አንድ ጊዜ በጎንደር ከተማ አንድን ስልጠና ለመስጠት በነበርኩበት ጊዜ የተከሰተ የግል ልምምዴን ላካፍላችሁ፡፡ ያረፍኩበት ሆቴል ከፍ ያለ ኮረብታ ላይ ስለነበረና አካባቢው በዛፎች በመከበቡ ምክንያት የራሱ ውበት ስላለው በዚያ ማረፍን እመርጣለሁ፡፡ በዚያ ባደርኩበት አንድ ሌሊት ግን አንድ ነገር ተከሰተ፡፡
ሌሊት ነቅቼ ወደ መታጠቢያ ቤት መሄድ ስላስፈለገኝ ከአልጋዬ ለመውጣት ተንቀሳቀስኩኝ፡፡ ከውጪ በመስኮት በኩል በመጋረጃው ሾልኮ የሚገባው ደብዛዛ ብርሃን ለእንቅስቃሴዬ በቂ ስለነበር ልክ ከአልጋዬ ስወርድ ወደ መታጠቢያ ቤቱ በሚወስደው አቅጣጫ አንድ “እባብ” ተጋድሞ አየሁኝ፡፡ ከብርሃኑ ደካማነት የተነሳ ይህንን “እባብ” ቅርጹን እንጂ መልኩንና ሁኔታውን መለየት አልቻልኩም፡፡ በጣም ደነገጥኩ፣ በጣምም ፈራሁ፡፡
ወደኋላዬ በመሰብሰብ ሁለንተናዬን ትራሴ ላይ አገኘሁት፡፡ ብዙ አሰብኩኝ፡፡ ብዙ አወጣሁኝ፣ አወረድኩኝ፡፡ ትንሽ ጊዜ ካቃጠልኩኝ በኋላ፣ በመጨረሻ ያለኝ ብቸኛ አማራጭ እንደምንም የእባቡን ክልል አለፌ መብራቱን ማብራት ነው፡፡ ትንሽ ከወላወልኩኝ በኋላ የፈጣሪዬን ስም እየጠራሁ፣ ጨለማውን ለማሸነፍ አይኖቼን አፍጥጬ፣ ጥግ ጥጉን ተራምጄ መብራቱን ልክ ሳበራው ለካ ያየሁት “እባብ” ማታ በድካም ስሜት ወደ አልጋ ስቸኩል የጣልኩት ቀበቶዬ ነበር፡፡
በዚህ ገጠመኜ የገባኝ ነገር ይህ ቀበቶ እባብ መስሎኝ በነበረበት ሰዓት፣ ልክ እውነተኛ እባብን ብጋፈጥ የሚሰማኝን የፍርሃት ስሜት ነው የሰጠኝ፡፡ ከዚህ ስሜት የተነሳ ልጮህ እችል ነበር፣ እዚያው አልጋዬ ላይ ሆኜ እስከሚነጋ አፍጥጬ ልጠብቅ እችል ነበር፣ ሰዎች ጋር ስልክ በመደወል ልበጠብጥ እችል ነበር . . .፡፡ በፍርሃት ተወጥሮና ታስሮ የነበረውን ማንነቴን ነጻ ያወጣው እውነቱን ለማወቅ መብራቱን ማብራቴ ነው፡፡
ለካ እይታ የእውነታን ያህል ጉልበት አለው፡፡ በሕይወታችን አንድ ነገር ባይኖርም እንኳን፣ እንዳለ ከቆጠርነውና ከፈራን ማንነታችንን አስሮ ሊያስቀምጠን እንደሚችል በሚገባ የተገነዘብኩት ያን ጊዜ ነው፡፡ መድሃኒቱ መብራቱን ማብራት ነበር፡፡
አንዳንድ ሰዎች ገና ለገና ሆኖብኛል . . . ሳይሆንብኝ አይቀርም . . . አለብኝ . . . ሳይኖብኝ አይቀርም . . . ሊሆን ነው . . . መሆኑ አይቀርም ከሚሉት ምክንያት-የለሽ ፍርሃት የተነሳ ታስረው አመታት ያሳልፋሉ፡፡ ይህ ፍርሃት፣ እምቅ ብቃታቸውን አፍኖ፣ ነጻነታቸውን ነፍጎ፣ የሌለውን ችግር እንዳለ አድርጎ፣ ያለውን ችግር ደግሞ እጅግ አግዝፎ በማሳየት ከሰው በታች ያደርጋቸዋል፡፡
መፍትሄው መብራቱን ማብራት ነው!!! መብራቱን ማብራት ማለት እውነታውን ለመጋፈጥ አይንን መግለጥ፣ ስለሁኔታችን ከበሰለ ሰው ጋር መወያየት፣ ምንም ነገር ቢሆን በፍርሃት ታስሮ ከመኖር እውነታውን ተጋፍጦ በነጻነት መኖር እንደሚመረጥ መገንዘብ ማለት ነው፡፡ አይህንን አትርሳ፣ መፍራት እስከምታቆም ድረስ መኖር አትጀምርም!
የቴሌግራም ቻናል ይቀላቀሉ
http://t.me//Dr_MehretDebebe