አቶ አቶ ባያሌዉ መነሻ
የኤጀንሲዉ የሙያ ደረጃ፣ጥናት እና እዉቅና አሰጣጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር
በአብክመ የሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ነባር ምዘና ማዕከላት የሙያ ደረጃቸው በተቀየሩ ሙያዎች እውቅናቸውን ሳያድሱ የምዘና አገልግሎት ጥያቄ የማያስተናግድ መሆኑን አስታዉቋል፡፡
የኤጀንሲዉ የሙያ ደረጃ፣ጥናት እና እዉቅና አሰጣጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ባያሌዉ መነሻ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ከስራ ገቢያው ፍላጎት ጋር ተያይዞ የሙያ ደረጃ ለውጥ ሲኖር በድሮው የሙያ ደረጃ የተሰጠ የስልጠና፣ የምዘና ማዕከል እና መዛኝነት ፈቃድ በአዲሱ የሙያ ደረጃ መቀየርና መታደስ እንዳለበት በስርዓቱ ሰነዶችና መመሪያዎች ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ በመሆኑም ከ2014 ዓመተ ምህረት ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም የሙያ ዘርፎች የሙያ ደረጃዎች እንዲቀየሩ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ስልጠናውም ሆነ ምዘናው በአዲሱ የሙያ ደረጃ እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡
ይሁን እንጅ በአዲሱ የሙያ ደረጃ መሰረት የምዘና ማዕከልነት ፈቃድ እድሳት ጥያቄ አቅርበው ሳያድሱ በአዲሱ የሙያ ደረጃ መሠረት በተዘጋጁ ሙያዎች የምዘና አገልግሎት ጥያቄ የሚያቀርቡ ነባር ምዘና ማዕከላት በርካታ ናቸው ብለዋል፡፡ ጥያቄው ህጋዊ ባለመሆኑ ምክንያት ሳይስተናገድ ሲቀር ደግሞ በተሳሳተ መንገድ እንደ የመልካም አስተዳደር ችግር እየተወሰደ ለስራ እንቅፋት ፈጥሮ እንደሚገኝ አቶ ባያሌዉ መነሻ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም አሰራርን እና መመሪያን ማክበር እና ማስከበር ለኤጀንሲው የተሰጠ ኃላፊነት በመሆኑም በድሮው የሙያ ደረጃ የምዘና ማዕከል ፈቃድ ወስደዉ የምዘና አገልግሎት እየሰጡ ያሉ እንዲሁም ለመስጠት ፍላጎት ያላችዉ ነባር የመንግስትና የግል አሰልጣኝ ኮሌጆች፣ ምርት እና አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉ ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም መካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ምዘና ማዕከላት በአዲሱ የሙያ ደረጃ መሰረት ለምዘናው የሚያስፈልጉ ቋሚ እና አለቂ እቃዎች እንዲሁም ለእድሳት የሚያስፈልጉ መስፈርቶች በማሟላት በሚገኙበት ክላሰተር ማዕከል ጥያቄ በማቅረብ የተሰጣቸዉን የምዘና ማዕከልነት ፈቃድ እንዲያድሱ አሳስበዉ ይህ ካልሆነ ግን በአሮጌው ፈቃድ ወስዶ በአዲሱ የሚቀርብ የምዘና አገልግሎት ጥያቄ የማይስተናገድ መሆኑ ታውቆ በዚህ ምክንያት ለሚፈጥር የተመዛኞች መጉላላት እና ችግር ኤጀንሲዉ ኃለፊነት የማይወሰድ መሆኑን በአጽኖት ተናግረዋል።