+++ ይግባኝ! +++
አንድ ሰው ለብዙ ዘመናት አብሮት በፍቅር ይኖር የነበረ ወዳጁን በቅንዓት ተነሳስቶ ይገድለዋል፡፡ በዚህም የወንጀል ሥራው ተከስሶ የፍርድ ብይን ያገኝ ዘንድ ሰዎች ከችሎት ፊት አቆሙት፡፡ ዳኛውም ወንጀለኛው ለፈጸመው የጭካኔና ሰብአዊነት የጎደለው ክፉ ተግባር በሕጉ መሠረት የሚገባውን የዕድሜ ልክ እስራት ወሰኑበት፡፡ወንጀላኛውም በተሰጠው ፍርድ ፍትሐዊነት ላይ እንዳላመነበት እና ለፍርዱ ማቅለያ የሚሆን የይግባኝ ጥያቄን ማቅረብ እንደሚፈልግ በእጁ እየጠቀሰ ዳኛውን ተለማመነ፡፡
በዚህ ጊዜ ዳኛው ምን ዓይነት ይግባኝ እንደሚያቀርብ ለመስማት የጓጉ መሆናቸውን በሚያሳብቅ መልኩ ቸኩለው እድሉን ሰጡት፡፡
ወንጀለኛ፡-ክቡር ፍርድ ቤቱ እንዲመለከትልኝ የምፈልገው አንድ ነገር አለ፡፡በርግጥ ይህን ሰው መግደሌን አልካድኩም፣ ነገር ግን እርሱን ለመግደል የፈጀብኝ እኮ አፍታ ነች እንደው ቢበዛ ዐሥር ደቂቃ ቢሆን ነው፡፡ ታዲያ እንዴት በዚህች አጭር ጊዜ ላጠፋሁት ጥፋት ዕድሜ ልክ ይፈረድብኛል? በማለት ጥያቄውን አቀረበ፡፡
ዳኛው ምን ብለው የሚመልሱለት ይመስላችኋል? መቼም ወንጀሉን ለመፈጸም ከፈጀበት ጊዜ ጋር ተነጻጽሮ ፍርዱ ሊቀልለት ይችላል የሚል የየዋሕ ሰው ግምት እንደማይኖራችሁ አልጠራጠርም፡፡ በፍርዱ ሂደት የሚታየው ወንጀሉን ሲፈጽም የወሰደበት የጊዜ መጠን ሳይሆን በዚያች ሰዓት የፈጸማት የወንጀሏ ክብደት ናት፡፡
ውድ ምዕመናን! አሁን እኛ የፍርድ ቤት ዘገባ ምን ይጠቅመናል ትሉ ይሆናል? ከዚህ በኋላ ግን የምንነጋገረው ፍትሕ ስለማይገኝባት ስለዚህች ምድር ፍርድ አይደለም፤ ስለ ሰማያዊው ፍርድ ነው እንጂ። ስለ ሥጋዊው የዳኝነትም ሥርዓት አይደለም፤ ስለመንፈሳዊው ፍርድ ነው እንጂ፡፡ ብዙ ወንድሞቻችን እና እኅቶቻችን ስለ እግዚአብሔር ፍርድ ዘላለማዊነት (eternal punishment) ባሰቡ ቁጥር ‹የሰው ልጅ በዚህች ምድር የሚኖረው የዕድሜ ልክ ስልሳ እና ሰባ ቢበዛም ሰማንያ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ የዕድሜ ወሰን ውስጥ ለተሠራ ኃጢአት እንዴት እግዚአብሔር ዘላለማዊ ፍርድን ይፈርዳል?› የሚል ጥያቄ በኅሊናቸው ይላወስባቸዋል፡፡
አንዳንዶቹም ለተገፉ ጠበቃ የሚሆን የእውነት ፈራጅ እግዚአብሔርን ፍርዱ ኢ-ፍትሐዊ (unfair judgment) ነው በማለት ይሞግታሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ምንም ስለ ‹ዘላለማዊ ሽልማቱ› (eternal reward) ‹ለምን ዘላለማዊ ሆነ?› የሚል ጥያቄን አለማቅረባቸው ትዝብት ውስጥ የሚጥላቸው ቢሆንም እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ግን ከላይ ባለው አጭር ምሳሌ መልሳቸውን ያገኛሉ፡፡
አስተውሉ! ለወንጀለኛ መቼም ፍርድ እንደሚገባው ማንም የሚያምንበት ጉዳይ ነው፡፡ ወንጀለኛ ከወንጀል እስካልጸዳ ድረስ ፍርድ ከእርሱ ጋር እንደ ጥላ ትከተለዋለች፡፡ ቅጣትንም እንደ አክሊል በራሱ ላይ ደፍቶ ይመላለሳል፡፡ ለኃጢአተኛም እንዲሁ ነው፡፡ ራሱን በንስሓ መርምሮ ፣ወድቆ ተነሥቶ ፣በሥጋው በደሙ(ቅዱስ ቁርባንን በመቀበል) አምላኩን እስካልታረቀ ድረስ ሁል ጊዜም ኃጢአተኛ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ኀዘኑን እጥፍ የሚያደርገው ያ ኃጢአተኛ በዚህ አቋሙ እያለ በሞት ከተወሰደ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰው የሚድንበትን መንፈሳዊ ተግባር ማከናወን የሚችለው በምድር በሕይወተ ሥጋ እስካለ ድረስ ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ከራሷ ከክርስቶስ ከታነጸችበት የሐዋርያት ትምህርትም አላገኘችውምና ሰው ከሞተ በኋላ በሰማይ የሚሰግድበት ፣መንፈሳዊ ምግባራትን የሚያደራጅበትና ኃጢአቱን የሚያስወግድበት ሥፍራ አለ ብላ አታምንም፡፡ ‹እም ድኅረ ሞቱ ለሰብእ አልቦቱ ንስሓ›/ ‹ለሰው ከሞቱ በኋላ ንስሓ የለውም› የሚለውን የአበው ቃል መመሪያዋ ታደርጋለች እንጂ፡፡
ስለዚህም በዚህ መልኩ የሞተ ሰው ኃጢአተኝነቱ ለዘላለም ነውና ፍርዱም ለዘላለም በማይጠፋ በዲንና በሚቃጠል የእሳት ባሕር ይሆናል፡፡ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው፡፡(ራእይ 21፤8) ከእንግዲህስ ከነኃጢአታችን ብንሞት የምንድንበት መሥዋዕት የለምና፣ ከአሁን ሰዓት ጀምሮ አምላክ በዓይነ ምሕረቱ እንዲመለከተን የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደተባሉት ወደ ተሾሙ ካህናት እንገስግስ። ንስሓ እንግባ፣ ቀኖናችንንም እንፈጽም። መጠየቅን በሚወድ በእርሱ ፊት ለፍርድ በቆምን ጊዜ መልስ የሚሆነንን የጽድቅን ጥሪት እናከማች!
‹አቤቱ እንደ ቸርነትህ ነው እንጂ እንደ በደላችን አይሁንብን!›
ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]@dnabel