ህዳር 6/2017 ዓ.ም
+++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
ከህዳር 3-6/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ሲካሄድ የቆየው 9ኛው ሃገር አቀፍ የሳይንስና ምህንድስና የፈጠራ ስራዎች ውድድር በተማሪዎችና መምህራን የተሰሩ የፈጠራ ስራዎች ለእይታ የቀረቡበት ነበር፡፡ ለተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው ውድድር አሸናፊ የሆኑ የፈጠራ ስራዎችን እና ማዕከላትን በመሸለም ተጠናቋል፡፡
ዶ/ር ቀናቱ አንጋሳ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አሳታፊነት ዳይሬክተር ይህ ውድድር በዩኒቨርሲቲው ለአራተኛ ጊዜ የተዘጋጀ መሆኑን በመጥቀስ ይህም ዩኒቨርሲቲው ለሳይንስ፤ቴክኖሎጂ፤ምህንድስና እና ሂሳብ ትምህርት ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ይህን የመሰለ የሳይንስና ምህንድስና ውድድር መደረጉ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችን ለማግኘት መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አጋር አካላት በዚህ ዘርፍ ላይ ተባብረው መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በማጠቃለያ መርሃ-ግብሩ ላይ በተለያዩ ዘርፎች ከ1ኛ እስከ 3ኛ ለወጡ ተወዳዳሪዎች የማበረታቻ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል ፡፡
ይህን ውድድር በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለአበረከቱ ተቋማት አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፤ስቴም ፓወር፣ ስቴም ሲነርጂ፣ጃይካ እና ትምህርት ለኢትዮጵያ የተሰኙ አጋር አካላት ለአደረጉት አስተዋጽኦ የምስጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡