ለመሆኑ በዓለም-አቀፍ ደረጃ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ስያሜ ያለው 'ኦቲዝም' አግባባዊ ስያሜው የቱ ይኾን?
~~~
መንደርደሪያ፦ ግለ-ምልከታ፡
በ'ርግጥ በሀገራችን ሁኔታ ከስያሜ ይልቅ መፍትሔ ላይ ማተኮር የተሻለ ቢኾንም ነገር-ግን ስያሜ በራሱ የማኅበረሰብ ግንዛቤ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅዖና ተፅዕኖ ስላለው ትኩረት እንዲሠጥበት ልፅፍ ወደድኹ፤ በሀገራችን ከስያሜ/ስም ጋር በተያያዘ በሌሎች የአዕምሮ ዕድገት እክሎች(?) አወዛጋቢ፣ ሥነ-ምግባራዊ መሠረት የሌላቸውን ቃላት መመልከት እንችላለን። ለምሳሌ፦
የአእምሮ ዝግመት (የአዕምሮ ዕድገት ዝግመት)
የአእምሮ በሽታ/ሕመም፣ ዘገምተኛ፣ ወ.ዘ.ተ
ምናልባትም ወደ-ፊት አሁን ላይ በስፋት በጥቅም ላይ ያለው ‛የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት’ ይሻሻል፣ ይቀየር ይኾናል።
በሀገራችንም እንደሳይንሱ ዕድገት፣ እንደግንዛቤ ደረጃችን ስያሜ አሰጣጣችን እያደገ መጥቷል። ይኽም ማለት ከዓመታት በፊት የነበሩ ሙሉበሙሉ ስሕተት ናቸው ማለት ተገቢ አይኾንም። የማህበራትና የድርጅቶችን ስያሜ ልብ ይሏል?
ስያሜ/ስም በበርካታ ዘዴዎች፣ ፅንሰ-ሃሳቦች ይሰጣል/ይበየናል፦ የመጀመሪያው ጉዳዩን በቋንቋ በመተርጎም (በ10ሩ የትርጉም ዘዴዎች)፣ በአገባባዊ ፍቺ፣ እንደወረደ ቋንቋው ሳይተረጎም፣ የጉዳዩን ሃሳብና ምንጭ በሚገልፅ ጭምቅ ቃል፣ ሰዎች ተሰባስበውና ተስማምተው በሚፈጥሩትና ሌሎች ( ይኽን ለቋንቋ ባለሞያዎች ልተወው ) በቋንቋችን የሕክምና፣ የተፈጥሮ ሳይንስና ሌሎች ዘርፎች ላይ ያሉ ቃላትን መተርጓም፣ ተገቢ/አስማሚ ቃል መጠቀም ላይ አሻሚና አዳጋች ነው። ለመተርጓምና ተገቢ ስያሜ ለማውጣት የቋንቋና ሥነ-ፅሑፍ ባለሞያ እና ጉዳዩ ላይ ጥልቅ ዕውቀትና መረዳት ይፈልጋል።
~~~
ወደቀደመ ነገሬ ስመለስ ከግሪክ ቋንቋ መነሻ በማድረግ የተሰየመው ኦቲዝም 'Autism' (autós) በሳይንስ ዕድገት በተለያየ ዘመን ስያሜው ወይም ኦቲዝም ከሚለው ቀጥሎ ያለው ሐረግ እየተለወጠ፣ እየተሻሻለ መጥቷል። በሀገራችንም ተቋማት፣ ባለሞያዎች፣ ወላጆችና የተለያዩ ማኅበረሰቦች በተለያዩ መንገድ ይገልፁታል ለምሳሌ፦
❝ ኦቲዝም
ኦቲዝም የነርቭና የእድገት እክል
ኦቲዝም የነርቭና የአንጎል ሥርዓት መዛባት
ኦቲስቲክ
ኦቲዝም የዕድገት እክል
ኦቲዝም ኅብር የአዕምሮ ዕድገት መዛባት
ኦቲዝም የአዕምሮ ዕድገት ሥርዓት መዛባት
በኦቲዝም ጥላ ሥር
የራስ ዓለም የባህርይ ችግር
ኦቲዝም የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት
ኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደር
የህብረ-ባህርይ የአዕምሮ ዕድገት መዛባት ወ.ዘ.ተ ❞
ልጆቹን/ዜጎቹን ደግሞ፦
❝ ኦቲዝም ያለበት
ከኦቲዝም ጋር የሚኖር
በኦቲዝም ጥላ ሥር ያለ
ኦቲስቲክ
የኦቲዝም ተጠቂ
የኦቲዝም ታማሚ/በሽተኛ እና ሌሎች ❞
ስያሜውን ከምልክቱ፣ ከመንስዔው፣ ከባህርይ፣ ከተፅዕኖው አያይዘው ብዙዎች ይጠቀሙበታል። በዓለማችን ያሉ የጥናትና ምርምር፣ የሕክምና እና ሳይንስ ተቋማትና ግለሰቦችም ጉዳዩ ላይ አሁንም እየተመራመሩ ቢኾንም ብዙዎቹ ግን 'Autism Spectrum Disorder' የሚለውን ይጠቀማሉ።
እኛስ በቋንቋችን አግባባዊ/ተስማሚ ስያሜችን የቱ ይኾን?
ዋኖስ መስፍን (@WanosMesfin)
የልዩ-ፍላጎት ትምህርት ባለሞያ