Latest Posts from Ethiopia Insider (@ethiopiainsidernews) on Telegram

Ethiopia Insider Telegram Posts  

Ethiopia Insider
Ethiopia Insider is a digital media that provides news, updates, analysis and features.
15,399 Subscribers
651 Photos
40 Videos
Last Updated 06.03.2025 19:14

Similar Channels

Event Addis Media
9,348 Subscribers
Ethio-Chamber
8,616 Subscribers

The latest content shared by Ethiopia Insider on Telegram

Ethiopia Insider

24 Feb, 00:04

8,104

በሬክተር ስኬል 5.3 የተለካ የመሬት መንቀጥቀጥ እሁድ ለሊት ተከሰተ

በኢትዮጵያ በሬክተር ስኬል 5.3 የተለካ የመሬት መንቀጥቀጥ ዛሬ እሁድ ለሊት 8 ሰዓት ከ44 ደቂቃ ላይ መከሰቱን የአውሮፓ ሜዲትራንያን ሴይስሞሎጂ ማዕከል (EMSC) አስታወቀ። ዘለግ ላሉ ሰከንዶች የቆየው የዛሬው የመሬት መንቀጥቀጥ ያስከተለው ንዝረት መዲናዋ አዲስ አበባ ድረስ ተሰምቷል።

የለሊቱ የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተው፤ ከጭሮ ከተማ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ እንደሆነ የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት ገልጿል። የመሬት መንቀጥቀጡ እንደ ጭሮ ከተማ ሁሉ በአዋሽም “ቀላል” የሆነ ንዝረት ማስከተሉን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጦችን የሚመዘግበው “ቮልካኖ ዲስከቨሪ” አመልክቷል።

ንዝረቱ “ደካማ” በሆነ መጠን ድሬዳዋ፣ ሂርና፣ በዴሳ፣ ገለምሶ፣ ደደር፣ አቦምሳ፣ ገዋኔ፣ መተሐራ፣ አዳማ፣ ወንጂ፣ ሞጆ እና ቢሾፍቱ ከተሞችን ማዳረሱን ይኸው ተቋም ጠቁሟል። ተመሳሳይ መጠን ያለው ንዝረት በደብረሲና፣ ደብረ ብርሃን፣ ከሚሴ፣ ባቲ፣ ኮምቦልቻ እና ደሴ ድረስ መሰማቱንም የ“ቮልካኖ ዲስከቨሪ” መረጃ ያሳያል።

ዛሬ እሁድ የካቲት 16 ለሊት የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ ካለፈው ዘጠኝ ቀን ወዲህ የተመዘገበ ከፍ ያለ መጠን ያለው ርዕደ መሬት ነው። ከመተሐራ ከተማ ስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ፤ የካቲት 7 እኩለ ለሊት ገደማ የተከሰተው እና በሬክተር ስኬል 6.0 የተለካው የመሬት መንቀጥቀጥ ባለፉት ወራት ሁሉ ከደረሱት ሁሉ በመጠን ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

@EthiopiaInsiderNews
Ethiopia Insider

20 Feb, 16:07

9,306

ቪዲዮ፦ የስራ ዘመኑ ለተጨማሪ አንድ ዓመት በፓርላማ የተራዘመለት የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፤ ወቅታዊ የስራ እንቅስቃሴዎቹን በተመለከተ በዛሬው ዕለት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል። በጋዜጣዊ መግለጫው ለተገኙ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል፤ “በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች መሳሪያ አንግበው ከሚፋለሙ ታጣቂዎች ጋር ንግግር ለማድረግ ሞክራችኋል?” የሚለው ይገኝበታል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ የኮሚሽኑ ዋና አላማ “ሁሉም በምክክር ሂደቱ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ነው” ብለዋል። ዋና ኮሚሽነሩ በዚሁ ምላሻቸው ከአንድ የታጣቂ ቡድን አመራር ጋር መነጋገራቸውን፤ ሆኖም ግን “ፋኖ መሆናቸውን እንደማያውቁ” ተናግረዋል።

“አንድ ታጣቂ ቡድን ራሳቸው ደውለውልኝ፤ አነጋግረውኝ ‘የምክክር ኮሚሽኑን ስራ ተገንዝበናል። ገለልተኛ መሆኑን ተገንዝበናል። በዚህ መሰረት ቀጥታ አጀንዳችንን ለእናንተ አቅርበን፤ ወደ ዱር የገባንበትን አጀንዳ ለእናንተ አምጥተን፤ ወደ ውይይት የሚቀርብ ከሆነ መሳሪያችንን ለማስቀመጥ ዝግጁ ነን’ የሚል ጥያቄ በቀጥታ ለእኔ ቀርቦልኛል” ሲሉ ፕሮፌሰር መስፍን ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ በአማራ ክልል ከሚያደርገው የምክክር ሂደት ጋር በተያያዘም፤ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጥያቄ ቀርቧል። የምክክር ኮሚሽኑ በአማራ ክልል በሚያደርገው እንቅስቃሴ “በህዝቡ ዘንድ ያለው አመኔታ እና ተቀባይነትን ምን ያህል ነው?” ለሚለው ጥያቄ፤ ከአስራ አንዱ የተቋሙ ኮሚሽነሮች አንዱ የሆኑት አቶ መላኩ ወልደማርያም ምላሽ ሰጥተዋል።

🔴 በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች የተሰጠውን ሙሉ ምላሽ ይህን ሊንክ ተጭነው ይመልከቱ ▶️ https://youtu.be/C5Q9ITR45qk

@EthiopiaInsiderNews
Ethiopia Insider

20 Feb, 11:05

8,443

በአርሲ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተከሰተ የእሳት አደጋ፤ ከሁለት ሳምንት በኋላም “መቆጣጠር አልተቻለም” ተባለ

በአርሲ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከሁለት ሳምንት በፊት የተቀሰቀሰ የእሳት አደጋ፤ እስከዛሬ ሐሙስ የካቲት 13፤ 2017 ድረስ በቁጥጥር ስር አለመዋሉን የአርሲ ዞን እና የፓርኩ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ።

ለእሳት ቃጠሎው መከሰት መንስኤ ናቸው በሚል የተጠረጠሩ 30 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም የአርሲ ዞን አስታውቋል። 

በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ስድስት ብሔራዊ ፓርኮች ውስጥ አንዱ የሆነው የአርሲ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙት የምኒልክ ድኩላ፣ የደጋ አጋዘን፣ ቀይ ቀበሮ እንዲሁም የሌሎች እንስሳት መኖሪያ ነው።

በ2003 ዓ.ም በብሔራዊ ደረጃ የተመዘገበው ፓርኩ፤ 84,100 ሄክታር የሚሸፍን ቦታን የሚያካልል ነው።

በፓርኩ ይዞታ ውስጥ በሚገኝ ጢቾ በተባለ ወረዳ ከሳምንት በፊት የተከሰተው የእሳት አደጋ፤ በአሁኑ ወቅት በ11 ወረዳዎች ላይ መስፋፋቱን የአርሲ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሀመድ ቲፎ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

በሰደድ እሳቱ “በከፍተኛ ሁኔታ” ጉዳት የደረሰበት ጭላሎ ጋለማ የተሰኘው የፓርኩ “ብሎክ” እንደሆነም ኃላፊው አስረድተዋል። 

የአርሲ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጭላሎ ጋለማ፣ ካካ፣ ሆንቆሎ እና ዴራ ዲልፈከር በተባሉ አራት “ብሎኮች” የተከፋፈለ ነው። ከእነዚህ ውስጥ ሰፊውን ቦታ የሚይዘው ጭላሎ ጋለማ 70,486 ሄክታር ስፋት አለው።

🔴 ለዝርዝሩ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15166/

@EthiopiaInsiderNews
Ethiopia Insider

19 Feb, 17:20

7,472

ለአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት የሚውለው ገንዘብ ምንጭ፤ የከተማይቱ “ግብር ከፋዮች” መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በአንድ ጊዜ በርካታ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር የሚያወጣው ገንዘብ ምንጭ፤ በከተማይቱ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ አነገጋረ። የከተማይቱ ከንቲባ አዳነች አቤቤ “የበጀታችን ምንጩ ግብር ነው። የከተማይቱ ግብር ከፋዮች ናቸው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የከተማይቱ ምክር ቤት አባላት ካለፈው ዓመት ጀምሮ በአዲስ አበባ እየተተገበረ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት የተመለከቱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶችን የሰነዘሩት፤ ዛሬ ረቡዕ የካቲት 12፤ 2017 በተካሄደ የምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ ላይ ነው።

አቶ ጋትዌች ዎርዲየው የተባሉ የከተማይቱ ምክር ቤት አባል “የኮሪደር ልማት በጀት ምንጩ ከየት ነው?” ሲሉ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል። ይህ የእርሳቸው ጥያቄ፤ በሌላኛው የምክር ቤት አባል አቶ ፍቃዱ ታምራት በተሰጠ አስተያየት ላይም ተንጸባርቋል።

የኮሪደር ልማት ስራው “ከስፋቱ አንጻር ሲታይ፣ ምን ያህል በጀት የወሰደ እንደሆነ ሲታይ፣ ምን ያህል ለውጥ ከተማዋ ላይ እያመጣ እንደሆነ ሲታይ፣ ብቻውን በቂ ነበር” ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ ይህንኑ አስመልክቶ ብዙ ሰዎች “በግርምት” የሚጠይቁት ጥያቄ “የከተማ አስተዳደሩ ይሄን ያህል ገንዘብ ከየት ሊያመጣ ቻለ?” የሚል እንደሆነ አመልክተዋል። 

ዶ/ር ወርቅነሽ ምትኩ የተባሉ የምክር ቤት አባል፤ “አንድ ከተማ በነበረው ሁኔታ፣ ከነበረው ገቢ፣ ይሄን ሁሉ ስኬት ማሳለጥ የሚችል ከሆነ፤ የት ነበርን? ይህ ገንዘብ ገንዘቡ ፈልቆ ነበር?” ሲሉ በገረሜታ ጠይቀዋል።

🔴 ለዝርዝሩ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15161/

@EthiopiaInsiderNews
Ethiopia Insider

19 Feb, 10:05

7,420

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ100 በላይ ሰራተኞቹ በአንድ ጊዜ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ተቀጥረው ደመወዝ ይከፈላቸው እንደነበር ደርሼባቸዋለሁ አለ   
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ100 በላይ የሚሆኑ ሰራተኞች “በሁለት እና በሶስት መስሪያ ቤቶች ተቀጥረው” ደመወዝ ሲከፈላቸው እንደነበር የከተማይቱ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ። የከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ሰራተኞች “ተጠያቂ ማድረጉንም” ከንቲባዋ ገልጸዋል።

አዳነች ይህንን የገለጹት፤ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ዛሬ ረቡዕ የካቲት 12፤ 2017 እያካሄደ ባለው መደበኛ ጉባኤ ላይ ባቀረቡት የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ነው።

ከንቲባዋ በዚሁ ሪፖርታቸው፤ የከተማ አስተዳደሩ የተቀናጀ የሲቪል ሰርቪስ መረጃ አያያዝ ስርዓት ተግባራዊ በማድረጉ፤ በስሩ ምን ያህል ሰራተኞች እንዳሉት ለማወቅ እንደቻለ ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ 168 ሺህ ያህል ሰራተኞቹን ፋይል “ስካን አድርጎ” ወደ ስርዓቱ እንዲገባ ካደረገ በኋላ በተደረገው ማጣራት፤ ከ100 በላይ የሚሆኑ ሰራተኞች “ያለአግባብ በሁለት እና በሶስት መስሪያ ቤቶች ተቀጥረው” ደመወዝ እንደሚከፈላቸው እንደተደረሰበት አብራርተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ሰራተኞች “ተጠያቂ” ማድረጉን አዳነች በሪፖርታቸው ቢጠቅሱም፤ የተወሰደባቸው እርምጃ ምን እንደሆነ ግን በዝርዝር ሳይገልጹ ቀርተዋል።

🔴 ሙሉ ዘገባውን ለማንበብ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15155/

@EthiopiaInsiderNews
Ethiopia Insider

18 Feb, 20:01

7,251

የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ “ቴክኒካዊ ድርድር” በመጪው መጋቢት ወር ይቀጥላል ተባለ

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ከፍተኛ ባለስልጣናት የተሳተፉበት የመጀመሪያው ዙር ቴክኒካዊ ድርድር ተጠናቀቀ። በቱርክ አንካራ ከተማ በተካሄደው ድርድር፤ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ እና የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አሊ ሞሐመድ ዑመር ተገኝተዋል።

በቱርክ በኩል በድርድሩ የተገኙት፤ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች በታህሳስ ወር መጀመሪያ ፊት ለፊት ከመገናኘታቸው በፊት በአዲስ አበባ እና በሞቃዲሾ ተመላልሰው ውይይቱን ያመቻቹት የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሐካን ፊዳን ናቸው።

በዛሬው ድርድር ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ የሁለቱን ሀገራት ልዑካን ቡድን በተናጠል እና በጋራ ማነጋገራቸውን መስሪያ ቤታቸው አስታውቋል።

ሐካን ፊደን በተናጠል እና በጋራ በተደረጉት ውይይቶች፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ልዩነት በበረታበት ዓለም ውስጥ ቀጠናዊ ትብብር ወሳኝ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በአጽንኦት መናገራቸውን የቱርክ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አመልክቷል።

ፊዳን በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተጀመረው ድርድር “የአፍሪካን ቀንድ መጻኢ ጊዜ ታሪካዊ ዕድል ይወክላል” በማለት ፋይዳውን ገልጸዋል።

🔴 ለዝርዝሩ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15146/

@EthiopiaInsiderNews
Ethiopia Insider

18 Feb, 15:50

6,862

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን “ደካማ የሆነ አፈጻጸም አሳይቷል ብለን እናስባለን” - ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ

ቪዲዮ፦ በዛሬው ዕለት በተካሄደው የፓርላማ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የስራ ሪፖርት ያቀረቡት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ ኮሚሽኑ በአዋጅ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ የምክክር፣ የአጀንዳ መለየት እና ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ስራዎችን ማከናወኑን ተናግረዋል። እነዚህ ሂደቶች በ10 ክልሎች እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቃቸውንም ገልጸዋል።

እርሳቸው ይህን ቢሉም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ ተወካይ የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ግን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ “ደካማ የሆነ አፈጻጸም አሳይቷል ብለን እናስባለን” ሲሉ ተደምጠዋል። እንደ ዶ/ር ደሳለኝ ሁሉ፤ ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ ተወካዮችም በኮሚሽኑ የስራ አፈጻጸም ያላቸውን አስተያየት እና ጥያቄ ሰንዝረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

🔴 ሶስቱ የፓርላማ አባላት በዛሬው ስብሰባ ላይ የተናገሩትን ለመመልከት ይህን ሊንክ ይጫኑ ➡️ https://youtu.be/xkJymS2kYOY

@EthiopiaInsiderNews
Ethiopia Insider

18 Feb, 11:13

7,199

የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ በፌደራል ፍርድ ቤት ከቀረቡባቸው ክሶች በነጻ እንዲሰናበቱ ተፈረደላቸው

🔴 አቶ ጸጋዬ ቱኬ በሌላ ፍርድ ቤት ክሶች ያለባቸው በመሆኑ በእስር ላይ ይቆያሉ ተብሏል

ቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጸጋዬ ቱኬ ከቀረቡባቸው ሁለት ክሶች በነጻ እንዲሰናበቱ በዛሬው ዕለት የፍርድ ውሳኔ እንደተሰጣቸው ከተከላካይ ጠበቆች አንዱ የሆኑት አቶ ገብረመድህን ተክላይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ።

ከቀድሞው ከንቲባ ጋር በአንድ መዝገብ የተከሰሱት የሲዳማ ክልል የቀድሞ ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ አበራ አሬራ እና የአቶ ጸጋዬ የእህት ልጅ የሆኑት አቶ አብርሃም አመሎም በተመሳሳይ በነጻ መሰናበታቸውን ጠበቃው ገልጸዋል።

በሶስቱ ተከሳሾች ላይ የፍርድ ውሳኔውን የሰጠው፤ ጉዳዩን ሲመረምር የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሀዋሳ ማዕከል ነው። ፍርድ ቤቱ ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 11፤ 2017 በዋለው ችሎት፤ “ሶስቱም ተከሳሾች የቀረበባቸውን ሁለቱንም የወንጀል ክሶች ያልፈጸሙና በሚገባ የተከላከሉ መሆናቸው በነጻ ተሰናብተዋል” ሲል ውሳኔ ማስተላለፉን ጠበቃ ገብረመድህን ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል ፍትህ ቢሮ በአቶ ጸጋዬ እና በሁለቱ ተከሳሾች ላይ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ክስ የመሰረተው፤ “የማይገባ ጥቅም በመቀበል የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል” እንዲሁም “በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስለው አቅርበዋል” በሚል ነበር።

ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሀዋሳ ማዕከል፤ ሶስቱም ተከሳሾች የቀረቡባቸውን ክሶች እንዲከላከሉ ባለፈው ጥቅምት ወር አጋማሽ ገደማ ብይን ሰጥቷል።

🔴 ለዝርዝሩ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15139/

@EthiopiaInsiderNews
Ethiopia Insider

18 Feb, 10:20

5,873

የተወካዮች ምክር ቤት የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽንን የስራ ዘመን ለአንድ ዓመት አራዘመ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 11፤ 2017 ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የስራ ዘመን ለአንድ አመት አራዘመ።

የኮሚሽኑን የስራ ዘመን ለማራዘም የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ፤ በሶስት የፓርላማ አባላት ተቃውሞ በአብላጫ ጽምጽ ጸድቋል። 

መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች “ወሳኝ ምክንያቶችን የመለየት” እና ውይይቶች የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በመለየት “ምክክር እንዲደረግባቸው የማመቻቸት” ዓላማ ይዞ የተቋቋመው ኮሚሽኑ፤ በአዋጅ የተቀመጠለት የስራ ዘመን ሶስት ዓመት ነው።

የተወካዮች ምክር ቤት በእረፍት ላይ ያሉትን የፓርላማ አባላት አስቸኳይ ስብሰባ የጠራው፤ የኮሚሽኑ የስራ ዘመን ከማለቁ ሁለት ቀን አስቀድሞ ነው።

ፓርላማው ኮሚሽኑ ለተጨማሪ አንድ ዓመት በስራ ላይ እንዲቆይ ውሳኔ ከማሳለፉ አስቀድሞ፤ የተቋሙን የሶስት ዓመታት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል።

ሪፖርቱን ለፓርላማ አባላት በንባብ ያቀረቡት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ ኮሚሽኑ በዚህ ጊዜ ውስጥ የምክክር፣ የአጀንዳ መለየት እና ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ስራዎችን በ10 ክልሎች እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ማጠናቀቁን አስታውቀዋል። 

🔴 ለዝርዝሩ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15130/

@EthiopiaInsiderNews
Ethiopia Insider

17 Feb, 14:44

6,117

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ “ቴክኒካዊ ድርድር” ዛሬ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ አመቻችነት የሚያካሄዱት “ቴክኒካዊ ድርድር” ዛሬ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።
በሶማሊያ
የማስታወቂያ፣ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ዳውድ አዌይስ የተመራ የልዑካን ቡድን ዛሬ ሰኞ ወደ አንካራ አቅንቷል። 

ሚኒስትሩ በኤክስ ይፋዊ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ የሁለቱን ሀገራት የመጀመሪያ ዙር ቴክኒካዊ ውይይት ለማስጀመር በአንካራ የሶማሊያ ልዑካንን መቀላቀላቸውን አስታውቀዋል።

ዳውድ አዌይስ በዚሁ መልዕክታቸው፤ ውይይቱ “የአንካራ ቃል ኪዳንን ተግባራዊ ለማድረግ መንገዶች ለማፈላለግ” ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ “ልዩነቶቻቸውን እና አወዛጋቢ ጉዳዮችን ወደ ኋላ ለመተው” እና “ትብብር ለማበጀት” በአንካራ ስምምነት የተፈራረሙት ባለፈው ታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር።

ሁለቱ ሀገራት በቱርክ አመቻችነት በተፈራረሙትን በዚሁ ስምምነታቸው፤ “አንዳቸው ለሌላው ሉዓላዊነት፣ አንድነት፣ ነጻነት እና የግዛት አንድነት ያላቸውን ክብር እና ቁርጠኝነት” መግለጻቸው ይታወሳል።   

🔴 ሙሉ ዘገባውን ለማንበብ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15123/

@EthiopiaInsiderNews