ሱሉልታ የካቲት 10/2017 ዓ.ም (አፍሌክስ)- አፍሌክስ ለባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር አመራሮች እና ባለሞያዎች መስጠት በጀመረው 2ተኛ ዙር የአመራር ልማት ስልጠና 270 የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመራሮች እና ባለሞያዎች ተሳታፊ መሆን ችለዋል።
የሃገሪቱን ተቋማት የአመራር ብቃት ለማሳደግ በመስራት ላይ የሚገኘው አፍሌክስ ከባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ፤ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመራሮች እና ባለሞያዎች 2ተኛ ዙር ስልጠና በአመራር ልማት ማዕከሉ መስጠት ጀምሯል።
ስልጠናው የአመራሩን ብቃት በማጠናከር ኪነ ጥበብ፣ ባህል፣ እና ስፖርት ለሃገር አንድነት እና ብልጽግና ያላቸውን ሚና አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።
በመክፈቻ ስነ ስርዐቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የባህልና ስፖርት ሚኒስትሯ ክብርት ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ “የዚህ ስልጠና ዋነኛ አላማ ባህልና ስፖርትን ለሃገረ መንግስት ግንባታ ለማዋል የሚያችለንን አቅም ማሳደግ ነው።” ብለዋል።
አያይዘውም ያደጉ ሃገራት ገጽታቸውን ለመገንባት ከተጠቀሙባቸው መሳሪያዎች መካከል ባህልና ስፖርት ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ “ኢትዮጵያ ያሏትን ቱባ ባህሎችም ሆነ የስፖርቱን ዘርፍ ለሃገራዊ አንድነት እና ገጽታ ግንባታ ለማዋል ሃላፊነታችንን እየተወጣን ነው ወይ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።” ሲሉ ተናግረዋል።