አቡነ ሀብተ ማርያም የዘውትር ጠባቂያቸው ቅዱስ ሚካኤል ካዘዛቸው በቀር ምንም አይሠሩም ነበር፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትንም ባነበቡ ጊዜ ኃይለ ቃሉን እየተረጎመ ምሥጢራትን ይነግራቸዋል፤ የተሰወረውንም ይገልጥላቸዋል፡፡ ከእንስሳት ጩኸት ጀምሮ ከዱር አራዊት ድምፅና እስከ አእዋፍ ቋንቋ ያለውን ያስረዳቸው ነበር፡፡
ይኸውም ቅዱስ መልአክ አንድ ቀን አቡነ ሀብተ ማርያምን ወደ ቤተ ክርስቲያን አስገብቷቸው ሥጋ ወደሙን ለመቀበል ተዘጋጅተው ሳለ ወንጌል የሚነበብበት ሰዓት ሲደርስ ያልተማረ ቄስ የክርስቶስ ጌትነቱን የምትናገር ወንጌልን ሲያነብ ‹‹ወዮሴፍ ብእሲሃ ለማርያም ጻድቅ ውእቱ›› የሚል ከቄሱ አፍ ይህን ንባብ አባታችን ሲሰሙ እጅግ ደንግጠው ወንጌል ወደሚነበብበት ስፍራ ሄደው የሚያነበውን ቄስ ገሠጹት፡፡ ‹‹ወዮሴፍሰ ፈሃሪሃ ለማርያም ጻድቅ ውእቱ በል እንጂ ብእሲሃ አትበል›› ብለው መከሩት፡፡ ቄሱም አቡነ ሀብተ ማርያም እንዳዘዙት ከስህተቱ ወደ ቀና ንባቡ ተመለሰ፡፡ ይህን ጊዜ ጌታችን ለአባታችን ድጋሚ ተገልጦላቸው ‹‹ሀብተ ማርያም ሆይ ይህን ትምህርትህን ወድጄ አመሰገንኩህ፣ የእናቴን የድንግል ማርያምን የድንግልናዋን ንጽሕና ስለ አከበርክ እኔም በመንግስተ ሰማያት ፈጽሜ አከብርሃለሁ›› አላቸው፡፡ ዳግመኛም ጌታችን ‹‹አሁንም ዮሴፍ ብእሲሃ ለማርያም የሚሉትን ሁሉ ለያቸው እንጂ አትተዋቸው፤ እንዲህ የሚል ጽሑፍም ብታገኝ እንዳይኖር እርሱን ፍቀህ ፈሃሪሃ ለማርያም የሚለውን ጻፍ›› ብሎ አባታችንን ካዘዛቸው በኋላ ሰላምታ ሰጥቷቸው ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡
አባታችንም በዚህ ጊዜ ፊታቸው ላይ ብርሃን ስለተሳለባቸውና እንደ ፀሐይ ስላበራ ሰዎችም አይተው ባደነቁ ጊዜ ወደ በዓታቸው ገቡና ጌታችንን ‹‹አቤቱ ጌታዬ ሆይ በሰው ፊት ክብሬን አትግለጥብኝ ሰውርልኝ፣ በቸርነትህም አድነኝ›› ብለው ጸለዩ፡፡እንዲህም ብለው በጸለዩ ጊዜ ፊታቸው መልኩ ተለውጦ እንደ ቀድሞው ሆነ፡፡
የአቡነ ሀብተ ማርያም የከበረች በረከታቸው ትደርብን አሜን።
https://t.me/MoaeTewahedoB