጣጠረው"፣
11.የተራዘመና ከጤናማው ልክ ያለፈ
ጩኸት ያልተጫነው  (ልኩ
በመቆጣጠሪያ መሣሪያው አሬንጓዴ
መብራት ላይ ያለ ነው።) የድምጽ
አጠቃቀም ጤናማነት የአእምሮን ሰላም
መጠበቅ ይኖርበታል።
     ሰው ወደ መንፈሳዊ ጉባኤ የሚመጣው
ሰላምን ፍለጋም አይደል?  እግዚአብሔር
ደግሞ የሰላም አምላክ ነው።
12.አክብሮተ እግዚአብሔርና ፍቅሩ የገዛው
አመራር እንዲሆን መናፈቅም አስፈላጊ
ነው።

(በሌላ ሚዲያ ቀርቦ የነበረና እዚህ ላይ መጠነኛ የሆነ የይዘት ለውጥ  የተደረገበት)

(ይቀጥላል)

Tesfaye Gabbiso

11 Feb, 05:39


የዝማሬና  አምልኮ መሪዎች
(ካለፈው የቀጠለ).

6. የአምልኮ መሪዎቹ በማስተዋልና በጥበብ ለመምራት ማሰብና መትጋት ይኖርባቸዋል። ዝማሬ ራሱ በማስተዋልና በጥበብ  የሚሰጥ አገልግሎት ነው። "እግዚአብሔር ለምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና በማስተዋል ዘምሩ።"(መዝ 47:7)  የምናስተውለው የእግዚአብሔርን ማንነት፣ ፈቃዱንና ሥራውን ነው።

ለዝማሬ አገልግሎት ስንቆም፣ ያለነው በማን ፊት እንደሆነ እያሰብንም  መሆን አለበት። ብዙ ጊዜ፣  የምንጨነቀውና የምንዘጋጀው በሰው ፊት ለሚኖረን አቀራረብ ብቻ መስሎ ይታያል። እግዚአብሔር ትዝ የሚለን ምናልባት አልፎ አልፎ ብቻ ሊሆን ይችላል። ለእግዚአብሔር ዕውቅና መሰጠትና በታላቅ አክብሮት ፊቱ መቅረብ ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባን ዝንባሌያችን ነው።

እግዚአብሔርን መፍራት - ማክበር - ጥበብ ነው። (ኢዮ 28:28። መዝ 5:7)  እርሱን አለመፍራት ግን ታላቅ ስንፍና ነው። በሌላ በኩል፣ ጥበቡ የዝማሬ አገባብና ሥርዓቱን - አካኼዱን፣ የድምጽ መጠን አጠቃቀምን፣ አጀማመርና አጨራረስን አውቆ ሥራ ላይ ማዋልን ይጨምራል፡፡

7. በዝማሬ ጉባዔን የሚመሩ ወገኖች በሁሉም ረገድ ባለ መልካም አርአያ ሊሆኑ ይገባል፡፡ መሪነት ምሳሌነት ነው ብለናል። ምሳሌነቱ በመዘመር ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ በጽድቅ አካኼድ ጭምር መሆን አለበት።

የምናገለግለው ጌታ ጽድቅን በመውደድ ዐመጽን የጠላ ነው።(ዕብ 2:9) የእርሱን መልካም አርአያ ልንከተል ተጠርተናል። በተራችን በመልካም የሕይወት ምሳሌነት ማገልገል ይገባናል። "ለሚያምኑት ምሳሌ ሁን እንጂ ማንም ታናሽነትህን አይናቀው።" (1 ጢሞ 4:12)

ልንሆን የምንችለው ከሁለት አንድ ነው፤ መሰናክል ወይም መልካም ምሳሌ። በጸጋ የተገነባና በብዙ የተደከመበት አገልግሎት በጎጂ ጠባይ ምክንያት እንዳይፈርስ በጥንቃቄና በመልካም ምሳሌነት ልንመላለስ ይገባል።(1 ቆሮ 13:1-7) መልካም ምሳሌ የተወልንን ኢየሱስን በመከተል (ዮሐ 13:14-16)ከኋላችን ላለው ትውልድ መልካም አርአያ ስለ መሆን እናስብ፤ እንመካከርም። በየቀኑም፣ በኃላፊነት ስሜት እንመላለስ።

መንፈሳዊ ዝማሬያችንና አምልኳችን አገልግሎትን በተረዱ አገልጋዮች የሚመራበት፣ እግዚአብሔር በመንፈስና በእውነት የሚመለክበት፣ የክርስቶስ ወንጌል በጥራት የሚነገርበት፣ ቅዱሳንም በደስታ እየተማሩ የሚያድጉበት ይሁንልን፡፡ ጌታ እግዚአብሔርም በጸጋው ይርዳን፡፡

(ይቀጥላል)

Tesfaye Gabbiso

04 Feb, 07:19


የዝማሬና  አምልኮ መሪዎች

(ካለፈው የቀጠለ)

4. በዝማሬ የጉባዔ አምልኮን የሚመሩ፣ የእግዚአብሔርን ቃልና የቤተ ክርስቲያንን አስተምሕሮ የሚያውቁና የሚያከብሩ ሊሆኑም ይገባል። መጽሐፉ በቆላስ 3:16 ላይ  "የክርስቶስ ቃል በሙላት ይኑርባችሁ" ካለ በኋላ ነው አያይዞ " ..ዘምሩ" ያለው። ቃሉ የዳንንበትና ነጻ የወጣንበት እውነት፣ የምንመራበት ብርሃንም ነው። (መዝ 119:105) የምናመልከውን አምላክ ማንነትና  ፈቃዱን ለማወቅ የበቃነው በቃሉ ነው። የቤተ ክርስቲያን የእምነት አቋምና አስተምሕሮ የሚመሠረተውም በቃሉ ዕውቀት ላይ ነው። አስተምሕሮው የእምነት አቋም መገለጫዋ ነው። በመሆኑም፣ ንግግራችን፣ አኗኗራችንና አሠራራችንም ይህኑ አቋም የሚያንጸባርቅ እንዲሆን ይጠበቃል።

ዘማሪዎች ስሕተትን ዘምረው፣ የሚያመልከውንም ምዕመን ያንኑ እንዳያስዘምሩት! እውነትን ግን የሚያስተጋቡና የሚያስተምሩ መልካም ምሳሌዎች መሆን አለባቸው። ስንመራ ሳለን፣ እኛን ራሳችንን፣ የቃሉ እውነት ይምራን፤ ይግዛንም። ለዚህ የሚሆን የልብ ፈቃድና ዝግጁነት ያለን ግን ስንቶች ነን?

5. በዝማሬ አገልግሎትና አመራር የሚተጉ ለክርስቶስም ለቤተ ክርስቲያንም የሚገዙ መሆን አለባቸው። ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው። በትሕትና መ' ገዛታችን ይ' ገባዋል።

ጠለቅ ያለና እውነተኛ የሆነ የቃሉ ዕውቀት በትሕትና ወደ ማገልገል ያመጣናል። ክርስቶስ ኢየሱስ በትሕትና የመታዘዝ ዋናው ምሳሌያችን ነው።(ፊል 2:5-5) ስናገለግል የትሕትና ዝንባሌ ይዘን፣ ትሕትናን በተግባርም ለብሰን መሆን አለበት።

አለመገዛት መታበይ ነው። "እግዚአብሔር ትቢተኞችን ይቃወማል። ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።" (ያዕ 4:6 ) ስንታበይ ሰውን እንንቃለን። የምንንቀውን ሰው እናቆስላለን እንጂ አንጠቅመውም። በእግዚአብሔርም ሆነ በሚገለገሉ ሰዎች ላይ መታበይ መንፈሳዊ አደጋን ይጋብዛል።  በዲያብሎስ ፍርድ ላይ ያስወድቃል።(1 ጢሞ 3:6)

ዘማሪዎች አባል የሆኑባት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በምታወጣው መርሐ ግብር የሚ' መሩና ሥርዓት (discipline) ያላቸው፣ በሚጠበቁበት ቦታም በሰዓቱ የሚገኙ ቀጠሮ አክባሪዎች መሆን ይጠበቅባቸዋል። ሁላችንም፣ ይህን ትሕትና ና ሥርዓት ይዘን ብናገለግል፣ እግዚአብሔር ከልባችን ይከበራል። የሚያከብሩትን ደግሞ እርሱ ራሱ ያከብራቸዋል። የናቁት ከሌላውም ይልቅ በእርሱ የተናቁ ይሆናሉ። (1ሳሙ 2:30) በዝማሬ የምናገልግል ሁላችን፣ ከመ' ናቅ ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ እንዲሆንልን በመ' ገዛት ዝቅ እያልን እናገልግለው።

(ይቀጥላል)

Tesfaye Gabbiso

28 Jan, 13:38


መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዝማሬና አምልኮ

ክፍል ሦስት

የዝማሬና  አምልኮ መሪዎች

የጉባዔ አምልኮን በዝማሬ መምራት የከበረ አገልግሎት ነው። መምራት መንገድ (ተገቢውን አቅጣጫ) ማሳየት ነው ። መሪነት ምሳሌነትም ነው። መሪው መንገድን አሳይቶ የሚመለስ አይደለም። ራሱም ይኼድበታል። የአምልኮ መሪው አምላኪውን ወደ አምላኩ ይመራል ተብሎ ይታመናል። መሪዎቹ፣ ጉባዔው በተለይ በዝማሬ ሲያመልክ ምንና እንዴት እንደሚዘምር አውቆ፣ ምን ጊዜ እንደሚጨርስ የሚያሳውቁ፣ እየዘመሩ የሚያስዘምሩም ናቸው። አገልግሎቱም በዘፈቀደ ሳይሆን፣  በዝግጅትና በጥንቃቄ የሚገባበትና የሚካኼድ መሆን ይኖርበታል። እንደ ሌላው  ሁሉ፣ ይኼኛውም  አገልግሎት  መሥፈርትን የተከተለ ስምሪትን ይጠይቃል። የጉባዔ አምልኮን በዝማሬ ከሚመሩ ወገኖች የሚጠበቁ ነገሮች፦


1.የዳኑ፣ (በመንፈስ ዳግመኛ የተወለዱ) ና ጌታ ክርስቶስን በሕይወታቸው የሚያውቁ  ሊሆኑ ይገባል። ጌታን በአእምሮ ማወቅና በሕይወት ግንኙነት ማወቅ የተለያየ ነው። በሕይወት ማወቅ ከእርሱ ጋር በጸሎት፣ በቃሉ ጥናት፣ ለቃሉም በመታዘዝና በፍቅር መጣበቅን የሳያል። መሪዎቹ፣ የተለወጠ ሕይወት ያላቸው፣ መለወጥ የጀመሩና በመለወጥ የሚያድጉ መሆናቸው መታየት አለበት።  ይህ መሠረታዊ ጉዳይ ነው።

2. የዝማሬ ጸጋ ( ስጦታው) ያላቸው ሊሆኑም ይገባል - ለዝማሬ የሚሆን አመቺ ድምጽ ያላቸው፣ የድምጽ ዓይነትና የምት ፍጥነትን እየለዩ የሚከተሉ መሆን ይኖርባቸዋል። የድምጽ መመቸት ግን ብቻውን በተገልጋይ ላይ ለውጥ አያመጣም። ድምጹ ለዝማሬ ተመችቶ ሕይወቱ ለተገልጋዮች የማይመች ሆኖ እንዳይገኝ  ለማለት ነው። ክርስቶስ ሳይሆን ዜማ (ሙዚቃ) ብቻ ስቦት ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ የመጣና ከአመጸኛ ባሕርዩ ያልተላቀቀ፣ ለመላቀቅም የማይሻ፣ ማንንም አያንጽም። በአምልኮ መካከል መንፈሳዊ ውጤት በተገልጋዮች ላይ ለማየት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መነካትና መለወጥ ያስፈልጋል። ከሚያምረው የድምጽ ስጦታ በፊት የሕይወት ለውጥ ያስፈልጋል።

3. በግልና በጋራ ቅዱስ ቃሉን በማጥናትና በጸሎት የሚተጉ - በቅዱሱ መንፈስም  ሁል ጊዜ የሚሞሉ (ኤፌ 5:18-20 )- ተዘጋጅተው የሚቆሙና ቃሉን ተመግበው የሚመግቡ መሆን አለባቸው። "ስለዚህ ወንድሞችን ብታሳስብ፥ በእምነትና በተከተልኸው በመልካም ትምህርት ቃል የምትመገብ የኢየሱስ ክርስቶስ መልካም አገልጋይ ትሆናለህ።"  (1 ጢሞ 4:6)  

(ይቀጥላል)

Tesfaye Gabbiso

21 Jan, 00:48


የአምልኮ ምንነት መንገድና መገለጫዎች

(ካለፈው የቀጠለ)

4.በጉባዔ ሲሆን፣ አምልኮው ለእግዚአብሔር ክብርና ለሰው መታነጽ እንዲውል በሥርዓት መካኼድ ይኖርበታል፡፡ ቃሉ "...ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት...  ሁሉ ለማነጽ ይሁን።" ስለሚል። (ቆሮ 10:31 ፤ 14:27)

ወደዚህ ግብ ለመድረስ እንዲቻል፣ "ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን።" ይላል። (14:40) የልሳኖች አጠቃቀም፣ የትንቢት መልዕክት፣ መግለጡም፣ ትምሕርቱም፣ መዝሙሩም የፈውስ አገልግሎቱም፣ በአገባብና በሥርዓት ይሁን ማለቱ ነው።እዚህ ላይ የምናየው ሥርዓት፣ ድርጊቶችን ቅደም ተከተል አስይዞ፣ ጊዜና ቦታ ወስኖ፣ ሁሉን በስጦታው መሠረት አሰልፎ፣ ባልተምታታና ለሁሉ ግልጽ የሆነ ትርጉም በሚሰጥ መልኩ የመፈጸም ጉዳይ ነው ለማለት ይቻላል።

የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጉባዔ ሲሰበሰቡ ሁሉን በአገባብና በሥርዓት እንዲያደርጉ ታዘዋል(1 ቆሮ 14፡40)፡፡ "ማንም ነቢይ ወይም መንፈሳዊ የሆነ ቢመስለው ይህች የጻፍሁላችሁ የጌታ ትእዛዝ እንደ ሆነች ይወቅ፤..." ያለውንም ልብ ይሏል። (14:37) በጉባዔ ስትሰበሰቡ ሥርዓት ይኑራችሁ ያለው ጌታ ራሱ ነበረ ማለት ነው።

በመንፈስ ቅዱስ የተሞላውና "ከሁላችሁ ይልቅ በልሳኖች እናገራለሁ" ያለ ጳውሎስ፣ (14:18) በመንፈሳዊ ስጦታዎች ይጠቀሙ ለነበሩት የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በሥርዓት የመገልገልን ጥቅም በሰፊው እንደጻፈላቸው እንመለከታለን። ጥቅሞቹ፦

1. ማስተዋልን በተሞላ መንገድ፣ ያለ ሁከት በማምለክ  ቤተ ክርስቲያንን (ቅዱሳንን) ማነጽ፤ (14:12 ። እግዚአብሔር "የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና፤"(14:33) ሥርዓትን መጠበቅ ሰላማዊ ግንኙነትን ያራምዳል። ሰላም በተራው፣ የማነጽ ውጤትን ለሚያመጣ አገልግሎት ምቹ መደላድል ይሆናል።

2. ለማያምን እንግዳ ታዳሚ ግራ የማያጋባና ግልጽ ትርጉም ያለው መልእክትን በማስተላለፍ ለጌታ ወድቆ ወደሚሰግድበት ደረጃ መምራት ነው። (14:15-25)

3. ባልታወከ ልብና አእምሮ፣ በሰከነም መንፈስ እግዚአብሔርን በአንድነት ማክበር/ ማማለክ ነው። (14:15-16 ና 25)

በዛሬ ዘመን፣ በተለምዶ፣ ‹‹የአምልኮ መሪዎች›› የምንባል በጉባኤ ፊት የምንቆመው ይህንን መመሪያ እያስታወስን በሥርዓት እንደምንመራ ታሳቢ ተደርጎ ነው፡፡ ሥርዓት ለአምልኮ ይዘታችን ውበትንም ይጨምራል። ጌታን የማክበርና የቅዱሳንን እምነት የማጠናከር ውጤት ለማየትም ያግዛል። ሥርዓት የለቀቀና የተዘበራረቀ ነገር ግን አያምርም። መጠንቀቅ ግን ያስፈልጋል፤ ሥርዓቱ ሕይወትና ኃይል የጎደለው የኃይማኖት መልክ ብቻ እንዳይሆን።

በእርግጥ ሥርዓትን የምናበጅ እኛ ሰዎች ልንሆን እንችላለን። የእግዚአብሔር ቃልና መንፈስ ግን በውስጣችን ያደረብን ነን። ውጤቱን በማለምና ለጌታ ብለን ለሰውም ሥርዓት ራሳችንን ልናስገዛ ይገባናል።(1 ጴጥ 2:13)

በሥርዓት ማምለክ፣ የአምልኮ መልኩን ብቻ በማሳመር፣ የመንፈስ ቅዱስን ሥራና መንፈሳዊ ነጻነትን ያለ አግባብ መገደብ መስሎ የሚታየንም ልንኖር እንችላለን፡፡ ሥርዓት የለሽነትንና ሁከትን ከመንፈስ ቅዱስ ሥራ ጋር ማገናኘት ደግሞ ትክክል አይሆንም። ሰይጣን ቢታወክ እኮ ቅር የሚለው የለም። ጌታን በሰላም ለማምለክ የተሰበሰቡ ቅዱሳን ልባቸው ከታወከስ ምን ይባላል? 

ከላይ እንደተመለከትነው፣ በጉባዔ አምልኮ ወቅት፣ ሥርዓትን መከተል ለውጤታማነት (ለመተናነጽ) በእጅጉ ይጠቅማል፡፡ ሰላማዊ የሆነ የጋራ ሥርዓት እየተከተልንም ቢሆን ፣ የአምልኮን ሕይወት ለዋጭ ኃይል መለማመድ እንችላለን። በሥርዓት ሆነን ረጋ ስንል፣ መንፈስ ቅዱስን በግልና በጥሞና ለማድመጥም ዕድል እናገኛለን።

አምልኳችን አዲስ ኪዳናዊውን መስመር ጠብቆ በሥርዓት የሚካሄድ ሲሆን በማያምኑት ሳይቀር እግዚአብሔር ይከበራል፡፡  በክርስቶስ አምነው ለሚድኑትም ሁኔታው የተመቸ ይሆናል (1 ቆሮ 14፡24-25)፡፡  በጊዜ ሒደት እያደገብን የመጣው የሥርዓት እጦት ግን አላስፈላጊ ነቀፋን አልጎተተም፤ የወንጌል አገልግሎት እንቅፋትም አልሆነም የሚል ይኖር ይሆን?

በየቦታው የምንገኝ፣ ቆም ብለን በማሰብና በመመካከር ይህን አሳሳቢ ሁኔታ ለማስተካከል ቆርጠን እንነሣ። አልያ ታላቅ በሆነ መንፈሳዊ ኪሣራ ላይ መውደቅ የማይቀር ይሆናል። እንግዲያው፣ በጉባዔ አምልኮ ረገድ፣ አያያዛችንን ለማስተካከል፣ የቤተ ክርስቲያንም ሆነ የአምልኮው "አመራር" የሚኖረው ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን ልንገነዘብና ልንንቀሳቀስ ይገባል፡፡

(ይቀጥላል)

Tesfaye Gabbiso

14 Jan, 02:55


የአምልኮ ምንነት መንገድና መገለጫዎች
(ካለፈው የቀጠለ)

3.የአምልኮ መገለጫዎች/መንገዶች በርካታ ናቸው፡፡ ከላይ እንደ መለከትነው፣

እግዚአብሔር  በሰው ሁለንተና፣  በመንፈስ፣ በነፍስና ፣ በስጋ (በአካል ) ይመለካል (ዘዳግ 6፡5፡፡ ሮሜ 12፡1)፡፡  እኛም ሰውነታችንን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርገን በማቅረብ እናመልካለን፤ እናገለግላለን። (ሮሜ 12:1) ልባዊ አክብሮትና አድናቆት፣ ፍቅርና ተመስጦ፣ ጾምና ጸሎት(የሐዋ 13፡2)፣  አካላዊ ስግደት፣ ጭብጨባና ሽብሸባ፣ በድምጽ የሚሆን ንግግራችን፣ የኃጢአት ኑዛዜያችን ሳይቀር የአምልኮ መገለጫዎች ናቸው።( ኢያ 7፡19፡፡ ኢሳ 6፡5) ማምለክ እግዚአብሔርን ማክበር ነው። ሰው ኃጢአቱን የሚናዘዘው ለእግዚአብሔር የሚሆን አክብሮት ሲኖረው ነው። ትዕቢተኛ አይናዘዝም። ስብከታችንና ዜማችን፣ በገንዘብና በንብረት መልክ የምናቀርበው ስጦታችን፣ ለተቸገሩት የምናበረክተው እርዳታችንና ‹‹በዓለም ከሚገኝ ዕድፍ›› ራሳችንን መጠበቅም (ያዕ 1፡26-27) …ወዘተ የአምልኮ መገለጫዎቻችን ናቸው፡፡

መንፈሳዊ ዜማ (ዝማሬ)  ከመገለጫዎቹ መካከል አንዱ ብቻ ነው፡፡ በዛሬ ዘመን ግን፣ ጥቂት በማይባሉ ወገኖች ዘንድ፣  እንደተመለከ የሚታሰበው ሲዘመር (በተለይ ከጠንካራ የአካል እንቅስቃሴ ጋር) ብቻ እንደሆነ ይመስላል፡፡ ይህ የአምልኮን ትኩረት ከዋናው ባለቤት ከእግዚአብሔር ላይ በማንሳት ወደ ሰው ከማውረድ ባሻገር መንፈሳዊውን ዝማሬ ወደ ስጋዊ መዝናኛነት እንዳይቀይረው ያሰጋል። (እስከ አሁንም ቀይሮት ካልሆነ ነው!)

ሌላው ደግሞ፣ በተለያዩ ቦታዎች በጉባዔ ሲጸለይ ቆይቶ መዘመር ሲጀመር "አሁን ወደ አምልኮ እንገባለን" መባሉ ነው፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፡፡ መባል ያለበትና የሚሻለው ‹‹አሁን ደግሞ በዝማሬ እናመልካለን›› ነው፡፡

በአሁን ጊዜ፣ በድምጽ አጠቃቀምና በአካላዊ እንቅስቃሴ ዙሪያ ማስተዋላችንን በብዙ የሚጠይቅ ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን።  ወደ ታይታዊነት ያዘነበሉ፣  ለዓይን፣ ለጆሮና ለአእምሮ እጅግ የሚከብዱ ትዕይንቶችና ድምጾችንም ለመሸከም እየተገደድን እንገኛለን። ይህን ቅሬታ እያሰሙ ያሉ ጥቂቶች አይደሉም። ጥቂቶችስ ቢሆኑ? በአፍቃሪና በሚራራ ልብ ሊታሰብላቸው አይገባምን? እንደነ ጳውሎስ፣ እኛስ በእግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን በሰው ፊትም መልካም የሆነውን ማሰብ አይገባንምን? (2 ቆሮ 8፡21) 

የካሜራና የድምጽ ቴክኖሎጂ አጠቃቀሙን ካለማወቅም ይሁን በቸልተኝነት ምክንያት፣ መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን አእምሯዊና አካላዊ ጤንነት ላይ ጭምር፣ ቀላል ያልሆነ ጉዳት እየደረሰ እንዳለም ታውቋል። ልባቸው በፍጥነት የሚመታባቸው፣ ጆሯቸው የመስማት አቅሙ የቀነሰባቸው ሰዎች ቁጥራቸው እየጨመረ ነው። በእውነተኛነት ጌታን ማምለክ የልብ ሰላምና እረፍት የሚያመጣ ሆኖ እያለ፣ የምንደርስበት የመጨረሻው ውጤት መታወክና መጨነቅ ከሆነ አንድ የሳትነው ነገር አለ ማለት ነው። ይህ ሁሉ በሚገባ ታስቦበት በአፋጣኝ መስተካከል አለበት። በስሜት ብቻ ሳይሆን በማስተዋል፣ በልብም ጭምር ስለ መዘመራችን ማረጋገጥ ይኖርብናል። ለእግዚአብሔር ክብርና ለእኛ መታነጽ እንዲሆን።

የአምልኮ ምንነትና መገለጫዎችን ከተመለከትን ዘንድ የአምልኮውን ዋና መንገድ ማስታወስም ይኖርብናል። በክርስቶስ በኩል፣ በመንፈስም (በመንፈስ ቅዱስ መሪነትና ከውስጣችን)፣ በእውነትም (በማስተዋልም) ማምለክ ዋናው መነሻችን ነው።

(ይቀጥላል)

Tesfaye Gabbiso

06 Jan, 18:05


"ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት።"   ለዓለም መድኃኒት ለጌታ ለኢየሱስ ነው ። (ማቴ፡2:11)

ማንነታችንን በፊቱ ጥለን ለማንነቱ እንስገድለት፤ ያለንን እያቀረብንለትም እናክብረው፤ ይገባዋል።

መልካም የልደቱ መታሰቢያ በዓል ለሁላችን!

Tesfaye Gabbiso

30 Dec, 19:51


መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዝማሬና አምልኮ

(ክፍል ሁለት)


የአምልኮ ምንነት፣ መንገድና መገለጫዎች
1.ማምለክ ለመለኮታዊ መገለጥ የአድናቆት፣ የፍቅር፣ የአክብሮት፣ የሰግደት፣  መሥዋዕት የማቅረብ፣ የመገዛትና የማገልገልም ምላሽ መስጠት ነው። የእኛ አምላክ ራሱን ለሰው በታላቅ ፍቅርና ክብር የገለጠና የሚገልጥ ነው።  ለዚህ መገለጡ የአምልኮ ምላሽ እየተሰጠው ለዘላለም ይኖራል። ምላሹ በተለያየ መንገድ የሚሰጥ ነው። (ዘፍጥ 12፡7፡፡ 2 ዜና 7:1-3። ኢሳ 6፡1-8) አብርሐም ለተገለጠለት እግዚአብሔር መሠዊያን ሠራ። የእስራኤል ልጆች በመቅደሱ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ክብር ባዩ ጊዜ በግንባራቸው ወድቀው ሰገዱ። ኢሳይያስ ለተገለጠለትና "ማንን እልካለሁ ? ማንስ ይኼድልናል?" በማለት ለጠየቀ  ታላቅ አምላክ  "እኔን ላከኝ" የሚል ምላሽ  በመስጠት አከበረው። በየዘመናቱ፣ በልዩ ልዩ መንገድ፣  ራሱን ለሰው የገለጠ አምላክ፣  አምልኮን ሊቀበል የሚገባው እውነተኛና ሕያው፣ የሰማይና የምድር ፈጣሪም ነው። (1 ተሰሎ 1፡10)፡፡  ይህ አምላክ በኃጢአት የወደቀን ሰው ወዶ በልጁ ክርስቶስ በኩል የድነትን መንገድ ያዘጋጀለት ነው። እግዚአብሔር በፍቅሩ የተገለጠላቸውና በክርስቶስ ሞት ከሞት የዳኑ ያመልኩታል።

እውነተኛ አማኞች ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ፣ ጌታና አዳኝ መሆኑ የተገለጠላቸው፣  ይህን መገለጥ  ተቀብለው የሚመሰክሩም ናቸው። (ማቴ 16: 15-17 ። ዮሐ 20:24-29) የልቡና ዓይናቸው ተከፍቶላቸው የመዳናቸው ምስጢር የተገለጠላቸው፣ (ኤፌ 1: 17-19) ስለ ተቀበሉት ምሕረት በምስጋና እየተሞሉ፣ ከልብ ጌታን ያመልኩታል፣ ያገለግሉታል። ሐዋርያው ጳውሎስ አንዱ ማሳያ ነው። (1 ጢሞ 1:15- 17)

ይህ አምልኮ ጠቅላላ የኑሮ ዘይቤያችንን ይጨምራል። ( ዘዳ 6:5 ። ሮሜ 12።   ያዕ 1፡26-27)  የልባችንን አሳብና ዝንባሌ፣ የአፋችንን መልካም ንግግር፣ የእጃችንን በጎ ሥራ ሁሉ ያጠቃልላል።

2.በብሉይ ኪዳን ዘመን፣ የአምልኮው መንገዶች መሥዋዕቶችና መሥዋዕት አቅራቢ ካሕናት ነበሩ፡፡ (ዘሌ 1-5፤16) በአዲስ ኪዳን የአምልኮው መንገድ ቤዛችን የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡ "በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም"  ብሏልና።(ዮሐ14:6) ክርስቶስ ኢየሱስ በመስቀል ደሙ ባስገኘልን ይቅርታና በከፈተልን በር ወደ እግዚአብሔር ፊት በእምነትና  በአምልኮ እንገባለን (ኤፌ 2፡18፡፡ ዕብ 4፡16፤10፡19)፡፡ እርሱ ሊቀ ካሕናታችን ነው፡፡ የአምልኮ መሪው ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ነው (ፊልጵ 3፡3)፡፡

(ይቀጥላል)

Tesfaye Gabbiso

24 Dec, 04:49


መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዝማሬና አምልኮ

የዝማሬ ምንነትና ባሕርያት

(ከለፈው የቀጠለ)


4. ዝማሬን ጨምሮ፣ ሁሉም መንፈሳዊ አገልግሎት በውጤታማነት ሊሰጥና ለራስም መታነጽ  የሚቻለው፣ በእግዚአብሔር ጸጋ እስከ ሆነ ድረስ ብቻ ነው። ከላይ "በጸጋው...ዘምሩ" ተብሏል። (ቆላ 3:16) በመለኮታዊ ኃይል መደገፋችን የግድ ነው። የእግዚአብሔር ጸጋ ሲገለጥ ሰው ይድናል። ከጥፋት ይተርፋል። በእምነቱም ይጸናል። እግዚአብሔር በተፈጥሮአችን ውስጥ የሚያስቀምጠው በጎ ስጦታ፣ ለምሳሌ ድምጻችን፣ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። መልካም ድምጽና ዜማ ግን መንፈሳዊ ውጤት የሚያመጣው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል (በጸጋው) ሲታገዝ ብቻ ነው።

5.መንፈሳዊ ዝማሬ በነጠላ (በሶሎ)፣ በአነስተኛ ቡድን (በመዘምራን)ና በጉባዔ ይቀርባል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ነጠላው ዘማሪና  ጉባዔው በቅብብሎሽ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጉባዔ ራሱን ችሎ  ይዘምራል (ዘጸ 15፡1-21፡፡ መዝ 136፡፡  ቆላ 3፡ 16- 17)፡፡ በብሉይ ዘመን፣ እንደ ንጉሡ ዳዊት ያሉ በነጠላ ዘምረዋል፡፡ ዳዊት ራሱ ከሌዋውያን መካከል ያደራጃቸው መዘምራን  ነበሩ።  መዘምራኑ መሪና የዜማ ዕቃ  የሚጫወቱ ነበሯቸው። (1 ዜና 16:4-28)

6.የአዲስ ኪዳን ዝማሬ የክርስቶስን ማንነትና ሥራ፣ ጌትነቱና አዳኝነቱን በአጽንኦት ከማውሳት የሚነሣ ነው።  (ራዕ 1፡5-6፤ 5:9–13 )፡፡ ስለ ጌትነቱ ፣ ስለ ታላቅነቱ ክርስቶስ ይወደሳል፤ ስለ አዳኝነቱ (ስለ ቤዛነቱ) ይመሰገናል፡፡  በክርስቶስ የመስቀሉ ሥራ እኛ ከሞት ወደ ሕይወት መሻገራችን (መዳናችን)፣ በተራው ለዝማሬና ለአምልኮ ያነሣሣናል፡፡ በአንድያ ልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል በታላቅ ምሕረቱ የጎበኘንን አምላክ፣ በመንፈስ ቅዱስ እየተመራን እንወድሰዋለን፤ በዝማሬያችንም እናመልከዋለን። መነሻችን ግን በክርስቶስ ሥራ መዳናችን ነው።  በሥራውና በስሙ የዳነ ያመሰግናል። ያመልካል።

(ይቀጥላል)

Tesfaye Gabbiso

17 Dec, 13:22


መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዝማሬና አምልኮ

(ከክፍል አንድ - የቀጠለ)

የዝማሬ ምንነትና ባሕርያት

1. የአማርኛ መዝገበ ቃላት ለዝማሬ የሚሰጠው ትርጉም "1. ዜማ።...2. በዜማ የሚቀርብ ውዳሴ፥ ምስጋና።... "የሚል ነው።* ሰፋ ባለ መልኩ ሲታይ፣ ዝማሬ  በጥበብ ተዘጋጅቶ የሚቀርብ፣ ስልታዊነትና ጥዑምነት ያለው፣ መልዕክት አዘል የሆነ ዜማ ነው ለማለትም ይቻላል። ዜማው በሰውም ሆነ በሙዚቃ መሣሪያ ድምጽ ለየብቻ ወይም በአንድነት የተቀናበረ ሊሆን ይችላል። የቃላቱ (የግጥሙ) መልእክት፣ በዋናነት ለአእምሮ የታቀደ ሲሆን፣ ዜማው በይበልጥ ስሜትን ይነካል፡፡ ጥበቡ የጽሑፍ ውበትን፣ ማለትም፣ የግጥም አጻጻፍና (የሐሰብ ፍሰት፣ የቃላት አመራረጥና ቤት አመታት ወዘተ) የዜማ አካኼድን ይጨምራል።

2. መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዝማሬ፣ መልእክቱ ከዘማሪው ወደ እግዚአብሔር፣ ወደ ሌሎች አድማጮችም የሚኼድ ነው፡፡ ወደ እግዚአብሔር ሲሆን ጸሎትና አምልኮ፣ ወደ ሰው ሲሆን ደግሞ ወንጌልን ማሠራጫ፣ መጽናኛና ማስተማርያ (ደቀ መዝሙር ማድረጊያ) ይሆናል፡፡  በዘመናችንም በእነዚህ ምድቦች ሥር የሚገኙ ዝማሬዎችን ለመመልከት እንችላለን። የጥንት ቤተ ክርስቲያን ምዕመንዋን (ሕጻናትን ጨምሮ) በደቀ መዝሙርነት ለማነጽ አስተምሕሯዋን ያሰረጸችው በዝማሬ ጭምር ነበር። ይህን እውነት ለማረጋገጥ፣ የቤተ ክርስቲያንን የአምልኮና የዝማሬ ታሪክ መለስ ብሎ መቃኘት ያስፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዝማሬ ለሚዘምረው ሰው ለራሱም መልእክት ይኖረዋል። እዚህ ላይ፣ "ነፍሴ ሆይ..."  እያልን የምናዜማቸውን መዝሙሮች እናስታውሳለን።

3. በመንፈሳዊ ጉባኤ ከሚሰጡት አገልግሎቶች መካከል ዝማሬ ተጠቅሷል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ "ለእያንዳንዱ ... ትምሕርት አለው፣ መግለጥ አለው፣ በልሳን መናገር አለው፣ መተርጎም አለው" በሚልበት ክፍል ውስጥ "መዝሙር አለው" በማለት ይጀምራል።(ቆሮ 14:26) በተጨማሪ፣  "የእግዚአብሔር (የክርስቶስ) ቃል በሙላት ይኑርባችሁ።** በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ አስተምሩና ገሥጹ። በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ። እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት።" የሚለውንም መመልከት ጠቃሚ ነው። (ቆላ 3:16-17) የጉባዔ አምልኳቸው የቃሉ አገልግሎትና በጸጋ ስጦታዎች መተናነጽ የሚጠበቅበት ነበረ። መዘመር ደግሞ እንደ ዋናው የአምልኮ ልምምዳቸው ባይታይም፣ አንዱ በመሆን አገልግሏል።

(ይቀጥላል)
-------------------------------------------------------------------
የግርጌ ማስታወሻ
* የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማእከል፣  አማርኛ መዝገበ ቃላት፣  (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማተሚያ ቤት፣ 2001) ገጽ 432
** "የእግዚአብሔር ቃል" የተባለው "የክርስቶስ ቃል" ነው (መጽሐፍ ቅዱስ - አ.መ.ት.)