አይመለከተኝም፤ የኔ ጉዳይ አይደለም፤ ኃላፊነት አልወስድም፤ ምንም አይነት ተጠያቂነት የለብኝም፤ የኔ ግዴታ አይደለም፤ ... የሚል ጽንሰ ሃሳብን ያነገበ በእኛ ዘንድ በሁሉ ስፍራ ቀስ በቀስ ተስፋፍቶ የገዘፈ አመለካከት ነው።
ይሄው እሳቤ ሀገር አፈረሰ፤ የስንቱን ቤት ሸረሸረ፤ ትውልድ አመከነ።
መዘዙና ይዞት የሚመጣው ውጤት ሁሉን የሚያዳርስና የጋራ ክስረት ላይ የሚጥል መሆኑን ባለማስተዋል የተወለደ እይታ ነው። ምን አገባኝ? ባይነት ተንሰራፍቶ አይተን እንዳላየን፣ ሰምተን እንዳልሰማን ስንሆን ስንቱ ስህተት ልክ ሆነ? ስንቱ ጥፋት ልማት ሆነ? ስንቱ በደል ፍትህ ሆነ? በትንሽ ምን አገባኝ ባይነት የጀመርነው ጉዞ ተስፋፍቶ እሄው ዛሬ ላይ ያገባኛል፣ ይመለከተኛል የሚል ህሊና ጠፍቶ ትውልድን ለህሊና መደንዘዝ፣ ለግብረ-ገብ እጦት፣ ለእሴት ልልነት ዳረገው ... ኸረ ስንቱን ስንቱን አሳየን።
ሀገር የምትፈርሰው ምን አገባኝ የሚሉ ዜጎች የበዙ እንደሆነ ነው። ምን አገባይ! አይመለከተኝም ያልነው ሁሉ እኛ ቸል ብንልም እርሱ መቼ ተወን? ይኸው ወደድንም ጠላን ሁላችን የዚህ መዘዝ ገፈት ቀማሽ ሆነን ሆምጣቴን በሁሉ ቦታ እየተጎነጨን እንገኛለን።
በልጆች፣ በታዳጊ ወጣቶች፣ በማሕበራዊ ድረ-ገጽ፣ በማሕበረሰብ መካከል፣ በተቋማት፣ በአገልግሎት ሰጪዎች፣ በንግዱ፣ በሕጉ፣ በጤናው፣ በመምህር ተማሪው፣ በትምህርት ተቋማት፣ በሀገር፣ በእምነት ተቋማት... በሚሆኑ ሁነቶች፣ ድርጊቶችን ተግባራት ከክፉ እንድንታደግ፣ ስህተትን እንድናርም፣ መፍትሔን እንድንሰጥ፣ ... ሁላችንን ይመለከተናል፤ ይህ ሁሉ የሁላችን ኃላፊነት ነው።
ለሚመለከተንና ኃላፊነታችን ለሆነ ጉዳይ ምን አገባኝ ብለን አንለፍ!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይጠብቅ! ይባርክ! ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም ይሁን!
ምንተስኖት መኩሪያ
ኅዳር 12/2017 ዓ.ም