أحدث المنشورات من ✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞ (@tsehaye_tsidk) على Telegram

منشورات ✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞ على Telegram

✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞
👉ፀሐየ ጽድቅ
የሕይወት መብራት የጽድቅ ብርሃን

በዚህ channel ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የጠበቁ ትምህርቶች እና መዝሙሮች እንዲሁም ቅዱሳንን እንዘክራለን ስለቅዱሳን እንማማራለን ዕለታዊ ዜና ቤተ-ክርስቲያ ስንክሳር ግጻዌ ጥያቄና መልስ እንዲሁም በየእለቱ አጥንትን የሚያጠነክሩ መንፈስን የሚያለመልሙ ጽሁፎችን ወደ እናንተ እናደርሳለን፡፡
ቻናሉን ይቀላቀሉ
@Tsehaye_Tsidk
ሼር ያርጉ!!
1,809 مشترك
818 صورة
7 فيديو
آخر تحديث 12.03.2025 09:47

أحدث المحتوى الذي تم مشاركته بواسطة ✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞ على Telegram

✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞

01 Mar, 21:51

255

#ቅድስት
#የዐቢይ_ጾም_ሁለተኛ_ሳምንት

የቅድስና ባለቤት የሆነው እርሱ እግዚአብሔር አምላክ ነው። እቀደስ አይል ቅዱስ፣ እባረክ አይል ቡሩክ ነው። በእርሱ የባሕርይ ቅድስና እኛን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ ቡሩክ ሆኖ ባረከን፣ ቅዱስ ሆኖ ቀደሰን፣ሕያው ሆኖ ሕያዋን አደረገን። የጸጋ ቅድስናንም ከእርሱ አገኘን። ቅድስናው የተለየ፣ የከበረ፣ የሚመሰገን፣ የሚሰጥ/የሚያድል፣ የሚያነጻ፣ የሚባርክ እናም የሚያስተሰርይ ስለሆነ እንከን፣ ጉድለት የሌለበት ምሉዕ ነው። ለባለሟሎቹ ቢሰጠው የማይጎድል፣ ተከፍሎ የሌለበት ቅድስና ሆኖ እኛም የቅድስና በጸጋ ተካፋይ ሆነናል።

የተሰጠንን ቅድስና ገንዘብ እንድናደርግ እና እንድንጠቀምበት ደግሞ በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በምጽዋትና በሌሎች በጎ ምግባራት መትጋት ይገባናል። ‹‹እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ›› እንዲል፡፡ (ዘፍ.፪፥፫፣ ዘሌ.፲፱፥፪) የት መሄድ እንዳለብንም በግልጽ ልበ አምላክ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ፤ ስለ ትምህርትህና ስለ እውነትህ ስምህን አመሰግናለሁ፤ በሁሉ ላይ ቅዱስ ስምህን ከፍ ከፍ አድርገሃልና›› ይላል። (መዝ.፻፴፯÷፪) የተቀደሰን መሥዋዕት በተቀደሰ ቦታ እንፈጽማለን። መቼ ቢሉ፣ በሰንበት፣ በበዓላት በማኅበረ ዐቢይ/ክርስቲያኖች በሚሰበሰቡበት፣ ስመ እግዚአብሔር በሚጠራበት፣ ታቦት  ባለበት፣ እግረ እግዚአብሔር በቆመበት ቅዱስ ስሙን ከፍ ከፍ በማድረግ ቅድስናን ገንዘብ እናደርጋለን።

ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ለዐቢይ ጾም ሁለተኛው እሑድ በአዘጋጀው ምስጋና አማካኝነት ዕለቱ ‹‹ቅድስት›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ትርጉሙም ‹‹የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች›› ማለት ነው።  (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ገጽ ፯፻፹፬) ቅድስት የሚለው ቃል ዕለቱ ‹‹ቅድስት›› ተብሎ የተሰየመበት ምክንያት ስለ ዕለተ ሰንበት እንዲሁም ስለ እግዚአብሔር አምላክ ፍጹም ቅድስና የሚያወሳ በመሆኑ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ፍጥረታቱ የእርሱን ስም በማመስገን ይኖሩ ዘንድ ለቅድስና ሕይወት ፈጥሯቸዋልና በሰንበት እሑድ ክርስቲያኖች የቅድስና ተግባራትን ከሌላው ቀን አብዝተው ይፈጽማሉ፡፡ ዕለት ከተግባር፣ ስም ከክብር የተባበረባት ክብርት ሰንበት ቅድስት ስለሆነች ቅዱስ ያሬድ “ቅድስት” ብሎ ጠራት። ይኸውም የምትቀድስ፣ ከብራ የምታከብረን፣ አክብረናት የምንከብርባት በመሆኗ ነው።

ለዚህም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓ “ግነዩ ለእግዚአብሔር ወጸውዑ ስሞ ወንግርዎሙ ለአሕዛብ ምግባሮ፤ ሀቡ ስብሐተ ለስሙ፤ አክብሩ ሰንበተ ተገበሩ ጽድቀ፤ ዝግቡ ለክሙ መዝገበ ዘበሰማያት ኀበ ፃፄ ኢያማስኖ ወኢይረክቦ ሰራቂ፤ ድልዋኒክሙ ንበሩ ዘበላዕሉ ጸልዩ ኀበ ሀሎ ክርስቶስ” ትርጉም፦ “ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ስሙንም ጥሩ፤ ሥራውንም ለአሕዛብ ንገሯቸው፤ ለስሙም ምስጋናን አቅርቡ ሰንበትን አክብሩ፤ እውነትንም አድርጉ፤ ብል የማያበላሸው ሌባም የማያገኘው በሰማያት ያለ መዝገብን ለእናንተ ሰብስቡ፤ ተዘጋጅታችሁም ተቀመጡ፤ ክርስቶስ ወዳለበት ወደ ላይ አስቡ፡፡“  ስለዚህ ሰው ሰንበትን አክብሮ ጾሞ ጸልዮ፣ ቅድስናን ጠብቆ መኖር እንዲችል እግዚአብሔር የፍቅሩ መገለጫ የሆኑ ትእዛዛቱ ይነግሩናል።

#ቅዱስ_ያሬድም_ወቅቱን “#ቅድስት” ብሎ ሲሰይም፦

፩. #የአርባ_ቀን_ጾም_መጀመሪያ_በመሆኑ፦ ዕለቱ ከዐቢይ ጾም ቀናት ውስጥ አርባው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም መጀመሪያ ስለሆነች፣

፪. #ቅድስት_ሰንበት_ላይ_በመዋሉ፣ እንግዲህ “የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ” ተብሏል፡፡ (ዘፀ.፳፥፰) የሰንበትን ቀን አስቀድሞ የቀደሰ የባረከ ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና፡፡” (ዘፍ.፪፥፫)

“ከምእመናን ወገን አንድስ እንኳን በእሑድ ቀን ለገንዘብ መትጋት፣ ገንዘቤን አምጣ ብሎ መጣላት እና ዋስ መያዝ አይገባውም። ሁሉም ምእመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን በንጽሕና በትሕትና ሆነው። ዳኛ ግብሬን፣ አበዳሪ ብድሬን፣ ኤጲስ ቆጶስ ዐሥራት በኵራት፣ ነጋ ድራስ ቀረጥ አምጡ ይሉናል ብለው ሳይፈሩ ይምጡ።

፫. #ወቅቱ_ወርኃ_ጾም_በመሆኑ፦ ምእመናን ይህንን ወቅት በጾም፣ በጸሎት፣ በእንባ፣ በስግደት፣ በአርምሞ፣ በመልካም ሥራ ቅድስናን የምናገኝበት፣ ጊዜው ሰው ወደ እግዚአብሔር አብዝቶ የሚተጋበት ወቅት በመሆኑ፣ ለእግዚአብሔር የሚገባ ነገር ለማድረግ የነገር ሁሉ መጀመሪያ፣ ለመልካም ነገር መነሻው በቅድስና በንጹሕ ልቡና መቅረብ ስለሆነ ቅድስት ብሏታል።  “እስመ ጾም እማ ለጸሎት ወእኅታ ለአርምሞ ወነቅዓ ለአንብዕ መቅድመ ኩሉ ግብር ሠናይት፤ ጾም ማለት የጸሎት እናት፣ የትሕትና እኅት፣ የእንባ ምንጭ፣የመልካም ሥራ ሁሉ መጀመሪያ ናት” እንዳለው ቅዱስ ያሬድ። ”ጾምን ቀድሱ፤ ጉባኤውንም ዐውጁ” የተባልን የተሰጠንን የጸጋ ቅድስና በእጃችን ላይ መኖሩን አመላካች ቃል ነው። (ኢዩ.፩፥፲፬)

፬. #የወንጌል_ትእዛዝ_በመሆኑ፡ ዕለቱን ተጠቅሞ ዓለምን አስተምሮበታል። “ዛቲ ዕለት እንተ ገብረ እግዚአብሔር ንትፈሣሕ ወንትሐሠይ ባቲ”  ትርጉም፡- “ይህች ዕለት እግዚአብሔር የሠራት ቀን  ናት፤ ሐሤትን እናድርግ፥ በእርስዋም ደስ ይበለን።” (መዝ.፻፲፯፥፳፬) ቅዱስ ዮሐንስም በራእዩ ሰንበት የጌታ ቀን ስለመሆኗ እንዲህ ይላል፤ “በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፡፡” (ራእ. ፩፥፲)

ሊቃውንቱ በፍትሐ ነገሥት “ተጋብኡ ኵሎ ዕለት ኀበ ቤተ ክርስቲያን ወፈድፋደሰ በዕለተ ሰንበት ወበበዓላት ወበዕለተ ትንሣኤ ዘውእቱ ዕለተ እሑድ” ትርጉም፦ “ሁልጊዜ በቤተ ክርስቲያን ተሰብሰቡ፤ ይልቁንም በዕለተ እሑድ፣ በዕለተ ቀዳሚት፣ በጌታ በዓላት ወደ ቤተ ክርስቲያን ተሰብሰቡ” በማለት አዘውናል፡፡ (ፍትሐ ነገሥት፣ ገጽ ፪፶፬)

በትጋት ጾመን፣ ጸልየን ርስቱን እንድንወርስ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃ፤ የቅዱሳን በረከት ይጠብቀን።

የዕለቱ መዝሙር (ከጾመ ድጓ)፦ ግነዩ ለእግዚአብሔር

#ምንባባት
➛ ፩ኛ ተሰ.፬÷፩-፲፫
➛ ፩ኛ ጴጥ.፩÷፲፫-ፍጻ.
➛ ሐዋ. ፲÷፲፯-፴

#ምስባክ
“እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ::
አሚን ወሠናይት ቅድሜሁ፣
ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ፤

(እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ፈጠረ፡፡ እምነትና በጎነት በፊቱ፣ ቅድስናና የክብር ገናናነት በመቅደሱ ውስጥ ናቸው፡፡”
(መዝ.፺፭÷፭)

#ወንጌል
(ማቴ.፮÷፲፮-፳፭)

#ቅዳሴ
ዘኤጲፋንዮስ 

(ማኅበረ ቅዱሳን)

@Tsehaye_Tsidk
@Tsehaye_Tsidk
✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞

01 Mar, 18:40

212



የዐቢይ ጾምን መግባት ምክንያት በማድረግ የተሰጠ ትምህርት
(በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)


የዛሬው ንግግሬ ለአንዳንዶቻችሁ አዲስና እንግዳ እንደሚኾንባችሁ ዐውቃለሁ፡፡ ነገር ግን በዓላማ (ድኅነትን ለማግኘት ብለን) እንጹም እንጂ እንዲሁ የልማድ ባርያዎች አንኹን ብዬ እማልዳችኋለሁ፡፡ በየቀኑ ከልክ በላይ በመብላትና በሆዳምነት የምታገኙት ጥቅም ምንድን ነው? ጥቅምስ ይቅርና ጭራሽ የከፋ ጉዳትን የሚያመጣባችሁ ነው፡፡ ተመልከቱ! ከልክ በላይ በመጠጣትና በመስከር የማስተዋል ልቡና ሲታወር የጾም ጥቅምዋም ምንም ምልክትን ሳያስቀር ያጠፋዋል፡፡ እስኪ ልጠይቃችሁ፦ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ብዙ ወይንን ከሚጠጡ፣ በየመሸታ ቤቱ አድረው ፀሐይ ከምትወጣባቸው፣ ለሚያገኛቸው ሰው ኹሉ ደስ ከማያሰኙ፣ ለቤተ ሰቦቻቸው ግድ ከሌላቸው፣ ሕፃን ዐዋቂው ከሚሳለቅባቸው፣ ራሳቸውን ባለመግዛታቸውና ያለጊዜው በኾነ ደስታ ደስ በመሰኘታቸው ምክንያት ከእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን ካጡ ከእነዚህ ሰዎች በላይ ማን ጎስቋላ ሰው አለ? ቅዱስ መጽሐፍስ እንዲህ የሚል አይደለምን?፡- “ሰካሮች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” /1ኛ ቆሮ.6፥10/፡፡ ወዮ! እንደ ጠዋት ጤዛ ለሚጠፋ፥ ያውም እጅግ ከባድ ጉዳትን የሚያመጣ እርካታን ለማግኘት ብለው፥ የዘለዓለምን መንግሥትን የሚያጡት እነዚህ ሰዎች ከሚያገኛቸው መከራ በላይ ምን መከራ አለ?

እዚህ ጉባኤ ከተሰበሰባችሁ ምእመናን መካከል አንድም ሰው እንኳን ቢኾን በዚህ ዓይነት ስንፍና መያ’ዝ የለበትም፤ እግዚአብሔር ይህን በፍጹም አይወደውም፡፡ ከዚህ ይልቅ እያንዳንዷን ቀን በትዕግሥትና ራስን በመግዛት እንዲሁም አብዝቶ መብላት ከሚያመጣው የመከራ አውሎ ነፋስ ተጠብቃችሁ ወደ ነፍሳችሁ ወደብ - ይኸውም ወደ እውነተኛ ጾም - ልትደርሱ ይገባችኋል፡፡ ይህን ያደረጋችሁ እንደኾነም ከእርስዋ የሚገኘውን ጥቅም በብዙ ታገኛላችሁ፡፡ በሌላ አነጋገር አብዝቶ መብላት የብዙ ውርደቶችና ኃጢአቶች ምንጭ እንደ ኾነ ኹሉ ጾምም የብዙ በረከቶችና ክብር ምክንያት ነው፡፡ እንደምታስታውሱት መጀመሪያ ላይ እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ሲፈጥር ለነፍሳቸው ድኅነት የሚኾን አንድ መፍትሔ እንደሚያስፈልጋቸው ያውቅ ነበር፡፡ በመኾኑም፥ ገና ከመነሻው አንሥቶ ለመጀመሪያው ሰው (ለአዳም) አንድ ትእዛዝ ሰጠው፤ እንዲህ በማለት፡- “በገነት ካለው ዛፍ ኹሉ ብላ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ” /ዘፍ.2፥16-17/፡፡ ይህ ስለ መብላትና ስለ አለመብላት የተገለጠው ኃይለ ቃል በምሥጢር ስለ ጾም የሚናገር ነው፡፡ ምንም እንኳን ሰው ይህቺን ትእዛዝ ይጠብቃት ዘንድ ቢታዘዝም እርሱ ግን አልጠበቃትም፡- ራሱን መግዛት አቃተው፤ ባለመታዘዝ ኃጢአት ውስጥ ወደቀ፤ በራሱ ላይም የሞት ፍርድን አመጣ፡፡ እንደምታስታውሱት ዲያብሎስ ክፉ መንፈስና የእኛ ጠላት ስለ ኾነ የመጀመሪያው ሰው አዳም በገነት ሲኖር እንዴት በነጻነት እንደሚኖርና ሥጋ ለብሶ ሳለ እንዴት የመላእክትን ኑሮ በምድር ላይ እንደሚኖር ተመለከተ፡፡ በመኾኑም፥ እንዴት እንደሚጥለው አሰበ፤ ታላቅ የኾነ ተስፋ በመስጠት ከልዕልናው አዋረደው፤ በዚህ ሽንገላዉም የነበረውን ሀብት ኹሉ ሰረቀው፡፡ በመጠን ያለመኖርና ከዓቅም በላይ የኾነን ነገር የመመኘት ክፋቱ ይኽን ያህል ነው፡፡ ጠቢቡ ሰውም ይህንን እንዲህ በማለት ግልፅ አድርጎታል፦ “በዲያብሎስ ቅንአት ምክንያት ሞት ወደ ዓለም ገባ” /ጥበ.2፥24/፡፡

ተወዳጆች ሆይ! ገና ከጥንቱ የሞት መግቢያው ራስን አለመግዛት መኾኑን ታያላችሁን? በኋላ ዘመን ላይም መጽሐፍ ቅዱስ አብዝቶ መብላትን እንዴት ደጋግሞ እንደሚነቅፈው አስተውሉ፡፡ በአንድ ስፍራ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፡- “ሕዝቡም ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ” (ዘጸ.32፥6)፤ በሌላ ቦታም፦ “በላ፥ ጠጣም፤ ወፈረ፥ ደነደነም፤ የመድኃኒቱንም አምላክ ናቀ” ይላል /ዘዳ.32፥15/፡፡ የሰዶም ኗሪዎችም እንደዚሁ ያን የማይበርድ ቍጣ በራሳቸው ላይ ያመጡት በዚህ ኃጢአት ምክንያት ነው፡፡ ሌላውን በደላቸውን እንኳን ሳንገልጠው የነቢዩን ቃላት አድምጡ፤ እንዲህ ያለውን፡- “የሰዶም ኃጢአት ይህ ነበረ፡- እንጀራን መጥገብ” /ሕዝ.16፥49/፡፡ በአጭር አነጋገር መብል ብዙውን ጊዜ እንደ ምንጭ ውኃ ነው፤ ወይም የክፋት ኹሉ ሥር ነው፡፡

ይቀጥላል....

(ኦሪት ዘፍጥረት ቅጽ 1 ገጽ 23-31 በገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተተረጎመ)


@Tsehaye_Tsidk
@Tsehaye_Tsidk
✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞

01 Mar, 08:26

231



የዐቢይ ጾምን መግባት ምክንያት በማድረግ የተሰጠ ትምህርት
(በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)


እንኪያስ እጅግ የምወዳችሁ ምእመናን ሆይ! ከኹሉም በፊት እነዚህን ነገሮች በስፋት እንነጋገርባቸው ዘንድ፤ ዳግመኛም አንዳች የሚረባንን ነገር ይዘን ወደ ቤታችን እንመለስ ዘንድ ቃላችንን በታላቅ ትጋትና ጉጉት ኾናችሁ ትቀበሉት ዘንድ አሳስባችኋለሁ፡፡ ኹላችንም ወደዚህ ጉባኤ ስንመጣ እንዲሁና ያለ ዓላማ አይደለም፡፡ ወሬ ለማውራት፤ ምን እንደ ተባለ እንኳን ሳንሰማ ለማጨብጨብ፤ ከዚያም ምንም የሚረባ ነገርን ሳንይዝ ወደ ቤታችን ለመመለስ ወደዚህ ጉባኤ አልመጣንም፡፡ እኔም የመጣሁት ለነፍሳችሁ ድኅነት የሚጠቅም አንዳች ነገርን ለመናገር ነው፤ እናንተም ስትመጡ በእኔ በባሪያው አድሮ እግዚአብሔር የሚናገረውን ነገር አድምጣችሁ ለመጠቀምና አንዳች የሚረባ ነገርን ይዛችሁ ወደ ቤታችሁ ለመመለስ ነው፡፡

ተመልከቱ! ቤተ ክርስቲያን ማለት ቤተ ድኅነት ናት፡፡ ወደ እርስዋ የሚመጡትም ለችግራቸው ተገቢውን መድኃኒት አግኝተው መሔድ አለባቸው፡፡ ተግባራዊ የኾነ ለውጥ ሳያመጡ ቃለ እግዚአብሔርን መማር ብቻ ምንም ጥቅም እንደሌለው ሲናገርም ንዑድ ክቡር የሚኾን ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፡- “በእግዚአብሔር ፊት የሚጸድቁት ሕግን የሚያደርጉት እንጂ ሕግን የሚሰሙ አይደሉም” /ሮሜ.2+13/። በቃል መነገሩ፤ በልብ መታሰቡ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት መዘገቡ ከፍ ከፍ ይበልና አምላካችን ክርስቶስም ሲያስተምር፡- “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ኹሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም” ብሏል /ማቴ.7፥21/፡፡ ስለዚህ ተወዳጆች ሆይ! ቃሉን በመስማታችን ብቻ አንዳች የምንጠቀመው ነገር ስለሌለ የሰማነውን የምናደርግ እንጂ የምንሰማ ብቻ አንኹን፡፡ እንዲህ ከኾነም እምነታችን ሕይወት ያለው እምነት ይኾናል፡፡

በመኾኑም፥ ስለ ጾም የሚሰጠውን ስብከት ለማዳመጥ እዝነ ልቡናችሁን ክፈቱ፡፡ ከትሕት እና ዓይናፋር ሙሽሪት ጋር ለማነጻጸር ያህል፡- ሙሽሪቱን በሰርግ አዳራሽ ኾነው የሚቀበሏት ሰዎች አስቀድመው ቤቱን ያስጌጡታል፤ ይጠርጉታል፡፡ የቆሸሸ ልብስን የለበሰ ሰው ወደ ሰርጉ አዳራሽ እንዳይገባ ያደርጉታል፡፡ ወደ አዳራሹ መግባት የሚችለው የሰርግ ልብስ የለበሰ ሰው ብቻ ነው፡፡ እናንተም እንዲህ ልታደርጉ ይገባችኋል፦ ልቡናችሁን በማንጻት፣ አብዝቶ ከመብላትና ራስን ካለመግዛት በመራቅ የምግባር እናት፣ የማስተዋልና የሌሎች ምግባራት ኹሉ ንግሥት የምትኾን ጾምን ደጀ ልቡናችሁን በመክፈት ልትቀበሏት ይገባችኋል፡፡ ይህን ያደረጋችሁ እንደ ኾነ ታላቅ ሐሴት ታደርጋላችሁ፤ እርስዋም ቁስለ ነፍሳችሁን ትፈውስላችኋለች፡፡ ሌላ ምሳሌ መስዬ ብነግራችሁ፦ ሐኪሞች በሕሙማን ሰውነት ውስጥ ያለውን ቆሻሻና መርዘኛ ፈሳሽን ማስወገድ ሲፈልጉ መጀመሪያ ሕሙማኑ ምግበ ሥጋን ከመውሰድ እንዲቈጠቡ ያደርጉዋቸዋል፡፡ ሕሙማኑ ለጊዜው ምግብን ከመብላት ካልተከለከሉ ግን ሐኪሞቹ የሚሰጡት መድኃኒት የተፈለገውን ያህል ውጤት አይሰጥም፡፡ እኛም የነፍስንና የሥጋን ቁስል የምትፈውሰውን ጾም ስንቀበላት ከዚህ በላይ ልንኾን ይገባናል ብዬ እነግራችኋለሁ፡፡ ድኅነትን የምንሻ ከኾነ ልቡናችንን ንጹህና ንቁ በማድረግ ልንወስዳት ይገባናል፤ እንዲህ ካልኾነ ግን ከጥቅሟ ይልቅ ጉዳቷ ያመዝናል፡፡

ይቀጥላል....

(ኦሪት ዘፍጥረት ቅጽ 1 ገጽ 23-31 በገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተተረጎመ)


@Tsehaye_Tsidk
@Tsehaye_Tsidk
✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞

28 Feb, 10:06

251

+• ልብ የሚዘልቁት የቅዱስ ኤፍሬም ድንቅ ጸሎቶች •+

ጸሎቶቻችን ሁሉ በምድራዊ ነገሮች ታጥረው እየተጉተመተሙ ለሚቀሩብን ከንቱ ለምንሆን ለእኛ የትሑቱ ቅዱስ ኤፍሬም ጸሎቶች እጅጉን አስተማሪ ናቸው:: በዚህ ተርጉሜ ያቀረብኳቸው ሁለት ጸሎቶች የሁላችንን ጸሎት ሰማያዊ በሆነው ቅኝት ያስተካክሉልን ዘንድ ተስፋ አደርጋለሁ:: ቅዱስ ኤፍሬም ስለ ምን እንደሚጸልይ ልብ እንበል:: ጸሎቱን እንጸልየው፤ የራሳችንንም ጸሎት እንቃኝበት::

+•ጸሎት አንድ•+

አቤቱ አምላኬ፤ የሕይወቴ ጌታ፤ በስንፍና እና በተመራማሪነት መንፈስ፤ እንዲያውም በመላቅ ምኞት እና በከንቱ ልፍለፋ መንፈስ እንዳልበከል ፈቃድህ ይሁንልኝ::

ከዚህ ይልቅ ለእኔ ለአገልጋይህ የንጽሕና እና የትሕትናን መንፈስ፤ እንዲያውም የትእግስትን እና ባልንጀራን የመውደድን መንፈስ ስጠኝ::

አቤቱ ጌታዬና ንጉሤ ሆይ፤ ለባልንጀሮቼ ክፉ ያለማሰብን እና የራሴን ኃጢአቶች የማየትን ጸጋ ስጠኝ::

አንተ ብጹዕ ነህና፤ ዛሬም ዘወትርም፤ ለዘለዓለሙ አሜን::

+• ጸሎት ሁለት •+

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የነገሥታት ንጉሥ፣ በሕይወትም ሆነ በሞት ላይ አንተ ኃያል ነህ:: ምስጢር የሆነውንና የተደበቀውን አንተ ታውቃለህ፤ አሳቦቻችንም ሆነ ስሜቶቻችን ከአንተ የተሸሸጉ አይደሉም::

ከምንታዌነት ፈውሰኝ፤ እኔ በአንተ ፊት ክፉ አድርጌያለሁ:: አሁን ሕያው መሆኔ እለት ከእለት ስትቀንስ፤ ኃጢአቶቼ ደግሞ ይጨምራሉ::
አቤቱ ጌታ፣ አምላከ ሥጋ ወነፍስ፣ የሥጋዬንም ሆነ የነፍሴን እጅግ ደካማ መሆን አንተ ታውቃለህ::

አቤቱ ጌታዬ፤ በድካሜ ውስጥ ጉልበትን ስጠኝ፣ በሐዘኔም ውስጥ አጽናኝ:: በቸርነት የላቅህ ጌታ ሆይ፤ አንተ ያደረግህልኝን ማሰብ እንዳልተው አመስጋኝ ነፍስን ስጠኝ:: በደሎቼን ሁሉ ይቅር በለኝ እንጂ ብዙ የሆኑትን ኃጢአቶቼን አታስብብኝ::

አቤቱ ጌታዬ፤ የኔ የክፉውን ኃጢአተኛ ጸሎት አትናቀው:: ከዚህ በፊት እንደጠበቀኝ ሁሉ ለወደፊትም እንዲጠብቀኝ በጸጋህ እስከመጨረሻው አጽናኝ:: ጥበብን ያስተማረኝ ያንተ ጸጋ ነው፤ የእርሷን [የጥበብን] መንገድ የሚከተሉ ብጹዓን ናቸው፤ የክብር አክሊልን ይቀዳጃሉና::

አቤቱ ጌታ ሆይ፤ ምንም የማልረባ ብሆንም ስንኳ አመሰግንሃለሁ፤ አከብርሃለውም፤ ለእኔ ያለህ ምህረት ገደብ የለውምና:: ረዳቴና ጠባቂዬ አንተ ነህ:: የግርማዊነት ስምህ ለዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን::

ለአንተ ለአምላካችን ምስጋና ይሁን::
                  አሜን::

@Tsehaye_Tsidk
@Tsehaye_Tsidk
✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞

26 Feb, 06:53

299


የዐቢይ ጾምን መግባት ምክንያት በማድረግ የተሰጠ ትምህርት
(በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)

የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን እንደዚህ በልጆቿ ስትደምቅ እናንተም ጉባኤውን ለመታደም ደስ ብሏችሁ ተሰባስባችሁ ስትመጡ ዐይቼ ሐሴት አደረግሁኝ፤ ደስም አለኝ፡፡ ፊታችሁ እንዴት በደስታ እንደ ተመላ ስመለከት ጠቢቡ “ልብ ደስ ሲለው ፊት ይበራል” እንዳለው ልባችሁ ምን ያህል እንደ ተደሰተ ተገነዘብሁኝ (ምሳ.15፥13)፡፡ በመኾኑም፥ ዛሬ ማለዳ የተነሣሁት ከወትሮው በተለየ ትጋት ነው፡፡ ይኸውም ይህን መንፈሳዊ ደስታ ከእናንተ ጋር እንድካፈልና ቀጣዩ ወራት ቁስለ ነፍሳችሁ ድኅነት የሚያገኝበት ወርሐ ጾም መኾኑን አበሥራችሁ ዘንድ ነው፡፡ የኹላችንም ጌታ ልዑል እግዚአብሔር፥ ልክ እንደ ደግ አባት ባለፉት ወራት ለሠራነው ኃጢአት ሥርየት እናገኝበት ዘንድ ሽቶ መድኃኒት የሚኾን ቅዱስ ጾምን አዘጋጅቶልናልና፡፡

ስለዚህ የነፍሳችን ጠባቂ (እግዚአብሔር) የሕመማችንን ፈውስ የምናገኝበትን መድኃኒት ስላዘጋጀልን እያመሰገንን ወርሐ ጾሙን ደስ ብሎን ልንቀበለው ይገባናል፡፡ ከእኛ መካከል ጾም በመግባቱ አንድስ እንኳን የሚከፋው ወይም የሚበሳጭ ሊኖር አይገባም፡፡ ወርሐ ጾሙን እንዲህ ደስ ተሰኝተን መቀበላችንን ዐይተውም አሕዛብ ይፈሩ፤ አይሁድም ይራዱ፡፡ በእኛና በእነርሱ መካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለ ዐይተውም ይማሩ፡፡ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን በዓል የምትሠራው ምእመናን ራሳቸውን መግዛት እንዲችሉ፣ በበጎ ምግባር ያጌጡ ያሸበረቁ እንዲኾኑ እንደ ኾነ፥ እነርሱ ግን በዓላትን የሚያደርጉት በዘፈንና በስካር ይህንም በመሰለ በሌላ ጸያፍ ግብር ለመንከባለል እንደ ኾነ ለይተው ይወቁ፡፡ በእርግጥም በዓል ተከበረ የሚባለው፡- ሰዎች ነፍሳቸውን ካዳኑበት፣ ውስጣዊ ሰላምንና ፍቅረ ቢጽን ገንዘብ ካደረጉበት፣ ዕለት ዕለት ከሚያጋጥማቸው የነፍስ መታወክ ካረፉበት፣ ያለ ሁካታና ጋጋታ እንዲሁም እንስሳትን በማረድ ከልክ በላይ ከኾነ መብልና መጠጥ ርቀው ያከበሩት እንደ ኾነ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዓል ተከበረ የሚባለው፡- አርምሞንና ጸጥታን፣ ፍቅርንና ደስታን፣ ሰላምንና ራስን መግዛትን፣ እንዲሁም ሌሎች እዚህ መዘርዘር የማንችላቸው ብዙ ምግባር ትሩፋቶችን ገንዘብ ያደረግንበት እንደ ኾነ ነው፡፡
ይቀጥላል.... (ኦሪት ዘፍጥረት ቅጽ 1 ገጽ 23-31 በገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተተረጎመ)

@Tsehaye_Tsidk
@Tsehaye_Tsidk
✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞

25 Feb, 17:14

293

እግዚአብሄር መንግስቱን በርካሽ ዋጋ ሸጠው በቀዝቃዛ ውሃ
በዘለላ እንባ እና
ማረኝ በሚል የወንበዴ ጩኸት

@Tsehaye_Tsidk
✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞

24 Feb, 07:46

288

📌ጾም የሥጋ ረሀብ አይደለም፤ የነፍስ ምግብ እንጂ። አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት ጾም የሥጋ ሥቃይ ሰማዕትነት ወይም መስቀል አይደለም፤ ሥጋ ከነፍስ ጋር የሚተባበርበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ከፍ ከፍ የሚልበት እንጂ። ስንጾም የመጾማችን ዕቅድ ሥጋችንን ለማንገላታት አይደለም፤ ጠባዩን ለመግራት እንጂ። ይህ በመሆኑም አንድ የሚጾም ሰው መንፈሳዊ እንጂ ሥጋዊ ሰው አይሆንም ማለት ነው።

ጾም መናኝ ነፍስ ስለሆነ በምናኔ ውስጥ ያለ ባልንጀራ ሥጋውን ይዞ ይጓዛል እንጂ፤ ብቻውን አይጓዝም። ጾም ማለት የተራበ ሥጋ ማለት አይደለም የመነነ ሥጋ እንጂ። ጾም የሥጋ ረሀብ አይደለም የሥጋ ልዕልና እና ንጽህና እንጂ ለመብላት የሚናፍቅ የሚራብ ሰውነት ያለበት ሁኔታ ማለትም አይደለም፤ መብላት ዋጋውን የሚያጣበትና ሰውነት ለመብላት ካለው ፍላጎት ራሱን የሚያላቅቅበት ሁኔታ እንጂ።

አቡነ ሺኖዳ

@Tsehaye_Tsidk
✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞

23 Feb, 14:11

260

ዘወረደ ብለን እንደጀመርን

ደብረዘይት: ከተራራው አናት ከምግባር ከጽናት ሳንጎድል ያገናኘን፤

ደግሞም በሆሳዕናው ዘምረን፣ በሕማሙ አልቅሰን አዝነን በትንሳኤው ለመደሰት፣ 'ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ' ለማለት ያብቃን፤

---------------------------------
መልካም ሱባዔ ይሁንልን።
ለሀገራችን ሰላሙን ይስጥልን።
ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን፤


@Tsehaye_Tsidk
✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞

23 Feb, 09:15

275

#ዘወረደ
(የዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት )


የዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት ዘወረደ ይባላል፡፡

‹‹ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ›› የሚልና ይህንን የመሳሰለ ጌታ እኛን ለማዳንና ፍቅሩን ሊገልጽልን ከሰማያት መውረዱን ከድንግል ማርያም የእኛን ሥጋ መዋሐዱን የሚያዘክር ምስጋና የሚቀርብበት ሳምንት ነው፡፡ ሌላም ስም አለው #ጾመ_ሕርቃል ይባላል፡፡ ይህ ጾም የጾም መግቢያ የመጀመሪያ ሳምንት የምንጾመው ጾም ሲሆን #ሕርቃል የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡

#ሕርቃል_ማን_ነው?
#ለምንስ_በስሙ_ተሰየመ?
በ614 ዓ.ም ኪርዮስ የተባለ የፋርስ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በመውረር ጥቃት አደረሰ፡፡ በዚህ ወቅት በኢየሩሳሌም ንግሥት ዕሌኒ በሠራችው ቤተመቅደስ ውስጥ ሲገባ ንግሥቷ በክብር አስቀምጣው የነበረው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንደ ፀሐይ ሲያበራ አገኘው፡፡ ቢነካው አቃጠለው ዲያቆናቱን አሸክሞ ሌላውን ንዋየ ቅድሳት ዘርፎ 60 ሺህ የሚደርሱትን አቁስሎ ገድሎ 3 ሺህ የሚሆኑትን ማርኮ ከተማዋንም ቃጥሎ ወደ ፋርስ ባቢሎን ይመለሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ከጦርነቱ ያመለጡ በየዋሻው በየጉራንጉሩ ገብተው የተሸሸጉ ተሰብስበው ከ14 ዓመት በኋላ በ628 ጩኸታቸውንና የደረሰባቸውን በደል ለክርስቲያኑ የሮም ንጉሥ ሕርቃል ይነግሩታል። እርሱም ሐዋርያት ሰውን የገ*ደ*ለ እድሜውን በሙሉ ይጹም ስላሉ እንዴት ላድርገው አላቸው እኛ የአንተን እድሜ ተከፋፍለን እንጾማለን ብለው አንድ አንድ ሳምንት ደርሷቸው ጾሙን በሚገባ ጾመውታል፡፡

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልና የተማረኩ ክርስቲያኖችን ለመመለስ ሕርቃል ጦር መዝዞ በኪርዮስ ላይ ተነሳበት ድል ለሕርቃል ሆነና መስቀሉን ያለበትን አጥቶ ሲቸገር መስቀሉን ሲቀብርና ዲያቆናቱን ሲያስገድል በመስኮት ሆና ያየችው ከኢየሩሳሌም የተማረከች አንዲት ብላቴና አሳይታው አውጥቶ በልብሰ መንግሥቱ ጠቅልሎ ወደ ቁስጥንጥንያ ተመለሰ፡፡ የተማረኩት በሙሉ ነጻ ወጡ ይህን ለማሰብ ለማስታወስ በተጨማሪ በኃጢአት ላይ ድል እንድናገኝ መንፈሳዊ ጦር በውስጣችን እንዲበዛልን መስቀልህ ከምርኮ እንደተመለሰ እኛንም ከኃጢአት ምርኮ መልሰን ለሕርቃል ድል መንሳትንና በጠላቶቹ ላይ ኃይልን እንደሰጠኸው ለእኛም በኃጢአት ላይ ድል መንሳት መንፈሳዊ ኃይልን ስጠን እያልን እንጾመዋለን፡፡

በጌታ ጾም ላይ እንዲጾም የሆነበት ምክንያት ጾሙ የጌታ ጾም በሚጾምበት ወቅት ላይ ስለተጾመ ቤተክርስቲያናችን አብራ ደንግጋዋለች፡፡ እዚህ ላይ በዚያን ጊዜ ለሕርቃል ሕዝቡ ሱባኤ ይዞለታል፡፡ ዛሬም እኛ ለቤተክርስቲያን ያደረግነውን በማሰብ እግዚአብሔር አምላክ ለሕርቃል የሰጠውን በጠላቶቹ ላይ ድል መንሳትን ለእኛም እንዲሰጠን የምንጠይቅበት ስለሆነ የመጀመሪያውን ሳምንት በሕርቃል ሰይመን ጾሙን እንጾማለን፡፡ የእኛ ጠላት የጨለማ ገዥ የሆነው ዲያቢሎስ ነውና እሱን ደግሞ በጾም እንደምናሸንፈው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፡፡

«#ዘወረደ» ማለትም በቀጥታ፣ ቃል በቃል ሲተረጐም «#የወረደ» ማለት ነው፡፡ ይህም በምስጢሩ አምላክ ወልደ አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም በቅዱስ ፈቃዱ ሰው ሆኖ ከሰማየ ሰማያት፣ ከባሕርይ ልዕልናው በትሕትና ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን የሚያመላክት፣ ይህም የሚታወስበት፣ የሚወሳበት የዐቢይ ጾም አንደኛው ሳምንት ነው፡፡ ዮሐ.3፥13፡፡

ሳምንቱ #ሙሴኒ ይባላል። ይህ የተባለበትም ምክንያት በዚሁ ሳምንት መጀመሪያ የሰኞ ዕዝል «ከመዝ ይቤ ሙሴ ፀዓቱ እምትእይንት» «ሙሴ ከከተማ መውጣቱ እንደዚህ ነው አለ» ስለሚል እንደዚሁም የዚሁ ዕለት ማለት የሰኞ አቡን «ሙሴኒ ይቤ በውስተ ኦሪት ምድር ሰናይት» እያለ የሙሴን ታሪክ ስለሚያጠቃቅስ ሳምንቱ ሙሴኒ ተባለ፡፡ ነቢያትም አርባ አርባ ቀን ጾመው ከአለፉ በኋላ የሙሴ ሕግና ትንቢተ ነቢያት ፈጻሚ የሆነው ምላካችን እንደ እነሱ 40 ቀንና 40 ሌሊት መጾሙን የሚያስታውስ ነው፡፡ /ዘፀ.24፥18፤ 1ኛ.ነገ.19፥8፤ ማቴ. 4፥1-4/፡፡

@Tsehaye_Tsidk
@Tsehaye_Tsidk
✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞

23 Feb, 06:14

377

#የካቲት_16

#ኪዳነ_ምሕረት (#የሰባቱ_ኪዳናት_ማሕተም)

የካቲት ዐሥራ ስድስት በዚችም ዕለት የክርስቲያን ወገኖች ሁሉም አማላክን ለወለደች ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓልን ያደርጋሉ። በዚች ዕለት መታሰቢያዋን ለሚያደርግ ስሟን ለሚጠራ ለድኆችና ለችግረኞች እስከ ቀዝቃዛ ውኃ ለሚሰጥ የክብር ባለቤት ከሆነ ከተወደደ ልጅዋ ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳንን ተቀብላለችና።

ይህችም የከበረች እመቤታችን ልጅዋ ንጹሕ ሥጋዋን ተዋሕዶ ከብቻዋ ኃጢአት በቀር የሰውነትን ሥራ ፈጽሞ ስለእኛ መዳን ወዶ ያደረገውን መከራ ተቀብሎ ሙቶ ተነሥቶ ከዐረገና በአባቱ ዕሪና ከተቀመጠ በኋላ እርሷን እናቱን ማርያምን በደቀ መዝሙሩ ዮሐንስ ዘንድ ትቷት ነበር እነሆ ልጅሽ እርሱንም እነሆዋት እናትህ ብሎ አደራ እንዳስጠበቀው።

ከዚያንም ጊዜ ጀምራ እመቤታችን ማርያም ትጸልይ ዘንድ ያለ ማቋረጥ ወደ ልጅዋ መቃብር ሁል ጊዜ ስትሔድ ኖረች ይኸውም ጎልጎታ ነው።

አይሁድም በአዩዋት ጊዜ ቍጣንና ቅናትን ተመልተው በድንጊያ ሊወግሩዋት ወደዱ እግዚአብሔርም ከዓይናቸው ሠወራት ከዚህም በኋላ ዳግመኛ መጥታ በዚያ እንዳትጸልይ ተማክረው ከመቃብሩ ዘንድ ጠባቂዎችን አኖሩ እርሷ ግን በየዕለቱ መሔድን አላቋረጠችም ጠባቆችም አያይዋትም የልጅዋ የጌትነቱ መጋረጃ ሠውርዋታልና መላእክትም መጥተው ያገለግሏታል ጌታችንም ዘወትር ይጐበኛታል የምትሻውንም ይፈጽምላት ነበር።

ከዚህም በኋላ መላእክት ወደ ሰማይ አሳረጓትና የጻድቃንን ማደሪያዎች አሳዩዋት አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብም ወዳሉበት አደረሱዋት ከአዳም ጀምሮ እስከዚያ ዕለት በአካለ ነፍስ ያሉ አባቶች ሁሉ አንቺን ከሥጋችን ሥጋን ከዐፅማችን ዐፅምን ለፈጠረልን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን የአምላክ ልጅ ከአንቺ ሰው በመሆኑ በአንቺ ድህነት አግኝተናል ከጥፋትም የሕይወት ወደብ ሆነሽልናልና እያሉ ሰገዱላት።

ከዚያም ወደ ተወደደ ልጅዋ የእሳት መጋረጃ ወደተተከለበት ወደ ጌትነቱ ዙፉን አደረሷት ጌታችንም እጇን ይዞ ወደ ውስጠኛው መጋረጃ አስገብቶ ከጌትነቱ ዙፋን ላይ አውጥቶ ከእርሱ ጋር አስቀመጣት ያዘጋጀላትንም ዐይን ያላየው ጆሮ ያልሰማው በሰው ልቡና ያልታሰበ ተድላ ደስታን ሁሉ ነገራት።

ከጌትነቱ ዙፋንም በታች የእስራኤል ንጉሥ አባቷ ዳዊትን የነቢያትና የመላእክት ማኀበር እንደ ግድግዳ ከበውት በመሰንቆ ሲያመሰግን አየችው እንዲህም ይላል ልጄ ስሚ በጆሮሽም አድምጪ ወገንሽን የአባትሽንም ወገን ርሺ ንጉሥ ደም ግባትሽን ወዷልና እርሱም ጌታሽ ነውና።

ዳግመኛም የሥቃይን ቦታ ያሳዩዋት ዘንድ መላእክት ከዚያ ውሰዷት ለሰይጣንና ለሠራዊቱ በእርሱ ጐዳና ለሚጓዙ ሁሉ ወደተዘጋጀ ወደጨለማው ዳርቻ አደረሷት እመቤታችን ማርያምም ወዮልኝ ወደዚያ እንዳይመጡ ለሰው ልጆች ማን በነገራቸው አለች መልአኩም አመቤቴ ቡርክት ማርያም ሆይ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ይኖራልና ለአንቺም ከአንቺ በኋላም በቃል ኪዳንሽ ለሚታመኑ አትፍሪ አላት ከዚህም በኋላ ወደ ቦታዋ መለሷት።

ከዚያንም ጊዜ ጀምራ እመቤታችን ድንግል ማርያም ስለ ኋጥአን እጅግ እያዘነች ኖረች እንደ ዛሬይቱም የካቲት ዐሥራ ስድስ ቀን በጎልጎታ ቦታ ቁማ ወደ ልጇ እንዲህ ብላ ለመነች ልጄ ሆይ በእግዚአብሔር አባትህ በክርስቶስ ስምህ ከአንተ ጋርም ህልው በሆነ አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ አማፅንሃለሁ ዓለም ሁሉ ሊሸከምህ የማይችል ሲሆን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በተሸከመችህ ማሕፀኔ አማፅንሃለሁ ልጄ ሆይ ያለ ሕማም ያለ ድካም ከእኔ በመውጣትህ በመወለድህ በአሳደጉህ ጡቶቼ በሳሙህ ከንፈሮቼ በአቀፋህ እጆቼ ከአንተ ጋር በተመላለሱ እግሮቼ አማፅንሃለሁ ። በውስጡ በተኛህበት በረት በተጠቀለልክበት ጨርቅ አማፅንሃለሁ የምወድህ ልጄ ሆይ በልቡናዬ ያለውን ሁሉ ትፈጽም ዘንድ የልመናዬን ቃል ሰምተህ ወደእኔ ትመጣ ዘንድ ወዳንተ ፈጽሜ እማልድሃለሁ።

የብርሃን እናቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንዲህ ብላ በጸለየች ጊዜ እነሆ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወረደ ከእርሱም ጋር አእላፍት መላእክት አሉ በዙሪያውም ሁነው ያመሰግኑታል እርሱም እናቴ ማርያም ሆይ ምን ላድርግልሽ አላት እመቤታችንም ለተወዳጅ ልጅዋ እንዲህ ብላ መለሰችለት ልጄ ወዳጄ ሆይጌታዬና ፈጣሪዬ አለኝታዬና መጠጊያዬ በእናቴ ማሕፀንም ሳለሁ ባንተ ጸናሁ አንተም ጠበቅኸኝ ሁልጊዜም ስም አጠራሬ አንተ ነህ።

አሁንም ጸሎቴንና ልመናዬን ስማኝ ቃሌንም አድምጥ እኔ እናትህ እኔም አገልጋይህ የምለምንህ ይህ ነው መታሰቢያዬን ለሚያደርጉ በስሜ አቢያተ ክርስቲያን ለሚሠሩ ወይም የተራቆተውን ለሚያለብሱ የተራበውን ለሚያጠግቡ የተጠማውንም ለሚያጠጡ የታመመውን ለሚጐበኙ ያዘነውን ለሚያረጋጉ የተከዘውንም ደስ ለሚያሰኙ ወይም ምስጋናዬን ለሚጽፉ ልጆቹንም በስሜ ለሚሰይም በበዓሌም ቀን በማኅሌት ለሚያመሰግን አቤቱ ዐይን ያላየውን ጆሮ ያልሰማውን በሰውም ልቡና ያልታሰበውን በጎ ዋጋ ስጣቸው በአማላጅነቴም የሚታመነውን ሁሉ ከሲኦል ነጻ አድርገው ከአንተ ጋር የደረሰብኝን ረኃቡንና ጥማቱን መከራውን ሁሉ አስብ አለችው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዳልሽው ይሁንልሽ የሰጠሁሽም ቃል ኪዳን እንዳይታበል በራሴ ማልኩልሽ አላት።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእመቤታችን ድንግል ማርያም በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት)
@Tsehaye_Tsidk
@Tsehaye_Tsidk