Latest Posts from ✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠ (@betgubae) on Telegram

✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠ Telegram Posts

✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠
በዚህ ቻናል በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በሰንበት ትምህርት ቤት የሚሰጠውን ተከታታይ ትምህርት በጉባኤ ተገኝተው መማር ላልቻሉ በሃገር ውስጥም ከሃገራችንም ውጪ ለሚኖሩ ምዕመናን መማማሪያ የተከፈተ ነው።
t.me/betgubae

የፌስቡክ ኣድራሻዬንም ይጎብኙ https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71
8,188 Subscribers
915 Photos
12 Videos
Last Updated 06.03.2025 02:30

The latest content shared by ✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠ on Telegram

✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

01 Mar, 16:48

1,567

#ቅድስት

የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሣምንት ቅድስት ይባላል።
- የተለየች ፤ የተባረከች ፤ የከበረች፣ ንጽሕት ማለት ነው::

ለምን ቅድስት ተባለ?

-> «ጾምን ቀድሰ ጉባኤውን አውጁ ሽማግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤተ ሰብስቡ፡፡»
(ት.ኢዩኤል 1፥14) ብሎ በነቢዩ ኢዮኤል አፍ የተናገረ ቅዱስ እግዚአብሔር የጾማት ጾም ስለሆነች (የጌታችን ጾም ከቅድስት ጀምሮ በመሆኑ) ቅድስት ትባላለች።

-> እንዲሁም የዲያብሎስን ፈተና ድል ለመንሳት በቅድስት ከተማ በሰሎሞን ቤተ መቅደስ ጫፍ የቆመባት ዕለት በመሆኗ (ማቴ 4፥5/ ዮሐ 10፥22-23 ) ሰው ሁሉ ጾምን ጾሞ እንደ ፈጣሪው ፈተናን ድል ነሥቶ ቅድስና እና ክብርን ያገኛልና ቅድስት ተብላለች።


--> ቅድስት ዕለተ ሰንበት
«እግዚአብሔር ሰባተኛይቱን ቀን ባረካት ቀደሳት» (ዘፍ 2÷3፣ ዘጸ 20፥8) ሰዎች ፍጥረት ያልተፈጠረባት ዕለት ብለው እንዳይንቋት እንዳያቃልሏት እረፍተ ሥጋ እረፈተ ነፍስ የተገኘባት ዕለት ስለሆነች ቀደሳት አለ፡፡ ቅዱስ ያሬድም " ሰንበትየ ቅድስትየ ዕንተ አዕረፍኩ እምኩሉ ግብርየ ይቤ እግዚኣብሔር " ብሉአል:: በዚህ እሁድ (ሳምንት ) ቀደሳት፣ አከበራት፣ ከፍ ከፍ አደረጋት :- የተባለች ሰንበትን የምትታሰብበት የሰንበትንም ቅድስና የሚመለከቱ መዝሙሮች የሚቀርብበት ሳምንት በመሆኑ ቅድስት ተብሏል።


-> መዝሙር ዘቅድስት ፦
ግነዩ ለእግዚአብሔር

-> ምንባባተ ቅድስት ዘቅዳሌ ፦
- 1ኛተሰሎ.4፥1-13
- 1ኛ.ጴጥ.1÷13-ፍም
- የሐዋ.10፥17-30
- ማቴ 6፥16-25 (4፥1-11)

-> ምስባክ ዘቅድስት፦
" እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ አሚን ወሰናይት ቅድሜሁ ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ "
ትርጉም፦ " እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ፥ ምስጋና ውበት በፊቱ ፥ ቅድስትነትና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው ። " (መዝ 95፥5)

-> ቅዳሴ ዘቅደስት፦
- ኤጲፋንዮስ

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

25 Feb, 02:18

2,577

✥✥✥ 0ቢይ ጾም እና ስያሜዎቹ ✥✥✥

➛ ይህ ጾም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ በገዳም ገብቶ 40 ቀንና 40 ሌሊት የጾመው ጾም ሲሆን በተለያዩ ስያሜዎች ይጠራል ፡፡


፩- 0ቢይ ጾም፡- 0ቢይ ማለት ታላቅ ማለት እንደሆነ ሁሉ ይህ ጾም " ዐቢይ እግዚአብሔር ወብዙኅ አኰቴቱ " "ዐቢይ እግዚአብሔር ወዐቢይ ኀይሉ " የተባለ ጌታ የጾመው ጾም በመሆኑ (መዝ 47፥1 / መዝ 146፥5)

-> ከጾሞች ሁሉ ታላቅ በረከትን የምናገኝበት በመሆኑ

-> በቀኑም ብዛት ከሌሎቹ አጽዋማት ይበልጣልና

-> ርዕሰ ኃጣውዕ (ታላላቅ ኃጢአቶች) ድል የተነሱበት ጾም በመሆኑ ታላቅ የሚለውን ስያሜ ይዟል ፡፡


፪- የሁዳዴ ጾም፡- ይህም የመንግሥት እርሻ ወይም ማንኛውም የሕዝብ ብዛት ያለበት ሥራ ሁሉ ሁዳዴ ስለሚባል ፥ የጥንት ዘመን ገባሮች ለባለርስቱ የሚያርሱት መሬት ( ሁዳድ ) ይባል እንደነበር ይህም ጾም ሠራኤ ሕግ ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ምዕመናንም ይንን እያሰቡ ከልሒቅ እስከ ደቂቅ ( ከትንሽ እስከ ትልቅ ) የሚጾሙት ስለሆነ ጾመ ሁዳዴ ተብሏል ፡፡ (ት. አሞ 7፥1)

፫- የካሣ ጾም፡- የቀድሞዎቹ ሰዎች አትብሉ የተባሉትን በመብላታቸው ከገነት ለመባረር ለውርደት ለሞት ለሲዖል ባርነት ተዳርገዋል ፡፡ ዳግማዊ አዳም የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስ በመብል ምክንያት ድቀት አግኝቶት ረሃብ ሥጋ ረሃበ ነፍስ ደርሶበት የነበረው ቀዳማዊ አዳምና ልጆቹ በፈቃዱ በጾመው ጾም ረሃበ ሥጋችንን ረሃበ ነፍሳችንን ሊያርቅልን ስለጾመው የካሣ ጾም ይባላል ፡፡

፬- የድል ጾም፡- አዳምና ሔዋን ከዚህ ዓለም ርቃ በምትገኝ በገነት ሳሉ በምክረ ከይሲ ተታለሉና ድል ሆኑ ፡፡ ተስፋ አበውን ሊፈጽም የመጣ ክርስቶስም ዲያብሎስን ድል ያደርግልን ዘንድ ተጠምቆ ሳይውል ሳያድር ከዚህ ዓለም ርቆ ወደ ገዳም በመሔድና ከሰው ተለይቶ 40 ቀንና 40 ሌሊት በመጾም ዲያብሎስን ፣ ፈቃደ ሥጋችንን ድል የምናደርግበት ኃይል አጎናጽፎን ፣ ሦስቱን የኃጢአት ራስ የተባሉት ድል የተነሱበት ዲያብሎስ ያፈረበት ስለሆነ የድል ጾም ይባላል ፡፡ (ማቴ 4)


፭- የመሸጋገሪያ ጾም፡- ነቢዩ ሙሴ 40 ቀንና 40 ሌሊት በሲና ተራራ ጾሞ እሥራኤል ዘሥጋን ከሕገ ልቡና ወደ ሕገ ኦሪት ያሸጋገረ ሲሆን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እሥራኤል ዘነፍስ የተባልነውን ከሕገ ኦሪት ወደ ሕገ ወንጌል 40 ቀንና ሌሊት በመጾም ያሸጋገረን በመሆኑ የመሸጋገሪ ጾም ተብሎ ይጠራል ፡፡

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ 

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

23 Feb, 17:45

2,975

✥ ዘወረደ ✥

-> የ0ቢይ ጾም የመጀመሪያው እሁድ (ሳምንት ) ዘወረደ ይባላል።

->ጌታችን እኛን ለማዳን ከሰማይ መውረዱን የሚነገርበት ሳምንት በመሆኑ ዘወረደ ተብሏል።

-> ከሰማይ ወረደ ማለት እርሱ የሌለበት ኖሮ ካለበት ወደዚህ መጣ ማለት አይደለም እርሱስ ጽርሐ አርያም ምጥቀቱ በርባኖስ ጥልቀቱ ፥ አድማስ ናጌብ ስፋቱ ተብሎ የማይነገርበት በዓለም ሙሉዕ ነውና ዓለማትን ቢወስን እንጂ ዓለማት እርሱን አይወስኑትም ።

-> የፀሐይ ብርሃን ከክበቡ ሳይለይ ከ0ይናችን ብሌን ጋር እንደሚዋሓድ ወልደም ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ በምልዓቱ መወሰን ሳይኖርበት በሥጋ ማርያም መገለጹን ሰው መሆኑን ያስረዳል ::

-> ከሰማይ ወረደ ሲባል ስንሰማ መረዳት የሚገባን

1- "ሰማይ" ያለው ዕበዩን፣ ክብሩን ፣ ልዕልናውን ፣ ጌትነቱን፣ መንግሥቱን ፣ ርቀቱን .... ነው :: ስለዚህ ከሰማይ ወረደ ማለት የባሪያውን መልክ ይዞ ሰው መሆኑን ለመግለጽ ነው። (ፊል 2፥6-8)

-> ሰው ሆኖ መፈጠር ታላቅ ክብር ነው ለአምላክ ግን ሰው መሆኑ ተዋርዶ ነውና ይልቁንም እኛን ለማዳን በለበሰው ሥጋ መራብ መጠማቱ ፣ መገረፍ መታመሙ ... እንኳን ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ይቅርና ከመላእክት እንኳን ያነሰበት ነው መላእክት በባህሪያቸው መራብ መጠማት፣ መታመም የለባቸውምና " ከመላእክት እንኳን አሳነስከው " ያለውም ስለዚህ ነው ። (መዝ 8፥5 / ዕብ 2፥7)

-> ይህ ማለት ግን ወልድ ሰው መሆኑ አምላክነቱን አጥቶ በዚህም ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ አነሰ ማለት አይደለም ጌታችንም "አብ ይበልጠኛል" ያለው በለበሰው ሥጋ ባገኘው መራብ መጠማት አነሰ ለማለት ነው አብ እና መንፈስ ቅዱስ ሰው ሆነው መራብ መጠማት ... ያላገኛቸው መሆኑን ለመግለጽ ነው። (ዮሐ.14፥28)

2- መጣ ወረደ መባሉ የሰው ልጅ በበደሉ ምክንያት ከአምላክ ምን ያህል ርቆ ኮብልሎ እንደነበር ተረዳ ስለዚህ የጠፋን እኛን ለመፈለግ የራቅነውን ወደርሱ ለማቅረብ መጥቷልና ዘወረደ ተባለ። (ሉቃ 15 )

3- የፍጥረት ጥንቱ መጸነሱ ነው ፥ የጌታችን ጥንቱ ግን ከማርያም ከተጸነሰ ወዲህ አይደለምና ዘወረደ የሚለው የጌታንን ቅድምናውን ያስረዳል።
-> ፎጢኖስ የተባለ መናፍቅ የወልድ ሕልውና ከማርያም ከተወለደ ወዲህ ነው (ለፌ እም ማርያም ) የሚል ነበር በቅዱስ መጽሐፍ ግን ስለ ወልድ ሕልውና ከማርያም በፊት ጥንት በማይነገርበት መጀመሪያ መሆኑን ያስረዱናል እነዚህ ማስረጃ ያድርጉ👇
- ዮሐ 1፥1 " በመጀመሪያ ቃል ነበረ.. "
- ዮሐ 8 " እውነት እውነት እላችዃለኹ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለኹ "
- ዮሐ 17 " አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር ባንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ። "

-> ቅዱስ ያሬድ ጾመ ድጓውን ሲጀምር " ሃሌ ሃሌ ሉያ ዘወረደ እም ላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ ወሚመ ኢያእመሩ እግዚአ ኩሉ ዘየሃዩ በቃሉ /
ከሰማየ ሰማያት የወረደ አይሁድ የሰቀሉት ሁሉን በቃሉ እንደሚያድን አይሁድ ያላወቁት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው " በማለት ሰው ሆኖ በአይሁድ ተዋርዶ ያገኘው መሆኑን የዚህን ሳምንት ጠቅላላ ሀሣብ ይገልጻል።

የዘወረደ የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)

ሃሌ ሉያ ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት በፍርሃት ወተኃሠዩ ሎቱ በረዓድ፤ /መዝ.፪፥፲፩/
እስመ ለዓለም ምሕረቱ ለትውልደ ትውልድ ጽድቁ ንሕነሰ ሕዝቡ፤ ባኡ ቅድሜሁ በተጋንዮ ወውስተ አዕጻዲሁ በስብሐት እመንዎ፤ /መዝ.፺፫፥፫-፭/
እስመ … ንጹም ጾመ ወናፈቅር ቢጸነ ፥ ወንትፋቀር በበይናቲነ፤ እስመ … አክብሩ ሰንበተ ተገበሩ ጽድቀ እስመ ሰንበትሰ በእንተ ሰብእ ተፈጥረት፤/ማቴ.፲፪፥፰/
እስመ … ምሕረተ ወፍትሐ አሀሊ ለከ እዜምር ወእሌቡ ፍኖተ ንጹሐ፤ እስመ ለዓለም ምሕረቱ ለትውልደ ትውልድ ጽድቁ ንሕነሰ ሕዝቡ አባግዓ መርዔቱ፨

ትርጕም፤ እግዚአብሔርን በመፍራት ተገዙለት፤ ለእርሱ መገዛትም ደስ ያሰኛችሁ፡፡ እግዚአብሔር ቸር ምሕረቱም ለዘለዓለም፣ እውነቱም ለልጅ ልጅ ነው፡፡ እኛስ ሕዝቡ የመሰማርያው በጎች ነን፡፡ ወደ ደጁ በመገዛት፤ ወደ አደባባዮቹም በምስጋና ግቡ፤ ጾምን እንጹም፤ ጓደኞቻችንን እናፍቅር፤ እርስ በርሳችንም እንፋቀር፡፡ ሰንበት ስለሰው ተሠርታለችና፤ ሰንበትን እናክብር፡፡ እውነትንም እንሥራ፤ አቤቱ ምሕረትንና ፍርድን እቀኝልሃለሁ፤ እዘምራለሁ፤ ንጹሕ መንገድንም አስተውላለሁ፡፡

የዘወረደ ምስባክ
(መዝ. 2፥11 ) " ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት ወተሐሠዩ ሎቱ በረዓድ። አጽንዕዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመዐፅ እግዚአብሔር።
ትርጉም፦ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፥ በረዓድም ደስ ይበላችሁ። ጥበብን አጽኑአት ፤ እግዚአብሔር እንዳይቆጣ። "

-> የዘወረደ ምንባብ 1 (ዕብ.13÷7-17)
-> የዘወረደ ምንባብ 2 (ያዕ.4÷6-ፍጻ.)
-> የዘወረደ ምንባብ 3 (ሐዋ.25÷13-ፍጻ.)

የዘወረደ ቅዳሴ

-> ቅዳሴ ዘእግዚእነ (ነአኩተከ )

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ 

https://t.me/+VBt2ld_HeykCaELL (ቴሌግራም ቻናል )

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

23 Feb, 07:16

2,142

" የሴቲቱ ዘር ራስ ራስህን ይቀጠቅጥሃል " ተብሎ ለአዳም የተገባው ኪዳን የተፈጸመባት መሆንዋን ለማጠየቅ እርሱን "የሴት ዘር " እርስዋንም "ሴት" ተብላለች። ይህም የአዳም የምህረት ኪዳን የተፈጸመባት በመሆኑዋ ኪዳነ ምህረት ትባላለች።

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

20 Feb, 18:24

3,025

አዳም (ሰው) ከውደቀት በፊት ሞት ለባሕርይ ይስማማው ነበርን ?

(ክፍል አንድ )

ለዚህ ጥያቄ አጭሩ መልስ ፦ አዳም እንዲሞት አልተፈጠረም ነገር ግን ሞት ለባሕርይው ይስማማው ነበር የሚል ነው ።

- ለዚህ ማስረጃ « መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ ፤ ከርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና ።» ( ዘፍ 2፥17 ) ባለው ቃል አዳም ሞት ለባሕርይው የሚስማማው መሆኑን ይገልጻል ምክንያቱም ፦
" ባሕርይ " ማለት የተፈጥሮ ነቅዕ የማይለወጥ .... ማለት ነውና ባህርይ ደግሞ የማይለወጥ ከሆነ አዳም ሞት ለባህርይው የማይስማማው ሆኖ ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ ዕፀ በለስን በልቶም እንኳን አይሞትም ነበር ምክንያቱም አስቀድመን እንዳልነው "ባሕርይ " የማይለወጥ በመሆኑ ነው፡፡

ለዚህ ጥሩ ማስረጃ የሚሆኑን መላእክት ናቸው ፦ መላእክት ሞት ለባህርያቸው የማይስማማቸው ናቸው በሊቃውንት መጽሐፍት እንዲሁም በአንድምታ ትርጓሜ በስፋት ተገልጿል ለምሳሌ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በአክሲማሮስ መጽሐፉ የመላእክት ተፈጥሮ ካለመኖር ወደመኖር ከምንም እንደሆነ እና ከእሳትና ከነፋስ ያልተፈጠሩ መሆኑን ለማስረዳት " መላእክት ከእሳትና ከነፋስ ተፈጥረውስ ቢሆን ኖሮ እንደኛ በሞቱ ነበር " በማለት ሞት ለባህርያቸው የማይስማማ መሆኑን ያስረዳል ::

በሌላም በኩል ጌታችን ለምን የመላእክት አካል ነስቶ አላዳነንም የሚለውን ሊቃውንት ሲያብራሩ " መላእክት ሞት በባህርያቸው የለባቸውምና አካላቸው (ተፈጥሮአቸው ) ለካሳ አይመችምና " በማለት ያስረዱና ።

እውነት ነው የአደም እና የሳጥናኤል በደል ተመሳሳይ ነው እርሱም አምላክነትን መሻት ነው ማወዳደር ካስፈለገም የሳጥናኤል በደል ይበልጣል ምክንያቱም አዳምስ ቢበድል ሳጥናኤል ምክንያት ሆኖት ነው ሳጥናኤል ግን በደልን ከልቡ አመንጭቶ ነው ነገር ግን የበደሉት ተመሳሳይ በደል ሆኖ ሳለ ሳጥናኤል አዳም ያገኘውን አይነት የአካል ሞት አላገኘውም ለምን ቢሉ ሳጥናኤል መልአክ እንደመሆኑ ተፈጥሮው (ባህርያው ) ሞት የማይስማማው በመሆኑ ነው ።

ስለዚህ አዳም ቀድሞም ከበደል በፊት ሞት ለባሕርይው የሚሰማማ ነበር ነገር ግን እንደ መላእክት ሕያው ሆኖ እንዲኖር እንጂ እንዲሞት አልተፈጠረም ነበር በበደለ ጊዜ ግን ለባህርይ ትስማማው የነበረ ሞት ሰለጠነበት ለዚህም " እግዚአብሔር ሞትን አልፈጠረምና ነዋሪ ይሆን ዘንድ ፍጥረትን ፈጥሯልና የሰዎች ጥፋት ደስ አያሰኘውምና " ( መጽ ጥበ1፥13 ) ። ይለናል ነገር ግን " በዲያብሎስ ቅንዓት ሞት መጣ ወደዚህ ዓለምም ገባ " ( መጽ ጥበ 2 ፥24 ) ።
" ስለዚህ ምክንያት ፥ ኀጢአት ባንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ ፥ በኀጢአትም ሞት ፤ እንደዚሁም ሁሉ ኀጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ " (ሮሜ 5 ፥ 12 )

-> በዚህ የምንረዳው ከበደል በፊት ከመልአካዊም በላይ በአምላካዊ አምሳል ሕያው የነበረው ባሕርያችን በበደል ምክንያት ሞት ቢሠለጥንብን ባሕርያችን የጎሰቆለ ሆነ ይህ ሁሉ ግን የሆነው ባህርያችን ሞት የሚሰማማው በመሆኑ ነው፡፡

በቀጣይ ጌታ ቢፈቅድ ብንኖር በበደላችን ምክንያት እንዲሰለጥንብን ያደረግነው ሞት በክርስቶስ ሞት ስልጣኑ መሻሩን እና ዛሬ የሞት አገልግሎት ሌላ መንገድ መያዙን እንመለከታለን ። ይቆየን
✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

09 Feb, 19:35

3,905

#ነቢዩ_ዮናስ_እና_ኪዳነ_ምህረት
#ነነዌ_እና_እኛ

👉 ዮናስ ለነነዌ ሰዎች መዳን ግድ አስፈላጊ ነበረ ለዚህም ነው ዮናስ ወደሌላ አገር ሸሽቶ ሊሄድ ቢፈልግም እግዚኣብሔር ግን በግድ ወደ ነነዌ ሰዎች እንዲሄድ ያደረገው። ለፍጥረትም መዳን እመቤታችን ግድ አስፈላጊ ሆናለች (የነነዌ ሕዝብ የዳነው ከራሱ ወገን ለነቢይነት የሚበቃ ሰው ባለመገኘቱ ሁሉ በደለኛ በመሆኑ ከሌላ አገር ከነቢያት ሁሉ ተለይቶ ተመርጦ ገሊላዊው ነቢዩ ዮናስ እንደተላከላቸው /፪ኛ ነገ.፲፬፡፳፭/፡፡

ከሰው ወገንም ሁሉ በደለኛ ሆኖ ሳለ ለዓለሙ ሁሉ መዳን ምክንያት እንድትሆን ገሊላዊቷ እመቤታችንን ከፍጥረቱ ሁሉ ለይቶ በንጽሕና እንድትጠበቅና ለእናትነን እንድትበቃ አድረጎ ከእርስዋ በነሣውም ሥጋ ዓለሙ አድኖባታል። ስለዚህም ነው የባህሪያችን መመኪያ የምንላት።

👉 ከዮናስ አንደበት በተገኘ በተነገረ ቃል ንጉሡ ጨምሮ መላው ሕዝብ ሁሉ በንስሓ እንደዳነ ከእመቤታችንም " ቃል ሥጋ ሆነ በእኛ ላይም አደረ " እንደተባለ እግዚኣብሔር ቃል ሰው ሆኖ የሰው ልጅን ሁሉ አድኗል። ( ዮሓ ፩፥፲፬)

👉 የዮናስን ስብከት አሕዛብ የሆኑ የነነዌ ሰዎች መቀበላቸው ይኽ ደግሞ አሕዛብ ክርስቶስን እንደሚቀበሉት በሃይማኖትም እንደሚድኑ ያሳውቃል ::

👉 በተጨማሪም አሕዛብ አሚነ ክርስቶስን እንደሚቀበሉና አይሁድ ከአሚነ ክርስቶስ እንደሚወጡ በነነዌ ሰዎች ተረጋግጧል። ቅዱስ ጄሮም ይህንን ሲገልጽልን “ አይሁድ ፍርድን በራሳቸው ላይ ጨመሩ፤ አሕዛብ ግን እምነትን ገንዘብ አደረጉ፡፡ የነነዌ ሰዎች በንስሓ ወደ አምላካቸው ተመለሱ፤ የእስራኤል ሰዎች ግን ንስሓ ባለ መግባታቸውና በጠማማ መንገዳቸው ስለጸኑ ጠፉ፡፡ እስራኤል መጽሐፍትን ተሸክመው ቀሩ፤ የነነዌ ሰዎች (አሕዛብ) ግን የመጽሓፍቱን ጌታ ተቀበሉት፡፡ እስራኤላውያን ነቢያት ነበሯቸው፤ የነነዌ ሰዎች ( አሕዛብ) ግን የነቢያቱን ሐሳብና መልእክት ገንዘብ አደረጉ፡፡ የእስራኤል ሰዎች ፊደሉ ገደላቸው፤ መንፈስ ግን የነነዌን ሰዎች (አሕዛብን) አዳናቸው፡፡” ብሎናል።

👉 ስለዚህም ነው ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም፡-  “የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚኽ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና” ያለን /ማቴ.፲፪፡፵፩/፡፡

👉 የነነዌ ሰዎች በዮናስ አንደበት የተነገረ ቃል ለንስሓ በቅተው ሳለ እኔ በክርስቶስ አንደበት የተነገረች ወንጌልን እየሰማሁ እንዴት ለንስሓ አልበቃሁም ብለን በራሳችን ፈርደን ንስሓ እንግባ ይህን ካላደረግን ግን ጌታችን እንዳለው የነነዌ ሰዎች ይፈዱብናል። ቸሩ መድኃኔ ዓለም ለንስሓ ያብቃን ኪዳነምህረት በአማላጅነት አትለየን🙏

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

09 Feb, 19:33

2,819

እንኳን ለጾመ ነነዌ አደረሰን

ስለ ጾሙ አጭር ማስገንዘቢያ እንሆ፡- ይህ ጾም በነቢዩ ዮናስ ተመክረው የነነዌ ሰዎች እና በእነርሱ ዘንድ ያሉ እንስሳትም.... ሳይቀሩ ከምግብ የተከለከሉበት ( የጾሙት) ጾም ነው፡፡ (ት.ዮና ምዕ.3)

- እንደ ዓቢይ ጾም ሰኞ ዕለትን አይለቅም ለ3 ዕለታት የሚጾም ነው።

- ይህ ጾም የሚጀመርበት መደበኛ ዕለት የለውም፡፡ ነገር ግን በጣም ወረደ ከተባለ ከጥር 17 በታች አይወርድም በጣም ወጣ ከተባለም ከየካቲት 21 አያልፍም በእነዚህ 35 ዕለታት ውስጥ እየተመለላሰ ይደርሳል፡፡


✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

28 Jan, 15:45

5,122

✥✥✥ አስተርእዮ-ማርያም ✥✥✥

" ማርያም ሞትኪ ይመስል ከብካበ "

" ድንግሊቱ የተፈጥሮን ሞት እንጂ የአዳምን ሞት አልተቀበለችም "

. የፍጥረታት ሁሉ ባለቤት የሆነው አምላካችን የቅርብ አገልጋዮቹ ከሆኑ ከሰማያውያን ከኪሩቤልና ከሱራፌል ይልቅ የመወደድና የመከበር ጸጋን አድሏታል ምክንያቱም የነሳው የእርሷን እንጂ የእነርሱን ሥጋ አይደለምና። (ዕብ 2፥12 )

. ወላድያነ ሰብእ ከሆኑ ከምድራውያን ፍጥረታትም ወላዲተ አምላክ በመሆን የተለየች " ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች " ናትና የልዕልናዋ መሠረትም ይህ ነው ::

. ይሁን እንጂ ሰው በመሆን የሰውነትን ሥራ ሁሉ መፈጸም ስላለ ወደ ላይኛው ሕይወት መሸጋገሪያ በሞት በኩል በትንሳኤ ስለሆነ " ሞትን ተቀብላለች " ። በዚህም ‹‹ለመለኮት ማደርያ ለመኾን የበቃችው ' ኃይል አርያማዊት ' ብትኾን ነው እንጂ ምድራዊት ሴትማ እንደምን ሰማይና ምድር የማይችለውን ልትሸከመው ይቻላታል?›› በማለት ሰው መሆንዋን
ለሚጠራጠሩ '' ሰው መሆንዋን " ተገልጧል።

👉 ፈጣሪ አዳምን ‹‹ዕፀ በለስን በበላህ ጊዜ የሞት ሞትን ትሞታለህ›› ያለውን ዘንግቶ ዕፀ በለስንም በልቶ የመጣበትን ሞት ድንግሊቱ የሞተች አይደለችም እርስዋስ የአዳምን (የበደልን) ሞት ሳይሆን የተፈጥሮ ሞትን ተቀብላለች፡፡ የተፈጥሮ ሞት የምንለው የሰው ልጅ ሲፈጠር ሞት እንዲሰለጥንበት ሆኖ ባይፈጠርም ሞት ግን ለባህርይው የሚስማማው ሆኖት ነው የተፈጠረው ከበደል በፊት ለባህርይው ይስማማው የነበረው ሞት ግን አልሰለጠነበትም ነበር ሕግን ተላልፎ ዕፀ በለስን በበላ ጊዜ ሞት የሚሰለጥንበት ሆነ ድንግሊቱ ግን ሕግን በመተላላፍ በአዳም በኩል የመጣውን ‹‹የሞት ሞትን ትሞታለህ›› የተባለው መርገም ስላልደረሰባት የበደል ሞትን ሳይሆን የተፈጥሮ ሞትን ተቀብላለች «ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዓጽብ ለኲሉ -ሞት ለሚሞት /ለሟች/ ይገባል የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል» (ቅዱስ ያሬድ)

- ለዚህም ነው የድንግል ማርያም ዕረፍት በመላአክት ምሥጋና በዳዊት ዝማሬ የታጀበ ስለነበር ሊቁ ይህንን ለመግለጽ "ማርያም ሞትኪ ይመስል ከብካበ" ማርያም ሆይ ዕለተ ዕረፍትሽ ደስታ የበዛበት ሠርግን ይመስላል አለ።

- ይህ ቢሆንም እስከ ዕለተ-ምጽአት ድረስ ግን በመቃብር እንድትጠብቀው አላደረጋትም እነአልዓዛር በተነሱበት ትንሳኤ ሳይሆን እንደልጅዋም ባለ ትንሣኤ በክብር እንድነትነሳና እንድታርግ አደረጋት ይህም የእግዚኣብሔር ድንቅ ሥራ ነውና በዚህም የእናቱን ክብር ገለጠ ፡፡ ( መዝ 131፡8 )
የእመቤታችን በረከቷ ፣ልመናዋና ጸሎቷ ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን !

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ

https://t.me/+VBt2ld_HeykCaELL (ቴሌግራም ቻናል )

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

25 Jan, 09:52

4,322

✥✥✥ዝርወተ ዐጽሙ ለማር ጊዮርጊስ✥✥✥

✥ ጥር ፲፰ ዕለት ለሰማዕቱ "ዝርወተ አጽሙ " ትባላለች:: በቁሙ አጥንቱ የተበተነበት እንደ ማለት ነው።

" ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም ናቁ ስለ መንግሥተ ሠማያትም መራራ ሞትን ታገሡ። " እንደተባለ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለዘመናት በብዙ ስቃያት ሲያስጨንቁት ኖረው በጽናቱ አሸነፋቸው:: 70 ነገሥታትን ከነ ሠራዊታቸው ከማሳፈሩ ባሻገርም በርካታ (በመቶ ሺ የሚቆጠሩ) አሕዛብን ማርኮ ለሰማዕትነት አበቃ::

✥ በዚህ የተበሳጨ ዱድያኖስም ኮከበ ፋርስ ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲቆራርጡት አዘዘ:: ወታደሮቹም ቅዱሱን ቆራርጠው በብረት ምጣድ ላይ ጠበሱት። ያለ ርሕራሔም አካሉን ኣሳረሩት። ቀጥለውም ፈጭተው ዐመድ አደረጉት። በኣካባቢው ወደ ነበረው ትልቅ ተራራ ጫፍ (ደብረ ይድራስ) ወጥተውም በነፋስ በተኑት:: “ሐረድዎ ወገመድዎ ወዘረዉ ሥጋሁ ከመ ዓመድ” እንዲል:: (ምቅናይ)

✥ እነርሱ ይህንን ፈጽመው ዘወር ሲሉ ግን የቅዱሱ ዐጽም ባረፈባቸው ዛፎች: ቅጠሎችና ድንጋዮች ሁሉ “ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት” የሚል ጽሑፍ ተገኘ:: ስለዚህም ይህቺ ዕለት ቅዱሱ አለቅነትን የተሾመባት ናት ማለት ነው:: ወዲያው ግን ኃያል ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተበተነበት ተነስቶ ወታደሮችን አገኛቸውና “በክርስቶስ እመኑ” ብሎ አስደንቆ ወደ ሕይወት መራቸው፣ ፸ ው ነገሥታት ግን አፈሩ። ሰማዕቱ አባታችን እኛንም በሃይማኖት በምግባር ያጽናን ተራዳኢነቱም አይለየን አሜን። 🙏

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ 

https://t.me/+VBt2ld_HeykCaELL (ቴሌግራም ቻናል )

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

19 Jan, 05:57

4,550

✝️ ታቦት በሄደበት አይመለስም

ታቦት በሄደበት አይመለስ ብለው ያወጁት አፄ ዘርዓ ያዕቆብ እንደሆኑ ይነገራል
ለዚህም ምክንያት የሆነው ታቦት የሚወጣው ለመባረክ ለመቀደስ በመሆኑ በሄደበት ከሚመለስ በሌላ መንገድ ተመልሶ ያልባረከውን እንዲባርክ በማሰብ ነው (ነገር ግን መመለሻ የሚሆን ሌላ መንገድ ከሌለ በሄደበት ይመለሳል) ።

እውነት ነው በዚህ የጥምቀት በዐል " የእግዚአብሔር ታቦት የገባበት ስፍራ ቅዱስ ነውና " 2ዜና 8፥11 ተብሎ እንደተነገረው ታቦት የሚሄደበት ቦታ እና የሚያርፍበትን ስፍራ ሁሉ የኢትዮጵያን ምድር እንደሚቀድስ እና ከሀገሪቱ ላይ ወረርሽኝ ... አጋንንትን እና የእነርሱን አሠራር ሁሉ እንደሚያርቅላት እናምናለን ።

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ 

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)