በሀገራችን ኢትዮጵያ እንደ ዩኒሴፍ ዘገባ 38.6% ከ5 አመት በታች ያሉ ልጆች የቀነጨሩ ሲሆኑ 21% የሚሆኑ 5 አመት በታች ያሉ ልጆች ከሚጠበቅባቸዉ ክብደት በታች ያሉ ሲሆን ከ15-49 ያሉ ሴቶች በምግብ እጥረት የተጎዱ ናቸው።
ስለተመጣጠነ ምግብ ማውራት ብዙ ሰው ቅንጦት ይመስለዋል፤ ነገር ግን ቅንጦት ሳይሆን እጅግ በጣም ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።
ምክኒያቱም የምግብ ጉዳይ ከጽንስ ጅምሮ እስከ 2 አመት ለልጆች የምናበላዉ እስከ ህይወት ፍጻሜያቸዉ ድረስ ተጽኖ ስለሚያመጣ ትኩረት ልናደርግ ይገባል።
ለልጆች መመገብ ካለብን ውስጥ፦
1፡ ጥሩ ቅባት (smart fat)፡
ህጻናት ትክክለኛ ቅባት/ fat /ያስፈልጋቸዋል። ይህ ማለት ዝቅተኛ ቅባት ሳይሆን ምርጥ ቅባት ያለዉ ምግብ ያስፈልጋቸዋል ማለት ነው።
-:ለህጻናት ጥሩ ቅባት ምንጭ ከሆኑ ምግቦች መካከል የባህር ምግብ(salmon)፣ ተልባ(flax oil)፣ አቮካዶ ፣ የአትክልት ዘይት ፣ ለውዝ (አላርጂክ ሊያስከትል ስለሚችል ከ2 አመት በኋላ)
- ለህጻናት ጥሩ ያልሆኑ ቅባቶች፡ ዘይት የበዛባቸውና የተጠበሱ ምግቦች፣ ብስኩት (crackers)
2: ጤናማ ስኳር (Best Carbs)
ህጻናት በተፈጥሮአቸዉ ስኳርና ጣፋጭ ነገሮችን ይወዳሉ፣ ሰዉነታቸዉም ይፈልጋል። ስኳር የሰዉነታቸዉ ዋናዉ ነዳጅ እና ሀይል ሰጪ ነዉ።
ጤናማ ስኳር የያዙ ምግቦች፦
አፕል ፣ ሙዝና ፍራፍሬ ፣ የጡት ወተት ፣ የወተት ተዋዖዎች (በተለይ ባዶ እርጎ) ፣ ትኩስ ፍራፍሬ፣ ፓስታ፣ ድንች ፣ አኩሪ አተር። ስኳር ድንች ፣ አትክልት እና አዝእርቶች።
3፡ ፕሮቲን
ፕሮቲን ገንቢ ምግብ በመባል ይታወቃል። ፕሮቲን ለእድገት፣ ለሰዉነትን ግንባታ ትልቁ ድርሻ ይወስዳል።
በፕሮቲን የበለጸጉ ምግቦች፦
የባህር ምግብ ፣ የወተት ተዋዕዖ (እርጎ፣ቺዝ እና ወተት) ፣ ጥራጥሬ (አኩሪ አተር፣ ምስር፣ ቦሎቄ)፣ ስጋና የዶሮ ስጋ፣ እንቁላል የለዉዝ ቅቤ ፣ያልተፈተጉ እህሎች (ስንዴ፣ ሩዝ፣ አጃ፣ በቆሎ እና ማሽላ)
4፡ በፋይበር የበለጸጉ ምግቦችን ማዘውተር
ፋይበር/ቃጫ/ የምንለዉ የማይፈጨው የአትክልት እና የፍራፍሬ አካል ነው። በተፈጥሮ አንሸራታችነት ባህሪ ስላለዉ ከሰውነታችን አላስፈላጊ የሆኑ ቆሻሻዎችን ለማሶገድ ይረዳል። ለህጻናት በፋይበር የበለጸገ ምግብ ሰገራቸዉ እንዲለሰልስና አላስፈላጊ ቆሻሻ ቶሎ እንዲወገድ ከመርዳቱም ባሻገር ድርቀትን ይከላከላል።
በፋይበር የበለጸጉ ምግቦች፦
አትክልት( ድንች ከነልጣጩ)፤ ያልተፈተጉ እህል፤ ቡኒ ሩዝ፤ ቦለቄ የመሳሰሉት፤ ካልተፈተገ እህል የተዘጋጀ ፓስታ፣ መኮረኒ፣ አጃ፣ ጥራጥሬ።
5፡ ቪታሚን
ከሶስቱ ዋና የምግብ ክፍሎች ( ቅባት፣ ፕሮቲን፣ ሃይል ሰጪ ምግቦች) በተጨማሪ ቪታሚን ለህጻናት እድገት ከፍተኛ አስተዋጾ ያደርጋል። እንደ ዋና ምግቦች( Macro nutrients) እኚህ ቪታሚንና ሚኒራለስ (micro nutrients) በቀጥታ ለሰዉነታችን ሃይል አይሰጡንም። ነገር ግን ለህጻናት የበሉት ምግብ በአግባቡ እንዲጠቅማቸውና የሰውነት ክፍላቸው በአግባቡ እንዲሰራ ያደርጋል።
ሰውነታችን እነዚህን ንጥረነገሮች ካላገኘ በአግባቡ መስራት አይችልም። ሰውነታችን 13 ቪታሚኖች ያስፈልጉታል። ቪታሚን A, C, D, E, K, እና 8 የ B ቤተሰቦች ማለትም thiamine, niacin riboflavin, pantothenic acid, biotin, folacin, B6 and B12.
6: ሚኒራልስ
እንደ ቪታሚንስ ሚኒራልስ (micro nutrients) የሚካተት ሲሆን ለህጻናት እድገት አስፈላጊ ንጥረነገር ነው። ሚኒራል የምንላቸው ካልሽየም፣ ፎስፈረስ፣ ማግኒዝየም እነዚህ ሶስቱ ጠንካራ አጥንትን ለመገንባት ይጠቅማሉ።
አይረን እና ኩፐር (copper) ደምን ይገነባሉ። ዚንክ( zinc) በሽታ የመከላከል አቅምን ይገነባል፣ሶዲየምና ፖታሺየም( sodium and potassium) ኤሌክትሮ ላይት የምንለዉ በሰውነታችን ውስጥ ያለውን የውሃ መጠን ይቆጣጠራል።
7፡ የአይረን መጠንን መጨመር
እያንዳንዱ የሰውነታችን ክፍል( organs) በአግባቡ እንዲሰራ ብረት በጣም አስፈላጊ ንጥረነገር ነው። ዋናው ስራውም ሂሞግሎቢንን (hemoglobin) መገንባት እና በቀይ የደም ሴል ውስጥ ያለውን ኦክስጅን የሚሸከም ነው።
አንድ ህጻን ልጅ ከ9_10 ወራት ውስጥ ሂሞግሎቢኑ መለካት አለበት፣ ይህም የሚሆንበት ምክኒያት ህጻኑ የደም ማነስ እጥረት ይኑርበት አይኑርበት ለማጣራት ነው።
በአይረን የበለጸጉ ምግቦች፦
የጡት ወተት፣ በብረት የበለጸጉ የህጻናት ወተቶች፣ የቲማቲም ጁስ፣ምስር፣ አኩሪ አተር፣አሳ፣ የዶሮ ስጋ፤ ቦለቄ እና የመሳሰሉት።
[ Source :-@BikuZega ]