"† በዘመኑ ሁሉ ፍጹም ሰላምን እግዚአብሔር ይሰጣት ዘንድ ስለ ኢትዮጵያ እንማልዳለን፤
† ዕውቀትን እሱን መፍራትንም እግዚአብሔር ይሰጣቸው ዘንድ ስለመኳንንትና ስልጣን ስላላቸው እንማልዳለን፤
† ስለ ዓለሙ ሁሉ እግዚአብሔር ማሰብን ያስቀድም ዘንድ እያንዳንዱም የሚያስፈልገውን ያማረውን የሚሻለውንም ያስብ ዘንድ ስለ ዓለሙ ሁሉ እንማልዳለን፤
† እግዚአብሔር ይቅርታ ባለው ቀኝ መርቶ በፍቅር እና በደኅንነት ወደ ማደሪያቸው ይመልሳቸው ዘንድ በባህር እና በየብስ ስለሚሄዱ ሰዎች እንማልዳለን፤
† እግዚአብሔር የዕለት የዕለት እንጀራቸውን ይሰጣቸው ዘንድ ስለተራቡና ስለተጠሙ ሰዎች እንማልዳለን፤
† እግዚአብሔር ፈፅሞ ያረጋጋቸው ዘንድ ስላዘኑ እና ስለተከዙ ሰዎች እብማልዳለን፤
† እግዚአብሔር ከእስራታቸው ይፈታቸው ዘንድ ስለታሰሩ ሰዎች እንማልዳለን፤
† እግዚአብሔር በሰላም ወደሃገራቸው ይመልሳቸው ዘንድ ስለተማረኩ ሰዎች እንማልዳለን፤
† እግዚአብሔር ትዕግስትን በጎ ትምህርትንም ይሰጣቸው ዘንድ የድካማቸውንም ፍጹም ዋጋ ይሰጣቸው ዘንድ ስለተሰደዱ ሰዎች እንማልዳለን፤
† እግዚአብሔር ፈጥኖ ያድናቸው ዘንድ ይቅርታውንና ቸርነቱንም ይልክላቸው ዘንድ ስለታመሙትና ስለድውያኑ እንማልዳለን፤
† ከቅድስት ቤተክርስቲያን ወገን ስለሞቱ ሰዎች እግዚአብሔር የእረፍት ቦታ ይሰጣቸው ዘንድ እንማልዳለን፤
† እግዚአብሔር እንዳይቀየማቸው ከመዓትም ተመልሶ ፍጹም ዕረፍትን ይሰጣቸው ዘንድ ስለበደሉ አባቶቻችን እና ወንድሞቻችን እንማልዳለን፤
† በሚያስፈልግበት ቦታ እግዚአብሔር ዝናቡን ያዘንብ ዘንድ ስለ ዝናብ እንማልዳለን፤
† የወንዙን ውሃ ምላልን ብለን እግዚአብሔር እነሱን እስከ ልካቸውና እስከወሰናቸው ይመላ ዘንድ ስለወንዝ እንማልዳለን፤
† ለዘር እና ለመከር ሊሆን እግዚአብሔር ለምድር ፍሬዋን ይሰጣት ዘንድ ስለ ምድር ፍሬ እንማልዳለን፤
† በጸሎት የምንለምንና የምንማልድ ሁላችንንም በሰላም በመንፈስ ይጠብቀን ፍቅርንም ይስጠን ዓይነ ልቡናችንን ያብራልን ፈቃዱም ሆኖ ጸሎታችንን ይቀበል ዘንድ ቀርበን እግዚአብሔርን እንለምነው!
ዐውቀን በሃብቱ እናድግ ዘንድ በእርሱም ስም እንመካ ዘንድ በነቢያት በሐዋርያትም መሰረት ላይ እንታነጽ ዘንድ እንግዲህ በመንፈስ ቅዱስ እንነሳ! ቀርበን አምላካችን እግዚአብሔርን እንለምነው ወዶ ጸሎታችንን ይቀበል ዘንድ:: " አሜን!
(በእንተ ቅድሳት)