أحدث المنشورات من ✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞ (@tsehaye_tsidk) على Telegram

منشورات ✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞ على Telegram

✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞
👉ፀሐየ ጽድቅ
የሕይወት መብራት የጽድቅ ብርሃን

በዚህ channel ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የጠበቁ ትምህርቶች እና መዝሙሮች እንዲሁም ቅዱሳንን እንዘክራለን ስለቅዱሳን እንማማራለን ዕለታዊ ዜና ቤተ-ክርስቲያ ስንክሳር ግጻዌ ጥያቄና መልስ እንዲሁም በየእለቱ አጥንትን የሚያጠነክሩ መንፈስን የሚያለመልሙ ጽሁፎችን ወደ እናንተ እናደርሳለን፡፡
ቻናሉን ይቀላቀሉ
@Tsehaye_Tsidk
ሼር ያርጉ!!
1,809 مشترك
818 صورة
7 فيديو
آخر تحديث 12.03.2025 09:47

أحدث المحتوى الذي تم مشاركته بواسطة ✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞ على Telegram

✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞

11 Mar, 12:21

109

ፕሮቴስታንታዊ enculturation በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ሲናኝ እያየን ነው። የዐደባባይ ዝርፊያዎች ቀጥለዋል።

እስካሁን ካቶሊኮች ነበሩ በየሔዱበት ሀገር የሚተገብሩትን የመመሳሰል ስልት (enculturation stratagy ይሉታል) እኛ ሀገርም ሲተገበሩ የነበሩት። ከትውፊታቸው፣ ከሥርዓታቸው የተለየ ቢሆን እንኳ በሔዱበት ሀገር ያለውን የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ወስደው ይጠቀማሉ።

በዚህ ምክንያት ነው ቫቲካን የማትጠቀመውንና የማያምኑበትን ታቦት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ካቶሊኮጭ የሚያከብሩ፣ ንግሥ የሚያነግሡ የሚመስሉት፣ መስቀል ደመራና ጥምቀትን በዐደባባይ ለማክበር የሚሞክሩት፣ ከቤተ ክርስቲያን ያስኮበለሏቸውን መርጌታዎች ተጠቅመው ማኅሌት የሚቆሙ የሚመስሉት፣ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ነዋያተ ቅድሳት የሚጠቀሙት፣ ወዘተ (ይህ የEnculturation ስልታቸው ከክርስትና በጣም የራቀ ባህላዊ ሥርዓት ባላቸው ማኅበረሰቦች ዘንድ ቢሆንም እንኳ ይተገብሩታል።)

ይህን የሚያደርጉበት ዓላማና ግብ አላቸው።

፩ኛ ለጊዜው «አንድ ነን፤» የሚል መልእክት በማድረስ በኦርቶዶክሳውያን ምእመናን አእምሮና ምልከታ ዘንድ በአስተምህሮ ያለንን ልዩነት መሸፋፈንና፣ የተለያየ ሃይማኖት ተከታዮች የመሆናችንን እውነት ቀስ በቀስ መሸርሸርና ድንበሩን ማጥፋት ነው።

፪ኛ የመጨረሻ ግቡ ደግሞ በ«አንድ ነን፤» ተኩላዊ ቅሰጣ በተፈጠረው ምቹና ለም ልብ ላይ የራሳቸውን ትምህርት በቀስታ የመዝራትና ከትውልዶች በኋላ በኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ ምትክ የራሳቸውን ማንበር ነው።

፫ኛ የጠላት ዲያብሎስ ወኪሎች በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚፈጽሙት መልከ ብዙ ጥቃት
ፍሬ አፍርቶ የቤተ ክርስቲያናችን ህልውና አደጋ ላይ ቢወድቅ የሚበተነውን ምእመን «አለንላችሁ» በማለት ወደ ራሳቸው መውሰድና ቤተ ክርስቲያንን መውረስ ሌላው ጊዜና አጋጣሚ የሚጠብቁለት ግባቸው ነው። ለዚህ ሥራ ስኬት የተዘጋጀ በጀትና የሰው ኃይል ስላላቸው ለመፈጸም አይቸገሩም።

አሁን ደግሞ ፕሮቴስታንቱም ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተሐድሶ ስም ለማስረግ ያደረገው ሙከራ ያሰበውን ያክል ስላልተሳካለት የካቶሊክን የመመሳሰል ስልት በመንግሥት በታገዘ ንጥቂያና ቅሰጣ ለመተግበር እየሞከረ ነው።

ከኦርቶዶክሳውያን ምን ይጠበቃል?

፩ኛ ይህን ሴራ ማወቅና ማሳወቅ የመጀመሪያው ራስን መከላከያ መንገድ ነው።

፪ኛ የተኛውን ቤተ ክህነት በመቀስቀስ፣ ወይም ፈቃደኛ የሆኑ ኦርቶዶክሳዊ የሕግ ሰዎችን በመጠቀም የቤተ ክርስቲያን አልባሳት፣ ነዋየ ቅድሳት፣ መጻሕፍት፣ ወዘተ ሕጋዊ ከለላ እንዲያገኙ ማድረግ ይኖርብናል።

፫ኛ ከሁሉ በላይ ግን የራሳችን፣ የቤተሰቦቻችንን እና በአካባቢያችን ያሉ ኦርቶዶክሳውያንን መንፈሳዊ ሕይወት መጠበቅ እና እንዲጠበቅ ድርሻችንን መወጣት፣ በቤተ ክርስቲያን ያለንን ሱታፌ ማሳደግ ቀዳሚው ነው።

~ @Wondwosen Wubie

@Tsehaye_Tsidk
@Tsehaye_Tsidk
✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞

09 Mar, 19:16

148

የሰውን ልጅ በሩህሩህነት አሸንፈው። ቀናተኛውን በመልካምነትህ እንዲደነቅ አድርገው፤ ሁሉንም ሰው ውደድ ነገር ግን ከሁሉም ሰው ጋር ርቀትህን ጠብቀህ ኑር።

             #አባ_እንጦንስ
✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞

09 Mar, 10:22

174

ቅዳሴ ተሰጥኦ (ማለትም በቅዳሴ መሀሉ ምዕመኑ የሚመልሰው ወይም የሚሳተፈው ) ነው

በየግሩፑ ያጋሩት
@Tsehaye_Tsidk
@Tsehaye_Tsidk
✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞

09 Mar, 06:58

168

#ምኩራብ
(የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት)

ምኩራብ ማለት ለአምልኮትና ለትምህርት ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጥ የአይሁድ ቤተ ጸሎት ነው። ጌታ በመዋዕለ ስብከቱ በእስራኤል ሀገር ብዙ ምኩራቦች ስለነበሩ እየገባ ወንጌልን አስተምሮባቸዋል። በዚህም “ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ ወመሀረ ቃለ ሃይማኖት” እንዲል ቅዱስ ያሬድ ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገብቶ የሃይማኖት ቃልን አስተማረ። ከሚለው የቅዱስ ያሬድ ዜማ ሥያሜውን አግኝቷል።

በምኩራብ ጸሎትና ትምህርት ይፈጸምበታል። መሥዋዕት ግን አይከናወንም። መሥዋዕት ግን በታላቁ ቤተ መቅደስ በኢየሩሳሌም ብቻ ይፈጸም ነበር። በዚህ ሳምንት የሚነገረው ታሪክ ጌታ ቤተ መቅደሱን የገበያ ማዕከል አድርገው ሸቀጥ ዘርግተው በጉን ላሙን ርግቡን እየሸጡ አገኛቸው። በዚህ ተቆጥቶ በጉን ላሙን ርግቡን ከምኩራብ አስወጥቶ ሸቀጣቸውንና መደርደሪያቸውን እንዲሁም ወርቅና ብራቸውን በነፋስ በተነባቸው ይላል።

በዚህ ሁኔታ ከቤተ መቅደስ አስወጥቶ "ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች እናንተ ግን የሽፍቶችና የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኋት" በማለት ወቅሷቸዋል። “አሰስሉ ወአውፅኡ ዘንተ እምዝየ ወኢትረስዩ ቤተ አቡየ ቤተ ምሥያጥ” እንዲል ዮሐ. 2፥16፤ ማቴ. 21፥13። ይህን ተአምር በማሳየት ቤተ ጸሎት የተቀደሰ ከገበያ የተለየ መሆኑን አስተምሮበታል።

በሰንበተ ምኩራብ ጌታ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለዋጮችን ማስወጣቱ ወርቅና ብሩን በነፋስ መበተኑ ላሞችን በጎችን በጅራፍ መግረፉ ቤተ መቅደሱን ማንጻቱ ወዘተ ይነገራል።

(የዚህም በዓል ታሪክ ዝርዝር ሁኔታው ማቴዎስ 21፥12-13 ላይ ተጠቅሷል፡፡)

#የቅዳሴ_ምንባባት፦

ቆላስ. 2፥16-23
«እንግዲህ በመብል ወይ በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፣ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው፡፡ .......፡፡»

ያዕ. 2፥14-26
«ወንድሞቼ ሆይ፣ እምነት አለኝ የሚል፣ ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን ......፡፡»

ሐዋ. 1ዐ፥1-9
«በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነው ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበር፡፡ እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ፡፡ ....፡፡"

#ምስባክ- መዝ 68፥9
እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ
ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ
ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ፡፡

(የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና
የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና
ነፍሴን በጾም አስመረርኋት፡፡)

#ወንጌል፡- ዮሐ 2፥12-25
«ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፣ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ፡፡ የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ ወደ መቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤ የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፣ .....፡፡»

(ከመድብለ ታሪክ እና ግጻዌ የተወሰደ)

#ይቀላቀሉን!!
@Tsehaye_Tsidk
@Tsehaye_Tsidk
✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞

08 Mar, 20:33

165

🫵 አንተ ሰው ቃለ እግዚአብሔርን ተማር፤ ባትለወጥም ዝም ብለህ ተማር! ኹልጊዜ ተማር። ላትስተካከል ትችላለህ፤ ላትለወጥ ትችላለህ፤ ግን ተማር። ቢያንስ ቢያንስ ጥሩ ሰው እንኳን ባትኾን ራስህን ለመውቀስ የምትችልበት ዓቅም ታገኛለህ። ካልተማርክ ግን ራስህን እንኳን መውቀስ የምትችልበት ዓቅም አታገኝም። ስለዚህ ተማር! ስትማር ቢያንስ ኃጢአት እንኳን ስትሠራ ራስህን እየወቀስክ ትሠራለህ። ይህች የንስሓ በር ትኾንልሃለች፡፡ አንድ ቀን ወደ ንስሓም ትመራሃለች።

  
#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ

ጌታም በወንጌል እንዲህ አለ:-
"የሰውነትህ
#መብራት ዓይንህ ናት። ዓይንህ ጤናማ በሆነች ጊዜ ሰውነትህ ሁሉ ደግሞ ብሩህ ይሆናል። ዓይንህ ታማሚ በሆነች ጊዜ ግን ሰውነትህ ደግሞ የጨለመ ይሆናል።"
(ሉቃ 11:34)


ሰላም እደሩልኝ....🧡

@Tsehaye_Tsidk
✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞

08 Mar, 08:08

179

+ የክፉ ቀን ‘ተመስገን’ +

አንዱ ሰው “የሰው ልጅ ሕይወት ውጣ ውረድ የበዛው ነው” ሲሉት “የኔ ሕይወት ታዲያ ምነው ውረድ ብቻ ሆነብኝ? ውጣው የታለ?” አለ ይባላል። ይህ ሰው እውነት አለው። አንዳንዴ የሰው ልጅ በመከራ ተወልዶ፥ በመከራ ኖሮ፥ በመከራ ሲያልፍ እንመለከታለን። በሕይወታችን ውስጥ መከራቸው ከመብዛቱ የተነሣ “ምነው ባለፈላቸው” ብለን የምንለምንላቸው ሰዎች አይጠፉም። በዚህ ጊዜ ‘ብርቱ ትግል የሚሰጠው ለብርቱ ወታደር ነው’ የሚለውን እያሰብን እንጽናናለን። በእርግጥ ትግሉ የሚመጣው ከእግዚአብሔር ብቻ አይደለም፤ ይህንን ደግሞ ከኢዮብ ታሪክ በላይ የሚያስረዳ ላይኖር ይችላል። 

ጻድቁ ኢዮብ ሰይጣን የሚቀናበት፥ ሰዎች ለመሆን የሚመኙት፥ እግዚአብሔር ደግሞ እጅግ የሚወድደው ሰው ነበር። ሰዎች የሌሎች ሰዎችን ሙገሳ በሚፈልጉበት ዓለም፥ ከፈጣሪው ዘንድ “በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹማና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም” (ኢዮ 1፡8) ተብሎ የተመሰከረለት ነው። ይህ መሆኑ ግን ከመከራ አልሸሸገውም። ከአሥር ሺህ በላይ የሆኑት ከብቶቹ የተወሰኑት ተማርከው፥ የተወሰኑት ተገድለው፥ የተቀሩት ደግሞ ከሰማይ በወረደ እሳት ተበልተው መጥፋታቸው ተነገረው። ሦስቱንም መርዶ የሰማው በተከታታይ ከመሆኑ የተነሳ፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ‘እርሱም ገና ሲናገር ሳለ ሌላ መጥቶ እንዲህ አለው’ እያለ ተገልጿል። አንዳንድ መርዶ የቀደመውን መርዶ ሰምተህ እስክትጨርስ ስንኳን አይጠብቅህም። ኢዮብ ይህንን ሁሉ ሰምቶ መጮኽ ሳይጀምር ሌላው ደርሶ ልጆቹ የነበሩበት ቤት በድንገተኛ ነፋስ ተንዶ አሥሩም ልጆቹ እንደሞቱ ነገረው።

ይህ ሁሉ ሆኖበት ኢዮብ ምን አለ? መጎናጸፊያውን ቀድዶ፥ ራሱን ተላጭቶ፥ በምድር ተደፍቶ ሰግዶ “እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔር ነሣ፤ እግዚአብሔርም እንደ ፈቀደ ሆነ፤ የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን” (ኢዮ 1፡21) ብሎ እግዚአብሔርን አመሰገነ። ንብረቱን ሁሉ ያጣው ኢዮብ እግዚአብሔርን አከበረ! አሥር ልጆቹን በአንዴ የተነጠቀው በምድር ላይ ሰግዶ እግዚአብሔርን አመሰገነ!

ልጆቿን ሁሉ በማጣቷ “የወላድ መካን” የሆነችው የኢዮብ ሚስት ወደ ባሏ ስትመጣ ጤናውንም ሳይቀር አጥቶ ከራስ ጸጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ በቁስል ተሸፍኖ አገኘችው። ደህና መካሪ መስላ ‘እግዚአብሔርን ስደብና ሙት’ (ኢዮ 2፡10) አለችው። ብዙዎቻችን ቢሆን “እውነትሽን ነው! በጽድቅ ሆኜ በኖርኩ እንዴት እንዲህ ያደርገኛል!” ብለን ለስድፍ አፋችንን በከፈትን ነበር። ኢዮብ ግን ቀና ብሎ አይቷት “አንቺ ከሰነፎች ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ!” ብሎ ገሰጻት። ከዚያም በኋላ ለሁላችንም ምክርና መጽናኛ የሚሆን ነገርን እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፥ ክፉውን ነገርስ አንታገሥምን?” (ኢዮ 2፡10)

ይህ ጥያቄ ለእኛም ነው። ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ከተቀበልን፥ ክፉውን አንታገሥምን? እግዚአብሔርን በሕይወታችን ውስጥ ባሉ ስኬቶች ብቻ መመዘን አይበቃንምን? እግዚአብሔር ቢከፋም ቢለማም፥ ቢደላም ቢጨንቅም የሚመለክ ታላቅ አምላክ አይደለምን? 

እግዚአብሔርህ ሆይ፥ ለውጣውም ለውረዱም ተመስገን!

@Tsehaye_Tsidk
@Tsehaye_Tsidk
✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞

06 Mar, 20:46

208

+++ "ለዚህ መች ጸለይን?" +++

በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ቤተሰባዊ የሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲረዳ የተቋቋመ የካህናት (የቀሳውስት) ጉባኤ ነበረ። የቀድሞው የቅብጥ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ሺኖዳም ይህን ስብስብ እንዲቀላቀሉ ለአባ ሚካኤል ባቀረቡላቸው ጥሪ መሠረት የዚህ ጉባኤ አባል ሆኑ። ታዲያ አንድ ቀን አባ ሚካኤልን ጨምሮ የጉባኤው የበላይ ኃላፊ የሆኑት ጳጳስና ሌሎችም ካህናት የተጣሉ ባልና ሚስትን ሊያስታርቁ ተሰበሰቡ። ይሁን እንጂ የባልና የሚስትየው ጠብ እንዲህ በቀላሉ ሊበርድ የሚችል አልነበረምና ጳጳሱም ሆኑ ቀሳውስቱም ሁለቱን ለማስማማት ብዙ ቢጥሩም ግን አልተሳካላቸውም።

በስተመጨረሻም ጳጳሱ ወደ አባ ሚካኤል እየጠቆሙ "አባ ሚካኤል ለምን ዝም ብለው ተቀመጡ? እስኪ እርሶ ይሻላል ብለው የሚያስቡትን ይንገሩን?" አሏቸው። አባ ሚካኤልም "ብፁዕነትዎ፣ እንጸልይበት!" አሉ። ጳጳሱም "ይህን ጉባኤ ከመጀመራችን በፊት እኮ ጸልየናል" ቢሏቸው አባ ሚካኤል "አዎን አባታችን፤ ለዚህ ችግር ግን አልጸለይንም" አሉ። ከዚያ ሁሉም ለጸሎት ተነሡ። በጳጳሱ ፈቃድ በአቡነ ሚካኤል መሪነት ጸሎት አደረጉ። ጸሎቱ እንዳለቀም እነዚያ የተጣሉት ባልና ሚስት ክርክራቸውን ሁሉ ትተው በጉባኤው ፊት በፍቅር ተቃቀፉ። ሰላም አወረዱ። ይህን ጊዜ ከቀሳውስቱ አንዱ "አባታችን ከመጀመሪያ እንዲህ ቢሉን ምን ነበር?! አሳረፉን እኮ" ብለው ጉባኤውን ፈገግ አሰኙት።

እኛስ ያልጸለይንባቸው ስንት ችሮች አሉብን?

ብዙ ቋጠሮ የሚፈታው ግን በብዙዎች የሚረሳው ትልቁ መፍትሔ፣ ጸሎት!!!

(አባ ሚካኤል ኢብራሂም (1899-1975) የግብጽ ቤተ ክርስቲያንን ለበርካታ ዓመታት በትጋት ያገለገሉና እጅግ የሚያስቀና የጸሎት ሕይወት የነበራቸው አባት ናቸው።)

#ዲያቆን_አቤል_ካሳሁን

@Tsehaye_Tsidk
@Tsehaye_Tsidk
✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞

06 Mar, 10:25

205

አንድ ካህን አባት አንድ ትዕግስት የጎደለው ወጣት የንስሀ ልጅ ነበራቸው። ይህ ወጣት በትንሹም በትልቁም ቱግ እያለ፤ ሰዎችን ያስቀይም ነበር።ከአንደበቱ ክፉ ቃላቶችን ስለሚያወጣ ከሰው ጋር መስማማት አልቻለም። ትዕግስት ፈፅሞ የለውም።ይህ ነገር እጅግ ያሳሰባቸው አባትም፤ ልጁን የሚለውጡበት ዘዴ ሲያወጡ ሲያወርዱ ቆይተው አንድ መፍትሄ ላይ ደረሱ።አንድ ቀንም በቀረጢት ሙሉ ሚስማር ያዙና ልጁን አስጠርተው እንዲህ አሉት“ልጄ ሆይ …ይህን በቀረጢት ያለውን ሚስማር ተቀበለኝ፤ሁሌም ትዕግስት በጎደለህ ጊዜ እና ሰው ባስቀየምክ ቁጥር አንድ ሚስማር የእንጨቱ አጥር ላይ ሰካ” አሉት።ልጁ ምንም ግራ ቢገባውም አባቱ እንዳዘዙት ማድረግ ጀመረ።

በመጀመሪያ ሰሞን በጣም ብዙ ሚስማሮችን ሰካ….ቀስ እያለ ግን በቀን እንጨቱ ላይ የሚሰካቸው ሚስማሮች ቁጥር እየቀነሰ መጣ…. እያለ…እያለ….በመጨረሻ ምንም ክፉ ያልተናገረ ቀን አንድም ሚስማር ሳይሰካ ዋለ።ልጁ በጣም ታጋሽ ሆኖ ባህሪው ተስተካከለ ማለት ነው። ይህንንም ለአባቱ አበሰረ።
አባም “ እሰይ ልጄ……አሁን ደግሞ ምንም ያልተናደድክ ቀን እና ክፉ ያልወጣህ ቀን በፊት ከሰካሃቸው ሚስማሮች ውስጥ አንዱን ንቀል” አሉት። ልጁ እንደተባለው አደረገ፤ከቀናት በኋላ ሁሉንም ሚስማሮች ነቅሎ ጨረሰ።ወደ አባም ሄዶ ሚስማሮችን አስረከበ።

አባም አንዲህ አሉት “አየህ ልጄ……አሁን የሰካሃቸውን ሚስማሮች ነቅለህ ጨርሰሃል…..በጣም ታጋሽ ሆነሃል ማለት ነው፤ነገር ግን እስቲ አጥሩን ተመለክት….ፈጽሞ እንደ ድሮው ሊሆን አይችልም፤ሚስማሩ ቢወጣም ተበሳስቷል። ክፉ ንግግርም ልክ እንደ ሚስማር ነው፤ሺህ ጊዜ ይቅር ብትልም፤ እንደሚስማሩ ጠባሳ ጥሎ ያልፋል ፤እናም ልጄ……..በህይወት ትዕግስት ይኑርህ…..አንደበትህን ቆጥብ” ብለው አስተማሩት። አንደበት ይገራል፤ አንደበትን የሚገራው መልካም አስተሳሰብ ነው።

በክፉ ንግግር ፤ በጭቅጭቅ፤ በስድብ እስከዛሬ ምን መልካም ነገሮች ሲፈጠሩ አየን? ስህተቶቻችን እየጎለጎልን በመነካከስ ምን ልዩነቶችን አጠበብን?………”ቃላት” ለሰው ልጅ ኑሮ የእስትንፋስ ያህል ዋጋ አለው። በቃላት ጦርነት ይነሳል፤በቃላት ሰላም ይሰፍናል…….
እስቲ ለጥቂት ቀናት እራሳችንን እንፈትነው…….መልካም መልካሙን በመናገር
ተወዳጆች ሆይ መጽሀፍ ቅዱስም እንዲህ ይለናል
-ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፥ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤ ከክፉ ፈቀቅ ይበል፥ መልካምንም ያድርግ፥ ሰላምን ይሻ ይከተለውም፤ 1ኛ የጴጥሮስ 3:10
-ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ናቸው፤ የሚወድዱአትም ፍሬዋን ይበላሉ።
መጽሐፈ ምሳሌ 18:21
የጠቢባን ከንፈር እውቀትን ትዘራለች፤ የሰነፎች ልብ ግን እንዲህ አይደለም። መጽሐፈ ምሳሌ 15:7

@Tsehaye_Tsidk
@Tsehaye_Tsidk
✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞

03 Mar, 17:28

229

+ ቅዱስ አጠራር +

ቅዱስ ጳውሎስ ፦ ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፥ ይህም እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ እንደ ሥራችን መጠን አይደለም ሲል ተናገረ፡፡ /2ጢሞ 1፡9/
መጠራትን ሁላችንም ተጠራርተን እናውቃለን፡፡ በጩኸትም በፉጨትም በእጅ ምልክትም በጥሪ ወረቀትም በስልክም ተጠራርተን እናውቃለን:: ቅዱስ አጠራር ግን እንደምን ያለ ነው? እግዚአብሔር ቅዱስ ነውና እርሱ ሰውን የሚጠራበት ጥሪም የተቀደሰ ነው፡፡ ይህ ጥሪ እንደምን ያለ ነው? ቅዱስ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ጥሪ ለምን ቅዱስ አጠራር አለው?

እርሱ ራሱ ከተጠራበት አጠራር እንጀምር ይሆን? ሳውል/ ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ሊያስርና ሊያሰቃይ ከበላይ አካል ደብዳቤን ተቀብሎ በደስታ እየቸኮለ ሲሔድ የበላዮች በላይ ደማስቆ ላይ አስቆመውና ጠራው፡፡ ለብዙዎች ሞት ፈቃድ ተቀብሎ ተሹሞ ሲመጣ ጌታ ከመንገድ አስቁሞ ለብዙዎች መዳንን እንዲሰብክ ፈቃድ ሠጠው፡፡ የጦር ዕቃ ጭኖ እየዛተ ሲመለስ ጦርና ጋሻውን አስጥሎ ራሱን ምርጥ ዕቃ አደረገው፡፡ በቅዱስ አጠራር የጠራው እግዚአብሔር ነውና!

ስለ ጴጥሮስ አጠራርስ ምን እንናገር? የሃምሳ አምስት ዓመቱ ዓሣ አጥማጅ ጎልማሳ ፣ ሌሊቱን ሙሉ መረቡን ጥሎ የሚያድረው ትዕግሥተኛ እንዴት እንደተጠራ ልብ በሉ፡፡ ለእርሱ ብዙ ዓሣ ከመያዝ በቀር ምንም ሕልም አልነበረውም፡፡ የታንኳዎቹን ቁጥር ከማብዛት የዓሣዎቹን ገበያ ከማስፋፋት በቀር በጎልማሳ ዕድሜው አዲስ ሕልም አልነበረውም፡፡

የመጦሪያ ዘመኑን እንዴት እንደሚያሳልፍና የዕድሜ ፀሐዩ ስትጠልቅ መረቡን አጥምዶ ለመመልከት ዝግጁ ከመሆን በቀር ምንም አዲስ ዕቅድ አልነበረውም:: ጀልባው ላይ ተሳፍሮ ደግ ደጉን የሚያወራው ናዝራዊ ግን ድንገት መጥቶ ጎልማሳነቱን እንደ ንሥር አደሰው፡፡ ሕይወቱን እንደ አዲስ አሁን እንደተወለደ ሕፃን ከሃምሳ ዓምስት ዓመቱ አስጀመረው፡፡ በዚያ ዕድሜው የሦስት ዓመት መንፈሳዊ ኮሌጅ ገብቶ በእሳትና በነፋስ ታጅቦ ተመርቆ : በሰባ ሁለት ቋንቋ እንደ አዲስ አፉን ፈትቶ እንዲያወራና ዓሣ ማስገሩን እርግፍ አድርጎ ትቶ በወንጌል መረብ ሰውን አጥማጅ እንዲሆን አደረገው፡፡ በድንቅ አጠራሩ የጠራው እግዚአብሔር ነውና!

  ስለ ሐዋርያው ናትናኤልስ እንናገር ይሆን? ጓደኛው ፊልጶስ "የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘነው" ብሎ ሲጠራው ብዙም ደስ አላለውም ነበር፡፡ የናዝሬቱ መሲሕ የሚል ቃል ሲስማ ከይሁዳ ቤተልሔም መሲህ እንደሚመጣ ከሚያውቀው ትንቢት ጋር አልገጥም ብሎት ‘ደግሞ ከናዝሬት መሲህ ይነሣል እንዴ?’ እያለ በምሁራዊ ትዝብት ተውጦ እስቲ ልየው በሚል ንቀት ሳይዋጥለት ነበር የመጣው፡፡ እስቲ ልየው ብሎ ያገኘው ናዝራዊ ግን ራሱን ልቡ ድረስ ተመለከተው፡፡ ሳያውቅ የጠቀሰውን ጥቅስ አስጥሎ የሚያውቀውን የራሱን የተሸሸገ ማንነት  ሲነግረው መቋቋም አልቻለም፡፡ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብሎ መሰከረ፡፡  እርሱ እንደመሰለው የጠራው ጓደኛው ፊልጶስ አልነበረም ፤ በቅዱስ አጠራሩ የጠራው እግዚአብሔር ነውና!

የቀሬናዊው ስምዖን አጠራር ግን ከሁሉ የባሰ ነበር ፤ እርሱ መንገደኛ ነበረ ፤ መንገድ አላፊ እንደሚጣደፍ እየተጣደፈ ነው፡፡ ሰንበት ሳይገባበት ለመጓዝ ከኢየሩሳሌም እየቸኮለ ሲወጣ አንድ ብዙ ሕዝብ አጅቦት ግማሹ በማዘን የሚጮኽለትና ግማሹ በጥላቻ የሚጮኽበት የሕማም ሰው ሲንገላታ ተመለከተ::

መንገዱን ገታ አድርጎ ትንሽ ሊመለከት እንጂ ሊቆይ ሃሳብ አልነበረውም:: ነገር ግን ወታደሮች ግድ አሉት:: ሳያስበው የጌታ የሕማሙ ተካፋይ የመስቀሉ ተከታይ ሆነ:: ዓለም የዳነበትና የጌታ ደምና ወዝ የፈሰሰበትን ቅዱስ መስቀል ተሸክሞ አንድ ምዕራፍ ተጉዋዘ:: ያገዝነው ሲመስለን የሚያግዘንን ያገለገልነው ሲመስለን የሚያከብረንን ክርስቶስን ተጠግቶ መቼም የማይገኝ ክብርን ተጎናጸፈ:: በዚያች ዕለት መስቀሉን ተሸከም ብለው የጠሩት እንደመሰለው ሮማውያን ወታደሮች አልነበሩም:: በቅዱስ አጠራር የጠራው እግዚአብሔር ነውና!

ጌታ ሆይ እኔ ባሪያህን የጠራህበት ቅዱስ አጠራር እንዴት ያለ ይሆን?  ስንቴ ጠርተኸኝ እንዳልሰማ ጥዬ ሔጄ ይሆን? የአንተን ጥሪ ገፍቼ ለዓለም ጥሪ ጉዋጉቼ ስንቴ ሔጄ ይሆን? "አብዝቼ ብጠራቸው አጥብቀው ከፊቴ ራቁ" ካልካቸው መካከል እሆን ይሆን?

እባክህን ባልሰማህም ጥራኝ : ባልመጣም ጥራኝ : ጴጥሮስ በባሕር ላይ እንደለመነህ "ወደ አንተ እመጣ ዘንድ እዘዘኝ" : እንደ አልዓዛር "ውጣ" ብለህ በቅዱስ አጠራር ጥራኝ:: እንደ ማቴዎስ ከቀራጭነት ገበታዬ ላይ : እንደ ዘኬዎስ ከዛፍ ላይ : እንደ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በሰረገላዬ ላይ ብቻ ባገኘኸኝ ቦታ ጥራኝ::

ሙት በሚቀሰቅስ ማዕበል በሚገሥፅ ድምፅህ ባልሰማህም ጥራኝ : ጆሮዬ አልሰማ ካለህ እንደ ማልኮስ ጆሮ ሠጥተህ አንተን ብቻ በሚሠሙ ጆሮዎች ፈውሰኝና ጥራኝ:: ዓይኔ ዓላይ ካለህ ከአፈር በምራቅህ ለውሰህ እያየሁ እንድመጣ አድርገህም ቢሆን ጥራኝ:: አሁን በቅዱስ አጠራርህ ስትጠራኝ ካልሰማሁህ በኁዋላ ልትፈርድ ስትመጣ "እናንተ የአባቴ ቡሩካን ወደ እኔ ኑ" የሚለው ቅዱስ አጠራርህንም ሳልሰማ መቅረቴ አይደል? አሁን ጥሪህን ካልሰማሁ በኁዋላ ቃለ ሕይወትን አልሰማምና እንደ ሥራዬ ሳይሆን እንደ አንተ አሳብና ጸጋ መጠን ጥራኝ!

"ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፥ ይህም እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ እንደ ሥራችን መጠን አይደለም"

#ዲ/ን _ሄኖክ_ኃይሌ

@Tsehaye_Tsidk
@Tsehaye_Tsidk
✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞

03 Mar, 16:14

172



የዐቢይ ጾምን መግባት ምክንያት በማድረግ የተሰጠ ትምህርት
(በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)


እንግዲህ አሁን ራስን አለመግዛት እንዴት አደገኛ እንደ ኾነ ተገነዘባችሁን? አሁን ደግሞ ጾም እንዴት ያለ በረከትን እንደሚያመጣ እንመልከት፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ አርባ ቀን ስለ ጾመ የእግዚአብሔር ሕግ የተጻፈበትን ጽላት ሊቀበል ችሏል /ዘጸ.24፥18/፡፡ ከተራራው ሲወርድ ግን አብዝቶ የሚበላና ኃጢአተኛ የኾነ ሕዝብ የእግዚአብሔርን ሕግ ቢቀበል ምንም ትርጉም የለውም በማለት በብዙ ምልጃ የተቀበለውን ጽላት ከእጁ ጥሎ ከተራራው በታች ሰበረው /ዘጸ.32፥19/፡፡ በመኾኑም፥ ይህ ታላቅ ነቢይ በሕዝቡ ኃጢአት ምክንያት በሰበረው ጽላት ፈንታ እንደ ቀድሞ ያለ ሌላ ጽላት ለመቀበል አርባ ቀንና አርባ ሌሊት መጾም ነበረበት /ዘጸ.34፥28/፡፡ በእሳት ሠረገላ ተነጥቆ ወደ ሰማያት የተወሰደው፣ እስከ ዛሬ ድረስም ሞትን ያልቀመሰው ታላቁ ነቢይ ኤልያስም ልክ እንደ ሙሴ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሟል /1ኛ ነገ.19፥8/፡፡ ልክ እንደዚሁ መንፈሰ ብርቱው ዳንኤልም አያሌ ቀናትን ይጾም ነበር፤ እንደ ሽልማትም እጅግ የሚያስደንቅ ራእይን ተቀብሏል፡- ቍጡዎቹን አንበሶች እንደሚያስለምዳቸው፣ ጥንተ ተፈጥሯቸው ተለውጦ ሳይኾን ከእነ ተናጣቂ ባሕርያቸው እንደ የዋህ በጎች እንደሚኾኑለት ዐየ፡፡ የነነዌ ሰዎችም እንደዚሁ በጾም መድኃኒትነት ከእግዚአብሔር ዘንድም ምሕረትን አግኝቷል፡፡ እንዲያውም በነነዌ የጾሙት ሰዎች ብቻ አልነበሩም፤ እንስሳቱም ጭምር እንጂ፡፡ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ሊያደርገው ከተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም /ዮና.3፥10/፡፡ ከብሉያትና ከሐዲሳት እንዲህ በመጾማቸው ምክንያት የተጠቀሙ ብዙ ሰዎችን መጥቀስ እንችላለን፤ ነገር ግን የኹላችንም ጌታ ወደ አደረገው መምጣት ሲገባን አገልጋዮቹን የምናየው ለምንድን ነው? እንደምታውቁት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሟል (ማቴ.4፥2፣ ሉቃ.4፥2)፡፡ ሲጾምም ዲያብሎስን ድል አድርጎ አሳይቶናል፡፡ ይኸውም የጾምን ትጥቅ ልንታጠቅ እንደሚገባንና ከዚህ በምናገኘው ኃይልም ብርቱ የሚኾን ጠላታችንን ድል ማድረግ እንደሚቻለን አርአያ ሲኾነን ነው፡፡

እዚህ ላይ ምናልባት ነገሮችን ጠለቅ አድርጎ የሚመረምርና ሐሳበ ልቡናዉን ንቁ ያደረገ ሰው፡- “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልክ እንደ አገልጋዮቹ አንዲት ቀንስ እንኳን ሳይጨምር የጾመው ስለ ምንድን ነው?” ብሎ ጥያቄ ሊያነሣ ይችላል፡፡ ጌታችን ይህንን ያደረገው ያለ ምክንያት ሳይኾን ከጥበቡና ሰውን ከመውደዱ የተነሣ ነው፡፡ ይኸውም፦ “ወደዚህ ምድር የመጣው ሥጋን ሳይለብስ ነው፤ ሰውም የኾነው በምትሐት ነው” ብለው ለሚነሡ ዐብዳን ሐሳባቸውን ይገታ ዘንድ አስቦ ልክ እንደ አገልጋዮቹ አንዲት ቀንስ እንኳን ሳይጨምር ጾመ፡፡ እንግዲህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደዚህ በገቢር ጾሞ ሳለ እንኳን እንደዚህ ያለ ምክንያት የሚያመጡ ከኾነ ከቸርነቱ የተነሣ ሊያመጡት የሚችሉትን ሰበብ አስቀድሞ ባይጥለው’ማ እንደ ምን የከፋ ነቀፋን ባመጡ ነበር? በመኾኑም፥ የእኛን ባሕርይ ገንዘብ እንዳደረገና ከእኛ የራቀ እንዳልኾነ ሲያስተምረን ከቀደሙት አባቶች ሳያተርፍ አርባ ቀን ጾመ፡፡

እጅግ የምወዳችሁ ምእመናን ሆይ! የጾም ጥቅምዋ ምን ያህል የበዛ እንደ ኾነና ነፍሳችን ከዚህ ብዙ ጥቅምን እንደምታገኝ ከጌታችን እና ከአገልጋዮቹ ተምረናል፡፡ ስለኾነም የጾም ወራት ሲቃረብ ግድየለሽነትንና ሞራለ ቢስነትን ከእኛ አስወግደን ንዑድ ክቡር የሚኾን ጳውሎስ፡- “የውጭው ሰውነታችን ይበልጥ ሲጠፋ የውስጡ ሰውነታችን ይበልጥ ይታደሳል” ብሎ እንዳስተማረን እጅግ ደስ ተሰኝተን ልንቀበለው ይገባናል ብዬ እማልዳችኋለሁ /2ኛ ቆሮ.4፥16/፡፡ ጾም የነፍስ ምግብ ነው፡፡ ምግበ ሥጋ ሰውነታችን እንዲወፍር እንደሚያደርግ ኹሉ ጾምም ነፍስን ያበረታል፤ ፈጣንና መንፈሳዊ ክንፍን ይሰጣታል፤ ወደ ሰማያዊ ምሥጢር ገብታ በፅሞና እንድትያዝ ያደርጋታል፤ የዚህን ዓለም ተድላና ደስታ እንድትንቅ ያስችላታል፡፡ ቀላል ጭነትን የተሸከሙ መርከቦች ፈጥነው ባሕሩን እንደሚሻገሩ፣ እጅግ ብዙ ጭነትን የተሸከሙት ግን ባሕሩንና ወጀቡን ቶሎ ማለፍ እንደሚያቅታቸው ኹሉ ልክ እንደዚሁ ጾምም ውሳጣዊ ዓይናችን እንዲበራ፣ የዚህ ዓለም ፈተናዎችን በቀላሉ መቋቋም እንድንችል፣ ወደ ሰማያዊ ምሥጢር እንድንገባ በዚያም ስላሉ አይነገሬ በረከቶችን እንድናስብ፣ በዚህ ዓለም ላይ ያሉት ኹሉም ነገሮች እንደ ጠዋት ጤዛ ፈጥነው የሚያልፉ እንደ ኾኑ እንድንገነዘብ ታደርለች፡፡ ከዚሁ በተቃራኒ አብዝቶ መብላትና ራስን አለመግዛት ደግሞ አእምሯችን የጠፋ፣ ሥጋችን የወፈረ፤ ውስጣችን በእግር ብረት የተጠፈረ፣ በዚህ ኹሉ ተከበንም እጅግ በከፉ ምግባራት የተያዝን፣ የዘለዓለማዊ ሕይወታችን ጠላቶች ኾነን እንድንጓዝ ያደርጉናል፡፡

ይቀጥላል....

(ኦሪት ዘፍጥረት ቅጽ 1 ገጽ 23-31 በገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተተረጎመ)


@Tsehaye_Tsidk
@Tsehaye_Tsidk