የካቲት 25-አስቀድሞ የማያምን አሕዛብ ሆኖ ሳለ የሰማዕታት አለቃ ቅዱስ ቴዎድሮስና ክብርት እመቤታችን ተገልጠውለት እንዲጠመቅ ከነገሩት በኋላ አምኖ የተጠመቀውና በኋላም ሰማዕት የሆነው ቅዱስ እንጦኒ ዕረፍቱ ነው፡፡
+ ቅዱሳን ሰማዕታት አውሳንዮስ፣ ፊልሞንና ድንግል የሆነች ሉቅያ ምስክርነታቸውን ፈጸሙ፡፡
+ በዋሻ ውስጥ የሚኖር አባ አቡፋና ዐረፈ፡፡
ቅዱስ እንጦኒ ሰማዕት፡- ይኽህም ታላቅ ሰማዕት ከዐረቦች ወገን የቆሮስ ሰው የሆነ ባለጸጋ ሲሆን በሰማዕታት አለቃ በቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም አጠገብ በወንዝ ደርቻ ይኖር ነበር፡፡ አብያተ ክርስቲያናትን የሚቃወም ሆኖ ቅዱስ ቍርባንን በመስረቅ ኅብስቱን ይበላዋል፣ የከበረ ደሙንም ከጽዋው ውስጥ ይጠጣል፣ የመሠዊያውንም ልብስ ገፎ በእሳት ያቃጥለው ነበር፡፡ አንድ ቀን በቅዳሴ ጊዜ በፈረሱ ተቀምጦ ቤተ ክርስቲያን ሲገባ ቅዱስ ቴዎድሮስ በራሱ ጦር ወግቶ ገሠጸው፡፡ በሌላኛው ቀንም ከሰገነት ቤቱ ላይ ተቀምጦ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ሲመለከት ካህናቱ መሥዋዕቱን ተሸክመው ወደ መቅደስ ሲገቡ አያቸው፡፡ በጻሕሉም ውስጥ ነጭ በግ ተኝቶ ከበላዩ ነጭ ርግብ ሲጋርደው በቅዳሴውም ፍጻሜ ያ በግ በየመለያያው የተከፋፈለ ሆኖ ካህናቱም ከተከፋፈለው ሥጋውን ሲቀበሉ ደሙን ከጽዋው ውስጥ ሲቀበሉ አየና እጅግ ተደነቀ፡፡ በልቡም ‹‹የክርስቲያን ሃይማኖት እጅግ ድንቅ ነው›› ብሎ አሰበ፡፡ ዳግመኛም ያ በግ ተመልሶ እንደ ቀድሞው ሕያው ሆኖ አየ፡፡ ከዚህም በኋላ ከመቀመጫ ወርዶ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ያየውን ሁሉ ለካህናቱ ነገራቸው፡፡ ካህናቱም ይኽ አሕዛብ ባየው ታላቅምሥጢር ተደንቀው እንዲጸልይ መከሩት፡፡
እርሱም ካህናቱ እንደመከሩት ሌሊት ሲጸልይ ሊቅ ቴዎድሮስ በፈረሱ ላይ ሆኖ ተለጠለትና ‹‹እነሆ በእኔ ላይ ሥዕሌን እስከወጋህ ድረስ ክፉ ሠራህ፣ በክብር ባለቤት በክርስቶስ ሥጋ ላይ ዘበትክ፣ አሁንም የዘላለምን ሕይወት ታገኝ ዘንድ ከክህደትህ ተመልሰህ በክብር ባለቤት በጌታችን እመን›› ብሎት ከእርሱ ተሰወረ፡፡ በማግሥቱም ይኽ አሕዛብ በፈረሱ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳሳት ገብቶ ያየውን ምሥጢር ሁሉ ነገራቸው፡፡ ሊቀ ጳጳሳቱም ‹‹በሕዝቡ ሁሉ ፊት እንዳላጠምቅህ እፈራለሁ ነገር ግን ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሂድ ጌታችን የሚያጠምቅህን ይሰጥሃል›› አሉት፡፡ ወደ ዮርዳኖስን ሄዶ በቤተ ክርስቲያን ሳለ ሌሊት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ነጭ ሐር ግምጃ ለብሳ ተገልጣለት አረጋጋችው፡፡ በእጇም ይዛ አነሣችውና ሊያደርገው የሚገባውን ነገረችው፡፡ ወደ ዮርዳኖስም ወንዝ ሄዶ ሁለት ገዳማውያን አባቶችን አገኘና ፍላጎቱን ነገራቸው፡፡ በገዳማውያኑም እጅ ከተጠመቀ በኋላ ስሙን ‹‹እንጦኒ›› ብለው ሰየሙት፡፡ አመንኩሰውትም በሰላም ሸኙትና ወደ ደማስቆ ሄዶ ቤቱ ገባ፡፡
ወገኖቹም ባዩት ጊዜ ‹‹ይህ የለበስከው ምንድን ነው?›› ሲሉት ክርስቲያን መሆኑን ነገራቸው፡፡ እነርሱም ይዘው እየጎተቱና እየደበደቡ መኰንኑ ዘንድ አቀረቡት፡፡ መኰንኑም ስለ እምነቱ በመረመረው ጊዜ እንጦኒ በጌታችን የሚያምን ክርስቲያን እንደሆነ በድፍረት መሰከረ፡፡ መኰንኑም ይዞ ጽኑ ሥቃይን ካሠቃየው በኋላ በእሥር ቤት ጣለው፡፡ እንጦኒም በሥቃይ ውስጥ ሆኖ በእሥር ቤት ሳለ በላዩ ብርሃን ወረደና ‹‹እንዮንዮስ ሆይ! አክሊል ተዘጋጅቶልሃልና አትፍራ›› የሚል ቃል ሰማ፡፡ ብርሃን የለበሱ ሁለት አረጋውያን መጥተው በራሱ ላይ የብርሃን አክሊል አኖሩ፡፡ በነጋም ጊዜ አደባባይ ወስደው ራሱን በሰይፍ ቆረጡትና በእንጨት ላይ ሰቀሉት፡፡ በሌሊትም በላዩ ብርሃን ሲወርድ አይተው በፍርሃት ሆነው ከተሰቀለበት አውርደው ጤግሮስ አቅራቢያ ቀበሩት፡፡ ከቅዱስ ሥጋውም ብዙ አስገራሚ ተአምራት ተገልጠው ታዩ፡፡ የሰማዕቱ የቅዱስ እንጦኒ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን!
+ + +
ቅዱሳን ሰማዕታት አውሳንዮስ፣ ፊልሞና እና ቅድስት ሉቅያ፡- እነዚህም ቅዱሳም በአፍራቅያ አገር ሳለ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አስተምሮ ያሳመናቸው ናቸው፡፡ ከሃድያንም ዝሑራ በሚባል ኮከብ ስም ለአርታዳሚ ጣዖት በዓልን ባደረጉ ጊዜ እነዚህ ሦስት ክርስቲያኖች በከሃድያኑ ስሕተት ሊዘብቱባቸው ወደ ጣዖት ቤቱ ገቡ፡፡ ጣዖት አምላኪዎቹም ለጣዖቶቻቸው መሥዋዕት ሲያቀርቡና ሲያመሰግኗቸው እነዚህ ክርስቲያኖች ባዩአቸው ጊዜ ሰዎቹ ዕውነተኛውን አምላክ ጌታችንን ክደው ጣዖታትን በማምለካቸው መንፈሳዊ ቅናት ልባቸው ነደደ፡፡ ፈጥነውም ወጥተው ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ጌታችንን ስሙን እየጠሩ እየሰገዱለት አመሰገኑት፡፡ ከዚያ ካሉት ውስጥ አንደኛው ሰው በሰማቸው ጊዜ በጣዖታቸው ላይ እንደዘበቱ የተናገሩትን አስታውሶ በከሃዲው መኮንን ዘንድ ወነጀላቸው፡፡
መኮንኑም ከወታደሮቹ ጋር ፈጥኖ ሄዶ እነዚህ ሦስቱ ክርስቲያኖች ያሉባትን ቤተ ክርስቲያን ከበባት፡፡ በዚህም ጊዜ ከምእመናን ሸሽተው ያመለጡ አሉ፡፡ ቅዱስ አውሳንዮስ፣ ቅዱስ ፊልሞና እና ቅድስት ሉቅያ ግን ክርስቲያን መሆናቸውን በመመስከር ለሰማዕትነት የተዘጋጁ ሆነው ራሳቸውን ለመኮንኑ አሳልፈው ሰጡ፡፡ መኮንኑም እነዚህን ሦስት ቅዱሳን ይዞ አሠቃያቸው፡፡ የብረት ዘንጎችን በእሳት አግሎ ጎኖቻቸውን ወግቶ አቃጠላቸው፡፡ ቀጥሎም የከበረ አውሳንዮስን ወደ ጉድጓድ ውስጥ ወረወሩትና ነፍሱን እስከሰጠ ድረስ በድንጋይ ወገሩት፡፡ የከበረ ፊልሞናን እና የከበረች ቅድስት ሉቅያን ግን ብዙ ጊዜ ጽኑ በሆኑ ሥቃዮች አሠቃዩአቸው፡፡ እነርሱም ነፍሳቸውን ይወስድ ዘንድ እግዚአብሔርን ለመኑት፡፡ እርሱም ልመናቸውን ተቀብሎ ነፍሳቸውን ወሰደ፡፡ ሦስቱም ቅዱሳን ሰማዕትነታቸውን በድል ፈጽመው የድል አክሊልን በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ፡፡ የሰማዕታቱ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን!
+ + +
አባ አቡፋና፡- ይኽም ቅዱስ አባት ብርሃን በሌለበት ዋሻ ውስጥ የሚኖር ሆኖ በሁለት ቀን አንድ ጊዜ ብቻ ይመገብ ነበር፡፡ የሚመገበውም ሆነ የሚጠጣው በመለኪያ ለክቶ ነው፡፡ በመዓልትም በሌሊትም 500 ጊዜ ይጸልያል፡፡ የከበረች የአርባ ቀንን ጾም ከሦስት ቀኖች በቀር ሳይበላ ይፈጽማል፡፡ በአንዲት ዕለትም ቁጥራቸው 20 የሆኑ ወንድሞች ሊጎበኙትና ከእርሱ ሊባረኩ መጡ፡፡ አባ አቡናፋም በበዓቱ የሚበላ የለም ነበርና ሦስት እንጀራን ፈልጎ አመጣ፡፡ እነዚህንም ሦስት እንጀራዎች ባርኮ ቢሰጣቸው ሃያውም ሰዎች ጠግበው እስኪተርፋቸው ድረስ ተመገቡ፡፡
በአንዲትም ዕለት አባ አቡናፋ ለደቀ መዛሙርቱ ‹‹እነሆ ዓለም አለፈ›› አላቸው፡፡ በጠየቁትም ጊዜ ‹‹እነሆ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ሞተ›› አላቸው፡፡ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን ሦስት መቶ የወርቅ ዲናር የያዘ እንግዳ በአንድ ቄስ ቤት አደረ፡፡ ቄሱም ስለ ገንዘብ ፍቅር እንግዳውን ገደለውና ወርቁን ወሰደ፡፡ ሬሳውንም ከአንድ መነኩሴ ደጅ ወስዶ ጣለው፡፡ ይህንንም ለአባ አቡናፋ በነገሩት ጊዜ ከሟቹ ላይ እንዲጥሉት ቆቡን ሰጣቸው፡፡ ወስደውም የአባ አቡናፋን ቆብ በላዩ ላይ በጣሉበት ጊዜ የሞተው ሰው ፈጥኖ ተነሣ፡፡ ስለ ገንዘብ ፍቅር ቄሱ እንገደለውም ሲነገራቸው እነርሱም እጅግ አደነቁ፡፡ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አንድ ሰው ከአባ አቡናፋ ቡራኬ ሊቀበል ወደ እርሱ ሲመጣ ልጁ በጉዞ ላይ ሞተ፡፡ ሰውየውም የሞተ ልጁን ተሸክሞ ወደ ቅዱስ አቡናፋ በመሄድ በፊቱ ሰግዶ የልጁን አስክሬን አስቀምጦ ተመለሰ፡፡ ያንጊዜም ልጁ ከሞት ተነሥቶ አባቱን ተከተለው፡፡በአባ አቡናፋ ዋሻ ደጃፍ የውኃ ምንጭ ነበረ፡፡ እርሱም ምሳርን በወረወረ ጊዜ ምሳሩ ነቢዩ አልሳዕ እንዳደረገው በውኃው ላይ