Tirita 97.6 FM Radio (@tiritaradio) Kanalının Son Gönderileri

Tirita 97.6 FM Radio Telegram Gönderileri

Tirita 97.6 FM Radio
ትርታ 97.6 ኤፍ ኤም ''ከልብዎ የቀረበ''

ትርታ ሚዲያ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያለ የንግድ መዝናኛ፣ ዜና እና ቢዝነስ ጭብጥ ያለው ሚዲያ ነው።
1,271 Abone
955 Fotoğraf
7 Video
Son Güncelleme 09.03.2025 15:19

Tirita 97.6 FM Radio tarafından Telegram'da paylaşılan en son içerikler

Tirita 97.6 FM Radio

17 Jan, 14:00

363

እንድታውቁት?
***
የአዲስ አበባ ፖሊስ ከጥር 10 እስከ ጥር 12 ቀን 2017 ዓ/ም ድረስ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶችን አስታውቋል

የአዲስ አበባ ፖሊስ በመግለጫው ከጥር 10 እስከ ጥር 12 ቀን 2017 ዓ/ም ድረስ ጃን ሜዳ እና አቃቂ ቃሊቲ ታቦት ማደሪያ በሚከበረው የከተራና የጥምቀት በዓል ምክንያት የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር የተወሰኑ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ ስለሚሆኑ አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ አስታውቋል፡፡

በዓሉ በሚከበርባቸው ቦታዎች ሁሉ ከአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ የስምሪት አቅጣጫን በመከተል ፀጥታ የማስከበር ተግባሩ የሚከናወን ሲሆን ከዚህም ጋር ተያይዞ ከጥር 10 ቀን 2017 ዓ/ም ጀምሮ በ11ዱም ክ/ከተሞች ጥምቀተ ባህር ባሉባቸው ቦታዎች ሁሉ በ500 ሜትር ክልል ውስጥ ታቦታት ሲወጡና ሲገቡ እንዲሁም በሚሄዱባቸው መንገዶች ለአጭር ጊዜም ይሁን ለረዥም ጊዜ ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ የተከለከለ መሆኑን ገልጿል።

እንዲሁም ከጥር 10 እስከ ጥር 12 ቀን 2017 ዓ/ም ድረስ በጃን ሜዳ እና አቃቂ ቃሊቲ ታቦት ማደሪያ በሚከበረው የከተራና የጥምቀት በዓል ምክንያት በአካባቢው የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር፦

ከ6 ኪሎ አደባባይ - ምኒልክ ሆስፒታል
ከምኒልክ ሆስፒታል - መከላከያ 3ኛ ሻለቃ አደባባይ
ከ3ኛ ሻለቃ አደባባይ - 6 ኪሎ አደባባይ እንዲሁም አቃቂ ቃሊቲ አካባቢ
ከዋልያ ቢራ - ጥሩነሽ ቤይጂንግ ሆስፒታል
ከአቃቂ ዋናው መንገድ - ጥሩነሽ ቤይጂንግ ሆስፒታል
ከ08 - አቃቂ ድልድይ ድረስ ከጥር 10 ቀን 2017 ዓ/ም ከጠዋቱ 4:00 ሰዓት ጀምሮ መንገዱ ለተሽከርካሪዎች ዝግ ስለሚሆን አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገዶችን መጠቀም እንደሚገባቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል።

#ትርታ 97.6 FM #ከልብዎ_የቀረበ
Tirita 97.6 FM Radio

15 Jan, 15:50

333

አንድ መቶ አዳዲስ የኤሌክትሪክ አውቶብሶች አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ
***
በአዲስ አበባ 100 የኤሌክትሪክ አውቶብሶች ከአንድ ወር በኋላ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን እንደገለጹት፤ የመዲናዋን የትራንስፖርት አገልግሎት ችግር ለመፍታትና አረንጓዴ ትራንስፖርት ስትራቴጂን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

በዚህም 100 የኤሌክትሪክ አውቶብሶች ገብተው እየተገጣጠሙ ነው ብለዋል። ከአንድ ወር በኋላም አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ መግለጻቸውን ትርታ ከተቋሙ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኤሌክትሪክ አውቶብሶች በብዛት እንዲገቡ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰው፤ ከ15 መቀመጫ በላይ ያላቸው ሚዲባሶችም ገብተው የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ አስታውሰዋል።

#ትርታ 97.6 FM #ከልብዎ_የቀረበ
Tirita 97.6 FM Radio

14 Jan, 13:49

361

የኃይል ስርቆት በፈፀሙ ደንበኞች ላይ እርምጃ ተወሰደ
***
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ደቡብ አዲስ አበባ ሪጅን ቆጣሪዎችን በመነካካት የኃይል ስርቆት በፈፀሙ የወፍጮ ቤት፣ የዳቦ እና የእንጀራ መጋገሪያ ቤት ደንበኞች ላይ እርምጃ መውሰዱን ገለጸ፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ 18 ዘመናዊ ቆጣሪዎች ላይ የኃይል ስርቆት የተፈፀመበት ሲሆን፣ በስርቆት ያጣውን ከ4 ሚለየን ብር በላይ የኃይል ፍጆታ ሂሳብ ገንዘብ ማስከፈሉን የሪጅኑ የኢነርጂ ማኔጅመንት ኃላፊ ለሚ አዱኛ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም 11 ሥርቆት የፈፀሙ ድርጅቶች ላይ ከ5 ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር ቅጣት እንዲቀጡ ማድረጉንና በስርቆት ወቅት ለተበላሹ ቆጣሪዎች 18 ሺህ ብር እንዲከፍሉ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የኃይል ስርቆት መረጃው የተገኘው ተቋሙ በሚጠቀመው መተግበሪያ አማካኝነት ሲሆን በዚህ ዓመት ብቻ በኃይል ስርቆት ላይ በተሳተፉ ስምንት ደንበኞች ላይ ክስ ተመስርቶ ክትትል እየተደረገባቸው እንደሆነና ሦስቱ በሂደት ላይ መሆናቸውን ሃላፊው መናገራቸውን ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

#ትርታ 97.6 FM #ከልብዎ_የቀረበ
Tirita 97.6 FM Radio

14 Jan, 13:17

412

የየመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ህንጻ ቤተክርስቲያን እድሳት ተጠናቆ ተመረቀ
***

እድሳቱ ሁለት ዓመታትን የፈጀው የታሪካዊዉ የመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ህንጻ ቤተክርስቲያን እድሳት ተጠናቆ ዛሬ ተመርቋል ፡፡

ህንፃ ቤተ ክርስቲያኑን መርቀው የከፈቱት ብፁእ ወ ቅዱስ አቡነ ማቲያስ ፓትሪያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ወ እጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሀይማኖት ናቸው።

መንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን 81 አመታትን ያስቆጠረ ባለ ታሪክ ቤተክርስቲያን ነው።

የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊነቱን በጠበቀ መልኩ ዕድሳት እንደተደረገለትም ተጠቁሟል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አክኪያጅና የባሕርዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም ሌሎች ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የመንበረ ፓትርያርክና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ሐላፊዎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የቡራኬ ቤተ ክርስቲያኑ ሥርዓት እየተከናወነ ይገኛል።

በቀደመ ስሙ መካነ ሥላሴ በኋላ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተባለው ይህው ቤተ ክርስትያን የዛሬ 81 ዓመት በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጥር 7ቀን 1936 ዓ.ም ግንባታው ተጠናቆ ቅዳሴ ቤቱ መከበሩን መረጃዎች ያስረዳሉ።

የመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል እድሳት በመጠናቀቁ ታቦቱም በበርካታ ምእመናን ህብረ ዝማሬና እልልታ ታጅቦ ወደ መንበረ ክብሩ ተመልሷል።

#ትርታ 97.6 FM #ከልብዎ_የቀረበ
Tirita 97.6 FM Radio

11 Jan, 20:05

299

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ  በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ የመጡትን የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐሙድን ተቀብለው ተወያይተዋል።

የሁለቱ አገራት መሪዎች ዛሬ በአዲስ አበባ የጋራ ፍላጎታቸው በሆኑ የተለያዩ የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ሀሳቦች መለዋወጣቸውን ባወጡት የጋራ አመልክተዋል።

የአገራቱን ህዝቦች የወንድማማችነት ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።

በየአገራቱ ያላቸው ሙሉ የዲፕሎማሲ ውክልና በመመለስ ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ወደ ነበረበት ለመመለስ እና ለማሻሻል ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

የአገራቱ መሪዎች የዲፕሎማሲ ሚሲዮኖቻቸው በባለብዝሃ ወገን እና በቀጣናዊ ፎረሞች ላይ የሀገራቱ የጋራ ፍላጎቶች ላይ በቅርበት መስራት እንዳለባቸው አጽንኦት የሰጡበት ጉዳይ እንደሆነ ነው በመግለጫው ላይ የተጠቆመው።

መሪዎቹ ለቀጣናው መረጋጋት የሁለቱ አገራት በጋራ መተማመን፣ ተአማኒነት እና መከባበር ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ትብብር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ለማሻሻል፣ የጋራ መግባባት ለመፍጠርና የጋራ ግቦችን እውን ለማድረግ በትብብር ለመስራት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በተጨማሪም በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የጸጥታና ደህንነት ትብብራቸውን ለማጠናከር ቀጣይነት ያለው ስራ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ተመላከቷል።

በየጊዜው እየደገ የመጣው እና አሳሳቢ የሆነው የታጠቁ ቡድኖች በቀጣናው ላይ የደቀኑት ስጋት በውይይቱ ላይ ተነስቷል።

የአገራቱ መሪዎች የጸጥታ ተቋማቶቻቸው መመሪያ በመስጠት ቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋት ያላቸውን ትብብር እንዲያጠናክሩ ለማድረግ ተስማማተዋል።

በተጨማሪም መሪዎቹ ሁለቱ አገራት በኢኮኖሚ፣ ኢንቨስትመንት እና ንግድ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጠንካራ የኢኮኖሚ ትብብር በመፍጠር የንግድ ትስስራቸውን የሚያሳልጡ የመሰረተ ልማት መስመሮችን ለማስፋት እና የጋራ ብልጽግናቸውን ለማረጋገጥ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው በጋራ መግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

መሪዎቹ ለአንካራው ስምምነት ትግበራ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገልጸው ስምምነቱ ከአገራቱ የወዳጅነት እና የአጋርነት መንፈስ የመነጨ መሆኑን አንስተዋል።

በስምምነቱ የተቀመጠውን የቴክኒክ ድርድሮች በፍጥነት እንዲጀመሩ ለማድረግ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን የጋራ መግለጫው ማመላከቱን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

#ትርታ 97.6 FM #ከልብዎ_የቀረበ
Tirita 97.6 FM Radio

11 Jan, 16:43

219

ሁለተኛዉ ዙር ተዋሕዶ ኤክስፖ በኤግዚቢሽን ማዕከል ተከፍቷል።

በሁለተኛዉ ዙር ተዋሕዶ ኤክስፖ ለመጀመሪያ ግዜ በሚካሄደው የጥምቀት ኤክስፖ ላይም፤ ነዋየ ቅድሳት፣ ባህላዊ አልባሳት፣ የማዕድ ቤት ዕቃዎችን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶች መቅረባቸው ተገልጿል።

ከጠዋት እስከ ምሽት ድረስ ከሚካሄዱ ግብይቶች ባሻገር ዝማሬዎችና የኪነ ጥበብ ስራዎች ይቀርባሉ ተብሏል።

በሁለተኛዉ ዙር ተዋሕዶ ኤክስፖ የመክፈቻ ፕሮግራም ላይም የሀይማኖት አባቶች ፣ ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች፤ እንዲሁም የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ተገኝተዉበታል።

ማርኮናል ኤቨንት ከጠቅላይ ቤተክህነትና ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የጥምቀት ኤክስፖው ከዛሬ ጥር 3 ቀን ጀምሮ እስከ ጥር 9 ቀን 2017 ዓም ድረስ ለተከታታይ 7 ቀናት በኤግዚቢሽን ማዕከል ይካሄዳል።

(በትባረክ ኢሳያስ)

#ትርታ 97.6 FM #ከልብዎ_የቀረበ
Tirita 97.6 FM Radio

10 Jan, 17:09

237

አሁናዊ መረጃ!
ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ
***
በትናንቱ እንግዳ የሕዋ ክስተት ዙሪያ ከተለያዩ የሕዋ አካላት መከታተያ እና የመረጃ ቋቶች ያገኘናቸውን መረጃዎች በማጠናቀር ባደረግነው ጥልቅ የሆነ ትንተና መሰረት የሚከተለው ሳይንሳዊ መላምት ላይ ደርሰናል።
በመረጃው መሰረት የሕዋ አካሉ ባለቤትነቱ የቻይና የሆነ ሺ ጂያን-19 (ShiJian-19) የተባለ ሳተላይት ቀሪ አካል ሊሆን እንደሚችል ያመላክታል።

ከዚህም በተጨማሪ የሳተላይቱን ቀሪ አካል የምህዋር እና የይዘት መረጃ ጨምረን ጠቅላላ ትንታኔውን ከዚህ ልጥፍ ጋር አጋርተናል። ሳተላይቱ በ መስከረም 17 2017 ዓ.ም ወደ ምህዋር የተወነጨፈ ሲሆን ተልዕኮውን ጨርሶ በ ጥቅምት 1 2017 ዓ.ም ወደ መሬት ተመልሷል።

ነገር ግን ሳተላይቱ በተልዕኮው ላይ ሲገለገልባቸው የነበሩ የተለያዩ ክፍሎቹ ከዋናው ሳተላይት ተነጥለው በምህዋር ላይ ሲዞሩ ቆይተዋል።

ለትንተናው የተጠቀምናቸው መረጃዎች ከሶስተኛ ወገን የመረጃ ቋቶች የተገኙ በመሆኑ የተረጋገጠ መረጃውን የሳተላይቱ ባለቤት ሃገር ቻይና እስክታረጋግጥ መጠበቅ ይኖርብናል።

ዋቢ ምንጮች፡

https://www.satcat.com/sats/61506
http://www.satflare.com/track.asp?q=61506&sid=2#TOP

#ትርታ 97.6 FM #ከልብዎ_የቀረበ
Tirita 97.6 FM Radio

10 Jan, 16:42

229

#አዲስ_መረጃ

ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ የተሰጠ
***
አስቀድመን ጥያቄ ባቀረብነው መሰረት የደረሱንን ቪዲዮዎችን እና በጉዳዩ ዙሪያ ያሉ ሌሎችን የመረጃ ምንጮችን ዋቢ አድርገን የሚከተለውን የእይታ ካርታ አዘጋጅተናል።

ከካርታው መመልከት እንደሚቻለው የታየው አካል በኢትዮጵያ ደቡብ እና ደቡበ ምዕራብ ክፍል አቋርጦ ወደ ኬንያ ሰሜናዊ ግዛት እንደገባ መመልከት ይቻላል። በሕዋ አካሉ ምንነት ላይ ያገኘነውን ተጨማሪ ማብራሪያ ከጥቂት ደቂቃዎችን በኋላ እናጋራለን።

#ትርታ 97.6 FM #ከልብዎ_የቀረበ
Tirita 97.6 FM Radio

10 Jan, 09:32

247

#አዲስ_መረጃ

በትናንትናው ምሽት በደቡብ ኢትዮጵያ ክፍል ሰማይ ላይ እየተቃጠለ ተቆራርጦ ወደ ምድር ሲጓዝ የታየው ቁስ በሰው ሰራሽ የስፔስ ቁስ ምክንያት የተከሰተ ሊሆን እንደሚችል የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦፓሻል ኢኒስቲትዩት ገለፀ፡፡

በተቋሙ የከባቢ አየር ሳይንስ ተመራማሪ የሆኑት ገመቹ ፋንታ (ዶ/ር) ከመንግስት መገናኛ ብዙሀን ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ጊዜ ያበቃላቸው ሳተላይት እንዲሁም ሳተላይቶችን የመጠቁባቸው የሮኬት  ቁርጥራጮች ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

በማንኛውም ሰው ሰራሽ መንገድ ህዋ ላይ  የሚንቀሳቀሱ ነገሮች ሊኖሩ ስለሚችሉ  ወደ ከባቢ አየር ውስጥ ሲገቡ  የመቃጠል እና ተሰባብሮ የመውረድ ምልክቶችን እንደሚያሳዩ ገልጸዋል፡፡

ክስተቱ የተፈጠረው በተፈጥሮአዊ የህዋ አካላት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡

ከመሬት እና ከሶላር ሲስተም አፈጣጠር አንጻር አለቶች በመኖራቸው  በማንኛውም ጊዜ እየተቆራረጡ ሊወርዱ እንደሚችሉ ነው ያነሱት፡፡

በዓለም ላይ እንደዚህ ያለ ሁነት እንደሚከሰቱ የሚናገሩት ተመራማሪው፤ አልፎ አልፎ ቁጥራቸው በርከት ያሉት  ወደ ምድር እንደሚወርዱም ገልፀዋል፡፡

ሰው የሚኖርበት ቦታ ከ 4 እስከ 5 በመቶ እንደማይበልጥ የሚናገሩት ተመራማሪው፤ ተቆራርጠው የሚወርዱ ነገሮች ከሰው ዕይታ ውጪ የሚከሰቱበት ሁኔታው ስለመኖሩም ጠቅሰዋል። አልፎ አልፎ ግን ለሰው ዕይታ እንደሚጋለጡም ነው አያይዘው የገለጹት፡፡

ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዓመት እስከ 6 ሺህ ድረስ ተቆራርጠው ምድር የሚደርሱ እና  አለፍ ሲልም የአሸዋ ቅንጣት በመሆን ወደ ምድር የሚወርዱ ስለመኖራቸው ነው ተመራማሪው የተናገሩት፡፡

የሚቃጠሉበት ምክንያት ደግሞ ወደ ከባቢ አየር ሲገቡ ከከባቢ አየር ጋር በሚያደርጉት ፍትጊያ የሚፈጠር ስለመሆኑም አያይዘዋል፡፡

"አሁን እንዳለን መረጃ በደቡባዊ  ክፍል የታየው ምስል ሰማይ ላይ እየተቃጠለ ነው የሄደው፤ አርፏል አላረፈም የሚለውን እስካሁን ማወቅ አልቻልንም" ብለዋል፡፡

ምድር ሦስት አራተኛዋ ውኃ በመሆኑ በአብዛኛው ውኃ ውስጥ እንደሚወድቅ የሚናገሩት ተመራማሪው፤ ሰዎች የሚኖሩበት አካባቢ ካልወደቀ በስተቀር ጉዳት እንደሌለው ነው የተናገሩት፡፡

#ትርታ 97.6 FM #ከልብዎ_የቀረበ
Tirita 97.6 FM Radio

10 Jan, 08:10

149

ትናንት ምሽት በደቡብና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍሎች በሰማይ ላይ ስለታየው ክስተት

የኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ በትናንትናው ዕለት ከምሽቱ 1፡30 ገደማ በደቡብና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍሎች በሰማይ ላይ እየተቀጣጠሉ በከፍተኛ ፍጥነት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቁስ አካላት ስብስብ መታየታቸውን አስታውቋል።

ተቋሙ በታዩት ተንቀሳቃሽ ምስሎች ለመመልከት እንደቻለውም የእነዚህ አካላት ስብስብ የጠፈር ፍርስራሾች አሊያም የሚቲዮር አለቶች እንደሚመስሉ ይፋ አድርጓል።

ስብስቡ ወደ ደቡባዊ የሃገሪቱ አቅጣጫ በከፍተኛ ፍጥነት በሰማይ ላይ ሲምዘገዘግ እንደነበረም ነው የተመላከተው።

የክስተቱን ተፈጥሮ በእርግጠኝነት ለማብራራት ያስችል ዘንድ ሁኔታውን በቅርበት እያጣራ እንደሚገኝ ተቋሙ ገልጿል።

የተጣራ መረጃ ሲደርስ ለህብረተሰቡ ይፋ እንደሚደረግም ተጠቁሟል።

የማጣራት ሥራው እስኪጠናቀቅ ድረስ ሁሉም ሰው በተረጋጋ መንፈስ እንዲጠባበቅ ተቋሙ አሳስቧል።

#ትርታ 97.6 FM #ከልብዎ_የቀረበ