አሻጋሪ ያልነው ፣ አሸባሪ ሆነ
እያለ ውስጥ ውስጡን ፣ ህዝብ ያጉረመርማል
ይሄ ምን ይገርማል?
"ህዝብ እየታረደ
የሰላም ሽልማት ፣ እሱ ይሸለማል"
እያለ አንዳንዱ ፣ በአሽሙር አንተን ያማል።
ይሄ ምን ይደንቃል?
እኔም አንድ ሰሞን ፣ በሚያሽኮረምም ቃል
እንዲህ ብዬ ነበር
በፍቅር ስብከትህ ፣ ልቤ እየራደ
"ከእባቦች እንቁላል ፣ እርግብ ተወለደ ።"
ብዬ ነበር ያኔ ፣ ምህረት ስትምገኝ
ተአምር መሥሎኝ ነበር
ከገዳዮች መሀል
"መግደል መሸነፍ ነው" ፣ ምትል አንተን ሳገኝ።
።።
ይሄ ምን ይገርማል?
"በግንቦት ሀያ ላይ ፣ ግንቦት ስላሴ ተቆጣ
ደርግ ጥሎን ሲሔድ ፣
ነፃ አውጪ ነኝ ብሎ ፣ሌላ ደርግ መጣ
ገዢ መንግስት ወርዶ ፣ ገዢ መንግስት ወጣ
ከተገዛች አይቀር
ድርሻዬ ይሰጠኝ ፣ ሀገሬ ተሽጣ"
ብዬ ነበር ያኔ
ዝም በል እያለ ፣ ሲገርፈኝ ወያኔ
ዝም አልልም ብዬ ፣ በሀገር ፍቅር ወኔ
የታገልኩት እኔ
ለቀብሬ አይደለም ፣ ቀን በቀን ለማልቀስ
ከሞት መች አዳነን
በታረድን ቁጥር ፣ ህወሐትንና ፣ ኦነግ ሸኔን መውቀስ
ማነው ከነትጥቁ
ወደሀገር ያስገባው ፣ ማነው ያስታጠቀስ?!
ፍትህ ስንጠይቅ
ሞት የሚፈርድብን ፣ የማን ሹም ነው ዳኛ
ማን ነው ስም ሚሰጠን
ስንሞት ኢትዮጵያዊ ፣ ስንኖር ነፍጠኛ
ብሎ የሚጠራን ፣ በጅምላ ስንረግፍ
ጭካኔ ሲበዛ ፣ በደል ሲያንገፈግፍ
እጥፍ ድርብ ሲሆን ፣ ይቀራል ያልነው ግፍ
ትጠብቃለህ ወይ?
ህዝብ እየተገፋ ፣ አንተን እንዲደግፍ
።
።።
እና
ሬሳ ተለቅሞ ፣ ፍትህ ስትቀር ኦና
ሰርክ እየታረደ ፣ ሚሞት የለምና
ወይ ህዝብህን አስታጥቅ ፣ ወይ መንግስት ሆነህ ና
ሀገር አይመራም!!!
"መግደል መሸነፍ ነው ፣ በሚል ፍልስፍና!
ሰው እየፈረሰ ፣ የለም ብልፅግና!