ባለፈው ዓመት ግንቦት በተደረገው ምርጫ ወደ ሥልጣን የመጡት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ለአራት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ኤርትራ ገቡ።
ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ከልዑክ ቡድናቸው ጋር አሥመራ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አቀባበል እንደተደረገላቸው የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገ/መስቀል በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት በቀጠናው ወደሚገኙ አገራት የተጓዙ ሲሆን፤ ወደ ኤርትራ ሲያቀኑ ግን በጥቂት ወራት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው።
የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር እንዳሉት፤ ፕሬዝዳንቱ ኤርትራ የተገኙት “ለሥራ ጉብኝት ነው” ከማለት ውጪ ሐሰን ሼክ መሐሙድ በአሥመራ ቆይታቸው ስለሚያከናውኗቸው ጉዳዮች ያሉት ነገር የለም።
ይሁን እንጂ በኤርትራ የሚገኙት የሶማሊያ ወታደሮች ጉዳይ የፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ የጉዞ አጀንዳ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
ፕሬዝዳንቱ ሐምሌ 2014 ዓ.ም. ወደ አሥመራ ባቀኑበት ወቅት በኤርትራ ሥልጠና ላይ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የሶማሊያ ወታደሮች የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘታቸው ይታወሳል።
የኤርትራ መንግሥት ሐምሌ 03/2014 ዓ.ም. ለሦስት ዓመታት ወታደራዊ ሥልጠና ሲወስዱ የነበሩት የሶማሊያ ወታደሮች ፕሬዝዳንቱ በተገኙበት ተመርቀዋል ብሎ ነበር።
እነዚህ ላለፉት ዓመታት በሶማሊያ ፖለቲካ ውስጥ አወዛጋቢ ሆኖ የቆዩትና በኤርትራ የሚገኙ የሶማሊያ ወታደሮች ጉዳይ የፕሬዝዳንቱን ጉዞ ተከትሎ ተመርቀዋል ይባል እንጂ የት እና በምን ሁኔታ ኤርትራ ውስጥ እንደቆዩ ግልጽ ሳይሆን ቆይቷል።
ወታደሮቹ በቀድሞ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ፋርማጆ አስተዳደር ወቅት ወደ ኤርትራ እንደተላኩ የሚታመን ሲሆን፤ የፋርማጆ ተቀናቃኞች ፕሬዝዳንቱ ወታደሮቹን ወዳልታወቀ ስፍራ ልከው በጦርነት ውስጥ እንዲሳተፉ አድርገዋል ሲሉ ሲወቅሷቸው ነበር።
ወታደሮቹን በተመለከተ ከሚያወዛግቡ ጉዳዮች መካከል አንዱ፤ የጦሩ አባላት በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከኤርትራ እና ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ጋር ወግነው የትግራይ ኃይሎችን ወግተዋል የሚለው ይገኝበታል።
የሶማሊያ ወታደሮች በኤርትራ ስለመገኘትም ሆነ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መሳተፋቸውን በተመለከተ የሞቃዲሾ መንግሥት አንዳንዴ ዝምታን ሲመርጥ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሚቀርብበትን ክስ ሲያስተባብል ቆይቷል።
የወታደሮቹ ቤተሰብ አባላትም የልጆቻቸውን አድራሻ በመጠየቅ በሶማሊያ ጎዳናዎች ላይ ለተቃውሞ አደባባይ መውጣታቸው ይታወሳል።
ወታደሮቹን በተመለከተ ይፋዊ ምላሽ ከመግሥት ከተሰጠባቸው አጋጣሚዎቹ አንዱ ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ በምርጫ መሸነፋቸውን ተከትሎ ሥልጣን ባስረከቡበት ወቅት የሰጡት ማረጋገጫ ይጠቀሳል።
ፋርማጆ በወቅቱ አምስት ሺህ የሶማሊያ መንግሥት ወታደሮች ኤርትራ ውስጥ ሥልጠና እየወሰዱ እንደሚገኙ ይፋ ያደረጉ ሲሆን፣ ምርጫው በተቃረበበት ጊዜ ፖለቲካዊ ተጽዕኖ እንዳይኖራቸው ባሉበት እንዲቆዩ መደረጉን አሳውቀው ነበር።
ከዚህ በኋላ አዲሱ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ወደ ኤርትራ አቅንተው በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በወታደሮቹ መካከል ሆነው ታይተዋል።
በወቅቱም ምን ያህል የሶማሊያ ወታደሮች ሥልጠናቸውን እንዳጠናቀቁ፣ ምን አይነት ሥልጠናዎችን እንደወሰዱ፣ ሶማሊያውያኑ ወደ ኤርትራ መቼ እንደገቡም ሆነ መቼ ወደ ትውልድ አገራቸው እንደሚመለሱ የተገለጸ ነገር አልነበረም።
ነገር ግን የሁለቱ አገራት መሪዎች ወታደሮቹ ወደ ሶማሊያ በሚመለሱበት ሁኔታ ላይ ተነጋግረው መስማማታቸው ተገልጾ ነበር።