ግብ ጠባቂው ባሀሩ ነጋሽ
ታላቁን ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስን ገና በለጋ እድሜው በመቀላቀል ከ17 ዓመት በታች፣ ከ20 ዓመት በታች እንዲሁም ዋና ቡድን ድረስ በማደግ በተለይም ደግሞ 2014 እና 2015 ዓ.ም በቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከአራት ዓመት በኋላ ለተከታታይ ቡድናችን ሻምፒዮን ሲሆንና የ2000 ዓ.ም ተይዞ የነበረውን የሃያ አራት ጨዋታዎች አለመሸነፍ ሪከርድ የተጋራው የግብ ጠባቂው ባህሩ ነጋሽ ሚና እጅግ በጣም የጎላ ነበር፡፡
በ2016 ዓ.ም የክለባችን ቋሚ ግብ ጠባቂ ከመሆን በተጨማሪ ለብሔራዊ ቡድንም መመረጥ ችሏል፡፡ በ2017 ዓ.ም የክለባችን ቅዱስ ጊዮርጊስ አምበል በመሆን የአምበልነት ሚናውን እየተወጣ ይገኛል፡፡
በመሆኑም አምበሉ ባህሩ ነጋሽ ቅዱስ ጊዮርጊስን በአምበልነት መምራት ስላለው ስሜት፣ በቡድኑ ውስጥ ስላለው የአንድነትና የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ዙሪያ አጠር ያለች ቆይታ አድርጓል፡፡
መልካም ቆይታ ይሁንላችሁ፡፡
👉 ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያክል ትልቅ ክለብ ውስጥ በአንበልነት ስትመረጥ ምን ተስማህ?
ባሀሩ ነጋሽ:- ለዚህ ትልቅ ቡድን ታምኖብኝ አምበል ሆኖ መመረጥ እድለኝነት ነው፣ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡
👉 ለመጀመሪያ ጊዜ ነው አምበል ሆነክ ቡድኑን እያገለገልክ ነው ያለኸውና የአንበልነት ኃላፊነት ምን ይመስላል?
ባሀሩ ነጋሽ:- እንኳን አንበል መሆን አይደለም፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋች መሆን እራሱ ብዙ ሀላፊነት ነው ያለው እና አንበል ደሞ ሰትሆኚ በጣም ብዙ ኃላፊነት ይኖሩብሻል፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ቢሆንም ይህንን ኃላፊነት የተቀበልኩት ከዚህ በፊት አምበል ከነበሩት ከቡድን አጋሮቼ ጋር ጥሩ የሚባል ጓደኝነትና መቀራረብ ስለነበረን ብዙም አልከበደኝም፣ እንደ አንበል ሜዳ ውስጥም ሆነ ከሜዳ ውጪ ኃላፊነቴን እየተወጣሁ እገኛለሁ ከአሰልጣኞቼ የሚሰጠኝን ስራ ወይም መመሪያ በአግባቡ እየተገበርኩ እገኛለሁ፡፡
👉 አሁን በቡድናችን ውስጥ ያለው አንድነትና የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና ምን ይመስላል?
ባሀሩ ነጋሽ:- የአሸናፊነት መንፈሳችን በጣም ከፍተኛ ነው፣ ሁሉም ተጨዋቾች እርስ በራሳችን እየተከባበርን ሁሉንም ነገር በህብረት እየሰራን እንገኛለን፡፡ የተሻለ አንድነትና ህብረት አለን ሁላችንም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በጋራ እየሰራን ነው፡፡
ክለባችንን የሚመጥን ውጤት ለማስመዝገብ ከሜዳው ውስጥም ሆነ ከሜዳ ውጪ በቅንጅትና በህብረት እየሰራን እንገኛለን፡፡
👉 የባሀሩ ነጋሽ የወደፊት እቅድ ምንድን ነው?
ባህሩ ነጋሽ:- በዚህ ዓመት የመጀመሪያ እቅዴ ከቡድኔ ጋር ዋንጫ ማንሳትና በግሌ ደግሞ የዓመቱ ምርጡ ግብ ጠባቂ ከመሆን በተጨማሪ ለብሔራዊ ቡድን በመመረጥ ሀገሬን ወክዬ መጫወት እፈልጋለሁ፡፡
👉 ለደጋፊዎቻችን የምታስተላልፈው መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥህ?
ባሀሩ ነጋሽ:- ለደጋፊዎቻን ማስተላለፍ ምፈልገው ነገር ቢኖር፣ በዚህ ሰዓት ከጎናችን ሆነው በየትኛውም ሰዓትና ቦታ ተገኝተው የተለመደውን ድጋፋቸው ከእኛ እንዳይለይ ማለት እፈልጋሁ፡፡
👉 ለነበረን አጭር ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ባሀሩ ነጋሽ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡