:
የ40/60 የመኖሪያ ቤቶች እጣ አወጣጥ ተገቢነትን በተመለከተ በአ.አ መስተዳድር: በኢት.ንግድ ባንክ እና በፌዴራል ቤቶችና ከተማ ልማት ሚኒስትር ላይ ክስ አቅርበን በሁሉም መዝገቦች(6 መዝገብ) በየደረጃው ባሉ ሁሉም ፍርድ ቤቶች አስፈርደን አፈጻጸም ደርሰን ቤቶቹን ልንቀበል በተቀጠርንበት ሳምንት ጉዳዩ ለህገመንግስት አጣሪ ተመርቶ ከዛም አልፎ ለፌዴሬሽን ምክርቤት ቀርቦ መስከረም 29 ቀን 2016 አ.ም ተከራክረን ያሸንፍንበት ህግ እንደተቀየረ ትላንት በቲክ ቶክ ሰማን!
ለአመታት የተከራከርንበትን ጉዳይ እንደው ውሳኔውን እንኳን አሳውቁን ስንል (ቢያንስ የውሳኔውን ግልባጭ ባትሰጡን እንኳን አንብቡልን እያልን እየለመንን ከርመን ) ለኛ ለዋናዎቹ ባለጉዳዮች እምቢ ብለው ለ11 ክልሎች የውሳኔ ግልባጭ ልከው ለኦሮሚያ ክልል የተላከው የውሳኔ ግልባጭ በቲክ ቶክ ሲዘዋወር አየን ውሳኔያችንን(መርዶአችንን) በቲክቶክ ሰማን!..ያው ሁሉ ነገር አሳፋሪ ነው !
የዛሬ አስር አመት መንግስት ያወጣውን ህግ ተማምነው አነስተኛ ንብረት ያላቸው ሸጠው:የሌላቸው ተበድረው :አንዳንዶቹ በአረብ ሃገር ለአመታት ለፍተው ያጠራቀሙትን ብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዝግ አካውንት ካስቀመጡ ከአስር አመት በኋላ መንግስት 'ተሳስቼ ነው ያንን ህግ ያወጣሁት! ከፈለጋችሁ ብራችሁን ውሰዱ!' ብሏል።
የዛሬ አስር አመት የሰጠኸውን ሁለት መቶ እና ሶስት መቶ ሺ ብር አሁን ሲመልስልህ አባቶች 'ወርቅ ላበደረ ጠጠር መለሰለት የሚሉት አንተ ላይ ደረሰ ማለት ነው!
እኔ ተራው ግለሰብ እንኳን ምናልባት ውሳኔው ቢቀየር(ህጉ ቢሻር) ለደምበኞቼ እንዴት እንደምነግራቸው ተሳቅቄ እንቅልፍ ባጣሁበት መንግስት ውሳኔውን በቲክቶክ ለቆት ሳይ እንዴት አልፈር?!!
የዛሬ አስር አመት የወጣ ያውም በወቅቱ ከነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ጀምሮ: የሃገሪቷ ትልቁ ባንክ ፕሬዝዳንት: የዋና ከተማ ከንቲባ:ሚኒስትሮች በየደቂቃው በቴሌቪዥን መስኮት እየቀረቡ ህዝቡን ወስውሰው አንጡራ ሃብቱን ከተቀባበሉት ከአስር አመት በኋላ ከፍትህ ይልቅ ህዝበኝነት በተጫነው አካሄድ እንደነሱ አባባል 'የባለፈው መንግስት ህግ' ህገመንግስታዊ አይደለም በማለት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሃብት ቅጠል የሚያደርግ ውሳኔ ይሰጣሉ!?
በዚህ አጋጣሚ በየደረጃው ያሉ ፍርድ ቤቶች ላሳዩት የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ እና ፍትሃዊነት ትልቅ ክብር ያለኝ መሆኑን መግለጽ እፈልጋለሁ ።እኔም የሙያ ባልደረቦቼም በዚህ ጉዳይ በሁሉም ፍርድቤቶች ጥያቄያችን ተቀባይነት አግኝቶ የከሰስናቸውን አካላት ረትተናል።ክርክሩ በፍርድ አደባባይ ተቀባይነት ያላገኘው መንግስት በፖለቲካ ተቋም ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ህግ ቀይሬዋለሁ ካለ ግን ምን ማድረግ ይቻላል?!
ቀጣዩ ሂደት ምንድነው?!
ከአመታት በፊት ኢፍትሃዊ የሆነውን አካሄድ አንቀበልም ብለን ስንነሳ በፍርድ ብናሸንፍ እንኳን የሆነ ቦታ ላይ ይህ አይነት የፖለቲካ ውሳኔ እንደሚያጋጥመን እናውቅ ነበር! እናም አሁንም ትግሉን እንቀጥላለን!!
ተቀባይነት ኖረውም አልኖረውም ይህን 'የተሳሳተ ' የተባለውን ህግ ባወጡ እና ባስፈጸሙ እንዲሁም በጊዜ በዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ህጉን ባላስለወጡ የቀድሞም ሆነ የአሁን ተቋማትና የተቋማት መሪዎች ላይ ክስ እናቀርባለን! ድምጻችን እስኪሰማ በደላችን እስኪሽር ድረስ በቻልነው መንገድ ሁሉ ፍትህ እንጠይቃለን!!
የሚሆነውን አብረን እናያለን!!
(እኔ ይህን አገልግሎት የምሰጠው የዛሬ አራት አመት በተከፈለኝ ክፍያ ብቻ ነው..ለማገዝ የሚፈልግ ማናቸውም ለፍትህ እቆማለሁ የሚል ባለሙያ ጆይን ሊያደርገን ይችላል)
ትግሉ ይቀጥላል!!