አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመረጃ አያያዝ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆንና የሚፈለጉ መረጃዎች በቀላሉ እንዲገኙ ለማድረግ የ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ተገልጋይ ፋይሎች በቴክኖሎጂ በመታገዝ በአዲስ መልክ ተደራጅተው አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ የአስተዳደሩን የ6 ወራት እቅድ አፈጻጸም እያቀረቡ ያሉት ከንቲባዋ÷ ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ከምትሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍና ሀገር አቀፍ ሚናዋን የሚመጥን፣ የከተሜነት ይዘት እንዲኖራት በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል፡፡
በ6 ወራት እቅድ አፈጻጸም መሰረት በከተማዋ የሚታዩትን ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስና ዘመን ያስቆጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት በማድረግ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏልም ነው ያሉት፡፡
የመረጃ አያያዝ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆንና የሚፈለጉ መረጃዎች በቀላሉ እንዲገኙ የሚያደርግ የ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ተገልጋይ ፋይሎች በቴክኖሎጂ በመታገዝ በአዲስ መልክ ተደራጅተው አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን አንስተዋል፡፡
217 ግንባታዎችን መጠናቀቃቸውና 13 ነባር ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች በተለያየ የአፈፃፀም ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ከንቲባዋ÷ 87 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ መከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡
በከተማዋ የቤት አቅርቦትን ለማሻሻል በመንግስት አስተባባሪነት፣ በሪል ስቴት፣ በመንግስት ገንቢነትና የተለያዩ የልማት አማራጮችን በመጠቀም 27 ሺህ 304 ቤቶች ተገንብተው አቅርቦት ላይ ተጨማሪ ግብዓት ሆነዋል ብለዋል፡፡
በልዩ ልዩ የቤት አቅርቦት አማራጮች 120 ሺህ ቤቶች ግንባታ ፕሮግራም እንደተጀመረ እንዲሁም 100 አዳዲስ ኤሌክትሪክ አውቶቡሶችን በማስገባት ነባሮችን ጨምሮ በቀን 1 ሺህ 408 አውቶቡሶችን በማሰማራት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በየሻምበል ምህረት