======================================
ህዳር 27/2017 ዓ.ም (ኢሚ) የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ከጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ ጋር የሀገር ውስጥ የህክምና ግብዓት በተለይም የህክምና ጎዝ፣ ባንዴጅ፣ እስዋብ እና ጥጦችን ሀገራዊ ፍላጎቶች እና የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን የሚያሳይ የዳሰሳ ጥናት ዉጤት መነሻ በማድረግ ግብዓቶቹን ሙሉ በሙሉ በሀገር ዉስጥ ምርቶች መተካት በሚቻልበት ሁኔታ ተወያይተዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ የሀገር ውስጥ ምርት መበረታታት ከአቅርቦት በተጨማሪ የስራ ዕድል እና ዘላቂ ኢኮኖሚ የሚፈጥር በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ብለዋል።
በመሆኑም ተግዳሮቶችን ለመፍታትና በቀጣይ ሌሎች ከውጪ የሚገዙ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር አምራቶች በአቅማቸዉ ልክ እንዲያመርቱ ለማደረግ በተሰራዉ ጥናት መሠረት ተገቢዉ ድጋፍና ክትትል ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ በበኩላቸዉ እስካሁን ይሰራበት የነበረውን የውጪ ግዥ የሚያበረታታ አሰራርን በመተካት የሀገር ውስጥ ምርት ግዥ የሚያበረታታ ስረዓት በመዘርጋት የዉጭ ጥገኝነትን መቀነስና መንግስትን የያዘዉን "ኢትዮጵያ ታምርትን" አላማ በማሳካት ለኢትዮጵያ ብልፅግና የበኩላችን መወጣት ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
አክለዉም የህክምና ግብዓት ጥራቱን የጠበቀ እና የህብረተሰቡን የመግዛት አቅም ያገናዘበ እንዲሆን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ በማብራራት ጥራት ያለውና የህብረተሰቡን የመግዛት አቅም ያገናዘበ ምርት እንዲያቀርቡ ከሀገር ውስጥ አምራቾች ጋር በቅርበት ይሰራል ብለዋል።
በውይይቱ ማጠቃለያ ከላይ የተዘረዘሩ ግብዓቶች የሀገር ዉስጥ ፍላጎትን በሀገር ዉስጥ ምርት ብቻ መሸፈን እንደሚቻል ሁለቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በመስማማት አፈፃፀሙን እንዲከታተሉ ከሁለቱም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ የባለሙያዎች ቡድን ተዋቅሯል።
#ኢትዮጵያ_ታምርት
#እኛም_እንሸምት
http://linktr.ee/fdremoi