አሪቲ ጎፈሬ ፡ ቄጠማ ከመከም፣
ያስራ አንዱን ደዌ ፡ ዳብሼ ልታከም
ተውረግርጋ መጣች፡ ኮረዳ መስከረም።
የሰኔ ምንጣፍ ላይ
ሃምሌን ተንተርሳ
ነሀሴዋን ለብሳ
ባያት ደሜ ሞቀ፡
አምና መጣች ብዬ
ጥላኝ መኮብለሏ፡ ካቅሌ ላይ ተፋቀ።
ጣለኝ ያልኩት ገዴ፡ ቅኔ ቀን ሲያዝብኝ፡
ጭቃዋ ላይ ወደቅሁ፡ አደይ በቀለብኝ።
ኮረዳ መስከረም...
ይቺ በላዔ-ሰብ
ይቺ ድራኩላ...
ይቺ ድራ ኩላ
የዘመን መንትያ
ክራንቻዋን ስላ፡
ያረጁ ዐይኖቿን
እንደልጅ ተ´ኩላ
አምናና ካቻምና
ያስተረፈችውን
እድሜዬን ልትበላ፤.
መጣች እፍረት የላት
መጣች ረፍት የላት።
እሷ ምን ቸገራት?
ደንግላ ስትመጣ
አቅፌ የምለቀው
ቆዳዋ ይፋጃል...
እሷ እየታደሰች
እሷ እየደምቀች
የኔ ቀን ያረጃል።
መጣች ነጋ ደግሞ
መጣሽ ነጋ ደግሞ...
ኮረዳ መስከረም...
አወይ ጅል መሆኔ
ጡትሽን ማመኔ
ዳሌ ቅንፍሽን
ልታቀፍ ማለሜ፡
ለሚሸሸኝ ገላ
እድሜ መሸለሜ፡
ባከምሽኝ በወሩ
አርጅተሽ ስትሄጂ
ደግሞ መታመሜ፣
በያመት ስትደምቂ
በያመት መክሰሜ።
መስከረም ኮረዳ
ውበትሽ ሊከዳ
ሊሄድ ሊሸሽ ገላሽ
ለምን ይሞቀኛል
ደስ ደስ ይለኛል
አካለ ቢስ ጥላሽ?
ኮረዳ መስከረም
ምን አለሽ አደንዝዝ
ያምና ክዳትሽን
ካይምሮ የሚደልዝ
«ነበር!» የሚያስረሳ
የወደቀን ፍሬ
አብዝቶ ሚያስነሳ፤
ያበረድሽው ደሜን
ከራርሞ የሚያግል
ዝንትዓለም ተኝቼሽ
ያስመሰለሽ ድንግል።
አፍዝ ምን አለሽ?
መስከረም ኮረዳ፡
በአሮጊት እስትንፋስ
በልጅ ልስልስ ቆዳ፣
የሚያውረገርግሽ
ችክችካ ድለቃው
ሄደሽ ተደምስሶ
ትዝታ እስኪቀዳ፡
እንደ አምና ካቻምናው
እስክንከዳዳ፡
እድሜ ምናባቱ
ይሄው ረጲሳ
ይኸው ረገዳ።
(ቼቼ... ሼሼ... ቼቼ)