የዓለም ጤና ድርጅት በዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ቅሬታ እና ክስ ቢቀርብም በጦርነት ለተጎዳው የትግራይ ክልል ህዝብ እርዳታ መጠየቁን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ባለፈው ዓርብ የኢትዮጵያ መንግስት ዶክተር ቴድሮስ ጎጂ እንዲሁም የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት እና TPLFን በመደገፍ የተሳሳተ ተግባር ላይ መሳተፋቸውን በመግለፅ ከሶ ድርጅቱ ምርመራ እንዲያከናውን መጠየቁ ይታወሳል።
ዛሬ የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ መንግስት በይፋ ክስ ማቅረቡን አረጋግጧል።
ድርጅቱ ግን 7 ሚሊዮን ለሚደርሰው የትግራይ ክልል ህዝብ መሰረታዊ አገልግሎት እንዲደርስ የኢትዮጵያ መንግስት እንዲፈቅድ መጠየቁን እንደሚቀጥል አሳውቋል።
ባለፈው ዓርብ ዕለት የኢትዮጵያ መንግስት ቅሬታውን ያቀረበው ባለፈው ሳምንት ዶ/ር ቴድሮስ መንግስት ወደትግራይ ክልል መድሃኒትና የነፍስ አድን እርዳታዎች እንዳይገባ እየከለከለ ነው በማለት በክልሉ ያለው ሁኔታ ሲኦል ነው ብለው ከገለፁ በኃላ ነው።
መንግስት ፥ ዶ/ር ቴድሮስ የሰጡት አሰተያየት የዓለም የጤና ድርጅትን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ እንደሚጥል ፤ የተጣለባቸውን ህጋዊ እና ሞያዊ ኃላፊነት ጥሰው በመገኘታቸው ምርመራ እንዲደረግ ጠይቆ ነበር።
በተመድ የኢትዮጵያ ልዑክም ዶ/ር ቴድሮስ የፖለቲካ ውግንና እንዳላቸው በመግለፅ ኢትዮጵያን ከሚመለከቱ ጉዳዮች እራሳቸው እዲያርቁ ጠይቆ እንደነበር የፈረሳይ ዜና አገልግሎትን ዋቢ አድርጎ ዶቼ ቨለ ሬድዮ ዘግቧል።
ዶ/ር ቴድሮስ ከሰጡት አስተያየት ጋር በተያያዘ የአማራ እና አፋር ክልል ባለስልጣናት ጠንካራ ትችት ሰንዝረው ዶ/ር ቴድሮስ የተናገሩት ለህወሓት ፕሮፖጋንዳ መሆኑንና በአፋር እና አማራ ክልል ህወሓት ስላደረሰው ጥፋት ተናግረው እንደማያውቁ መግለፃቸው አይዘነጋም።
@tikvahethiopia