ጥር23/2017ዓ.ም
የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ አንዴ ማማ ከተባለ ሀገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተባበር አገልግሎት በሰጡ ወረቀቶች የተለያዩ ለቤትና ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ከወረቀት የሚሰሩ የእጅ ሥራ ውጤቶችን የኢንተርፕራይዙ የቢሮ ውበትና የቢሮ አገልግሎት ከሚሰሩ የተውጣጡ ለአስራ ሰባት ሴት ሠራተኞች ለ21 ቀናት ሥልጠና ተሰጠ፡፡
የስልጠናውን አስፈላጊነት በተመለከተ በኢንተርፕራይዙ ስርዓተ ፆታ ጉዳዮች ቡድን መሪ ወ/ሪት መስታወት ንጉሴ፣ ሴቶች በተሰማሩበት የስራ ዘርፎች ሁሉ ለሃገር እያበረከቱት ያለው አስተዋፅዖ ከፍተኛ በመሆኑም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ማሰልጠን እና አቅማቸውን ከፍ በማድረግ የሥራ እድሎችን በመፍጠር በተሰማሩበት ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አንዴ ማማ የበጎ አድራጎት ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ሚካኤል ኃይሌ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ የሚያሰለጥነው ስልጠና ጥቅም ላይ የዋሉ እና ተመልሰው ለጽሕፈት ሥራ የማይሆኑ ወረቀቶችን በመጠቀም የወረቀት ቅርጻ ቅርጾች አዘገጃጀት ላይ ነው፡፡ በመሆኑንም ሠልጣኞች ከዚህ ስልጠና በኃላ በበጎ አድራጎት ድርጅቱ በኩል የሥራ እድል እንዲያገኙ እና የገበያ ትስስር ሊፈጥሩላቸው እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ሰልጣኞችም በበኩላቸው የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ የስርዓተ ፆታ ጉዳዬች ቡድን ከአንዴ ማማ በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በጋራ በመቀናጀት አገልግሎት የሰጡ ወረቀቶችን ተጠቅመው የእጅ ሥራ ውጤቶችን አሰራር መሰልጠናቸው የራሳቸውንም ሆነ የቤተሰባቸውን የኢኮኖሚ አቅም መገንባት የሚያስችል ትልቅ መሠረት መሆኑን ተናግረዋል።