ሀበሻ 🇪🇹 @habeshaethiopia7 Channel on Telegram

ሀበሻ 🇪🇹

@habeshaethiopia7


🇪🇹 ኢትዮጽያዊነታችንን የምናሳይበት 🤝 አንድነታችንን የምናጠነክርበት 🥰 ፍቅርን የምንማርበት ቻናል ነው ።
☞☞ @Ferhanhabesha

ሀበሻ 🇪🇹 (Amharic)

ሀበሻ 🇪🇹 በኢትዮጽያዊነታችን እና በአስተዳዳሪ ማህበረሰብ ላይ ያለው አገልግሎት ነው። ይህ አገልግሎት የሚፈውሱትን ሱስና ልፌት የሚሳቡትን ፍቅር ላይ የሚጠነከሩ ነው። እኛም ይህን አገልግሎትን ያሳኮኑ እና የእኛን በዓል እንቅስቃሴ እንያስከብራት። ከዚህ በፊት ተጨማሪ እንዲህ-እንዲሳቁ ይጠቁም።nለተጨማሪ አርሴሽን ያለባቸውን የሀበሻ አገልግሎቶችን ያገኛሉ። ከጠቅላላ ፊት የተለያዩ እና ተፈላጊ አይነቶችን ለማስተምረያ እና የሚረዱበት ነገር ማስከበራ እና መጠቀም እንደሚችሉት ይጠቀሙ። ይህ አገልግሎት ከታችኛው ወይም ከቆሞው የሚፈጥሩት ምንጮችን የሚቀበሉ አገልግሎቶች ናቸው። ስለሚይስፍ ተጀምሯን: @Ferhanhabesha

ሀበሻ 🇪🇹

01 Jan, 17:17


አርቲስት ጌትነት እንየው

አምነው የወደዱ፣
ወደው የተካዱ፣
ተክደው የራዱ፣
ፍርሃት አንሸራቶ ቁልቁል የጣላቸው፣
የብቸኛ ልቦች የትነው መውደቂያቸው?
የትነው መድረካቸው?
ማነው አጃቢያቸው?
እንዴት ነው ምታቸው?
የተካዱ ልቦች አጋር የራቃቸው፣
የሚያቀነቅኑት ምንድን ነው ዜማቸው?
የተመረኮዙት እምነት ታጥፎባቸው፣
ድንገት የወደቁ ፍቅር ያዳጣቸው፣
ሚስጥር የሚያጋሩት ሰው የበረዳቸው፣
ብቸኝነት ሰርጎ ብቻ ያስቀራቸው፣
ዝምተኛ ልቦች ምን ይሆን ቋንቋቸው?
ከየት ነው ጥሪያቸው?
በየት ነው ጉዟቸው?
የት ነው መድረሻቸው?
እንደ ሰብአሰገል ጠቅሶ የሚመራቸው፣
የቃተቱ ልቦች የታል ኮከባቸው?
መቼም ከአምላክ ትንፋሽ ከውሃ ከአፈሩ፣
ከእምንት እና እውነት ከፍቅር ሲሰሩ፣
ዝምተኛ ልቦች ጥንቱን ሲፈጥሩ፣
ተገፍትረው ወድቀው፣
ደቀው እንዳይቀሩ፣
በተስፋ ጸንተው ነው ዘላለም ሊኖሩ።

ሀበሻ 🇪🇹

29 Dec, 08:43


ትላንት ሌሊቱን መነጋገሪያ ነበር እናቱ በጠና የታመመችበት አይመስልም እየጀነጀናት መስሏታል የወጣትነት እድሜ አብሯት እየተሳሳቀ ነው የእናቱን ሂሳብ ሊያወራርድ ነው በሆቴሉ የተገኘው የሆቴሉ እንግዳ ተቀባይ ጋር ወሬያቸው ሞቅ ብሏል። አንድ የ26 አመት ወጣት ከፊትለፊቷ ጃኬት ተጀቡኖ ከፊቷ ቆሞ እያወሩ ነው።

ከቀናት በፊት የሊዩጂ ኒኮላስ እናት ይታመማሉ ታድያ በአሜሪካ የህክምና ወጪ ከእኛም ሃገር በበለጠ እጅጉን ውድ ነው ለዚህም ተብሎ የተለያዩ የመድህን ( Insurance ) ተቋማት በዚህ የጤና ዘርፍ ቢሰማሩም ላለመክፈል ግን ሰውን ያንገላታሉ።

የሊዩጂ እናትም ታማ የደረሳት ነገር ቢኖር እንግልት ነበር በዚህም እናቱ በጣም ስትሰቃይበት ጊዜ ሊዩጂ ኒውዮርክ ውስጥ በሚገኘው ሆቴል አመታዊ የመድህን ድርጅቶች ስብሰባ ላይ የተንገላታበትን የአሜሪካ መድህን ድርጅት ዋና ሃላፊ ብሪያን ቶምሰንን ለመግደል ያስባል።

ታህሳስ 9 2024, ኒውዮርክ ሆቴል ውስጥ በመገኘት ከእንግዳ ተቀባይ ሴት ጋር ወሬያቸውን ያደሩታል እርሱ ብሪያን እየጠበቀ ያወራታል። እርሷም በወሬው መሃል ፈገግታዋን እየሰጠችው ማስክህን አውልቅ እስኪ ስትለው ያወልቅና ፈገግ ካለላት በውሃላ መልሶ ያደርገዋል። ከሆቴሉም ወጥቶ በረንዳው ላይ ብሪያንን ጠብቆ ይገለዋል። ከዛም ወደመጣበት በመመለስ ሳለ በዛች ማስኩን ባወለቀበት ቅፅበት ያለችው ምስሉ በካሜራ በመያዙ ፖሊሶች እጅ ይገባል።

ተመልከት ምስሉ ላይ ያለችው እናቱ እንዳትመስልህ ካረን ፍሪድማን ትባላለች። መቼም ላምበርጊኒ መኪና ሲባል ሰምተህ ታውቃለህ የአምራች ድርጅቱ እሳት የላሰች በረዶ ፈልጣ ቤተመንግስት አፋር ላይ ያቆመች ጠበቃ ናት። አሁን ደግሞ ለሊዩጂ ጥብቅና ቆማ ከወንጀሉ ነፃ ልታወጣው ተሰይማለች።

ከአሜሪካኖች ሁለት ነገራቸው ይገርመኛል የፍትህ ነፃነት ስርአታቸው።

ግርምት አንድ ፍትህ

ብሪያንን የገደለበት የቪዲዮ ማስረጃ አለ ግን ሊዩጂም ትላንት ፍርድቤት ሲቀርቡ ሽምጥጥጥ አድርገው ክደዋል ጠበቃዋም ነፃ እንደምታወጣው ታምናለች።

ግርምት ሁለት ነፃነት
አሜሪካ ውስጥ የጠበቆች ክፍያ እና ነፃ ሲወጣ እንዳይቸገር ተብሎ GoFundMe እየተሰበሰበለት ሲሆን አሁን ያለበትን ባላቅም በመጀመሪያ ቀን ነበር ግን $150,000 ዶላሮችን ያለፈው። ከዚህ በላይ አሜሪካኖቹን በየመንገዱ እያቆመ የጠየቀው SkyNews ሁሉም ተጠያቂዎች ሊዪጂ ልክ ሰርቷል የሚሉ ሲሆኑ ጭራሽ ቦስተን ውስጥ ኮንሰርት ተዘጋጅቶ ለሱ አዲስ ሙዚቃ ተዘፍኖለት ነበር።

እኛ ሃገር ቢሆንስ ኖሮ. . . እስክንደርስባቸው ለሌላ ሃገር ፍትህ እንጠይቃለን ፍትህ ለሊዪጂ

(✍️ፕ/ር ሔኖክ አረጋ)

ሀበሻ 🇪🇹

28 Dec, 05:41


የሲዳማ ሴቶች ባህላዊ አለባበስ ባጠቃላይ በ3 ይከፈላል።

የሲዳማ ሴቶች ባህላዊ አልባሳታቸውን እና ጌጣ ጌጦቻቸውን በጥንቃቄ በመያዝ ልምዳቸው ይታወቃል።

ልብሶቻቸው እና ጌጣ ጌጦቻቸው ጥሩ መዓዛ እንዲኖራቸው የተለያዩ የዛፍ ሥራ ሥሮች ፣ቅጠላ ቅጠሎች እና ቅርፊቶች በማደባለቅ የተቀመመ ንጥረ ነገር ያዘጋጃሉ።

የሲዳማ ሕፃናት ሴት ልጆች የሚለብሱት ከበግ ቆዳ ተለፍቶ የሚዘጋጅ ለምድ (Lande) ይሰኛል።

ወጣት ልጃገረዶች ደግሞ ከውስጥ ቆሎ (Qolo) የሚባል ልብስ የሚለብሱ ሲሆን ከላይ ከጥጃ ቆዳ ተለፍቶ የሚዘጋጅ ለምድ (Qonxolo) ይደርባሉ፡፡

የልጃገረዶች ቆሎ የተሰኘው ልብስ ከጥጥ የሚሠራ ሆኖ ከላይ እስከ ታች ተደርጎ የሚሰፋ የተለያዩ ቀለማት ባላቸው አዝራሮች፣ ጨሌዎችና ፈትሎች እንዲያሸበርቅን ይደረጋል፡፡

ዕድሜያቸው ለትዳር የደረሱ የሲዳማ ሴቶች ዱቤ (Dubbe) የሚባል ከቆዳ የሚሠራ ልብስ ይለብሳሉ፡፡

ላገባች ሴት ባሏ ዎዳሬ (Woodare) ይገዛላታል፡፡

ዎዳሬ ከበሬ ቆዳ የሚሠራ ሲሆን ቆዳው እጅግ የለሰለሰ ነው፡፡ አለባበሱም በሁለት በማጠፍና በወገብ ላይ በቆዳ የሚሠራ መቀነት በቁኔ (Qu’ne) በማሠር እጥፋቱ ወደ ታች በመልቀቅ ነው፡፡

ለጋብቻ የደረሰች ልጃገረድ ስታገባ ከእናቷ በስጦታ መልክ የሚሰጣትን ዎዳሬ ታጥቃ በልዩ ጌጣ ጌጦች ያሽቆጠቆጠ ለምድ ደርባና ተሞሽራ ስትወጣ በተለየ ሁኔታ የተጌጠ ቆሎና ቆንጦሎ ደርባ ነው፡፡

የሲዳማ ሴቶች ጎርፋ (Gorfa)፣ ቱባ (Tuba)፣ ዱዳ (Dudda)፣ ቦኬ (Boke) የሚባሉ ከቆዳ የሚሠሩ አልባሳትን ይለብሳሉ፡፡

ቦኬ፣ ወዳሬ የክት ልብሶች ሲሆኑ ቱባና ዲዳ በአዘቦት ቀናትና በሥራ ቀናት ጊዜ የሚለበሱ አልባሳት ናቸው፡፡

ከጎርፋ በስተቀር ከላይ የተጠቀሱ አልባሳት ከወገብ በታች የሚታጠቋቸው ሲሆን ጎርፉ በተለያየ ጨሌዎች ያጌጠና ሴቶች ወደ አደባባይ ሲወጡ ከላይ የሚደርቡት ካባ ነው፡፡

ሁለት ቆንጦሎ ከፊትና ከኋላ በማጠፍ መልበስ በሲዳማ ሴቶች ዘንድ የድሎት ወይም የቅንጦት ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

በዚህ አለባበስ የሚታወቁ አበዛኞቹ ሴቶች “La’ma Lamu Landite” ተብለው ይወደሳሉ ትርጉሙም በሁለት ለምድ የተቀማጠለች መሆኗን የሚገልጽ ነው፡፡

(አዲስ1879)
(VOA)
እርስዎ የሚያውቁትን ባህላዊ አለባበስ ቢያጋሩን!

ሀበሻ 🇪🇹

14 Dec, 08:24


በሐመር ወረዳ ሴቶች በሕይወት ለሌለ ሰው ተድረው ከሟች ዘመድ እንዲወልዱ የሚያደርገው ባህላዊ ስርዓት መቀጠሉ ተገለጸ

👉በወረዳው በሩብ ዓመቱ ሦስት ሴቶች በሕይወት ለሌሉ ወንዶች ተድረዋል

በደቡብ ኦሞ ዞን ሐመር ወረዳ ሴቶች ለሞተ ሰው ተድረው ከሟች ዘመድ እንዲወልዱ የሚያደርገው ባህላዊ ስርዓት መቀጠሉን የወረዳው ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል።

"በወረዳው 'ኮይካ' ወይም ጥሎሽ ለማግኘት ሲባል ሴት ልጅ አትማርም፤ ይህም ብቻ ሳይሆን ሴት ልጅ የገቢ ምንጭ ተደርጋ በእርሷ ገቢ ወንድ ልጅ እንዲያገባ ይደረጋል" ሲሉ፤ በቢሮው የሴቶችና ሕጻናት መብት ደህንነት ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ የሆኑት ወይዘሮ ሙሉነሽ ጨረና ለአሐዱ ተናግረዋል።

ይህንን ተከትሎም በወረዳው ያለእድሜ ጋብቻ በስፋት እየተስተዋለ መሆኑን ቡድን መሪዋ ገልጸዋል።

"በተለይም ደግሞ ለ'ቦርከካ' ወይም ለሞተ ሰው ይዳራሉ፤ ይህ የሚሆነው ለሞተ ሰው ሚስት መኖር አለበት በሚል ምክንያት" እንደሆነ የተናገሩት ወ/ሮ ሙሉነሽ፤ "በዚህ ሳያበቃ ሴቷ ከሟች ዘመድ እንድትወልድ ተደርጎ የሚወለደው ልጅ በሞተው ሰው ሥም እንዲጠራ ይደረጋል" ብለዋል።

በዚህም በወረዳው በ2017 ሩብ ዓመት ሦስት ሴቶች በሕይወት ለሌሉ ወንዶች መዳራቸውን ተናግረዋል።

"በሌላ በኩልም ያለአቻ ጋብቻ በሐመር ወረዳ ከሚታዩ ችግሮች አንዱ ነው" ያሉም ሲሆን፤ በጣም በእድሜ የገፋ አባት ከስምንት ዓመት ሕጻን ልጅ ጀምሮ እንደሚያገባ ገልጸዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ አንድ ሰው ሃብት ካለው፤ ድርብ ጋብቻ ወይም ሁለት ሚስት እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ወንድ ልጅ የሚያገባው ከብት መዝለል ሲችል ብቻ መሆኑን በመግለጽ፤ "በዚህ የተነሳ ለወንዱ ቤተሰቦች እንደ ስጦታ የሚታሰብ እናቶችን ጨምሮ ሴቶች ይገረፋሉ" ብለዋል።

በዚህ ምክንያት የሚገረፉ ሴቶች ሰውነት ስለሚተለተል የእጅና የጡት አካል መጉደልን ጨምሮ በሕመም ሲሰቃዩ ቆይተው ሕይወታቸውን የሚያጡ ሴቶች እንዳሉ ተናግረዋል።

"ይህን መሰሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት በወረዳው በስፋት ይስተዋላል" የሚሉት ወይዘሮ ሙሉነሽ፤ ሴት ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንደማይላኩም ጨምረው ገልጸዋል።

ወደ ትምህርት ቤት የማይላኩበትን ምክንያት ሲያስረዱም፤ "ሕጻናት ቶሎ ታጭተው ከጥሎሽ ከብት፣ ፍየል፣ ማር እና የተለያዩ መሳሪያዎች የሚገኙ በመሆኑ ነው" ብለዋል።

"ትልቁና ዋነኛው ችግር ሴት ልጅን አሳንሶ ማየት ነው" ያሉት ቡድን መሪዋ፤ ሴት የንብረት ባለቤትነት እንደሌላትም ገልጸዋል።

"ችግሩን ለመቅረፍ ከግንዛቤ መፍጠር ጀምሮ የተወሰኑ ሥራዎች ቢሰሩም፤ ጠንከር ያለ ሥራ ተስራቷል ለማለት አያስደፍርም" ሲሉም ለአሐዱ ተናግረዋል።

በተጨማሪም "ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱ ጋር ተያይዞ በተፈጠረላቸው ግንዛቤ መሻሻሎችን ያሳዩ አካላትም የማበረታቻ ድጋፍ አልተደረገላቸውም" ብለዋል።

(አሐዱ ሬዲዮ)

ሀበሻ 🇪🇹

13 Dec, 18:23


🇸🇾 ሶሪያ : ልብ የሚሰበር ክስተት

#Ethiopia | አሳዛኝ እውነት፤ ማንም ሰው መሸከም ከሚችለው በላይ መከራ የወረደበት አባት

አንድ እግሩን በአደጋ በማጣቱ በሁለት ክራንች ( የብረት ድጋፍ) እየታገዘ ይራመዳል ።

ከስደት ወደ ትውልድ ቄዬው ከነልጁ እየተመለሰ ነው።

የስድስት ዓመቱ ኡመር ተልሃ የአባቱን ሰዉ ሰራሽ እግር በሁለት እጆቹ አቅፎ ፈጠን እየለ ለመሄድ በማሰብ ይወተረተራል ። አባቱ አይኑን ከልጁ አልነቀለም ።

የተሸከመው ሰው ሰራሽ እግር እይታውን ጋርዶት እንዳይወድቅ ስጋት ገብቶታል ።
ኡመር አንድ የቀረው ብቸኛው የአይኑ ማረፊያ ነው።

በባዕድ ሀገር በስደት ዓለም ሆስፒታል እግሩ ተቆርጦ ከአጠገቡ ሳይለይ ያስታመመው ትንሹ ኡመር በህይወት ያለው ብቸኛው ልጁ ነው ።

እንደ ዛሬው ሁለቱ ብቻ ሳይቀሩ የዛሬ 11 አመት ጦርነት ሸሽተው አገራቸውን ሶሪያን ጥለው ሲሰደዱ አምስት ነበሩ።

ቆይቶ እዚያው የተወለደው ኡመር ደግሞ 6ኛ የቤተሰቡ አባል ሆኖ ተቀላቀለ ።

በወቅቱ ሰውን ከሚበላው የጦርነት አቶን እሳት መሃል ሙሉ አካላቸውን እና የቤተሰብ ቁጥራቸው ሳይጐድል ቱርክ መግባታቸውን እንደ ትልቅ ዕድል ቆጥረውትም ነበር ።

ከ11 ዓመታት የስደት ኑሮ በኋላ ለ61 ዓመታት ሶሪያን ረግጦ የገዛው የባዝ ፓርቲ ሲሸነፍ የቱርክ ድንበርን አቋርጠው ሁለቱ ፤ አባትና ልጅ ብቻ ወደ መንደራቸው እየተመለሱ ነው ።

6 አመቱ ኡመር የተወለደው ቱርክ ቢሆንም ያጣውን የእናት ናፍቆት ሶሪያ ባላቸው አክስቱ ፍቅር ሊያስታግስ ጉዞውን ለመጨረስ ጓጉቷል ።

ባለ ክራንቹ መሐመድ እና የአባቱን ሰው ሰራሽ እግር የተሸከመው ከስደት ተመላሽ ኡመርን ያየው የአናዶሉ ዘጋቢ ጠጋ ብሎ ወደ ሀገር መመለስ የሚፈጥረውን ስሜት አባቱን ጠየቀ ።

የመሐመድ ዓይኖች በእንባ ተሞሉ ያሳለፈው መከራ ከፊቱ ተደቀነ ።
የህይወት ታሪኩን ውጣ ውረድና የዕጣ ፋንታን አይቀሬነት ዘርዝሮ ነገረው ።

የዛሬ 11 አመት ባለቤቴንና የዚህን ልጅ ታላቅ ወንድም አለ መሐመድ ወደ ኡመር በእጁ እየጠቆመ ፣ የልጆቼን ወንድ እያት እና የሴት አያትን ይዥ ነበር ቱርክ የገባሁት ።

በዚሁ አገር ደቡባዊ ቱርክ ሃታይ ግዛት የካቲት 6 ቀን 2023 የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ሰለባ ሆነን እንጂ አለ በትካዜ።

የመሬት መንቀጥቀጡ የበርካቶችን ህይወት ቀጥፎ ከፍተኛ የአካል ጉዳትና ንብረት አውድሟል፡፡

ከአምስት ቀን ፍለጋ በኋላ በነፍስ አድን ሠራተኞች ከፍርስራሽ ስር እኔና የስድስት ዓመት ልጄ ዑመር ብቻ ተረፈን ወጣን ሲል ዘረዘረ።
በደረሰብኝ ጉዳት ምክንያት አንድ እግሬ ተቆረጠ ።

ታድያ ይህንን እንዴት ብዬ ስሜቱን ልንገርህ ሲል ከእንባው ጋር እየታገለ ገለጸ ።

እኔ የናፍቀኝ የትውልድ ሀገሬ ሶሪያ ስመለስ ልጄ ከአክስቱ ይገናኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ በቃ ይኸው ነው ።
ከመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው በኋላ በቱርክ ዜጐች የተደረገልኝ ድጋፍ ከምናገረው በላይ ነው ።

ከህዝቡ በተጨማሪ የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጠይብ ኤርዶጋንን ማመስገን እፈልጋለሁ በብዙ አግዘውኛል ሲል ተናግሯል ።

የሀገሬ ሰው "ለመከራ የጣፈው ፤ ቢነግድ አያተርፈው" የሚለው ይሄኔ ነው ።

ምስጋናው ሀይሉ

ሀበሻ 🇪🇹

10 Dec, 09:02


ሲያነቃቁን ለምን አንነቃም? ሙተን ይሆን እንዴ?
(አሌክስ አብርሃም)

ለመጀመሪያ ጊዜ self-help book የሚሏቸውን ሳነብ በጣም ነቅቸ ነበር! አስታውሳለሁ የ Rhonda Byrne ን The secret ሳነብ በጣም ከመንቃቴ የተነሳ ለስራ እጀን ከመጠቀም ይልቅ አዕምሮየን ለመጠቀም ወስኘ ነበር። ለምሳሌ መብራት አጥፍቸ ከመተኛት ተኝቸ መብራቱ ልክ እንቅልፍ ሲወስደኝ ይጠፋል ብየ ለራሴ እነግረዋለሁ፤ጧት ስነሳ እንደበራ ባገኘው አልደነቅም፣ ከእንቅልፌ ከመንቃቴ አንድ ደይቃ በፊት በራሱ ጊዜ እንደበራ አምናለሁ። የወሩ የመብራት ሂሳብ ግን የነገረኝ ሌላ ሆነ፤ ተው ወንድሜ በጣም አትንቃ አለኝ። እናም እያጠፋሁ መተኛት ጀመርኩ። ከ1890 ዓ/ም ጀምሮ መብራት ሀይል መብራት ያላጠፋበት ብቸኛ ወር ነበር። ስንነቃ አይወዱ😀

ኦሾን ያነበቡ የኔ ዘመን ወጣቶች ደግሞ "ሐይማኖት ባህል ገለመሌ ከጫነብን ፍዘት ወጣን" አሉና በየመንገዱ ፀጉራቸውን በመፍተል መቆዘም ጀመሩ፤ ይህንንም "ውስጣዊ ንቃት" አሉት። ከአመታት በኋላ ሁሉም ጠበል ገብተው እየጮሁ ከንቃታቸው በጣም ነቁ። በቀን አምስቴ ኡዱ የሚያደርጉ፣ ለጁመዓ የሽቷቸው መዓዛ ከሞያሌ የሚጣራ ፣ እንዴት ያሉ ንፁህ ሙስሊም ወዳጆቸ ሳይቀሩ ጀዝበው ገላቸውን መታጠብ አቁመው ነበርኮ! ስንት ተቀርቶባቸው ተመለሱ። የዛን ሰሞን ወጣቱ ሁሉ ውስጣችን በራልን እያለ ስንት ጨለማ ተከናነበ። ራሳቸውን ያጠፉም ነበሩ። ኦሾና አለቃ ገብርሃና ተረታቸው እንጅ ኑሯቸው አያምርም።

ይሄው በዚህኛው ዘመን ደግሞ አነቃቂወች እንደአሸን ፈሉና "ያሰብከውን ትሆናለህ፣ ነኝ በል፣ አለኝ በል፣ ደርሻለሁ በል፣ እችላለሁ በል፣ በሀሳብህ መኪና አስነሳ፣ አሉ፤ ወጣቱ የሀሳብ መኪና አስነሳ፤ በሀሳብ ሲጋልብ ራሱጋር ተጋጨ፣ ቤተሰቡ ጋር ተጋጨ፣ አገሩ ጋር ተጋጨ፣ፈጣሪው ጋር ተጋጨ ። ከሆነስ ሆነና ለምንድነው በዚህ ዘመን ይሄ ሀሁሉ አነቃቂ ንግግር ያላነቃን? የእውነት የሆነ ጊዜ ያነቃን ነበርኮ፣ እየቆየ ግን እንኳን ሊያነቃን ያስተኛን ጀመረ፤ እኮ ለምን?

የህክምና ባለሙያወች ከተሳሳትኩ አፉ ብለው ያርሙኝና በእነሱ ሙያ Drug tolerance የሚሉት ነገር አለ አሉ፤ በትክክል ከተረዳሁት ለሆነ ህመም የተሰጣችሁ መድሀኒት ከሆነ ጊዜ በኋላ በሽታችሁ ጋር ይግባቡና ፍሬንድ ይሆናሉ። በሽታው መድሃኒቱን ይላመደዋል።ጉቦ እንደበላ ደንብ አስከባሪ በሽታችሁ መንገድ ዳር ሲያሰጣችሁ መድሀኒቱ እንዳላየ ያልፈዋል። ለምሳሌ የእንቅልፍ ችግር ገጠማችሁና በሐኪማችሁ የእንቅልፍ ኪኒን ታዘዘላችሁ እንበል ፤ የመጀመሪያ ሰሞን ድብን ያለ እንቅልፍ ያስወስዳችኋል፤ እየቆየ ሰውነታችሁ ሲላመደው መድሀኒቱን ውጣችሁም ቁልጭ ቁልጭ ስትሉ ታነጋላችሁ። ወይ አይነቱን ወይ መጠኑን ባለሙያ ካልቀየረው በቃ ለውጥ የለም። አይ መጠኑን ራሴ እቀይረዋለሁ ብላችሁ ጨመር አድርጋችሁ ከወሰዳችሁ ደግሞ ትተኙ ይሆናል ግን እንደገና ላትነሱ ትችላላችሁ።

ወደህይወት ስናመጣው እኛ ኢትዮጵያዊያን በአሁኑ ሰዓት ማንኛውንም ማነቃቂያ ከመላመድ አልፈን እንደዘፈን ሸምድደነው አብረን እየደገምነው ነው። ገና ፊቱን ስታዮት አብራችሁ "ብሮሮሮሮሮ" አትሉም?! ለዛ ነው ከነዋሪ መካሪና ዘማሪ የበዛው። የፈለገ ብንመከር ብንዘከር ብንሰበክ ብንወገዝ ወይ ፍንክች። አሁን ሞራል፣ ሐይማኖት፣ የአገርም ይሁን የሰው ፍቅር፣ ይሉኝታ ፣መማር ፣ የራስ ክብር ተተተወዘተ አእምሯችን ተላምዷቸው ተራ ነገር ሁነውብናል።

የሞራል ተቋሞቹ በሞራል ድሽቀት ከተራው ህዝብ ቀድመው ባፍጢማቸው ተተክለዋል፤ የትዳር ሰባኪወቹ ማግባትና መፍታት መድረክ ላይ እንደመውጣትና መውረድ ቀሏቸዋል። እንደውም የጓዳቸውን ውድቀት እንደባንዲራ በአደባባይ እየሰቀሉ እዮልን ባይ ሆነዋል። አሁን እንደህዝብ ሁለት ነገሮች ብቻ ናቸው የሚያነቁን ወይ (((ብር ማጣት))) አልያም (((ብር ማግኘት)))። ይሄ የመጨረሻው ዶዝ(መጠን) ነው! ሰው ክብሬ ገመናየ ማንነቴ የሚለውን ነገር ሁሉ ይዞ ገበያ ከወረደ ምን ይመልሰዋል?! ከዚህ በኋላስ? ምን ያነቃን ይሆን? ምክንያቱም በብር የሚመጣ ንቃት በአንዴ አይረካም፤ እንደአደንዛዢ ዕፅ በየቀኑ መጠኑን እየጨመሩ ካልተወጉት መጨረሻ የለውም። መመለስም መቀጠልም የማንችልበት አውላላ ሜዳ ላይ የሚያስቀር መርገምት ነው!! ምን ላድርግ ቸገረኝ፣ የማደርገው አጣሁ በሚል ሰበብ ከሰውነት ድንበር ከምንርቅ በየግላችን "ይሄንኛው ነገሬ ለገበያ ከሚቀርብ ሞቴን እመርጣለሁ" የምንልለት የሆነ መስመር ልናሰምር ግድ ነው። ሰው ራሱ ወስኖ ያሰመረውን መስመር ከሞት በስተቀር ምን ያሻግረዋል?!

ሀበሻ 🇪🇹

18 Nov, 18:12


''ተምሬ የት ልደርስ?'' የሚለው አስተሳሰብ እየሰፋና እየሰረገ መምጣቱ አላሳሰባችሁም?

የምር ከማልጠብቃቸው ሰዎች ሁሉ መስማት ጀምሬአለሁ።

ብቸኛው የችግር መፍቻ ቁልፍ ንግድ/ ''business'' እንደሆነ ብቻ እየታሰበ መምጣቱ አሳሳቢ ብቻ ሳይሆን ልክ ያልሆነም ነው።

በአንድ ዘርፍ ብቻ ዓለም ልትቆም አትችልም።

በታላላቅ ሃይማኖቶች አስተምህሮ የፈጣሪ ስጦታ የተለያየ እንደሆነ ተነግሮናል። ንግድ ጥበብ ነው። ሁላችንም ነጋዴ ልንሆን አንችልም።

ምርጥ ነጋዴ ለመሆን ራሱ ከፈጣሪ የተሰጠህን ጸጋ በትምህርትና በክሂሎት ልታሳድገው/ልታበለጽገው ግድ ነው።

እሺ አንተ ነጋዴ ሆንክ፤

- ልጅህን ማስተማር የምትፈልገው የት ነው?
መርካቶ ነው?
- ስኳር ሕመምተኛ ሆንክ። የት ልትሔድ ነው?
- ንብረትህን/እድሜህን የሚያሳጣ ችግር ገጠመህ። ጠበቃው ከየት ሊመጣ ነው?
- ልጅህ የመደፈር አደጋ ደረሰባት። ማንን ልትጠራ ነው?
- ሚስትህ ምጥ አፋፋማት፤ ማን ጋ ልትሮጥ ነው?
- ታክስ አናትህ ላይ ቢቆለል ማንን ልታማክር ነው?
- በቅርቡ የሚደረመስ ሕንፃ መሥራት ነው የምትፈልገው?
- ገንዘብህ በአግባቡ ማኔጅ መደረግ የለበትም?
- አዳዲስ ግኝቶችን የሚያመጡልን ተመራማሪዎች አያስፈልጉንም?
.
.
.
ሁላችንም ነጋዴ መሆን አንችልም። ከፈጣሪ የተሰጠንን የተለያየ ጥበብ በትምህርትና ክሂሎት ካዳበርን ባለጸጋነትን የሚከለክለን የለም።

መሠረትን ማናጋት ሁሉንም ሥርዓት ማናጋት ነው። ትምህርት የሁሉም ሥርዓቶች መሠረት ነው። የትምህርት ሥርዓት መበላሸት እና በትምህርት ተስፋ መቁረጥ በሁሉም ሥርዓቶች ላይ ለመቆጣጠር የሚያዳግት የካንሰር ሴል እንደመዝራት ያለ ነው።

Via Hawlet Ahmed

🙏🙏🙏

🌴🌴🌴

ሀበሻ 🇪🇹

17 Nov, 05:00


'መልኬ-ዜፓም'
=========
ቤንዞዳኣዜፒን (Benzodiazepine) የሚባሉ የአእምሮ መድሀኒቶች አሉ። ሰዎች እንቅልፍ እንዲወስዳቸው (hypnotic)፣ እንዲረጋጉ (Sedative)፣ እና ጭንቀት እንዲቀንስ (anxiolytic) ያደርጋሉ። እነዚህ መድሀኒቶች ጭንቀትን የሚቀንሱት ወዲያው ነው። ሆኖም ግን አእምሮ ላይ ሱስ ሊሆኑ ስለሚችሉ የግድ አስፈላጊ ካልሆነ አይታዘዙም። ሲታዘዙም ሱስ እንዳያስከትሉ ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው። በዚህ መደብ ውስጥ ያሉት መድሀኒቶች አብዛኞቹ ስማቸው መጨረሻቸው ላይ 'ዜፓም' አላቸው። ዲያዜፓም፣ ሎራዜፓም፣ ክሎናዜፓም...ወዘተ።

የአእምሮ ህክምና ስፔሻላይዜሽን ስንማር አማኑኤል ሆስፒታል ዋርድ አራት የመርመርያ ክፍል ብዙ የተናደዱ፣ ወይም በጣም የተጨናነቁ ታካሚዎች የመመርመሪያ ክፍል ገብተው ሲወጡ ተረጋግተው እናያቸዋለን። እዚያ ክፍል ውስጥ "ዳያዜፓም ወይም ክሎናዜፓም የሚሰጣቸው ሰው አለ እንዴ?" ብለን እንገረም ነበር።

ዋርድ አራት የመመርመሪያ ክፍል ዳያዜፓም አይታደልም። አንድ የአእምሮ ሀኪም እጅግ በተረጋጋ ሁኔታ ታካሚዎችን ያናግራሉ። በፅሞና ስለሚያዳምጡና ድምፃቸው በጣም ለስለስ ያለ ስለሆነ ተናዶ የሚጮህን ሰው የማረጋጋት አቅም (soothing quality) አለው- ዶ/ር መልካሙ አግደው። ከዛ በኋላ ሬዚደንቶች 'መልኬ-ዜፓም' የሚል ቅፅል ስም አወጣንላቸው። የተቆጣ ወይም የተበሳጨ ታካሚ ወደ ዋራድ አራት መመርመርያ ክፍል ሲሄድ ካየነው "ቆይ መልኬ-ዜፓም ሲያገኝ ይረጋጋል።" እንል ነበር። 😂

ዶ/ር መልካሙ ለሆስፒታሉ ሰራተኞችና ለሬዚደንቶች መልካም አርአያ ናቸው። ያልተገባ ነገር ከተመለከቱም ረጋ ባለ አንደበት "ልጆች እንደሱ አይደረግም እ?" ብለው ይገስፃሉ።

ለጋለ ስሜት ነገር መፍትሄው ቀዝቃዛ ውሀ እንደሆነ ዶ/ር መልካሙ 'መልኬ-ዜፓም' እየሰጡ በተግባር አስተምረውናል። ዶ/ር መልካሙ ለብዙ አስርት አመታት አማኑኤል ሆስፒታልን አገልግለው አሁን በጡረታ ላይ ናቸው።

ያለ አእምሮ ጤና፤ ጤና የለም!!!
ስለረጅም ጊዜ አገልግሎትዎ እናመሰግናለን።
ዶ/ር ዮናስ ላቀው

ሀበሻ 🇪🇹

13 Nov, 11:26


ታሪክ ታሪክ ካሉማ ከመጀመሪያው ነው!
..
.
ታሪክህ...
-2 ኛው ሚኒሊክ በሜንጫ ጡት ሲጨረግድ አይጀምርም!
ወይም...
- ሳባ ለሰሎሞን ገልባ 1 ኛው ሚኒሊክ ከጠይምነቱጋ ጠብ ሲልም አይጀምርም።
.
.
የመጀመሪያውን ታሪክ ለማወቅ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች እንተዋወቅ።
የመጀመሪያዎቹ የሰው ልጆች እነማን ናቸው?
.
99 % አንባቢ መልሱን ይስታል።
.
እኔም ለመጀመርያ ስጠየቅ አዳምና ሔዋን ብዬ ስቻለሁ። እነሱ ፍጡራን እንጂ የሰው ልጆች አይደሉም።
.
አቤል እና ቃኤል።
.
አይገርምም የመጀመሪያው ታሪካችን መገዳደል መሆኑ! ቃኤልና አቤል ወንዝ ዳር ተቃቅፈው ሲሮጡ፤ ጋደም ብለው ስለብቸኝነታቸው እያወሩ "እኔ አለውልህ፣ ካንተ ወደማን እሔዳለሁ" ሲባባሉ፤ ምድር የሁለቱ ብቻ የመሆኗ ስፋት አስደስቷቸው ስላላዩአቸው አዳዲስ ቦታዎች በምናብ ሲሔዱ አልተጻፈው። ገደለው ነው ታሪክህ።
.
ታላቅየው ታናሽየው ገደለው።
ለምን?
መስዋእቱ ስለተወደደለት። በማ ስለተወደደ? በፈጣሪው። ታሪክን የምንፈትሽ ከሆነ ግለሰቦቹን የተዋወቅንበት መንገድ ላይ እናተኩር። በጎሳቸው ሳይሆን በስነ-ምግባራቸው ጎልተው ይታያሉ። ስለዚህ ሁለቱን ስብእና(personality) እናድርጋቸውና ቀደዳችንን እንቀጥል። personal-reality።
.
የተገደለው ስብዕና ምን አይነት Reality ነው?
.
1. አቤል።
ጩጬ ነው። የሚደክላት የታላቅ ወንድሙ እህት አሪፍ ነበረች አሉ። (ይሔ በአዋልድ የተጻፈ እንጂ በዘፍጥረት የተጻፈ ስለሆነ በከፊል ተቀብለነው እንቀጥል።) አርብቶ አደር ነው። ይሔ ግን ተጽፏል። ከእለታት አንድ ቀን የድካማቸው ፍሬ ለአምላካቸው በማቅረብ ልማድ ላይ አቤል ከከብቶቹ መሀል የሰባውን ለአምላኩ #ተጨንቆ ያቀርብ ነበር።
.
2. ቃኤልስ?
.
(ይሔ አባታችን ሆኖ ስለሚቀጥል ከአቤል በተሻለ ራቅ እና ጠለቅ አድርገን እንቆፍረዋለን)
.
ቃኤል ታላቅ ነው።
የሚደክላት የወንድሙ መንትያ ጉጭማ ሆናበት ነዶታል አሉ። (ይሔም አልተጻፈም) ገበሬ ነው። አቤል ያቀረበ ቀን እሱም ከፍሬው ለአምላኩ ያቀርብ ነበር።
መተርጉማን ቃኤል #ተጨንቆ ያለማቅረቡን ምክንያት ሲያፈላልጉ በአቤል እህት ጉጭማ መሆን ተናዶ ሊሆን የሚችለውን የሳቡ ይመስላል። ሊያስማም ላያስማማም ይችላል።
.
✔️ ከ ንባቡ ብዙም ሳንርቅ ግን ሌላ ታኮ ብናስቀምጥ የሆነ የትርጉም ገንቦ ይቆማል።
.
.
ከወላጆቹ የሰማው የመዘበጥ ታሪክ አለ። ታሪኩ ያስቆጣው ይመስላል። #ክፍ ብሎ ያባረረን መለማመጥ አያስፈልግም አይነት ቂም።
.
Bro..ወላጆች ከሚኒሊክም ባይጀምሩ የሚነግሩህ የመጠለዝ ታሪክ ከሆነ Fuck it. አትቀበል ዘባጩ ፈጣሪም ይሁን ምኒሊክ #ተዘብጠን_ነበር ካሉህ መሰዋትህን ታበላሻለህ።
.
የሱ ልጆች የመሰሉህን ትጠምዳለህ ነገር።
ግን ደሞ ወላጆቹ ትርክቱን ለታላቅየው ብቻ ስለማይነግሩ እንዴት የተነገረው ቂም ታናሹ ላይ አልሰራም የሚል መከራከሪያ ይነሳል!
(ዘር ሁሉ መልካም መሬት ላይ አይወድቅም። ጭንጫ፣ እሾህ፣አለት ላይም ይወድቃል ብለን ብንመክትስ? 😁 መንታ ሆነው ጽንፍ የረገጡ ወንድማማቾች ብዙ አናቅም!!)
.
እንዲህም ብቻ ላይሆን ይችላል። ቃኤል ግን አምላኩ ለሚበላው #አለመጣሩ ፈጥጦ ታይቷል።
አለመጣር #nihilism! ነው።
.
ኒሒሊዝም "ሁሉ ከንቱ የከንቱ ከንቱ ነፋስን እንደመከተል..." የሚል የጠቢብ ቃል ላይ የቆመ ኩርፊያ። እኮ? ማን የፈጠረውን ከንቱ የምትለው? ግጥምህን ከንቱ ልበል? ሚስትህን ወይስ ልጅህን ጎዶሎ ብዬ ፈገግታህን ልጠብቅ(👊 አፍንጫዬ ላይ)
.
ንግግሩ ወይም ሀሳቡ እውነት ቢሆንኳ ጥበብ ነገር ይጎለዋል። ከንቱ መሆን ወይም መጠለዝ ማነው መጥፎ ብቻ ያደረገው?
.
❤ መፍረስ ውስጥ ህይወት የለምን? ቅጠሎች ባይረግፉ?(አፈር ለምነቱን ያጣል)! በሽታ እንዳይኖር ባክቴሪያ ከምድር ቢጠፋ( ሰገራህ አይበሰብስም)! አሲድ ባይኖር(ጨጓራህ አይፈጭም) ወይም በቀላሉ ሴጣን ገነት እንዳይገባ እባብ ባይፈጠር..አዳም ባይበላ..እግዜር አዳምን ባይፈጥረው
.
.
ስለዚህ ወንድሜ ሆይ እህ ብለህ ስማኝ....ወላጆች "አባትህ ተዘብጦአል"ን ከሚኒሊክም ባይጀምሩ የሚነግሩህ የመጠለዝ ታሪክ ካለ Fuck it. አትቀበል ዘባጩ ፈጣሪም ይሁን ምኒሊክ #ተዘብጠን_ነበር ካሉህ መሰዋትህን ተቀባይ ተጣለህ። ተቀባይ-ነትን ደሞ ትፈልግ የለ?
accepted መሆን😍
በሀይሉ ሙሉጌታ

ሀበሻ 🇪🇹

29 Oct, 13:04


አልቃሽና አጫዋች
(በእውቀቱ ስዩም)

ቦጋለ በሚባል ስም የሚታወቁ ሁለት ስመጥር ሰዎችን አውቃለሁ፤ የመጀመርያው የ”ፍቅር እስከመቃብሩ” ገበሬ፥ ቦጋለ መብራቱ ነው፤ ሁለተኛው በገሀድ ኖሮ አልፏል፤ድሮ በጎጃም ሽማግሌዎች ክፉ ሰው ሲራግሙ፥ “ ቦጋለ ያይኔ አበባ ስምህን ይጥራው “ይሉ ነበር ይባላል፤

ቦጋለ ያይኔ አበባ ስመጥር አልቃሽ ነበር፤ የጥንት አልቃሾች ቀላል ሰው እንዳይመስሏችሁ፤ በለቅሶ ወቅት የሚታየውን ትርምስ እና ጫጫታ ወደ ኪነጥበብ ትርኢት የሚቀይሩበት ተሰጥኦ ነበራቸው ::

ቦጋለ ያይኔ አበባ በወጣትነቱ ያገሩን መሬት አርሷል፤ እንዲሁም ያገሩን መሬት በእግሩ አዳርሷል፤ ወደ አልቃሽነት ሙያ እስኪገባ ድረስ ግን የረባ ስኬት አላገኘም ነበር፤ ይህንን በማስመልከት፥ እንደ ግለ-ታሪክ እና Cv በምትቆጠርለት እንጉርጉሮው እንዲህ ብሎ ነበር፤

“አርሼም አየሁት ፥
ነግጄም አየሁት
አልሰሰመረም ሀብቴ
አልቅሼ እበላለሁ እንደ ልጅነቴ “

ቦጋለ ያይኔ አበባ ከዘመናት ባንዱ ወግ፥ ደርሶት ሴት ልጁን ዳረ፤ እንጀራ ሆኖት የቆየው ሞት አሁን በሌላ ገጹ ተከሰተ፤ ሙሽሪት በሰርጓ በሳምንቱ ተቀጠፈች፤ እልልታው ወደ እሪታ የተቀየረበት ቦጋለ በተሰበረ ልብ ይቺን ውብ እንጉርጉሮ ወረወረ፦

“እንዲህ ያለ አምቻ፥ ክብሩን የዘነጋ
በፈረስ ሰጥቼው ፥ መለሰልኝ ባልጋ”

ኪነጥበብ ፥ አስቀያሚ መከራን ወደ ውበት መቀየር እንደምትችል ይቺ እንጉርጉሮ ምስክር ናት፤

ከሞት ሁሉ ቅስም ሰባሪው የልጅ ሞት ይመስለኛል ፤ ከወሎ የፈለቀች ከወዳጄ የሰማሁዋት ፥አንድ ጨዋታ ትዝ ትለኛለች፤ አያ ሙሄ የተባለ ገበሬ ልጁ ሞቶበት ፥ጎጆው በርንዳ ላይ ከርትም ብሎ ይቆዝማል ፤ ባለንጀራው አዋ ይመር አጠገቡ ተቀምጧል፤ አዋ ይመር ወዳጁን በቃል ማጽናናት በቂ ሆኖ አላገኘውም ፤ የወዳጁን ልጅ የቀሰፈውን ፈጣሪ ለመበቀል ስለፈለገ ፥ ጠመንጃውን አነጣጥሮ ወደ ሰማይ ተኮሰ፤

ተኩሱ በረድ ሲል አዘንተኛው አያ ሙሄ ወዳጁን እያየ እንዲህ አለ፤

“ካገኘከው ገላገልኸን፤ ከሳትኸው ግን አስፈጀኸን”🙂

ሀበሻ 🇪🇹

27 Oct, 13:39


#አሁንና_በመጨረሻ
*****
ይህቺ ዓለም ለማንም ደንታ የላትም ። አንተም ለእሷ ደንታ አይኑርህ ። አንተ ኖርክ አልኖርክ ይህቺ ዓለም ምንም አይመስላትም ። አንተ ቁጥር ነህ ። እንዳንተ አይነት የትዬለሌ ሚሊዮኖች በዚያ መንገድ አልፈዋል ። በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩት መሀል አንተ አንዱ ቁጥር ነህ ። ማንም ከዚያ መሀል አንተን ለይቶ አያውቅህም ። ስጋ የለህም ፤ ውበት የለህም ፤ ሀብት የለህም ፤ ልጆች የሉህም ፤ እውቀት የለህም ፤ ዝና የለህም ። ምንም የለህም ። አንተ ራስህ የለህም ። ቦርጭህ ፣ ቁመናህ ፣ ዳሌዋ ፣ ሽንጧ ፣ ስንቱን ያደባደበ ውበት ደም ግባቷ ፣ " በየት አለፈች ? " ያስባለ መልኳ በመጨረሻ አንዱ ጋ አፈር ውስጥ ተጥሎ ሁሉም ረግፎ አንዱ ከሌላው የማይለይ ያገጠጠ አጥንት ሆኖ ይቀራል ። ነበር ነህ አንተ ። ነበርሽ ነሽ አንቺ ። ዓለምን በጥፍርህ ቆንጥጠህ የያዝካት የሚመስልህ ነገር በመጨረሻ በቃ ምንም አይደለም ። አንተም ራስህ ምንም አይደለህም ።

" እፀድቃለሁ " እና " እኮነናለሁ " ን ተወው ። እሱ ባንተ እጅ አይደለም ። በሰሪው እጅ ነው ። ራስህን የማታውቅ ፍጡር የሰሪውን ሀሳብ ልትረዳ አትችልም ። አሁን ነህ አንተ ። ነገ አይደለህም ። ነገ የለህም ። ደግ ብትሆን ፤ መልካም ብትሆን ለአሁን ነው ። ለጽድቅ አይደለም ። አሁን ላይ መልካምነት የሚባል የብዙሀን ስምምነት አለ ። ለእሱ ተዘጋጅ ። ነገን ተወው ። ከሞትክ በኋላ የሚሆነውን በማሰብ ጊዜህን አታቃጥል ። ስለማታውቀው ነገ በማሰብ የምታውቀው ዛሬን አታበላሽ ። ከቻልክ ዛሬህ ነገህን እንዲሰራ አድርገው ። ዛሬን ስራው ። ዛሬ አይቆጭህ ። ዛሬህ ተስፋ መሆን ባይችል እንኳን ፀፀት አታድርገው ። ዓለምን ልቀቃት ። ለህሊናህ እንጂ ለዓለም አትጨነቅ ። ዓለምን ለመለወጥ አትነሳ ። ማንም ዓለምን የለወጠ ግለሰብ የለም ። ይልቁን ህሊናህን ለመለወጥ ተነሳ ። ህሊናህ ነው ዓለም ።

አንተ አሁን ማንንም ሁን ። በመጨረሻ ግን ከታች በምስሉ የምታየውን ነህ ። የአሁን ማንነቴ በስተ ቀኝ የተኛው እንደሚሆን በየዕለቱ አስባለሁ ። ማን እንደዚያ ያልሆነ ፤ የማይሆን አለ ? ማንም የለም ። ለወሬ ነጋሪ የሚቀር እንኳን ማንም የለም ። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሁን ፣ ጳጳሱን ሁን ፣ ቱጃሩን ሁን ፣ ማንንም ሁን ፣ ምንንም ሁን ፤ በመጨረሻ ከታች ያለውን ነህ ። ብትፈልግ ለመርሳት ሞክር ። ግን ምንም አይረዳህም ። አይቀርልህም ። እንዳለመታደል ሆኖ ብዙ ሰው መርሳት የሚፈልገው ይህንን ነው ። ለዚህም ይሆናል ክፋታችን የበዛው ። ብትፈልገውም ብትጠላውም በመጨረሻ ላይ " አስከፊ " ውን ምስል ነህ ። እሱን መርሳት ነው ህሊናችንን ሆድ የሚያደርገው ። አፈር ቤት በለው ሰማይ ቤት መቆጨት መናደድ የለም ። መመለስ የለም ። ስህተትን ማረም የለም ። ያኔ ቢቆጭህ የሚቆጭህን ዛሬ አስወግደው ። አውቀን እየካድነው እንጂ ክፋት ይታወቃል ። ሰውን ማስቀየም ፣ ሰውን መበደል ይታወቃል ። እሱን ታገል ።

ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ

ሀበሻ 🇪🇹

25 Oct, 11:07


ምን አልባት እኛ ያለን የሆነ ሰው ህልሙ ነው!
ምን አልባት እኛ ያለን የሆነ ሰው ፀሎቱ ነው !
ምን አልባት እኛ ያለፈን የማይጠቅመን ነው!
ምን አልባት ያሳመመን ሊያስተምረን ነው!
ምን አልባት የሆንነው የሆኑትን እንድንረዳ ነው !
ምን አልባት የተበለሻሸው እንድንቀያይረው ነው!
ምን አልባት አማራጭ ያጣነው አማራጭ እንድናመጣ ነው !
ŠAdhanom Mitiku

ሀበሻ 🇪🇹

19 Oct, 16:24


ችግራችሁን እያየን ያልደረስንላችሁ ይቅርታ!
ችግራችንን እያያችሁ ያልደረሳችሁልንም ይቅርታ!
(አሌክስ አብርሃም)

ፍቅር ብቻውን መልስ የሚሆንበት ጊዜ ላይ አይደለንም።
በማንም ላይ መፍረድ ከባድ ነው። ሲቸገሩ መርዳት አለመቻል ከሚፈጥረው ህመም ለመራቅ ከምንወዳቸው ወዳጆቻችን እንርቃለን። ዓይናቸው ውስጥ ያለውን ስቃይ ላለማየት ዓይናችንን እንሰብራለን።የአቅማችንን መደገፍ እንኳን ከአቅም በላይ ሆኗል። የተወለድንበት እና ያደግንበት ስር የሰደደ አብሮነት፣ መረዳዳት አሁን እግር ከወርች ካሰረን ኑሮ ጋር አብሮ አልሄድ ብሎ አስጨንቆናል።

ረስተነው ወደወዳጆቻችን መንገድ ከጀመርን ፣ልንደውል ስልክ ካነሳን በኋላ ባዶ አይናቸው እጃችሁ ከምን ቢለንስ ብለን ተመልሰናል። ከመሄዳችን በላይ ምን ይዛችሁ መጣችሁ የሚለን አንደበታቸው ሳይሆን ኑሯቸው ሁኗል። የተጨነቀ መንፈስ፣ የተጨነቀ አየር። የማንንም እርዳታ የማይፈልጉ መንፈሰ ፅኑ ወዳጆቻችን ነገሮች ከአቅም በላይ ሆነውባቸው በዓይናቸው ባዶ ኪሳችንን ሲቃኙ ብናይ መርዳቱ ቢቀር አንታዘባቸውም። "እንትናም ተቸገረ?" ብለን አናሾካሹክም።

ይገባናል ሰው ወደገደል ቢወድቅ አዳነውም አላዳነውም አጠገቡ ያገኘውን ሳርም ይሁን ቅጠል በደመነፍስ ጨምድዶ እንደሚይዝ። ሁላችንም ገደሉ ውስጥ ነን።ልብሳችንን አንቀው የሚማፀኑን እኛም የሌሎችን ልብስ አንቀን መንጠልጠላችንን ያውቃሉ። የመያያዙ መጨረሻ፣ የገደሉ ጫፍ የት እንደሆነ ማን ያውቃል?! እጃችን እየዛለ ነው። ደመነፍስ ላይ ነን። ማንንም ለመዳን እንይዛለን በማንም እንያዛለን። ችግራችሁን እያየን ያልደረስንላችሁ ይቅርታ። ችግራችንን እያያችሁ ያልደረሳችሁልንም ይቅርታ። ሁላችንም ገደሉ ውስጥ ነን።

ሀበሻ 🇪🇹

08 Jun, 11:28


በስዕሉ ላይ የወጣትነትና የስተርጅና ሥዕሎች ይታያሉ፣ ጋሽ ስብሐት የጠላውና የተቸው ዕርጅና መጥቶ እፊቱ ገጭ አለ። ጋሽ ስብሐት በመስተዋት ራሱን እያየ በርጅናው ይቀልድ እንደነበረ ይወሳል፣ ቀስ ብሎ ራሱንና ፊቱን እያሻሸ፦

"ተይኮ ተይኮ ተይኮ ተይኮ
እኔ ሰሞንኛ ቆራቢ ነኝኮ
እያሉ በናፍቆት መሰንቋቸው
ወጣትነቴን አስታወሱኝ
ባይቀሰቅሱኝ ምንቸገራቸው?
ውብ ወጣትነቴ ሄደች
እየተንሳፈፈች
ያመጣት የግዜ ወንዝ ወሰዳት
እንግዲህ
ቀስ በቀስ
ሳይታወቀኝ
ግንባሬ እየገፋ
በራዬ እየሰፋ
ሽበቴ እየበዛ
ዕድሜዬ እየገፋ ሄደ
አልፈልግም እምቢ
ማርጀት አልፈልግም
መሞት አልፈልግም
እምቢ አልፈልግም
እምቢ እምቢ እምቢ"

ብሎ ነበር በሌሊቱ አይነጋልኝ ሌላው መፅሐፉ። ዋ! ጋሽ ስብሐት ምስኪንና አሳዛኝ ሠው፣ እምቢ አላረጅም አለ ግን አረጀ፣ እምቢ አልሞትም አለ ግን ሞተ።

ነፍስ ይማር እንላለን፣ ትኩሳት እንደ ተገለፀው ትምህርት አዘል ነው፣ ወጣትነታችሁን ተንከባከቡ ይላል፣ እንዴት ? አንብቡ መልሱ እዚያው አለ።

በቸር እንሰንብት።

ሀበሻ 🇪🇹

08 Jun, 11:28


ታላቁ ደራሲ / ስብሐት ገ/እግዚአብሔር፦

ጋሼ ስብሐት ብለው ይጠሩታል ብዙዎቹ፣ ለሕይወት ቁብ የሌለው፣ በመፃፍና በድርሰት የታጠረ፣ ኢንተርቪው ሲደረግ በቀልድ አዋዝቶ የሚመልሳቸው መልሶች፣ ሕይወትንና የኑሮ ውጥንቅጥን አቅሎ የሚያይ፣ በሕይወት የሚያጋጥሙትን ክስተቶች ለመቀበል ቸል የማይል ሠው ነበር ጋሽ ስብሐት።

የፃፋቸውን ድርሰቶችና፣ በጋዜጦችና መፅሔቶች ያስተላለፋቸው ፅሑፎች ሲታዩ ይዘታቸው ገራሚ ነው፣ ቅርፃቸውም የሚያምርና የተሽሞነሞነ። ከጋሽ ስብሐት ድርሰቶች ልብን የሚሠቅሉና በተለዬ መልክ የተፃፉ ትኩሳትና ሌቱም አይነጋልኝ ናቸው፣ ለትውስታ በትካሳት ላይ ከዚህ በፊት ያስተላለፍኩት ፅሑፍ ተለጥፏል። በሌቱም አይነጋልኝ ድርሰቱ ያስተላለፋቸው መልእክቶች ገራሚ ናቸው። በተለይ በአማርኛ ሥነ ፅሑፍ ያልተለመዱ ቃላትን እንደወረዱ ፈሰስ ለማድረግና ታቡን ለመጣስ የመጀመሪያው ሠው ጋሽ ስብሐት ይመሥላል። ለምሳሌ ከዚሁ ድረሰቱ ተቀንጭባ የተለጠፈች ፅሑፍ አለች፣ ስብሐት ለምንም ታቡ ደንታ እንደሌለው የምትገልፅ። በዚያች ፅሑፍ ታቡን አጥባቂዎች ብቻ ሳይሆኑ የማያጠብቁም ሠዎች "የማይጋሩት" ክስተት እናያለን አንዲት ሴትን ለብዙ መጋራት። በድርሰቱ ሙሉ ተብላ የምትጠራ ከማሚት ጋር የምትኖር ሴተኛ አዳሪ አለች፣ እርሷን አንዱ ለአዳር ይዟት ሄደ ከአምሥት ጓደኞቹም ጋር ተጋሯት፣ ግንኙነትን የፈፀሙ ስድስት ናቸው፣ አንድ ለስድስት ብንል ያስኬደን ይሆን ? በብዙዎች አስተያዬት ይህ ሰብአዊ ባኅሪይ ሳይሆን እንደ እንሰሳዊ ባኅሪይነት የሚታሰብ ነው /የፈረደበት እንስሳ ብዙ ሥም ይሰጠዋል/። በውነት ነውን ? የሚል ጥያቄ ብናነሳ መልሱ አይደለም ነው። ስብሐት ያነሳው የሠው ልጅ ከሚኖርበት ሕይወት በመነሳት ነው፣ የሠው ልጅ ጨለማን ወይም አለመጋለጥን ተገን አድርጎ የሚፈፅመው ተግባር። ክስተቱን ፈፃሚዎች እንስሳትም ሠዎችም ናቸው፣ ልዩነቱ እንስሳት በግልፅ የሠው ልጅ በሥውር ማድረጋቸው ብቻ ነው። እንግዲህ ጋሽ ስብሐት የሠው ልጅ በሥውር የሚከውነውን ነው አደባባይ ያወጣውና፣ ጥፋተኝነቱ እምኑ ላይ ነው።

ጋሽ ስብሐት ነባራዊ እውነታን ለምን እንሸፋፍነዋለን ባይ ነው፣ የሚወደደውም በዚህ ፀባዩ ነው። ለምሳሌ ለማንኛውም የሠውነት ክፍል ስም እንዳለው ሁሉ ለመራቢያ አካላትም ሥም አለ። መራቢያ አካላትን በሥማቸው መጥራቱ፣ ሥማቸውን አደባባይ ማውጣቱ ክፋቱ ምንድርነው በማለት ራሡን ከጠየቀና ከራሡ ጋር ከተስማማ በኋላ ነው አደባባይ ያወጣው። በዚህ ቅንጣት እንደማያፍርና ተፈጥሯዊ በሆነ ነገር አፋችንን መሸበብ እንደሌለብን ነው የገለፀልን። ለምሳሌ እንደነ ሮዛ ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለትን የመሣሠሉ ድርሰቶች ታቡን መጣስ የተማሩት ከጋሽ ስብሐት እንደሆነ ይታሠባል።

ይህን ከብልግና ጋር የምናያይዘው ከሆነ ነው ትልቁ ስሕተት፣ ተፈጥሮን በተሠጠው ሥም በአደባባይ መጥራት በምንም መልኩ ብልግና ሊሆን አይችልም፣ ይህን እውነታ የማንም ልብ ሊዘነጋው አይገባም ከነባራዊ እውነታ ልንርቅ ስለማንችል።

በተለጠፈው ትኩሳት ድርሰቱ አስተያዬት ላይ ብዙ ሀሳቦች ተሰንዝረዋል የጋሽ ስብሐት፣ በዚያ ድርሰቱ ብዙ ነገር እንዳስተማረን፣ ወጣትነትን፣ እርጅናን፣ ሪቮሊሲዮንን፣ ፍቅርን፣ የመለየት ምሬትን፣ የጓደኝነት ሚስጥራትን፣ ሌሎችንም ክስተቶች። የተለጠፈውን አስተያዬት አንብባችሁ ተረዱ፣ ሀሳብም ሰንዝሩ። አስተያዬቱን እነሆኝ፦

ትኩሳት የስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ወጣትነት ትውስታ ድርሰት፦

ስብሐት በወጣትነቱ፣ ስብሐት በስርጅናው ስዕሎቹ እታች ይታያሉ፣ ስብሐት ወጣትነትን እንደሚያደንቅ ሁሉ እርጅናን ይፈራ ነበር፣ እርጅና ቃሉ ያሸማቅቀዋል። በፈረንሣይ ሀገር የ፪ኛ ዲግሪ ትምህርቱን በሚከታተልበት ወቅት በየቦታው የፈረንሣይ ሴትና ወንድ አዛውንቶች ያጋጥሙታል፣ የእርጅናንም አስፈሪነት ያስገነዝቡታል፤ ስብሐት ይህንን በትኩሳት መፅሐፉ እንዲህ ይገልፀዋል፦

" በጣም ይቀፋሉ የፈረንጅ ሽማግለዎችና አሮጊቶች። ጨምዳዳ ቆዳቸው የተሰነጣጠቀ ደረቅ ሠም ይመስላል። ቀጥቃጣዎች። ዝምተኞች። አገጫቸው ተገንጥሎ ወደ ታች የወደቀ፣ ከንፈራቸው የተንጠለጠለ፣ ጥርሳቸው የፈራረሰ ሽማግሌዎች። ጥርሳቸው አልቆ አፋቸው ወደ ውስጥ የጎደጎደ ፅማም አሮጊቶች። የመኖር ግዜያቸው አልፎ የሞት ግዜያቸውን ዘመናዊ ህክምና ከልክሏቸው ፣ ታችኛ ከንፈራቸውን እንደ ጡጦ እየጠቡ ሞትን ሲጠብቁ የሚውሉ የሕይወት ኦናዎች። ለዓይን ብቻ ሳይሆን ለአፍንጫም ይቀፋሉ ። የልዩ ልዩ መድኃኒት ፣ የእርጅና፣ የሞት ሽታ፣ ሳይቀበር መግማት የጀመረ ሥጋ።"

ለስብሐት አስፈሪው እርጅና እንደዚያ ነበር የሚታየው፣ አበስኩ ገበርኩ የሚያሰኝ፣ ተላላፊ በሽታን የመሠለ። ወጣትነትስ? እንዲህ ይገልፀዋል፦

" ጥሩ ነው ወጣት መሆን ገንዘብ ባይኖርህም ጤና ይኖርሀል፣ መልክ ባይኖርህም አንጎል ይኖርሀል፣ ዕውቀት ባይኖርህም ጉራ ይኖርሀል፣ ፍቅር ባይኖርህም ተስፋ ይኖርሀል፣ ደስታ ባይኖርህም ንዴት ይኖርሀል፣ መጨቆን ቢኖርብህ ሪቮሉሽን ታነሳለህ-------መኖር ቢያስጠላህ ወይም ቢያቅትህ ራስህን ትገድላለህ፣ ሠው ባያውቀም ቅሉ ታሪክ ይኖርሀል ወጣት ነህና።"

ወይ ጋሽ ስብሐት የሚገርም ነው። እስቲ የንዴት መኖር፣ የጉራ መኖርና ራስን መግደል እንዴት እንደ መፍትሔ ሀሳብ ይቆጠራል። ምናልባት የወጣትነት ድፍረትና ቆራጥነት እነዚህንም እንደ መፍትሔ ሀሳብ ያስቆጥር ይሆን።

ጋሽ ስብሐት በትኩሣት መፅሐፉ ብዙ ነገር ይላል፣ በብዙ ነገር ይፈላሰፋል፣ በፈረንሳይ ተማሪ በነበረበት ግዜ ማነሁለል ይችልበት ነበር፣ ከቆነጃጅት የፈረንሳይ እንስት ወጣቶች ጋር ዓለሙን ቀጭቷል፣ በቋንቋው ያነሆልላል፣ ዐዕምሮው ለዕውቀት ክፍት ነበር፣ በጥቂት ግዜ የፈረንሳይኛ ቋንቋን በቁጥጥሩ ስር አድርጎት ነበር፣ ችሎታው በዛዚ ርዕስ የንኮሎን መፅሐፍ በአማርኛ እንዲተረጉም አብቅቶታል፣ ጨዋነቱ፣መልከ መልካምነቱና ከፍተኛ የቀለም ቀበኛነቱ ተወዳጅነትን አትርፎለት ነበር።

የምትወደውንና መልከመልካሟን ፈረንሣይት ወጣት እንዲህ ይገልፃታል፦

" ሲልቢ በጣም ቆንጆ ናት፣ እጥር ምጥን ያለች ፈረንሳዊት ሆና ቡናማ ጉልህ አይኖችዋ ውስጥና ውብ አፍዋ ዙሪያ እንደ ነበልባል የሚውለበለበው ፈገግታዋ ልብ ያሞቃል። ወደ ኋላ የተለቀቀው ንፁህ ጥቁር ፀጉሯ ያብለጨልጫል ------ከታች ደግሞ አበጥ ያለው ዳሌዋ እንደ ፀጉሯ ይወዛወዛል። እግርዋ በብዙ ጥንቃቄ የተቀረፀ ውብ ፍጥረት ነው። ፍቅርም ምቾትም የምትቀሠቅስ ወጣት ትመስላለች።"

ስብሐት ቀላል ሠው አልነበረም። በሲልቢ እጅግ በጣም የሚወደድና የሚፈቀር ወጣት ነበር። በመፅሐፉ እንደተገለፀው የስብሐት ጨዋነትና በራስ ላይ የነበረው ዕምነት፣ ደንታ ቢስነት ብዙም ለሴትም ሆነ ለሌላ አለመጨናነቅ በሲልቢ ተወዳጅ አድርጎታል። ባይታወቅበትምና በድብቅ ቢይዘውም ቅብጥብጥ ወጣቷን ማፈቀሩና እንደምታስቀናውም በመፅሐፉ ገልጿል።

ባጠቃላይ ትኩሳት መፅሐፉ ትኩስ ጉልበት ስላለው የወጣቶች ከስብሐት ስራዎች ቀዳሚ ምርጫ መሆኑን ብዙ ወጣቶች ያወሳሉ።

በዚህ መፅሐፉ ስብሐት ስለ ፍቅርና ቅናት ተቃርኖና ጥምርታዊ ግንኙነት፣ ገፅታን ስለማንበብ፣ ስለ ሪቮሊሲዮን፣ የወጣትነትና አዛውንትነት የሕይወት ሂደት፣ የሴት ልጅ ውበትና መስህብነት፣ የፍቅር ሳይኮሎጂ፣ የቋንቋ ክህሎት ጠቀሜታ፣ ሠውን ከእንስሳት የሚለዩ ሠብአዊ ባኅሪያት፣ የወጣትነት ትርጉምና መገለጫዎቹ፣ ግዜን ስለ መመንዘርና መጠቀም፣ ምሳሌያዊ አገላለፆች፣ ስለ ጭቡና ጭቆናንም አካቶ በሚያስደምም ሁኔታ ከሽኖ አቅርቧል።

ሀበሻ 🇪🇹

15 Apr, 21:46


''ሰው ሲታመም የምንጠይቀው ከቋጠሮ ሰሐን ጋር ነው"
አለማየሁ ገላጋይ

ሰው ሲታሰር ' እግዚአብሔር ያውጣህ ' የምንለው ከፍትፍት አገልግል ጋር ነው ....አራስ የምትጠይቀው ከፔርሙዝ አጥሚት ጋር ነው ... የክርስትና አባታችን ለፋሲካ አክፋዩን የሚጠብቀው ድፎ ዳቦ ና አረቄ ነው ...እዝንተኛ የምናስተዛዝነው ሰባት እንጀራ ከአንድ ሰሐን ወጥ ጋር ነው ...ሟች የምንሸኘው ከገንቦ ጠላና ከለምለም እንጀራ ጋር ነው ...የቅዱሳንና የመልአክታት ተራዳኢነት የሚጎበኘን በስማቸው ከዘከርን ነው።

...ሰዕለታችን በሬ ወይም በግ ነው ...ሰርጋችን ፣ ልደታችን፣ እርቃችን፣ ሹመታችን፣ አምልኳችን፣ የሚበላ ነገርን ሙጥኝ ያሉ ናቸው ... ...ሌላው ቀርቶ አንድ ሰው ተምሮ ሲመረቅ ይዘን የምንሄደለት ስጦታ ብዕር ወይንም መጽሐፍ አይደለም ፤ ኬክ ፣ ብርቱካን ፣ ሙዝ ...ነው ።

በሽተኛ ስትጠይቅ ከብርቱካንና ከሙዝ ይልቅ መጽሐፍ መውሰድ እንደማላገጥ ይቆጠራል ። ጊዜውን ይገፋበት ዘንድ መጽሐፍ ማበርከት በሽተኛው እንዳይድን ከመመኘት እኩል ነው ። ለኛ ለኢትዮጵያውያን መጻሕፍት ከባዶ ገበታችን በስተዚያ የተቀመጡ ትርፍ ነገሮች ናቸው ። መጻሕፍት የሚያስፈልጉት ገበታችን ሞልቶ ከገነፈለ በኃላ ነው ብለን በይነናል። ገበታችንም አይሞላ ፤ መጻሕፍቱም አይነሱም ። ያልተረዳነው ቢኖር ለገበታ መትረፍረፍ ዙሪያ ጥምጥም ጉዞ መጻሕፍት አቋራጭ መንገድ መሆናቸውን ነው ።እንዴት ታዲያ ማንበብ መብላትን ይቅደም ? መቼ ይሆን ከምንኮራባቸው ባህሎቻችን በላይ ማንበብ ባህላችን ሆኖ የምንታወቅበት ናየምንኮራበት?......'''''

አለማየሁ ገላጋይ

ሀበሻ 🇪🇹

03 Mar, 04:50


#ትግራይ

" ' ያንቺ እቃ ብቻዬን ጠላ እየሸጥኩ ያሳደኳቸውን 2 ወንድ ልጆቼን ይመልስልኛል ወይ ? ' ነው ያለችኝ ! " - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በታሪካዊቷ ዓድዋ ከተማ በነበረው የዓድዋ ድል በዓል  ላይ እምባ እየተናነቃቸው 😭 ንግግር አድርገው ነበር።

እሳቸው በእንባ ንግግር ሲያደርጉ የበዓሉ ታዳሚ ህዝብ ከፍተኛ የሀዘን ስሜቱ ከፊቱ ይነበብ እንደነበር በስፍራው የነበረው የቲክቫህ ቤተሰብ አባል ገልጿል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ምን አሉ ?

" ዛሬ ወደ ትግራይ ስመለስ በህሊናዬ የሚመጡብኝ ብዙ ትዝታዎች አሉብኝ።

ይቅርታ አድርጉልኝና አጋጣሚውን ተጠቅሜ ማንሳት እፈልጋለሁ።

በትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልለው ከነበሩ ወገኖች መካከል አንዷ ፈንጠር ብላ የተቀመጠች አንዲት ሴት ለማነጋገር ሞክሬ ነበር።

በተፈናቃዮች ካምፕ ጉብኝት ልብን የሚሰብር  ነው። ከቤት ንብረታቸው ወጥተው ፣ ክብራቸውን አጥተው ቁጭ ብለው ጉብኝት .. እኛ ደግሞ እንመጣለን ልናያቸው።

ታዲያ ያችን ሴት ጠጋ ብዬ ሳነጋግራት፤ በጥሩ አልመለሰችልኝም። ጥቂት ያመጣሁትን እቃ እንድታከፋፍልልኝ ነበር ልጠይቃት የነበረው ' ያንቺን እቃ አልፈልግም ' አለችኝ።

በሆስፒታል እና በመጠለያ ጣቢያቸው ሄጄ ያየዋቸዋን ሴቶች በእጅጉ አስባቸዋለሁ። እቺን ሴትዮ ለምንድነው የምትመልሽልኝ ስላት ' ያንቺ እቃ ብቻዬን ጠላ እየሸጥኩ ያሳደኳቸውን ሁለት ወንድ ልጆቼን ይመልስልኛል ወይ ? ' ነው ያለችኝ መልስ የለኝም ፤ አይመልስም ብቻ ነው ያልኳት።

ጦርነቱ ተዛምቶ በአፋር ክልል ሰመራ ሆስፒታል ህክምና ላይ የነበሩ የተማረኩ የህወሓት ታጋይ ሴቶችን አግኝቻቸዋለሁ ሳናግራቸው ያሉኝ ከልቤ አይጠፋም ፤ ቦታቸው እዛ አልነበራም ትምህርት ቤት ነው።

ያሉኝ ' እኛ መመለስ የምንፈልገው ወደ ትምህርት ቤት ነው ' ይሄንን ወግቼ ያንን አሸንፌ የሚል ዓላማ አልነበራቸውም። በክፍላቸው ግርግዳ ላይ የፃፉት የለጠፉት የአፋር ህዝብ እንዴት ደግ እንደሆነ ነው። ኢትዮጵያዊ ለኢትዮጵያዊ እንዴት እንደሚረዳዳ ነው።

ሌሎችም አሉ ብዙ እርጉዝ ሆነው ሶስት ልጅ ወልደው ሲንከራተቱ የነበሩ ... ለማንኛውም ብዙ መንከራተት ነበር።

ዛሬ እዚህ ቆሜ የትግራይ እናቶች ያሳለፉትን #ሰቆቃ በእውነቱ እረዳለሁ ለማለት ነው ይሄን ሁሉ የምናገረው። እግዚአብሔር ብርታቱን ይስጥዎ !!

ዞሮ ዞሮ የማንኛውም ግጭት መጨረሻው ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ የሰላም ስምምነት መፈረሙ አይቀርምና ይህ ሳይሆን ተጨራርሰን ተጨካክነን ፣ ዘርና ሃይማኖት መለያያ አድርገን ሃይማኖቶችን ከፋፍለን ሳይሆን በቅድሚያ መከላከል እንዳለብን መገንዘብ አለብን።

የዓድዋ ባለቤቶች እንዳልሆንን ገፅታችንን አጉድፈን አበላሽተናል። "

#TikvahFamilyAdawa

@tikvahethiopia

ሀበሻ 🇪🇹

02 Mar, 20:08


አድዋ የአለምን አካሄድ የለወጠ ታላቅ ክስተት ነው።

የአድዋ ድል ባይኖር አለም መልኳ ተለውጦ ሌላ ይሆን ነበር።
የሐርቫርድ ዩኒቨርስቲው Raymond jonas "The battle of Adwa" በሚል መፅሐፉ እስከ አሁን ከተለመደው የተለየ ሃሳብ ስለ አድዋ ድል አስፍሯል።

እንደ ፀሐፊው ሃሳብ ፥ ኢትዮጵያ በአድዋ ጦርነት በጣሊያን ወራሪ ብትሸነፍ ኖሮ አለም መልኳ ይለወጥ ነበር። አፍሪካ እንደ አውስትራሊያ ፥ ኒውዝላንድ እና ሰሜን አሜሪካ የነጮች መኖሪያ ወደ መሆን ትሸጋገር ነበር። አፍሪካዊ ሙሉ ለሙሉ በነጮች መዳፍ ውስጥ ገብቶ በጦርነት ፥ በበሽታ እና በባ*ርነት ቁጥሩ ተመናምኖ በገዛ ምድሩ አና*ሳ እንዳይሆን መሰረት የጣለው የአድዋ ድል ነው።

የአውሮፓ የጋለ መስፋፋት ህልም ላይ ውሃን የቸለሰ ድል ነው ፥ አድዋ። ጥቁሮች የነጭን የባርነት ቀንበር እንዲፋለሙ የልብ ልብ ሰጥቷል፥ ነጮች ደግሞ ቆም ብለው እንዲያስቡ የማስጠንቀቂያ ደውልን ደውሏል።

የ "The Battle of Adwa" ፀሐፊ 'በአድዋ የተነሳ አፍሪካ የነጮች መኖሪያ ከመሆን ከመተርፏ በተጨማሪ አውሮፓውያን ወደ ኢሲያ እንደልብ እንዲይስፋፉ እግድን ፈጥሮባቸዋል' ይላል።

የዚህ ትርጉሙ ምንድነው? አድዋ ያለ ጥርጥር የአለምን መልክ እንደወሰነ አስረጅ አይደለም?

ተስፋኣብ ተሾመ

ሀበሻ 🇪🇹

02 Mar, 04:36


የንባብ ባህላችን እየተዳከመ ነው ሲባል ይገርመኛል፤ ሲጀመር የንባብ ባህል ኑሮን ያውቃል ወይ? እዛና እዚህ በግለሰቦች ላይ የተንጠለጠለ የግል ፍላጎት ባህል ይባላል? እንዳውም "አንባቢ የመምሰል" እና "በንባብ የመጎራት" ባህላችን አስቀያሚ ባህል ፈጥሯል! "ምሁር ቅብ" የመሆን ባህል!? የፈረደበትን ጎግል ዞር ብታደርግበት ሌጣውን የሚቀር "ምሁር" ነው በየሚዲያው አገር ይያዝ የሚለው!

ሀበሻ 🇪🇹

01 Mar, 06:55


"ሴቶች በምንም አይማልሉም አትድከሙ!"
(አሌክስ አብርሃም)

በነገራችን ላይ እንደምታስቡት ሴት"መጀንጀን" ላይ አሪፍ አይደለሁም! ስለመጨረሻ ጅንጀናየ ላውጋችሁ! የሆነ ጊዜ አምስት መንገዶች አስር ማሳለጫዎች ምናምን የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ሴት ልጅ በራሱ የሚተማመን ወንዳወንድ ወንድ ትወዳለች የሚል ነገር ሰማሁ! እና አንዲት በዛ ሰሞን የወደድኳትን ልጅ ማማለል ፈለኩ! ተቀጣጥረን ተገናኘን ምሳ አብረን በላን (በድሮሮሮሮሮሮሮ ጊዜ የዛሬ ስድስት ዓመት ሰዎች ምሳ ይገባበዙ ነበር) እና ከመሬት ተነስቸ ጀብዱ ነገር ማውራት ጀመርኩ!

"ይገርምሻል የሆነ ጊዜ አንድ ዳይኖሰር የሚያክል በሬ ከቄራ አመለጠ ፤ እና ከቄራ ቡልጋሪያ ድረስ ሰባት ወንዶች ሶስት ሴቶች ሁለት መኪና በቀንዱ እየወጋ አተረማመሰው! ፖሊስ ሁሉ ማስቆም አልቻለም! እና እኔ ስደርስ ወደሆኑ አሮጊት ቀንዱን አሹሎ እየሮጠ ነበር ... በባልቴቷና በበሬው መካከል ሶስት የበሬ እርምጃ ሲቀር ተፈትልኬ ሮጥኩና መሀላቸው ገብቸ ስቆም ጫማየ እንደመኪና ጎማ ፉጭጭጭጭጭጭ አለ! በሬው ደንግጦ ቆመና ተፋጠን እንደቆምን በቀስታ ቀረብኩት .... በእግሩ አስፋልቱን እየቆፈረ ሊወጋኝ ሲሞክር ሸወድኩትና አንገቱ ላይ የታሰረውን ገመድ ቀጨም አድርጌ ለባለቤቱ አስረከብኩ! ይገርምሻል በተፈጥሮየ አልፈራም!

ልጅቱ ስትሰማኝ ቆየችና የበሬውን ነገር እንዳልሰማ ሰው " ዳይኖሰር ስትል አስታወስከኝ! ለምን ዛሬ ኤድናሞል ሙቪ አናይም? አሪፍ የዳይኖሰር ሙቪ አላቸው" ብላ በሚያማምሩ አይኖቿ አየችኝ! ጀብዱየን ውሃ ቸለሰችበት! ቅር እንዳለኝ ወደኤድናሞል የሚወስደን ታክሲ ስንጠብቅ አስገራሚ ነገር ተፈጠረ .... በሬ! የፈረጠጠ በሬ መንገዱን እያመሰው ከፊት ለፊታችን መጣ ... በእርግጥ ነፍሴን ለማትረፍ ባደረኩት ሩጫ ከበሬው የበለጠ ብዙ ሰው እየገፋሁ ሳልጥል አልቀረሁም! ልጅቱ ጋር በተፈጠረው ግር ግር እንደተጠፋፋን ከዛ በኋላ አልተገናኘንም! በእርግጥ ትዝ ያለችኝም የሆነ ካፌ ገብቸ ሁለት ሊትሩን ውሃ ከጠጣሁ በኋላ ነው!

ሀበሻ 🇪🇹

26 Feb, 14:12


ቀጥ ብለህ ቁም!
(አሌክስ አብርሃም)

ጎተራ ኮንዶሚኒየም ስኖር ወጣት ባልና ሚስት ጎረቤቶች ነበሩኝ! በጣም የሚፋቀሩ ! እና ሌሊት ሌሊት አንዳንድ ተቀባይነት የሌላቸው ድምፆች ያለዕቅድ ግድግዳውን አልፈው ይረብሹኝ ነበር! ሌላ ሌላው ነገር ሳይሆን በተለይ ሚስቱ የባሏን ስም በቁልምጫ ስትጠራው "ምናለ ይሄን ለቁልምጫ የማይመች ስም ቢያስቀይረው" እያልኩ በሌሊቱ አስባለሁ! ወይም የብዕር ስም እንደሚባለው የእንትን ...ስም ቢጠቀሙ! ከነገሩ ይልቅ የስሙ ቁልምጫ ነበር በሀፍረት ጆሮየን የሚያግለው! (ለአንባቢወቸ የስነ ልቦናና የስነ ተዋልዶ ስሜት ስል ስሙን እዘለዋለሁ)

አንድ ቀን ድንገት ቤቱን ለቀው ሄዱ! ለአንድ ሳምንት ከደበረኝ በኋላ😀 ሌሎች ባልና ሚስቶች ተከራዮች ገቡ! በተለይ ሚስትየዋ የፆሎት ሰው ነች! ባሏ ስራ ሲሄድ ቤቷን ዘግታ ይሄን አጋንንት ስትለበልበው ነው የምትውለው...ከጎተራ ልቀቅ ...ከሳሪስ ልቀቅ ...ከቦሌ ልቀቅ...ከቡልቡላ ....ስገስፅ ነው የምትውለው! ለወሬ ነጋሪ አንድ አጋንንት አዲሳባ አታስቀርም! ድምጿ ራሱ ጎርናና እና አስፈሪ ከመሆኑ ብዛት እኔ ራሱ ልለቅ ይቃጣኝ ነበር! ፀባችን ከስጋና ደም አይደለም ስትል ሻንጣየን አስቀምጨ ተረጋጋሁ!

እና አንድ ሌሊት ያ ድምፅ አነቃኝ ! መጀመሪያ ሹክሹክታ ነበር በኋላ ግን ድምጿ ጨመረ " በአንተ ላይ በተሰጠኝ ስልጣን አዝሃለሁ... ቀጥ ብለህ ቁም ! የተፈጠርክበትን አላማ ትፈፅም ዘንድ ቀጥ ብለህ ቁም ! ስራህን እስክታከናውን ፀንተህ ቁም! የሚያልፈሰፍስህ መንፈስ አሁን ተመታ! ..."

"አሜን" ይላል ባሏ በሚያሳዝን ድምፅ! ምንድነው ይሄ ቁም የሚባል ነገር ? ብየ እኔም በቀስታ ፀለይኩ "ጌታ ሆይ ምንም ድምፅ የማያሳልፍ ግድግዳ ባለው ቤት ባርከኝ! ልጅህን ክፉ የሚያሳስበውን መንፈስ ከጎተራ ...ወሎ ሰፈር ...ከቦሌ... ከቡልቡላ ...ንቀለው! ከሶስት ወር በኋላ ፆሎቴ ሰመረ እኔን ከጎተራ ነቀለኝ!

ሀበሻ 🇪🇹

26 Nov, 07:02


[እኔ አለሁ እንዳለሁ
እንዴት ነሽ እመ?]

ከጦርነት ቀጠና ወጥቼ አዲስ አበባ እንደገባሁ የመጀመሪያው ስራየ ስራቦታ ጎራ ማለትና ቤት መፈለግ ነበር። እውነት ለመናገር ከሆነ አዲስ በብዙ ግልምጫዎችና በሰቃዥ የኑሮ ውድነት የታጀበች እጅግ ባይተዋር ከተማ ሆና ነው የጠበቀችኝ።

አዲስ አበባ ቁመት ሙሉ እንባ ስጋ ሙሉ ኧረወይለሊቴ ሆናለች ወገን።

“ጃክሮስ ቆንጆ ቤት አግኝቼልሀለሁ” ደላላው ነበር

ሄድኩ

ቤቷ ሁለት በሶስት ናት። ጭራሽ መሀከሉ ላይ እንደሰፊው ህዝብ መድረሻ ያጣ የሚመስል ኮለን ተገትሯል።

“ኧኸ እንዴት ነው ወደድሻት? 3500 ናት”

ምን ነካህ ደላላ!? ይሄኮ እንኳን አልጋ ሊያዘረጋ ጠረንጴዛና ወንበር ሊይዝ ፍራሽ እንኳን ካላጠፍኩት አያስነጥፈኝም።

😳

የውሻውን ቤት ነው እንዴ ልታከራዮኝ ያሰባችሁት🤔

“ውሻውማ የተሻለ አግኝቶ ስለወጣ ነው እምናከራይህ” አከራዩዋ

እንባየ ደርሶ ግጥም አለ🥴

ደግሞ ሌላ ቤት መስቀል ፍላወር

“ድርድር የለውም። 6 ክፈል” ሸምገል ያሉ ናቸው አከራዮ

ቆንጀት ያለ ቤት ነው እሺ እከፍላለሁ

“ታመሻለህ?”

አዎ አንዳንዴ ሚቲንግ ሲኖረኝ እስከ 4 ምናምን ላመሽ እችላለሁ

“አይሆንም አይሆንም እስከ 2 ልፍቀድልህ”

እንዴ ልጅዎ አደረጉኝ እንዴ!

“ምን አልክ? ይሄንም እኔ ሆኜ ነው”

እንዴ ትራንስፖርቱ ራሱ ያስመሻል እኮ። ቁልፍ ካለ ይስጡኝ ላስቀርጸው።

“ቁልፍ? ለምንድን ነው ቁልፍ እምሰጥህ? አምሽተህ እየገባህ ልታዘርፈኝ!”

እ😳

“ተወው ለሌላ አከራየዋለሁ። በዚያ በኩል ውጣ”

እንባየ ደርሶ ግጥም አለ🥴

ከሰአቱን ድክም ሲለኝ ልረፍ ምሳም ልብላ ብየ የሆነ ሆቴል ገባሁ

ቅቅል ተፈርሾ አምጪልኝ።

By the way ቅቅል ኢዝ ማይ ተወዳጅ ምግብ

በድንች፣ በካሮት እና በሆኑ ቅጠላቅጠሎች የታጀቡ 3 ግድንግድየ ቅልጥሞች መረቅ ደፍቀው መጡ

ተጠራጠራጠርኩ

ሂሳብ ስንት ነው እናት?

“550”

እ😳

እንስቷ እንባዋ ደርሶ ግጥም አለ🥴

ከጎጃም በእግርና በባጃጅ ያስወጣኸኝ አንድየ አንተ ታውቃለህ ብየ በላሁት

ሂሳብ ከፍየ ስወጣ ከጀርባየ የሆነ ድምፅ ሰምቼ ዞር ስል አስተጋጇ እጇን እያውለበለበች

“ዌል ካም ቱ አዲስ የዝቅተኛው ማህበረሰብ አባል” ስትለኝ ደረስኩ

እስኪ ሆዴ ቻለው ቻለው ቻለው እያልኩ ወደስራ ቦታየ ወክ አደርግ ጀመር

አለም ሲኒማን እልፍ ስትሉ ባስ መጠበቂያው አለአይደል፣ አንድ በግምት 60 ዎቹ አካባቢ የሆነ ሰውየ እግሩን አጥፎ ወንበሩ ላይ ተቀምጦ አይኑን ጨፍኖ
“ኦም…ኦ….ም…. ኦ….ም” ይላል

ሆዴ ቦጭ ቦጭ አለ
ዝርዝር የአምስት ብር ሳንቲሞች መፀወትኩት

ሰውየው ግን አንድ አይኑን ገልጦ
“ወንድም ዮጋ እየሰራሁ እንጂ እየለመንኩ አይደለም። አዲስ አበባ መቆየት ከቻልክ ይጠቅምሀል ገንዘብህን ያዝ” አለኝ

አደነጋገጤ😳

ህዝቤ እንዳለ ለቆ ነው🤔

ቢሮ ልደርስ አካባቢ የሆነ ሙዚቃ ሰመቼ ዞር ስል የሬሳ ሳጥን የሚሸጥበት ሱቅ ላይ ሁለት ወጣቶች እየቃሙ በትንሽየ ስፒከር

“ጉርምርሜ ና ጉርምርሜ ያሆ መሌ ያሆ መሌ ና ጉርምርምርሜ” የሚል ሙዚቃ ያዳምጣሉ

ጆሮየ ፕራንክ ነው በለኝ😳

እውነት ለመናገር የሬሳ ሳጥን መሸጫ ውስጥ ሙዚቃ ስሰማ ይህ የመጀመሪያየ ነው

“የኔ ልጅ ተውው አሽሙር ነው። መንገድህን ቀጥል” አሉኝ በአጠገቤ ሲያልፉ የነበሩ እናት

ወይ አዲስ አበባ እንዲህ ሁሉን ነገር ድብልቅልቅ አደርጋ ትጠብቀኝ። ታክሲዎች ትንሽ መንገድ አምቦራችተውህ 10 ብር አምጣ ይሉሀል። ከመሸብህ ይሄ ብር ሁለት እጥፍ ሁሉ ሊሆን ይችላል። ራይድ ልያዝ ካልክ happy textile road bruh በሶስት ቀን ሆድህ ፈርደሀል ማለት ነው!

ደግሞ ሰው ምንድን ነው እንዲህ የተፈራራው🤔ለንደን ያለህ ይመስል ማንም ሰላም ሊልህ አይፈልግም። ሰላምታ ብታቀርብም አበጀህ የሚልህ የለም።

ወንድም ሰአት ስንት ነ..?

“እግዜር ይስጥልኝ እኔ ራሱ የታክሲ ብቻ ነው የቀረኝ። እህል ከቀመስኩ ዛሬ ሁለት ወሬን ደፈንኩ”

እ😳

“ተወኝ በቃ እኔ የትኛውንም ፖለቲካ ፓርቲ አልደግፍም። የሁሉም ባንክ አካውንት አለኝ”

ዋ ኧረ ምንጉድ ነው ብየ ወደ ጎዳናየ ተመለስኩ

ወገን እንግዲህ አዲስ ጥይት አልተተኮሰባትም እንጂ ጦርነት ላይ ናት የሚባለው ነገር እውነት ነው መሰል…

ቢጨንቀኝ
እመ ጋ ደወልኩና
“እመ ለካንስ ይሆን መስሎኝ እንዲያው ሳላውቀው ከሞት ሸሽቼ ወደ ሞት ነው የመጣሁት” አልኳት

እመ ግን ሳግ በሚተናነቀው ድምፅ
ምን አለችኝ?

“ልጅ ታምሩ ምን የሚያጓጓ ህይወት ኖሮህ ነው ሞት የሚያስፈራህ!”

እንባየ ደርሶ ግጥም አለ🥴

@wegoch
@wegoch
@paappii

By Tamiru Temesgen

ሀበሻ 🇪🇹

16 Nov, 16:39


የአድዋው ጀግና ራስ መኰንን የታፈነው ዜና መዋዕል በአማርኛ ተተርጉሞ ለንባብ በቃ!

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ከሚይዙት ታላላቅ የጦር ሰዎች ውስጥ ቀዳሚው ራስ መኰንን ናቸው፡፡ እኒህ ታላቅ የጦር መሪ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አባት፤ የምኒልክ ዙፋን ታማኝ፤ የሣህለ ሥላሴ የሥጋም የመንፈስም ውርስ ያላቸው ታላቅ የጦር ሰው ናቸው ፡፡
 
ይህ ዜና መዋዕል መነሻውን ከዘመነ አክሱም በማድረግ የንግሥና ሐረጎችን እያጣቀሰ፣ ዋናውን የታሪክ መቼቱን ዐፄ ምኒልክ አንኮበር ላይ ከተወለዱበት ከ1836 ዓ.ም. ያደርጋል፡፡ ከዚህ ዘመን ጀምሮ ፍሰቱ እስከ 1910 ዓ.ም. ዋዜማ ይቀጥላል፡፡

በእነዚህ ዘመናት በኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት የተከናወኑ ታላላቅ ተግባራት በዚህ ዜና መዋዕል ተመዝግበዋል፡፡ የመጽሐፉ ርእስና ዋና ተተራኪ ራስ መኰንን ይሁኑ እንጅ በሐረር የተሾሙ ደጃዝማቾች የአስተዳደር ሁኔታ፣ ሐረርና ጅጅጋ ሲያዙ የተካሄዱ ጦርነቶች፣ በምሥራቅ ኢትዮጵያ የተተከሉ ቀዳምያን አድባራት ዝርዝርና የአተካከል ታሪክ፣ በማዕከላዊ መንግሥት የነበሩ የሥልጣን ሽኩቻዎች፣ የአድዋ ጦርነትና ሌሎችም አካባቢያውያን ዘመቻዎች ተካተዋል፡፡

ስለሆነም ይህ ዜና መዋዕል በዘመኑ ስለነበረችው ታሪካዊቷ ኢትዮጵያ አስተዳደር አንደኛ ሁነኛ ምንጭ ሆኖ ሊጠቀስ የሚችል ድንቅ ትርጉም ነው፡፡

ዜና መዋዕሉን አንብቦ ምስክርነቱን የሰጠው ደብተራና የሕግ ባለሙያው በአማን ነጸረ የዜና መዋዕሉ ጸሐፊ ግራጌታ ኃይለጊዮርጊስ የአጻጻፍ ክህሎታቸውን እንዲህ ሲል አወድሶታል፡- ‹‹… ጸሐፊው ፍሬ ነገር አያዛቡም፡፡ ታሪክ አያንዛዙም፡፡ የድርጊት ጊዜን፣ ቦታንና ሁኔታን አይስቱም፡፡ ከቀደምት ጸሐፍት በተለየ ዓመተ ምሕረትን በጥንቃቄ ይመዘግባሉ፡፡ ከውጋዴን እስከ አድዋ ዐቢይ ድርጊት የተፈጸመባቸው የቦታ ስሞችን ፊደል ሳያዛንፉ ጠንቅቀው ይጽፋሉ…››

ሀበሻ 🇪🇹

14 Nov, 11:03


"ዛሬ ቅዳሜ አይደለም" በተሰኘው መጽሐፍ ዙሪያ የተሰጠ ዳሰሳ።

በዮሴፍ ተመስገን (የቋንቋ እና ሥነ ፅሁፍ መምህር)

ክፍል አንድ

በአዳም ረታ የምናውቀው የህጽናዊነት አጻጻፍ በ “ዛሬ ቅዳሜ አይደለም” መጽሐፍ ውስጥ ረብቦበታል የሚል ሀሳብ ውስጤ ተፈጥሮ ነበር፡፡ (ለመጀመሪያ ጊዜ ሳነበው፡፡)

ነገር ግን ከደራሲው ማረጋገጫ ካላገኘሁ በስተቀር ይህንን ሀሳብ እንድቀይር የሚገፋፋ ስሜት ከውስጤ ተፈጥሯል፡፡ (ለሁለተኛ ጊዜ ሳነበው፡፡) መጽሐፉን ሁለት ጊዜ አንብቤው የተፈጠረብኝ ስሜት ሁለት አይነት ነውና የማስቀምጠው አልሆነም፡፡ እሰልሠው ግድ ነው፡፡
የመጽሐፉ ደራሲ ናትናኤል ቀረዓለም “ዛሬ ቅዳሜ አይደለም” የመጀመሪያ የታተመ መጽሐፉ እንጂ የመጀመሪያ መጽሐፉ ላለመሆኑ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ቁጭ ብለን እናጠናቸው ዘንድ ሊያስገድዱን የሚቃጣቸው ቴክኒኮችን በመጽሐፉ ውስጥ አካቷል፡፡ (ዶክተር እንዳለጌታ ከበደ ለዚህም ይመስለኛል መጽሐፉን “ቋንቋው ፣ ቴክኒኩ እና የሀሳቡ ፍሰት አጃኢብ ነው፡፡) ሲል የገለጸው፡፡

መጽሐፍ አንብቤ የመጽሐፍ ዘውግ ፣ ቴክኒክ እና የአጻጻፍ ስልት መለየት እስኪሳነኝ ድረስ ስደነቅ ይህ የመጀመሪያዬ ነው ብል ብዙም ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡ “ምን አይነት መጽሐፍ ነው?” ብዬ ከማንበቤ በፊት ለጠየቅኩት ጥያቄ ያገኘሁት መልስ “በአጫጭር ታሪኮች እንዲሁም በዘፈቀደ ሀሳቦች የተዋቀረ” የሚል መልስ ነበር ያገኘሁት፡፡ ያገኘሁት መልስ እውነት ያልነበረ ስለመሆኑ እመሰክራለሁ፡፡ 

የመጽሐፉ የመጀመሪያ ገጽ ላይ…
“…እውነት የሚባል ነገር የለም! ሊል ፈልጎ…”
“…እውነት የሚባል ነገር የለም! ማለቱ እውነት አይሆንምና ተወው…” (ገጽ 1) የሚል ሀሳብ ስታገኙ አንዴ አንብበን ወደ ቀጣዩ ገጽ እንሻገር ዘንድ መጽሐፉ እንዴት ይፈቅድልናል?

ሮማን ተወልደ መጽሐፉን ስትገልጸው “አጫጭርም ወጥም ፣ ወጥም አጫጭርም ፣ ፍልስፍናዊ ልብ ወለድ” ብላዋለች፡፡ እውነት አላት፡፡ ያለማቋረጥ የሚዥጎደጎዱ ጥያቄዎቹ እና የተሰመረበት ምላሽ ሳይሰጥ አንባቢውን አስተክዞ ፣ ማለቂያ ወደሌለው የሀሳብ ዓለም አሻግሮ መጽሐፉ ወደ ቀጣዩ ገጽ ይሻገራል፡፡

“…ልጄ ማታ በጊዜ ነው የምትመጣው?” እናቱ ጠየቁት፡፡
“እርግጠኛ አይደለሁም እማዬ!” መለሰ፡፡
እየወጣ ማብሰልሰል ጀመረ፡፡
“እርግጠኛ አይደለሁም!” ስል ምን ማለቴ ነው?
በምንም አይነት ነገር ላይ በእርግጠኝነት እርግጠኛ መሆን ይቻል ይሆን?
በጊዜ ስለመምጣቴ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ጭራሽ ስለመመለሴስ እርግጠኛ መሆን እችላለሁ?
አይመስለኝም፡፡
ሰው እኮ እርግጠኛ ስለመሆኑ ራሱ በእርግጠኝነት መናገር አይችልም፡፡
እኔም… ሰው እርግጠኛ ስለመሆኑ በእርግጠኝነት መናገር አይችልም ብዬ በእርግጠኝነት መናገር አልችልም፡፡”
ማብሰልሰሉን ቀጠለ፡፡… (ገጽ 44)

ማብሰልሰሉን የሚቀጥለው ገጸ ባህሪው ብቻ ሳይሆን ተደራሲው መሆኑንም ማስተዋል ልብ ይሏል፡፡

ይህ በየመሀሉ ከእናቱ እና እህቱ ጋር የሚጨዋወት ገጸ ባህሪይ ካፌው ውስጥ የሚመሰጠው እንዲሁም ከመምህራኑ ጋር የሚከራከረው መምህር ይሆንን ብዬ እጠረጥራለሁ፡፡ (ገጸ ባህርያቱ ስም አልተሰጣቸውምና እርግጠኛ ለመሆን ቢከብደኝም እርግጠኛ የሆንኩ ይመስለኛል፡፡ ያው መጽሐፉ “ሰው ሾለ አንድ ነገር በእርግጠኝነት እርግጠኛ መሆን አይችልም…” ብሎ እንዳይሞግተኝ እየሰጋሁ፡፡ 
መጽሐፉ በዚህ ገጸ ባህርይ ላይ ያጠነጥናል የሚል ድምዳሜ መስጠት ግን ስህተት መፍጠርም ይሆናል፡፡ በአጫጭር እና ራሳቸውን የቻሉ በሚመስሉን (ራሳቸውን የቻሉ ሊሆኑም ከሌሎች ጋር ሊደጋገፉ ቢችሉም) ታሪኮች ውስጥ አላገኘነውም ይሆን የሚል ጥያቄን ማስከተሉ አልቀረም፡፡

…በብቸኝነት አላደገም፡፡
በብቸኝነት አድጓልም፡፡
ከሰው አልተለየምና በብቸኝነት አላደገም፡፡
ሰው መሀል ሆኖ ተነጥሏልና ብቸኝነት አጥቅቶታል፡፡
ፀሐይ በብቸኝነት የምታንጸባርቀውን ጨረር ተመልክቶ ብቸኝነቱ ኃይል ስለመሆኑ አያስብም፡፡
ውብ ቅላጼ ያለው ሕብረ ዝማሬ አድምጦ ብቸኝነቱ ድክመት ስለመሆኑ አያስብም፡፡
እሱ እሱ ነው፡፡
ብቸኛ የሆነ፡፡
ብቸኛም ያልሆነ፡፡  (ገጽ 10)

የገጸ ባህርያቱ ስም አልባ መሆን ገጸ ባህርያቱን እንዳንወዳቸው ወይም እንዳንጠላቸው አላገደንምና (እሷ ፣ እሱ እንዲሁም እነሱ) ያጎደሉብን የለም፡፡ እንዲያው አንዳንዴ ጥቂት እንድንመራመር እና የመጽሐፉን ገጽ እንድንገለብጥ ማመንታት ውስጥ ቢከቱንም፡፡

ይቀጥላል

ሀበሻ 🇪🇹

13 Nov, 09:08


ማስታወሻ - ዘነበ ወላ

በስብሐት ገብረእግዚአብሔር (1928 እስከ 2004ዓ.ም) የሕይወት ታሪክና ኪነጥበባዊ ክህሎት ዙሪያ በዘነበ ወላ በተጻፈው "ማስታወሻ" መጽሐፍ ላይ የኢትዮጵያ ቡክ ፎረም አሰናኞችና ተሳታፊዎች ውይይት ያደርጋሉ።

የውይይቱ ሊንክ:

https://www.clubhouse.com/invite/DwdI13znJQ0b03yXn5ad0Aq8Wp5dcBo9N0:jx_iw6QCLbPwS2D4t4CwauP7Is16VSledfGjvY_K2G8

ሀበሻ 🇪🇹

13 Nov, 09:05


‘ጊዜ ድሮ ቀረ’
(ጋዜጠኛና የኪነጥበብ ባለሙያ ተፈሪ ዓለሙ)


ድሮ ጊዜ ነበር!!!
ጠላትን ለማጥመድ ወዳጅ ለመሰብሰብ፣
ፍቅር ለመጠንሰስ ሴራ ለመሸረብ።
የፍንጥር ለማለት ለመጣል ደንቃራ፣
ለወሬ ክርክር ለምክር ለሴራ።
ለስድብ ሰላምታም፣
ለውዳሴ ሃሜታም።
አድፍጦ ለማድባት ለመደበቅ ሸሽቶ፣
ግብዣ ለመታደም ለመጋበዝ ጠርቶ።
ለጠብ ቀን ለመቁረጥ ለፍልሚያ ቀጠሮ፣
ሰዓት …
ዕለት …
ዓመት …
ጊዜ ነበር ድሮ!
ዘንድሮ ጊዜ የለም!!!
ከሚፈቅዱት ወዳጅ ከሚወድዱት ጋርም፣
ቆይታ ለመያዝ ወግ ለመደርደርም።
አላደርስ እያለ ለእግዚአብሔር ሰላምታ፣
ዛሬ ምን ጊዜ አለ ለፍቅር ጨዋታ፧
ለምን ሰው ዘንድሮም ጠብ ጠብ ያሰኘዋል፧
ምን ያኳርፈዋል፧
ያቀያይመዋል፧
እንኳን ተቀያይሞ በጥል ተራርቆ፣
ጠኗል መተያየት ከአንጀት ተነፋፍቆ።
መቼ ጊዜ አለና፧፧፧
የሃሳብ መለያየት በአንድ አለመግጠሙ፣
ያለ ነው ይኖራል አለመጣጣሙ።
በጋራ ሚከፈል ብዙ እቁብ እያለን፣
ሃሳባችን ቢለይ እኛን ምን ለያየን፧


ጎበዝ!
መኖር እንደዚህ ነው!!!
ከልዩነት በላይ ከቅራኔ ልቆ፣
አልፎ ሂያጅ ትኩሳት ግጭቶችን ንቆ።
አርቆ አስተውሎ የጋራን አላማ፣
በፈገግታ አንግቶ የኩርፊያን ጨለማ።
ጠብ መምጫውን መንገድ ባቋራጭ አሳብሮ፣
ጠብ መንጃውን መሪ አፈሙዝ አዙሮ።
አይተው እንዳላዩ እንዳልሰሙ ሰምተው፣
ቸለል ቀለል አርገው በማለፍ በመተው፡
ችሎ ተችሎ ነው ሰው አብሮ ሚኖረው!
በመቻቻል እንጂ እየተላለፉ፣
በትንሽ ትልቁ ከተኮራረፉ፧
መቼ ቀን ሊገፉ!
ይሞቷታል እንጂ ቂም እንደቋጠሩ፣
በንዴት፣ በጸጸት፣ ቁ…ጭት እያረሩ፡
መቼ ሰላም ሊያድሩ፧
ለመወቃቀስም ቆሞ ባደባባይ፣
ለመግለጥ ደመና በይቅርታ ፀሃይ።
የለ አቃቤ ሰዓት፣
ለምልጃ ደጅ ጥናት።
መቼ ጊዜ ተርፎ መቼ ጊዜ አለና፧
ድሮ እንጂ ዘንድሮ ቀርቷል ሽምግልና።
ተጣልቶ መታረቅ ላማላጅ ቀጠሮ፣
ለይቅርታ ካሣ ጊዜ የለም ዘንድሮ፡
ጊዜ ቀረ ድሮ።


@kederasiyan

ሀበሻ 🇪🇹

11 Nov, 16:30


"አውሮራ"
"ታላቁ ተቃርኖ"
"የቄሳር እንባ"
"አስኳላ"
"ሕንፍሽፍሽ"
"የሱፍ አበባ"
"አንፋሮ"

የተሰኙትን መጻሕፍት የደረሰው ሀብታሙ አለባቸው።

ሀበሻ 🇪🇹

11 Nov, 09:18


ለትምህርት ለንግድ ለግል ንባብ ልምዳችሁ ይጠቅማቹሃልና የምትፈልጉት በዚህ ሊንክ    @abumame በኩል ስለዋጋው አውሩን ::