ቢሾፍቱ፣ የካቲት 26/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሰላም ግንባታ ዙሪያ ከንግድ መገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)፤ የንግድ መገናኛ ብዙኃን ለማህበረሰቡ የመረጃ ምንጭ ከመሆናቸው ባለፈ በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ በመግለፅ፤ ትልቁ ስኬት ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላ ለማብረድ ከመሞከር ይልቅ ከመፈጠራቸው በፊት የመከላከል ስራ መስራት አዋጭ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የንግድ መገናኛ ብዙኃን ትውልድን በመቅረጽ ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በኃላፊነትና በአንድነት መንፈስ በሰላም ግንባታ ላይ በትኩረት መስራትና ሚናቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የንግድ መገናኛ ብዙኃን በሰላም ግንባታ ዙሪያ ያላቸው ሚና በተመለከተ እንዲሁም ህብረ ብሔራዊ አንድነት እና አሰባሳቢ ትርክት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
#ብቁ_መገናኛ_ብዙኃን_ለማህበረሰባዊ_ንቃት
#የጥላቻ_ንግግርና_ሐሰተኛ_መረጃን_በጋራ_እንከላከል