አባታዊ መልዕክት !
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የ2017 ዓ.ም የጾመ ነነዌ የሰላምና የጸሎት አዋጅ መግለጫ ሰጥተዋል።
ከመግለጫቸው የተወሰደ ፦
" ለችግሮች ሁሉ መፍትሔ አላቸው፤ መፍትሔውም የሚገኘው ከእግዚአብሔርና ከእኛ ነው፤ ከእኛ በንስሓ ተመልሰን ከልብ እግዚአብሔርን ይቅርታ መጠየቅና ከክፉ ተግባራችን በእውነት መጸጸት ይጠበቃል፤ እግዚአብሔር ደግሞ ይህንን ዓይነቱ ንስሓ ከኛ መኖሩ ሲመለከት ምሕረትና ይቅርታን ይለግሰናል፤በዚህም መፍትሔና ፈውስ ይገኛል።
ከዚህ አንጻር በአሁኑ ጊዜ ለሀገራችንና ለዓለማችን ስጋት የሆኑ የጦርነት ክሥተቶች፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የአየር መዛባት፣ የድርቅ መከሠት፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ የሰላም መደፍረስ፣ የሰላማውያን ወገኖች መጎዳት፣ የፍቅርና የአንድነት መላላት ወዘተ. . . . ከምድራችን ተወግደው ፍጹም ምሕረትና ሰላም እናገኝ ዘንድ በኃጢኣታችን ተጸጽተን በምህላ ንስሓ መግባት አለብን።
ከዚህ አኳያ ከጥንት ጀምሮ በቤተክርስቲያናችን ቀኖናዊ ሥርዓት መሠረት በየዓመቱ የሚጾመው ጾመ ነነዌ ለዚህ አመቺ ጊዜ ስለሆነ ከየካቲት 3 ቀን 2017 ዓመተ ምሕረት ጀምሮ ለሦስት ቀናት ከልኂቅ እስከ ደቂቅ ሁላችንም ጠዋትና ማታ በየቤተክርስቲያኑ ዐውደ ምሕረት እየተገኘን በንስሓ በዕንባ በጸሎት በምህላ የእግዚአብሔርን ምሕረትና ይቅርታ እንድንጠይቅ፤ እንደዚሁም በሀገራችንና በውጭ ያላችሁ ሊቃውንተ ሕዝብ ቀኖናውን ጠብቃችሁ ይህንን በማስፈጸም ምህላውን በቀኖናው መሠረት እንድታከናውኑ በእግዚአብሔር ስም አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን። "
(የቅዱስነታቸው ሙሉ መግለጫ ከላይ ተያይዟል)
@tikvahethiopia