Brown Empire @bempire1819 Channel on Telegram

Brown Empire

@bempire1819


👋🏾

Brown Empire (English)

Welcome to Brown Empire, a thriving community for lovers of all things brown! Are you someone who appreciates the warmth and richness of brown tones? Do you find comfort in the earthy hues that brown has to offer? If so, you have come to the right place. Brown Empire is a Telegram channel dedicated to celebrating the beauty of brown in all its shades and forms. From fashion to interior design, nature photography to artistic creations, our channel is a treasure trove of inspiration for anyone who adores this versatile color. Join us at @bempire1819 and immerse yourself in a world where brown is the reigning monarch. Let's paint the town brown together! #BrownEmpire #AllThingsBrown

Brown Empire

17 Jan, 07:48


“ወዲያው ተመለስሽ ወይስ ሰው ጠየቅሽ?”
“እ?”
“ወርደሽ ልትፈልጊው ወይ መኪና ውስጥ ልጠብቂው አልሞከርሽም?”
“ስልኩ ዘግቶበት ነው ብዬ ስላሰብኩ ትንሽ መኪናዬ ውስጥ እንዳለሁ ጠብቄዋለሁ፣ ከዛ ግን ምሽትም ስለነበረ ከዛ በላይ መጠበቁ ስላስፈራኝ ወደቤቴ ተመለስኩ”
“እንዴት ይመስል ነበር ግንኙነታችሁ? እሱ ላንቺ ያለው ስሜት?”
“ፓርኪንግ ላይ ነው የተዋወቅነው። ከመኪናዬ ስወርድ ለከፈኝ፣ ልሳደብ ስዞር የሊሊ እንጀራ አባት እንደሆነ ተረዳሁ፣ አክብሬ ዝም ብልም እሱ ግን ማቆም አልቻለም ስላናደደኝ ለምን የውሸት ተስፋ እየሰጠሁ አልጫወትበትም ብዬ ሳቅኩለት፣ ሀሳቤ የወደድኩት መስዬ ቀርቤ ሊሊን ያደረጋትን ላስለፈልፈው እና በማስረጃ ላሳስረው ነበር። በመሀል የዴዚ ጉዳይ ተጨመረ።”

“ሴክሹዋል ግንኙ..”
“በጭራሽ!”
*

ሊሊ የሳጅን ዳሂላ ቢሮ ቁጭ ብላለች፣ ጥፍሯን ክርክም እያደረገች ትበላለች።
“እጅሽን ተይ” ዳሂላ ከውጪ ገብታ ወንበር ስባ እየተቀመጠች አለቻት
ሊሊ እጇን ከአፏ እያወጣች “ለምዶብኝ”
“ከእንጀራ አባትሽ አንዱአለም ጋር ምን አይነት ቀረቤታ ነበራችሁ? ትወጂው ነበር? ጥሩ ሰው ነበር?”
“ነግሬሽ ነበር ከ..”
ሳጅን ዳሂላ ወደ ሪከርደሩ እያሳየቸት “ድገሚው”

“አንዷለም የአካባቢው ሰዎች እናቴን ጋለሞታ እያሉ ሲያስቸግሯት አፋቸውን ለማዘጋት ከአንዷ ላይ የወሰደችው የሰው ካንሰር ነበር። የሄደበት እሱ የነካው ሁሉ የሚበላሽ አይነት.. እሱ ቤታችን ከመጣ ጀምሮ ህይወታችን ከቀደመው ብሶ ተናጋ። እኔንም በልጅነቴ ደፈረኝ እናቴንመ ከእኔ ነጠቀኝ።”

“አዝናለሁ፣ በስንት አመትሽ ማለት ነው?”
“በአስራሶስት”
“አልከሰሳችሁም?”
ሊሊ በአሉታ ራሷን ነቀነቀች
“ለምን?”
“እናቴ ልታምነኝ ሰልቻለችም ነበር፣ ስለዚህ ፖሊስ ያምነኛል ብዬ አላሰብኩም ፈራሁ።”
“ ይሄ የሆነው ከአንዴ በላይ ነው?”
“አዎ ራሴን መከላከል እስክጀምር ድረስ”
“መከላከል ማለት?”
“ስልሽ “እጮሀለሁ” እያልኩ ማስፈራራት ፣ መኝታ ቤቴ መተኛት ትቼ በሩ ቅርብ ወዳለበት ሳሎን መተኛት እስክጀምር ድረስ፣ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ ራሴን የምከላከልባቸው ሴንጢዎች መግዛት ጀመርኩ።”

ሳጅን ዳሂላ ድንግጥ አለች

“ም..ምነው?” ሊሊ የዳሂላን ድንጋጤ አይታ ጠየቀች
ሳጅን ዳሂላ ከ መሳቢያዋ ውስጥ ለኤግዚቢትነት የያዘችውን ሴንጢ አውጥታ ጠረጴዛው ላይ አደረገች።

“እንዴ? ይሄ? ይሄ … “
“ያንቺ ነው?”
“አዎ!”
“ለመጨረሻ ግዜ አንዱአለምን ያየሽው መቼ ነው? “ከስምንት ቀን በፊት ማለት ነው? እንደዛ መሰለኝ”
“ሰአቱ?”
“ጠዋት ላይ ከቤት ሲወጣ”
“አውርታችሁ ነበር?”
“በጭራሽ!”

ሳጅን ዳሂላ በሀይል እየተነፈሰች “ሊሊ ላዩ ላይ ያለው አሻራ እስኪጣራ ድረስ ማረፊያ ቤት መቆየት አለብሽ”

“ምን?”
“አዎን! አዝናለሁ።”
*

ሀረግ እና ሮዝ የሀረግ መኪና ውስጥ ቁጭ ብለው ከዳሂላ ጋ የምትጯጯኸውን አበባን ያያሉ።

“ልጄን ተዋት እኔን ያዙኝ ብትፈልጉ ብዙ ሆናለች በልጅነቷ በቃ” እያለች ታለቅሳለች

“ያደረገችው ይመስልሻል?” ሮዝ ጠየቀች
“አላውቅም።”
“ምስኪን ሊሊ”
“እሷ እንዳላደረገችው በምን አወቅሽ?”
“ኧረ በፍፁም!”

አበባ ከእምባዋ ላይ ቀና ስትል በድንገት ከነሀረግ ጋ አይን ለአይን ተጋጨች፣ ወዲያውኑ አንድ ነገር እንዳሰበች ሁሉ ወደነሱ መኪና ተንደርድራ ሄደች።
እንደተጠጋችም የመስኮቱን መስታወት ዝቅ እንዲያደርጉላት ጠየቀች።

የፊቷ የደም ስሮች እንደተወጣጠሩ ከአይኗ እምባ ዱብ ዱብ እያለ “እባካችሁ ልጄን አትርፉልኝ” አለች።
*
ሀረግና እና ሮዝ አበባ ቤት ቁጭ ብለው የሰሙትን ባለማመን ደንግጠው ቀርተዋል።
“ይሄ በፍፁም ሊሆን አይችልም” አለች ሮዝ
“ምን ማስረጃ አለሽ?” አለች ሀረግ

አበባ በሀሳብ ወደዛን ቀን ማታ ትመለሳለች።

የዛን ለት እዚህ አንቺ ጋ ከመጣሁ በኋላ ወደቤት ስመለስ የሆነውን ሁሉ እያሰብኩ ሄድኩ፣ በስቃይ ኖሬአለሁ ሰውነቴ የማይሆነውን ህልም የሚያልመው አእምሮዬ ጋ ድብድብ ገብቶ ለአለፉት አምስት አመታት መላ አካሌ የጦር ሜዳ ነበር። ያን ለት የሰነበተ ህመም ሁሉ ተሰማኝ፣ እያንዳንዷ ያመረቀዘች ቁስል ፈነዳች፣ ባላይም ልጄን አምናታለሁ ደፍሮብኛል። አላምንሽም ብዬ ልጄ ውስጥ የሰራሁት በደል ፀፀት ሆኖ ሰውነቴን ወረረኝ፣ እኔ ከውስጥ በር ቆልፈሽ ተኚ ስላት ጭንቀት እንዳለባት ትነግረኛለች እኔ አልተረዳኋትም ተነስታ ሳሎን ስትተኛ እየጠገበች ይመስለኝ ነበር። መቼም ይቅር በለኝ የምልበት ሞራሉ የለኝም። ይቅር አይበለኝ ግን እኔኑ ይቅጣኝ መድሀኒያለም ልጄ በቃት.. የዛን ለት ቤተክርስቲያን ገብቼ አልቅሼ ቤት ስደርስ ልጄ እንደገባሁ ተጠመጠመችብኝ፣ እንደዛ ካቀፈችኝ ረጅም ግዜ ነበር። እሷው ተበድላ እሷው ይቅር አለችኝ። እኔ ማለት ሲገባኝ እሷ አለሁልሽ አለችኝ። ተላቅስን ይቅር ተባብለን ልንተኛ ስንል አንዱአለም ደወለ እና ጃኬቱን እንዳቀብለው ጠየቀኝ፣ እሺ ብዬ ልወጣ ስል “ደክሞሻል እረፊ እኔ አቀብለዋለሁ” ብላ አለች። እሺ አልኩ እና ይዛ ሄደች እኔም አረፍ አልኩ እውነትም ደክሞኝ ነበር ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወሰደኝ።

ወደ አምስት ሰአት አካባቢ፣ የበር መከፈት ስሰማ ሊሊ መምጣቷን ሳላረጋግጥ እንቅልፍ እንደጣለኝ ትውስ ሲለኝ ብርግግ ብዬ ተነስቼ ወደሳሎን ሄድኩ። ያየሁትን ሳላይ ምድር ተከፍታ ብትውጠኝ ምኞቴ ነበር። ልጄ ከአግር እስከራሷ በደም ተጨማልቃለች። ሳሎኑ መሬቱ ሶፋው ሁሉ አልቀረም ይዛው የሄደችውን ጃኬት ለብሳዋለች። ገደልኩት ብላ ተንደርድራ መጥታ አቀፈችኝ። 18 ግዜ ወጋሁት አስራ ሶሰት ግዜ ለደፈረኝ፣ አምስቱን ደግሞ ለነጠቀን እድሜ ጨመርኩለት አለችኝ። “ደግሞ ፀጉሩን ተቆርጦ ሽቶ ተቀብቶ ሌላ ሴት ሊያገኝ እኮ ነው አንቺን ጃኬት አቀብይኝ የሚልሽ” ብላኝ ሳቀች። አቅፊያት እናት እነደቀበረ አነባሁ። እሷ ግን ምንም! አስገብቼ ሻወር ሳጣጥባት ሁሉ ደንዝዛ ነበር። ልብሷን ቀያይሬ አስተኛኋት።

ሌሊቱን ማስረጃ የሚሆን ነገር በሙሉ አፀዳሁ። ከጥፍሯ ውስጥ ሁሉ ደም አውጥቼ ጥፍሯን ቆርጫለሁ። ያ ሴንጢ ግን አብሯት ቤት አልመጣም። ነገር የሚሆነው እሱ እንደሚሆን ጠርጥሬያለሁ።

ሌሊት ላይ ቆሜ ልብስ እያጠብኩ ተነስታ ወደኔ ስትመጣ ምንም እንዳልተፈጠረ ሆና ነበር። ግራ ቢገባኝም እንደዛ መሆኑ ይሻላል ብዬ ዝም አልኩ። በነጋታውም ስለሁኔታው ታዋራኛለች ብዬ ብጠብቅ የለም። ጭራሽ መጥፋቱ ያስገርማት ጀመር። ታማለች እንዳልል ሌላ ሁሉ ነገሯ ጤነኛ ነው። ግን ስለዛ ጉዳይ ምንም ትውስታ የላትም።

“ እሺ ይሄ ሁሉ ነገር ሆነ እንበል ምን ማስረጃ አለሽ?” ሀረግ በድጋሚ ጠየቀች?

“ምንም ማስረጃ የለኝም ሁሉንም ነገር እንደምታዩት ቀያይሬዋለሁ በኔ ቤት ልጄን ማትረፌ ነበር።”

ሮዝ የሊሊን ፍረስትሬሽን አስባ አለቀሰች። ሀረግ አሁንም በጥርጣሬ ውስጥ ነች።

ይቀጥላል..


አንድ የመጨረሻ ክፍል ይቀረዋል። 🫶🏾

Brown Empire

17 Jan, 07:48


ኢንስፔክተር ማሞ፣ ሳጅን ዳሂላ ቢሮ በሩን በርግዶ ሲገባ ዳሂላ ቢሮ ውስጥ ሀረግ ቁጭ ብላለች።
ሁለቱም ኢንስፔክተር ማሞን አፍጥጠው አዩት፣ በሩን እንደተበረገደ ትቶት ሊቀመጥ ወንበር ሲስብ ሀረግ ከመቀመጫዋ ተነሳች።

ሳጅን ዳሂላ “ወዴት ነው ወይዘሮ ሀረግ?” አለች መሀል ኢንተሮጌሽን መሀል ላይ ተነስታ ልትወጣ የቆመችውን ሀረግን ወደላይ እየተመለከተች።

ሀረግ ወደ ዳሂላ እየተመለከተች “ሳጅን ዳሂላ ጉዳዩን የያዝሽው አንቺ እንደሆንሽ ነው የማውቀው” በርጋታ በትቢት ወደላይ የሚያያትን ኢንስፔክተር ማሞ ወደታች እያየች “ህግ ቦታ የምንመጣው የሚከበር ስርአት እስካለ ነው።” ብላ ቀልጠፍ ብላ ከቢሮው ወጣች።

“እንዴት ነው የሚያደርጋት? ማነኝ ብላ ነው የምታስበው?” አለ ኢንስፔክተር ማሞ በብስጭት

“እሱን ጥያቄ ለራስህ ጠይቀህ መልስ ስታገኝለት እናወራለን” አለች ዳሂላ በብስጭት

“እዚህ የመጣችው እኮ የልጇን አጋች በመግደል በተጠርጣሪነት እንጂ ተበዳይ ሆና አይደለም!”

“ቢሆንስ ማስረጃ እስካላገኘህ ድረስ በፍቃደኝነት እንዲመጡ ትጠይቃለህ እንጂ በግዴታ ልታመጣቸው አትችልም። ሲጀመር እዚህ ኬዝ ውስጥ አትግባ ብዬህ ነበር አይደል?”

“ቆይ አንቺ ይሄን ኬዝ ለብቻሽ መያዙ ይከብድሻል ስትባይ ለምን ክፋት መሰለሽ? የኔ መኖር ላንቺም ጠቃሚ ነው።”

“ያንተ እርዳታ ለግዜው አያስፈልገኝም፣ ሲያስፈልገኝ በሙያዊ ግዴታህ ታግዘኛለህ፣ ለአሁን ግን አመሰግናለሁ።”

*
ሀረግ ካፌ ውስጥ ቁጭ ብላ ጥቁር ማኪያቶ ትጠጣለች፣ ከነጋ ሆዷ ውስጥ የገባው ብቸኛ ነገር ይኸው ማኪያቶ ነው። በአንዱአለም ድንገተኛ ሞት እጅግ በጣም በሽቃለች። በህይወቷ ሰው ገድላ ባታውቅም አንዱአለምን ግን ላትምረዉ መሳሪያዋን ወልውላ አዘጋጅታ ነበር። በህይወቷ ቁጭ ብላ የማታሰላስለው ብዙ የያዘቻቸው ቂሞች አሉ። አታስባቸውም ማንነቷን እንዲቆጣሩ ፈቃድ አትሰጣቸውም ግን ያ ሁሉ ልክ ፒንክ ሩም ውሰጥ እስክትገባ ድረስ ነው ከዚያ ወዲያ ሙሉ መሪውን ለስሜቷ ትለቃለች።

“ምነው አልወደድሽውም እንዴ?” የአስተናጋጁ ድምፅ ቀሰቀሳት።

ሁለቴ ፉት ወዳለችለት ማኪያቶ አየች።

*
ሊሊ ሮዝ አፓርትመንት ውስጥ ወዲህ ወዲያ ትዘዋወራለች፣ የሆነውን ነገር ለማመን ከብዷታል።
ሮዝ ያፈላችውን ሻይ እያቀረበች “ቁጭ አትይም ሊሊ” አለች ሀሳቧ ብትን ያለውን ሊሊን እያየች

“እሷም ላትሆን ትችላለች እኔ የፈራሁት እንደውም ሀረግን ነው።”

“ስላላየሻት እኮ ነው።”
“ደንግጣ ነው የሚሆነው እንጂ አበባ ያን የማድረግ አቅም ያላት አይመስለኝም።”
“አዪ አሁን እንኳ ሁሉን ሰው ሁሉንም ነገር የማድረግ አቅም እንዳለው እየተሰማኝ ነው። ብቻ switch የሚያደርገው point ላይ ይድረስ እንጂ።”

“I’m happy ስለሞተ!” አለች ሮዝ ምንም ርህራሄ በሌለው ፊት

ሊሊ አይታት በመስማማት ራሷን ነቀነቀች።

*
የሳጅን ዳሂላ ቢሮ ውስጥ አበባ ከመቼውም በበለጠ እርጋታ ተቀምጣለች።

ሳጅን ዳሂላ ሪከርደሩን ከፍታ ጥያቄዋን ጀመረች

“አንዱአለምን ለመጨረሻ ግዜ ያየሽው መቼ ነው?”
“ለመጨረሻ ግዜ ከስምንት ቀን በፊት መሆኑ ነው”

“የት ነው እንዴት ስንት ሰአት ላይ? ለምን? ዘርዘር አድርገሽ ንገሪኝ”

“ቤቴ ነበርኩ ጃኬት አቀብይኝ ብሎ ወደማታ ደወለ፣ ቀኑን ሙሉ ቤት አልነበረም፣ ጧት እንደወጣ ነበር እኔም የመጨረሻ ግዜ ጠዋት ነው ያየሁት፣ ጃኬቱን ይዤለት ብሄድም አላገኘሁትም።”

“እንዴት አላገኘሁትም? የት ሄደ ስልክ ደወልሽ?”
“አዎ ደወልኩ በመጀመሪያው አነሳ እና ግሮሰሪው ጋ እንዳለ እና እዛው ታክሲ ተራው ጋ ቆሜ እንድጠብቀው ነገረኝ ወደሱ እንድሄድ አልፈለገም። ቆሜ ጠበቅኩት ሲቆይ መልሼ ደወልኩ አያነሳም ደጋግሜ ሞከርኩ ጭራሽ ዘጋው። በብስጭት ወደቤቴ ሄድኩ”

“ለምን ይመስልሻል ወደ ግሮሰሪው እንዳትጠጊ የፈለገው?”

አበባ አንገራግራ “አንዲት ልጅ እግር ቢጤ …” አፏ ተሳሰረ፣ በሀይል ተንፍሳ “ አንዲት ልጅ ወሽሟል ለዛ ይመስለኛል”

ዳሂላ ሀዘኗን እየተቆጣጠረች ከዴስኳ ስር ሶፍት አውጥታ ሰጠቻት

አበባ ሳትፈልግ ያቀረረችውን እምባ በንዴት ጠረገች

“ልጅቷን ታውቂያታለሽ?”
“አዎን ቤቷ ሄጄ አናግሬያት ነበር”
“እሱን በቅድሜያ አናግረሽዋል?”
“አንዷለምን እኮ አያናግሩትም፣ ወይ ይችሉታል ወይ …”
ሳጅን ዳሂላ በትግስት ጠበቀች
አበባ በእምሮዋ ያሰበችው ፈገግ እንዳስባላት ሁሉ ሆነችና ወዲያው ስሜቷን ተቆጣጥራ “ወይ.. ይተውታል”

ሳጅን ዳሂላ አበባን ትኩር ብላ አጠናቻት
“በባለቤትሽ ሞት ምን ተሰማሽ?”
“ምንም!”
“እንዴት ምንም?”
“እየወጣ አንድ ሳምንት፣ ሁለት ሳምንት ወር ድረስ እየጠፋ መምጣት አስለምዶኝ ነበር፣ ይመጣል ብዬ ቤቱን አፀዳድቼ ቀለም ቀያይሬ ተመልሶ ቤቱን እንዲወደው ሞክሬ እየጠበቅኩት ነበር። ከልጅቷ ጋ ያለውን ጫጉላ እስኪጨርስ፣ ግን ቀረ፣ ሞተ።”

“ማን የገደለው ይመስልሻል?”
“አላውቅም። የማውቀው ሁሉም ሰው እሱን የሚችልበት የኔ አይነት መሬትነት እንደሌለው ነው።”
ዳሂላ ከመሳቢያ ውስጥ በላስቲክ የታሸገ ሴንጢ አውጥታ ጠረጴዛ ላይ እያደረገች “ይሄን ስለት ከዚህ በፊት አይተሽው ታውቂያለሽ?”
የአበባ አይኖች ሳያስፈቅዷት በድጋሚ እምባ ሞሉ፣ እግሯ ተንቀጠቀጠ፣ ድምፅዋም ከዳት
“አ.አ. አላውቅም..”
ሳጅን ዳሂላ በትኩረት ከአየቻት በኋላ ስክርቢቶና ወረቀት ሰጥታት
“የልጅቷን አድራሻ እዚህ ጋ ታስቀምጪልኝ” አለቻት።
አበባ እስክርቢቶውን አነሳች
*
ሳጅን ዳሂላ ሮዝ አፓርትመንት በር ላይ ቆማ ደውል ትደውላለች፣ ሮዝ ፈጠን ብላ ከፈተች… ዳሂላ መታወቂያዋን አሳይታ ወደውስጥ ገባች።

“አቤት ኢንስፔክተር?”
“ዋና ሳጅን ዳሂላ”
አርማት ቤቱን ዞር ዞር ብላ ቃኘች
“እዚህ አካባቢ እንዴት ነው ግርግሩ?”
“ውጪ ስትወጪ ነው እንጂ እዚህ ውስጥ ምንም ጫጫ…”
ሳታስጨርሳት “ወንዶቹ አይተናኮሉም? እኛ ፖሊስ ጣቢያ ከሚመጡት ውስጥ በዋነኝነት የለከፋ እና ጉንተላ ክሶች ከዚህ አካባቢ ነው የሚመጡት… ያው ማስረጃ ስለሌው ራሳችሁን መከላከያ ያዙ እንላቸዋለን”

ሮዝ ግር እንዳላት የሳጅንን ወሬ ለመያዝ በአትኩሮት ትከታተላለች

“እና ራስሽን መከላከያ ፔፐር ሰረፕሬይ፣ ሴንጢ ምናምን የለሽም?”

“የለኝም እስካሁን እንዳልሺው አይነት ጥቃት ደርሶብኝ አያውቅም።”

“አሀ ከአንዱአለም ጋ የነበረሽን ግንኙነት ምንድን ነው?”

“ምንም”
“እንዴት ምንም ሰው ሌላ ነገር እያወራ ነው”
“ ሊሆን ይችላል ግን እኔ ከሱ ጋ አንድ ሚሽን ነበረኝ እሱንም አሳክቻለሁ”
“ስልኩ ላይ የተገኘው የመጨረሻው ሜሴጅ የአንቺ “ጨርሻለሁ” የሚለው ነው ምንድንነው የጨረሽው?”
ሮዝ በረጅሙ ተንፍሳ ሳጅን ዳሂላን እንዲቀመጡ ጋብዛ ቁጭ እያለች
“የዛን ለት ልንገናኝ ተቀጣጥረን ነበር፣ ጨርሼያለሁ ያልኩት ለብሼ መጨረሴን እና ልወጣ እንደሆነ ለመናገር ማመላከቴ ነበር። እሱን የማገኝበት ምክንያቱ ደግሞ እኔጋ የያዝኩትን ሪከርድ ተጠቅሜ ህፃን ዴዚን ከደበቀበት እንዲያወጣ ለማድረግ ነበር።”
“የምን ሪከርድ?”
ሮዝ ከስልኳ ላይ ሪከርዱን ትከፍተዋለች።
“ይሄን ይዘሽ ለምን ወደፖሊስ አልመጣሽም ነበር?”
“አንዱአለም የዛች ልጅ አፋኝ ብቻ አልነበረም የእንጀራ ልጁንም በ13 አመቷ አስገድዶ ደፍሯታል። ያንንም እንዲያምንልኝ ነበር ፍላጎቴ”
“ለመጨረሻ ግዜ አንዱአለምን ያየሽው መቼ ነው?”
“እንዳልኩሽ የዛን ለት ማታ ቀጠሮ ነበረን”
“የት ተገናኛችሁ?”
“አልተገናኘንም፣ እኔ ነበርኩ ፒክ የማደርገው፣ ያለኝ ቦታ ደርሼ ስደውልለት ስልኩ ዝግ ነበር።”

Brown Empire

16 Jan, 18:45


Well, what a year.

የዛሬ አመት በዚህ ግዜ፣ በጥምቀት እለት አንድ ፅሁፍ አነበብኩ። ፅሁፉ ክፋት የለውም የሆነ ደብል ስታንዳርድ ብቻ ነበረው። በላይፍ ቦይ ሳሙና ብብቱን የታጠበ ጎበዝ ደራሲ የፃፈው ፅሁፍ ነበር፣ ተረት ተረት ከሚፅፉ ወንዶች መሀል በስንት ውበት የጨመቅኩትን እውነት አወዳደረብኝና ተከፋሁ።

ምንግዜም፣ ከማልገባቸው ሰዎች ምንም ጠብቄ አላውቅም። በትንሹም ቢሆን ዘይቤዬ እና አቅጣጫዬን ያገኙታል የምላቸው ግን የሽርደዳ ቅመም፣ የሽሙጥ ማሟሻ ሊያደርጉኝ ሲሞክሩ ብዙ ግዜ ከፍቶኝ ያውቃል። የዛሬ አመትም የተፈጠረው ይሄው ነበር። ኢነርጂያቸውን የማምናቸው ሰዎች ላይ ግማሽ የመኖር ተስፋዬ አለ። አንበስ ዘውድ ብለው በአፍጢሜ ሲደፉኝ ደፍተውኝም እንዳያመኝ ሲጠብቁ የሚሰማኝ ስሜት አካላዊ ህመም ነው። ስስ ነኝ አለሜን ለመደበላለቅ አንድ የወደድኩት በአካል አይቼው የማላውቀው ሰው አስተያየት በቂዬ ያህል ስስ ነኝ። የማልወዳቸው ሰዎች ትኩረቴን አያገኙም ከአገኙም ብዙ ሳይለፉ ለነሱ ኢንዲፍረንት መሆኔን ማወቃቸው አይቀርም።
ያም ያስቀየማቸዋል፣ ያም አለሜን እንግጭ አያደርገውም። ልቤ ጠባብ ነች የብዙ ሰው ዳና አትችልም፣ ጥቂት ሰው ይገባል፣ እነሱኑ አቆላጵሳለሁ፣ በነሱው ድምጥማጤ ይጠፋል፣ ደግሞ መልሼ እነሳለሁ። ይሄንንም ደፍሮ ከሚሉት ጥቂት ሰዎች ውስጥ አንዷ በመሆኔ ሰው’ነት ይሰማኛል።

ሴት በገዛ ሀገሯ እንደሁለተኛ ዜጋ እንድትቆጠር፣ እንዳታድግ፣ ራሷን እንዳትችል የምትደረገው በወንድ ብቻ አይደለም፣ በገዛ ሴትም ጭምር ነው። ፉክክሩ፣ ውድድሩ፣ ቅናቱ፣ ጥላቻው እንደጭስ እያንዣበበ አንገቴ ዙሪያ ሲጠብቅ ልብ ለማለት ግዜ አልፈጀብኝም። ግን ሶሻል ሚዲያ ላይ ሰው እንዲወደኝ ብዬ ሰርከስ የምሰራ፣ የሰው የማስተጋባ ሚዜ አልነበርኩም። ጭሱ እንዲላላልኝ ብዬ የአንዷን የአጥር ወፍ ገንፎ ሳማስል፣ ገፁን ያላነበብኩት መፅሀፍ ሳስተዋውቅ፣ በአካል የማልወዳት ጋ በፎቶ ተለጥፌ ፎቶ ፖስት ሳደርግ፣ ሚስትየዋጋ ውዬ ባልዬው ጋ ስተኛ አልገኝም። አይደለም ከሰው ከራሴ ጋ የሚያኳርፈኝ ከፍ ያለ የራስ ክብር አለኝ። ይሄንንም ኢጎ የሚለው አይጠፋም።

በፌስቡክ ቆይታዬ ለሚወዱኝ የሰጠሁትን መፅሀፍ፣ ሀሳብ እና ፍቅር ያህል፣ ለጠሉኝም ነቀፌታን እና ንቀቴን ሰጥቻለሁ። መልአክ አልነበርኩም። ለመምሰልም ሞክሬም አላውቅም። የተሳሳትኩባቸው ግዜዎች ይኖራሉ፣ ሁልግዜ ልክ አልነበርኩም። በአካል የሚያውቁኝ የሚመሰክሩትን ያህል ሰው አክባሪ እና ይሉተኛ ነኝ። በሶሻል ሚዲያ ግን ሀሳቤን ፊርምሊ ከመናገር ያለፈ እንዲሁም እንደማንኛውም ፌስቡከር ከአልፎ አልፎ ሺት ፖስት ያለፈ ሰው ላይ ዳሜጅ ያደረሰ ክፋት አሰላስዬ አድርጌ አላውቅም። i’m extremely empathetic towards people, ቁጥብ ህይወቴ ላይ ገፍቶ መጥቶ ስርአት እንደሌለው የተራራ ነፋስ አገላብጩ እሄዳለሁ ላለ መደዴ ግን ምንግዜም መልስ አለኝ። ካርማን የምጠብቅ ቪክትም መሆን አልችልም።

“እከክ ፆታ”
የማይወዱኝ እንደማይወዱኝ ለመንገር እቺ ቃል በቂያቸው ነበረች። ፌምኒስት ነኝ ስል ከድንግል ማርያም ጋ እንዴት እንዳገናኙኝ አላውቅም። የኔን መሄድ፣ ማቅናት፣ እልፍ ማለት፣ ማደግ የምትጠላ ኢንተርናላይዝድ ሚሶጂኒ ካንሰር የሆነባት ሴትን ስደግፍም ሳቀናም አልገኝም። ሞራላዊ ግዴታዬም አይደለም። በዛም ምክንያት ማነቆ የሆኑ ሴቶችን የፓትሪያርኪ የመሀፀኑ ግድግዳዎችን እከክ ፆታ ብያቸዋለሁ ዛሬም እደግመዋለሁ።

ረጅም ግዜ ቪክትም ላለመሆን፣ ላለመምሰል ከራሴ ጋ ስታገል ቆይቻለሁ። “ ምናባቱ “ እያልኩ! ግን ቪክትም ነበርኩ የሶሻል ሚዲያ ሳይበር ቡሊይንግ ሰለባ ነበርኩ። ጠንካራ ስለመሰልኩ አይዞሽም ፣ ደህና ነሽም ያለኝ አልነበረም። “ጏደኛዬ” ብሎ እንኳ ለእምሮዬ የተጨነቀልኝ አልነበረም። ግዜዬን እና ማንነቴን የሰዋሁለት የእውነት የመሰለኝ “ጏደኝነት” ከጠዪዎቼ፣ ከስም አጥፊዎቼ ጋ ምንም እንዳልመሰለው አብሮ ሲስቅ ሲጫወት ማየት የዚህ አመት እጣ ፋንታዬ ነበር።
አዎ ታምሜ ነበር። የግሪሳው መፈናጠር ሳይሆን አሉኝ የምላቸው አለሁ ለማለት ግድ ማጣት እና ዝምታ አሳምሞኝ ነበር። እኔም በዝምታ አልፌዋለሁ። ልመስገን፣ ዛሬ ደህና ነኝ።

ይሄ አመት ብዙ ነገር አስተምሮኛል፣ በህይወት ቋሚ ነገር የለም፣ መጪው ይሄዳል ያለ ነው። ጏደኝነት የሚሰጠውን መከባበር እና ንፁህ ፍቅር፣ ክብር ከማያውቅ እና ራሱን ከማያከብር ተራ ሰው መጠበቅ ትቦ ጋ ቆሞ ግሩም መአዛን እንደመጠበቅ ነው። ግድየለም ይዤው ውስጤ የማጎለብተው ጥላቻ የለም። በአመት ውስጥ ስም እየዘነጋሁ “ያ ደሞ ማን ነበረ?” ማለት ከጀመርኩ ምናልባት የተፈጠረውንም እንዳልተፈጠረ የምረሳበት ግዜ ሩቅ አይደለም። አልፎ አልፎ ትውስታ የሚገልበው ረመጥ ይኖረኝ ይሆናል። እሱም ያለ ነው።

ደግሞም ተክሻለሁ፣ የማያኮርፈኝ፣ ምን ለማለት ፈልገሽ ነበር፣ አስረጂኝ፣ ይቅርታ፣ አይ ጋት ዩ፣ አይዞን፣ ማውራት ትፈልጊያለሽ?፣ አሞሻል አብረን እንሂድ፣ ጭማሪ ከአስፈለገሽ ንገሪኝ የሚል ጏደኝነትም አግኝቻለሁ። እቺን አመት ጎንና ጎኔን ይዘው ከአሻገሩኝ ውስጥ ይሄ ፕሮፋውንድ ጏደኝነት አንዱ ነው።
የሰው ልጅ ተስፈኛ ነው። ተሰፋ መንገደኛ ነው በጉዞውም ላይ የልቡን አይነት ወዳጅ ያገኛል። ለሁሉም የተከፉበት ቦታ ላይ አለመቆየቱ ጥሩ ነው። 🤍✌🏾

Brown Empire

09 Jan, 11:12


“ባክሽ ምናለች በይኝ ይገኛል”
“አዪ you underestimate him በነገራችን ላይ ሊሊዬ፣ remember last time እሱ እንደዚህ የተቀነባበረ ሴራ አይሰራም ስትዪ”

“እና ጠፍቶ ይቀራል እያልሽኝ ነው?”

“ፖሊስ ስራዬ ብሎ ካልፈለገው ድብን አድርጎ”

“አዪ ፖሊስ?!”

“እሱን ነው እኮ የምልሽ፣ ቆይ ግን የት ሊሄድ ይችላል? የሚሄድባቸው ቦታዎች ይታወቃሉ ስለዚህ ከዛ መጀመር እንችላለን”

“እንደኔ እንደኔ ለዘላለም ባይመለስ!”

“በቃ?! ቢታሰር የእጁን ቢያገኝ ደስ አይልሽም?”

“ይለኛል እሱማ!”

“የእጁን ማግኘትማ አለበት! ካልሆነ አመል አይለቅም በየሄደበት ችግር መፍጠሩ አይቀርም።”

በር ሲንኳኳ ሁለቱም ንግግራቸውን ገታ አድርገው ወደውጪ ተመለከቱ፣ ሮዝ ልትከፍት ወደበሩ ሄደች ሀረግ ነበረች።
ሮዝ በግርታ “አቤት ምን ነበር?”

ሊሊ ወደነሱ ሄዳ ሀረግን ስታያት “እንዴ ወሮ ሀረግ እዚህ ምን ታደርጊያለሽ?”
ሮዝ ግራ ተጋብታ ሊሊን ታያታለች
“የዴዚ እናት ነች ወይዘሮ ሀረግ ትባላለች”

“ኦህ እንዴት ነሽ ወይዘሮ ሀረግ ልጅሽን በሰላም ስላገኘሻት ደስ ብሎኛል፣ እንኳን ደስ ያለሽ!”

“የታለ ያ ውሻ?”

ሁለቱም ደንግጠው እየተያዩ
“ማን ነው ደግሞ እሱ?”
“ውሽማሽ!” ሀረግ ጥርሷን እንደነከሰች ትመልሳለች

“አንቺ ደግሞ ይሄን እንዴት አወቅሽ?” ሊሊ ተደናግራ

“አንቺ አይመለከትሽም? አንቺኛዋ መልሺ”

“ከይቅርታ ጋር ወይዘሮ ሀረግ fix your tone and attitude when you talk to me, and understand that I don’t owe you any explanation”

“እንደምታስቢው አይደለም ወይዘሮ ሀረግ ይሄን ነገር ፖሊስም ሆነ እኛ ሳንጠረጥር በቅድሚያ ያወቀችው እሷ ነበረች”

“እሱን ነው እኮ እያልኩ ያለሁት ውሽማው ስለነበረች በዚህ ነገር ዉስጥ ተባባሪ ነበረች”

ሮዝ በእርጋታ ከስልኳ ላይ ቅጂውን ትከፍታለች፣ የአንዱአለም ድምፅ ይሰማል።

“ይሄን ማስረጃ ከያዝሽ ታዲያ ለምን አስቀድመሽ አልነገርሽኝም? ወይ ፖሊስ ጋ መሄድ ለምን አልፈለግሽም?”

“አንዱአለም የልጅሽ አጋች ብቻ አይደለም፣ የብዙ ወንጀሎች ፈፃሚ ነው። ለሁሉም በቂ ማስረጃ ስለፈለግን ግዜ እየገዛን ነበር”

“አንድ ግዜ ከተያዘ አንዱ ሌላውን ወንጀል እንደሚያወጣው አልጠረጠራችሁም። ወይስ የልጅቷ ጎረምሳ ጋ መቆየት ችግር ያመጣል ብላችሁ አላሰባችሁም?”

ሮዝ “ልክ ነሽ ወይዘሮ ሀረግ እሱን ሳላስብ ቀርቼ አይደለም ሆኖም ግን እኔም ይሄን መረጃ ከረፈደ ነው ያገኘሁት ግን ደግሞ እንደነገርኩሽ አንዱአለም አጋች ብቻ አይደለም። ግን ለመሆኑ አንዱአለምን በግልሽ ለመፈለግ አንቺስ ምን አነሳሳሽ?”

“ሀላፊነት ስላለብኝ ሁሉንም ስራ ለፖሊስ ብለን ስንተው መድረስ ከሌለበት በላይ ዳሜጅ ስለሚደርስ!”

“ልትገዪው ነው የምትፈልጊው?” ሊሊ ድንገት ጠየቀቻት?

ሀረግ ቆም ብላ አይታት

“እንዲታሰር እና ቅጣቱን እንዲያገኝ”

“እሱ የፖሊስ ስራ አይደለም?”

“የኔም ስራ ነው።”

“የእኛም ስራ ነው፣ አንድ ላይ ብንፈልገው ከፖሊስ በፈጠነ የምናገኘው ይመስለኛል፣ አይመስላችሁም?”

ሶስቱም እርስ በርስ ተያዩ።

ሀረግ ሊሊን ተመልክታት

“ሁለታችሁም ለእንደዚህ አይነት ነገር ብሩህ ፊውቸራችሁ ሊያሳስባችሁ የሚገባ ነበር። ምን ተፈጠረ? “

ሊሊ ተረጋግታ ቁጭ እያለች… ለአንቺ ልጅ ብቻ ሳይሆን ለኔም ልጅነት ተጠያቂ ነው፣ ለእናቴም አእምሮ ጤና፣ ለሁለታችንም ሰላም። በ13 አመቴ በተደጋጋሚ ደፍሮኛል”

ሀረግ በሩን ዘግታ ትመልሳ ትቀመጣለች

“እናቴ ላይ ከብዙ ሴቶች ጋ ማግጧል፣ ከማህበረሰብ ታድጎ የብቻው መጫወቻ አድርጏታል። ለእኔ ለልጇ እንዳትቆም አድርጏል። ጥቃቱ አካላዊ ብቻ አይደለም። ማንም አይቶ ሊፈርድልን እንዳይችል በስነልቦናችን ተጫውቶብናል።”

“እኔ በልጅነቴ በገዛ አባቴ በተደጋጋሚ ተደፍሬያለሁ አርግዤም አስወርጃለሁ፣ በአባቴ የተነሳ በልጅነቴ ከቤት ጠፍቼ ብዙ ስቃይ አይቻለሁ፣ የማይድን ትራውማም ተሸካሚ ነኝ። እናቴም በእሱ ምክንያት አእምሯዋን አጥታለች። እስከዛሬም ነገ ዛሬ እያልኩ አላየኋትም። በስልክ በየለቱ ባወራትም በየለቱ እንዳዲስ እየረሳችኝ እንደአዲስ ታስታውሰኛለች። ይሄ ሁሉ consequence በማያውቁ ትላልቅ ማህበረሰብ ያቆላጰሳቸው ራስወዳድ ጅቦች የሆነ ነው። ስለዚህ ምንድን ነው የምንጠብቀው?”

ሀረግ እምባዋ ብዥ አድርጏት ታያቸዋለች፣ ሶፋው መደገፊያ ላይ ደገፍ ብላ እየቆመች..
“ልጄ… ልጄ ዴዚም ተደፍራለች፣ ግን ቃሉን ሲሰጥ ፈልጋ ነው ብሏል። እሷም ፈልጋ እንደሆነ አምናለች፣ ግን የ13 አመት ልጅ ስለሆነች ከተጠያቂነት አያድነውም፣ ቢሆንም ግን የፖሊሶቹ አስተያየት ልክ አልነበረም። ነገሩን ከቁም ነገር አልያዙትም ፈልጋለች ብለው ልጁን ከሚገባው ቅጣት ሊያቀሉለት ይችላሉ። ስጋቴ እሱ ብቻ ሳይሆን ዴዚ ታግታ በነበረበት ግዜ ውስጥ ተደውሎ ገንዘብ አልተጠየቅንም ስለዚህ በፍላጎት ኮብልላ ነው ወደሚል መንገድ እየሄዱ ነው፣ አንዱአለምም በዚህ ግርግር ነፃ ሊለቀቅ ይችላል።
ስለዚህ አስቀድሜ እጄ ማስገባት አለብኝ። “

“እጃችን*”
ሮዝ ታርማታለች

ሀረግ ፈገግ ብላ አይታቸው “እመኑኝና በኔ ጣሉት ልጅነታችሁን ለመካስ ወጣትነታችሁን አትሰዉ!
ይሄ ውይይትም ሆነ እኔ እዚህ መገኘቴ እንዳልተፈጠረ በመርሳት እኔን ማገዝ ትችላላችሁ።
ቃል ግቡልኝ ለኔ እንደምትተውት!”

ሁለቱም በቅሬታ ቃል ይገባሉ።
ሀረግ ወጥታ ትሄዳለች።
*

የነ ሊሊ ቤት ከወትሮው በተለየ ንፁህ ሆኗል። ይሔን ሰሞን ሊሊ ስትወጣ ስትገባ እናቷ አጎንብሳ እያንዳንዱን ነጥብ ቆሻሻ ስትፈቀፍቅ፣ ስታፀዳ እና ቤቱን ቀለም ስትቀባ፣ አሮጌ ስትጥል ነው የምታያት። የሶፋ ልብስ፣ አንሶላ እና የአንዱአለም ልብሶች በሙሉ ለልዋጭ ተለውጠዋል። ለቀናት ያለማንም እርዳታ ቤቷን ቀለም ቀብታ ጨረሰች፣ የቤቱ አቀማመጥ ተቀይሯል፣ የሊሊን ክፍል ኪችን አድርጋ ኪችኑን ቀባብታ እና አፅድታ ቀየረችላት። ከጀርባውም ትልቅ መስኮት አስገብታ በቂ ብርሀን እና አየር እንዲገባላት አደረገች። ፀጉሯን ባጭሩ ተቆረጠች። አይኗ ላይ ያለአግባብ የምትሞጅረውን ኩል እና ማስካራ አውጥታ ጥላለች። ንፁህ የአርባዎቹ መጀመሪያ ሴት ሆናለች።

ሊሊ የእናቷ ነገር የማትፈልገውን እውነት እንድታምን እየታገላት ቢሆንም እስከመጨረሻው የሚሆነውን ለማየት እየጠበቀች ነው። ከእናቷ ለውጥ የመጣ ደስታ ቢኖርም አብሮት ትልቅ ስጋትም አለ። እናቷ አንዱአለም የሚባል አምስት አመት አብሯት የኖረን ሰው ከእጣቢ ጋ እንደደፋችው ማንኪያ ዘንግታዋለች። በዚያም የተመቻቸ ሰላም ላይ ትመስላለች።

ሊሊ ሳሎን ቁጭ ብላ የእናቷን ሲቪ እያስተካከለች ቴሌቪዥኑ ላይ ሰበር ዜና መጣ።

“በዛሬው እለት ሰሞኑን በጥብቅ ክትትል ፍለጋ ሲደረግበት የነበረው ህፃን ዴዚ አለማየሁን ለሁለት ሳምንታት አግቶ የቆየው ተጠርጣሪ አንዱአለም ካሳ ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት ተገድሎ ሬሳው በእንስሳ ተበልቶ ተገኝቷል።

ሊሊ በድንጋጤ
ወደእናቷ ዞረች። አበባ ትንሽ ትኩር ብላ ካየች በኋላ ሊገነፍል ወደተቃረበው ወተቷ ጠጋ ብላ “እፍ እፍ” ማለት ጀመረች።

ሊሊ አእምሮዋ ወደ ሀረግ ደግሞም ወደ እናቷ እንደ ፒንግ ፖንግ ኳስ ተላጋ።

ይቀጥላል…

Brown Empire

09 Jan, 11:12


የዱር አበቦች
ክፍል 9
ሀረግ x አበባ x ሮዝ x ሊሊx ዳሂላ


ሊሊ ሳሎን ተቀምጣ የእናቷን መምጣት እየተጠባበቀች ነው። በመሀል አልፎ አልፎ ሀሳብ ጭልጥ አድርጎ ይወስዳታል። ሮዝ ከአንዱአለም ጋ ቁጭ ብላ ምግብ መብላት መቻሏ ራሱ ያስገርማታል። ምናልባት የቀዳችውን ድምፅ ባትሰማ መጀመሪያውኑ ልትበቀልላት መቅረቧን ለማመን ትቸገር ነበር።

የሮዝን የልጅነት ታሪክ ስታውቅ ደግሞ ከአንዱአለም የባሰም እንዳለ አወቀች፣ እንጀራአባት ሲገርማት አባትም ጠላት የሚሆንበት አለ። ምናልባት በህይወቷ ውስጥ በዚህ ሰአት ሮዝ ባትኖር ኖሮ ምን እንደምትሆን አታውቅም። እሷን ካገኘች ወዲያ የውስጧ ጩኸት ቀንሷል፣ ንዴቷ በርዷል፣ የአይኗ ሳቅ ተመልሷል።

እናቷን ስታስብ ግን ጥልቅ ሀዘን ይሰማት ጀመር። ምናልባት እንዲህ በግዜ እንደኔ የምታዋራው ብታገኝ ትድን ነበር ይሆን እያለች ተብሰለሰለች። ግማሽ ጎኗ ለምን እንደሚያዝንላት ይጠይቃታል። ግማሽ ጎኗ ጤነኛዋን አበባ ማወቅ ይፈልጋል። አሁንም አይዞሿን፣ ልጄ አጥፍቻለሁ ይቅር በይኝ፣ ከዚህ በኋላ እክስሻለሁ፣ አለሁልሽ ብላ እንድትመለስ የሚፈልግ በአንድ እግሩ የቆመ ተስፋ ውስጧ አላት።

ምናልባት አንዱአለም ብቻዋን አግኝቶ አእምሯዋ ላይ በአላዋቂ እግሩ ባይረመርማት ትተርፍ ነበር? ምናልባት ማህበረሰብ ልጇን ልታሳድግ የቀረችውን አንድ ወላጅ መንቀፍ ትቶ ጥሎ የሄደውን ቢያብጠለጥል የተሻለ ይሆን ነበር?

ሁላችንም “ጦስሽን!” መባል ነው የቀረብን! “ይቅራ! ብቻ አንቺ ደህና ሁኚ! አእምሮሽን ጠብቂ!” ብሎ ለምለም ቃል የሚዘራ ጠፍቶ ነው በትውልድ የሚምዘገዘግ የብቸኝነት፣ ያለመፈለግ፣ በቂ ያለመሆን ህመም በዘረመል የሚቀጥለው።

*
ሳጅን ዳሂላ ቢሮዋ አምሽታ የአንዱአለምን ፋይል እና የልጆቹን ቃል ከመዝገብ ላይ ታገላብጣለች። ወረቀት ላይ ከፃፈችው ማስታወሻ ውስጥ “የአባባ ሱቅ”የሚለው ተከቦበታል። ሰአቷን አየች እና አንገራግራ ከቢሮ ልትወጣ ጃኬቷን አነሳች። በዛው ቅፅበት ግን ስልኳ ላይ መልክት ተከታትሎ ገባ። ወዲያው ከunknown ቁጥር ስልክ ጥሪ ደረሳት።

ሄሎ ሳጅን ዳሂላ
“ሀሎ ሳጅን ልጄን አግኝቻታለሁ፣ ግን አሁኑኑ እርዳታሽ ያስፈልግኛል።” አለች ሀረግ ከወዲያኛው መስመር

*
ሀረግ ካጠለቀችው ሰማያዊ የላስቲክ ጏንት ላይ ደም ጠብ ጠብ ይላል። እጆቿ በቦክስ እና በእልህ ዝለው በቸልታ ተዘርግተዋል። ከፊት ለፊቷ ጋሽ በላይ(አባባ) እና አላዛር (የአንዱአለም ጏደኛ የአባባ የመጨረሻ ልጅ) በገመድ ታስሮ አፉ ተጠቅጥቆ ከተሰበረ አፍንጫው ደም እያዝረበረበ አጎንብሶ ቁጭ ብሏል። አባባ በድንጋጤና እና በተስፋ መቁረጥ አንዴ ልጃቸውን አንዴ ሀረግን ያዩዋቸዋል።
“ብዬ ነበር ምን ዋጋ አለው” ብለው እንደርሳቸው በእርጅና የነተበ አረፍተነገር አልሞሰሞሱ እና ችፍ ያለ ላባቸውን በደከመ እጃቸው ከግምባራቸው ጠረጉ። ውሀ ሊጠይቋት ወደ ውሀ ጃሩ ተመልክተው እጃቸውን አመላከቱ እና በሀሳብ ብቻ ገቱት።

ሀረግ ሁኔታቸው ገብቷት ከእጇ ላይ ደም ያጨማለቀውን ጏንት አውልቃ በላስቲክ ጠቅልላ ኪሷ ከተተች። ውሀውንም ቀድታ አቀበለቻቸው። ከክብራቸው እና ከእውነት ጋ (ምንም ቢሆን ልጄ ነው ምንም ቢሆን ልጇ ናት ከሚል) ለሰከንድ ተፋልመው ተቀበሏት።

እንደጨረሱ አስነስታ ወደመኝታ ክፍል ወስዳ “እዚህ ጋደም ይበሉ” ብላቸው ልትወጣ ስትል

አባባ አልጋው ላይ በቀስታ እያረፉ “አሁን ምን ልታደርጊው ነው? የዱርዬ ነፍስ እጅሽ ላይ አታድርጊ ለፖሊስ ስጪው”

ቆም ብላ ከአዳመጠቻቸዉ በኋላ
“አይተዋት ያውቃሉ?” ብላ ጠየቀቻቸዉ

“እህ ልጅቱን? አዎን መች በግዴታ ተያዘች? ቤት ውስጥ ትላወስ የለም? መች በግዞት የመጣች መሰለኝ? ተዋደው እንደሆን ብዬ ዝም አልኩ። በርግጥ በግድስ ቢመስለኝ ምን ማድረግ እችል ነበር? ይገድለኛል! ስንት እዳ ውስጥ ገባሁ መሰለሽ! በወለዱት አለመታደልን ያህል እርግማን የለም!”

ሀረግ የሰማችው ልቧን እንደሰበረው ስሜት አልባ ፊቷ ሆኖ እንደማያውቀው ሲጨማደድ ያስታውቃል።
“በወለዱት አለመታደል…” ደገመችው እና መኝታውን ላያቸው ላይ ዘግታ ወጣች።

ቀጥሎ ያለው ክፍል ከውስጥ ይንኳኳል። “አላዛር?! አንተ አላዛር?! ኧረ ዛሬ ደግሞ ለምንድን ነው የተቆለፈብኝ?! ይሰማኛል እኮ ኮቴህ! ሽንቴ መጥቷል እባክህ ክፈትልኝ”

ሀረግ “ልጅሽም አለችበት፣ ፈልጋ ነው በግድ አይደለም” የሚሉት የአላዛር ቃሎች አፍንጫውን እንዳትሰብረው ባያቅቧትም፣ የሱም ቃሎች እንደቀስት እየተወረወሩ ልቧን ፍርስርሱን አውጥተውታል። ሀረግ ከውጪ እንደቆመች አፏን ይዛ ትክን ብላ ወደውስጥ አለቀሰች።

ከዚህ ሁሉ በኋላ የልጇን ፊት ማየት ፈራች፣ አልፈልግሽም ብትላትስ? የዚኔ ነበር ወደ ሳጅን ዳሂላ ደውላ እሷ እንዳገኘቻት እንዲመስል የተነጋገሩት።

ስልኳ ሲጠራ
ለዳሂላ በር ልትከፍት ሄደች።
*
ሮዝ አልጋዋ ላይ ዝርር ብላ ታስባለች። አንድ ልክ ያልሆነ ነገር እንዳለ ቀልቧ ነግሯታል። የሚያምር የራት ቀሚሷ ላይ ቀይ የደም ነጠብጣብ ይታያል፣ ወገቧን አንዳች ህመም ይገዘግዛታል፣ ከቦርሳዋ ፔንኪለር አውጥታ ወሰደች እና አይኗን ጨፍና ለመተኛት ሞከረች።

*
ሊሊ ሶፋ ላይ ከተኛችበት ሌሊት ላይ የማሽን ድምፅ ቀሰቀሳት፣ ሰአት አይታ ተነስታ ወደኪችን ሄደች፣ አበባ ፀጉሯን ታጥባ በፎጣ እንደጠቀለለችው እርጥብ ገላዋን በደንብ ሳታደርቅ ፒጃማ ላይዋ ላይ ልጥፍ እንዳለ ልብስ ታጥባለች።

ሊሊ ድንግር ብሏት አይታት
“እማ ስንት ሰአት መጥተሽ ነው? ለመሆኑ ሰአቱን አይተሽዋል? ምነው በሌሊት”

አበባ ልጇን አያየች “እንቅልፍ እምቢ ብሎኝ እኮ ነው፣ ቀሰቀስኩሽ አይደል? ጨርሻለሁ ሀያ ደቂቃ ታገሺኝ”

እናቷ ፊት ላይ የሆነ ብርሀን አለ፣ ቆንጆ ፊቷ ከበፊቱ ደምቆ በርቷል፣ ንቃት አለው። የረጅም ግዜ ድብርቷ የተገፈፈ ይመስላል..

“በሰላም ነው እማ?”
በድጋሚ ጠየቀቻት

ፈገግ እንዳለች በአዎንታ እና ቸልታ ራሷን ነቀነቀች

ሊሊ እናቷን በዚህ መረጋጋት አታውቃትም… ግራ እንደገባት “አንዱአለምስ?”

“ደሞ እሱ የት ነው ተብሎ ይጠየቃል? ይትም ሊሆን ይችላል ሂጂ ተኚ አንቺ እኔም ጨርሻለሁ ትንሽ ነው የቀረኝ”

ሊሊ ግር እንዳላት ወደመኝታዋ ተመለሰች።

*
አለማየሁ ሶፋ ላይ እግሩን ዘርግቶ እንደተኛ ቴሌቪዥኑ ላይ መግለጫ የምትሰጠዉን ሳጅን ዳሂላን ይመለከታል።
ዴዚ ተጣጥባ እና ልብሷን ቀይራ ከአባቷ አጠገብ ተቀምጣ በኩርፊያ ስልኳን እየነካካች ነው። ቴሌቪዥን ላይ ያለችውን ሳጅን ዳሂላን በመጥፎ አይን ቆረጥ እያደረገች ታያለች።

ሀረግ ኦፕን ኪችንኣቸው ውስጥ ካቢኔቱ ጋ ቆማ የዴዚን የሆስፒታል ውጤት እየተመለከተች ነው። ድንግል እንዳልሆነች ከሚያሳየው ውጤት ባለፈ የእርግዝና የኤች አይቪ ውጤቶች ትንሽ ግዜ እንደሚፈልጉ የሚያሳውቅ ወረቀትና እና የሌሎች ተጏዳኝ በሽታዎች ምርመራ ውጤት ይዛለች። ጭንቀቷን ስብስብ አድርጋ እንደዋጠች የቱጋ እንዳጠፋች ለማወቅ በሀሳብ ባዘነች። በልጇ ብትበሳጭም ልትፈርድባት ግን አትችልም። ምንም ቢሆን ተጠያቂነቱን እና ሀላፊነቱን የሚወስደው በእድሜ የበሰሉት ናቸውና ክሱን በእገታ ብቻ ሳይሆን ያልደረሰች ህፃን ልጅ ግሩም በማድረግና በመድፈር ወደሚለው አሳደገችው። ይሄንን ሆን ብላ ፖሊስ እንዲይዘው ብትፈልግም በዚህም በዚያም ብላ አንዱአለምን ቀድማ እጇ ማስገባት እንዳለባት ግን አምናለች። እንደዛ ካልሆነ ውስጧ የሚንተከተከው መጠቃት ተረጋግቶ መቼም አይተኛም።
*

ሊሊ እና ሮዝ በዴዚ መገኘት ደስ ቢላቸውም የአንዱአለም መሰወር ግን አትክኗቸዋል።

Brown Empire

02 Jan, 06:58


“አበባ እባላለሁ አታውቂኝ ይሆናል፣ ታውቂኝም ይሆናል? አላውቅም የአንዱአለም ባለቤት የሰማኒያ ሚስቱ ነኝ።”

“እሺ ምን ልርዳሽ ወይዘሮ አበባ” ግር እንዳላት ጠየቀች

“ወይዘሮ አበባ?! ሃሃ፣ ይሄ ወይዘሮ… ወይዘሮ ለመባል ሆኜም ለመቅረት ብዙ ሆኜ ነበር። ፍዳ ነው የበላሁት ለወይዘሮነት”

ቤቷን እየተዟዟረች ታያለች..

“አንዴ ወይዘሮ ከሆኑ በኋላ ፍቺም ወይዘሪት አያስብልም በርግጥ” ሮዝ መለሰች

አበባ ንግገሯ የለግጥ ነው እንዲሁ ለወሬዋ መልስ መሆኑን ለማጣራት ለሰከንዶች የሮዝ ፊት ላይ በቆንጆ አይኖቿ ተሽከረከረች።

“ይቅርታ ወይዘሮ አበባ የምረዳሽ ነገር አለ?”
ሮዝ በጨዋነት ደግማ ጠየቀች።

“ቆንጆ ነሽ፣ ወጣት ነሽ፣ እንደማየው ከሆነ የልጅ ሀብታም ነሽ፣ እኩያ አጥተሽ ነው? እንደ አንዱአለም አይነት ባለጌ፣ ሴት አሳዳጅ፣ እና ለስሙ ባለትዳር ከሆነ ወንድ ጋ የተለጠፍሽው?”

አበባ በፍፁም ግርምት ጠየቀቻት…
ሮዝ ከአበባ ይልቅ እናቷ መምጣቷን ስታውቅ መኝታ ቤት ገብታ ለምታዳምጠው ሊሊ ተጨነቀች።

አበባ ከሮዝ መልስ ስታጣ “አይሆንሽም ልጄ? አይሆንሽም! ብታተርፊ በሽታ ነው። ነፍስ መጣጭ ነው እሱ! ክፉ መንፈስ! ተይልኝ ልልሽ አይደለም አመጣጤ፣ ስሰማ ልጅ መሆንሽን ስላወቅኩ ቢያንስ ከዚህ ወዲያ በግድየለሽነት አልለፈው ብዬ ነው። አይሆንሽም!”

አበባ ሮዝ ባልለቀቀችው በር በፍጥነት ወጥታ ሄደች።

ሮዝ በድንጋጤ እንደቆመች ሊሊ ከመኝታ ቤት ወጣች።
*

ሊሊ ቁና ቁና ትተነፍሳለች። ቤቷ ገብታ እናቷን ማቀፍ ፈልጋለች። የሰማችውን ማመን አቅቷታል! አንዱአለም የዚህን ያህል ቀመረኛ ክፉ አይመስላትም ነበር። እንዲሁ ሀገር ወለድ፣ ማህበረሰብ “ወንድ አይደለህ” ብሎ ያበረታታው አህያ ነበር የሚመስላት።

በሮዝ ፕላን መሰረት ያገኙትን መረጃ ፖሊስ ጋ ለመውሰድ ቢያስቡም አንዱአለም 25 አመት እስርቤት ቢቀለብ የእናቷም፣ የእሷም፣ የዴዚም ቁስል እንደማይጠግ አውቀዋል። ስለዚህ ሌላ ፕላን መንደፍ ስለነበረባቸው በንፁህ ጭንቅላት ለማውራት ለበነጋታው ተቀጣጥረዋል። ሊሊ ግን ወደቤቷ እየሄደች አላልቅ ያላትን መንገድ ስትራመድ ከእሷ የተነጠቀው ልጅነት ከእናቷ የተመጠጠው ነፍስ አንገበገባት። ቤት ስትገባ እናቷን ከረጅም አመታት በኋላ አቅፋ ሳመቻት። አበባ ድንዝዝ እንዳለች ከሊሊ ኪስ ምንጣፍ ላይ የወደቀውን ሴንጢ ትመለከታለች።

*
ሀረግ የአባባ ሱቅ ጋ ስትደርስ ለአይን ያዝ አድርጏል፣ አካባቢው ላይ ብቸኛ ብርሀን የሱቋ ወጋገን ብቻ ነበረ። አባባ ትልቅ ሽማግሌ ናቸው ደገፍ ብለው ያንጎላጅጃሉ። ሱቁን ብታንኳኳም አልሰሟትም። ከውስጥ አንድ ጎረምሳ “ይሄ ሽማግሌ አሁንስ አረጀ” እያለ መጣ።
ሀረግ ልጁ የለበሰውን ልብስ ከላይ እስከ እግሩ ተመለከተች። ጃኬቱ ባሏ አለማየሁ ለአንዱአለም የሰጠው ነበር። ስክሪኑ የፈሰሰውን የእግሩን አውራጣቱን አየች።
“እናት ግዜ አለሽ መሰለኝ” አላት በሹፈት
ቀዝቀዝ እንዳለች በባሏ ጃኬት ኮሌታ አንገትና አንገቱን በፍጥነት ስባ ከሱቁ ብረት መስኮት ጋ አጋጨችው።

አባባ አሁንም አልነቁም።
*
አበባ ለአንዱአለም ደውላ “ደርሻለሁ ተቀበለኝ ጃኬትህን የታለህ? “አለችው
“ግሮሰሪው ጋ ነኝ የታለሽ?” እያለ ከሁካታ ውስጥ ወጣ፣ ከሌላ ግዜ በተለየ ሽቅርቅር ብሏል፣ ሽቶም ተቀብቷል”
*
ሮዝ ራት ልብስ ለብሳለች። በመስታወት ራሷን አይታ ቀይ ሊፕስቲኳን ቦግ አድርጋ ተቀባች።
አንዱአለም ጥቁር እና ጠይም ሴቶች ቀይ ሊፕስቲክ ሲቀቡ ሰይጣን እንደሚመስሉት ነግሯት ያውቃል። አፏን እስከመጨረሻው ከፍታ ሳቀች።

የወይን መክፈቻ ቦርሳዋ ውስጥ እየከተተች ለአንዱ አለም ቴክስት አደረገች።
“ጨርሻለሁ”

ይቀጥላል…

Brown Empire

02 Jan, 06:58


የዱር አበቦች
ክፍል 8
ሀረግ

ሀረግ የ38 አመት ሴት ነች፣ በህግ ሙያ ተምራ ተመርቃ የመንግስት ስራ ከጀመረች በትንሽ ግዜ ውስጥ የአእምሮዋን ንቃት እና ለአመነችበት ጉዳይ ታማኝነቷን በማየት መንግስት በደህንነት ቀጠራት። ለነገሮች ቀዝቃዛ ነች። ቸኩላ የምታሳየው ስሜት የለም። ማንም ሰው በአላት ችሎታ እንዲገረም እና የተለየ ትኩረት እንዲሰጣት አትፈልግም። በዝግታ ስራዋን ትሰራለች። አንዳንድ ግዜ ጠንካራ ውሳኔ የሚጠይቅ ኬዝ ያጋጥማታል። እሱንም በዝምታ እና ከበረዶ በበረደ ስሜት ትወጣታዋለች።

ቤቷ ስትሄድ ሚስት እና እናት ነች። ለሁለቱም ስሞች የተለየ ግነት ያለው ስብእና የላትም። ሁሉም ቦታ በቅዝቃዜ ማድረግ ያለባትን የምታደርግ ሀላፊነቷን በታማኝነት የምትወጣ አይነት ሰው ነች።ከስራዋ ውጪ የተቀረ ግዜዋን በመስሪያ ቤቷ ጂም ውስጥ ታሳልፋለች። የአእምሮዋ ጥንካሬ የሰውነቷን ባላንስ እንዲያደርግ ታደርጋለች።

ባሏ አለማየሁ ከእሷ የተለየ ነው። እኩል ምላሽ በመንፈግ እስክታደክመው ድረስ ስፍስፍ ብሎ ይወዳት ነበር። ዛሬ ዛሬ ገብታው ቅዝቅዝ እስኪል ድረስ ለእሷ ያለው ፍቅር የሚያስጨንቅ ነበር። የተዋወቁት የደህንነት መስሪያ ቤት ከገባች በኋላ ነው። አንድ ግዜ አንድ ላይ የያዙትን ኬዝ በመወጣት ላይ ሳሉ ደም ሲያይ ብዥ የሚልበት አለማየሁ የሀገር ሚስጥር የያዘ ጠላት ሚስጥር እንዲያወጣ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ለመጀመሪያ ግዜ ሀረግን በዚህ ልክ ያረጋጋትን ቅዝቃዜ ነፍስ ዘርቶ አየው። ምህረት እና ስሜት የለሽ ነበረች። አቅለሽልሾት ከክፍሉ ወጥቶ ሲቀር ኦፕሬሽኑን ቀጥ አድርጋ የጠላት ኮድ ከሰውዬው ሆድ ገፍታ ከምላሱ ላይ የተቀበለችው ብቻዋን ነበር። ሰውዬው ዛሬ ላይ ከአስሩ ውስጥ ሰባቱ ጣቶቹ ጥፍር አያውቁም።

ከዛ እለት በኋላ አለማየሁ ሀረግን ቅዝቃዜዋ ውስጥ ያለውን ጭካኔ ስላየ ይፈራት ጀመር። በግዜ ሂደት ፍርሀቱ ፍቅሩን አደበዘዘበት። ለፍቅር የተፈጠረው አለማየሁ ከውስጡ የሚገነፍለውን ፍቅር ሙሉ በሙሉ ልጁ ላይ በማዋል ትዳራቸው በዴዚ በኩል ፀንቶ እንዲቆይ አደረገ።

ሀረግ ስለአስተዳደጓ አታወራም ብቻ ሳይሆን አታስብምም። ቤተሰቦቿ የት እንዳሉ ለማንም አትናገርም። ከአገኘቻቸውም ድፍን ዘጠኝ አመት ሆኗታል። እዚህ ሰፈር ከገቡ ስድሰት አመታቸው ሲሆን መኖሪያ ቤት ከዚህ በፊት ሁለቴ ቀይረዋል። ልጇ ስትታገት መጀመሪያ ያሰበችው በስራ በሉል የተጋጨችው አካልን ነበር። ነገሩ በፍጥነት ወደፖሊስ እንዲሄድ ባትፈልግም ጉዳዩን ያወቁት የበላይ አዛዦቿ ነገሩ ከፖሊስ መጀመሩ እንደማይከፋ አሳመኗት። ተመላልሳም ጉዳዩን እንዴት እንደያዙት ለማየት ሞከረች፣ የባለቤቷ የአለማየሁ ያህል በፖሊስ ተስፋ ባይኖራትም በተቻላት መጠን እንደማንኛውም ሰው በህጋዊ መንገድ ጉዳዩ እንዲታይ ትግስት አድርጋ ለመጠበቅ ሞከረች፣ በመሀል ግን ሴት ልጇ ምን አይነት ቦታ እንዳለች ለማወቅ እንኳን ከአጋቾች የሚጠበቀው ስልክ በመቅረቱ ስጋት እየገባት መጣ።

ጉዳዩ የገንዘብ ሳይሆን እነሱን የመበቀል እየመሰላት ሲመጣ ከዚህ በፊት የማያውቃት አይነት ጭንቀት ለቀቀባት። በአንድ በኩል አለማየሁ ያለበት ዴቨስቴሽን አስፈሪ ሆኖባታል። እንደተራ ሰው ፖሊስ ጋ ሲመላለስ ከፖሊስ ቢሮ የጫማ ሽታ ብቻ ነበር ያተረፈው። አስሙ ተነስቶበት ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ተናንቆት ከቆየ በኋላ ይባስ ብሎ ብልብ ድካም ወድቆ ሆስፒታል ገባ። ሀረግ ባሏ መታመሙን ብትጠላውም ለትንሽ ቀን ሆስፒታል እንዲቆይ መደረጉ ግን ለእሷ በነፃነት የመንቀሳቀስ እድል ሰጣት።
*
ኢንሄለሩን በአንድ እጇ እንደያዘች ፖስታውን የካፖርቷ ኪስ ከትታ ከቤት ወጣች። ማረጋገጫ ብታጣም ወደኋላ ተመልሳ ብዙ ነገሮች እርስ በርሳቸው አያያዘች። በዝግታ ስትነዳ ለተመለከታት አእምሮዋ ውስጥ በሰፊው የተዘረጋ ፕላን ያለ አይመስልም፣ ጉሮሮዋ ላይም ሀይለኛ የተደፈርኩ ስሜት ተሰንቅሮ በትንሽ ቦታ ብቻ በእርጋታ እየተነፈሰች እንዳለች ለመንገር ያዳግታል።

*

ሳጅን ዳሂላ ከፊቷ በእርጋታ የተቀመጠችውን ሀረግን እየተመለከተች፣ እንደሌሎቹ በሀሰት ተስፋ ልትሸነግላት አልሞከረችም።

“እውነት ለመናገር እገታ ከሆነ እስካሁን ሊደውሉ ይገባ ነበር፣ እሱን ተከትለን አንድ አቅጣጫ እናገኛለን ብዬ ነበር። ግን ምንም የምንይዘው መንገድ ጠፍቶናል”

“ይቅርታ ሳጅን ዳሂላ”

ሳጅን ዳሂላ ለመጀመሪያ ግዜ ስሟ በስርአቱ ስለተጠራ እንግዳ የሆነ ምቾት ተሰማት

“ልጄ ታክሲ ውስጥ ተሳፍረው የነበሩት ልጆች ስታነጋግሯቸው ያለውን ሪፖርት ማየት እችላለሁ?”

“ይቅርታ ..”

ሀረግ ለመጀመሪያ ግዜ የደህንነት መታወቂያዋን አውጥታ እያሳየቻት… “ሳጅን ዳሂላ ይሄ ሚስጥር ከእኔና ከአንቺ ከአለፈ የሀገርን ሚስጥር በማዝረክረክ እንደሚያስጠይቅሽ እየነገርኩሽ መዝገቡን እንድታቀብይኝ እጠይቅሻለሁ?”

ሳጅን ዳሂላ በመስማማት ጭንቅላቷን እየወዘወዘች “ወይዘሮ ሀረግ ይሄንን ኬዝ አሳልፌ ብሰጥሽ እኔም ተጠያቂ ከመሆን አልድንም ስለዚህ የሚያስፈልግሸን በፎቶ ብትወስጂ ለእኔም ለአንቺም ጉዳት የለውም።”
ሳጅን ዳሂላ መዝገቡን ከፊቷ አስቀምጣ የቢሮውን በር ልትቆልፍ ተነሳች።

ሀረግ ፎቶ አንስታ ጨርሳ እንደተነሳች

ሳጅን ዳሂላ “ይቅናሽ ወይዘሮ ሀረግ! በማስፈልግሽ ሰአት አለሁ!” ብላ የቆለፈችውን በር ከፈተችላት።

ሀረግ አመሰግና ወጥታ ሄደች።
*
አመሻሹ ላይ አንዱአለም ከአንዲት ወጣት ሴት ጋ ባር ውስጥ ሲገባ ከመኪናዋ ሳትወርድ ፎቶ ያነሳችውን ፋይል በጥንቃቄ እያየች ከውጪ ቆየቻቸው። ከሁሉም ልጆች ቃል በተደጋጋሚ ያነበበችው “የአባባ ሱቅ” እና “ጥፍር የሌለው የእግር አውራ ጣት” የሚለውን ቃል ብቻ ነው።

እነአንዱአለም ከባሩ ሲወጡ በቀስታ ተከተለቻቸው። አንዱአለም ሰፈሩ ሲደርስ ከልጅቷ መኪና ወርዶ እጁን አፉ ላይ አጣብቆ ስሞ መልሶ ዘረጋ፣ ከመኪናው ውስጥ ግን ምላሽ አልነበረም። እንዲያውም መኪናው በፍጥነት ከዛ ቦታ ተሰወረ። ሀረግ በቅርብ ርቀት ተከተለቻት፣ አንድ አፓርትመንት ጋ ስትደርስ አሽከርካሪዋ መኪናዋን ፓርክ አድርጋ ወደ ሀረግ መኪና ተቃረበች። ሀረግ ወደእሷ እንደምትመጣ ስታዉቅ አዙራ ወደመጣችበት ተመለሰች።

*
አበባ እና ሀረግ ካፌ ቁጭ ብለዋል። ሀረግ እንቅልፍ ሳይተኙ በሰነበቱ አይኖቿ አበባን ከእግር እስከራሷ ትገመግማታለች።

አበባ የሰማችውን በትክክሉ የተቀበለቻት አትመስልም። ከጣቶቿ ትነሽ ወጣ ብለው ያደጉ ጥፍሮቿ ውስጥ ጥቁር ቆሻሻ ተሰግስጏል። ቀይ ቆንጆ ብትሆንም መልኳ ሁሌም የሆነ የረሳችው ነገር ያለ ያህል እዚህ ያለመሆን አይነት ጉድለት አለበት።

ማዶ ማዶ አይታ ሲደክማት
“ ይሁን እስኪ ይሁንለት እቺ ህይወት ለእንደሱ ላሉ ነው የሆነችው። “
አለች በከባዱ ተንፍሳ።
“ስለ ልጅሽ ግን ምንም የማውቀው ነገር የለም፣ ቦትራፋ ነው ቢያውቅ ያወራ ነበር፣ ቀድሞውንስ ምን እውቀት ኖሮት እንዲህ የተራቀቀ ወንጀል ይሰራል?”የእሱ እውቀት ሴት ማሳደድ ነው” ከንፈሯን በንቀት አንሻፈፈች

ሀረግ ሂሳብ እየከፈለች፣ የምትፈልገው አይነት እሳት ከአበባ በማጣቷ ልትሄድ ተነሳች
አበባ ግን አንዱአለም ህይወቷ ውስጥ ከገባ ጀምሮ ያሰማት ንቀት በተቀመጠችበት ተጭኗት እንደተቀመጠች ቀረች።

*
አበባ ሮዝ በር ላይ ቆማለች።
ሮዝ አንገራግራ ከፈተች። አበባ ሮዝን ከእግር እስከራሷ እያየች
“አንቺ ነሽ ሮዝ?”
ሮዝ አንገራግራ በአዎንታ ራሷን ነቀነቀች።

ገፋ አድርጋት ወደውስጥ ገባች

ሮዝ በሩን እንደያዘች በግርታ ቆማ ቀረች

Brown Empire

27 Dec, 06:58


አለማየሁ ራሱን እንደማዞር ብሎት ቢጫ የተቀባውን የፖሊስ አጥር ታክኮ ተቀመጠ። ሀረግ የምታደርገው ጠፍቷት በትግስት ፖሊሶቹ የሚሉትን ለመስማት በትግስት ትጠባበቃለች።

ሳጅን ዳሂላ መጥታ
“እስኪ አንዴ እንደማመጥ እዚህ ጋ ጫጫታ በመፍጠር የምታመጡት ነገር የለም፣ አንድ በአንድ ወደቢሮ እየገባችሁ አድራሻችሁን ትነግሩናላችሁ በየቤታችሁ እየመጣን የምንፈልገውን ኢንፎርሜሽን እንሰበስባለን። የዴዚ ወላጆች እኔን ተከተሉኝ ሌሎቻችሁ ባልደረባዬ ጋ በተራ እየገባችሁ አድራሻ አሰመዝግባችሁ ሂዱ። ሰንፈልጋችሁ እንጠራችኋለን ወይ እንመጣለን።

ሀረግ ዞር ብላ ባለቤቷን በአይኗ ፈለገች። ዝልፍልፍ ብሎ አጥሩ ስር እንደተቀመጠ ነው።
“አሌክስ?”
ቆፍጠን ብላ ተጣራች

አለማየሁ ሚስቱን ሀረግን ቀና ብሎ አያት፣ እቃ የጠፋባት አትመስልም ጥንካሬዋን እያደነቀ ብድግ ብሎ ተከተላት
*

አንዱ አለም ቁና ቁና ይተነፍሳል ፣ ሳጅን ዳሂላ በዝምታ አንዱአለምን ስታየው ቆይታ
“እንደሰማሁት ከሆነ ለልጅቷ የተለየ ቅርበት ነበረክ”

“የተለየ ስትይ ?”
ለሶስተኛ ግዜ ከቢሮው ጠረምጴዛ ላይ ሶፍት መዘዘ እና ግምባሩን ጠረገ! ብጣሽ ሶፍት በላቡ በስብሳ ግምባሩ ላይ ቀረች!
“አዎ ወይ አይ በማለት ተባበረኝ፣ ቅርበት ነበረክ አልነበረክም?”

“አዎ ማለትት ? ቤተሰቦቿ ቤተሰቦቼ ናቸው።”
“ በስጋ ዝምድና?”
“ሳይሆን? ያቀርቡኛል እንደቤተሰብ”
“የሌሎቹስ?”
“እምልሽ ከሁሉም ጋ ጥሩ ቅርበት ነው ያለኝ፣ ግን ከነሱ ጋ በደንብ ቅርብ ነኝ”
ለአራተኛ ግዜ ሶፍት ሊስብ እጁን ዘረጋ፣ ሳጅን ዳሂላ ቀደመችው እና ሶፍቱን አንስታ ከስር አስቀመጠችው።
አንዱአለም እጁ እንደተንከረፈፈ ቀረ!

“ከልጆቹ ምስክርነት እንዳወቅሁት መኪናውን ባስቆሙህ ፍጥነት አይናቸውን እንዲይዙ ስትነግራቸው እንደነበር ነው።” ጥያቄውን ቀጠለች!
“አዎ ምክንያቱም ጭንቅላቴ ላይ ተደግኖ ለልጆቹ እንዳስተላልፍ የተነገረኝ መልክት እሱ ስለነበር ነው።”
“ታጣቂዎቹ ጭምብል አለበሱም ነበር? ለምን ልጆቹ አይናቸውን እንዲይዙ ፈለጉ?”
“እህህ አዎ አይ ለብሰዋል ግን ያው እኔንጃ እንዳይለዩ ሰግተው ይሆን?”
“እንዳይለዩ ከሰጉ የአካባቢው ሰዎች ናቸው ማለት ነው። “
“አላላ ውቅም እኔ”
“አንተን አይንህን አላስጨፈኑህም አይደል? ቁመናቸውን አይተህ የምታውቃቸው አልመሰሉህም?”
“አልዋሽሽም ሳጅን ለነፍሴ ፈርቼ ነበር በዛ ላይ ሁሉም ነገር ፈጣጠነብኝ ስለዚህ ልብ አላልኩም”
“እዚህ ወንጀል ላይ እጅህ የለበትም አቶ አንዱአለም?”
“ኧረ?” ቁጭ ብድግ አለ “በፍፁም ውለታቸው ይሄ አይደለም ለቤተሰቦቿ”
“እሺ፣ መኪናህ ላልተወሰኑ ቀናት እኛው ጋ ትቆያለች አንተ መሄድ ትችላለህ በምንፈልግህ ሰአት ትመጣለህ!”

“እእሺ!”
/አንዱ አለም በቅሬታ ተነስቶ ወጣ/
*

ሳጅን ዳሂላ የነአንዱአለምን ቤት በጥንቃቄ እየተመለከተች ነው። ሊሊ የሳጅንን እንቅስቃሴ እያየች ቁጭ ብላለች። አበባ ታጉረመርማለች
“ምን አልሺኝ ወይዘሮ አበባ?” አለች ድንገት ሳጅን ዳሂላ
አበባ እንደህፃን ልጅ አንገቷን ደፋች
“አንዱአለም ቤት ውስጥ ስላለው ባህሪ ልትነግሪኝ ትችያለሽ?”
“ከወንጀሉ ጋ ምን ያያይዘዋል እሱ?”
/አለች አበባ በቁጣ/

“እኔ ልነግርሽ እችላለሁ” አለች ሊሊ

አበባ አይን አይኗን በስጋት አየቻት
“ቀጥይ ሊሊ”
“አንዱአለም ለእኔ እንጀራ አባቴ ነው። እንጀራ አባቴ ስለሆነ አይደለም ግን ለእኔና ለእናቴ ጥሩ ባህሪ የለውም። ለውጪ ሰው ግን ሟች ነው። የቤት ቀጋ የውጪ አልጋ የሚባል አይነቱ ነው።

“ሊሊ?!”
አበባ በቁጣ አፈጠጠችባት

“ግን ይሄን ወንጀል አሰካክቶ ይሰራል ወይ ካልሺኝ አይመስለኝም ነው። ምክንያቱም ደደብ ነው፣ በድድብናው ነው ሰው የሚጎዳው!”

ሳጅን ዳሂላ
ሁለቱንም አመስግና ስትወጣ አንዱአለም ላይ ያላት ጥርጣሬ በግማሽ ቀንሶ ነበር።

*
አለማየሁ ከፖሊስ ጣቢያ መልስ በጭንቀት ተቀምጧል። ለቁጥር በሚያዳግት መልኩ ባለፉት ጥቂት ቀናቶች ውስጥ ፖሊስ ጣቢያ ተመላልሷል። ግን ምንም ነገር የለም። የአንዱአለምም ታክሲ እንደተመለሰለት አይቷል።

“ጭራሽ ሀሳባቸውን ከአንዱአለም ተብዬ ላይ ያነሱ ይመስላሉ” አለች ሀረግ ለቀናት ባልተኙ አይኖቿ ሰማይ ምድሩ የዞረበትን ባሏን እየተመለከተች።

ታውቃለች ካልበረታች ልጇን ብቻ ሳይሆን ባሏንም እንደምታጣ። ልባቸውን ነው የተነጠቁት አሁን ቀስ ብላ በዴዚ ልብ ፈንታ የሷን ልብ ለብርታትነት ካልሰጠችው አለማየሁ ይደክማል! አጠገቡ ሄዳ ቁጭ ብላ እጆቹን ይዛ “አሌክስ?! ተመልከተኝ?!” አለችው ቁፍጥን ባለ ድምፅ።
አሌክስ እምባ ባዘሉ አይኖቹ ተመለከታት “እናገኛታለን!” እጆቹን የሷ በማይመስል ሀይል ጭምቅ አደረገችው።
እርገጠኝነቷ ትንሽ ረፍት ሰጠው። ታፋዋ ላይ ደገፍ ብሎ ለቀናት ያመቀውን ትንፋሽ ተነፈሰ!

*
ዴዚ ከታገተች 15 ቀን ሆናት፣ አንዱ አለም ክትትሉ ከእሱ ላይ እስኪነሳ ድረስ ገንዘብ መጠየቁንም መደራደሩንም አልፈለገም። አለማየሁ አስሙ ልብ ህመሙን ስላስነሳበት ሆስፒታል መተኛት ግድ ሆነበት፣ ያን ግዜ ነበር ሀረግ የአለማየሁን ኢንሄለር ከቤት ልታመጣለት ሄዳ መሳቢያውን ስትከፍት የዴዚን የምስጋና ቀን ደብዳቤ ያገኘችው።

ግር ብሏት ከፍታ ማንበብ ጀመረች “ አሌክስዬ በአለም ሁሉ ቢፈለግ የአንተ አይነት አባት የለም፡ እድለኛ ነኝ በጣም፣ እስከዛሬ ለሆንክልኝ እና ወደፊትም ለምትሆንልኝ ሁሉ አመሰግናለሁ እወድሀለሁ የኔ አባት”

ሀረግ ብዥዥ አለባት

…
ይቀጥላል…

Brown Empire

27 Dec, 06:58


የዱር አበቦች
ክፍል 7
ዴዚ

ዴዚ የ13 አመት ታዳጊ ልጅ ብትሆንም የሰውነቷ ቅርፅ የ18 አመት ኮረዳ ያስመስላታል። ትላልቅ ወንዶች ፊቷን አይተው ልጅነቷን መረዳት ቢችሉም ስትዞር ልጅነቷን ይረሱታል።
በባህሪዋ ፈጣን እና ቀልጣፋ የምትባል ስትሆን በምትገመተው እድሜ ክልልም ለመገኘት ስትል እድሜዋን የምትዋሽ ነች። መሞካሸትን እና አይን ውስጥ መግባት የሚያስደስታት አይነት ለቤተሰቧ ብቸኛ ልጅ ነች።

ከምንም በላይ ደግሞ በአንዱአለም መወደድ ያስደስታታል። አንዱአለም ወደትምህርት ቤት የሚያመላልሳት የሰርቪሳቸው ሹፌር ሲሆን ከሌሎች ተማሪዎች በተለየ ይንከባከባታል፣ የተማሪዎች ወላጆች በገራገርነቱ እና በሰላምተኝነቱ ያውቁታል። ልጆቹንም ቢሆን አቅፎ ብድግ በማድረግ፣ በመኮርኮር እና በመላፋት ያለውን ቅርበት ለማሳየት ይሞክራል።

ከትምህርት ቤት ወደቤት ሲሄዱ ምንግዜም ቆመው የሚፈልጉትን የሚገዙባት አንዲት የሽማግሌ ሱቅ አለች። እዛ አካባቢ ከሷ ሱቅ በስተቀር ሌላ የለም። በዛም ምክንያት ተማሪዎች የኪስ ገንዘባቸውን ለቺፕስ እና ሌሎች ጣፋጭ ነገሮች አባባ ሱቅ ያውሉታል፣ አልፎ አልፎ አንዱአለም የነሸጠው ግዜም ለሁሉም በእሱ ወጪ ይገዛላቸዋል።

ብዙ ግዜ ለዴዚ በራሱ ወጪ የሚገዛላት ሲሆን ከሌሎች ተማሪዎችም፣ ከእኩዮቿም በተለየ ይንከባከባታል። ብዙ ግዜ ከጀርባዋ ወረድ ብሎ ባለ ቦታ ላይ እንደጏደኛ ደገፍ እያደረገ በመያዝ ወደሰውነቱ እያቀረበ ይታከካታል፣ ትንሽ ጣቱም ሁልግዜ ጎኗን በመኮርኮር አታርፍም። አንዱአለም ከግዜ ብዛት የገባው ነገር ይሄን ባህሪውን ገዝቶ ለረጅም ግዜ ራሱን መቋቋም እንደማይችል ነው። ያልገባው ነገር ዴዚ እንደስከዛሬዎቹ ልጆች ፐርፌክት ቪክትም መሆን አለመቻሏ ነው።
*

አለማየሁ እና ሀረግ ዴዚ አንድ ልጃቸው ናት። ለእነሱ እንደልባቸው ነች። በእሷ ነው ደም የሚረጩት፣ የሚያፈቅሩት፣ የሚደሰቱት። በተለይ የአለማየሁ ይለያል። ለልጁ የሚያደርገውን እንደቤተክርስቲያን አስራት ማንም አይቶት እንዲያመሰግነው አያደርገውም። በዝግታ በየእለቱ ዪኒፎርሟን አጥቦ፣ ተኩሶ፣ ጫማዋን ጠርጎ፣ ፒጃማዋን አስተካክሎ ፀጉሯን አሲይዞ፣ አስጠንቶ ፣ አዋርቶ ፣ክፍሏን አፅድቶ ነው የያዛት። ሀረግ በበኩሏ ልጇን የባሏን ያህል ብትወዳትም ዴዚ ለሰው ግድ የማይሰጣት፣ ሲበዛ ትኩረት ወዳጅ እና ራስወዳድ ልጅ እየፈጠሩ እንደሆነ ማወቅ አላቃታትም።
በተደጋጋሚ አለማየሁን አንዳንድ ነገሮች በራሷ እንድታደርግ እንዲተውላት ብትጠይቀውም ሁለት የት ወደቀ ብለው ከማይጠይቁ እናትና አባት የመጣው አለማየሁ ለልጁ እሱ ጠይቆም ሳይጠይቅም እንደልጅ ሳይደረግለት ያደገውን በሙሉ ከመጠን ባለፈ መልኩ ለልጁ በማድረጉ ክፋቱ አልታየውም።

ሁለቱም በስራቸው ደህና ቦታ የደረሱ የመንግስት ተቀጣሪዎች ሲሆኑ አንፈላሶ የሚያኖር ጥሩ ሀብት ያካበቱ ናቸው። እርስ በርስ ያላቸው ፍቅር ከግዜ በኋላ ቢደበዝዝም የፍቅራቸው መገላለጫ እና የቤታቸው ሙቀት ዴዚ ነች። በእሷ ውስጥ ይዋደዳሉ። በእሷ ውስጥ ይኖራሉ። የሚጠበቅባቸውን በየእለቱ ያደርጋሉ።

እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ አለማየሁ ልጁን ትምህርት ቤት የሚያመላልሰው ራሱ ነበር። ከአለፈው አመት ጀምሮ ግን ዴዚ ሰባተኛ ክፍል ስትገባ ከጓደኞቿ ጋር በሰርቪስ መመላለስ እንደምትፈልግ ተናግራ በቃሏ ስለፀናች አባት ቅር ቢለውም እናት በመፍቀዷ አንዷለም ጋ ሰርቪስ ጀመረች።

ለትንሽ ግዜ አባት ቢሰጋም በቆይታ ግን የአንዱአለምን ገራገርነት እና ለልጆች ያለውን ፍቅር ሲያይ ተረጋጋ። እንደውም አልፎ አልፎ ቤታቸው እየጠሩ ይጋብዙትና ጉርሻ ገንዘብ ከደሞዙ ላይ ይጨምሩለት ጀመር። የአለማየሁ ልብስ እና ጫማም ሳይቀር ይሰጠው ጀመር።

አንዱአለም ግን ቤታቸው ገብቶ በወጣ ቁጥር የሀብታቸው መጠን እና ከእነሱ በተጨማሪ ሊያገኘው የሚችለውን ገንዘብ ማሰላሰል ጀመረ። ሀብታም ከመሆናቸው ባለፈ ግን ሁለቱም የመንግስት ተቀጣሪ እንጂ ምን እንደሚሰሩ ማወቅ አልቻለም። ብዙ ሰውም አያውቅም። በተለያየ ግዜ ከዴዚም ለማወጣጣት ቢሞክርም ቤተሰቦቿ ገንዘብ ከማምጣት ያለፈ እንዴት እንደሚያመጡት ለማወቅ ግድ አልነበራትም።
በዚህ ሰአት የሚያሳስባት ስታድጊ አገባሻለሁ የሚለው የአንዱአለም ቃል ነበር። ህልሟ 18 አመት ነበር።

*
አለማየሁ ሻይ የጠጣበትን ብርጭቆ እያጠበ ነው። ሀረግ ቦርሳዋን እና ላፕቶፗን አሰናድታ ልትወጣ እንዳለች በቁሟ ቡናዋን እየጠጣች ነው። ዴዚ አፏውስጥ የጎረሰችውን ምግብ በችኮላ ውጣ ለአንዱአለም ክላክስ ተጣድፋ ቻው ሊላት የቆመውን የአባቷን እቅፍ ትታ በሩጫ ወደታክሲዋ ሮጠች። የባሏን ቅር መሰኘት ልብ ያለችው ሀረግ በልጇ ፈንታ ሄዳ አቅፋ እየሳመችው፣ ልታሳስቀው ሞከረች።

ሁለቱም ወደየስራቸው ሊወጡ ሲሉ ሀረግ የዴዚን አሳይመንት ጠረጴዛው ላይ አየች።
“አዪ እቺ ልጅ ስትቸኩል አሳይመንቷን ሳትይዝ” አለችና እግረመንገዷን ልታቀብላት ይዛው ወደ መኪናዋ ገባች።

መንገድ እንደጀመረችም ከአሳይመንቷ ውስጥ በፖስታ የታሸገ ወረቀት ዱብ አለ። ሀረግ ተንጠራርታ አንስታ ስታየው ከውጪ ምንም የተፃፈበት ነገር አልነበረም። ዳሽቦርዱ ላይ ወርወር አድርጋው መንገዷን ቀጠለች።
*

ዴዚ ከእናቷ የተቀበለችው አሳይመንት ውስጥ የአስቀመጠችውን ፖስታ ብትፈልግ አጣችው! የዛን ለት ተጨናንቃ ወይ እናቴ አግኝታዋለች ወይ የምግብ ጠረጴዛው ላይ ትቼዋለሁ እያለች ስትብሰለሰል ዋለች። ትምህርትቤታቸው የምስጋና ቀን ሲከበር ለምታመሰግነው አንዱአለም የፃፈችው ደብዳቤ ነበር።

*
ሀረግ ቢሮ ሆና የልጇ ፖስታ ትዝ ብሏት ከመኪና ውስጥ አምጥታ ከፈተችው..
“ከሌሎች በተለየ ስለምትንከባከበኝ አመሰግናለሁ፣ እወድሀለሁ።”

ከD ለA ይላል።

ሀረግ ልጇ ከእሷ አስበልጣ አለማየሁን ስለምትወደው ትንሽ ቅናት ቢጤ ቢሰማትም አንድ ስትሪክት ወላጅ ስለሚያስፈልግ ዴዚ ላይ ቆፍጠን በማለቷ አለመመረጧን አልጠላችውም።
*

እረፍት ሰአት ላይ ዴዚ በረንዳ ላይ ብቻዋን የቆመችውን ሊሊን ከታች ሆና ወደላይ ታያታለች፣ ከአንዱአለም ጋ አንድ ቤት ውስጥ መኖሯን ስታስብ የማታውቀው የቅናት መንፈስ ከመቅፅፈት ተጠናወታት። አንዱአለም በሚነግራት የተጋነኑ ውሸቶች ምክንያት ጨምሮ ሊሊን ከመቼውም በላይ ጠላቻት።

ሊሊ ለሰላምታ እጇን አውለበለበችላት!

ዴዚ ገላምጣት ጥላት ሄደች።

*
የወደቤት ሰአት ደርሶ ዴዚ ሰርቪሷ ውስጥ ገባች። አንዱአለም እንደወትሮው ደስተኛ አልነበረም፣ ፊቱ በላብ ወርዝቷል፣ የግምባሩ ጅማቶች ተወጣጥረዋል። ቶሎ ቶሎ ይተነፍሳል። ተማሪዎቹን እያከላፈተ በፍጥነት አስገብቶ ዘጋው። ዴዚ እንደሌላው ግዜ በሞቅታ ሰላም ሳይላት ስለቀረ ቅር አላት እምባ እምባ አላት። አኩርፋ ግምባሯን ደፍታ እንደተኛች አባባ ሱቅ ጋ ደረሱ።

እዛ አካባቢ ጋራጅ እና በቆርቆሮ የተከበቡ ሰፋፊ የኮንስትራሽን ቦታዎች ባለፈ የአባባ ሱቅ ብቻ ነው ያለው። ዴዚ በዛ ስታልፍ ሁልግዜ ከሚገርማት ነገር ውስጥ አንዱ እዛ አካባቢ ያሉ ሰዎች በምን ታክሲ እንደሚሄዱ ነው። ምክንያቱም ከላይም ከታችም ሞልቶ የሚያልፉ ታክሲዎች እንጂ መሀል ላይ ቆም ብሎ የሚጭን የለም። በአጠቃላይ በጭርታ የተላበሰ አስፈሪ ሰፈር ነው።

ዴዚ በድንገት በተኛችበት ፊቷን ተሸፍና አፏ ታፍኖ ከመኪና ላይ ተወሰደች።
*

አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ በታክሲው ልጆች ወላጆች ሁከት ተሞልቷል! አንዱአለም እየተርበተበተ ቆሟል! የሚደማመጥ የለም ሁሉም እኩል ይጮሀል።

Brown Empire

23 Dec, 07:52


Channel photo updated

Brown Empire

20 Dec, 11:10


ነይ ፅግዬ እዚህ ሳፋው መሀል ቁሚ አይዞሽ አትፍሪኝ እኔ እህትሽ ነኝ እሺ!

ፅጌ ራቁቷን እያፈረች ሳፋው መሀል ቆመች!

“ውይ እህቴን የወር አበባ ጀምሮሻል? ወይስ?” ስምየለሽ ራሷን ተጠራጠረች።

“አዎን ጀምሮኛል”

“ምነው በልጅነትሽ! ምን አስቸኮለው? በይ እሱ አካባቢ ከራስሽ ውጪ ማንም ሊነካሽ አይገባም እሺ ፅግዬ፣ አፍሽን፣ መቀመጫሽን፣ ጡትሽን ማንም ቢሆን እንዲነካሽ እንዳታደርጊ እሺ! ደግሞ ጠንካራ ሁኚ እሺ?! የድሀ ልጅ ዘመዱ የገዛ ጥንካሬው ብቻ ነው፣ ቀልጣፋም ሁኚ በምትችይው ነገር የሚጠቅምሽን ሰው ለማገዝ ሞክሪ፣ ሰው ነው ለሰው መድሀኒቱም በሽታውም!”

ፅጌ ሙቁ ውሀ በገላዋ ሲፈስ ደስስ አላት።

“የናትሽን ስልክ አታውቂም?”
“ስልክ የላትም!”

“አትዋሽኝ ፅግዬ እዚህ ብቻሽን በልጅነትሽ ምነው ቤተሰብ ይሻላል ከምንም!”

“አይሻልም!”

ስም የለሽ የፅጌን እድፉም እግሮች ከመፈተግ ቆጠብ ብላ ፊቷን አስተዋለቻት!

የፅጌ አይን ጥግ ላይ የወደቀ አረንጏዴ መጫወቻ እያስተዋለ ነበር።

*
ከአስራ አንድ አመት በኋላ

ቀለም ቡና አፍልታ ከዘቢብ ጋ እየጠጡ ነው። ቀለም የዘቢብ ነገር የቁም ቅዠቷ ነው። ሰዉ በዚህ ልክ ከነበረበት የአእምሮ ጤና ሲፋለስ አይታ አታውቅም! አበደ፣ ሰይጣን ተጠናወተው ሲባል ሰምታለች የዘቡ ግን ያ እንዳልሆነ ታውቃለች። አይኗ ስር ነው እንደማብሪያ ማጥፊያ ቀጭ ብላ የተቀየረችው። አይታለች ናፍቆት፣ ፀፀት፣ የጥፋተኝነት እና የአቅመቢስነት ስሜት ጤናማ ጏደኛዋን አእምሮ ስውር ሲያደርጋት፣ ባታይ የምታምነው አይነት አልነበረም። ለወሬ የማይመች አይነት ነው። ባታይ እሷም እንደሌላ ጎረቤት ትሸሽ ነበር። ፓስተር ሞላንም ይቅር ለማለት ሰባት ድፍን አመታት ወስደውባታል። ግዜን ምን ያደርጉታል?! ጌታ ነውና እንዳዘዘ ነው። አንድ እለት ስትነሳ ልቧ ውስጥ ምህረትን አገኘች። ይቅር አለችው። አንዳንድ በደል ተበዳዩ ብቻ የሚያስቀምጠው ቁርሾ ነው።

“አወቅኩት እኮ ነጠላዬን ምን እንደነካው? ቀለምዬ”
አለች ዘቢብ ድንገት

“የቱን ነጠላ ዘቡ?”

“ምነው ቆንጥሬ ሳጥበው ምን ሆኖ ስትይኝ አልነበር? “

ቀለም ለማስታወስ ከሻሿ ያመለጡ ሽበት ፀጉሮቿን ደባበሰች..
“መቼ ዘቡ? “

“ቅድም ነዋ”

የዘቡ ቅድም ከአስራአንድ አመት በፊት እንደሆነ ቀለም አሁን አሁን እየገባት መጥቷል
“እሺ ምን ሆነ ነው ያልሺኝ?”

“እየውልሽ ፅግዬ እኮ ናት ፅጉ፣ ውይ ፅጉ አትበይኝ ብላኛላች ለካ አባትዋ ስለሚላት ጠልታው እኮ ነው”

“እሱንማ ነግረሺኝ ዘቡ”

ዘቢብ ብዥ የሚለውን የሆሳእናን ሀሩር ሊያረጁ በጀመሩ አይኖቿ እያየች
“ፅጌረዳዬ ናት ለካ ያን የዛገ ወጥመድ ስትጎትት በቆየችበት እጇ አቅፋ ስትስመኝ ያስነካችብኝ፣ ባውቅ ኖሮ መች አጥበው ነበር”

ቀለም ከንፈሯን መጥጣ በሀዘኔታ አየቻት።

*
ከአስራ አንድ አመት በፊት

ፅጌ የወደቀውን መጫወቻ እያየች በዝምታ ከቆየች በኋላ

“ይናፍቅሻል? ልጅሽ?” ፀጉሯን ልትሰራ ስምየለሽ ስር እንደተቀመጠች ጠየቀች

ስምየለሽ የፅጌ ብሩህነት እየገረማት “ህም! ናፍቆቱ ህመም ሆኖ ያመኛል ብል ይቀላል ፅግዬ፣ ልጅ በሙሉ አይኔ የማልመለከተው ለልጄ ያልሆንኩትን ለሌላ መሆን ስለማልፈለግ ነው። አንቺስ ትናፍቅሻለች? እናትሽ?”

“ብዙ! ብዙ ነው የምትናፍቀኝ፣ ግንንን … ወደእሷ አልመለስም እሺ?! ማደጎውን አስመዝግቢኝ?!”

“አሁንማ እኔም ተመለሺ አልልሽም፣ እሷው ፈልጋሽ ከመጣች እሰየው፤ ካልሆነ ግን እዛ አውሬ ጋ አትመለሺም! ጉዲፈቻውን እስኪ ትግስት ስትመጣ እንጠይቃታለን እሷ ነች ፈረንጆቹ ጋ ፅዳት የምትሰራው።”

ፅጌ በእሺታ ጭንቅላቷን ወዘወዘች።

*
ሮዝ ማታ አልጋዋ ላይ ጋለል እንዳለች በፍርሀት ስልኳን አንስታ ከኢቢኤስ ያገኘችውን ስልክ ቁጥር አውጥታ ደወለች፣ አንዴም ጠርቶ ሳይጨርስ ስልኩ በፍጥነት ተነሳ!

“ፅግዬ ነሽ?”
ሮዝ ልቧ ትርክከ‍እ አለ!
“እማ.. እማዬ?!”
“ፅገሬዳዬ?! እልልልልልልልልል” በዛኛው በኩል ስልኩ በጩኸት ተናጋ!

“ማነው ቆይ ላናግር ስጪኝ ዘቡ፣ ሞላ ይሆናል ቆይ ስጪኝ?!”

ስልኩን ቀለም ትቀበላታለች

“ሄሎ ሞላ?”
ሮዝ በደስታ እና ባለማመን መሀል ሆና እያነባች “ፅጌ ነኝ ቀለም” ሳግ አፈናት

የቀለም እልልታ ቤቱን አናወጠው፣ ዘቢብ ስልኩን ከቀለም ነጥቃ ተቀብላ መዘመር ጀመረች

“ኧረረረረረ ስንቱ ስንቱ ስንቱ ስንቱ ታለፈ! እየሱስ እየቀደመመመመ!”

ሮዝ እያለቀሰች አብራ ልትዘምር ሞከረች!

ይቀጥላል…

[ስም የለሽ - ከየመሀል ልጅ “መጫወቻው” ከሀርካሂንኬኒኒ “ብርቱቀይ ናፍቆት” ታሪኮች ላይ የተወሰደች ካራክተር ስትሆን በሁለቱም ታሪክ ላይ ስም ያልተሰጣት ስለነበረች እዚህ ላይ መስጠቱ ስላልተስማማኝ በስም የለሽ እንድትቀጥል ተደርጋለች።]

Brown Empire

20 Dec, 11:10


የዱር አበቦች
ክፍል 6
ሊሊx ሮዝ

ሮዝ ባር ውስጥ ቁጭ ብላለች። ከሌላውግዜ በተለየ ዘነጥ ለማለት ሞክራለች። ሁለት የምግብ ሰሀኖች ከፊቷ ያለው ጠረምጴዛ ላይ ቁጭ ብለዋል? የእሷ ሰሀን ብዙ አልተነካም ሌላኛው ባዶ ሆኗል። አንዷለም ከመታጠቢያ ቤት ወጥቶ እርጥብ እጁን ፀጉሩ ላይ እየጠረገ ከሮዝ ፊት ለፊት እግሩን አንፈራጥጦ ተቀመጠ።

ሮዝ ሳቅ ብላ ተቀበለችው፣ እግሯ ድረስ መጥቶ ያጣበባትን አንድ እግሩን በእግሯ ገፍታ ወደ ህጋዊ ቦታው መለሰችው።

“ይሄ ነገር ደስ አይልሽም አይደል?” አለ መላ ፊቱ በደስታ እንደፈካ

“እግር የሰው ቦታ ድረስ ከፍቶ መቀመጥ ምኑ ደስ ይላል?” አይኗን አይኑ ላይ ለስለስ አድርጋ እንደተከለች ሰላሳ ሁለት ጥርሷን አሳየችው።

የተናገረችውን እውነት በማር እይታዋ እና ፈገግታዋ አደባብሳ አስዋጠችው። አንዱአለም እግሩን እየሰበሰበ ቢሉን አየ
“እንዴ? ይሄ ሁሉ ከፈልሽ ለዚች ምግብ እና መጠጥ?” የሚለውን ሳይሰማ ፊቱን ብቻ ከሩቅ ላየው ሰው የአያቱን ሞት የተረዳ ነው የሚመስለው። “ዝምብለሽ እኮ ነው እዛው ጃምቦአችንን..”

“ኔክስት ታይም” ብላ አቋርጣው ፈገግታዋን ለታመመ ኢጎው ለገሰችው።
“አንድ ሰሞኑን የምትለቀቅ ገንዘብ አለችኝ ይዤሽ ከከተማ ነው የምወጣው ኩሹ ቆንጅዬ!”

“ባይሆን እሱ ጥሩ ፕላን ይመስላል!”
አለች ፈገግ እንዳለች።
“እኔ የምለው ዛሬ መቼም አብረን ነን አይደል?” አለ በቆርፋዳ እጁ ታፋዋን በጠረቤዛ ስር ጨመቅ እያደረገ።

ሮዝ ፊቷ ላይ መረበሽ አይታይም ጥርሷን ብቻ እንደገጠመች “ይሄን ጥያቄ ዳግመኛ ስታነሳ ከዛች ሚስትህ ጋ ተለያይተህ መሆን እንዳለብህ ነግሬህ ነበር“

“ኧረ ኩሹ ተይ ነግሬሽ! አልጋ ለይቼ እንደምኖር እያወቅሽ?”

ያዘነችለት መሰለች!

የአንዱ አለም ስልክ ጠርቶ ተነስቶ ሊሄድ ሲል ሮዝ በእጇ ያዝ አድርጋዉ እጇን ልትጣብ ተነሳች። አንድ ኤርፖዷን ቴብሉ ላይ ትታ፣ አንድኛውን ጆሮዋ ላይ እንደተወች ስልኳን ላይቭ ሊስን ላይ አድርጋ ወደመታጠቢያ ክፍል ሄደች።

“አንተ ምንድን ነው አስር ግዜ የምደውልልኝ?” አንዱአለም አንባረቀ!
“ነገርኩህ አይደል እንዴ ዛሬ አልችልም ብዬ፣ አስር ግዜ ዴዚ ዴዚ አትበል ደግሞ! (አንሾካሾከ) ስሟን አትጥራራራ! ልጅቷ በል አላልኩህም?! ጫፍ የደረሰ ነገር ይበላሽና ውርድ ከራሴ! ምግብ እና መኝታ እንዳትነሷት ደግሞ! ጭረት እንዳይታይባት… ኧ? አልበላም አለች? በጉልበትህ እየዳህክም ቢሆን አጫውተህ መግባት ነግሬያለሁ! ትንሿ አበባ መጠውለግ የለባትም። ስማ ስማ ስማ ደግሞ ተሳስተክ ስሜን እሷ ፊት እንዳጠራ!”

ሮዝ በመላ ሰዉነቷ የሚላወሰውን ብርክ መቆጣጠር አቃታት።
ወደቦታዋ ስትመለስ ብሩህ ለሆነ ሰው ልከ እንዳልነበረች ታስታውቅ ነበር። አንዱአለም ግን ለዛ ያልታደለ ነበርና ልብ ሳይል ቀረ።

ከባሩ ወጥተው በሮዝ መኪና መንገድ ሲጀምሩ አንድ ሴት በፍጥነት ወደመኪናዋ ገብታ ተከተለቻቸው።

*

ዩኒቨርሲቲ በር ላይ ሮዝ ቆማ ሊሊን እየጠበቀች ነው። ከግቢው ውስጥ በሳምንት ውስጥ ጉስቁል ያለችው ሊሊ በጀርባዋ ከያዘችው ቦርሳ በተጨማሪ ይዛ የሄደችው ሻንጣ ትታ በችኮላ ስትመጣ አየቻት።

ሮዝ ሁኔታዋ ልክ እንዳልሆነ ገብቷት አጠገቧ እንደደረሰች “ሊሊ ምነው ደህና አይደለሽም እንዴ?” አለቻት..
ሊሊ ሰላምታዋንም ጥያቄዋንም ችላ ብላ መኪና ውስጥ ኋላ ወንበር ገብታ ተኛች።

ሮዝ ግራ እንደገባት ወደመኪናዋ ተመልሳ ገባች።

*
ሊሊ ተጣጥባ እና ልብስ ቀይራ ያለቀሰችበት አይኗ እንደቀላ ቁጭ ብላለች።

ሮዝ ልታፅናናት የቻለችውን እየሞከረች ነው “በቃ ጦስሽን ይዞ ይሂድ፣ ሌላ አማራጭ እንፈልጋለን! እዚህ እንደሆነ ሄደሽ የምትከሺበት ሲስተምም የለም ትርፉ በብስጭት የሚመጣ በሽታ ብቻ ነው።”

“አንድ ያለኝ ተስፋዬን ነው የተነጠቅኩት እኮ ሮዝ! እንዴት አንዲት ሀገር በዚህ ልክ ለዜጋዎቿ ግዴየለሽ ትሆናለች? የኛ ደህነንት እንዴት አያሳስባትም? በፈተና ሰበብ ከቤት ወጥተን ሄደን በዚህ ልክ ተጉላልተን መምጣት ነበረብን? በር የሌለው ዶርም ውስጥ እንዴት እንድናድር ይደረጋል? መዘረፉን እሺ የቀራቸው የለም ግን ብንደፈርስ? እንዴት ሴት ዶርም ወንድ ሲገባ ዝም ይባላል? ጥሩ እንቅልፍ አግኝተን መፈተን ሲገባን ጭራሽ ከአሁን አሁን ማን መጣ እያልን በር በሌለው ክፍል ስንጠባበቅ እንደር?

በዛ ላይ የምንበላውን ከሚነጥቁ ዱርዬዎች እንኳ የሚያስጥል ሴኪዩሪቲ የለ! በባዶ ሆዳችን ሳንተኛ አድረን ፈተና እንድንፈተን ይጠብቁናል? ውጤትም እንድናመጣ?
በጣም በዛ! ሀገሩ ሁሉ እንዴት ከሊቅ እስኪደቂቅ በአይመለከተኝም በምናገባኝ የተሞላ ይሆናል?”
በሹራቧ እጄታ እምባዋን ከፊቷ ሞዠቀችው

“አንድ ያለኝ ማምለጫዬ ትምህርቴ ነበር፣ አንድ ያለኝ ፍትሄ፣ ነፃነቴ! እሱንም ተነጠቅኩኝ። እንደዛ በችግር መሀል ፀንቼ የተማርኩት ፈተናዬን ሳልጨርስ ሰአቱ ሳይሞላ መቆም ሰለሰለቸው ብቻ በማናለብኝ ወረቀቴን መሀይም ልነጠቅ አልነበረም። “

ሮዝ የምትለው ጠፍቷት በዝምታ ታዳምጣታለች!

“በቃ ጎዳና መውጣቴ ነው።”
“ተይ እንዴ? እኔ የትሄጄ ነው ጎዳና የምትወድቂው? እንደሱ አትበይ! ፌሊየር የህይወታችን አንዱ ክፍል ነው። በዚህ ሳይሆን በሌላ እንሞክራለን ደግሞ!”

ሊሊ በቀላሉ የምትፅናና አትመስልም ረጅም ግዜ የገዛችው ንዴት እና እልኋ ገንፍሏል።

*
ከአስራ አንድ አመት በፊት

ፅጌ ከሶስቱ ፅዳቶች ጋ ምግብ ቤት ቁጭ ብላለች የአንዷን የፅዳት ጋውን ለብሳለች፣ አንገቷንና ራሷንም በሻርፕ ጠምልለዋታል።

“አቤት የዘንድሮ ግፍ ግን ያልቅ ይሆን? አሁን እቺን አንድ ፍሬ ልጅ መድፈር?” አለች ትግስት የተባለችው

ፅጌ ሻዩዋን ልትጠጣ ካለችበት ቀና ብላ አየቻት።

“ማን ተደፈረች ብሎሽ ነው እርግጠኛ የሆንሺው? ይሄኔ ቤት አስቸግራ ወጥታ ነው? እኔምልሽ አንቺ ልጅ የእጅ አመል አለብሽ እንዴ?” አቦ ቀጠለች።

ሶስተኛዋ ሴት በሁለቱ ጏደኞቿ ጥያቄዎች ተሰላችታ
“ኧረ ስለፈጠረሽ አቦ እንደዚህ ልጅ አይጠየቅም እስኪ ትብላ ትጨርስ መጀመሪያ እርቧታል እኮ!”

“የት ነው ቤትሽ? ትንሿ?”

“ቤት የለኝም መንገድ ነው የማድረው” ፅጌ መለሰች

“እንዴ እናትሽስ?”

“እእ ..እናቴ?”

*
ሆሳእና
ከአስራ አንድ አመት በኋላ

ዘቢብ የቤቱ ስልክ የሚቀመጥበት አጠገብ ተቀምጣ ደጅ ደጁን ታያለች! አስራ አንዱ አመታቶች በሁለት ተባዝተው አስገርጅፈዋታል።
ውጪው ጠራራ ነው። ፀሀዩ እንቅስቃሴዎቹን ሁሉ በድሮ ካሜር የተቀረፁ ምስሎች ያስመስላቸዋል።

“ስማ ሞላዬ ስልኩን አንሳው እንጂ ልጄ ደወለች እኮ አቀብለኝ!”

ፓስተር ሞላ አጠገቧ የተቀመጠውን ያልጠራውን ስልክ ብድግ አድርጎ ሰጣት።

ዘቢብ የጆሮውን ማስደገፊያ ሳም ሳም እያደረገች
“እሰይ ልጄ የምነግርሽ ነበረኝ እንኳን ደወልሽ፣ አዎ እወድሻለሁ! እኔም ልጄ!
እኔም እወድሻለሁ!
እኔም በጣም እወድሻለሁ!”

ቀለሟ ወደቤታቸው ሰላም እያለች ገባች፣ ፓስተር ሞላ በትንሽ ሻንጣ ያዘጋጀውን ልብስ ይዞ ብድግ አለ። “በይ ቀለሟ አደራ! ቢበዛ 2 ሳምንት ነው የምቆየው ፣ ምናልባት ቶሎ ከተገኘች ቶሎ ባትመለስ ጥሩ ነው ስላሉ ነው እሱንም፣ አደራ ቀለሟ ዘቢቤን አደራ!” ብሎ የዘቢብን አይበሉባ ስሞ ከቤት ወጣ።

“ቸር ወሬ ያሰማን የዘቢብ አምላክ ልጇን ያሳያት!” መረቀች ቀለሟ።


*
ከአስራ አንድ አመት በፊት

ፅጌ ስም የለሽ ቤት ተቀምጣ በባሊ የሚበረዘውን ፍል ውሀ ታያለች። ቤቱ ከውስጥ በመቀርቀሪያ ተዘግቷል

Brown Empire

19 Dec, 05:19


የዱር አበቦች

ክፍል 5
ሊሊ x ሮዝ

*

ሮዝ አፓርትመንት ውስጥ ሊሊ እግሯን ሰብስባ ሶፋ ላይ እያጠናች ተቀምጣለች። በቀናቶች ውስጥ 12ኛ ክፍል ፈተና ተፈታኝ ስለሆነች ዝግጅት ላይ ነች፣ የበረከት ደጀኔ መዝሙር በዝግታ በአፓርትመንቱ ባዶ ቦታ ላይ ሳልሳ ይደንሳል…

“በማልፍበት መንገድ በህይወት ጎዳና
በየለት ውሎዬ ሳልፍ በጎንበስ ቀና
ሊገቡኝ አልቻሉም ለምን? ከዛስ ወዴት?
ለማ? መቼ? በማ? ቀጣዩስ ወዴት?”

ሮዝ ቴሌቪዥኑ ተሰቅሎ በምስል ብቻ ብልጭ ድርግም ከሚልበት ስር ቆማ ቡና እየሰራች ነው። ፀጉሯ አጭር ነው። እጇ እና እግሯ ላይ ካሏት ንቅሳቶች ውስጥ ሌላኛው ኢሮቦረስ ነው። ለስላሳ ጠይም ገላዋ በአንድ ወቅት ጭፍቅ ጥቁር እንደነበር ወጥነቱ ያመላክታል።

“በዚህ ሁሉ ነፍሴ ስትጨነቅ
ያረጋጋል አንድን ነገርን ማወቅ
ሉዋላዊ
እግዚአብሄር ሉዋላዊ ነው።”

“ህም! ሉዋላዊ?! Sovereignty is just Devine word for dictator” ለራሷ አጉረመረመች።

ሊሊ መዝሙሩን አቁማ ቲቪውን ድምፅ ሰጠችው። ኢቢኤስ ላይ አንድ አባት ቀርበው ልጃቸውን እየፈለጉ ነው። ዮናስ ከሰውዬው እጅ የአንዲት ልጅ ፎቶ ተቀብሎ ለስክሪኑ አዞረው…

ሮዝ የምታማስለውን ቡና ትታ ወደኋላ ራቅ ብላ ቲቪውን ጨረፍ አድርጋ አየች።
ፊቷ ጠይምነቱ ላይ በርገንዲ ደም ተከለሰበት። ሰውነቷ ይንቀጠቀጥ ጀመር፣ አይኗን ከሽማግሌው አስፈሪ ግምባር እንደምንም ጎትታ አርቴፊሻል እግሩ ላይ ሰካችው። በንዴት በደፈረሰው ፊቷ ውስጥ ትንሽ እርካታ ብልጭ አለ።

ዮናስ ቴሌቪዥኑ ውስጥ ቀጠለ …
“ልጅ ፅጌረዳ ከሆሳእና ከተማ ከጠፋች 11 አመት ሆኗታል አሁን ላይ የ22 አመት ወጣት ነች፣ እንግዲህ ይሄን ፎቶ በማመሳከር ፅጌን የምታውቁ ወይም ትመስላለች ብላችሁ የምትሉ ካላችሁ ከእኚህ ምስኪን አባቷ ጋ በማገናኘት ውለታን እንድትውሉ እንጠይቃለን”

ተመልካቹ በሞቅታ አጨበጨበ።

ሮዝ ከቲቪው በኩል አጠፋችው።

“እንዴ ለምን አጠፋሽው?” አለች ሊሊ

/ሮዝ ደንገጥ ብላ እየዞረች/
“እእ እንዴ እያጠናሽ አይደለም እንዴ? እኔንጃ፣ አይጨንቁም ሰውዬው የሆነ ደፋሪ አይመስሉም? “

/ሊሊ ድንግር ብሏት/
“ይመስላሉ?”

“Yeah that face is creepy”

“እኔንጃ እኔ ደግሞ አሳዝነውኝ እያየኋቸው ነበር፣ ለእኔ ደፋሪ የሚመስሉኝ ሰዎች እንደ አንዱ አለም አይነት ፊት ያላቸው ናቸው።”

/ሮዝ ዞር ብላ አይታት/
“ይቅርታ ሊሊዬ ወደዚህ ርእስ ላመጣሽ ፈልጌ አልነበረም።”

“ግን እኮ ማለት ነው? ይሄኔ ለሌላዋ ደፋሪ የሚመስላት እኛ ጨዋ የሚመስለን አይነት ሰው ሊሆን ይችላል አይደል? አንድ መልክ የላቸው መቼስ? ለምሳሌ ቲቸር ሰመረን አይታው ይሄ ደፋሪ ይመስላል የምትል ትኖራለች! ምናልባት የሷ ደፋሪ እንደ ቲቸር ሰመረ ጭምት ይመስል ይሆናል…”

“Yep, ለዛ ነው guilty until proven innocent የሚባለው። ፊት አይተን ማወቅ አንችልም፣ ስራም አይተን ማወቅ አንችልም፣ እስኪያጠቁን ድረስ ዘመድ ነን፣ አንዳንዴም አብረሻቸው እስካልኖርሽ you will never know. የሚንቀጠቀጡ እጆቿን እርስበእርሳቸው አያይዛ ለመረጋጋት ሞከረች።

“ሲያሳዝን ግን”

“ምኑ?”
ደንገጥ ብላ ጠየቀች፣ ሮዝ ከምንም በላይ ሲታዘንላት ትጠላለች፣ የሆነችውን አውጥታ መናገር የምትጠላው ስሟ”ያቺ በአባቷ የተደፈረችው ልጅ” እንዳይሆን፣ ታሪኳ ከጉብዝና ይልቅ ከከንፈር መጠጣ ጋ እንዳይነሳ ሰለምትፈልግ ነው።

“በ ቆሻሾች ሰዎች ምክንያት እድሜ ልክ ሁሉንም ወንድ በጥርጣሬ እያዩ መኖር… አያሳዝንም?”

“ እእእ በጣም”

“እኔማ ሊቀርቡኝ የሚፈልጉት ወንዶች ሁሉ አጋጣሚውን ቢያገኙ የማይተውኝ ስለሚመስለኝ ሲስቁ ወይ የሆነ ቃል ሲናገሩ ፣ የሚወዱት ነገር ብቻ ሁሉ ነገራቸው ውስጥ አንዱአለምን የሚመስል ነገር እየፈለግኩ በግድ እርቃቸዋለሁ።”

/ሮዝ ወደኋላ ዞራ ሊሊን እያየቻት/
“ታውቂያለሽ አንቺ ጠንካራ ልጅ ነሽ፣ ምን ያህሎቻችን የሆነብንን ነገር ማውራት እንደማንችል ታውቂያለሽ? ማለቴ በጣም ብዙ ሰርቫይቨሮች ስለመደፈራቸው ሲያወሩ በቀላሉ ትሪገርድ ሆነው ወደ ህመማቸው ይመለሳሉ፣ sometimes no amount of therapy will fix you”

“ምን አማራጭ ነበረኝ ብለሽ ነው? ጠንካራ ከመሆን ውጪ! በግዜ ነው ከራሴ ሌላ ማንም እንደማይቆምልኝ የተረዳሁት። የገዛ እናቴ መከታ ሳትሆነኝ ስትቀር ራሴን ለመከላከል እኔ ብቻ እንዳለሁ ገባኝ። ድጋሚ ሰውነቴን እንዳይነካኝ በመወሰኔ ተረፍኩ፣ እንጂማ ይሄኔ የበሽታ መናሀሪያ እና የልጅ እናት አድርጎኝ ነበር።”

“ለዚህ ነው እኮ የምኮራብሽ” ሮዝ ፊት ላይ ለስለስ ያለ ኩራት ይታያል።

ሊሊ በፈገግታ ተመልክታት
“አንድ ግዜ ሚስተር ሰመረ ሊያናግረኝ ቢሮ ጠርቶኝ ነበር። እንዲሁ ሁኔታዬን ተመልክቶ ልክ እንዳልሆንኩ ገባው መሰል ላናግርሽ ብሎ ጠራኝ፣ ብታይ ሌላ አይደለም የሚመለከተኝ ሰው መኖሩ በትንሹም ቢሆን የማላውቀውን ምቾት ሰጠኝ፣ ለካ ገፄ ሲለዋወጥ፣ ከሌሎች የተለየ እንግዳ ባህሪ ሲኖረኝ ተመልክቶ ምክንያቱን በጥሩ ጎን ለማወቅ የሚጥር ሰው መኖሩ ደስ አስባለኝ! ጥሩ ሰው ነው፣ ከልቡ ለሁላችንም ያስብልናል። ግን ደግሞ በሰአቱ ልቤ ምንም ፈቃደኛ ሆኖ ችግሬን ላካፍለው አልፈለግኩም ነበር። የፈለግኩት እህት ነበር። እንዳንቺ።”

ሮዝ ፈገግ ብላ እያየቻት

"I know that there are some pains you can't express to everyone አይደል? Because they can only imagine it እንጂ they won’t feel it. You simply cannot relate to every lady because you both have periods, Some ladies don't experience pain while having period at the same level you experience it, some might do but they forget as soon as it goes, while some of us live in constant fear of how the coming month might be worsening with excruciating pain.

Sometimes Pain can gain power through recognition and because of that some people won’t open up easy, and other times talking about it helps some individuals feel better. Same pain, different experience, even more different way of coping mechanisms.

እኔ በበኩሌ በመሸሽ አምናለሁ፣ ተጋፍጠን የማንችላቸው ችግሮች ስላሉ፣ አንቺን ደግሞ የማደንቅሽ መጋፈጥ በመቻልሽ ነው።
ከምንም ደግሞ የሚያስደስተኝ በዚህ ሁሉ መሀል ለትምህርትሽ ያለሽ ፍቅር ነዉ።”

ሊሊ ሮዝ ያለቻትን በዝምታ ስታሰላስል ቆይታ ቀጠለች
“ብቸኛ ማምለጫዬ ትምህርቴ ነው። ከነዚህ ሰዎች የምገላገልበት ብቸኛ መንገዴ በጥሩ ውጤት አልፌ ዩንቨርሲቲ መሄድ ብቻ ነው። “

“ታውቂያለሽ እኔ ትምህርቴ ላይ ጎበዝ አልነበርኩም my adoptive parents እሱ ስለገባቸው ወደሙዚቃው እንዳተኩር አደረጉኝ። መዝሙር ስለምወድ ብዙ የምሰራው እሱን ነበር።”

“በእግዛብሄር ታምኛለሽ ሮዝ?”

“አዎ ግን ብዙ ጥያቄዎች አሉኝ ያልመለሰልኝ”

“የሚመልስልን ይመስልሻል?”

“ይመስለኛል፣ የሚያክመን፣ የሚያድነን ይመስለኛል።”ቀ

Brown Empire

19 Dec, 05:19


“በይበልጥ ግን ቀድሞውኑ እንዳንታመም ቢያደርገን!”

ሮዝ በፀጥታ የሚደማ ልቧን እያዳመጠች “yeah I sometimes wonder where was he all those cruel times too?”

“ከዚህ በስንት አመትሽ ነበር ወደውጪ የሄድሽው?”

“አስራ ሁለት ሊሆነኝ ሲል፣ ምነው?”
“ያ ተአምር ነው ብለሽ ታስቢያለሽ? ምናልባት ባለው ሁኔታ እዚህ ብትቆዪ ኖሮ መንገድ ላይ በመደፈር ብቻ ላይበቃ ይችላል፣ መውለድ እና ሱሰኛ ሆኖ መቅረት …”

ሊሊ አንጠልጥላ ተወችው።
“ምናልባት ተአምር ይሆናል፣ ግን ደግሞ የኔ አይነት ህይወት ያላቸው ብዙ ሴቶች አሉ፣ ተአምር ከሆነ ለምን እኔ ብቻ እንድል ከማድረግ ያለፈ የመመረጥ ስሜት እንዲሰማኝ አያደርገኝም”

*
ከአስራአንድ አመት በፊት

ዶሮ የጫነው መኪና ሊመሻሽ ሲል መናሀሪያ ደረሰ። እንቅልፍ ያሸለባት ፅጌ ጫጫታው ቀሰቀሳት። ብንን ብላ ስታይ ህዝብ ጥቅጥቅ ያለበት ቦታ ላይ ነች፣ ልውረድ አልውረድ እያለች ስታመነታ አዲስአባ መግባቷን ፊትለፊቷ ባሉት የካፌ ስሞች ተረዳች። ቀስ ብላ ከገባችበት ማዳበሪያ ወጥታ ከመኪናው ጀርባ ወረደች።

ፅጌ በብርድ እንደተጨማደደች ውጥንቅጡ መሀል ቆማለች ሰማይ መሬቱን፣ የሰውን ግርግር እያየች ፈዛለች፣ ርቧታል። ወደጥግ ሄዳ ቁጭ ከማለቷ አስር ሳንቲም ፊቷ ወደቀላት። ምሽት ላይ
የተጠራቀመላትን ሳንቲሟን እየቆጠረች እያለ ትናንሽ እግሮች ዙሪያዋን ከበቧት፣ ቀና ከማለቷ ከበድ ያለ ጥፊ የተጎሳቆለ ፊቷን አጠናገራት! ዞረባት ቀና ብላ ማየትም ስላልቻለች
ፊቷን በሁለት እጆቿ ይዛ አንገቷን ቀበረች።

ከመሀላቸው አንዲት ሴት / ቢጡ/ በጩኸት ልጁን ትቆጣው ጀመር
“አንተ ያምሀል እንዴ? ለምናባህ ትመታታለህ? ደደብ! አሁን እቺ ምን አቅም አላትና ነው በዚህ መጅ እጅህ የምታፍሳት?!”

አጠገቡ ያለው ሌላው ወንድ / ማሜ/ ጎንበስ ብሎ የተበተኑትን ሳንቲሞች እየለቀመ “ለምዶበት ዱላ ይወዳል፣ በበፊት ህይወቱ አህያ ነበር እና የጌቶቹ ቂም ስላለበት ሁሉን ካልተማታሁ ይላል ለዛ ነው እሺ ፈላዋ እንዳትቆረጥሚበት”

ፅጌ የተመታችውን ጉንጯን ይዛ ልታያቸዉ አጨነቆረች፣ በፍርሀት ቁልጭ ቁልጭ እያለች ታያቸው ጀመር።

ካራ የገዛ ጏደኞቹ እሷ ፊት ስላሳጡት እየተሳደበ ቀድሞ ሄደ።

ማሜ የለቀመውን ሳንቲም በቀዳዳ ሱሪው ውስጥ ባፈነገጠው የኪሱ ምላስ ውስጥ እየከተተ “ምስኪን ፊት አለሽ ይሄን ሁሉ ሳንቲም በአንድ ለት ከሰራሽ ታስፈልጊናለሽ ነይ ተከተይን እኛጋ ታድሪያለሽ እ?!”

ቢጡ ከማሜ ቀበል ብላ “በይ ነይ እንጂ! ከኛ ጋ ቦታ እንፈልግልሻለን እዚህ ከቆየሽ የዱርዬ መጫወቻ ነው የምትሆኚው።”

ፅጌ ቀስስ ብላ ትነስታ እየፈራች ተከተለቻቸው።

*
ከአስራአንድ አመት በኋላ

ሮዝ ቤት ሊሊ በደስታ እየተፍነከነከች ፈተና ለመፈተን ለአንድ ሳምንት የተመደበችበት ዩኒቨርስቲ ለመሄድ ሮዝ የገዛችላትን እቃዎቿን በሻንጣ እየከተተች ነው።

ሮዝ ስልክ ላይ “1ኡ” በሚል ስም ሴቭ የተደረገ ስም ስልክ ይደውላል፣ ሮዝ ሳይለንት አድርጋው ወደ ሊሊ ቀልቧን መልሳ
“እኔ የምልሽ ሊሉ ያቺ ልጅ መጨረሻዋ ምን ሆነ? ታገተች ያልሽኝ?”

ሊሊ በከባዱ ተንፍሳ “ምንም የለም እስካሁን ባክሽ መኪናውንም አልመለሱለትም ፖሊስ ጋ እንደያዙት ነው።”

“እሱ እጁ ያለበት ይመስልሻል?”

“አዪ እንዲህ ማሰብ እንኳ የሚችል አይመስለኝም፣ ይሄ እኮ በደንብ የተቀነባበረ ሴራ ነው።”

“እኔንጃ፣ ከሱ መኪና ተመርጣ እሷ ብቻ ከተወሰደች
ትንሽማ የሚያውቀው ነገር ይኖራል”

“እኔንጃ እኔ እንኳ ደደብ እንደሆነ ስለማውቅ እሱን በዚህ አልጠረጠርኩትም፣ ይልቅስ አባቷ ሊቀውስ ነው። እናቷ ትሻላለች በጥንካሬ የሚፈለገውን ሁሉ እያደረገች ያለችው እሷ ነች፣ አያድርስ ነው፣ አሳዘኑኝ!”
*

ከ11 አመት በፊት

አሜሪካን ግቢ ስር መደዳውን እነካራ በውሾቻቸው ተከበው ተኝተዋል። ሌሊት ላይ ሁሉም በማስቲሽ አብደው ሲያንኮራፉ፣ ካራ ከተኛበት ብድግ ብሎ ሄዶ ፅጌን አፏን እፍን አድርጎ እየጎተተ ወደጨለማ ይዟት ገባ። ፅጌ ካራን በጣም ትፈራዋለች፣ አፏን ባይዛትም እንደማትጮህ ታውቃለች። ድልድይ ስር ሲደርሱ ገፍትሮ መሬት ጣላትና በገመድ ተብትቦ ሲባጎ ወገቡ ላይ ያሰረውን ሱሪውን መፍታት ጀመረ። ከጀርባው ግው የሚል ድምፅ ተሰማ እና ካራ በአፍጢሙ ጭንቅላቱን እንደያዘ ፅጌ እግር ስር ተዘረገፈ። ፅጌ በጩኸት አካባቢውን ልታቀልጠው ስትል ቢጡ ተንደርድራ አፏን አፈነቻት።

ቢጡ ፅጌን እየጎተተች አስነስታ
“ተነሺ ነይ ተከተይኝ በዚህ “ እየሮጡ ወደጨለማው ገቡ። ብዙ ከሄዱ በኋላ አንድ መታጠፊያ ጋ ሲደርሱ ቢጡ ፅጌን አቁማ አይን አይኗን እያየች “ሂጂ”ትላታለች።

ፅጌ የቢጡን ፊት እያየች “ብቻዬን? ወዴት ልሂድ?”

“አላውቅም አሁን በፍጥነት ከዚህ ሂጂ!”
ድምፅዋ ውስጥ ቆራጥነት አለ።
“በይ ሂጂ! ሂጂ አልኩሽ!”
ቢጡ እየገፋች ታባርራታለች
ፅጌ እያለቀሰች እግሯ ወዳመራት ሮጠች።

*

ከአስራአንድ አመት በኋላ።

ሆሳእና ገብርኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ
ፓስተር ሞላ አባ አብርሀም ፊት ተቀምጦ መሬት መሬት ያያል፣ ያለፉት አስራ አንድ አመታቶች የተለያዩ የፀፀት ሰምበሮች ያረፈበት ፊቱ ገርጅፏል። ከምንም ከምንም የሚስቱን ዘቢብ አእምሮ ጤና ማወኩ የእግር እሳት ሆኖበት ኖሯል። እሱ እግሩ ተቆርጦ ሲያገግም ባለቤቱ ዘቢብ ግን በልጇ ላይ ካደረገው በደል መዳን አልቻለችም። በይበልጥ የአካባቢው ህዝብ የተሰበረ ልቧ ላይ “ይቅር በይው” በሚል ቃል የየራሱን ጩቤ በማዋጣት እንዳትድን አድርገው ወጋጏት። መጀመሪያ ልብ ስብራት ነበር፣ ከዛ ቁጭት ሆነ፣ ከዛ ናፍቆት ሆነባት፣ ከዛ ምንም ለማድረግ አቅም ማጣት ሆነ፣ ለመበቀል እግዚአብሄርን ማስከፋት ሆነባት፣ ፀለየች አእምሮዬን ንሳኝ ብላ ፀለየች፣ ነሳት።

“ልጄ የነፍስ አባት የለሁም?” ጠየቁ አባ አብርሀም

ፓስተር ሞላ የሚለው ጠፍቶት አሰብ አድርጎ “ሀጢያቴ ላለፉት 11 አመታት ሲያሳድደኝ እና ሲሳለቅብኝ ነው የኖረው፣ አሁን ግን ይቅርታዬ በኔና በጌታ መሀል ብቻ እንዲቀር ብዬ እርስዎ ጋ መጣሁ”

“እኮ በሀይማኖታችሁ የነፍስ አባት የለም ልጄ?” እንግዳ የሆነባቸው አባ አብርሀም ጠየቁ
“እኛማ እግዚአብሄር ፊት እንበረከካለን እንጂ”

“ታዲያ እሱ አልተሻለም? የእኔ መስማት ምን ጥቅም አለው?”

እባክዎ እርስዎ ዝም ብለው ይስሙኝ”
ፓስተር ሞላ በተማፅኖ ጠየቀ።

አባ አብርሀም እንደተጨነቁ ሊሰሙ ተስማሙ

ፓስተር ሞላ ጭንቅ ብሎት ደጅ ደጁን እያየ ጀመረ…

“እድገቴ ከሀይለኛ አባት ጋ ነበር። እናቴን የሚደበድብ፣ የሰፈር ወንድ የሚፈራው፣ ሁሉን በጉልበቱ የሚያደርግ፣ ጠብደል ብረት የሚሰብር ነበር።
ልጅ ሆኜ እንደፈለገው አይነት ወንድ ልጅ አልሆንኩለትም፣ ባገኘዉ አጋጣሚ ሁሉ “ልፍስፍስ እያለ ሲሰድበኝ ገና ሶስት አመቴ ነበር ፣ ጥፋት ሳጠፋ ቀሚስ እያስለበሰ በሰፈር ሰው ያስቅብኝ ነበር። የሚገርመው ግን መሆን የምፈልገው እሱኑ ነበር። የጉልበት ችግር ባይኖርብኝም ልቤ ግን እውነትም እሱ እንደሚለው ልፍስፍስ ነበር። ከየት እንደመጣ የማላውቀው ሀፍረት ጋ ነው አብሬ ያደግኩት፣ የምፈልገው በሰው ላይ ስልጣን የማግኘት የመፈራት አቅም ሳይኖረኝ አደግኩ።

ሚስትም ሳገባ ስራ የሌለኝ ከርታታ ነበርኩ፣ ባለቤቴ ነበረች እንደወንድ ወጥታ ሰርታ የምታስተዳድረን። በዚህ ምክንያት አንድ ጉልበቴን ወይ ስልጣኔን የማሳየው… “ / ድምፁ ይቆራረጣል/ “የገዛ ልጄ ላይ ..

Brown Empire

19 Dec, 05:19


” … /እንባው ታግሎ አሸነፈው/ ግልብጥ ግልብጥ እያለ እንደሚነቀነቅ የሞላ ጀሪካን በጉንጮቹ ላይ ፈሰሰ! “ጉልበቴን ልጄ ላይ አወጣሁት!” ተንሰቀሰቀ።
በዛም ልጄ ተበቅላኝ ጥላኝ ጠፋች! ባለቤቴም አእምሮዋን ሳተች!”

አባ አብርሀም ብድግ ብለው ቆሙ
“ልጄ?
እኔ ይቅር እንዲልህ እፀልይልሀለሁ ግን አንተ ልጅቷ የሄደችበት ሄደህ፣ ፈልገህ አግኝተህ ከበደሏ አንፃት?”

ፓስተር ሞላ የሚዝረበረብ ንፍጡን በመሀረብ እየጠረገ
“አልገባኝም አባ፣ ከበደሏ?”

“አዎን! ምንም በማታውቀው ህፃን ልብ ውስጥ የቀመምከውን ክፋት እኔ ፊት እንደሆንከው ሆነህ ለይቅርታ ለምናት! አባትህም እኔጋ ቢመጣ የምለው ይህንኑ ነው። እግርህ ስር ወድቆ ይቅርታን እንዲለምንህ”

*

ከ11 አመት በፊት

ፅጌ አይኗን ስትገልጥ አፍንጫቸው ድረስ የተሸፈኑ ሶሰት መንገድ ፅዳት ሰራተኞች ወደታች እያዩአት ነው። ሰውነቷ ቀዝቅዞ መንቀሳቀስ አልቻለችም። ከታች ወደላይ ታያቸዋለች … የሚሉት በጭልጭልታ ነው የሚሰማት

አንደኛዋ የፅጌን አይን መገለጥ አይታ “እሰይ አለች በህይወት” አለች።
ሌላኛዋ ወደ ፅጌ ጎንበስ ብላ
“እናት ይሰማሻል? ፣ ደፍረዋት ይሆን እንዴ?” አለች መልሳ ቀና ብላ ሶስተኛ ጓደኛቸውን እያየች።

ፅጌ በግድ አፏን አላቃ በብርድ ከሚንዘፈዘፍ ገላዋ ውስጥ አንድ ቃል ወረወረች።
“በረደኝ”
*
ይቀጥላል…

Brown Empire

13 Dec, 01:30


“ልጄ? ልጄ? ልጅሽ ሞታለች አንዴ ሳይሆን ብዙ ግዜ! ባለመፈለግ፣ ባለመወደድ፣ በጥቃት፣ ባለመታመን! ብዙ ግዜ ገድለሻታል!
ይታይሻል ይሄ? “
ሊሊ ሹራቧን ሰብስባ በሴንጢ የተበጣ ጠባሳዎቿን ክንዷን ገልጣ እያሳየቻት “ይሄ ከአንቺ ለመራቅ የተደረገ ግን ያልተሳካ ጥረት ውጤት ነው!”

አበባ መሬት ዝርግፍ ብላ ስቅስቅ ብላ ማልቀስ ጀመረች።
ሊሊ ለእናቷ እምባ ከተጠያቂነት ማምለጫ መንገድዋ እንደሆነ ታውቃለች።

*
ማታ አምስት ሰአት አካባቢ አበባ ሳሎን ሶፋ ላይ ተደግፋ ታንጎላጅጃለች። ፊቷ በእምባ በድካም በእንቅልፍ እና በጀማሪ እርጅና ዝሏል! ሊሊ እናቷን ቆም ብላ አየቻት፣ ይህ ነው የማትለው የሀዘን ስሜት ሆዷን አንቦጫቦጨው!
አንጀቷ በሀዘን ተላወሰ! ታሳዝናታለች ግን ልታድናት ወይ ልትወዳት የማትችልበት ርቀት ድረስ ሄዳለች፣ ሩቅቅ ነች! ከዚህ በኋላ እናቷ ሞገደኛ ውቅያኖስ መሀል በጀልባ የቆመች ተስፋ የሌላት ቀዛፊ ነች። እስክትሰጥም በየግዜው ልትሰናበታት እጇን ከማውለብለብ ያለፈ ስባ ልታወጣት እንደማትችል ታውቃለች። እዛ ለመድረስ ብዙ ስህተት ሰርታለች፣ ደርሶላት እና ልቧ ፈቅዶላት እጇን ብትዘረጋላት እንኳን ስባ ታሰጥማታለች እንጂ ድና እንደማትወጣ ታውቃለች።

ሊሊ በፊቷ ላይ ሽር ያለ ዳና ቢስ እምባ እያበሰች ቀስ ብላ ወደ እናቷ መኝታ ገባች፣ ሴንጢዋን የአንዱአለም እቃ ውስጥ መፈለግ ጀመረች።

በዛው ቅፅበት አንዱአለም ከውጪ በሩን ብርግድ አድርጎ ገባ። ሌላ ግዜ መኪናውን ፓርክ ሲያደርግ ይሰሙት ነበር። ዛሬ ግን ፀጥ ካለ ኦና ውስጥ ድንገት ዘው ብሎ መጣ! አበባ ከምታንጎላጅበት ብርግግ ብላ ተነስታ ሰማይ ምድሩን ስራቸው ተወጣጥሮ በቀሉ አይኖቿ ተመለከተች። ሊሊም በድንጋጤ ከበሩ ስር ተደብቃ ቆመች።

አንዱአለም ጭንቅላቱን ይዞ ገብቶ ቁጭ አለ። አበባ ግራ ተጋብታ “ምን ሆነሀል? በስማምበወልድ መንፈስ ቅዱስ?! ምንድን ነው እሱ?”

“ጉድ ሆነናል ባክሽ!” አለ አንዱአለም እንዳቀረቀረ

“ምን ተፈጠረ? አንዱ? ምን ተፈጠረ? ንገረኝ!”
አበባ ተርበተበተች “መኪናው ምን ሆነ?”

“መኪናው ምንም አልሆነም ለግዜው፣ ፖሊስ ጣቢያ ምርመራ ስር ነው። ዴዚን ግን … ወይኔ! ዴዚን ግን ወሰዷት!”

“እነማን? ማናት ዴዚ?!”

የሊሊ ጆሮ ይበልጥ ቆመ!

“ዛሬ ከትምህርት ቤት ስንመጣ እዛች ጠባቧ መንገድ ጋ አጋቾች አስቁመው በመሳሪያ አስፈራርተዉ ዴዚን አፍነው ወሰዷት!”

“የጉድ ቀን አይመሽ እቴ የዛሬውስ የተለየ ነው” አለች አበባ አንዱአለምን ፍጥጥ ብላ እያየችው።

ሊሊ ከመኝታ ቤት ሴንጢዋን ይዛ እያደባች ወደ መኝታ ክፍሏ ተመለሰች፣ የሰማችውን መልሳ መልሳ አእምሮዋ ውስጥ ደጋገመችው።

ይቀጥላል…

Brown Empire

13 Dec, 01:30


የዱር አበቦች
ክፍል 4
ሊሊ

ትምህርት ቤት ክፍል ውስጥ አረንጏዴው ሰሌዳ ላይ ኩዊዝ ተሰጥቷቸዋል።

ሊሊ ተመስጣ እየሰራች ነው፣ የደብተሯ ጥራት እና ፅሁፏ ፐርፌክሽኒስት መሆኗን ይናገራል። ቲቸር ሰመረ ጥሩ አስተማሪ ብቻ ሳይሆን ጥሩም ሰው ነው። ከተማሪዎቹ ጋ ያለው ቅርበት አንዳንዴ ተመኝቶት መሆን ያልቻለውን ሙያ በዚህ በኩል እንዲያገኘው አድርጎታል። ልቡ ትልቅ ነው፣ ለተማሪዎቹ የታላቅ ወንድም ያህል ይሳሳል። የስሜታቸውን መለዋወጥ በቀላሉ ማወቅ ስለሚችል የትምህርት ቤቱ የተማሪዎች አማካሪ ሆኗል።

ቲቸር ሰመረ እየዞረ የተማሪዎቹን አሰራር ሲያይ ቆይቶ፣ ሊሊ ጋ ደረሰ፣ ወንበሯን ተደግፎ የሰራችውን ለማየት እጁን ሰደድ አደረገ፣ ቅርበት የሚረብሻት ሊሊ ግን በሪፍሌክስ እጁን አሽቀነጠረችው።

ቲቸር ሰመረ ያልጠበቀው ሆኖ ቢደነግጥም፣ ከራሱ ድንጋጤ ይልቅ የሊሊ ስላሳሰበው ሊያረጋጋት ሞከረ።

*
ሊሊ አንኳኩታ ቲቸር ሰመረ ቢሮ ገባች፣ እሱ ቀድሟት ቢሮ ተገኝቶ እንድትገባ በሚጋብዝ ወንድማዊ ፈገግታ ተቀበላት።

“ግቢ ሊሊ”
እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ ስሟን ላላ አድርጎ እንደባህሪው የሚጠራው እሱ ብቻ ነበረ። አዲስ ያፈራቻት ጏደኛ ሮዝ እስክትመጣ ድረስ።

በሩ ክፍት እንደሆነ ገብታ ትቀመጣለች፤ ቲቸር ሰመረ በሩን ለመዝጋት ከመቀመጫው ተነስቶ ሄደ..

“እባክህ ሚስተር አትዝጋው!” አለች ሊሊ በጭንቀት

ቲቸር ሰመረ እርምጃውን ገታ አድርጎ ወደቦታው ተመልሶ እየተቀመጠ።

“መጠየቅ እችላለሁ ለምን እንዳይዘጋ እንደፈለግሽ?”

“በር ሲዘጋ ይጨንቀኛል፣ ክላስተርፎቢክ ነኝ መሰለኝ” አለች ሊሊ

ቲቸር ሰመረ ስልኩን አውጥቶ ጉግል ያደርግና
“ i see, አየሽ አስተማሪም ከተማሪው ይማራል አንድ ነገር ካንቺ አወቅኩ ዛሬ”

ሊሊ ፈገግ ለማለት ትሞክራለች

“እኔ ደሞ ስለሪፍሌክስ አክሽን ወይንም በቀላሉ ፍሊንች ስለማድረግ የማውቀውን ልንገርሽ ሊሊ?”

ሊሊ በአዎንታ ራሷን ነቀነቀች።

ቲቸር ሰመረ ፈቃደኛነቷን ተመልክቶ ቀጠለ
“እንዲህ አይነት ነገር ብዙ ግዜ አንድ ሰው ቨለነረብል በሆነበት ሰአት ጥቃት ሲደርስበት እና አእምሯችን በአልተዘጋጀበት መልኩ መረበሽ ሲገጥመው በድጋሚ በሌላ ግዜ ሰውነታችን እነዛን አይነት ምልክቶች ያነበበ ሲመስለው ጥቃት እንዳይደርስበት ያለአእምሯችን ተሳታፊነት ሰውነታችን ራሱን ለመከላከል የሚያደርገው ቅድመ ጥንቃቄ ወይም ድንጋጤ ነው። እና ስለዛሬው የክፍል ውስጥ ኢንሲደንት እንድናወራ ስለፈለግኩ ነው የጠራሁሽ?”

ሊሊ ፊቷ ርብሽ ይላል

“ችግር አለ ሊሊ? ከአለ ምንግዜም የተማሪዎቼን ችግር ለመጋራት እዚህ እንደሆንኩ ታውቂያለሽ”

“ክፍል ውስጥ ስለተፈጠረው ነገር ይቅርታ ሚስተር ፣ እንዳልከው ሳላስበው የሆነ ነገር ነው። ለምን እንደሆነ ግን አላወቅኩም እኔም”

“አንቺ የትምህርት ቤታችን ጎበዝ ተማሪ ነሽ በዛላይ ባንቺ እድሜ የምትሆን እህት አለችኝ እኔም፣ ችግር ካለ አብረን የምንፈታበትን መንገድ ለማግኘት ዝግጁ ነኝ”

ሊሊ ትንሽ አሰላሰለች… የረበሻት ነገር እንደተናገረ ሁሉ ቲቸር ሰመረ ያለውን በውስጧ ገረበችውና ልትናገር ጀመረች…

“ይቅርታ ሚስተር … እህት ባይኖርህ እና የትምህርት ቤታችን ሰነፍ ወይ አስቸጋሪ ተማሪ ብሆን እንደ ሰው ልትረዳኝ ትሞክር ነበር?”

ቲቸር ሰመረ ትንሽ እንደማሰብ ይልና
“የማልዋሽሽ እህት ስላለችኝ እና ለእሷ ቅርብ ሰለሆንኩ ስለሴቶች ስሜት በንባብ ደረጃ ከማውቀው በተሻለ እንዳውቅ ሆኛለሁ፣ በተረፈ ግን የሳይኮሎጂ ምሩቅ መሆኔን አትርሺ፣ ሙያው ደግሞ ሰነፍ ጎበዝ ፣ወንድ ሴት፣ አስቸጋሪ ጨዋ፣ ትልቅ ትንሽ ሳይል ሁሉንም እንደሰው አረዳዱን ማስተካከል እና ድብቁን የአእምሮ ክፍል መግለጥ ነው። አንድ ሰው የሚያደርገውን ለምን እንደሚያደርገው፣ ባህሪ ነው ብሎ የያዘውን ልማድ ከምን አንፃር እንደሚያደርገው ማስረዳት እና ልክ ያልሆነውን እንዲቀይር ማገዝ የሙያ ግዴታዬ ነው።“

ሊሊ በገባኝ ጭንቅላቷን እያወዛወዘች “ልታግዘኝ ስላሰብክ አመሰግናለሁ ሚስተር ከልቤ፣ ግን ለግዜው እኔጋ ምንም ችግር የለም።”

ቲቸር ሰመረ ሳይዋጥለት እየተመለከታት “እሺ ግን አስታውሺ ልታማክሪኝ የምትፈልጊው ጉዳይ ካለ የቲቸር ሰመረ ቢሮ በርም ጆሮም ሁልግዜ ክፍት ነው።”

ሊሊ ፈገግ ብላ በእሺታ ራሷን ነቅንቃ ከቢሮው ወጣች።

*
የትምህርት መውጫ ሰአት ላይ ሊሊ ከክፍሏ በር ላይ ቆማ ወደታች እየጮኸ እና የታክሲ ቦዲ እየመታ በእሱ ታክሲ የተኮናተሩትን ተማሪዎች የሚያስገባውን አንዱአለምን ታየዋለች።

ዴዚ የ7ኛ ክፍል ተማሪ እየሮጠች ከሁሉም መጨረሻ ወደታክሲው ትገባለች። አንዱአለም ጨዋዊ በአልሆነ መንገድ ከጀርባዋ በታች ያለ ክፍሏን ደገፍ አድርጎ ይዞ ወደታክሲው ያስገባታል። ዴዚ ዞር ብላ አንዱአለምን ፈገግ ብላ ታየዋለች። አንዱአለምም በከባዱ እየገለፈጠ ወደ ጋቢና ገብቶ ታክሲውን አስነሳ።

ሊሊ ያየችው ሁሉ አደጋ እንዳለው ሰውነቷ ነግሯት በድንጋጤ በአለችበት ደንዝዛ ቀረች።

*

ሊሊ ቤት ስትገባ መሽቶ ነበር፣ የአስሩም ጣቶቿ ጉልበቶች ቀላ ብለው በልዘዋል። እጥፍ ዘርጋ እያደረገቻቸው ወደ መኝታ ክፍሏ ልትገባ ስትል እናቷ ቁዝም ብላ ሳሎን እንደተቀመጠች አስተዋለቸ። ሰላምም ሳትላት ወደውስጥ ልታልፍ ስትል

“ይቅርታ!” አለች አበባ በለሆሳስ

ሊሊ የሰማችውን ማመን አቅቷት ጆሮዋን እየተጠራጠረች ቆም አለች።

“ይቅርታ መሆን ያለብኝን አይነት እናት ስላልሆንኩ!”

ሊሊ ግራ ገብቷት የእናቷን የገረጣ ፊት እየተመለከተች
“ስራ አልሄድሽም እንዴ ዛሬ? ደህና ነሽ?”

“አይደለሁም!” ብላ የተናነቃት እምባ ይሰነጥቃታል።

ሊሊ በሀይል ተንፍሳ እናቷ አጠገብ ትቀመጣለች።

“ሊሊ?”

“አቤት”

“ፅንሱን አስወረድኩት”!
ሊሊ በድንጋጤ ዞር ብላ የእናቷን ሆድ ታያለች

አበባ ታለቅሳለች
እንዳልሺኝ ሴት ብትሆንስ? ፈራሁ!

“ለምን ፈራሽ?!”
“እያወቅሽ…”
“አላውቅም ኧረ በፍፁም” የሊሊ ድምፅ ወደቁጣ ተቀየረ

“እሷንስ እንደማይደፍራት… “

“ስለዚህ ታውቂ ነበር!” አላስጨረሰቻትም! “ስነግርሽም ውሸትሽን ነው የምትይኝ እያወቅሽ ነበር፣ ህም… እሱ አኮ አይደለም ጠላቴ አንቺ ነሽ!”

“እንደሰ‍ኡ አትበይ ሊሊ በእኔ ቦታ ሆነሽ አላየሽውም…”

ሊሊ ተነስታ ቆመች፣ እናቷን የምትሰማት አትመስልም… አይኖቿ በንዴት ፈጥጠዋል… ልቧ በፍጥነት ይመታል…

“ምናልባት እሱ የገዛ ልጁን ላይነካ ይችል ይሆናል፣ አንቺ ግን እሱ ቢተውሽ ያለወንድ መኖር ስለማታውቂበት ሌላ ወንድ ማምጣትሽ አይቀርም እሱ ወንድ ደግሞ … አይ ሳስበው ጥሩ ውሳኔ ነው! ብራቮ አበባ! ግን ይበልጥ ጥሩ የሚሆነው ምን ነበር መሰለሽ? አንቺንም እሱንም አምነሽ ከመጀመሪያውም ባትፀንሺ!”

አበባ በእልህ እምባ ውጥርጥር እንዳለች ብድግ ብላ ሊሊ ፊት እየቆመች

“መቼ ይሆን የምትረጂኝ? ላስጥልሽ ያልቻልኩት…

“ያልቻልኩት? ያልቻልኩት? ሞክሬ ነበር እያልሽ ነው?”

“ዝም ያልኩት ስለፈራሁ ነው፣ እሱም እንደአባትሽ ጥሎኝ እንዳይሄድ ስለፈራሁ! ብቻዬን መኖር ስላልቻልኩ! ጋለሞታ ከሚል ስም እና ከሰው ላለመገለል! በስንት መከራ ያገኘሁትን ተቀባይነት …ላለማጣት!

“ይሰማሻል ግን ለራስሽ ምን እንደምትይ? ለተቀባይነትሽ ስትይ እኔን እንድ ልጅሽን ሰዋሺኝ! መስዋትነት ከፈልሺብኝ! መቼም መቼምምም ይቅር አልልሽም! እናቴ ሆነሽ ልትጠብቂኝ ሲገባ በስቃዬ ተወዳጀሽብኝ! ስነግርሽ እንኳን ውሸታም አደረግሺኝ!”


“ልጄ ባክሽ…”

1,381

subscribers

83

photos

29

videos