🔴 “ አምልጠን እንኳ ብንወጣ ያመለጠውን ኢትዮጵያዊ ለሚይዙ 500 ዶላር ይከፈላቸዋል። ” -ኢትዮጵያዊያን በማይናማር
🔵 “ ደብድበውት ራሱን አያውቅም ወጣቶች ተሸክመው ሆስፒታል ሲወስዱት የውጪ ዜጋ አናክምም ብለው መለሱት ” - በእንባ የታጀቡ እናት
ሰርተን እንለወጣለን፣ ቤተሰብም እንለውጣለን ብለው ከአገር የወጡ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በማይናማር በስቃይ ውስጥ መሆናቸው ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ መገለጻችን አይዘነጋም።
ኢትዮጵያዊያኑ ከሀገር ሲወጡ የተነገራቸውና አሁን ያሉበት ሁኔታ የማይገናኝ ነው።
ጉልበታቸው እየተበዘበዘ ከሆኑም ባሻገር የሚፈጸምባቸው ድብደባና የአካል ጉዳት አሰቃቂ መሆኑን የገፈቱ ቀማሾች ከዚህ ቀደም ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸው ነበር።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ ኢትዮጵያዊያኑን ወደ አገራቸው ለመመለስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተየጋገረ መሆኑን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ መግለጹ ይታወሳል።
የኢትዮጵያዊያኖቹ ጉዳይ አሁንስ ከምን ደረሰ ?
በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ፣ ያገቷቸው አካላት ካሉበት አገር መንግስት ጋር ያላቸውን ግንኙት…በተመለከተ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ማብራሪያ የጠየቃቸው በማይናማር የሚገኙት ኢትዮጵያዊያን፣ በጣም በከፋ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን በሀዘን ስሜት ገልጸው፣ የመንግስትን እርዳታ ጠይቀዋል።
በዝርዝር ምን አሉ ?
“ የኢትዮጵያ መንግስት ሙሉ ኃላፊነት ወስዶ ከረዳን ብቻ ነው መውጣት የሚቻለው። የሌሎች አገራት እንዳደረጉት። ነገር ግን የተባልነው ነገር የለም እስካሁን በስቃይ ላይ ነን።
ያለንበት አገር ብዙም የተጠናከረ መንግስት የለውም። እንደሚታወቀው ወታደራዊ መንግስት ነውና። መንግስት ከመንግስት ጋር ተነጋግሮ ሊያስወጣን ከቻለ ብቻ ነው እንጂ።
እንወጣለን በሚል ተስፋ እያደረግን፣ እያለምን ነው እንጂ እስካሁን ምንም የተባልነው ነገር የለም። የኢትዮጵያ መንግስት ጫና ካላደረገ በስተቀር የያዙን ሽፍታዎችና የአገሪቱ መንግስት በጥቅም የተሳሰሩ ናቸውና መውጣት ይከብዳል።
አምልጠን እንኳ ብንወጣ ያመለጠውን ኢትዮጵያዊ ለሚይዙ 500 ዶላር ይከፈላቸዋል። ስለዚህ ተሳክቶልን ብናመልጥ እንኳ የአካባቢው ማህበረሰብ ይዞ አሳልፎ ይሰጠናል።
ሽፍቶቹ በቁጥር ብዙ ባይሆኑም መመሪያ የተሰጣቸው ናቸው። በዬቦታው ተሰራጭተው ነው የሚጠብቁት። ከእገታ ቦታው ወጣ ብለው በእስናይፐር የሚጠብቀ አሉ። በቁጥር ትንሽ ቢሆኑም የተጠናከረ ጥበቃ ላይ ያሉ ሽፍቶች ናቸው የያዙን።
የሚያሰሩን ቻይያዎች ናቸው። ያለነው ማይናማር ነው። ዜጎቹ ግን የቻይና ናቸው። ከአገሪቱ መንግስት ጋር በጥቅም የተሳሰሩ ናቸው። ለዚሁ መንግስት ግብር ይከፍላሁና ነገሩን ከባድ ያደረገው ከመንግስት ጋር የተያያዙ መሆናቸው ነው።
ወታደራዊ መንግስት ነው ያለው። ስለዚህ ከእኛ ከሚሰበሰው ገቢ ውስጥ ለመንግስት ይከፈላል። ለዛም ነው ሽፍቶቹ ደኀንነታቸው ተጠብቆ ሙሉ ድፍረት አግኝተው የሚሰሩት። የሕግ ከለላም አላቸው ነገሩ የተሳሰረ ነው። አጠቃላይ የአገራቱ መንግስት ሁኔታውን ሁሉ ያውቃል።
በስልክ እየደወልን ቤተሰብን ከመጠየቅ በስተቀር የኢትዮጵያ መንግስት ስለመውጣታችን እንዲህ ነው ያለን የሰማነው ነገር የለም። እባካችሁ በሕይወት ድረሱልን ” ሲሉ ተማጽነዋል።
ልጆቻቸው፣ የትዳር አጋሮቻቸው፣ እህትና ወንድሞቻቸው በማይናማር በከፋ ሁኔታ የሚገኙ ቤተሰቦች በበኩላቸው፣ ለወራት በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደሆኑ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
ልጃቸው የታገተባቸው አንዲት እናት እያለቀሱ በሰጡን ቃል፣ “ እኛም በጭንቀት ተሰቃዬን እንዴት አድርጌ እንደምገልጽ አላውቅም ” ሲሉ ጭንቀታቸውን አጋርተዋል።
እኝሁ እናት አክለው ፦
“ ደብድበውት ራሱን አያውቅም ወጣቶች ተሸክመው ሆስፒታል ቢወስዱት 'የውጪ አገር ዜጋ አናክምም ' ብለው መለሱት።
እንደ ዜጋ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት ሲገባው ‘የራሳቸው ጉዳይ’ የተባለ ነው የሚመስለው። በጣም ያሳዝናል ለመናገር በጣም ነው የሚቸግረኝ።
እንደ ወላድ ይጨንቃል። ተቸግረን አሳድገን እንዲህ ሲሆኑ። እንደ ሀገር እኛ ከኡጋንዳ ሀገር በታች ነው እንዴ የኛ ሀገር መንግስት ! እንዲያው ጆሮ ዳባ ብለውን ነው እንጂ።
ስቲል ይሄዳሉ ልጆች ወደ ውጪ አገር። አምባሳደሩን ገብተን የውጪ ጉዳይ ቆንጽላ ጽህፈት ቤት ተሰባስበን አነጋግረን ነበር ከ15 ቀናት በፊት።
ልጆቻችን አካለ ጎደሎ እየሆኑ፣ በሥነ ልቦና እየተሰቃዩ፣ እየተጎዱ ነው ዳግም ሌላ ወጣት እንዳይሄድ ስንል ‘የመንቀሳቀስ መብትን መንፈግ ነው የሚሆነው እኛ እንዴት ብለን እናሳግዳለን ?’ ነው ያሉን ” ሲሉ ገልጸዋል።
ገና የ8 ወር ልጅ ይዘው የቀሩ የትዳር አጋራቸው በማይናማር እንደታገተባቸው የገለጹ ሌላኛዋ እናት በበኩላቸው፣ ባለቤታቸው በከፋ ሁኔታ እንደሚገኝ፣ ልጅ አዝለው ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ድረስ ቢሄዱም አጥጋቢ ምላሽ እንዳላገኙ ተናግረዋል።
በዝርዝር ምን አሉ ?
“ ባለቤቴ ማይናማር በስቃይ ውሰጥ ነው። ከሄደ 5 ወራት አስቆጥሯል። ‘የሥራ እድል አለ’ ተብሎ በደላሎች አማካኝነት ነበር ወደ ታይላንድ የሄደው። በሙያው ሐኪም ነው። ከሄደ በኋላ ግን ታይላንድ አይደለም የቀረው ወደ ማይናማር ነው የወሰዱት።
ያለበት ሁኔታ በጣም ከባድ ነው። የጨለማ ክፍል የሚባል አለ፤ ድብደባ አለ። በነገረኝ መሠረት አሰቃቂ ሁኔታ ነው። እኔም መፍትሄ ፍለጋ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ልጅ አዝዬ ጭምር ብዙ ጊዜ ተመላልሻለሁ።
የሚሰጠኝ ምላሽ በራሳቸው ፍላጎት እንደሄዱ፣ በሕገወጥ መንገድ እንደሄዱ ነው። ከሦስት ቀናት በፊትም ሂጀ ነበርና ከታች ያሉት የቀረበውን ቅሬታ ካሳወቁ ከ10 ወራት በላይ እንዳስቆጠረ፣ ግን መፍትሄ እንዳልተገኘለት ነው የነገሩኝ።
‘ ከላይ ያሉት አካላት ናቸው መስራት ያለባቸው ’ ነው ያሉኝ። ጥሩ መልስ የሰጠን የኤምባሲ አካል ግን አላገኘንም። ቤተሰቡ በጭንቀት ውስጥ ነው ያለው። ባለቤቴ ከሄደ በኋላ ኑሮው ከብዶኛል።
ስለእርሱ መጨነቁ፣ የኑሮ ውድነቱ ተደራረቡብኝ። የባለቤቴ ደመወዝ ተቋርጧል። አዲስ አበባ ከተማ ላይ ብቻዬን ልጅ እያሳደኩ ስቃይ ላይ ነኝ።
የኢትዮጵያ መንግስት በደንብ ትኩረት ሰጥቶ ቢሰራበት የማይናማር መንግስት ሊለቃቸው እንደሚችል ባለቤቴ ነገሮኛል። ባለቤቴ ጋር የነበሩ የህንድ አገር ዜጎች ወጥተዋል። መንግስት መፍትሄ ይስጠን ” ሲሉ ተማጽነዋል።
ማይናማር ውስጥ የሚገኙ የታጋች ኢትዮጵያዊያኑ ወላጅች ያቋቋሙት ኮሚቴ በበኩሉ፣ መፍትሄ እየጠየቀ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ምን እየሰራ እንሆነ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ከሰጠው ምላሽ ጋር በቀጣይ ይቀርባል።
#TikivahEthiopiaFamilyAA
@tekivah_ethiopia