ጥር 22 / 2017 ዓ.ም - የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ከየካቲት 1 አስከ 2 / 2017 ዓ.ም ለሁለት ቀናት በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ያደርጋሉ፡፡
ባለስልጣኗ ከከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት የሚያደርጉ ሲሆን ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ እ.ኤ.አ በ2019 የተቋሙ ኀላፊ ከሆኑ በኋላ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያቸው መሆኑ ታውቋል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር በኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ ቅድሚያ በሚሳጣቸው ፖሊሲዎች እና በኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ዙሪያ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ዳይሬክተሯ በጉብኝታቸው ወቅት ከግሉ ዘርፍ ተወካዮች ጋር በኢትዮጵያ ስላለው የንግድ ሁኔታ እና በኢኮኖሚ እድሎች ዙሪያ ውይይት የሚያካሂዱ ከመሆኑም በተጨማሪ በሀገሪቱ በማህበራዊ ልማት የተሰሩ ስራዎችን እነደሚጎበኙ ታውቋል፡፡