35ኛ ሳምንት
5ኛ ቀን
ባለጠጋ ለመሆን የሚፈልጉ ግን ወደ ፈተናና ወደ ወጥመድ፣ እንዲሁም ሰዎችን ወደ መፍረስና ወደ ጥፋት ወደሚያዘቅጠው ወደ ብዙ ከንቱና ክፉ ምኞት ይወድቃሉ። ምክንያቱም የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው። አንዳንዶች ባለጠጋ ለመሆን ካላቸው ጕጕት የተነሣ ከእምነት መንገድ ስተው ሄደዋል፤ ራሳቸውንም በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።
1 ጢሞቴዎስ 6፥9-10
ይህ ቃል በሕይወት መንገድ ላይ እየከነፉ በብልጽግና አውራ ጎዳና ላይ ወጥተው እየፈረጠጡ ላሉት ሰዎች በትልቅ ፊደላት ጎልቶ ተጽፎ ከመንገዳቸው ዳር ተተክሎ የምትሄዱበት መንገድ ወደ ድሎት ሳይሆን ወደ ጥፋትና ስቃይ የሚወስድ ነው የሚል ማስጠንቀቂያ ነው።
ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ያሉት አማኞች በብልፅግና ምኞት ተወግተው ከእምነት ስተው መዳረሻው ጥፋት እንዳይሆን ጢሞቴዎስን አስጠንቅቃቸው በማለት ያዘዋል።
የብልፅግና ትምህርት በቤተክርስቲያን ውስጥ መሰበክ ከተጀመረ ሰዎች ተስፋቸውን በክርስቶስ ላይ ሳይሆን በሚጠፋ ምድራዊ ሃብት ላይ እንዲያደርጉ ያስታቸዋል።
ዓለማዊ ምኞትን እንዲክዱ ሳይሆን ይባሱኑ ስስትና መጎምጀት እንዲያይልባቸው ያደርጋል። ነፍሳቸውን በምኞት ባህር ውስጥ በማስጠም ኑሮዬ በቃኝ ከሚለው የአመስጋኝነትን ሕይወት ነቅሎ በማጉረምረም ጥላ ሥር ያኖራቸዋል።
በቤተክርስቲያን አዳራሽ ውስጥ የሚሰብኩት የብልፅግና ዲስኩሮች በክርስቶስ ስምና አውዱን በሳተ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ስለሚሸፈኑ እጅግ አደገኛና አሳች ናቸው።
እነዚህ የገንዘብ ሰባኪዎች ተከታዮቻቸውን ቀስ በቀስ በመስቀል ላይ የሞተላቸውንና ነፍሳቸውን ያዳናቸውን ኢየሱስን ከልባቸው ላይ ፍቆ የሚፈልጉትን በመስጠት የሚባርካቸውንና ምኞታቸውን ለሟሟለት እንደ ካፌ አስተናጋጅ ጎንበስ ብሎ የሚታዘዝላቸውን ሌላ ኢየሱስ በራሳቸው አእምሮ ውስጥ ፈጥረው እንዲያመልኩ ያደርጓቸዋል።
በዚህ የብልፅግና ምኞት የተጠቁት አማኞች አመስጋኞች መሆን አይችሉም፣ እርካታ የላቸውም፣ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው አይነት መርህ የሚከተሉ ናቸው። አምጣ እንጂ እንካ ጨርሶ አያውቃቸውም።
በተለይ በዚህ ዘመን ያሉት ሰዎች ይህ የስስት ካንሰር እንደ ወረርሽኝ ስለገባባቸው ሃብት እናገኝበታለን ብለው ያሰቡትን ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ወደ ኋላ አይሉም።
የዛሬው ንብረት ማከማቸት እንጂ የነገው ተጠያቂነት ግድ አይሰጣቸውም። ሁሉን ነገር የሚያደርጉት እራሳቸውን ማዕከል አድርገው ነው። የሌሎች ሕይወት ይጎዳ ይሆን፣ እግዚአብሔር ምን ይለኛል፣ ቅድስናዬን ያጎድፋል ወይ ብለው በጭራሽ አያስቡትም።
አንድ ሰው በሕይወት ዘመኑ ያከማቸውን ንብረት አንዱንም ከሞት ወንዝ ማሻገር አይችልም። እራቁታችንን እንደ ተወለድን ራቁታችንን እንቀበራለን። ከሞት በስቲያ የሚጠብቀን ሃብት ለድሆች ያካፈልነውና ለወንጌል አገልግሎት የሰጠነው ንብረት ብቻ ነው።
ወገኖቼ! የልግስና እንቅፋት የብልፅግና ምኞት ነው። መሰብሰብን ብቸኛው የሕይወታቸው መርህ አድርገው ለሚኖሩ ሰዎች መቆረስ እንግዳ ቋንቋ ነው። ሆኖም ግን ገዳይ ከሆነው የስስትና የመሰብሰብ በሽታ የሚያድነን ብቸኛው መድኃኒት በልግስና መስጠት ነው።
ሕይወትን ትርጉም ያለውና ጣፋጭ የሚያደርገው መቀበልና መሰብሰብ ሳይሆን መስጠትና ማካፈል ነው። ውስጣችን የሚረካው ለተቸገሩት ስናካፍል ነው።
የብልፅና ምኞትና የገንዘብ ፍቅር ነድፎን ከሕይወት መስመር እንዳያስተን የልግስና መጠናችንን ከፍ በማድረግ ነፍሳችን እንድናተርፍ ጌታ ማስተዋሉን ያብዛልን።
ዛሬ የማሰላስለው እውነት፦ ከባለጠግነት ምኞትና ከገንዘብ ፍቅር የመጠበቅ ጥሪ ከሞት የመጠበቅ ያህል አንገብጋቢ ጥሪ ነው።
የዛሬው ፀሎት፦ እግዚአብሔር ሆይ ልቤን ከሚመርዘው አፍቅሮተ ንዋይና የብልፅግና ምኞት በቃልህ ልቤን መጠበቅ እንድችል እንድትረዳኝ እለምንሃለሁ። አሜን!!!
መልካም ቀን!!
@artios_media
@artios_media
@artios_media