እስካሁን ካቶሊኮች ነበሩ በየሔዱበት ሀገር የሚተገብሩትን የመመሳሰል ስልት (enculturation stratagy ይሉታል) እኛ ሀገርም ሲተገበሩ የነበሩት። ከትውፊታቸው፣ ከሥርዓታቸው የተለየ ቢሆን እንኳ በሔዱበት ሀገር ያለውን የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ወስደው ይጠቀማሉ።
በዚህ ምክንያት ነው ቫቲካን የማትጠቀመውንና የማያምኑበትን ታቦት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ካቶሊኮጭ የሚያከብሩ፣ ንግሥ የሚያነግሡ የሚመስሉት፣ መስቀል ደመራና ጥምቀትን በዐደባባይ ለማክበር የሚሞክሩት፣ ከቤተ ክርስቲያን ያስኮበለሏቸውን መርጌታዎች ተጠቅመው ማኅሌት የሚቆሙ የሚመስሉት፣ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ነዋያተ ቅድሳት የሚጠቀሙት፣ ወዘተ (ይህ የEnculturation ስልታቸው ከክርስትና በጣም የራቀ ባህላዊ ሥርዓት ባላቸው ማኅበረሰቦች ዘንድ ቢሆንም እንኳ ይተገብሩታል።)
ይህን የሚያደርጉበት ዓላማና ግብ አላቸው።
፩ኛ ለጊዜው «አንድ ነን፤» የሚል መልእክት በማድረስ በኦርቶዶክሳውያን ምእመናን አእምሮና ምልከታ ዘንድ በአስተምህሮ ያለንን ልዩነት መሸፋፈንና፣ የተለያየ ሃይማኖት ተከታዮች የመሆናችንን እውነት ቀስ በቀስ መሸርሸርና ድንበሩን ማጥፋት ነው።
፪ኛ የመጨረሻ ግቡ ደግሞ በ«አንድ ነን፤» ተኩላዊ ቅሰጣ በተፈጠረው ምቹና ለም ልብ ላይ የራሳቸውን ትምህርት በቀስታ የመዝራትና ከትውልዶች በኋላ በኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ ምትክ የራሳቸውን ማንበር ነው።
፫ኛ የጠላት ዲያብሎስ ወኪሎች በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚፈጽሙት መልከ ብዙ ጥቃት
ፍሬ አፍርቶ የቤተ ክርስቲያናችን ህልውና አደጋ ላይ ቢወድቅ የሚበተነውን ምእመን «አለንላችሁ» በማለት ወደ ራሳቸው መውሰድና ቤተ ክርስቲያንን መውረስ ሌላው ጊዜና አጋጣሚ የሚጠብቁለት ግባቸው ነው። ለዚህ ሥራ ስኬት የተዘጋጀ በጀትና የሰው ኃይል ስላላቸው ለመፈጸም አይቸገሩም።
አሁን ደግሞ ፕሮቴስታንቱም ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተሐድሶ ስም ለማስረግ ያደረገው ሙከራ ያሰበውን ያክል ስላልተሳካለት የካቶሊክን የመመሳሰል ስልት በመንግሥት በታገዘ ንጥቂያና ቅሰጣ ለመተግበር እየሞከረ ነው።
ከኦርቶዶክሳውያን ምን ይጠበቃል?
፩ኛ ይህን ሴራ ማወቅና ማሳወቅ የመጀመሪያው ራስን መከላከያ መንገድ ነው።
፪ኛ የተኛውን ቤተ ክህነት በመቀስቀስ፣ ወይም ፈቃደኛ የሆኑ ኦርቶዶክሳዊ የሕግ ሰዎችን በመጠቀም የቤተ ክርስቲያን አልባሳት፣ ነዋየ ቅድሳት፣ መጻሕፍት፣ ወዘተ ሕጋዊ ከለላ እንዲያገኙ ማድረግ ይኖርብናል።
፫ኛ ከሁሉ በላይ ግን የራሳችን፣ የቤተሰቦቻችንን እና በአካባቢያችን ያሉ ኦርቶዶክሳውያንን መንፈሳዊ ሕይወት መጠበቅ እና እንዲጠበቅ ድርሻችንን መወጣት፣ በቤተ ክርስቲያን ያለንን ሱታፌ ማሳደግ ቀዳሚው ነው።
~ @Wondwosen Wubie
@Tsehaye_Tsidk
@Tsehaye_Tsidk