ከልዑል ዘወልደ ገፅ የተወሰደ 'እውነተኛ ታሪክ'
ሰላም የነበርኩ ሰው ፥ በድንገትት መለዋወጤ መነኩሴውን አስደንግጦታል ። እኔ ወደቤታችን ሩጫ በቀረው እርምጃ በረርኩ ። መነኩሴው ሊከተለኝ ሲሞክር ፥ ተመለስ ! ብዬ አምባረኹበት ። ደግሞ ደነገጠ ፥ የኔ ጌታ! ለእኔ የሚታየኝ መች ይታየውና?!
በሩን ከፍቼ ወደቤት ስሮጥ ፥ ሀይለኛ ንፋስ በሩን ዘጋው ፤ ግውውው ።
ባሌ የደጃፌ ኩርብታ ላይ ፤ እግሩን አሰፈፍቶ ተቀምጧል ። ክው አልኩ ፤ ምነው አለኝ ? (ምንም ባላወቀ ንፁህ ፊት) ተን..ተባ..ተብ..ኩ ። ቀስ ብሎ ወደኔ ተጠጋና የሚለበልብ እጁ ሰንዝሮ አጣፋኝ ። አፍታ አልወሰደበትም ። መለመኛ ቃል ማውጣት እስኪያቅተኝ አንቆ ፤ ወደላይ አንጠለጠለኝ ። እጁ ላይ መሞት እንደተመኘሁ ፤ እድሉን አልሰጠኝም ። ከፍ አርጎ ሲለቀኝ ፥ እግሩ ስር ተዘረገፍኩ ። እቺ እግርሽ ነች አይደል እረፍት የነሳችሽ ? ብሎ ካቲዬና ቁርጭምጭሚቴ መሀል ቆመብኝ ። ከዛ በኋላ አላውቅም ፤ ራሴን ሳትኹ ።
ሥነቃ ራሴን ዱብቲ ሆስፒታል ከሶስት ታማሚ ጋር አገኘውት ። ቀኝ እግሬ ታሽጓል ፤ ክንዴና ሰውነቴ በላልዞል ። ነርሷ መጥታ አይዞሽ ?! አሁን ደህና ነሽ ። ባልሽ ነው እዚህ ያመጣሽ ፥ ከሰዓታት በፊት ነው የወጣው ! ደውይለትና የሚገዙ መድሀኒቶች ይገዛዛልሽ !! አለች ። እንደዛ ብላኝ ሳትጨርስ ፥ ወደ ክፍሉ ገባ ። ለኔ ያለቺኝን ለሱም ደግማ አስረዳችው ። ከርሷ ጋር ፈገግ ብሎ አውርቷት ወደኔ ሲዞር አውሬ ሆኗል ።
መሀል ግንባሬን የውሸት ስሞ ፤ በአባትና ወንድምሽ አትማሪም ? አለኝ ፤ መመለስ አልችልም ። ራስጌ ጋር ተቀምጦ የነበረን የመድሀኒት ማዘዣ በእጁ ይዞ ወጣ ። ከነርሷ ጋር ተከታትለው ሊወጡ ሲል ፥ እንደምንም ተንጠራርቼ እጄን አሳየኋት ። ወዬ ! ምን ልርዳሽ ብላኝ ፤ ተመለሰች ። አፌን እንደምንም እያንቀጠቀጥኩ ቀኑን ጠየኳት ። አልሰማቺኝም ። ደገምኩላት ፤ አልሰማቺኝም ። ከብዙ የተሳሳቱ ግምቶች በኋላ ...
እ...ቀኑ ነው ማወቅ የፈለግሽው ? ቅዳሜ !!!
ከህመሜ ይልቅ ጭንቀቴ ከአባ ጋር ሆኖ ፤ አገግሜ ከሆስፒታለሉ ወጣሁ ። አንድ የማላቃት ደንገጡር እንድታስታምመኝ (እንድትከታተለኝም ይሆናል) ተመድባለች ። ወደ ቤት ብገባም ጨርሶ አልሻረልኝም ፤ ከአልጋ ላይ ለመነሳት የሚያስችል አቅም አልነበረኝም ።
እንደተኛሁ በሩ ጓ ባለ ቁጥር ፥ ልቤ አብራኝ ትንጓጓለች ። በነዛ ቀናት የአባን መልዕክተኛ እንደጠበኩት በህይወት የጠበኹት ነገር ያለ አይመስለኝም ። ከሰውም ሆነ ከባሌ ከተያየሁ እንዲሁ ሁለት ሳምንት ተቆጠረ ። በሶስተኛው ሳምንት ማክሰኞ እለት ፥ አትክልት ውሃ እያጠጣሁ የግቢው በር ተንኳኳ ። ይሄን ድምፅ ከምንም በላይ ስመኘው ነበር ፤ እንደምንም እያነከስኩ ተንደሮድሬ ከፈትኹ ።
መልክተኛ አልነበረም ፤ አባ እራሳቸው ናቸው ። ለማኝ መስለው ስለ አርሴማ ?አሉኝ ። አርሴማ ትስጥልኝ ! አሜን የኔ ልጅ ፥ ዛሬ ለሊት ዘጠኝ ሰዓት ፀሎት እንቆማለን ፥ ኪዳን እንዳትቀሪ ! ብለው ተሰናበቱኝ ።
አልመሽልሽ ብሎኝ ዋለና ለሊቱ እንደተጋመሰ ፥ ወደ ቤተክርስትያን ሄድኩ ። ሁለት የማላቃቸው ሰዎች ከአባ ጋር አብረዋቸው አሉ ። አይደለም እንግዳ ሰው አይቼ በትንንሸሽ ተባይ የምደነግጥ ፥ ድንጉጥ ሆኛለሁ ። ደነገጥኹ ። አይዞሽ ከቅዱስ ያሬድ አንቺን ለመታደግ እዚህ ድረስ የመጡ ካህናት ናቸው አሉኝ ። በስጋ ለማያውቁኝ ዋጋ ቢስ የጂኒ ሚስት ፥ በተከፈለልኝ መስዋዕትነት ተደነቅኹ ።
መመካከር ጀመርን ። መጀመሪያ የምንሰጥሽን እምነት ግማሽ ፤ በቤትሽ ጣሪያ ላይ አድርጊው ። ገሚሱን ደግሞ ፥ ጂኒው ባልሽ ከመመለሱ በፊት (ጠዋት 12:00) በጠበል ውሃ ባርከሽ እንድትጠጪ ይሁን ! በሚለው ተስማማን ።
ደስ አለኝ ፤ ግን ደግሞ ሌላም ስሜት እየተሰማኝ ነበር ። ግርታዬን ሲመለከቱ ፥ አይዞሽ በፀሎት እናግዝሻለን አሉኝ ። ቆይ ቤተሰቤስ ? አልኹ ፥ የቀሩኝን ስጋዎች አስታውሼ ። በዚህ ሰዓት ስህተቶቼ ከኔ ውጪ ሌላ ማንንም ሰው ለአደጋ ሲያጋልጡ ማየት አልፈልግም ። ስለቤተሰብሽ ማረግ ያለብሽን እንመካከራለን ! አሉኝ ። አምኛቸው ከመሄድ ውጪ የማደርገው ምንም ነገር አልነበረም ።
ወደቤት እንደሄድኩ እንደተባልኩት በጣሪያዬ አድርጌ ተኛሁ ። ጠፍቶ የከረመው ባሌ ፤ በጠዋት መጣ ። ሁሌም እንደሚያደርገው ፤ ስሜን አቆላምጦ እየተጣራ ወደውስጥ ዘለቀ ። ድምፁን ስሰማ ደስ አለኝ ፤ ናፍቆኝ'ም ነበር ። መሄድ እንደምትፈልግ ግን ደግሞ የማትራመድ አይነት ሰው ነኝ አይደል ? ቢፈረድብኝም አላዝንም ። ብቻ ፤ ቤት ውስጥ ሲገባ የናፍቆት ድምፁ በንኖ መነጫነጭ ጀመረ ።
ፊቱን አኮስሶ ምንድነው ቤቱ የሚሸተው?! አለ ። እንደተኛሁና እንዳልሰማሁት ፥ ዝም አልኹ ። የሚሸት ምንም ነገር በቤት ውስጥ አላደረኹም ። እየተነጫነጨ ከቤት ሲወጣ ፤ እየተንጠራራሁ ተከትዬው ወጣሁ ።
ይቀጥላል
@fekernferan
@fekernferan
@fekernferan