ኤቢሲ ዜና የጥር 20 :2017
አገዛዙ በአማራ ክልል ሰዎችን በመደዳ ማሰሩንና የመብት ጥሰት ማድረሱን ዓለም አቀፉ ማሕበረሠብ በዝምታ አልፎታል በማለት አምንስቲ ኢንተርናሽናል ቅሬታዉን ገልጿል።
ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት እንደሚለዉ አገዛዙ በአማራ ክልል በሺሕ የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን በመደዳና በጅምላ ማሰር የጀመረዉ ባለፈዉ መስከረም ነዉ።
እስራቱ የተጀመረበትን አራተኛ ወር ምክንያት በማድረግ የአምስንቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅና የደቡባዊ አፍሪቃ ኃላፊ ትጌሬ ቻጉታሕ በሰጡት አስተያየት «አማራ ክልል በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች በመደዳና በጅምላ ሲታሰሩ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዝም ማለቱ ከማሳፈር በላይ ነዉ ብለዋል።
በጅምላና በመደዳ የታሰሩት ሰዎች እንዲለቀቁ የኢትዮጵያ የልማት አጋሮች፣ ዓለም አቀፍና የአፍሪቃ የመብት ተሟጋች አካላት ተፅዕኖ የማድረግ አቅማቸዉን እንዲጠቀሙም ኃላፊዉ ጠይቀዋል። ቻጉታሕ እንዳሉት አገዛዙ የሕግ-ሥርዓትን አሁንም እየጣሰ ነዉ ብለዋል።
ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ «የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብቶች ቀዉስን» እይቶ እንዳላየ ማለፍ የለበትም ብለዋልም።
የአምንስቲ ኢንተርናሽና ባለሥልጣን እንዳሉት «ክስ ሳይመሰረትባቸዉና ሳይፈረድባቸዉ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን ለወራት ማሰር «የሕግ ጥሰት ብቻ ሳይሆን ግልፅ የሰብአዊ መብት ጥሰትም ነዉ» ብለዋል።
የአገዛዙ ባለሥልጣናት በሐገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የሲቪክ ማሕበራትን ማገዳቸዉንም ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ተቃዉሟል።
አምንስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለዉ የአገዛዙ ጦር ኃይልና የአማራ ክልል ፀጥታ አስከባሪዎች በሺሕ የሚቆጠሩ የአማራ ክልል ነዋሪዎችን እያሰሩ ወደተለያዩ አራት ማጎሪያ ማዕከላት መላክ የጀመሩት መስከረም 28 ቀን 2024 ነበር ሲልም ገልጿል።
አገዛዙ በአማራ ክልል ብቻ በአራት ማጎሪያ ጣቢያዎች 6ሺህ የሚጠጉ አማራዎች መታሠራቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት ማስታወቁ ይታወሳል።