" በወርኃ ጾም ከመልካም ኅሊና የሚመነጭ መልካም ስራ ማከናወን ግድ ይለናል፤ ምክንያቱም ጾምን የምንጾመው መልካም ኅሊና ኖሮን ለእግዚአብሔር ለመታዘዝና ለመገዛት ነው " - ቅዱስነታቸው
የጾመ ኢየሱስ ሱባዔ (ዐቢይ ጾም)ን አስመልክቶ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከቅዱስነታቸው መልዕክት ፦
" ጾመ ኢየሱስ እያልን በየዓመቱ የምንጾመው የታላቁ ጾማችን ዓላማ ዲያብሎስን ለማሸነፍ ነው፤ የዲያብሎስ ማሸነፊያ ስልት የመልካም ኅሊና ልዕልና ነው፤ ሰውነታችን በመብልና በመጠጥ ሲደነድን መልካም ኅሊና በውስጣችን ዓቅም ያጥረዋል፤ መልካም ኅሊና ሲያጥረን ዲያብሎስ ዘው ብሎ ይገባና ወደ ክፉ ኅሊና፣ ከዚያም ወደ ግብረ ኃጢኣት ይወስደናል፤ በዚህ ጊዜ እኛ ተሸናፊዎች እሱ ኣሸናፊ ይሆናል፤ በአንጻሩ ደግሞ ሰውነታችን ከመብልና ከመጠጥ ሲለይ መልካም ኅሊና፣ ቊጥብነት፣ ማስተዋልና ማመዛዘን በውስጣችን ትልቅ ጉልበት ያገኛሉ፤ እነሱ ጐለበቱ ማለት ዲያብሎስ መግቢያ አጣ ማለት ነው፤ እሱ ካልገባ ግብረ ኃጢኣት አንፈጽምም፤ በዚህ ጊዜ ዲያብሎስ ተሸናፊ እኛ ኣሸናፊዎች እንሆናለን፤ ስለሆነም ጾምን የምንጾመው በዚህ ስልት ዲያብሎስንና ግብረ ኃጢአትን ለማሸነፍ ነው።
ከዚህ አኳያ ዲያብሎስን ለማሸነፍ መጾም ግድ ስለሆነ ጌታችን በከፈተልንና ባሳየን መንገድ እንጾማለን፤ እንግዲህ በወርኃ ጾም ከመልካም ኅሊና የሚመነጭ መልካም ስራ ማከናወን ግድ ይለናል፤ ምክንያቱም ጾምን የምንጾመው መልካም ኅሊና ኖሮን ለእግዚአብሔር ለመታዘዝና ለመገዛት፣ ከዚያም ከቃሉ በተነገረን መሠረት የተራቡትን ልንመግብ፣ የተራቈቱትን ልናለብስ፣ የተጣሉትን ልናስታርቅ፣ ፍትሕ ያጡትን ፍትሕ እንዲያገኙ ልናደርግ፣ ለንኡሳን የሕብረተ ሰብ ክፍሎች የተለየ ትኵረት ልንሰጥ፤ እኩልና ፍትሓዊ የሀብት ክፍፍል በሰው ልጆች መካከል ልናረጋግጥ፣ ሰብኣዊ ክብር እንዳይነካ ጦርነት፣ ጥላቻ፣ አደገኛ የቃላት ውርወራና መነቃቀፍ እንዲቀር ልናደርግ ነው ፤ በዚህ መንፈስ ጾሙን ከጾምን ጾማችን ግቡን መትቶአል፤ ዲያብሎስም ተሸንፎአል ማለት ነው፤ ስለሆነም በዚህ መንፈስ ጾሙን ልንጾም ይገባል፡፡
ወርኀ ጾሙን የተራበውን በመመገብ የተራቈተውን በማልበስ በኃላፊነት ያለን የኅብረተሰብ መሪዎችም ፍትሕንና እኩልነትን በማስፈንና ከነገሮች ሁሉ በፊት ለሰላምና ለአንድነት ቅድሚያ በመስጠት ጾሙን እንድናሳልፍ በእግዚአብሔር ስም አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን። "
(የቅዱስነታቸው ሙሉ መልዕክት ከላይ ተያይዟል)
@Tsehaye_Tsidk