ኅዳር 17/2017 (አዲስ ዋልታ) ሩሲያ 5 ከፍተኛ የእንግሊዝ ባለስልጣናትና በርካታ የፓርላማ አባላት ወደ አገሯ እንዳይገቡ ማገዷን አስታወቀች።
እግድ የተጣለባቸው ባለስጣናት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሯ አንጌላ ሬይነር፣ የአገር ውስጥ ሚኒስትሯ ይቬት ኩፐር፣ የኢነርጂ ሚኒስትሩ ኤድ ሚልባንድ፣ የጤና ሚኒስትሩ ዌስ ስቲሪንግ፣ ቻንስለሯ ሬቸል ሪቭስ እና በርካታ የፓርላማ አባላት ናቸው።
ሩሲያ ይህን ውሳኔ ያስተላለፈችው ባለስልጣናቱ ጸረ-ሩሲያ አቋም ያንጸባርቃሉ በሚል መሆኑ ስካይ ኒውስ ዘግቧል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የእንግሊዝ መንግስት ለዓለም መረጋጋት ሲል የያዘውን ስልታዊ ፍጥጫ እንዲተው ተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበን ነበር ብሏል።
ይህ ባለመሆኑ ሩሲያ በጸፋዋ ግለሰቦች፣ የእንግሊዝ ፖለቲካዊ ተቋማት፣ ወታደራዊ ክፍሎች፣ የተራቀቁ ቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪዎች እና ጸረ-ሩሲያ አቋም ሲያንጸባርቁ የነበሩ ሚዲያዎች ሁሉ ወደ አገሬ እንዳይገቡ ስትል ውሳኔ አስተላልፋለች ተብሏል።
ሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ አንግሊዝ በሩሲያ ላይ ማዕቀብ ጥላ ነበረ ሲሆን ሩሲያ በምላሹ የአሁኑን የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪዬር ስታርመርን ጨምሮ በዴቪድ ላሚ እና በርካታ የወግ አጥባቂ የፖለቲካ አመራሮች ላይ እገዳ ማስተላለፏ ይታወሳል።
ሩሲያና እንግሊዝ ከሰሞኑ ከፍተኛ ፍጥጫ ውስጥ የገቡ ሲሆን ሩሲያ በሰላይነት የጠረጠረችውን እንግሊዛዊ ዲፕሎማት ከአገሯ አባርራለች።
ከዚህ በተጨማሪ እንግሊዝ ለዩክሬን ሚሳኤል በመስጠትና ሩሲያ ላይ ጥቃት እንደትሰነዝር መፍቀዷ ሞስኮን ያስቆጣ እንደነበርና ፕሬዝዳንት ቭላስሚር ፑቲን ለዚህ ድርጊቷ አንግሊዝን በሚሳኤል ልንመታ እንችላለን ሲሊ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።