"በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ አልሁ።ከዝምታ የተነሣ እንደ ዲዳ ሆንሁ፥ ለበጎ እንኳ ዝም አልሁ፥ …"(መዝ 39:-1 - 2) አንደበትን መጠበቅ ከብዙ ነገር ያድናል። ከአንደበት የሚፈልቅ ብዙ ቃል አለ :-
1ኛ, መልካም ቃል ! መልካም ቃል ያንጻል ያፅናናል ይጠግናል ያበረታታል……ወዘተርፈ በአንጻሩም
2ኛ, ክፉ ቃል ! ክፉ ቃል ያፈርሳል፣ ይሰብራል፣ ያደክማል፣ያጠፋል፣ ይገላል፣ ያቆስላል……ወዘተ ብዙዎች እንደሚያስቡት ብዙ ማውራት ብዙ ማወቅ አይደለም። አዋቂ ተግባሩ እንጂ ንግግሩ እንዲገልጠው አይፈልግም። አበው "ዝምታ ወርቅ ነው" ሲሉ የዝምታን ጥቅም በመረዳት ነው።
* ቅዱስ ቃሉ ሰው እንደመጣለት መናገር እንደሌለበት አጥብቆ ይናገራል::
* ሰው ቢናገር እንኳ መጠቀም ያለበት:-
የተቀመሙ ቃላቶችን እንደሆነ ቅዱስ ቃሉ ይነግረናል።
" ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፥ በጨው እንደ ተቀመመ፥ በጸጋ ይሁን።"( ቆላ 4:-6)
* የተቀመመና በፀጋ የሆነ ንግግር ! በዘይትና በቃሉ እውነት የተለወሰ በጎና መልካም የሆነ የሚያንጽ ቃል ነው ።
" ሰው ሁሉ በእሳት ይቀመማልና፥ መሥዋዕትም ሁሉ በጨው ይቀመማል።"(ማር 9:49)
* ንግግር በጨው ይቀመማል ?
ጨው የማይገባበት የቅመም አይነት የለም ! ጨው መራራውን ያጣፍጣል!
" እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም።"
(ማቴ 5:13)
* ጨው ምንሞ ቅመምን የሚቀምም ቢሆንም አስፈላጊ የሚሆነው ጨውነቱን እስከጠበቀ ጊዜ ድረስ ብቻ ነው !
" ጨው መልካም ነው፤ ጨው ግን አልጫ ቢሆን በምን ታጣፍጡታላችሁ? በነፍሳችሁ ጨው ይኑርባችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ተስማሙ።"(ማር 9:50)
* ጨው ጨውነቱን ባይጠብቅ ድንጋይ ይሆናል ::
1,ወደ ውጭ ይጣላል !
2, በሰው ይረገጣል !
3, ለምንም የማይጠቅም የሆናል !
ብዙዎች የተቀመመ ንግግር የላቸውም
*ለዚህ ነው አነፅን ሲሉ የሚያፈርሱት !
*ፈወስን ሲሉ የሚያቆስሉት !
* ጠገንን ሲሉ የሚሰብሩት !
* ተከልን ሲሉ የሚነቅሉት ! ኧረ ስንቱ
* አንደበት :- እሳት ነው የፍጥረትን ሩጫ ያቃጥላል ! (ያዕ 3:-5-6)
" እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ፥ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል።አንደበትም እሳት ነው። አንደበት በብልቶቻችን መካከል ዓመፀኛ ዓለም ሆኖአል፤ ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና፥ የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል፥ በገሃነምም ይቃጠላል።"
*ነጻነት ያለው አንደበት ሰውን በኃጢያት
ያሳድፋል ! ወዳጆችን ይለያያል ! ጥልና ግጭትን ይዘራል ! ያገዳድላል ያጠፋፋል። ሰው በወንድማማች መካከል ጠብ የሚዘራው በአንደበቱ ቃል ነው። " እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፥ ሰባትንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፤..... በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ። "( ምሳሌ 6:-16,19)
* ልብ በሉ :- አስቴር ሳትነግስ የማንነቷ ወሬ ቢቀድም ሞት የተፈረደባቸውን ህዝቧን ባልታደገች ነበር።
* ሳምሶንም የኃይሉን ሚስጥር በመዘክዘኩ በጠላት እጅ ወደቀ !
" ነገ ር ግን ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍ ራቅ፤ ኃጢአተኝነታቸውን ከፊት ይልቅ ይጨምራሉና፥ ቃላቸውም እንደ ጭንቁር ይባላል፤"(2ኛ ጢሞቴዎስ 2:16)
* ብዙዎች ያወቁ እየመሰላቸው እንደ ጭንቁር በሚባላ ቃላቸው ስንቶችን ገደሉ?
* ኢዮብ ለአፅናኞቹ ያላቸውን ተመልከቱ
( ኢዮ ም13:- 5)
"ምነው ዝም ብላችሁ ብትኖሩ!
ይህ ጥበብ በሆነላችሁ ነበር።"
አፅናኞች ከሚናገሩት ከንቱ ንግግር ዝምታ እንደሚሻል ይናገራል ! ቅዱስ ቃሉ :- " ምላሳቸውን እንደ እባብ ሳሉ፤ ከከንፈራቸው በታች የእፉኝት መርዝ ነው።"(መዝሙረ ዳዊት 140:3)
*በዚህ መርዝ ስንቱ ተነድፎ ይሆን ?
ለዚህ ነው ! ዳዊት" አቤቱ፥ ለአፌ ጠባቂ አኑር፥ የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ።"ያለው
(መዝ 141:3)
* ስለዚህ በሁሉ አንጻር መጠንቀቁ ይበጃል !
" እኔ እላችኋለሁ፥ ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤" (ማቴ 12:36) ስለዚህ እኛስ ምን እናድርግ :-
1ኛ,አንደበት በመጠበቅ የፍጥረት ሩጫ ከማቃጠል እንጠበቅ !
2ኛ,ሞት እና ህይወት በአንደበት ላይ ነው በመሆኑም ሕይወትን እንምረጥ !
3ኛ,አንደበቱን የሚጠበቅ ከተማን ከሚያስተዳድር ይበልጣልና በብልጫ ሕይወት እንኑር !
4ኛ,አንደበቱን እያሳተ የሚያመልክ የሚመስለው የሱ አምልኮ ከንቱ ነውና ከከንቱ አምልኮ እንውጣ !
5ኛ,አንደበትን መጠበቅ ወሳኝ የመንፈሳዊ ሕይወት ምዕራፍ እንደሆነ እንወቅ !
6ኛ, አንደበትን መጠበቅ ከጥፋትና ከፍረድ ይታደገናልና ከአንደበት ለሚወጣ ቃል ትኩረት እንስጥ ቃላትን አንምረጥ !
7ኛ,አንደበትን መጠበቅ እግዚአብሔር ከሚጸየፈው ኃጢያት ይጠብቀናል አብልጠን እንጠንቀቅ !
https://t.me/joinchat/AAAAAEQpgnjWczaPdu0FwA
➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖
🚀🚀 @sozo_purity 🚻🚻 @sozo_family