1፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የናይጀሪያ ባለሥልጣናት የሚያካሂዱበትን ስም ማጥፋት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት እንዲያስቆሙለት በደብዳቤ መጠየቁን የአገሩቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የናይጀሪያ አየር መንገድ ቢቋቋም ኢትዮጵያዊያን የአዲሱን አየር መንገድ የሃላፊነት ቦታዎች እንዲይዙ ታስቦ እንደነበር፣ የአየር መንገዱ ትርፍ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚሄድና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ታክስ እንደማይከፍል አድርገው የአገሪቱ ሲቪል አቬሽን ሚንስትር የሚያሠራጩት መረጃ እውነታነት እንደሌለው አየር መንገዱ መግለጡን ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። ሲቢል አቬሽን ሚንስትሩ ለምን ስሙን እንደሚያጠፉ ግልጽ እንዳልኾነለት የጠቀሰው አየር መንገዱ፣ የናይጀሪያ መንግሥት የአገሪቱን አየር መንገድ በጋራ ለማቋቋም በተደረሰበት ስምምነት ላይ ሃሳቡን በመቀየሩ ችግር እንደሌለበት ገልጧል ተብሏል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ49 በመቶ ድርሻ የናይጀሪያ አየር መንገድን ለማቋቋም የደረሰበት ስምምነት መክሸፉ ይታወሳል።
2፤ መንግሥት የታክስ ገቢው ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የሚኖረውን ድርሻ በ2016 ዓ፣ም ከነበረበት 6 ነጥብ 3 በመቶ በ2020 ዓ፣ም መጨረሻ ወደ 13 ነጥብ 2 በመቶ ለማድረስ ማቀዱ ተሰምቷል። ዋዜማ የተመለከተችው አንድ የገንዘብ ሚንስቴር ሰነድ፣ ገቢን ለማሳደግ የታቀደው የታክስ ፖሊሲዎችን በማሻሻል ተጨማሪ ገቢ በማግኘት ነው። መንግሥት እስከ 2020 ዓ፣ም ተግባራዊ የሚያደርጋቸው የታክስ ማሻሻያዎች፣ የታክስ ገቢው ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የሚኖረውን ጥምርታ በ4 መቶኛ እንደሚያደርሱት ሰነዱ ይጠቅሳል። መንግሥት ወደፊት ለመጣል ካሰበው ታክስ መካከል፣ በተሽከርካሪ ዝውውር ላይ የሚጣል ታክስ አንዱ ነው።
3፤ በትግራይ ክልል ከሰሜኑ ጦርነት አስቀድሞ ለንግዱ ማኅበረሰብ ለተሰጡ ብድሮችና ወለዶች መንግሥት 'ፖለቲካዊ መፍትሔ' እንዲሰጥ ለመጠየቅ የፊርማ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ እየተካሄደ መኾኑን ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል። በክልሉ ከተሞች የተጀመረው የፊርማ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ መስማቱን ዘገባው አመልክቷል። ብሔራዊ ባንክ፣ ባንኮች በክልሉ ከጦርነቱ በፊት ለሰጧቸው ብድሮች የመክፈያውን ጊዜ እስከ ታኅሳስ 2017 ዓ፣ም እንዲያራዝሙ ቀደም ሲል ማዘዙ አይዘነጋም።
4፤ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል ዮሃንስ ቧያሌው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ክርስቲያን ታደለና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ካሳ ተሻገር ትናንት ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር። ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ቀደም ሲል ክሱን አሻሽሎ እንዲያቀርብ በሰጠው ትዕዛዝ ላይ ውሳኔ ለመስጠት የተቀመጠ ቢኾንም፣ ዓቃቤ ሕግ ግን ክስ ማሻሻል የለብኝም በማለት የፍርድ ቤቱን ሂደት በጠቅላይ ፍርድ ቤት ለጊዜው አሳግዶታል። ፍርድ ቤቱ ይሻሻል ያለው ክስ፣ ዓቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ የተነሳ ሞተዋል ያላቸውን ከ1 ሺሕ በላይ ሰዎች ዝርዝርና አድራሻ እንዲገልጽ ነበር።
5፤ በመርካቶ ሸማ ተራ በተባለ አካባቢ ትናንት ምሽት የተነሳው ከፍተኛ የእሳት አደጋ በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል። በርካታ የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎችና ሠራተኞች የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር ከአራት ሰዓታት በላይ ከፍተኛ ጥረት እንዳደረጉ የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አባቤ አስታውቀዋል። ከምሽቱ 1:00 ሰዓት ገደማ የተነሳውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር የተቻለው፣ ከምሽቱ 5:00 ሰዓት በኋላ እንደነበር ታውቋል። [ዋዜማ]