“አስተማሪህ ከእንግዲህ አይሰወርብህም፤ ዐይኖችህም አስተማሪህን ያያሉ። ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዘወር ብትል ጆሮህ ከኋላህ፣ “መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ” የሚል ድምፅ ይሰማል” - ኢሳ. 30:20 - 21
ባለፈው ፖስቴ የዚህን ትምህርት ክፍል አንድ ማለትም፣ “መጸለይን አስተምረን” (ሉቃ. 11:1) ተመልክተናል፡፡ አሁን ደግሞ ክፍል ሁለትን፣ ማለትም፣ “እድሜአችንን መቁጠር አስተምረን” የሚለውን እንመለከታለን፡፡
“ጥበብን የተሞላ ልብ ይኖረን ዘንድ፣ እድሜአችንን መቁጠር አስተምረን” - መዝ. 90፡12
ይህ ጸሎት ዘመናችን ይህንና ያንን በማድረግ ስንባክን እንዳያልፍ ያለንበት እድሜና ያለንበት የእድገት ደረጃ የት እንደሆነ እንድናስብ ጌታ እንዲረዳን የምንጸልየው ጸሎት ነው፡፡ ያለንበትን የእድሜ ደረጃ ማሰብና ለዚያ የሚመጥን ሁኔታ ላይ መሆናችንን ማሰላሰል በቀጥታ የሚመራን ጥበብን ማዳበር እንዳለብን ወደማሰብ ነው፡፡
በሌላ አገላለጽ፣ በዚህ አካሄዳችን ጊዜያችንን በሚገባ ተጠቅመንበትና ተልእኳችንን ፈጽመን እንደማናልፍ በምናስብበት ጊዜና ወደ ኋላ እንደቀረን የላቀ ጥበብ እንደሚያስፈልገን ወደማሰብ እንሄዳለን፡፡
“እንግዲህ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ። ቀኖቹ ክፉ ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ” (ኤፌ. 5፡15-16)፡፡ የዘመናችን ነገር ላይ በሚገባ ቆጠራ የማድረግን ነገር ጌታ ሲያስተምረን ዘመኑን ከተለያዩ አሰራሮች በመዋጀት ለእሴቶቻችን እና ለአላማችን የሚመጥንን የጥበብ ኑሮ መኖር እንጀምራል፡፡
ጌታ ሆይ፣ ያሰብክልንን ሳንኖር ዘመን እንዳያልፍብን እድሜያችንን መቁጠርን አስተምረን!
Dr. Eyob Mamo
@revealjesus